ስለ ቅዱስ ፖትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር መግለጫ ተሰጠ

ሐሴ 12 ቀን 2004 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

መካነ ድራችን  በግልጥ ባልታወቀ ምክንያት የሲስተም ችግር ገጥሞት ስለነበር መረጃዎችን በወቅቱ ማድረስ ባለመቻላችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፖትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ሥርዓተ ቀብር በማስመልከት ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጠ፡፡

 

መግለጫውን የሰጡት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ዋና ጸሓፊ፣ የከፋ ቤንችና ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑabune paulose በመግለጫቸውም “ቅዱስነታቸው ሐሙስ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ መለየታቸውን በዕለቱ መግለጻችን ይታወቃል፡፡ በቀጣይነትም የቅዱስነታቸውን የቀብር ሥነ ሥርዓት አፈጻጸም ጊዜና ቦታ በተከታታይ የሚገለጽ መሆኑን በሰጠነው ማሳሰቢያ መሠረት የቀብር ሥነሥርዓቱ ሐሙስ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ እስከዚያው ድረስ ምእመናንና ምእመናት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመገኘት ሃዘናቸውን መግለጽ የሚችሉ መሆኑን እንገልጻለን” ብለዋል፡፡

 

ስለ አሟሟታቸው ማብራሪያ እንዲሰጡ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ቅዱስነታቸው ሱባኤውን ሳያቋርጡ እሑድ ቀድሰው ሰኞና ማክሰኞም ቅዳሴውን እየመሩ መገኘታቸውንና ከሰዓት በኋላ ህመም ስለተሰማቸወ ወደ ሕክምና መሔዳቸውን የገለጹ ሲሆን እረፍት እንዲያደርጉ በሐኪም ከተነገራቸው በኋላ በዚያው የእግዚአብሔር ጥሪ ሆኖ ሌሊት 11፡00 ሰዓት ላይ ማረፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ስለ ቅዱስነታቸው ሕመም ሲያብራሩ “ብዙ ታመው ቤት አልዋሉም፡፡ ሥራም አላቋረጡም፣ ያልታሰበ ነገር ስለነበር በሞታቸው በጣም ተደናግጠናል፡፡ ሕመማቸው የስኳር ሕመም ጠንቅ ነው፡፡ ቀዶ ጥገናም አልተደገላቸውም በትናንትናው ዕለት እኔ ነኝ አጥቤ የገነዝኳቸው፡፡” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያኑ ቀኖና እንደሚያዘው አንድ ፖትርያርክ ሲያርፍ አቃቤ መንበር በዕለቱ መሠየም እንዳለበት ይገልጻልና ይህ ለምን ተፈጻሚ አልሆነም? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በፓትርያርኩ ጽ/ቤት ሓላፊ እንዲሁም በቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ አማካይነት ሥራዎች እንደሚከናወኑ፣ ከቅዱስ ፖትርያርኩ የቀብር ሥነ ሥርዓት በኋላ አቃቤ መንበር እንደሚሰይምና ይህም በመመካከርና በመስማማት ውሳኔውን መወሰናቸውን አብራርተዋል፡፡

 

ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያኑን ለመምራት ምን ያህል ዝግጁ ነው? ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱም “ይህ ጸሎት የሚጠይቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር abune paulosእየረዳን፣ በምዕመናን ጸሎት እየተረዳን የተቻለንን ሁሉ እንጥራለን፡፡” ያሉ ሲሆን ከሰሜን አሜሪካ ካሉ አባቶች ጋር እየተካሄደ የነበረው እርቀ ሰላም እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

 

የቅዱስነታቸው የቀብር ቦታን አስመልክቶ እንዳልተናዘዙና በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ከልጅነታቸው ጀምሮ በቅስና እያሉ ባገለገሉበት፣ በተማሩበት፣ ከእስር ቤት ከተፈቱ በኋላ ክብር ባገኙበት በመንብረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲሆን ተወስኗል” ብለዋል፡፡

 

የቅዱስ ፖትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር ዝርዝር መረጃም እንደሚከተለው ሰጥተዋል፡፡

  • ረቡዕ ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ የቅዱስነታቸው አስከሬን ከመንበረ ፓትርያርክ በግልጽ ሠረገላ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያመራል፡፡
  • ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ ጸሎተ ፍትሀት እየተከናወነ ያድራል፡፡
  • ሌሊት ሥርዓተ ቅዳሴ በሦስቱም መንበር በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ይቀደሳል፡፡
  • ከሥርዓተ ቅዳሴ በኋላ አስከሬናቸው ወደ ዐውደ ምሕረት በማውጣት ምዕመናን በተገኙበት ጸሎተ ፍትሀቱ ይቀጥላል፡፡
  • ከውጭ ሀገር የመጡ የአኀት ቤተ ክርስቲያናት ፖትርያርኮች ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ፡፡
  • የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ንግግር ያደርጋሉ፡፡
  • የቅዱስነታቸው የሕይወት ታሪክ በቅዱስ ሲኖዶስ በተፈቀደላቸው ሊቀ ጳጳስ ይነበባል፡፡
  • አስከሬናቸው በቤተ ክርስቲያኑ ዑደት ያደርጋል፡፡
  • በመጨረሻም ሥርዓተ ቀብራቸው ይፈጸማል፡፡