ሐዊረ ሕይወት ፤የሕይወት ጉዞ መጋቢት 2/2004 ዓ.ም
ተጨማሪ ፎቶዎችን ለመጎብኘት www.facebook.com/mahiberekidusan ሐዊረ ሕይወት ፤የሕይወት ጉዞ መጋቢት 2/2004 ዓ.ም የሚለውን የፎቶ ማህደር ይመለከቱ
ተጨማሪ ፎቶዎችን ለመጎብኘት www.facebook.com/mahiberekidusan ሐዊረ ሕይወት ፤የሕይወት ጉዞ መጋቢት 2/2004 ዓ.ም የሚለውን የፎቶ ማህደር ይመለከቱ
መጋቢት 1/2004 ዓ.ም.
የአሰቦት ቅድስት ሥላሴና የአባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም ደን በእሳት የተቃጠለ ሲሆን ለማጥፋት በማኅበረ መነኮሳቱና ምዕመናን እንዲሁም በፌደራል ፖሊስና በኦሮሚያ ፖሊስ ከፍተኛ ጥረት ከአምስት ቀናት በኋላ ሊጠፋ ችሏል፡፡
የአሰቦት ገዳም በ13ኛው መቶ ክ/ዘመን በአባ ሳሙኤል ዘወገግ የተመሠረተ ሲሆን በ15ኛው መቶ ክ/ዘመን አህመድ ግራኝ አጠፋው፡፡ የገዳሙ መነኮሳትም ከሞት የተረፉት ተበታተኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ለረጅም ዘመናት አገልግሎት መስጠት ያልቻለ ቢሆንም አንዳንድ መናንያን ወደቦታው በመሔድ በጸሎት ተወስነው ይኖሩ እንደነበር ይነገራል፡፡ በ1911 ዓ.ም. ንግስት ዘውዲቱ እንደገና ገዳሙ እንዲመሰረት አደረጉ፡፡
በ1928 ዓ.ም. የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በመውረሩ ገዳሙን ለማጥፋት ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ አፄ ኃ/ሥላሴ በ1936 ዓ.ም. በተጠናከረ ሁኔታ ገድመው፣ መተዳደሪያ፣ ርስት ጉልት ሰጥተውና ለመነኮሳት መኖሪያ አሰርተው በሥርዓት እንዲጠበቅ አደረጉ፡፡ ሣራ ማርያም አካባቢ / ከአሰቦት ገዳም በስተምዕራብ/ እስከ 300 ወታደሮች ተመድበው ገዳሙንና ደኑን ሲጠብቁ እንደነበር አበመኔቱ የታሪክ ማኅደርን ጠቅሰው ይገልጻሉ፡፡ በ1969 ዓ.ም. የሶማሊያ ጦር ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረገውን ጥረት ተከትሎ ወታደሮቹ በመወሰዳቸው ገዳሙ አደጋ ስላንዣበበበት ከገዳሙ የተውጣጡ አራት መነኮሳት ብቻ በየቀኑ መጠበቅ ጀመሩ፡፡ አሁንም በዚህ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡
ለመሆኑ የእሳት ቃጠሎው መነሻው ምንድነው? እንዴትስ አለፈ?
የካቲት 20 ቀን
እንደ ገዳሙ አባቶች ገለጻ አራት የሚሆኑ ሰዎች የአሰቦት ቅድስት ሥላሴና የአባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ሲሆን ማንነታቸው ያልታወቀ ዘራፊዎች ጥቅጥቅ ያለውን ጫካ ሰንጥቀው በመገሥገስ ላይ ናቸው፡፡ ከሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ጀርባ የገዳሙ 62 ከብቶችና 25 አህዮች ለግጦሽ ተሰማርተዋል፡፡ ወደ ገዳሙ እየቀረቡ የመጡት ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ከብቶቹን ፍለጋ ጥቅጥቅ ያለው ደን ውስጥ ተሸጎጡ፡፡ ከዚያም ደኑ ሳይበግራቸው ከብቶቹን አግኝተው መንዳት ጀመሩ፡፡ የገዳሙ መነኮሳት እንዳይደርሱባቸውም በተጠንቀቅ ግራ ቀኝ እየተገላመጡ የሚመጣውን ኀይል ለመመከት በመዘጋጀት በጥድፊያ ከብቶቹን ነዷቸው፡፡
የገዳሙ ጥበቃ አባላት የእለቱ ተረኞች ሁለት ብቻ ሲሆኑ ከብቶቹ መነዳታቸውን በመረዳታቸው እየጮሁ ተከተሏቸው፡፡ ማኅበረ መነኮሳቱም ተሰባስበው ከብቶቹን ለማስጣል ተረባረቡ፡፡ ከብቶቹን ለመውሰድ የቋመጡት ዘራፊዎች እንዳልተሳካላቸው ሲረዱ ከብቶቹን ጥለው ፈረጠጡ፡፡ መነኮሳቱ ከብቶቻቸውን ይዘው ወደ ገዳማቸው በመመለስ አገር ሰላም ነው ብለው ጸሎት ላይ ተጠምደዋል፡፡
ድንገት ከአሰቦት ሥላሴ ገዳም በስተጀርባ ከሚገኘው ደን የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የእሳት ጭላንጭል መታየት ጀመረ፡፡ ከብቶቹን ለመዝረፍ ያደረጉት ጥረት ያልተሳካላቸው ደኑን በእሳት አያይዘው ጠፍተዋል፡፡ የደኑን መያያዝ ያስተዋሉት ማኅበረ መነኮሳት እሳቱን ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀረ፡፡ እሳቱ ደኑን እየበላ ወደፊት ለፊት ወዳለው የተራራው ክፍል መቅረቡን ቀጠለ፡፡ ሌሊቱን ሙሉ መነኮሳቱና መነኮሳይያት ለማጥፋት ሳይቻላቸው ንጋቱ ተተካ፡፡ የደረሰላቸው ግን አልነበረም፡፡
የካቲት 21 ቀን
የገዳሙ ዋና መጋቢና ምክትል አበመኔት በሆኑት አባ ዘወልደ ማርያም አስተባባሪነት ለሚመለከታቸው ለሐገረ ስብከቱና ለወረዳው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ፤ እንዲሁም ለማኅበረ ቅዱሳን የሜኤሶ ወረዳ ማዕከል አባላት ህዝበ ክርስቲያኑን እንዲቀሰቅሱ በመደወል አሳወቁ፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን የሜኤሶ ወረዳ ማእከል አባላት ከወረዳው ቤተ ክህነት ሓላፊዎች ጋር በመሆን ለሚመለከታቸው አካላት ለሐገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ፤ ለአሰበ ተፈሪ፣ ለድሬዳዋ፣ ለሐረር፣ ለአለማያ፤ ለበዴሳ፤ ለናዝሬትና ሌሎችም የማኅበረ ቅዱሳን ማእከላት በማሳወቅ ምእመናንን አስተባብረው እንዲመጡ ለማድረግ ጥረት ተደረገ፡፡ በሜኤሶ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያንና አጎራባች አብያተ ክርስቲያናት የአደጋ ጊዜ ጥሪ ደወል በማሰማት ለምእመናን ስለ ጉዳዩ ተገለጸ፡፡ ለፌዴራል ፖሊስ፤ ለኦሮሚያ ፓሊስ፣ ለሐገረስብከት ጽ/ቤት፣ ለወረዳ አስተዳደሮች ሁሉ ለማሳወቅ ጥረቶች ተደረጉ፡፡
የገዳሙ አበምኔት ከአሰቦት ከተማ እስከ ገዳሙ ያለውን የ18 ኪሎ ሜትር የመኪና መንገድ ለመሥራት የተቋቋመው የመንገድ ሥራ ኮሚቴ ለውይይት ባቀረበላቸው ጥሪ መሠረት አዲስ አበባ ነው የሚገኙት፡፡ የገዳሙ ደን በእሳት መያያዝ የሰሙት በ21/6/2004 ዓ.ም. ጠዋት ነው፡፡፡ ገዳሙ በዋና መጋቢና ም/አበምኔቱ አባ ዘወልደ ማርያም በመመራት ላይ ነው፡፡
ምእመናን ጀሪካን ከየቤታቸው በማሰባሰብ ውኃ ሞልተው ወንዶች በጭንቅላታቸው፤ ሴቶች በወገባቸው አዝለው የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ተቀብለው በእንባ እየተራጩ ከአሰቦት ከተማ እስከ ገዳሙ ያለውን የ18 ኪሎ ሜትር መንገድ መጓጓዣ ስለሌለ በእግር ጉዞ ተያያዙት፡፡
የሜኤሶ ከተማ ግብርና ጽ/ቤት የመኪና እርዳታ እንዲያደርጉ በመጠየቃቸው አንድ ፒክ አፕ መኪና በመስጠት ውኃዎቹ በጀሪካን እየተሞሉ ተጫኑ፡፡ 30 የሚደርሱ የመጀመሪያዎቹ ግብረ ኃይሎች በመኪናው ተሳፍረው ቦታው ደርሰው በጀሪካን ውኃ እያፈሰሱ በቅጠል ለማጥፋት ጥረት አደረጉ፡፡ ከእሳቱ ፍጥነትና ከእሳት አጥፊው ማነስ ጋር ተዳምሮ የማይመጣጠን ሆነ፡፡ አካባቢዉ የሃዘን ቀጠና ሆነ፡፡ አቅመ ደካሞች መነኮሳትና መነኮሳይያት የአገር ሽማግሌዎች አንገታቸውን ቀና አድርገው ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ በእንባ የታገዘ ጸሎት ከማድረስ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ እሳቱ እየገሰገሰ ነው፡፡
የሀገረ ስብከትና የየወረዳዎቹ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች፤ የኦሮሚያ ፓሊስ ኃይል፤ የፌደራል ፖሊስ ልዩ ኃይል፤ በተለይም ወጣቶች፤ የየቤተ ክርስቲያኑ ሰ/ት/ቤቶች አባላት፤ ማኅበራትና ምእመናን እየገሰገሱ ነው፡፡ ገዳሙ ከተገደመ ጀምሮ ለ800 ዓመታት በግርማ ሞገሳቸው የሚታወቁት የዝግባ፣ የጥድ፣ የዋርካ፣ የወይራ ሰማይ ጠቀስ ዛፎች የእሳቱን ቃጠሎ መቋቋም ተስኗቸው በመገንደስ ላይ ናቸው፡፡
ሕዝበ ክርስቲያኑ እየወደቀ እየተነሣ ማጥፋቱን ተያይዞታል፡፡ እሳቱ በነፋሱ ታግዞ ይምዘገዘጋል፡፡ የዱር እንስሳትና አዕዋፍ የሚደርሱበት ጠፍቷቸው ይተራመሳሉ፡፡ ምእመናን ለማጥፋት ይሯሯጣሉ፡፡ የእሳቱ ነበልባል ከ10 ሜትር በላይ ከፍ ብሏል፡፡ እንደ ዘንዶ እየተጥመለመለ እየተወረወረ የሚወጣውን ፍለጋ ይወነጨፋል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚተመውን እሳት እያዩ “አንቺ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከምትቃጠይ እግዚአብሔር እኛን ያስቀድመን፡፡ ጥፋትሽን አያሳየን” የሚሉ ምእመናን ያለ የሌለ ጉልበታቸውን በመጠቀም ጦርነት ከእሳቱ ጋር ገጥመዋል፡፡ እሳቱ ፍጥነቱን ጨመረ፡፡ ብርሃንም ለጨለማ እጇን ሰጠች፡፡ ክርሰቲያን ተስፋ አይቆርጥም አይደል? እሳቱ ቢያንስ ቤተ ክርስቲያኑንና የልማት ተቋማቱን እንዳይበላ ለመከላከል እየተፍጨረጨሩ ነው፡፡
አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሦስት ጊዜ በላይ የእሳት አደጋ ተከስቷል፡፡ በራሳቸው ጥረት እሳቱን በቁጥጥር ስር አውለውት ነበር፡፡ የዛሬው ግን የሚቻል አልሆነም፡፡
ምእመናን በጨለማው እየተሯሯጡ ጀሪካኖቻቸውን ተሸክመውና አዝለው የቻለ ለመነኮሳቱና ለምእመናን የሚሆን ስንቅ እየያዘ 18 ኪሎ ሜትሩን እየወደቁ እየተነሱ፣ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እያነቡ ይከንፋሉ፡፡
እግዚአብሔር በአውሎና በወጀብ መካከል መንገድ አለው
እሳቱን በማጥፋት ሂደት ውስጥ እያሉ የካቲት 21 በግምት ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት አካባቢ አንድ አሳዛኝ ክስተት ተፈጠረ፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን የሜኤሶ ወረዳ ማእከል ሰብሳቢ ዲያቆን ዘውገ በቀለ እንደገለጹት እሳቱ 10 ሜትር ያህል ተምዘግዝጎ እየነጎደ በንፋሱ ታግዞ በቡድን በማጥፋት የነበሩ ወንድሞችና እኅቶችን ለሁለት ከፈላቸው፡፡ በመካከላቸው ታላቅ የእሳት ባሕር ተከሰተ፡፡ ነበልባሉ ገረፋቸው ራሳቸውን ለመከላከል ትግል ገጠሙ፡፡ ወደላይ የተከፈለው ቡድን እንደምንም አመለጠ፡፡ የታችኛው ቡድን 18 ወጣቶች ግን ዙሪያቸውን በእሳት ተከበቡ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የሜኤሶ ወረዳ ማኅበረ ቅዱሳን አባላትና የሰ/ት/ቤት አባላት ነበሩ፡፡ ከእነሱም ውስጥ ደግሞ ሁለቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ከላይ ያሉ ምእመናን ከለቅሶና ዋይታ ውጪ ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡ እሳቱ ጥርሱን አግጦ አፉን ከፍቶ እነሱንም ሊበላ በመጣደፍ ላይ ነው፡፡ “አይቴ ሀሎከ አምላከ አበዊነ?” የአባቶቻችን አምላክ ወዴት ነህ? ከዚህ መዓት አውጣን?! በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮሁ፣ ያድናቸው ዘንድ መማጸን ወይም በእሳቱ መበላት፡፡ እንደ ንሥር ክንፍ ኖሯቸው በረው አይወጡ ነገር እሳቱ አያስጠጋም፡፡ ተሰባስበው አንድ ነገር አደረጉ፡፡ የኅብረት ጸሎት ማድረግ፡፡ እንባና ለቅሶ ተደባለቀ፡፡ውዳሴ ማርያም ተጀመረ፡፡ በጸሎት ይተጋሉ፡፡ እሳቱ እየተምዘገዘገ ሊውጣቸው በመቅረብ ላይ ነው፡፡ ከላይ ዋይታና ለቅሶ ይሰማቸዋል፡፡ እነሱ ደግሞ ውዳሴ ማርያም በመድገም ላይ ተጠምደዋል፡፡ በዚህ ቅጽበት አሁንም አንድ እፎይታን የሚፈጥር ክስተት ተፈጠረ፡፡ ዞር ብለው ሲመለከቱ አጠገባቸው አነስተኛ ዋሻ አገኙ፡፡ ሁሉም ዘለው ዋሻው ውስጥ ገቡ፡፡ እሳቱ በአምስት ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ዋሻው እላዩ ላይ የእሳት ዝናብ እየወረደበት ነው፡፡ እሳቱን አመለጥን ሲሉ በጪሱ ደግሞ ታፈኑ፡፡
ውዳሴ ማርያም ጸሎቱ ቀጥሏል፡፡ እኩለ ሌሊት እየተቃረበ ቢሆንም እሳቱ እያየለ ወንድሞችና እኅቶችም በእሳቱ እንደተከበቡ ነው፡፡ ከላይ ነበልባል ከስር ፍምና ጪስ ብቻ፡፡ ከላይ ካሉትና እሳቱን በማጥፋት ላይ ከሚገኙት መካከል በትርፍ ጊዜያቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙ ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት ከዚህ በላይ መታገስ አልቻሉም፡፡ በፌስታል የታሰረ ዳቦ ይዘው ብንሞትም ስለ ሃይማኖታችን እንሙት፡፡ እነዚህ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ሲሞቱ ዝም ብለን አንመለከትም” በማለት አንድ ወንድም አስከትለው ከሞቱ አጽማቸውን እንሰበስባለን፡፡ ካልሞቱም በሕይወት አብረን እንድናለን፡፡ ከሞትንም አብረን እንሞታለን፡፡ በማለት አፉን ከፍቶ ወደሚጠብቃቻው እሳት ውስጥ ተወርውረው ገቡ፡፡
የእግዚአብሔር ተአምር ሆነና እየተንሸራተቱ እሳቱ ላይ እየተረማመዱ እየተለበለቡ ከወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው ጋር ዋሻው ውስጥ ተቀላቀሉ፡፡ አልሞቱም ተቃቅፈው በእንባ ተራጩ፡፡ በድካምና በረሃብ የደከመ ሰውነታቸውን ያጠነክሩ ዘንድ የያዙትን ዳቦ ሰጧቸው፡፡ መዝሙር ይዘመራል፣ እሳቱ ደግሞ ይቀርባል፡፡ መውጫ ቀዳዳ ሁሉ ተደፍኗል፡፡ ከሞት ጋር ተፋጠዋል፡፡ ራሳቸውን ለአምላካቸው ከመስጠት ውጪ ምንም ምርጫ አልነበራቸውም፡፡ ሰለስቱ ደቂቅን ያዳነ አምላክ እንዲያድናቸው ይማጸናሉ፡፡ ባያድናቸውም ስለ ሐይማኖታቸውም እንኳን ለመሞት ቆርጠዋል፡፡ ዝማሬው ግን ቀጥሏል፡፡ “አድኝኝ እናቴ ከስጋ ፈተና….” በዝማሬው መካከል አንዱ በጭንቀት እንደ ተዋጠ አንድ ነገር ትዝ አለው፡፡ ከነኀጢያቴ ልሞት ነው ማለት ነው? ከመሞቴ በፊት የንስሐ አባቴ ጋር መደወል አለብኝ” በማለት ስልኩን ደወለ፡፡ “አባቴ በእሳት ተከበናል፤ እኔና ጓደኞቼ መሞታችን ነው፤ እባክዎ ከመሞታችን በፊት ይፍቱን!” ያቀረበው ጥያቄ ነበር፡፡ የተደናገጡት አባት፡፡” “አይዟችሁ፡፡ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ ሁላችሁንም እግዚአብሔር ይፍታችሁ!” አሏቸው የመረጋጋ ስሜት ውስጡ ተፈጠረ፡፡ በእሳት ውስጥ ከተከበቡት መካካል አንዱ የማኅበረ ቅዱሳን የሜኤሶ ወረዳ ማእከል ሰብሳቢ ዲ/ን ዘውገ በቀለ ሲሆን ስለሁኔታው ሲገልጽ ” በሕይወትና በሞት መካከል ሆነን ምንም ማድረግ ሳንችል ቀርተን በጣም ያዘንኩት የእኛ መሞት ሳይሆን በዝምታ ተውጠን ተራራው በእሳት ሲበላ ፤ከአባቶቻችን ለትውልድ የተላለፈ ማንነትና ቅርስ ሲናድ ማየቴ ነበር ያስለቀሰኝ” በማለት ነበር የገለጸው፡፡ ሊነጋ ሲል ደግሞ እግዚአብሔር ከንጋቱ ጋር ተገለጠ፡፡ እሳቱ በአንደኛው አቅጣጫ ነፋስ ወደታች ገፍቶት ጠፋ፡፡ ነገር ግን ፍሙን መርገጥ ስለማይችሉ ጥቂት መጠበቅ ነበረባቸው ታግሰው ቆዩ፡፡ ምንም እንዳልተፈጠረ በመቁጠር፤ ከሞት ጋር ግብግብ የፈጠሩበትን ሁሉ ረስተው የሚቃጠለውን ደን ለማጥፋት ፈጠኑ፡፡
የካቲት 22 ቀን
የገዳሙ አበምኔት አዲስ አበባ የሔዱበትን ጉዳይ ሳይጨርሱ ወደ ገዳሙ ተመለሱ፡፡ እሳቱን የማጥፋት ተግባር ቀጥሏል፡፡ ከሐረር፣ ከድሬዳዋ፣ ከአለማያና ከናዝሬት ምእመናን እየጎረፉ ነው፡፡ እሳቱን ለማጥፋት ውኃው በእጅ ይረጫል በቅጠል ይቀጠቀጣል፡፡ እሳቱ ተራራውን ጨርሶ ጫፍ ላይ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እየገሰገሰ ነው፡፡ ከመነኮሳት መኖሪያ የ50 ሜትር ርቀት ብቻ ቀርቶታል፡፡ ባሕታዊ መርአዊ /መነኮሳቱ አይዋ መርኣዊ ይሏቸዋል/ የ80 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ ከዐርባ ዓመታት በላይ በገዳሙ ውስጥ ኖረዋል፡፡ እሳቱ ከበአታቸው ጋር ፊት ለፊት ተፋጠዋል፡፡ የ50 ሜትር ርቀት ላይ አባ ዘወልደ ማርያም እቃቸውን እንዲወጣ ቢጠይቋቸው አሻፈረኝ አሉ፡፡ “የኔን በአት እግዚአብሔር አያቃጥለውም” በማለት ጸኑ፡፡ በጀሪካን ጸበል ይዘው በመሔድ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ በማለት ሦስት ጊዜ ረጩት፡፡ እሳቱ ተጥመልምሎ ወደ ምዕራብ ዞረ፡፡ እግዚአብሔር ተአምራቱን ገለጠ፡፡ የመነኮሳቱ ቤቶችም ከመቃጠል ዳኑ፡፡
እሳቱ ተራራውን አገባዶታል፡፡ በልምላሜ ግርማ ሞገስ ተውቦ የሀገር ሀብት፣ የብርቅዬ የዲር እንስሳት አእዋፍ የመናንያንና የተሰወሩ አባቶች መኖሪያ ያ አሰቦት ተራራ እርቃኑን ቀርቷል፡፡ ድንጋዩ ገጦ ባዶውን ተጋልጧል፡፡ ጥቁር የሃዘን ልብስ ለብሷል፡፡ ከሰዓት በኋላ ጋብ ለማለት ሞከረ፡፡ ምእመናን ዝለዋል፤ አቅማቸው ተሟጧል፡፡ እሳቱም አብሮ ተዳከመ፡፡ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ሲሆን እሳቱም ምእመናንና ማኅበረ መነኮሳቱ የእፎይታን አየር ተነፈሱ፡፡ እሳቱ ቢጠፋም ፍሙ ሙሉ ለሙሉ ባለመጥፋቱ ደግሞ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለው ሥጋት የሁሉም ቢሆንም ምእመናን በተከሰተው ነገር እያዘኑና እያለቀሱ ወደ መጡበት መመለስ ግድ ሆነ፡፡ የሜኤሶ ወረዳ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና የወረዳው ቤተ ክህነት ጸሓፊና ሌሎችም ከመነኮሳቱ ጋር በመነጋገር ለማደር ወሰኑ፡፡
የካቲት 23 ቀን
እሳቱ በመጥፋቱ ቀኑን ሙሉ ለሚመለከታቸው አካላት በስልክ በማሳወቅ የጥበቃው ሁኔታ እንዲጠናከር ለማድረግ አቤቱታ በማቅረብ ተዋለ፡፡ መነኮሳቱም በመሰባሰብ ወደፊት በገዳሙ ሕልውና ዙሪያ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በመመካከር ነው ያለፈው፡፡ የገዳሙ ግርማ ሞገስ የነበረው በሺዎች ሄክታር የሚገመተው ደን ወድሟል፡፡ የቀረው በአባ ሳሙኤል ገዳም በኩል ያለው ደን ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመጋቢት 2000 ዓ.ም. ደግሞ 11,000 /አስራ አንድ ሺህ/ ሄክታር ደን መቃጠሉ ይታወሳል፡፡
አመሻሽ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና የወረዳው ቤተ ክህነት ጸሓፊን ጨምሮ ሁላችንም ከአባቶች ቡራኬ ተቀብለን ጉዟችንን ወደ ሜኤሶ ለማድረግ ወስነን ተሰናብተን፡፡ 6 ኪሎ ሜትር ቁልቁለቱን ተያያዝነው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሲሆን ቁልቁለቱን እንደጨረስን ቀና ብለን ወደ ተራራው ተመለከትን፡፡ በልምላሜና በሰንሰለታማነት የሚታወቀው ሰማይ ጠቀሱ ተራራ፤ የገዳማውያን አባቶች መኖሪያ ፤ ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው ዳዋ ለብሰው ግርማ ለሊቱን ድምጸ አራዊቱን ጸበ አጋንንቱን ታግሰው ለሃገር ለወገን የሚጸልዩበት ደንና ዋሻ በከፊል ወድሟል፡፡
አንገታችንን ወደ ላይ እንዳቀናን እንባችን ፈሰሰ፡፡ መልሰን ደግሞ ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ተመለከትን፡፡ ከተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ አዲስ የደን ቃጠሎ መከሰቱን ተመለከትን፡፡ በዚያች ቅጽበትና ሰዓት የተለኮሰ ነው፡፡ እሳቱ ገና መጀመሩ ነው፡፡ እኛ ካለንበት ቢያንስ የ3 ሰዓት መንገድ ሊያስኬድ የሚችል ነው፡፡ በስልክ ለአበምኔቱ አሳውቀን ሕዝቡን የመቀስቀስ ሥራ ተጀመረ፡፡ በምሽት መሔዱ አደጋ ስለሚያስከትል ያለው ምርጫ እስኪነጋ መጠበቅ ነው፡፡ እሳቱም ባለበት ቆሞ አይጠብቅ ያገኘውን እያጨደ እየሰለቀጠ መጓዙን ይቀጥላል፡፡ ምን ምርጫ አለን?! እሳቱ ወደ ለአባ ሳሙኤል ገዳም መነኮሳይያት መንደር ተምዘገዘገ፡፡
የካቲት 24 ቀን
መረጃው የደረሳቸው ምእመናን፣ የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ በመሰብሰብ በሌሊት ጉዞ ተጀመረ፡፡ ቦታው ሲደረስ ግን ያጋጠመው ችግር የከፋ ነበር፡፡ ማንነታቸው ያልታወቀ ግለሰቦች በምእመናንና በፌደራል ፖሊስ ላይ የተኩስ እሩምታ ከፈቱ፡፡ በቦታውም ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተላኩ ልኡካን በተገኙበት የፌደራል ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ተኩስ የከፈቱ ታጣቂዎችን ከአካባቢው ማራቅ በመቻሉ እሳቱን ለማጥፋት ጥረቱ ቀጠለ፡፡ ወደ የቤቱ ተበታትኖ የነበረው ማኅበረ ምእመናን ጀሪካናቸውን ውኃ ሞልተው ለማጥፋት ተፋጠኑ፡፡ አመሻሽ ላይ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡
ማኅበረ መነኮሳቱ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከፌደራል ፖሊስ ተወካዮችና ባለሥልጣናት ጋር በጥበቃ ዙሪያ ውይይት የተካሔደ ሲሆን በፌደራል ደረጀ መፍትሔ እንደሚሰጥ ለመነኮሳቱ ተገልጾላቸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመነኮሳቱ ከመንግሥት የጥበቃ ኀይል እንዲመደብላቸው ለጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “በተከሰተው ቃጠሎ አዝኛለሁ ለቅዱስ ፖትርያርኩ ስለ ጉዳዩ አሳውቃለሁ፡፡ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔ ይሰጥበታል” በማለት ማኅበረ መነኮሳቱንና ምእመናንን አጽናንተዋል፡፡
የገዳሙ አበምኔት ከዚህ በፊት ስለተከሰተው የደን ቃጠሎ ሲገልጹም በ2000 ዓ.ም. በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍተኛ መጠን ያለው ደን በእሳት ቃጠሎ እንደወደመ በማስታወስ “ደኑን ለመጠበቅ ከመንግሥት ጥበቃ እንዲመደብልን በተደጋጋሚ አሳውቀናል፡፡ ደኑ የገዳሙ ብቻ ሳይሆን የሐገር ሀብት ነው፡፡ በረሃማነትን ለመከላከል መንግሥት ጥረት እያደረገ ባለበት ሁኔታ ውስጥ እንዲህ አስከፊ የደን ውድመት መድረሱ አሳዝኖኛል” ብለዋል፡፡ ስጋቱ ግን አሁንም ቀጥሏል፡፡
በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ቃጠሎ መንስኤዎች ሁለት እንደሆኑ ማኅበረ መነኮሳቱ ይገልጻሉ፡፡ አንደኛው በዋነኛነት አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ከብቶቻቸውን ሳር ለማብላት በሚል የገዳሙን ክልል ጥሰው መግባትና የገዳሙን ከብቶች በየጊዜው ለመዝረፍ መሞከራቸው ነው፡፡ ካልተሳካላቸው ደኑ ላይ እሳት ለቀውበት ይጠፋሉ፡፡ በተደጋጋሚ ከብቶችን የዘረፉ ሲሆን ጉዳዩ በሽምግልና እየተያዘ ለመስተዳደር አካላት አቤቱታ በማቅረብ የማስመለስ ሒደት ነው ያለው፡፡ አልፎ አልፎም እያስቀሩባቸው እንደሆነ በሃዘን ተውጠው መነኮሳቱ ይገለጻሉ፡፡ አሁንም በስጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ በምሽት ተደብቀው ዛፍ እየቆረጡ በመውሰድ መተዳደሪያ ያደረጉ ሕገ ወጥ ዛፍ ቆራጮች ከጊዜ ወደጊዜ ቁጥራቸው መጨመሩ ሌላው ስጋታቸው ነው፡፡ ቀን ስለሚደርስባቸው ጨለማን ተገን በማድረግ በቡድን ወደገዳሙ ክልል በመግባት፣ እንዲታያቸው እሳት በማቀጣጠል ዛፎችን ይጨፈጭፋሉ፡፡ እሳቱን ሳያጠፉት ይሔዳሉ፡፡ ቃጠሎም ይቀሰቀሳል፡፡
በገዳሙ ውስጥ የመነኮሳት መኖሪያ በቅድስት ሥላሴ ገዳም ዙሪያ ሲሆን የመነኮሳይያት መኖሪያ ደግሞ ገዳሙን በመሠረቱት በአባ ሳሙኤል ዘወገግ ገዳም ዙሪያ ነው፡፡ 50 መነኮሳት፣ 25 መነኮሳይያት፣ መናንያን ባህታውያን የአብነት ተማሪዎችን ጨምሮ 170 የሚሆኑት በገዳሙ ውስጥ ይኖራሉ፡፡
የገዳሙ አበምኔት አባ ተክለ ማርያምና የገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት እሳቱን በማጥፋት የተባበሩትን ሁሉ በእግዚአብሔር ስም አመስግነዋል፡፡ ለመሆኑ ለገዳሙ ደህንነት ማነው ኃላፊነቱን የሚወስደው? “ ዲያብሎስ ቀስቱን ጨረሰ ዝናሩንም አራገፈ ቤተ ክርስቲያንን ግን ሊያጠፋት አልቻለም” እንዳለው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅድስት ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ላይ ተመስርታለችና ከቶ የሲኦል ደጆች ሊያነዋውጧት አይችሉም!!!
የካቲት 29/2004 ዓ.ም.
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ሰው ሁሉ በሥጋም ሆነ በነፍስ ታሞ ነበር፡፡ እርሱ ወደዚህ ዓለም የመጣው የሰው ልጆች ሁሉ አባትና መድኀኒት ስለሆነና ከዚህ በሽታቸው ሊያድናቸው ነው፡፡ ይህ ስለሆነ ወደ እኛ ከመጣ በኋላ ስለ መጣበት ዓላማ እንዲህ በማለት ተናገረን፡- «. . . ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፤ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ፤ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል. . .» ሉቃ 4፥17-19፡፡ ይህ በመሆኑም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድረ እስራኤል ተዘዋውሮ በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙ በሽተኞችን ሁሉ አድኗቸዋል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ይህን ሁኔታ የገለጸው እንዲህ በማለት ነው፡- «. . . የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር፡፡ ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ፤ አጋንንት ያደሩባቸውን፤ በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፤ ፈወሳቸውም፡፡» ማቴ 4፥23-24፡፡
ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን እያደረገ በምድረ እስራኤል ሲዞር ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ለ38 ዓመታት ያህል በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ በአልጋው ላይ ተኝቶ የነበረውን በሽተኛ ሰው ኢየሩሳሌም ውስጥ በምትገኘውና ቤተ ሳይዳ በምትባለው የመጠመቂያ ቦታ ያገኘው፡፡ በዚህች የጸበል ቦታ ላይ ተኝቶ ድኅነቱን ለማግኘት ይጠባበቅ የነበረው ይህ ሰው ብቻ አልነበረም፤ሌሎችም በተለያዩ በሽታዎች የተያያዙ ብዛት ያላቸው በሽተኞች ጭምር እንጂ፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይህን ሁኔታ የገለጸው እንዲህ በማለት ነው፡- «. . . በሽተኞችና ዕውሮች፣ አንካሶችም፣ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር፡፡» ዮሐ 5፥3፡፡ እነዚህ ሁሉ በሽተኞች በዚያች አምስት መተላለፊያ ባሏት የመጠመቂያ ቦታ ላይ ተኝተው ይጠባበቁ የነበረው የጌታ መልአክ ወርዶ ጠበሉን ሲያናውጠው ቀድሞ ወደ ውኃው የሚገባ ስለሚድን ነበር፡፡ መልአኩ ወርዶ ውኃውን ሲያናውጠው ሊፈወስ የሚችለው አንድ በሽተኛ ብቻ ነበር፡፡ መልአኩ ቤተ ሳይዳ ተብላ የምትጠራውን ጸበል ሲያናውጣት ይህን በሽተኛ ሰው ወደ ጸበሉ ቦታ ተሸክሞ የሚያደርሰው ሰው ስላልነበረው ፈውስን ሊያገኝ አልቻለም ነበር፡፡ እርሱ ለ38 ዓመታት ያህል በመጠመቂያዋ አጠገብ ሊተኛ የቻለው ምንም ዓይነት ሰው ወይም ዘመድ ወይም ወገን ስላልነበረው ነው፡፡
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች የመጠመቂያ ቦታ የመጣው በተለይ ይህን ሰው ለመፈወስ ነው፡፡ ምክንያቱም ወንጌላዊው ዮሐንስ «ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ. . .» (ዮሐ 5፥7) ብሎ የጻፈልን ለ38 ዓመታት ያህል መተኛቱን አውቆ ሊያድነው መምጣቱን ከአነጋገሩ ስለ ተረዳ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ምድራውያን ሀኪሞች፡- እንዴት ያደርግሃል? ከጀመረህ ስንት ጊዜ ይሆንሃል? ልትታመም የቻልኸው በምን ምክንያት ይመስልሃል? ሳይል በአምላክነቱ ሁሉንም ነገር ያውቅ ስለ ነበር «ልትድን ትወዳለህን?» በማለት ፈቃደኛነቱን ከጠየቀው በኋላ «ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ. . .» በማለት በቃሉ ስለ ፈወሰው አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ሊሔድ ችሏል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ከነበረበት በሽታ ጤናማ ሊሆን ያልቻለበትን ምክንያት ሲናገር «ጌታ ሆይ፡- ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ነገር ግን እኔ ልመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል. . .» (ዮሐ 5፥7) ነበር ያለው፡፡
ዛሬም ቢሆን «ሰው የለኝም» የሚለው ቃል የብዙ ሰዎች ምክንያት ነው፡፡ ለምን ትምህርትህን አልቀጠልህም ተብሎ የሚጠየቅ ሰው እንድማር የሚረዳኝ ሰው የለኝም ይላል፡፡ ለምን ሥራ አልጀመርሽም የምትባል ሴት ልጅ ሥራ የሚያስገባኝ ሰው የለኝም ትላለች፡፡ ልትድኑ ያልቻላችሁት ለምንድር ነው ተብለው የሚጠየቁ ሰዎችም የምንታከምበት ገንዘብ የሚሰጠን ሰው የለንም ይላሉ፡፡ ብዙ ሰዎች በብዙ ቦታዎች ላይ አጥብቀው የሚሹት ወይም የሚፈልጉት የሰዎችን መኖር ወይም እርዳታ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እኛ አጥብቀን ልንሻው የሚያስፈልገን ነገር የእግዚአብሔርን እርዳታና ማዳን መሆን አለበት፡፡ የምንበላው ምግብ፣ የምንጠጣው መጠጥ፣ የምንለብሰው ልብስ፣ የምንጠለልበት መጠለያ፣ የምንማርበትና የምንታከምበት ገንዘብና የምንፈልገውን ሥራ መሥራት የምንችልበትን መንገድ ሊያድሉን የሚችሉት ሰዎች ናቸው ብለን ስለ ወሰንን ሁሉን ሊሰጥ ከሚችለው ከእግዚአብሔር ላይ ዓይኖቻችንን አንሥተናል፡፡ የሚያበላ፣ የሚያጠጣ፣ የሚያለብስ፣ መጠለያ የሚሰጥ፣ ሥራን የሚባርክ፣ የሚፈውስ፣ የሚያበለጽግ፣ የሚያኖር እግዚአብሔር መሆኑን አስረግጠን ስላላመንንና መታመኛችንን ሁሉ በሰዎች ላይ ስላደረግን ልንድን አልቻልንም፡፡ ይህ በሽተኛ ሰው እድናለሁ ብሎ የተኛው የእግዚአብሔርን እርዳታ አገኛለሁ ብሎ ሳይሆን የአንድን ጎልማሳ ሰው ፈርጣማ ክንድ ስለ ነበር ሊድን አልቻለም፡፡ እርሱ የዳነው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያድነው እንደሚችል ባመነ ጊዜ ነበር፡፡ ለመዳንና ሌሎች ያጣናቸውን ነገሮች ለማግኘት በእግዚአብሔር ማመን ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ማመን ከዚያም መዳን!
እግዚአብሔር ያለው ሰው ሁሉም ነገር አለው፤ እግዚአብሔር የሌለው ሰው ግን ሁሉም ነገር ያለው ይመስለዋል እንጂ ምንም ነገር የለውም፡፡ የተማረ ቢመስልም አልተማረም፤ሥራ ያለው ይምሰለው እንጂ ሥራ የለውም፤ጤና ያለው ይምሰለው እንጂ ጤና የለውም፤ ሀብት ያለው ይምሰለው እንጂ ድሃ ነው፤ የለበሰ ይምሰለው እንጂ እርቃኑን ነው፤ እግዚአብሔርን ሳያምኑ የሚገኝ ትምህርት፣ ሥራ፣ ጤና፣ ልብስ፣ ሀብት. . . ወዘተ በከንቱ የሚጠፉ ናቸውና፡፡ ላጣው ነገር ሁሉ እንደ መፍትሔ አድርጎ ሰውን የሚያቀርብና መፍትሔ ሲያጣ ሰው ስለሌለኝ ነው በማለት ምክንያት የሚቀርብ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት ደካማ ወይም ባዶ መሆኑን ይህ ሁኔታ ያረጋግጥልናል፡፡
መፃጒዕ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር በማድረግ ከሰው የሚበልጥ መሆኑን ቢያውቅ ኖሮ እንዲህ አይልም ነበር፡፡ ብዙ ሰዎችም ከሰዎች ይልቅ የሚያምኑ እግዚአብሔርን ቢሆኑ ኖሮ ችግር ላይ አይወድቁም ነበር፡፡ ሰው በሰው ከሚታመን ይልቅ በእግዚአብሔር ቢታመን የሚሻል መሆኑን ነቢዩ ዳዊት ሲናገር እንዲህ ብሏል፡- «ለእኔስ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ መታመኛዬም እግዚአብሔር ነው፤» መዝ 72፥28፡፡ ብዙዎች ግን መታመኛቸውን ወደ ሰው ስላደረጉ ወደ እግዚአብሔር ሊቀርቡ አልቻሉም፡፡ በእግዚአብሔር አምኖ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመቅረብ ጠበል ከመጠመቅ፣ በእምነት ከመታሸትና ቅብዓ ቅዱስ ከመቀባትና በመስቀል ከመዳሰስ ይልቅ በሰዎች አምኖ ወደ ጠንቋዩ፣ ወደ ቃልቻው፣ ወደ ዛር ጎታቹ በመቅረብ እርሱ አድርጉ የሚላቸውን ነገሮች ማድረግን የሚሻል መፍትሔ አድርገው ተቀብለውታል፡፡
በእግዚአብሔር አምናለሁ ማለት ብቻም ድኅነትን ወይም ያጡትን ነገር አያስገኝም፤ለመዳን ያመኑትን ነገር በሥራ መግለጽ ያስፈልጋልና፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንዲሁ በአፋቸው ብቻ በእግዚአብሔር እናምናለን በማለት ቢናገሩም እምነታቸውን በሥራ ለመግለጽ ስላልቻሉ ሊድኑ አልቻሉም፡፡ በዚህ ጊዜ ጉድለቱ ከእነርሱ አለማመን እንደ መጣ አድርገው ስለማይቀበሉ እግዚአብሔርን ሲያማርሩ እንመለከታለን፡፡ ሰው ግን የሚድነው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም ጭምር ነው፡፡ አባታችን አብርሃም በእምነት የጸደቀ ሰው ቢሆንም ይህን እምነቱን በሥራ አስረግጦ የገለጸው እግዚአብሔር አድርግ ወይም ሥራ ያለውን ነገር ስለ ሠራ ነው፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር አምኜያለሁ ብሎ በኀጢአት ከተሞላው ከከለዳውያን አገር ከዑር ለመውጣት ፈቃደኛ ባይሆን ኖሮ እግዚአብሔር የገባለትን ቃል ኪዳን በሙሉ ሊያገኝ አይችልም ነበር፡፡ ማመን፤ ካመኑ በኋላ ያመኑበትን ነገር በሥራ መግለጽ የክርስትና ዐቢይ መርሆ ነው፡፡ ይህ ስለሆነም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እንዲህ በማለት የተናገረው፡- «ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡» ያዕ 2፥26፡፡
ሥራና እምነት የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ እምነት ያለ ሥራ፤ ሥራም ያለ እምነት ዋጋ ወይም ድኅነት ሊያሰጡ አይችሉም ማለት ነው፡፡ የሰው ሥጋ ሞተ የሚባለው ነፍሱ ስትለየው ነው፤ የሰው እምነት ምውት ነው የምንለውም ሥራ ሲለየው ነው፡፡ ለማመንማ አጋንንትም እግዚአብሔርን ያምኑታል በፊቱም ይንቀጠቀጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ እምነታቸውን በሥራ ሊገልጹት ስላልቻሉ ወይም ስላልፈቀዱ ሊድኑ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ታሞ ለረዥም ጊዜ በአልጋ ላይ የተኛ ሰው እግዚአብሔርን አምናለሁ እያለ ይህ እምነቱን በሥራ መግለጽ የማይችል ከሆነ የእርሱ እምነት ከአጋንንት እምነት ጋር የሚመሳሰል ስለሆነ ድኖ የተኛበትን አልጋ ተሸክሞ መሔድ አልቻለም፡፡ ይህ ሰው እምነቱን እግዚአብሔር በሚከብርባቸው ሥራዎች ሳያስደግፍ እርሱ የማይከብርባቸውን ሥራዎች የሚሠራ ከሆነ ሊድን አይችልም፤ሥራዎቹ ይበልጥ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያጣሉት ሥራዎች ናቸውና፡፡ አንድ ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው ልብስና ምግብ ላጡ ሰዎች እምነቱን ምግብና ልብስ በመስጠት ወይም በሥራ በመግለጽ ሊታደጋቸው ይገባዋል እንጂ ያለ ምንም ዓይነት በጎ ሥራ ሳያደርግላቸው «በደኅና ሒዱ፤ እሳት ሙቁ፤ ጥገቡም» ቢላቸውና ለሰውነታቸው የሚያስፈልጋቸውን ምግብና ልብስ ባይሰጣቸው (ያዕ 2፥14-16) የእርሱ እምነት በሥራ ስላልተገለጸ እምነቱ የክርስቲያን እምነት ሳይሆን የአጋንንት እምነት ነው ማለት ነው፡፡
ሰው በእግዚአብሔር መታመኑን ትቶ በሰው የሚታመን ከሆነና የታመነበትን ሰው አንድ ቀን እንደ መፃጉዕ ከአጠገቡ ሲያጣው ወይም ልብስ፣ ምግብና ጤና ሊያድለው ሲያቅተው ወይም ያለ ልብስና ያለ ምግብ እሳት ሙቅ እና ጥገብ ሲለው ለ38 ዓመታት ያህል በደዌ ዳኛ እና በአልጋ ቁራኛ ተይዞ ሊቆይ ይችላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በበሽታው ወይም በቁስሎቹ ምክንያት ከፍተኛ ሥቃይ የደረሰበት ሰው ጻድቁ ኢዮብ ነው፡፡ ኢዮብ ሥጋውን በገል እስከሚፍቅ ድረስ ነው የተሰቃየው፡፡ ይሁን እንጂ እምነትን ከሥራ ጋር አስተባብሮ የያዘ ሰው ስለ ነበር እግዚአብሔር አምላክ ፈውሶታል፤ያጣውንም ነገር ሁለት እጥፍ አድርጎ መልሶለታል፡፡ ስለሆነም ሰው ከበሽታው ሊፈወስና ያጣው ነገር ሁለት እጥፍ ሆኖ እንዲመለስለት ከፈለገ ፍጹም በእግዚአብሔር ማመንና የጽድቅ ሥራዎችን መሥራት ይገባዋል፡፡ መፃጉዕ ለእነዚህ ሁሉ ዘመናት በአልጋው ላይ ሊተኛ የቻለው በኀጢአቱ ምክንያት መሆኑን የወንጌሉ ቃል እንዲህ በማለት ገልጦታል፡- «ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና፡- እነሆ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደፊት ኀጢአት አትሥራ አለው፡፡» ዮሐ 5፡14፡፡ ሕመም በኢዮብ ላይ እንደ ተገለጠው ለፈተና ሊገለጥ እንደሚችል ሁሉ በመፃጒዕ ላይም ለኀጢአት ተገልጦአል፡፡ በዘውሩ ተወልደ ላይ የእግዚአብሔር ክብር እንዲገለጥበት እንደ ተገለጠውም ሊገለጥ ይችላል፡፡ በመሆኑም በመፃጉዕ ላይ የተገለጠው ደዌ በሠራው ኀጢአት አማካይነት የመጣ ስለሆነ ጌታ «ከዚህ የበለጠ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኀጢአት አትሥራ፡፡» (ዮሐ 5፡14) በማለት አስጠንቅቆታል፡፡
ዛሬም ቢሆን ሰው ሁሉ በኀጢአት ደዌ ተይዟል፡፡ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጠብ፣ ክርክር፣ ውሸት፣ ስርቆት፣ ስድብ፣ ዋልጌነት፣. . . ወዘተ በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚዘወተሩ የኀጢአት ዓይነቶች ናቸው፡፡ የለበስነው ሥጋ ድካምና ኀጢአት የሚስማማው ሥጋ ስለሆነ ሁላችንም በአንዱ ወይም በሌላው የኀጢአት ዓይነት እንሰነካከላለን፡፡ ሁሉም ሰው ኀጢአተኛ ሰው መሆኑን ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በአንደኛ መልእክቱ ውስጥ እንዲህ በማለት ገልጾታል፡- «ኀጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም፡፡» 1ኛ ዮሐ 1፥8፡፡ ሁሉም ሰው ኀጢአተኛ ከሆነ ደግሞ ድኅነትን ወይም ፈውስን ለማግኘት «አቤቱ፡- እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ፡፡ ከበደሌም ፈጽሞ እጠበኝ፤ ከኀጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፤ ኀጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና፡፡» (መዝ 50፡1-3) እያለ በየጊዜው ንስሓ በመግባት ምሕረት የሚያድለውን ጌታ መለመን አለበት፡፡ እንደ መፃጒዕ ስለ ሠራው ሥራ ሳይፀፀት «ሰው የለኝም» እያለ በስሞታ የሚቆይ ሰው ድኅነትን ሊያገኝ አይችልም፡፡ ዘወትር እንደ ቅዱስ ዳዊት ኀጢአቱን በዓይኖቹ ፊት የሚመለከት ሰው በሠራው ኀጢአት ዘወትር እየተፀፀት ዕንባዎቹን በመኝታው ላይ ያፈስሳል፡፡
ዛሬ ግን ብዙ ሰዎች ኀጢአት መሥራታቸው ከቶውኑ ትዝ ስለማይላቸው በንስሓ ሊመለሱ አልቻሉም፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ዕድሚያቸውን የሚያሳልፉት በኀጢአት አልጋ ላይ ተንጋልለው ነው፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድመን ከተኛንበት የኀጢአት አልጋችን ላይ በመነሣት ይህንኑ አልጋችንን ተሸክመን እንድንሔድ በመናገር የሚገድል ኀጢአችንን በመከራው፣ በሞቱና በትንሣኤው ቢያጠፋልንም ተመልሰን እዚያው አልጋችን ላይ በኀጢአት ተጠልፈን ወድቀናል፡፡ ከአሁን በኋላ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኀጢአት ወድቀው በንስሓ ለመመለስ ላልቻሉት ኀጢአተኞች ለሁለተኛ ጊዜ «አልጋህን ተሸክመህ ሒድ» ለማለት በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት አይገለጥም፡- «የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡» (ማቴ 25፡30) በማለት ሊፈርድበት እንጂ፡፡ የአምላካችን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይሁን፤አሜን፡፡
ይቆየን፡፡
በጎውን ሁሉ ለእኛ ያደረገና የሚያደርግ እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤አሜን፡፡
የካቲት 29/2004 ዓ.ም.
ይህ ከላይ ያነሣነው ርዕስ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት መጾሙን ያስተምረናል፡፡
በዚህ ኀይለ ቃል ሁለት ታላላቅ ቁም ነገሮችን ቃላትን እንመለከታለን
በቅድሚያ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት የሚለውን ከእነ ምስጢሩ እንመለከተዋለን፡፡ ቀጥለን ደግሞ ጌታችንስ ለምን አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ? የሚለውን እንመለከታለን እግዚአብሔር አይነልቡናችንን ይክፈትልን፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን የፈጠረውን የሰው ልጆችን አባት አዳምን፣ በልጅነት አክብሮ ገነት ያስገባው በፈጠረው በአርባ ቀኑ ነው፡፡ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘገብሮ ለአዳም” አዳምን የፈጠረ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው እያሉ እያመሰገኑ መላእክት ወደገነት አስገብተውታል /ቀሌ.4፥/
“ወላምድኅረ ተፈጸመ ለአዳም ፵ መዋዕል በምድር ኀበ ተፈጥረ አባዕናሁ ውስተ ገነተ ኤዶም ኩፋ.9፥12 ለአዳም አርባ ቀን ከተፈጸመለት በኋላ ወደገነት አስገባነው፡፡ ሔዋንንም በሁለት አርባ ማለትም በሰማኒያ ቀኑዋ ወደገነት አስገቧት ኩፋ.4፥12
በተጨማሪም አዳም ትእዛዘ እግዚአብሔር ካፈረሰ በኋላ ዲያብሎስ በአቋራጭ መጥቶ አስወጣው እንጂ ሱባኤ የገባው ለአርባ ቀናት ነበር፡፡ ይህን አርባ ቀን የሰው ልጆች ከስህተት በኋላ በቀንም ሆነ በዓመት ለጾም፣ ለሱባኤ፣ ከዚያ አልፎ ለመቅጫነት አግልሏል፡፡
በኦሪት ዘፍጥረት እንደምናነበው የሰው ልጅ በንፍር ውኃ የተቀጣው አርባ መአልትና ሌሊት ነበር፡፡ “አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናም አዘንማለሁና የፈጠርሁትንም ፍጥረት በምድር ላይ አጠፋለሁና ዘፍ.7፥12 “የሰማይ መስኮቶች ተከፈቱ ዝናቡም አርባ መአልትና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ” ዘፍ.7፥12
በዚህ ዐይነት አርባ ቀን እግዚአብሔር ሰውን እንደቀጣበት እናያለን፡፡ መቅጣት ብቻ ሳይሆን በዚህ የአርባ መአልትና የአርባ ሌሊት ዝናም ምድርን ከበዛባት ርኲሰት አጥቧታል፡፡ ምክንያቱም የጥምቀት ምሳሌ ነውና፡፡ ማየ አይህ /የጥፋት ውኃ/ የጥምቀት ምሳሌ ለመሆኑ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡” 2ጴጥ.3፥20ና21
አሁንም ከዚሁ ሳንርቅ የመርከቧ መስኮቶች የተከፈቱት በአርባ ቀን መሆኑን ይገልጻል፡፡ “ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ” ዘፍ.8፥6 መርከቧ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ እስራኤል ወደ ምድረ ርስት ያደረጉት ጉዞ አርባ ዓመት እንደፈጀ ተጽፏል፡፡ ይህም መንገድ ደግሞ የአርባ ቀን መንገድ ነበር በእግዚአብሔር ቁጣ ወደ አርባ ዓመታት ተለወጠ እንጂ፡፡ “በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ ዓመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ” ዕብ.3፥7-19 ሲል ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎታል፡፡
እስራኤል አርባ ዘመን መና ከደመና እየወረደላቸው ተመግበዋል፣ ውኃ ከአለት እየፈለቀላቸው ጠጥተዋል፡፡ ሲያምጹም ተቀጥተዋል፡፡ ሙሴ ወንድሞቹን እስራኤልን ለመጎብኘት የመጣው በአርባ ዓመት ነበር “በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ የሥራቸውን መከራ ተመለከተ” ዘፀ.3፥11 ሐዋ.7፥23 የተሰደደውም በዚሁ እድሜው ነው፡፡ በምድያም በግ በመጠበቅ አርባ ዘመን ኖሯል እንደገና እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ እንዲያወጣ እግዚአብሔር የላከው በአርባ ዘመን ነበር፡፡ “አርባ ዓመትም ሲሞላ የጌታ መልአክ በሲና ተራራ ምድረ በዳ ታየው፡፡ ዘፀ.3፥30
ይህም ብቻ አይደለም ሙሴ ለዚህ አገልግሎት በተመረጠበት ጊዜ በሲና ተራራ አርባ ቀንና ሌሊት ጾሟል “ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ቆየ” ዘፀ.24፥19 ዝም ብሎ ሥራ ፈትቶ አይደለም የቆየው እየሠራ ነው ሥራውም ጾም ነው፡፡ “እግዚአብሔርም ሙሴን በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው በዚያም አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበር አልበላም አልጠጣም” ዘፀ.34፥27 እየጾመ ነበር ማለት ነው በዚህ ጾሙ ሙሴ የቃል ኪዳኑን ጽላቶች ተቀብሎበታል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ከንቱ ሳይሆን ዋጋ ያለው እንደሆነ ነው፡፡ የኤልያስ ጉዞ አርባ ቀን አርባ ሌሊት እንደነበረ ተጽፏል፡፡ “የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና የምትሔድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ አለው ተነሥቶም በላ ጠጣ በዚያም ምግብ ኀይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሔደ” 1ነገ.19፥4-8
ሕዝቅኤል አርባ ቀን ጾሞ 600 ሙታን አስነሥቷል፡፡ እዝራ ሱቱኤል አርባ ቀን ጾሞ የጠፋ መጻሕፍትን መልሷል አብረው የነበሩ አምስት ሰዎች ቀን ቀን ይጽፋሉ ማታ ማታ ጥቂት እህል ውኃ ይቀምሱ ነበር እዝ.ሱቱ.13፥23-25 ጌታችን በተወለደ በአርባ ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቷል ሉቃ.2፥22 ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መአልትና ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2 በተነሣ በአርባኛው ቀን ወደሰማይ አረገ ሐዋ.11፥10 ሰው በተጸነሰ በአርባ ቀኑ ተስዕሎተ መልክዕ ይፈጸምለታል፡፡ “በአርባ ቀን ትሾመዋለህ” እንዲል ቅዱስ አትናቴዎስ ወንድ በተወለደ በአርባ ቀኑ ሴትም በ80 ሁለት አርባ ክርስትና ይነሣል፡፡ ሰው በአረፈ በአርባ ቀኑ ጸሎተ ፍትሐት ይደርስለታል፡፡ ሰው በአርባ ቀን ጸሎት ተክሊል ይደርስለታል ፍት.ነገ. እን.24 ገጽ 322
አርባ ቀን ይህን ያህል ምስጢር ያለው ቀኑ ነው ጌታችን ለምን? አርባ ቀን ጾመ ስንል ከላይ ያየናቸው አበው ነቢያት ብዙውን ጊዜ የጾሙት አርባ ቀን ነው፡፡ ቢቀንስ አጎደለ ከፍ ቢያደርግ አበዛ ብለው አይሁድ የነቢያትን ሕግ አፈረሰ በማለት ትምህርቱ አንቀበልም ባሉ ነበርና ይህን ምክንያት ለመንሳት አርባ መአልትና ሌሊት ጾመ፡፡ እስራአል 40 ዓመት ተጉዘው ምድረ ርስት ገብተዋል፡፡ እናንተም 40 ቀን ብትጾሙ ገነት መንግሥተ ሰማያት ትገባላችሁ ሲለን ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው የጥፋት ውኃ በምድር አርባ ቀንና ሌሊት ዘነመ ምድር ነጻች ሰው አርባ ቀንና ሌሊት ቢጾም ርስት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳል ሲለን ነው፡፡ ጾም ለርስት ለመንግሥተ ሰማያት የሚያበቃ ከኀጢአት የሚያነጻ እንደሆነ ሊያስተምረን በኦሪት በተጾመው ቁጥር ጾሞ ሥርዓትን ሰጠቶናል፡፡
ጾም ማለት ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ፍት.አን.15 “ጾምሰ ተከልኦተ ብዕሊ ዕምመብልዕ በጊዜ እውቅ” ጾም ማለት በታወቀው ዕለት በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ መብል መጠጥ የኀጢአት መሠረት ነው በመብል ምክንያት ሞት በሰው ልጆች ላይ መጣ “ይችን ዕፀ በለስ ብትበሉ ሞትን ትሞታላችሁ” ዘፍ.2፥17
መብል መጠጥ ከልክ ሲያልፍ ከተዘወተረም ከእግዚአብሔር ይለያል፤ “ያዕቆብ በላ ጠገበ ወፈረ ገዘፈ ደነደነ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ተወ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር ተለየ” ዘዳ.32፥15-17 “የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥን አትሰብክም” ሮሜ.14፥16፣ 1ቆሮ.8፥8-13 “ዛሬ የሚራቡ የሚጠሙ ብፁአን ናቸው ይጠግባሉና ማቴ.5፥6 ጾም የሥጋ መቅጫ ነው፤ “ነፍሴን /ሰውነቴን/ በጾም ቀጣኋት መዝ.68፥10 ጾም በነቢያት የተመሠረተ በክርስቶስ የጸና በሐዋርያትም የተሰበከና የተረጋገጠ ለክርስቲያኖች ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረን ይህን ጾም ከምግብ ለመከልከል ጋር ጸሎትን፥ ስግደትን፥ ምጽዋትንና የንስሐ ዕንባን ጨምረን እንጹመው፡፡ ጌታችንና ነቢያት፣ ሐዋርያት የተውልን መንፈሳዊ መሣሪያ ነውና፡፡
መዋዕለ ጾሙን በሰላመ ያስፈጽመን
26/2004 ዓ.ም.
• የመብዐ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እየተካሔደ ነው፡፡
በጧፍ፣ በዕጣን፣ በዘቢብና በንዋያተ ቅድሳት እጥረት ምክንያት መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ያቋረጡ ገዳማትና የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን ለመታደግ “የመብዐ ሳምንት” በሚል የተዘጋጀው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተጀመረ፡፡ በገጠር አድባራትና ገዳማት ያለው የመብዐ ችግር አሳሳቢ እንደሆነም ተገለጠ፡፡
ከትናንትና በስትያ የካቲት 24 ቀን 2004 ዓ.ም በተደረገው የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ባስተላለፉት መልእክት “ከዚህ ቀደም ‘ሁለት ልብሶች ያሉት’ በሚል መርሐ ግብር በአብነት ት/ቤቶችና ገዳማት ያለውን የአልባሳት ችግር ለመቅረፍ ምእመናንና የማኅበሩ አባላት እንደተረባረቡ አስታውሰው፣ ኢትዮጵያ ዘወትር ወደ እግዚአብሔር እጆቿን የምትዘረጋባቸው የአባቶቻችን እጆች እንዳይታጠፉ አሁንም መረባረብ አለብን” ብለዋል፡፡
ሊቀ ትጉሃን አያይዘውም፣ እንደ ሌሎች አኃት አብያተ ክርስቲያናት ለወደፊቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በደንቡ አጥንቶት ቤተ ክርስቲያናችን ራሷን አደራጅታ መባዎችን ለእግዚአብሔር እንደሚገባ በጥራት አዘጋጅታ ከሌሎች ጥገኝነት የምትላቀቅበት ጊዜ እስከሚመጣ ለጊዜውም ቢሆን ያለውን ችግር መቅረፍ እንድንችል በተለይ በዚህ የፆምና የጸሎት ሠዓት ከእኛ ብዙ ይጠበቃል በማለት አሳስበዋል፡፡
በክብር እንግድነት ተገኝተው መርሐ ግብሩን በይፋ የከፈቱት ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል “በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ” ሉቃ. 13፥24 በሚል ርዕስ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ከትምህርቱ ጋር አያይዘው ባስተላለፉት መልእክት “መብዐ የክርስትና መነሻ፣ የሙታን ማስቀደሻ፣ የክብረ ቅዱሳን መወደሻ ነው፡፡ ተመስጋኙ እግዚአብሔር አመስጋኙ ሰው ቢሆንም፣ እነዚህ ነገሮች ካልተሟሉ ቅዳሴ የለም፤ ቅዳሴ ከሌለ ደግሞ ሠላም የለም፤ ጠለ በረከትም ይቀራል ማለት ነው፡፡ ከተወደሰ ከተቀደሰ ግን ሰዎች ይሰማሉ፣ ይማራሉ፣ ይጸልያሉ፣ ይፆማሉ፤ እግዚአብሔርም ጠለ በረከቱን ይሰጣል፡፡ በዚህ መንገድም በረከት ይገኛል፡፡ የምትሰጡትንም ለእግዚአብሔር አደራ ስጡ” ብለዋል፡፡
“ከሁሉም ከባዱ የችግሩ አካል ክርስትና ማስነሻ መብዐ አለመኖሩ ነው፡፡” ያሉት ብፁዕነታቸው “በ40 በ80 ቀን ተጠምቆ ሥጋወደሙን በምን ይቀበለው?” በማለት በሀዘን ስሜታችውን ገልጠዋል፡፡
እርሳቸው በሚያስተዳድሩት ሀገረ ስብከት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የገለጡት ብፁዕነታቸው “ከአልባሳት ችግር አንፃር የካህናት ባለቤቶች የነበሩ እናቶች ሲሞቱ ሥጋወደሙ ሲቀበሉበት የነበረውን ቀሚሳቸውን መቀደሻ ይሁንልኝ እያሉ ተናዘው ይሞታሉ፡፡ በእናቶች ቀሚስ ነው የሚቀደሰው፡፡ ለክርስትና ማንሻም አንድ ወይም ሁለት ፍሬ ዘቢብ ታሽቶ ነው የሚቀደሰው፡፡ ይኸውም ከአንዱ ወደ ሌላው አጥቢያ የውሎ መንገድ ተጉዘው የሚያስቀድሱ፣ ክርስትናም የሚያስነሱ ብዙዎች ናቸው፡፡” በማለት መራራውንና አሳዛኙን እውነት አስረድተዋል፡፡
መርሐ ግብሩ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አዘጋጅነት ከየካቲት 24 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2004 ዓ.ም በማኅበሩ ዋና ማዕከል ጽ/ቤት ላይ ይከናወናል፡፡ ምእመናን ከእነዚህ ቀናት በኋላም በክፍሉ ጊዜአዊ እርዳታ አሰባሳቢ አማካኝነት መብዐ ማስገባት እንደሚችሉ ታውቋል፡፡
የካቲት 24/2004 ዓ.ም.
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ በሦስተኛው ቀን በገሊላ አውራጃ በቃና መንደር ከእናቱ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ከአሥራ ሁለት ሐዋርያቱ ጋር በዶኪማስ ቤት ሠርግ ተጠርቶ ነበር፡፡ በዚያም ወይን ጠጅ አልቆባቸው አፍረውና ተሸማቀው የነበሩትን ጋባዦች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ውኃውን የወይን ጠጅ አድርጎ በመቀየር ከዕፍረት አድኗቸዋል፤ ክብሩን በመጀመሪያ ተአምሩ ገልጧል፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አምነዋል፤ዮሐ 2፥1-11፡፡
ጌታችን ከዚህ በኋላ የአይሁድ ፋሲካ ቀርቦ ስለ ነበር የሔደው ወደ ኢየሩሳሌም ነበር፡፡ በዚያ የተመለከተው ነገር ግን በዶኪማስ ሠርግ ቤት ውስጥ ከተመለከተው የአክብሮት ጥሪና መስተንግዶ ጋር ሲነጻጸር ፍጹም ተቃራኒ ነበር፡፡ ጌታ ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ከገባ በኋላ በቀጥታ ያቀናው ወደ ቤተ መቅደስ ነው፡፡
በእኛ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እኛ ከአንዱ ከተማ ተነሥተን ወደ ሌላው ከተማ ስንደርስ ወይም ገና ካለንበት ከተማ ከመነሣታችን በፊት ቅድሚያ ሰጥተን የምናጣራው ወይም የምንጠይቀው ጉዳይ በከተማይቱ ውስጥ ስላለው የተሻለ መኝታ፣ ጥራት ስላለው ምግብና መጠጥ እንዲሁም ተመራጭ ስለ ሆነው ገላ መታጠቢያ ቤት ነው እንጂ በከማይቱ ውስጥ ስላሉት የተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት፣ በዚያ ስለሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት ወይም ስለሚገጥሙአቸው የዲያብሎስ ውጊያዎች አይደለም፡፡ ስለሆነም እኛ ከአንድ ከተማ ተነሥተን ወደ ሌላ ከተማ ስንደርስ አስቀድመን ልንጠይቃቸው ስለሚገቡን አንገብጋቢ ጉዳዮች እንድንጠይቅና ወደዚያ ከተማ እንድንደርስ ያበቃንን አምላክ እናመሰግን ዘንድ በመጀመሪያ መሔድ የሚገባን ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሆኑን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያስተምረን ወደ ቤተ መቅደስ ሔዷል፡፡
የአይሁድ የፋሲካ በዓል አይሁድ በኀጢአታቸው ምክንያት በግብጽ ምድር ለ430 ዓመታት በባርነት በግፍ ሲገዙ ከቆዩ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ እነርሱን በነቢዩ በሙሴ አማካይነት በኀይልና በተለያዩ ተአምራት በማውጣት ይህን የዘላለም መታሰቢያ እንዲሆናቸው አድርጎ የሰጣቸው ታላቅ የመሻገር በዓል ነው፤ ዘጸ 12፡፡ አይሁድ ይህ ታላቅ የእግዚአብሔር በዓል ሊከበር በቀረበበት አጭር ጊዜ ውስጥ ስለ በዓሉ አከባበር እና ሊከናወኑ በሚገባቸው ቅድመ ዝግጅቶች ላይ ባተሌ መሆን ሲገባቸው ለምስጋና፣ ለጸሎት፣ ለተመስጦ፣ ለስግደት፣ መባ ለማቅረብና ለሥርየት በታነጸው ቤተ መቅደስ ውስጥ በሬዎች፣ በጎችና ርግቦች በማስገባትና ከሕዝቡ ጋር ሲነጋገዱበትና ጥቁር ገበያ አድርገው ገንዘብ ሲለዋወጡበት ነበር ኢየሱስ ክርስቶስ ያገኛቸው፡፡ ሊያደርጉ የማይገባቸውን ነገር ሊያደርጉ በማይገባቸው ቦታ ላይ ሲያደርጉ ነው ያገኛቸው፡፡ ምስጋና፣ ጸሎት፣ ተመስጦ፣ ስግደት፣ መባ ማቅረብና ሥርየት ማግኘት ከዋጋ ውጣ ውረድ፣ ከቀንስ አትቀንስ ክርክር፣ ከጫጫታ፣ ከንጥቂያ፣ ከስድብና ከድብድብ ጋር ምንም ዓይነት መስማማት የለውም፡፡ የቤተ መቅደስን ንጽሕና መጠበቅና ቤተ መቅደስን በከብቶች አዛባና ሽንት ማቆሸሽ ፍጹም የማይገናኙ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ጸሎትና ምስጋና በዋጋ ክርክርና በሁካታ መተካቱ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያስቆጣ እኩይ ተግባር ነው፡፡
ዛሬም እንዲሁ ነው፡፡ አንዳንዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመጡ በኋላ ስለ ንግድና ስለ ገንዘብ ልውውጥ እንዲሁም ገንዘብ ስለሚገኝበት ሁኔታ መከራከራቸውና መንጫጫታቸው ከአይሁድ ክርክርና ጫጫታ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ዛሬ ምስጋና ለማቅረብ፣ ጾም ለመያዝ፣ ስግደት ለመስገድ፣ በተመስጦ ለመቆየት፣ መባ ለማቅረብና ኀጢአትን ለንስሓ አባት በመናዘዝ ሥርየት ለማግኘት ክርስቲያን ተብለው የተጠሩ አማኞች እግዚአብሔርን ለማገልገል ይህን ያህል ገንዘብ ክፈሉን፣ የላመና የጣመ ምግብና መጠጥ አቅርቡልን፣ የተደላደለ መኝታ አንጥፉልን፤ድምፃችንን እጅግ አጉልታችሁ አሰሙልን፤ይህን ካላደረጋችሁልን ወይም ይህን ካልከፈላችሁን አናገለግልም እያሉ ሲታበዩ ማየትና መስማት የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡ አልፎ ተርፎ በቤተ መቅደስና በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በነገር ቀንስ-አትቀንስ ሁካታና ጫጫታ ለመደራደር መሞከር ከአይሁድ ተግባር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ የኢየሱስ ክርስቶስን የቁጣ ጅራፍ የሚያስነሣ ተግባር ነው፤በማይገባው ቦታ ላይ የሚፈጸም የማይገባ ተግባር ነውና፡፡
ባቀረበው ምስጋና፣ ባደረሰው ጸሎት፣ በሰገደው ስግደት፣ በጾመው ጾም፣ በያዘው ንስሓና በሰጠው መባ ተባርኮ፣ ተቀድሶና ሥርየት አግኝቶ በደስታ ወደ ቤቱ መመለስ የሚገባው ምእመን ገንዘብ የሚገኝበትን ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የገንዘብ መድረክ ስለሚገኝበት ሁኔታ ወይም የእግዚአብሔርን ቤት የንግድና የኑፋቄ ቤት ለማድረግ በመሞከር ተከራክሮና ተንጫጭቶ፤ተጣልቶና ተኮራርፎ መለያይት የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ አይሁድ በቤቱ ውስጥ ለፈጸሙት እኩይ ተግባር በንስሓ ተመልሰው ጌታን ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ ጭራሽ ለደረሰባቸው ቅጣት እርሱን ምልክት መጠየቃቸው አሳዛኝም አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን በጥምቀት ልጅነትን፣ በሜሮን መታተምን፣ በንስሓ ሥርየትን፣ በእምነት መንግሥተ ሰማያትን ያሰጠችና የምታሰጥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የንግድ ቤት ለማድረግ ሞክረው ያልተሳካላቸው ሰዎች ከጥፋት በፊት ይቅርታ እንዲጠይቁ ታሳስባለች፡፡
ይህ ስለሆነ ነው የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቁጣ በእነዚህ ሰዎች ላይ እጅግ የነደደው፡፡ ከዚህ በኋላ ጅራፍ አበጅቶ ይሻሻጡና ይለዋወጡ የነበሩትን ሰዎችና የሚሸጡትን በሬዎች፣ በጎችና ርግቦች እየገረፈ ከቤቱ ካስወጣ በኋላ የለዋጮችን ገበታዎች ገለባብጦባቸዋል፤ የሚለዋወጡባቸውን ገንዘቦችም በታትኖባቸዋል፡፡ ይህን ከማድረጉ በፊት ግን «የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት፡፡» በማለት ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቶአቸዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በከፍተኛ ቅንዓት ይህን ሁሉ ነገር ሲያከናውን አብረውት የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ያሰላስሉና ያስቡ የነበረው አባታቸው ቅዱስ ዳዊት ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅንዓት በትንቢት መነጽር የተመለከተው ትንቢት መፈጸሙን ነበር፡- «. . . ቤትህ ቅንዓት ይበላኛል፤» (መዝ 68፡9) የሚለው፡፡ ከዚህ በኋላ እነዚህ እኩያን አይሁድ ያደረገውን ነገር በምን ሥልጣን እንደሚያደርግ ይህን ለማድረጉም ምን ዐይነት ምልክት ሊሰጣቸው እንደሚችል ሲጠይቁት «ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስት ቀንም አፈርሰዋለሁ . . .» (ዮሐ 2፡19) በማለት ለእነርሱ ያልገባቸውን ነገር ስለ ገዛ ራሱ ሞትና ስለ ትንሣኤው በቤተ መቅደሱ መስሎ ነግሯቸዋል፡፡ ይህን አባባሉንም አብረውት የነበሩት ሐዋርያቱ ጌታ ከሙታን መካከል ከተነሣ በኋላ በመጽሐፍ የተጻፈውንና ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገውን ነገር በማሰብ በእርሱ አምነዋል፡፡ አይሁድ ግን ያደረጉት ክፉ ሥራ ሳያንሳቸው ለምልክት ጥየቃ ተመልሰው ወደ እርሱ በመምጣታቸው ለጥፋት ተዳርገዋል፡፡
አንድም ቤተ መቅደስ ተብሎ የተጠራው ይህ የእኛ ሰውነት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሁኔታ በመልእክቱ መላልሶና አስረግጦ ገልጦታል፡- «የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፤ ያውም እናንተ ናችሁ፡፡» 1ኛ ቆሮ. 3፥16-17፤1ኛ ቆሮ. 6፥19-20፡፡ ሰው የራሱ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚኖረውና ሊኖር የሚገባው ደግሞ እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚኖረውም እኛን በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ወይም በዋጋ ስለ ገዛንና መልሶ የራሱ ስላደረገን ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ በላይ እኛን በመልኩና በምሳሌው የፈጠረን በእኛ ውስጥ ስለሚያድርና እኛን ቤተ መቅደሱ ስላደረገን ነው፡፡ ይህ በመሆኑም እኛም ይህን አክበሮ፣ ባርኮና ቀድሶ የሰጠንን ቤተ መቅደስ ያለ ምንም ዕድፈትና ቆሻሻ በቅድስናና በንጽሕና ልንጠብቀው ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይሁድ እንዳደረጉት በከብቶች አዛባና ሽንት ሊቆሽሽ አይገባውም፡፡ አዛባና ሽንት የተባለው ኀጢአትና በደል ነው፡፡ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖት ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ ምቀኝነት. . . ወዘተ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይኸውም እኛን የሚያቆሽሽ አዛባ ነው፡፡
እግዚአብሔር ደግሞ በቆሸሸ ቤት ውስጥ አይኖርም፡፡ የምንኖርበት ምድራዊ ቤት በተለያዩ ምክንያቶች ሲቆሽሽ ደስ እንደማይለን ሁሉ እኛም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ (ራሳችንን) ስናቆሽሽ እግዚአብሔርን እንደማናስደስተው በማወቅ በንስሓ ልናጸዳው ይገባናል፡፡ እኛ ይህን ሰውነታችንን ወይም ይህን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በተለያዩ የኀጢአት ዐይነቶች የምናፈርሰው ከሆነ እግዚአብሔር ደግሞ አፍራሾቹን እኛን ያፈርሰናል፡፡ ዛሬ ብዙዎች የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ወይም ሰውነታቸውን በተለያዩ ክፉ ቅጠሎች ማለትም በትንምባሆ፣ በሺሻና በጫት እያፈረሱት ነው፡፡ ከልክ ባለፈ መጠጥና በዝሙትም እያፈረሱት ነው፡፡ በሀሜትና በአሉባልታም እያፈረሱት ነው፡፡ በሐሰትና በስርቆትም እያፈረሱት ነው፡፡ እጅግ ብዙ የሚታገሥ እግዚአብሔር ደግሞ በንስሓ ካልተመለሱ እነርሱን አንድ ቀን ያፈርሳቸዋል፡፡ እርሱ ዛሬ ለአይሁድ ያነሳውን የገመድ ጅራፍ በእኛ ላይ በድጋሚ ለማንሣት ድጋሚ ይወለድ ዘንድ አይመጣም፤ በፍርድ ቀን በእሳት ጅራፍ ለመግረፍ እንጂ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ብዙዎች የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስን በተለያየ ምክንያት ሲያፈርሱ ለሚመለከት ሰው መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ «ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን?» (1ኛ ቆሮ 6፡19) በማለት በጻፈው የተግሣፅ ቃል ላይ በተመስጦ እንዲቆይ ያደርገውና በሰዎች አለማወቅ እንዲያዝንም ሆነ እንዲያለቅስ ያደርገዋል፡፡ «አታውቁምን?» የሚለው ቃል የእኛን አለማወቅ ያጎላብኛል፡፡ ይኸው ሐዋርያ «አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤. . .» (1ኛ ቆሮ 2፡8) በማለት ተናግሯል፡፡ ይህ ኀይለ ቃል ለአይሁድ ብቻ የተነገረ የሚመስለን ከሆነ ዛሬም እኛ አላወቅንም ማለት ነው፡፡ እነርሱ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሰቀሉት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ብዙዎቻችን ግን ኀጢአት በሠራን ቁጥር በሥራችን ብዙ ጊዜ መላልሰን እየሰቀልነው ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ብዛት ያላቸው የኀጢአት ሥራዎችን ሲሠሩ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነ ሰውነታቸው እየሰቀሉትና እያፈረሱት መሆናቸውን በትክክል ቢያውቁ ኖሮ ከዚህ ክፉ ሥራቸው በታቀቡ ነበር፡፡ ባለማወቃቸው ግን የራሳቸውን፣ የሌሎችንና የእግዚአብሔርን አብያተ መቅደሰ እያፈረሱ ነው፤ በማፍረሳቸውም እግዚአብሔር እነርሱን እያፈረሳቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የምንታነጽ እንጂ የምንፈርስ ከመሆን ያድነን፡፡ የአምላካችን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይሁን፤አሜን፡፡
ይቆየን፡፡
በጎውን ሁሉ ለእኛ ያደረገና የሚያደርግ እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤አሜን፡፡
የካቲት 22/2004 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሙቀት መጨመርን ለመቀነስ ያሏት ብዝኀ ሕይወት አስተዋጽኦቸው ከፍተኛ መሆኑን በማኅበረ ቅዱሳን ሙያ አገልግሎትና አቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል ሓላፊ ዶ/ር ሳሙኤል ኀይለ ማርያም አስታወቁ፡፡
ሓላፊው እንደገለጹት ማኅበረ ቅዱሳን በእቅድ ሊሠራቸው ካቀዳቸው መካከል የብዝኀ ሕይወት ጥበቃ በታላቁ ደብረ ሊባኖስ ገዳም እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ገዳማትና አድባራት ያሏት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሳሙኤል የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ለጥናት መመረጡ ለጥናቱ መከናወን አመቺነት ካለው የቦታ ቅርበትና ከገዳሙ የብዝኀ ሕይወት ይዘትና ጥራት አንጻር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በደብረ ሊባኖስ ገዳም በጀመረው በዚህ ጥናት ላይ የግብርና ባለሞያዎች፣ የግብርና ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች እና በካርበን ልቀት ዙሪያ ልምድና ምርምር ያደርጉ ባለሞያዎች ያሉት ቡድን አቋቁሟል፡፡ ቡድኑ ከገዳሙ አመራር አካላትና ከማኅበረ ቅዱሳን ፍቼ ማእከል ጋር በመሆን ጥናቱን እያከናወነ መሆኑን ዶ/ር ሳሙኤል ጠቅሰው በጥናቱ ውጤትም ላይ መሠረት ያደረገ ፕሮጀክት በገዳሙ ላይ የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጥናቱም የገዳሙን የብዝኀ ሕይወት ያለበትን ደረጃ እንዲሁም በብዝኀ ሕይወቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያደርሱትን ነገሮች መለየት፣ የዚህ ጥናት በመነሣት በቀጣይ መሠራት የሚገባቸውን ጉዳዮች ጭምር መሠረት ያደረገ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
የደብረ ሊባኖስ ገዳም የብዝኀ ሕይወት ጥናት ቡድን ፕሮጀክቱን ሲተገብር የገዳሙ የአካባቢ ልማት እቅድ የሚወጣለት ሲሆን በገዳሙ ያሉት ብዝኀ ሕይወት ያለባቸው ቦታዎች ተለይተው ልዩ እንክብካቤ የሚደረግላቸው ይሆናል፡፡ የገዳሙም አኗኗር ብዝኀ ሕይወቱን ከመጠበቅ አንጻር መሆኑን ነው የተገለጸው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ለብዝኀ ሕይወት ጥበቃ ከመቼውም በላይ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሞያዎችና መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በጥምረት ይሠራል ያሉት ዶ/ር ሳሙኤል ገልጸው ተፈጥሮአዊ ነገሮችን መንከባከብም ሆነ መጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታም መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የብዝኀ ሕይወት ጥናት በአሁን ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት እያገኘ ሲሆን በዓለማችን በየጊዜው በሚፈጠረው የሙቀት መጠን መጨመር ምክንያት ዓለማችንን አስጊ ደረጃ እያደረሳት ይገኛል፡፡
የካቲት 22/2004 ዓ.ም.
በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል ከጥናትና ምርምር ማእከል ባለሙያ ምሑራን ጋር የምክክር መድረክ መርሐ ግብር እንደሚያካሔድ አስታወቀ፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ዳሬክተርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአርኪዮሎጂና ቅርስ አስተዳደር መምህር የሆኑት ዲ/ን መንግሥቱ ጎበዜ እንደገለጹት ምሁራን ለቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን፤ ለምሑራን ያላቸውን ተወራራሽ ጠቀሜታ በማጉላት፣ የምሑራንንም ፋይዳ ከቤተ ክርስቲያን ያገኙትንም ለመግለጽ ዐቢይ መርሐ ግብር መሆኑ ገልጸዋል፡፡ ይህ የውይይት መድረክ ለጥናትና ምርምር ማእከሉ አገልግሎቱን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ የሌሎች ምሁራንን ድጋፍ ለማግኘትና ምሑራንም የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንዲያግዙ ለማነቃቃት ያግዛል፡፡ ምሑራኑም የጥናት ጽሑፎቻቸውን በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እንዲያደርጉ ከማገዝም በላይ ቤተ ክርስቲያንም ትልቅ የመረጃ ምንጭ በመሆን ለጥናታቸው ውጤታማነት ፋይዳዋ ታላቅ መሆኑን የሚረዱበት ይሆናል ብለዋል፡፡
በዚህ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች መርሐ ግብር ላይ የዘርፉ ባለሞያዎች የሚገኙ ሲሆን መርሐ ግብሩም በአዲስ አበባ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም እንደሚካሔድ ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የጥናትና ምርምር ማእከሉ የካቲት 24 ቀን 2004 ዓ.ም በብሔራዊ ሙዚየም “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን፣ ሀገርና የሀገር ሉዓላዊነት” በሚል ርዕስ ጥናት እንደሚቀርብ ገልጻôል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለአድዋ ድል መገኘት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ድርሻ በመሆኑ በዓሉን ጥናታዊ ጽሑፍ እየቀረበ በየዓመቱ እንዲከበር በተሳታፊዎች የተሰጠ ጥቆማ ስለነበር የአድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግና ለሀገር አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ሚና ማጉላት ዓላማ ያለው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቅዳሜ የካቲት 24 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ በብሔራዊ ሙዚየም የሚቀርበው “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን፣ ሀገርና የሀገር ሉዓላዊነት” ርዕስ በዋናነት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሀገርን ሉዓላዊነት በመጠበቅ አንጻር ምእመኗን አስተባብራ ድል ያስገኘች መሆኗ እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከባሕል ወረራ ሀገርን የመከላከል ያላት አስተዋጽኦ ለማስገንዘብ የሚያስችል መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸው በብሔራዊ ሙዚየም በሚደረገው መርሐ ግብር ሁላችሁም ተጋብዛችኋል በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የካቲት 21/2004 ዓ.ም.
የጥንታዊው አሰቦት ገዳም ደን ዳግም የእሳት አደጋ ቃጠሎ ደረሰበት፡፡
የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴና አባ ሳሙኤል ገዳም ደን ትላንት የካቲት 20 ቀን 2004 ዓ.ም. ባልታወቀ ምክንያት በተነሣ እሳት ቃጠሎ ደረሰበት፡፡
ትላንት ከቀኑ 5፡00 ሰዓት የተነሣው እሳት እስከአሁን ድረስ ያልጠፋ መሆኑንን የገለጹት የገዳሙ አገልጋይ አባ ወልዴ እንዳሉት እሳቱ እየተስፋፋ ከደኑ አልፎ ወደ ቅድስት ሥላሴ የአባቶች ገዳም እየተቃረበ መሆኑንን ገልጸዋል፡፡
እሳቱን ለማጥፋት የአካባቢው ገበሬ ማኅበር ጥረት እያደረገ ቢሆንም ከውኃ እጥረትና ከሰው ኀይል ማነስ የተነሣ ይህ ዜና እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ እሳቱ አለመጥፋቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዝርዝርሩን እንደደረሰን እናሳውቃለን፡፡