ፍረጃና መዘዙ
ፍረጃ አንድን አካል ወይም ሰው ማንነቱን የማይገልጠው ስም፣ እውነታን ባላገናዘበ መልኩ ግላዊና ማኅበረሰባዊ በሆነ መንገድ ለሰዎች ስያሜ መስጠት ፣ ከአንድ ጉዳይ ተነሥቶ ሁሉን መጥላትና ማንቋሸሽ ነው፡፡ ፍረጃውን የሚያደርጉ ሰዎችም ፍረጃውን መሠረት አድርገው በክፉ የፈረጁት ግለሰብ ወይም ቡድን አንዳች ቅጣት እንዲደርስበት ስለሚፈልጉ ለዚያ ፍረጃና ቅጣት ምስክር አድርገው የሚያቀርቡት እውነታን ሳይሆን የራሳቸውን ትርክት ነው፡፡ ፍረጃ ሰዎችን ለማግለልና ለመነጠልም እንደ መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግልና በቀላሉ የማይነቀልም ሂደት/ቀጣይነት ያለው ነው፡፡ ፍረጃውን ለሚያደርጉ ሰዎችና ፍረጃቸውንም ለሚቀበሉ ሰዎች በፈረጇቸው ሰዎች ላይ ከሕግና ከሥርዓት ወጥተው የራሳቸውን ፍርድ በመስጠት ከድብደባ እስከ ግድያ የሚደርስ ወንጀል እንዲፈጽሙ ያደርጋቸዋል፡፡