በሶዲቾ ዋሻ የእመቤታችን ጽላት በአገር ሽማግሌዎች እየተጠበቀ ነው

 

 

 መስከረም 9ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በከምባታ ጠምባሮ ዞን ልዩ ስሙ ሶዲቾ ዋሻ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ በ984 ዓ.ም. የነበረ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጽላት በአገር ሽማግሌዎች እየተጠበቀ ነው፡፡

 

በግንቦት ወር ላይ ቆሞስ አባ ኤልያስ የተባሉ አባት ወደ ሶዲቾ ዋሻ በመምጣት ከሚመለከታቸው የቤተክርስቲያንና የዞኑ የመንግስት አካላት ፈቃድ በማግኘት ከዋሻው ውስጥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግልማርያም ጽላት፤ የአንድ አባት አጽምና የእጅ መስቀል በቁፋሮ ማውጣታቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በሥፍራው በሚከናውነው የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ብዙዎች በጸበል እየተፈወሱ ሲሆን ኢ- አማንያንም ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡ ይህ ያሳሰባቸው አንዳንድ ግለሰቦች በቡድን በመደራጀት በቦታው ላይ የሚገኙትን አባት ቆሞስ አባ ኤልያስን ከአካባቢው እንዲለቁ በማስገደድ፤ በማስፈራራትና ድንጋይ በመወርወር ደብድበው ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸው የሚታወስ ነው፡፡ በርካታ ጸበል ሊጠመቁ የመጡ ምእመናንም በድንጋይ ድብደባ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የወረዳውና የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች ከምእመናን ጋር በመሆን ለሚመለከተው የወረዳ፤ ብሎም የዞኑ መንግስት ባለሥልጣናት ድረስ ጉዳዩን በመውሰድ እልባት እንዲያገኝ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ከወረዳው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ነገር ግን የወረዳው ካቢኔ በዋሻው ውስጥ የሚገኘውን ጽላት አቅራቢያው ወደሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ወስዳችሁ እንድታስገቡ፤ ቦታውንም እንድትለቁ በማለት መስከረም 3 ቀን 2005 ዓ.ም. የመጨረሻ የቀን ገደብ አስቀምጦ እንደነበር የወረዳው ቤተ ክህነት ሓላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ በዞን ደረጃ እንዲታይ ቢደረግም መፍትሔ ማግኘት ባለመቻሉ ወደ ክልል በመሔድ አቤቱታ በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡

 

ጽላቱን ያገኙት አባት ቆሞስ አባ ኤልያስ ማንንም እንዳያጠምቁ፤ እንዳያስተምሩ፤ የማዕጠንትም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንዳያከናውኑ ተከልክለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ቆሞስ አባ ኤልያስ ከዋሻው በመውጣት ወዳልታወቀ ሥፍራ በመሔድ ሱባኤ እንደገቡ የሚነገር ሲሆን ጽላቱ በአካባቢው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ በሆኑ የአገር ሽማግሌዎች ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑን የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ አባ ኃይለ ሚካኤል ገልጸዋል፡፡

 

 

5ኛው ሀገር አቀፍ ዓመታዊ ዐውደ ጥናት ተካሔደ

 

መስከረም 3 ቀን 2006 ዓ.ም.

 
በእንዳለ ደምስስ

tena 3በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው 5ኛው ሀገረ አቀፍ ዓመታዊ ዐውደ ጥናት “ጥናትና ምርምር ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ መጠናከር” በሚል ጳጉሜ 2 እና 3 ቀን 2005 ዓ.ም. በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ተካሄደ፡፡

በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “እግዚአብሔር ሲፈቅድ ልጆቹን ለመልካም ነገር ያውላቸዋል፡፡ የዚህ ጉባኤ ዓላማም ለመልካም ሥራ ነው፡፡ መልካም ሰዎች ለመልካም ነገር ይውላሉና፡፡ ሰው ሰውን አፍቃሪ፤ ረጂ፤ ለሀገሩም ለእግዚአብሔር የተመቸ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የዘመኑ የፈጠራ ትምህርት ከመንፈሳዊ ትምህርት ጋር በተያያዘ መመራመርን ይጠይቃል፡፡ ሰው ካወቀ ለሌላው ያሳውቃል፤ ለሌላው ያስረዳል፤ መልካም መሳሪያም ይሆናል፡፡ ይህ የተጀመረው ምርምርና ጥናት እኛንም የበለጠ ያፋቅረናል፤ በሃይማኖት እንድንቆም፤ የበለጠም እንድንሠራ ያደርገናል፡፡ የተሸሸገውን ታሪካችንን፤ያሳውቀናል፤ ልጆቻችንንም ተረካቢ ያደርጋቸዋል፡፡ ጥሩ ጅምር በመሆኑ በዚሁ እንድንቀጥል ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው ዐውደ ጥናት ስምንት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል “ጥንታዊ ቅርሶችን ከመጠበቅና ከማሰባሰብ አንጻር የካህናት ሚና” በፕሮፌሰር አየለ በክሪ በመቀሌtena 3 2 ዩኒቨርስቲ የታሪክና ባህል ጥናት መምህር፤ “ልማትና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በአቶ ፀጋዬ አስገለ እና በመምህር ካኽሳዬ ገብረ እግዚአብሔር፤ “ሥርዓተ ፆታና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በወ/ሮ ሐረገወይን ቸርነት በፐብሊክ ሣይንስና ምግብ ዋስትና የሥርዓተ ፆታ አማካሪ፤ “የሕይወት ምህንድስና፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በአቶ ኃይለ ማርያም ላቀው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤሌክትሪካል ኢንጂነር ቅዳሜ ጳጉሜ 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በዐውደ ጥናቱ ላይ የቀረቡ አራት ጥናታዊ ጽሑፎች ናቸው፡፡

እሑድ በተካሄደው ቀጣይ ዐውደ ጥናትም አራት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ “የበዓላት አከባበር፤ ቱሪዝምና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በአቶ ባንታለም ታደሰ በጎንደር ዩኒቨርቲ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር፤ “የሃይማኖት ቱሪዝም ልማት ተግዳሮት እና ትንበያ” በአቶ ኤርሚያስ ክፍሌ በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ወንዶ ገነት ስኩል ኦፍ ዋይልድ ላይፍ እና ቱሪዝም መምህር፤ “ሳይንስና ሃይማኖት እንዴት ይለያያሉ” በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ መምህር፤ “ሃይማኖታዊ እሳቤዎች በሳይንስ እይታ” በዶክተር አብርሃም አምኃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው ዐውደ ጥናት ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በጥናት አቅራቢዎች ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ሰፊ ውይይትም ተካሂዶባቸዋል፡፡ ዐውደ ጥናቱ ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት የቀጥታ ስርጭት ሽፋን የነበረው ሲሆን በርካታ በተለያዩ አህጉራት የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ተከታትለውታል፡፡ ጥያቄዎቻቸውንም በማቅረብ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠርና አጠቃቀሙ

ዲ/ን ኃ/ኢየሱስ ቢያ

የዘመን አቆጣጠር ማለት፡- ዓመታትን፤ ወራትን፣ ሳምንታትን፣ ዕለታትን፤ ደቂቃንና ድቁቅ ሰዓታትን በየሥፍራቸው የሚገልጽ፤ የሚተነትን፤ የሚለካ የቤተ ክርስቲያን የቁጥር ትምህርት ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ተመርምረው ተመዝነው ተቆጥረው ሲያበቁ ምድብና ቀመር ተሰጥቶአቸው የሚገኙበትን ውሳኔና ድንጋጌ የሚያሰማ የዘመን አቆጣጠር ሐሳበ ዘመን ይባላል፡፡
ዓመታታ፣ ወራት፣ ሳምንታት፣ ዕለታትና ሰዓታት የሚለኩት /የሚቆጠሩት በሰባቱ መሰፈሪያና በሰባቱ አዕዋዳት ነው፤ እነሱም፡-
1.    ሰባቱ መስፈርታት
–    ሳድሲት
–    ኃምሲት
–    ራብዒት
–    ሣልሲት
–    ካልዒት
–    ኬክሮስ
–    ዕለት ይባላሉ
2.    ሰባቱ አዕዋዳት
–    ዐውደ ዕለት፡- ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያሉት ሰባቱ ዕለታት ናቸው፤ አውራህን ለማስገኘት በዚህ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
–    ዐውደ ወርኅ፡- በፀሐይ 30 ዕለታት በጨረቃ 29/30 ዕለታት ናቸው ዓመታትን ለማስገኘት በዚህ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
–    ዐውደ ዓመት፡- በፀሐይ ቀን አቆጣጠር 365 ቀን ከ15 ኬክሮስ፡፡ በጨረቃ ቀን አቆጣጠር 354 ቀን ከ22 ኬኬሮስ ነው፡፡ እነዚህ 3ቱ በዕለት ሲቆጠሩ አራቱ በዓመት ይቆጠራሉ፡፡ ዘመናትን ለማስገኘት በዚህ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
–    ዐውደ ፀሐይ፡- 28 ዓመት ነው በዚህ ዕለትና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፡፡
–    ዐውደ አበቅቴ፡- 19 ዓመት ነው በዚህ ፀሐይና ጨረቃ ይገናኙበታል፡፡
–    ዐውደ ማኅተም፡- 76 ዓመት ነው በዚህ አበቅቴና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፡፡
–    ዐውደ ቀመር፡- 532 ዓመት ነው በዚህ ዕለትና ወንጌላዊ አበቅቴም ይገናኙበታል፡፡
የዘመናት/የጊዜያት ክፍልና መጠን
1 ዓመት በፀሐይ 365 ቀን ከ15 ኬክሮስ፣ በጨረቃ 354 ቀን ከ22 ኬኬሮስ ነው፡፡ 1 ወር በፀሐይ 30 ዕለታት አሉት በጨረቃ 29/30 ዕለታት አሉት፡፡ ዕለት 24 ሰዓት ነው፤ ቀን 12 ሰዓት ነው ፤ ሰዓት 60 ደቂቃ ነው ፤ ደቂቃ 60 ካልዒት ነው ፤ካልዒት 1 ቅጽበት ነው፡፡ ኬክሮስ ማለት የክፍል ዕለት ሳምንት ነው /የዕለት 1/60ኛው ወይም 1/24ኛ ሰዓት ነው/ 1 ዕለት 24 ሰዓት ወይም 60 ኬክሮስ ማለት ነው፡፡
ክፍለ ዓመት /የዓመት ክፍሎች/
1.    መፀው፡- ከመስከረም 26 እስከ ታኅሳስ 25 ቀናት ድረስ ያለው ክፍለ ዓመት መጸው ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ዓመት ሌሊቱ ረጅም ቀኑ አጭር ነው፡፡
2.    በጋ፡- ከታኅሳስ 26 እስከ መጋቢት 25 ቀናት ድረስ ያለው ክፍለ ዓመት በጋ ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ዓመት የቀኑና የሌሊቱ ርዝመት እኩል ነው፡፡
3.    ፀደይ፡- ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25 ቀናት ድረስ ያለው ፀደይ ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ዓመት ቀኑ ይረዝማል ሌሊቱ ያጥራል፡፡
4.    ክረምት፡- ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 ቀናት ድረስ ያለው ክረምት ይባላል፡፡ በዚህ ከፍለ ዓመት የቀኑና የሌሊቱ ርዝመት እኩል ነው፡፡
በአራቱ ወንጌላውያን መካከል የዘመናት አከፋፈል /ርክክብ/
1.    ማቴዎስ ዘመኑን ከምሽቱ በ 1ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከሌሊቱ በ6 ሰዓት ይፈጽማል፡፡
2.    ማርቆስ ዘመኑን ከሌሊቱ በሰባት ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከጠዋቱ በ12 ሰዓት ይፈጽማል፡፡
3.    ሉቃስ ዘመኑን ከጠዋቱ በ1 ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ በቀትር በ6 ሰዓት ይፈጽማል፡፡
4.    ዮሐንስ ዘመኑን ከቀኑ በሰባት ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከቀትር በኋላ በ12 ሰዓት ይፈጽማል፡፡

የየወራቱ ሌሊትና ቀን ስፍረ ሰዓት
1.    የመስከረም ወር ሌሊቱ 12 ሰዓት መዐልቱ 12 ሰዓት ነው፡፡
2.    የጥቅምት ወር ሌሊቱ 13 ሰዓት መዐልቱ 11 ሰዓት ነው፡፡
3.    የኅዳር ወር ሌሊቱ 14 ሰዓት መዐልቱ 10 ሰዓት ነው፡፡
4.    የታኅሣሥ ወር ሌሊቱ 15 ሰዓት መዐልቱ 9 ሰዓት ነው፡፡
5.    የጥር ወር ሌሊቱ 14 ሰዓት መዐልቱ 10 ሰዓት ነው፡፡
6.    የየካቲት  ወር ሌሊቱ 13 ሰዓት መዐልቱ 11 ሰዓት ነው፡፡
7.    የመጋቢት ወር ሌሊቱ 12 ሰዓት መዐልቱ 12 ሰዓት ነው፡፡
8.    የሚያዝያ ወር ሌሊቱ 11 ሰዓት መዐልቱ 13 ሰዓት ነው፡፡
9.    የግንቦት ወር ሌሊቱ 10 ሰዓት መዐልቱ 14 ሰዓት ነው፡፡
10.    የሰኔ ወር ሌሊቱ 19 ሰዓት መዐልቱ 15 ሰዓት ነው፡፡
11.    የሐምሌ ወር ሌሊቱ 10 ሰዓት መዐልቱ 14 ሰዓት ነው፡፡
12.    የነሐሴ ወር ሌሊቱ 11 ሰዓት መዐልቱ 13 ሰዓት ነው፡፡
የበዓላትና የአጽዋማት ኢየዐርግና ኢይወረድ
1.    ጾመ ነነዌ ከጥር 17 ቀን በታች ከየካቲት 21 ቀን በላይ አይውልም
2.    ዐቢይ ጾም ከየካቲት 1 ቀን በታች ከመጋቢት 5 ቀን በላይ አይውልም
3.    ደብረ ዘይት ከየካቲት 28 ቀን በታች ከሚያዝያ 2 ቀን በላይ አይውልም፡፡
4.    በዓለ ሆሣዕና ከመጋቢት 19 ቀን በታች ከሚያዝያ 23 ቀን በላይ አይውልም፡፡
5.    በዓለ ስቅለት ከመጋቢት 24 ቀን በታች ከሚያዝያ 28 ቀን በላይ አይውልም፡፡
6.    በዓለ ትንሣኤ ከመጋቢት 26 ቀን በታች ከሚያዝያ 3ዐ ቀን በላይ አይውልም፡፡
7.    ርክበ ካህናት ከሚያዝያ 20 ቀን በታች ከግንቦት 24 ቀን በላይ አይውልም፡፡
8.    በዓለ ዕርገት ከግንቦት 5 ቀን በታች ከሰኔ 19 ቀን በላይ አይውልም፡፡
9.    ጾመ ሐዋርያት ከግንቦት 16 ቀን በታች ከሰኔ 20 ቀን በላይ አይውልም፡፡
10.    ጾመ ድኅነት ከግንቦት 18 ቀን በታች ከሰኔ 22 ቀን በላይ አይውልም፡፡
ሁለት ዓይነት የተውሳክ አቆጣጠር አለ
1.    የዕለት ተውሳክ በቅዳሜ ይጀምራል፡፡
የቅዳሜ ተውሳክ 8፤ የእሑድ ተውሳክ 7፤ የሰኞ ተውሳክ 6፤ የማክሰኞ ተውሳክ 5፤ የረቡዕ ተውሳክ 4፤ የሐሙስ ተውሳክ 3፤ የዓርብ ተውሳክ 2
2.    የአጽዋማትና የበዓላት ተውሳክ
የነነዌ ተውሳክ 0፤ የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14፤ የደብረ ዘይት ተውሳክ 1፤ የሆሣዕና ተውሳክ 2፤ የስቅለት ተውሳክ 7፤ የትንሣኤ ተውሳክ 9፤ የርክበ ካህናት ተውሳክ 3፤ የዕርገት ተውሳክ 18፤ የጰራቅሊጦስ 28፤ የጾመ ሐዋርየት ተውሳክ 29፤ የጾመ ድኅነት ተውሳክ 1
በዓላትና አጽዋማት የሚውሉበት ቀን
–    ጾመ ነነዌ
–    ዐብይ ጾም
–    ጾመ ሐዋርያት
                     ሰኞ                   
–    ደብረ ዘይት
–    ሆሣዕና
–    ትንሣኤ
–    ጰራቅሊጦስ
                      እሑድ
–    ስቅለት
                      ዓርብ
–    ርክበ ካህናት
–    ጾመ ድኅነት
                       ረቡዕ
–    ዕርገት
                      ሐሙስ ቀን ይሆናል፡፡
ይቀጥላል

 

ከሶዲቾ ዋሻ ጽላት ያገኙት አባት ከፍተኛ ድብደባ ደረሰባቸው

በከምባታ ጠምባሮ ዞን በሶዲቾ ዋሻ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጽላትና ንዋያተ ቅድሳት በቁፋሮ እንዲወጣ ያደረጉት አባት ቆሞስ አባ ኤልያስ ጳጉሜ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. ከፍተኛ ድብደባ ደረሰባቸው፡፡
ዋሻው በ1998 ዓ.ም. የተገኘና የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቅርስነት ከያዛቸው የመስህብ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ በአካባቢው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ቁጥር አነስተኛ ሲሆን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች እንደሚበዙ ይታወቃል፡፡ ከዋሻው መገኘት በኋላ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች በዋሻው ውስጥ በዓመት 2 እና 3 ጊዜያት ጉባኤ ያካሒዱበት እንደነበር ይነገራል፡፡ በቅርቡ በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. ቆሞስ አባ ኤልያስ የተባሉ አባት ወደ ሥፍራው በመምጣት በቦታው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳትና ቅርሶች እንዲሁም ጽላት እንደሚገኝ፤ ይህንንም ማውጣት እንዲችሉ ከዞኑ የመንግስት አካላት፤ ከሀገረ ስብከቱና ከወረዳው ቤተ ክህነት ፈቃድ ማግኘታቸውን አባ ኤልያስ ይገልጻሉ፡፡ ሀገረ ስብከቱም ሆነ ወረዳ ቤተ ክህነቱ ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡
ቆሞስ አባ ኤልያስ በዋሻው ውስጥ ቁፋሮ በማካሔድም የአንድ አባት አጽም፤ የእጅ መስቀልና በ984 ዓ.ም. /ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት/ የነበረ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጽላት አግኝተዋል፡፡ በቦታው የነበረውንም ጸበል ባርከው በርካታ ምእመናንና ኢ-አማንያንን በማጥመቅ እየተፈወሱ እንደሚገኙ ቆሞስ አባ ኤልያስ ይገልጻሉ፡፡ ወደ ሥፍራው በሔድንበት ወቅት ለአራት ዓመታት ሙሉ ሰውነታቸው የማይንቀሳቀስና የአልጋ ቁራኛ የነበሩ አባት ሙሉ ለሙሉ መዳናቸውን በአካል ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡ በቁጥር 38 የሚሆኑ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች አምነው ለመጠመቅ መቻላቸውንም ቆሞስ አባ ኤልያስ ይናገራሉ፡፡
ጉዳዩ ያሳሰባቸው አንዳንድ ግለሰቦች በቡድን በመሆን ድንጋይ በመወርወርና በመዛት ከቦታው እንዲለቁ ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ሙከራዎች ማድረጋቸውን ቆሞስ አባ ኤልያስ እና የዓይን እማኞች ያረጋግጣሉ፡፡
ጳጉሜ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. ግን የግለሰቦቹ የኃይል እርምጃ ተጠናክሮ ድንጋይ በመወርወር ቆሞስ አባ ኤልያስን በመደብደብ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱባቸው ከወረዳው ቤተ ክህነት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ለወረዳው አቅራቢያ ወደሆነ የህክምና መስጫ ጣቢያ በመውሰድም ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛሉ፡፡ ጉዳዩን ለመፍታትና ዘላቂ እልባት ለመስጠትም የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ከሚመለከታቸው የዞኑ የመንግስት አካላት ጋር እየተነጋገሩ እንደሚገኙ ከወረዳው ቤተ ክህነት ያገኘነው የመረጃ ምንጭ ያመለክታል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ የአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

ጳጉሜን 4 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

new 4

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለ2006 ዓ.ም. አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ፡፡

ቅዱስነታቸው እግዚአብሔር ለፍጡራን ከሰጣቸው መልካም ስጦታዎች መካከል የዘመን ስጦታ የመጀመሪያውን ደረጃ እንደሚይዝ በመግለጽ ከ2005 ዓም. ዘመነ ማቴዎስ ወደ 2006 ዓ.ም. ዘመነ ማርቆስ በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

አዲሱን ዘመን ሥራ በመሥራት ማሳለፍ እንደሚገባ ሲገልጹም “እያንዳንዱ ሰው ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ በኅሊናው ማቃጨል ያለበት ዓብይ ነገር በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሓላፊነቴ ምን ሠራሁ፤ ምንስ ቀረኝ? ለአዲስ ዓመትስ ምን ሠርቼ ከእግዚአብሔር ጋር ተባባሪ ልሁን የሚለውን ነው፡፡ ሥራ መሥራት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መተባበር ነውና፡፡ እያንዳንዱ ሰው ይህንን አስተሳሰብ አንግቦ አዲሱን ዘመን በአዲስ መንፈስ ከተቀበለው እውነትም ዘመኑን በሥራ ወደ አዲስነት ይለውጣል፡፡” በማለት ቅዱስነታቸው ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየታየ ያለውንና በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ወጣቶች ፍልሰትና እልቂትን ለመከላከል ሕዝቡ ልጆቹን ማስተማር እንዳለበትም በመልእክታቸው ጠቁመዋል፡፡
በወሊድ ወቅት ለሞት የሚጋለጡ እናቶችና ሕፃናትን አስመልክቶም በሀገራችን የእናቶችና ሕፃናት ሞት ለመቀነስና ለመከላከል ታስቦ እየታካሔደ ያለውን እንክብካቤ የተሳካ ይሆን ዘንድ ሁሉም ሊደግፈውና በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
     

new 4 1new 4 2

ማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አመራር ጠቅላላ ጉባኤውን አካሔደ

ነሐሴ 27 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

tekelala gu 

  • ማኅበሩ አዲስ ዋና ጸሓፊ መርጧል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን በየ ስድስት ወሩ አንድ ጊዜ የሚያካሒደውን የሥራ አመራር ጠቅላላ ጉባኤ ከነሐሴ 25 እስከ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. አካሔደ፡፡ የስድሰት ወራት የማኅበሩን የሥራ አፈጻጸም በመገምገም አጽድቋል፡፡

tekelala gu 2በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርትና ሥልጠና ማእከል ለሁለት ቀናት በቆየው መርሐ ግብር የስድስት ወራት የሥራ አመራር ቃለ ጉባኤ ቀርቦ የጸደቀ ሲሆን፣ የሥራ አመራር ጉባኤ ጽ/ቤት፣ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ጽ/ቤት፣ የኤዲቶሪያል ቦርድ ጽ/ቤትና የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ሪፓርቶች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸው ጸድቀዋል፡፡ በተጨማሪም በማእከላት የፋናንስ አያያዝ ፕሮጀክት በ2006 ዓ.ም. ዕቅድና ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ተወያይቷል፡፡

ማኅበሩን በዋና ጸሓፊነት ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲመሩ የነበሩት ዲያቆን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የአገልግሎት ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው ጠቅላላ ጉባኤው አዲስ ዋና ጸሓፊ መርጧል፡፡ በዚህም መሠረት የልማት ተቋማት አስተዳደር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ ተሰፋዬ ቢሆነኝን ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት ማኅበሩን በዋና ጸሐፊነት እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል፡፡

ፍኖተ ሐመረ ጽድቅ ዐውደ ርዕይ ተከፈተ

ነሐሴ 24 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ዐውደ ርዕዩ እሰከ ከነሐሴ 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ይቆያል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍልን የሃያ ዓመታት የአገልግሎት ጉዞ የሚያሳይ ፍኖተ ሐመረ ጽድቅ ዐውደ ርዕይ በማኅበሩ ሕንፃ ላይ ተከፈተ፡፡

ht
ፍኖጸተ ሐመረ ጽድቅ ዐውደ ርዕይ ነሐሴ 23 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የቦረና፤ አማሮና ቡርጂ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ሰላማ የታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳምና የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና አገልጋዮች በተገኙበት መርቀው ከፍተዋል፡፡

ht 2ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የቦረና አማሮና ቡርጂ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሐመር መጽሔትና የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ያደረጉትን አስተዋጽኦ፤ እንዲሁም ከአመሠራረታቸው ጀምሮ የተጓዙበትን ሂደት በጥልቀት አብራርተዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም. ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የማኅበሩ አባላት በተገኙበት ውይይት በማካሔድ ሐመር መጽሔት ተብሎ እንዲሰየም ውሳኔ ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

ብፁዕነታቸው የኅትመት ውጤቶቹ እየሰጡ የሚገኙትን አገልግሎት ሲገልጹም “በሐመር መጽሔትና በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የሚጻፈው፤ የሚነበበው ነገረ ድኅነትን ያመለክታል፡፡ የምንድንበትን መንገድ የሚያስተምሩ፤ ፃድቃን ሰማዕታት አማላጅ መሆናቸውን የሚያውጁ፤ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ የሁሉ ጌታ፤ የሁሉ ፈጠሪ መሆኑን የሚመሰክሩ፤ እምነትንና ምግባርን የሚያስተምሩ ናቸው” ብለዋል፡፡

ምእመናንን በማነጽ ረገድም “ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው የማያውቁ ወንድሞችና እኅቶች የኅትመት ውጤቶቹን በማንበብ ራሣቸውን በማረም እምነታቸውን እንዲያውቁና እንዲጸኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ አልፎም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እየተሰራጩ ምእመናንን በመታደግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ታላቅ ሐዋርያዊ አገልግሎት ነው” በማለት ወደፊትም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ht 3
የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ የማኅበሩ የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን ያላቸውን ፋይዳ በማስመልከት “በሐመር መጽሔትና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የተጀመረው አገልግሎት እድገት በማሳየት ሌሎች የኅትመት ውጤቶችን በመውሰድ ምእመናንን በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤቶችንም በመጠቀም የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ዘርፍ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በአንድ ጊዜ በመድረስ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ያስችለዋል” ብለዋል፡፡

ዲያቆን ዶክተር መርሻ አለኸኝ የሚዲያ ዋና ክፍል ሓላፊ የዐውደ ርዕዩ አስፈላጊነት በሚመለከት “ዐውደ ርዕዩ የሐመር መጽሔትና የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በሃያ ዓመታት ጉዞ ውስጥ ያሳዩአቸውን ጠንካራና ደካማ ጎን ለይተን እንድናውቅ፤ የኅትመትም ይሁን የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው የአገልግሎት ዘርፍ የወደፊት አቅጣጫ እንድንተልም ይረዳናል” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በሚቀጥለው ወር በመንፈሳዊው ሚዲያ ዘርፍ ልምድ ባላቸው አንጋፋ ጋዜጠኞች አማካይነት በማኅበሩ የኅትመት ሚዲያ ላይ ዐውደ ጥናት እንደሚካሔድ ገልጸዋል፡፡

ht 4ዐውደ ርዕዩ አራት አበይት ክፍሎች ሲኖሩት ዝክረ ሐመረ ጽድቅ፤ መዛግብትና ቁሳቁስ፤ የፎግራፍና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዘርፍ እንቅስቃሴን ይዳስሳል፡፡ ዐውደ ርዕዩ እሰከ ነሐሴ 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ሲሆን ምእመናን አራት ኪሎ በሚገኘው በማኅበሩ ሕንፃ ላይ ከጠዋቱ 4፤00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2፤00 ሰዓት ድረስ እንዲመለከቱ ተጋብዘዋል፡፡

በግብፅ አብያተ ክርስቲያናትና ክርስቲያኖች የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነው

ነሐሴ 11 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

egy firየፕሬዚዳንት ሙሐመድ ሙርሲ ደጋፊዎች የሆኑት የሙስሊም ወንድማማቾች በግብፅ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ጥቃት እየፈጸሙ እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ የመረጃ ምንጮች በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ በተለይም በዲልጋ፤ ሚና፤ እና ሶሃግ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ የሚና ቅድስት ማርያምና የአብርሃም አብያተ ክርስቲያናት የሙስሊም ወንድማማቾችና ደጋፊዎች በእሳት አያይዘዋቸዋል፡፡ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችንም ሶሃግ በሚገኘው ማር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ወርውረዋል፡፡

ከካይሮ የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የአልቃይዳ መለያ የሆነው ጥቁር ባንዲራ እየተሰቀለባቸው ሲሆን በተለይም የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ይገኝበታል፡፡

በላይኛው ግብፅም በርካታ አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉና ጥቃት እየደረሰባቸው ሲሆን ክርስቲያኖችም መገደላቸውን ከግብፅ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ለመውጣት መገደዳቸውንም እነዚሁ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው ሊቢያዊው ታማር ረሻድ የተባለው ተቃዋሚ “ለፓትርያርክ ታዎድሮስ መልካም ዜና ልነግራቸው እፈልጋለሁ፡፡ በግብፅ ምድር ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት የማይኖሩበት ጊዜው ደርሷል” በማለት ለቴሌቪዥን ጣቢያው ሲናገር ተደምጧል፡፡

በላይኛው ግብፅ ከሚገኙት ሚና፤ አስዩትና ሶሃግ በተጨማሪ የክርስቲያኖች መኖሪያና የሥራ ቦታዎች በእሳት ተያይዘዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱም አገልግሎታቸውን ማቋረጣቸውን ዓለም አቀፍ የዜና ምንጮች እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዝርወት ክፍል ሁለት

ሐምሌ 3 ቀን 2005 ዓ.ም

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ

ባለፈው ዕትማችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በዝርወት /ከኢትዮጵያ ውጪ/ ያደረገችውን ረዥም ሐዋርያዊ ጉዞ የሚዳስስ ጽሑፍ ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ ቀጣዩን ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

2. አፍሪካ
የኢ.ኦ.ተ.ቤ. የጥቁሩን ሕዝብ መወከል የሚያስችላት ታሪካዊ አጋጣሚ ቢኖራትም ከዓለም ቀድማ በተመሠረተችበት አህጉር ለሚገኘው ሕዝቧ የሰጠችው አገልግሎት ሰፊ የሚባል አይደለም፡፡ እሷ አገልግሎት ባለመስጠቷ ጥቁሩ ሕዝብ ባሕሉና ልማዱ በፈጠረው ሀገረ ሰብአዊ እምነት ተይዞ ከአሚነ እግዚአብሔር ርቆ ለረጅም ዘመናት እንዲቆይ ሆኗል፡፡ አፍሪካውያን ከብዙ ሺሕ ዓመታት በኋላ ከኢትዮጵያ በእጅጉ ዘግይተው ወንጌልን የተቀበሉ አውሮ¬ውያን ያስተማሯቸውን ተቀብለዋል፡፡ ይልቁንም ቤተ ክርስቲያናችን ወደ ሕዝቡ መሔዷ ቀርቶ ራሱ ሕዝቡ እሷን ፈልጎ እንዲመጣ ኾኗል፡፡ በእርግጥ ቤተ ክርስቲያናችን ቀደም ባሉት ጊዜያት እስከ ሱዳንና ሱማልያ ተስፋ ፍታ እስልምና እስከሚቀማት ድረስ በርካታ አፍሪካውያንን በሃይማኖት ይዛ እንደቆየች የሚያስረዱ የታሪክ መዛግብት አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በአፍሪካ ያላት የሳሳ ታሪክ በአጭሩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

2.1 ኬንያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ1967/68 ዓ.ም ጀምሮ በናይሮቢ አገልግሎት መስጠት ጀምራለች፡፡ በ1978 ዓ.ም የተመሠረተው የደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንም ለምእመናን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በስደተኞች ካምፕ የመድኃኔዓለምና ለኬንያዎች የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በስደተኞተ ካምፕ አካባቢ እንዳለ ይነገራል፡፡

 
2.2 ሱዳን
በካርቱም ከተማ ቤተ ክርስቲያን ተቋቁማ ከ1932 ዓ.ም ጀምሮ አገል ግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች፡፡

2.3 ደቡብ አፍሪካ
ይህች ሀገር ከኢትዮጵያውያኑ በተጨማሪ ለኢትዮጵያና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያኗ ልዩ ፍቅር ያላቸውና የኢ.ኦ.ተ.ቤ. ተከታዮች ነን ብለው የሚያምኑ ሰዎች በብዛት የሚኖሩባት ናት፡፡ እነዚህ ሰዎች ይህንን እምነታቸውን በተግባር ለመተርጎም እ.ኤ.አ. ከ1872 ዓ.ም ጀምሮ እንቅስቃሴ አድርገው እ.ኤ.አ. በ1892 ዓ.ም. የተወሰኑ ምእመናን ከነበሩበት የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ተለይተው በመውጣት “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” ብለው አቋቋሙ፡፡ ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት በጣልያኖች ላይ የተቀዳጀችው የድል ዜና እንቅስቃሴያቸውን የበለጠ እንዲጎለብትና ማኅበራቸው እንዲጠናከር አድርጓል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በነበሩባት ውስጣዊ ችገሮች የተነሣ የፈለጉትን ያህል ልታጠናክራቸው ባትችልም አልፎ አልፎ በሚያገኙት ዕርዳታና የአይዞአችሁ መልእክት ቤተ ክርስቲያናችን በአካባቢው ላለው ሕዝብ አገልግሎት ስትሰጥ እንድትቆይ አድርጓታል፡፡ በ1993 ዓ.ም ደግሞ በስደት ወደ አካባቢ የሔዱ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ከደቡብ አፍሪካውያኑ የእምነት ወንድሞቻቸው ጋር በመተባበር የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን አቋቁመዋል፡፡

3. አውሮፖ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ እግሯ አውሮፖን የረገጠው /በጊዜው በኢጣልያ ፍሎሬንስ በተደረገው ዓለም ዐቀፍ የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ከኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ተመርጠው በተላኩ ልኡካን አማካይነት /ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ  እንደኾነ ታሪክ እማኝነቱን ቢሰጥም በይፋ በተደራጀ መልኩ ተቋቁማ አገልግሎት መስጠት የጀመረችው በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣልያን በተወረረችበት ጊዜ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሎንዶን ካደረጉት ስደት ጋር ለአጭር ጊዜም ቢሆን በተሰጠው አገልግሎት ጀምሮ በ1964 ዓ.ም በትውልደ ጃማይካውያን የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች አማካይነት ተቋማዊ መልክ ይዞ እንዲቀጥል የተደረገው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በታላቋ ብሪታንያ አምስት ያህል አብያተ ክርስቲያናትና ከሦስት በላይ የጽዋ ማኅበራት ይገኛሉ፡፡

ከእንግሊዝ ቀጥሎ ቤተ ክርስቲያና ችን የደረሰችበት ሀገር ጀርመን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በአካባቢው እንቅስቃሴ የጀመረችው በወቅቱ ለትምህርት ወደዚህ ሀገር መጥተው በነበሩት መልአከ ሰላም ዶ/ር መርዐዊ ተበጀና ዶ/ር በዕደ ማርያም አማካይነት ሲኾን በአሁኑ ወቅት ሰባት ያህል አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና ከሦስት የማያንሱ የጽዋ ማኅበራት ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ15 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም በግሪክ /አንድ/፣ በጣልያን /ሦስት/፣ በስዊዘርላንድ /ሦስት/ በስዊድን /ሁለት/፣ በኖርዌይ /ሁለት/፣ በቤልጅየም /አንድ/፣ በኦስትርያ /አንድ/፣ በፈረንሳይ /አንድ/ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን ወደ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ለማደግ ክትትል እየተደረገላቸው ያሉ ጽዋ ማኅበራት በተለያዩ የአውሮ¬ፖ ሀገራት አሉ፡፡

4. አውስትራሊያ
በዚህ አህጉር የቤተ ክርስቲያናችን እንቅስቃሴ ጥንታዊ የሚባል አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሦስት ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን እንደዚሁ በጽዋ ማኅበርነት የተደራጁ የምእመናን ኅብረቶች አሉ፡፡

5. ሰሜን አሜሪካ
የቤተ ክርስቲያናችን የሰሜን አሜሪካ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ ሲኾን ቤተ ክርስቲያን በኦፊሴል የተመሠረተችው ግን በ1951 ዓ.ም በአቡነ ቴዎፍሎስ ተባርኮ ኒውዮርክ ላይ በተቋቋመው የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ነበር፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን የተቋቋመው በወቅቱ የኢትዮጵያን የጥቁር ሕዝብ አርአያነት አምነው ያስተጋቡ ለነበሩ አፍሪካ አሜሪካውያን ሲሆን ቤተ ክርስቲያኑ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሮ በተቋቋመበት ዕለት 275 አፍሪካ አሜሪካውያን በመጠመቅ የቤተ ክርስቲያን አካል እንደሆኑ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ዓይነት በርቀት ለናፈቃት ጥቁሩ ሕዝብ ፓ-ስፊክን አቋርጣ የተቋቋመችለት ቤተ ክርስቲያን እየዋለ እያደረ በልዩ ልዩ ምክንያት ሀገሩን ትቶ ወደ አህጉሩ የሚሰደደው ሕዝብ ቁጥር እየበዛ ሲሔድ እሷም እየተስፋፋች ዛሬ ካለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በአህጉሩ ከ90 በላይ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ 

 
6. ካናዳ
በካናዳ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተጀመረው በቶሮንቶ ከተማ በአንድ ምእመን ድጋፍ በተገዛ ሕንፃ ውስጥ በ1964 ዓ.ም ሲሆን በአሁኑ ወቅት በመላ አህጉሩ ከሃያ አምስት በላይ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡

7. ካሪብያን ሀገሮች
በዚህ ትሪንዳድ ቶቤጎን ጉያናንና ጃማይካን በሚያጠቃልለው አካባቢ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የጀመረችው በ1964 ዓ.ም. በአባ ገብረ ኢየሱስ /በኋላ አቡነ አትናቴዎስና አቶ አበራ ጀንበሬ አማካይነት ሲኾን በአሁኑ ወቅት ከአምስት በላይ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡

8. ትሪንዳድና ቶቤጎ
ቤተ ክርስቲያን በቅኝ ገዥዎቹ በደረሰበት ተፅዕኖ በማንነት ፍለጋ ይናውዝ ለነበረው ለዚህ አካባቢ ጥቁር ሕዝብ አገልግሎት መስጠት የጀመረችው ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በተደረጉ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴዎች በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ነፍሳት በጥምቀት ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ተወልደው በቤተ ክርስቲያን ዕቅፍ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እየገቡም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዚህ አካባቢ ከአምስት ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡  

9. ጃማይካ
በዚህ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ የነጻነታቸው ተስፋ ምድራዊ ርስት አድርገው ይቆጥሯት ለነበረችው ኢትዮጵያ አጋርነታቸውን ለማሳየት “ራስ ተፈሪያን” የሚል ቡድን መሥርተው ነበር፡፡ ንጉሡ በ1958 ዓ.ም በጃማይካ ይፋ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የመሆን ፍላጎት እያየለ በመምጣቱ የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን በኪንግስተን ጃማይካ ተቋቋመች፡፡ ከዚያም በኋላ ግንቦት 6 ቀን 1962 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ጃማይካ ሲገቡ ብሔራዊ አቀባበል በተደረገላቸው ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ አማካይነት ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥታ ዛሬ ካለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡

II. አስተዳደራዊ መዋቅር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከላይ በቀረበው መልኩ ዓለም ዐቀፋዊ አገልግሎት ስትሰጥ እንደየዘመኑ ሁኔታ የራሷን አስተዳደራዊ መዋቅር እየዘረጋች ሲሆን ዛሬ ባለችበት ደረጃ የዝርወት እንቅስቃሴዋን በመምራት ላይ ያለችው 12 ያህል አህጉረ ስብከትን በማቋቋም ነው፡፡ እነዚህም የመላ አፍሪካ ሀገረ ስብከት፣ የአውስትራሊያ ሀገረ ስብከት፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገረ ስብከት፣ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት፣ የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ሀገረ ስብከት፣ የኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት፣ የዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት፣ የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት፣ የካሪብያን ሀገራት ሀገረ ስብከትና የካናዳ ሀገረ ስብከት ናቸው፡፡

 
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ ማለፍ የሌለበት ቤተ ክርስቲያናችን በልዩ ልዩ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት መካከል ማኅበራዊ መረዳዳትንና ቅርርብን ዓላማው አድርጎ በ1948 ዓ.ም በአምስተርዳም የተመሠረተው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት /World Council of Cherches/ ሲመሠረት በመሳተፍ ከመሠረቱ ሀገራት አንዷ መሆኗ ነው፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ ደረጃ በ1963 ዓ.ም ናይሮቢ ኬንያ ላይ የተቋቋመው የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ መሥራች አባል ናት፡፡ ከያዝነው ርእስ አንጻር የቤተ ክርስቲያኗ የእነዚህ ጉባኤያት አባል መሆን ብዙም የጠቀማት አይመስልም፡፡ ወይም ጉባኤያቱን በአግባቡ መጠቀም አልቻለችም፡፡ 

    
III.  ችግሮች
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓላማዋ ሰማያዊ እንደመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የዓላማዋ ተፃራሪ በሆነው ዲያብሎስ ስትፈተን ኖራለች አሁንም በመፈተን ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ አካባቢ ያለችዋ ቤተ ክርስቲያናችንም ከምሥረ ታዋ ጀምሮ ልዩ ልዩ ችግሮች አጋጥመዋታል፡፡ ዛሬም እነዚሁ ችግሮች ሰማያዊ አገልግሎቷን በስፋት በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነው በጉያዋ ለተሰበሰቡ ስዱዳን ልጆቿ እንዳትሰጥ ያደርጓታል፡፡

በአካባቢው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያሉባትን ችግሮች ውስጣዊ እና ውጫዊ ብለን ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ ውስጣዊ ስንል በየደረጃው ካሉ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኗ አካላት፣ ካህናት፣ ምእመናን፣ ሰበካ ጉባኤያት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ወ.ዘ.ተ.፣ የሚመጡ ችግሮችን ሲሆን ውጫዊ ስንል ደግሞ ከቤተ ክርስቲያኗ ውጭ ካሉ አካባቢያዊ ነባራዊ ሁናቴዎች የሚመጡትን ችግሮች ነው፡፡

አቡነ ጎርጎርዮስ የሥልጠና ማእከል የበገና ተማሪዎችን አስመረቀ

ሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም.

በታመነ ተክለ ዮሐንስ

begena 16የማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት የአቡነ ጎርጎርዮስ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል በዜማ መሣሪያ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች እሑድ ሐምሌ 6 ቀን 2005 ዓ.ም አስመረቀ፡፡ ማእከሉ በመደበኛ የትምህርት መርሐ ግብሩ የአስኳላ ትምህርትን የሚሰጥ ሲሆን፤ በማታ እና በእሑድ ቅዳሜ የሥልጠና መርሐ ግብሩ ደግሞ የአብነትና የዜማ መሣሪያዎችን ሥልጠና ያካሄዳል፡፡ በያዝነው ዓመት በማታው መርሐ ግብር ለተከታታይ ዘጠኝ ወራት ሲሰጥ በነበረው የዜማ መሣሪያዎች ሥልጠና 208 ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ ከ170 በላይ የሆኑት በበገና እንዲሁም ቀሪዎቹ 30 ደግሞ በመሰንቆ የሠለጠኑ ናቸው፡፡

በተቋሙ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አብዮት እሸቱ እንደገለጹት “በትምህርት መርሐ ግብሩ የሚሰጡት የአብነት ትምህርቶች (ግዕዝና የቅዳሴ ተሰጥኦ) እንዲሁም የዜማ መሣሪያዎች (በገና፣ መሰንቆ፣ ዋሽንትና ከበሮ) ሥልጠና፤ በዋነኝነት ዓላማ አድርገው የያዙት የሠልጣኞቹን የመንፈሳዊ ሕይወት ተመስጦ ለማሳደግ ሲሆን፤ በተያያዥነትም ወደቀጣዩ ትውልድ የሚደረገውን  የመንፈሳዊ ቅርስ የቅብብል መንገድ ለማጠናከር ነው” ብለዋል፡፡ ሠልጣኞቹ ከምረቃ በኋላ በ2003 ዓ.ም በተመሠረተው የበገና ቤተሰብ ማኅበር በመታቀፍ ጥምቀትን በመሰሉ ታላላቅ መንፈሳዊና የሕዝብ ክብረ በዓላት ላይና በሌሎች ወሳኝ መድረኮች ላይ የበገና አገልግሎትን ይሰጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ካለው የአቅም እጥረት እና የጥያቄ ብዛት አንጻር ተመጣጣኝ የሆነ አገልግሎት ለምእመናኑም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ማበርከት እንዳልተቻለ አሳውቀዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ “የትምህርትና የሥልጠና ዘርፉን በመምህራን ከማጎልበት አንጻር የመምህራን የትምህርት ማስረጃ የተሟላ ካለመሆን የተነሣ የበገና መምህራን እጥረት የሚታይ ሲሆን፤ እንደመፍትሄ እየተወሰደ ያለ እርምጃ ቢኖር ከምሩቃን መካከል የላቀ ብቃት ያሳዩትን በመምረጥና ልዩ ሥልጠና በመስጠት ተተኪ መምህራንን የማፍራት ሥራ ነው” ብለዋል፡፡ ነገር ግን በሌሎች የዜማ ትምህርት ዘርፎች መሰል ችግሮች እንደማይታዩ ገልጸው፤ ይልቁንም ከቅዱስ ያሬድ የዜማ ትምህርት ቤት በሚወጡ መምህራን በመታገዝ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እንደሚሰጥ አሳውቀዋል፡፡ ማእከሉ ከያዘው የተደራሽነት  ዓላማ አንጻር ሥልጠናውን ለማንኛውም አካል በግልጽ የሚሰጥ ሲሆን፤ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት አሥር ያህል የውጭ ዜጎች በበገና ላይ ያተኮረ ሥልጠና ወስደዋል፡፡

የሥልጠና ማእከሉ በቀጣይ የተደራጀ መዋቅር በመቅረጽ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና አስተምህሮ አንጻር የተፈቀዱትን የዜማ መሣሪያዎች ሥልጠና፤ የአብነት ትምህርትን በተጠናከረ መልኩ ለመቀጠልና ከተቋሙ የሚመረቁ ተማሪዎች ሕጋዊ የሆነ እውቅና እንዲያገኙ እንዲሁም ማእከሉን ወደ TVT ደረጃ ለማሳደግ ከትምህርት ሚኒስቴር እውቅናን ለመጠየቅ ተቋሙ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ሓላፊው  ባስተላለፉት መልእክት  ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃይማኖትና ብሔር ሳይለይ የሀገር ቅርስ የሆነውን የበገና ትምህርት ቢማር በመጪው ትውልድ ከሚመጣ ወቀሳ መዳን እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡