ማእከሉ ጠቅላላ ጉባኤውን ሊያካሂድ ነው

ጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤውን የፊታችን ቅዳሜና እሑድ እንደሚያካሂድ የማእከሉ ዋና ጸሐፊ አቶ ካሳሁን ኀይሌ አስታወቁ፡፡ ቅዳሜ ጥቅምት 17 ቀን 2005 ዓ.ም ከሰዓት በፊት በሚኖረው የመክፈቻ  መርሐ ግብር ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የዋናው ማእከል ተወካይ፣ የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሊቃነ መናብርት ከየግቢ ጉባኤያትና ከሠራተኛ ጉባኤያት የሚወከሉ ተወካዮች እንደሚገኙ ያስታወቁት አቶ ካሣሁን፡- “የ2004 ዓ.ም የሥራ አፈጻጻምን መገምገም፣ በጸደቀው የማኅበሩ መሪ ዕቅድ ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀውንና ከጥር 1 እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2005 ዓ.ም የሚያገለግለውን ዕቅድ ተወያይቶ ማጽደቅ በዋነኝነት በዚህ ጉባኤ የሚፈጸሙ ተግባራት ናቸው” ብለዋል፡፡

 

ጉባኤው  በሁለት የመወያያ ርዕሶች ላይ እንደሚመክር የታወቀ ሲሆን፤ ከ800 እስከ 1200 የሚደርሱ የማእከሉ አባላት እንደሚታደሙበት ከማእከሉ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

700 ምእመናን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ተመለሱ

ጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


በቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ለማ በየነ አማካኝነት፥ ለ31ኛው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አጠቃላይ መንፈሳዊ የሰበካ ጉባኤ የቀረበው ሪፖርት፤ ለ28 ዓመታት ያህል በሰዩ ወረዳ ሹሻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንና በአጥቢያው የሚገኙ ምእመናን ከእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸው በመለየት የቆዩትን ሁለት ቀንደኛ የተሐድሶ መናፍቃን መሪዎች ተውግዘው  መለየታቸውን አመለከተ፡፡

 

በተሐድሶ መናፍቃን ሴራ በየዋህነት የተወሰዱ ምእመናንን በንስሐ  ለመቀበልና መናፍቃኑ “የሹሻ ቅዱስ ገብርኤል ምክር ቤት ” በሚል ስያሜ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት የተነጠሉትን በብፁዕ አቡነ ሄኖክ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ትዕግሥት የተሞላበት በሳል አመራር የሹሻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን ለማስመለስ ስድስት ወራት መውሰዱን ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ሐዲስ ለማ በየነ  አስረድተው፤ ምእመናኑ ባለማወቅና በመናፍቃኑ ስውር ሴራ ተታለው ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው መቆየታቸው እንዳሳዘናቸውና በመጨረሻ ግን የተለዩአትን እናት ቤተ ክርስቲያንን ለመቀላለቀል መቻላቸው እንዳስደሰታቸው በመግለጽ፡- “የሰባክያነ ወንጌልና የአገልጋይ ካህናትን ችግር ለመቅረፍ በመላው ዓለም የሚገኙ የቅድሰት ቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች ከሀገረ ስብከቱ ጎን በመቆም የተቻላቸውን ድጋፍ እንዲያበረክቱልን በታላቅ ትሕትና እጠይቃለሁ” ብለዋል፡፡

 

በመናፍቃኑ ተታለው የቆዩት ምእመናን መጋቢት 19 ቀን 2004 ዓ.ም በሹሻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መጽሐፈ ቄደር በተደረሰበት ማየ ንስሐ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት ተቀላቅለዋል፡፡

medere kebde

ማኅበረ ቅዱሳን በምድረ ከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ያስገነባቸው ፕሮጀክቶች ተመረቁ፡፡

ጥቅምት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ


medere kebdeማኅበረ ቅዱሳን በጉራጌ ሀገረ ስብከት በምድረ ከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ሲያከናውናቸው የነበሩት የመጠጥ ውኃና የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የከምባታ፣ ሀድያ፣ ጉራጌና ስልጢ አህጉረ ስብከትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ተመረቁ፡፡

 

የምረቃ መርሐ ግብሩ ጸሎተ ወንጌል በማድረስ የተጀመረ ሲሆን 100 ሺህ ሊትር መያዝ የሚችለው የኮንክሪት የውኃ ማጠራቀሚያmedere kebde 1 በብፁዕነታቸው ተመርቋል፡፡ በተጨማሪም የአብነት ትምህርት ቤቱ በብፁዕነታቸው ተባርኮ የተመረቀ ሲሆን እያንዳንዱን ክፍል በመዘዋወር ጎብኝተዋል፡፡ በግንባታው የተካተቱት 12 የተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎችና ሌሎች 4  ለመምህራን የተዘጋጁት ክፍሎች ሲሆኑ በእያንዳንዱ የተማሪዎች ማደሪያ ክፍል ባለ 2 ተደራራቢ አልጋዎች ይገኛሉ፡፡ 4 ለመምህራን የተዘጋጁት ክፍሎች በቅርቡ ሙሉ የመኝታ ቁሳቁስ እንደሚሟላላቸው ተገልጿል፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በሰጡት ቃለ ምዕዳን “በዚህ ታላቅ ገዳም በቅዱሳን አባቶቻችን በታሪካቸውና በገድላቸው እንዲሁም በቃል ኪዳናቸው አሻራ ላይ ነው ያለነው፡፡ የቅዱሳን በረከት ለኢትዮጵያ ሀገራችን ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ዓለም በመከራ ሲናጥ ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን የያዙ ቅዱሳን ጸሎትና አፅማቸው ጠብቋታል፡፡ የጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በተጋድሎ ከፀኑበት ቦታ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ያኔ በዚህ ቦታ ላይ እነሱና መላእክት ብቻ ነበሩ የከተሙት፡፡ ምድራውያን ሰዎች ሰማያውያን መላእክት የሆኑበት ቦታ ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ እኛ በዚህ አለም ስንኖር የቅዱሳኑን ፈለግ ተከትለን ለበረከት ነው የመጣነው፡፡ በዚህ ቦታ ተገኝታችሁ ይህንን ቅዱስ ገዳም ለመርዳትና ለመደገፍ የወጣችሁ፤ የወረዳችሁ ሁሉ ዋጋችሁ ታላቅ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

 

medere kebde 4የምድረ ከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም አበምኔት አባ አብርሃም ወልደ ኢየሱስም ማኅበረ ቅዱሳን ስላከናወነው ተግባር ሲገልጹ “ማኅበረ ቅዱሳን እያከናወነ ያለው አገልግሎት ለዓመታት ስንቸገርበት የነበረውን የውኃ ችግር የፈታ ነው፡፡ ለ6 ወራት ከብቶች በ3 ቀናት ልዩነት ነው ውኃ የሚያገኙት፡፡ እኛም የገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት በሳምንት በነፍስ ወከፍ 10 ሊትር ውኃ ብቻ ነው የምናገኘው፡፡ ከዚህ በፊት ውኃ ለማምጣት እስከ 40 ደቂቃ ይወስድብን ነበር፡፡ ሄደንም ወረፋ ጠብቀን ነው የምናገኘው፡፡ አንዳንዴም ተሰልፈንም ላይሳካልን ይችላል፡፡ ዛሬ ማኅበረ ቅዱሳን ከ100 ሺህ ሊትር ውኃ የሚይዝ ማጠራቀሚያ ሠርቶልን ችግራችን ተወግዷል፡፡” በማለት በውኃ ችግር ምክንያት ያጋጠማቸውን ሁሉ መፍትሔ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የአብነት ትምህርት ቤቱን በማስመልከት 48 ተማሪዎች ተቀብሎ ማስተማር እንደሚያስችልና የግንባታ ወጪውን ገዳሙ በመሸፈን ማኅበረ ቅዱሳን 150 ቆርቆሮ፤ 24 አልጋ፤ 24 ፍራሽ፤ 48 ብርድ ልብስ፤ 48 አንሶላ፤ 48 ትራስ  ወጪውን በመቻል ለምረቃ እንደበቃ ገልጸዋል፡፡

 

በገዳሙ ውስጥ ከሚታዩ ከፍተኛ ችግሮች መካከል አንዱ የምግብ አቅርቦት እጥረት እንደሆነ የገለጹት የገዳሙ አበምኔት ለተማሪዎቹ የተያዘ በጀት ባለመኖሩ ማኅበረ መነኮሳቱ በየቀኑ ከሚሰጣቸው ዳቤ እየቆረሱ በማካፈል ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ በገዳሙ ውስጥ 28 መነኮሳይት፤ 41 መነኮሳትና መናንያን ፤48 የአብነት ተማሪዎች እንደሚገኙና የምግብ ፍጆታቸውንም በየዓመቱ መጋቢት 5 ቀን በሚከበረው የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የእረፍታቸው መታሰቢያ በዓል ቀን ለማክበር ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከሚመጡ ምእመናንና በጎ አድራጊዎች ከሚለግሱት እንደሆነ አበምኔቱ ይናገራሉ፡፡

 

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የቦርድ ሰብሳቢ ኢንጂነር ግዛቸው ሲሳይ ለምድረ ከብድmedere kebde 3 አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ማኅበሩ ስላከናወነው ሥራ ባቀረቡት ሪፖርት “የውኃ ታንከር ሥራው በግንቦት ወር 2004 ዓ.ም. እንዲጠናቀቅ በማድረግ ውኃ መያዝ እንዲችል ተደርጓል፤፤ ግንባታው የተሠራው ከመሬት በላይ ሲሆን 100 ሺህ ሊትር ውኃ የመያዝ አቅም አለው፡፡ በገዳሙ አካባቢ ምንም የገጸ ምድርም ሆነ የከርሰ ምድር ውኃ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ያለው ብቸኛ አማራጭ ከዝናብ የሚገኘውን ውኃ ከጣሪያ ላይ በመሰብሰብ /Roof Catchment/ ዘዴ በመጠቀም ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት በመሠራቱ ምክንያት ቢያንስ ለ50 መነኮሳት ለእያንዳንዳቸው በቀን እስከ 7 ሊትር ውኃ ዓመቱን ሙሉ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡” በማለት ያብራሩ ሲሆን በውኃ እጦት ምክንያት ይሰደዱ የነበሩት መነኮሳትና መናንያን ቁጥር እንደሚቀንስና ወደ ገዳሙ የሚመጡ መናንያን ቁጥርም ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ለውኃ ፕሮጀክቱም 493፣459.25 ብር እንደሚያስፈልገው  በእቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በ409፣572 ብር ወጪ ሊጠናቀቅ መቻሉንና ወጪውንም ከተለያዩ በጎ አድራጊ ምእመናን ፤ የድሬዳዋ የቀድሞ ተመራቂዎች የቅድስት ድንግል ማርያም ጽዋ ማኅበርና ከባንኮች የሠራተኛ ጉባኤ እንደተገኘ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

ሁለተኛው ፐሮጀክት የአብነት ትምህርት ቤቱ ሲሆን 124፣466.10 ወጪ በማድረግ የቆርቆሮ፤ የአልጋ፤ የፍራሽ፤ የአንሶላና የትራስ ወጪዎችን መሸፈን እንደተቻለ በሪፖርታቸው ያመለከቱ ሲሆን ከፊል ወጪውን በማኅበረ ቅዱሳን የካናዳ ማእከል በኩል እንደተገኘ ማኅበሩ ለአንድ የአብነት መምህር በየወሩ 300 ብር ድጎማ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ለሁለቱ ፕሮጀክቶች 534፣038.10 ብር ወጪ መሆኑንም በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡

 

የተጠናቀቁትም ፕሮጀክቶች በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያምና በገዳሙ አበምኔት አባ አብርሃም ወልደ ኢየሱስ መካከል የፕሮጀክት ርክክብ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው ለገዳሙ አበምኔት ለአባ አብርሃም ወልደ ኢየሱስ የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ያዘጋጀላቸውን ስጦታ ያበረከተ ሲሆን አባ አብርሐምም ለቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍልና ፕሮጀክቱን በተገቢው ሁኔታ በመሥራት ላጠናቀቀው ተቋራጭ ልዩ ስጦታ አበርክተዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ አባላት፤ በጎ አድራጊ ምእመናን የተገኙ ሲሆን በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ትምህርተ ወንጌል፤ በማኅበሩ መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬ፤ እንዲሁም የቅኔ ዘረፋ በገዳሙ መምህር ቀርቧል፡፡ በመጨረሻም  በብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የከምባታ፣ ሀድያ፣ ጉራጌና ስልጢ አህጉረ ስብከትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ቡራኬና ጸሎት ተጠናቋል፡፡

metshate 3

2ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥናት መጽሔት ተመረቀ

ጥቅምት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

metshate 3በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል የተዘጋጀው 2ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥናት መጽሔት/Journal/ ጥቅምት 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ተመረቀ፡፡ በጥናት መጽሔቱ የምረቃ መርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ዑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል አማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ፤ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የሰሜን ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የጥናት መጽሔቱን በማዘጋጀት የተሳተፉ ምሁራን፤ ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምሁራን የተገኙ ሲሆን በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቡራኬ በጸሎት ተከፍቷል፡፡

 

የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ዲያቆን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያም የቀረበ ሲሆን በመልእክታቸውም “ማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል ሲያቋቁም ቤተ ክርስቲያን ያለፈችበትን ፈርጀ ብዙ ተግዳሮቶች መንፈሳዊና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አጥንቶ ትክክለኛ መፍትሔ ለመጠቆም፤ ርቀው ያሉትን  የቤተ ክርስቲያን ምሁራን ለማቅረብ፤ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ቀርበው በሙያቸው እንዲያገለግሉ ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ቤተ ክርስቲያን ቀመስ የሆነው የሀገሪቱ ሁለንተናዊ ሀብት በጥናትና ምርምር መሣሪያነት በመግለጽ፤ በመተንተንና በማሳተም ለዓለም ህዝብ ለማድረስ፤ በውጤቱም ቤተ ክርስቲያን የቁሳዊና መንፈሳዊ ግኝቶች ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል ነው፡፡” በማለት መልእክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የዕለቱን  ጉባኤ በንግግር እንዲከፍቱ በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል አማካሪ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ኀላፊ የሆኑትን ዶክተር ውዱ ጣፈጠን ጋብዘዋል፡፡

 

ዶክተር ውዱ ጣፈጠ ባደረጉት ንግግር “ቤተ ክርስቲያናችን የፍልስፍና ፤ የሥነ ጽሁፍ፤ የሥነ ሕንፃ፤ የሥነ ሥዕል፤ የሥነ ሰብዕ፤ የሥነ ማኅበረሰብ፤ የአስተዳደርና የሥነ ትምህርት . . . ወዘተ መድብለ ጸጋ ያላት ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ሀብት በአግባቡ እንድትጠቀምበት መመርመር፤ ለቀጣዩ ትውልድ የእውቀት ምንጭ በሚሆን መልኩ ማደራጀትና ማስተባበር የሚጠበቅ ሥራ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን ፈርጀ ሰፊ ሀብት ለልማት ለማዋል ወቅታዊና ነባራዊ ችግሮችን በጥናትና ምርምር በታገዘ መልኩ ለመፍታት መንቀሳቀሱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡” በማለት የገለጹ ሲሆን የጥናት መጽሔቱ ለኅትመት እንዲበቃ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱትን አካላት አመስግነዋል፡፡

 

መጽሔቱ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ዑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል አማካሪ ቦርድ ሰብሳቢmetshate አማካይነት ተባርኮ የተመረቀ ሲሆን በሰጡት ቃለ ምእዳን “የማር፣ የአትክልት፣ የገብስ ጭማቂ መጠጣት የተለመደ ነው፡፡ ትልቁ ጭማቂ ግን ከሰው አእምሮ የፈለቀውን መጠጣት ነው፡፡ ያውም ከሊቃውንቱ የመነጨውን፡፡ ታሪካችን እንዲጠበቅ ያደርጋልና፡፡ ይህ የጥናት መጽሔት ብዙ ምርምር የተደረገበትና ለቤተ ክርስቲያን፣ ለአገር እድገት፣ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት፣ ባሕል፣ ወግና እምነት ተጠብቆ እንዲሸጋገር የሚያደርግ፤ ለትውልዱ ለማስተላለፍ የሚጠቅም ነው” ብለዋል፡፡

 

የጥናት መጽሔቱን ለማዘጋጀት በተደረገው ጥረት ከፍተኛ ትብብር ሲያደርጉ የነበሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን እንዲሁም ተሳታፊዎች በጥናት መጽሔቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ሎሬት ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ የጥናት መጽሔቱ ስለሚኖረው ጠቀሜታ ሲገልጹ “ጥናትና ምርምር ለአንድ ሀገር መሠረት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ የእውቀት ክምችቶች አሉ፡፡ ከምሁራን ብዙ ጠይበቃል፡፡ የጥናት መጽሔቱም ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገራችን ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው፡፡ በእኛ በኩል ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁዎች ነን” በማለት ተናግረዋል፡፡

 

በጥናት መጽሔቱ ላይ በመሳተፍ ጊዜያቸውን፣ እውቀታቸውን በማካፈልና በማዘጋጀት ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው ወንድሞችና እኅቶች እንዲሁም ድርጅቶች ከብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ዑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል የአማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ፤ እንዲሁም ከብፁዕ አቡነ ኤልያስ የሰሜን ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እጅ ማእከሉ ያዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

 

በዚሁ ወቅት ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የሰሜን ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ ምእዳን “ይህች የጥናት መጽሔት ገና ካፊያ ናት፡፡  ኢትዮጵያ ያላት ሀብት እንደ ውቅያኖስ ተቀድቶ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሳንባ ነው የምትተነፍሰው፡፡ መኩሪያዋም መመኪያዋም ቤተ ክርስቲያን ናት ገና ብዙ ይቀራል ይቀጥላል” ብለዋል፡፡

 

metshate 2በመርሐ ግብሩ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን የመዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን የጥናትና ምርምር ማእከሉ ዋና ዳይሬክተር ዮሐንስ አድገ በጥናቱ ላይ የተሳተፉትን፤ የማማከር ሥራ ያከናወኑትን፤ መጽሔቱን በመገምገም ሙያዊ ድጋፋቸውን በመስጠት ለተባበሩት ምሁራን ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

 

በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ዑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል የአማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ ቡራኬና ጸሎት የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

ማኅበሩ በሬድዮ ማሰራጫው ላይ የአየር ሞገድ ለውጥ አደረገ፡፡

ጥቅምት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

በማኅበረ ቅዱሳን ኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የሬድዮና ቴሌቪዥን ዝግጅት ክፍል ዘወትር አርብ ከምሽቱ 3፡30 እስከ 4፡30 ያሰራጭ የነበረውን ትምህርታዊ የሬድዮ ዝግጅት የአየር ሞገድ ለውጥ በማድረግ በ19 ሜትር ባንድ 15335 ኪሎ ኸርዝ አጭር ሞገድ አማካኝነት በተሻለ ጥራት ከጥቅምት 9/2005 ዓ.ም. ጀምሮ ማስደመጥ እንደሚጀምር በማኅበረ ቅዱሳን የሬድዮና ቴሌቭዥን ፕሮግራም አስተባባሪ ዲ/ን ሄኖክ ኀይሌ አስታወቁ፡፡ እንዲሁም ከዚህ ቀደም የተላለፉ መርሐ ግብሮችን www.dtradio.org ላይ መከታተል እንደሚቻል አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ከሰባት ሺህ በላይ በሌላ እምነት የነበሩ ሰዎች ተጠመቁ

ጥቅምት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

 

በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ባሳለፍነው የ2004 ዓ.ም. ቁጥራቸው ሰባት ሺህ አንድ መቶ አርባ አንድ ሰዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖት በመቀበል መጠመቃቸውን የሀገረ ስብከቱ ሪፓርት አመለከተ፡፡

 

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሀን ወንድወሰን ገ/ሥላሌ ለ31ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ባቀረቡት ሪፓርት የሕግ ታሪሚዎች በተለያዩ ቤተ እምነቶች ውስጥ ከነበሩ ሰዎች መካከል ሰባት ሺህ አንድ መቶ አርባ አንድ ሰዎች ሊጠመቁ ችለዋል” ብለዋል፡፡

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የከሰዓት በኋላ ውሎ

ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


31ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከዛሬው የከሰዓት በኋላ መርሐ ግብሩ ላይ የትግራይ ማእከላዊ ዞን፣ /የአክሱም/፣ የሲዳሞ፣ የሰሜን ጎንደር፣ የምሥራቅ ሐረርጌ፣ የጅማ ዞን፣ የመቀሌ ዞን፣ የኢሊባቡር፣ የድሬዳዋ፣ የጋሞ ጎፋ፣ የሰሜን ወሎ፣ የባሌ፣ የደቡብ ጎንደር የምሥራቅ ወለጋ፣ የአርሲ፣ የትግራይ ምሥራቅ ዞን /የአዲግራት/፣ አህጉረ ስብከቶች የበጀት ዓመቱን ሪፓርታቸውን በሥራ አስኪያጆቻቸው አማካኝነት ለጉባኤው አቅርበው መርሐ ግብሩ በጸሎት ተፈጽሟል፡፡ 31ኛው መደበኛ ጉባኤ ነገ ጧት 2፡30 ላይ ይቀጥላል፡፡

የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ 31ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ጧት 3 ሰዓት ላይ በተካሄደው ጸሎት ተከፈተ፡፡

ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


ጉባኤው ከዛሬ ጥቅምት 6 ቀን ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ጥቅምት 11 ቀን ድረስ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ አማካኝነት አምስት አባላት ያሉበት አርቃቂ ኮሚቴ የተሰየመ ሲሆን፤ ይህንኑ ተከትሎ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐቃቢ መንበረ ፓትርያርክ የጉባኤው መክፈቻ ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በዚሁ ቃለ ቡራኬያቸው “በዚህ ጉባኤ የታደማችሁ አባቶቼ ወንድሞቼ እንኳን ለዚህ ቀን አደረሳችሁ፡፡” ካሉ በኋላ  “ሐዋርያዊት የሆነች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በቀኖናዋ ቅዱሳን ያሰኘቻቸው ልጆቿ አያሌ ናቸው፡፡ ቅድስናናን የሚያሰጠው የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ጠብቀን በቤተ ክርስቲያናችን ሊሠራ የሚገባውን ወስነን እንሠራለን” ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በ2005 ዓ.ም. ለመፈጸም ያሰበቻቸውን የዕቅድ ሪፓርት በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊሊጶስ የቀረበ ሲሆን ብፁዕነታቸው “በልዑል እግዚአብሔር አባታዊ ፈቃድ ከሐምሌ ወር 2003 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ወጥተን ወርደን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እድገትና ልማት፣ በሕዝባችን ሰላምና አንድነት፣ ሠርተን የሥራችንን የሥራ ክንውኖችና ውጤቶች እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነን ለመገምገም ያበቃንንና የሰበሰበንን አምላክ ደግመን ደጋግመን እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡ በብፁዕ ሥራ አስኪያጅ ጋባዥነትም በአቶ ተስፋዬ ውብሸት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የ2004 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ ክንውን አጠቃላይ ሪፓርት ቀርቧል፡፡ ምክትል ሥራ አስኪያጁ በሪፓርታቸው፡- “ቅርሶችን በዓለም ዐቀፍ ምዝገባ ሰነድ ለማስያዝና የደመራ መስቀል በዓላችንን በዮኔስኮ ለማስመዝገብ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ እንዲሁም የቅዱስ ያሬድ ዜማንና ሥርዐቱን ፊደላትና አኀዞችን የጥምቀት በዓልንም በቀጣይ ለማስመዝገብ ጥናቱ ተፈጽሟል” ብለዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አማካኝነት በ2004 ዓ.ም. የተሠራውን አስመልክቶ ሲናገሩ “በተቀናጀ የገጠር ልማት 26,864,687.00/ በመመደብ 923,254 ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዐሥር ፕሮጀክቶችን በተለያዩ ክልሎች ዘርግቶ ሠርቷል፡፡ ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ፣ በተቀናጀ የገጠር ልማት፣ በውኃ አቅርቦትና ንጽሕና አጠባበቅ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከል፣ በገዳማት ልማት፣ በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ክብካቤና ድጋፍ 26 ፕሮጀክቶን ዘርግቶ በ120,955,270.00 ብር በጀት ተግባራዊ አድርጓል” ብለዋል፡፡ ከሻይ እረፍት መልስ “ግጭት፣ የግጭት መንስኤና አፈታት” በሚል ርዕስ በልማት ኮሚሽን የስደተኞች ጉዳይ ሓላፊ አቶ ይልቃል ሽፈራው አማካኝነት ቀርቦ በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አማካኝነት ጉባኤው ተወያይቷል፡፡

 

ከምሳ ሰዓት በፊት የነበረው መርሐ ግብርም 6 ሰዓት ከሃያ ላይ በጸሎት ተዘግቷል፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤውን አካሄደ

ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

 

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤውን ቅዳሜ ጥቅምት 3 ቀን 2005 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው ሀርመኒ ሆቴል አካሂዷል፡፡ በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የሲዳማ ጌዲኦ ቡርጂና አማሮ ልዩ ልዩ ወረዳዎች  ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ዶክተር አባ ኀይለ ማርያም መልሴ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን ጨምሮ ከአብያተ ክርስቲያናት የተወከሉና የማኅበሩ አባላት ተገኝተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በአሁኑ ጊዜ በትርጉም፣ በኅትመትና በስርጭት ሥራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ያስታወሱት የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ይልማ ጌታሁን “በዘመናችን እየጨመረ የመጣውን የቅዱሳት መጽሐፍት ፍላጎት ስንመለከት ጥረታችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማጠናከር እንዳለብን ይታመናል፡፡ ይህንን ተግባር ደግሞ በተገቢው መንገድ ለማከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሓላፊነታቸውን ባግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡ ማኅበሩ በያዝነው ዓመት በሰባት ዋና ዋና ዘርፎች ሊሠራቸው ያሰባቸውን ዕቅዶች በሪፖርታቸው ያካተቱት  ዋና ጸሐፊው፥ በአባላት ምዝገባና በቅስቀሳ ዘርፍ ሁሉንም ክርስቲያን ለማሳተፍ መጠነ ሰፊ ቅስቀሳና ምዝገባ ለማከናወን እንዳቀደ አስታውቀዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የወንጌላውያን ኅብረትና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በአባልነት ተካተዋል፡፡

Dn. mulugeta

በአባቶች መካከል የተጀመረው የዕርቀ ሰላሙ ውይይት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

ጥቅምት 2 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


Dn. mulugetaየማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራርና የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤያት መስከረም 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በጋራ ባካሄዱት ስብሰባ በአስተዳደርና በተወሰኑ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን አተረጓጎም ልዩነት ምክንያት ለሁለት አሠርት ዓመታት ተለያይተው በቆዩ አባቶች መካከል የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት እስከ መጨረሻው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ “የስብሰባው ዋነኛ አጀንዳ በአገር ውስጥና በውጪ አገር በሚገኙ አባቶች መካከል የተጀመረው ውይይት ከሁሉም ጉዳዮች በፊት ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲሠራና እንዲፈጸም የማኅበሩ ፍላጎት መሆኑን ለማስታወቅና እንደ ጥያቄም ለማቅረብ ነው፡፡” በማለት መስከረም 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ስለተካሄደው ስብሰባ መግለጫ የሰጡት የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያም ናቸው፡፡

 

ዋና ጸሐፊው ለመካነ ድራችን በሰጡት መግለጫ “የማኅበሩ አባላትም ሆኑ ሌሎቹም ምእመናን የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት በጥሩ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ተግተው መጸለይ ይገባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የሰላሙንና የዕርቁን ሁኔታ ሊያደናቅፉ የሚችሉ ጉዳዮችን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱም አንድነቷ ተመልሶ የምትሠራበት ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ማኅበሩ የሚጠበቅበትን አገልግሎት ለመፈጸም ዝግጁ ነው፡፡ ስለሆነም የማኅበሩ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መምህራን ጭምር የማኅበሩን አቋም የማስታወቅ ሓላፊነት አለባቸው፡፡” ብለዋል፡፡

 

እርቁ እንዴት ይሁን? እንዴት ይፈጸም የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጣቸው በሁለቱም ቦታዎች በሚገኙ አባቶችና በአስታሪቂ ሽማግሌዎች መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት መተው እንደሚገባ ያስታወቁት ዲ/ን ሙሉጌታ የተጀመረው እርቅ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግና እግዚአብሔርንም በጸሎት እንዲማጸን አሳስበዋል፡፡

 

ዋና ጸሐፊው በማጠቃለያ መልእክታቸው፡- “ፍቅር ሰላምና አንድነት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ስምረት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ ሁል ጊዜ ለፍቅር ለመግባባትና አብሮ ለመሥራት በሰላም ለመኖር ሁሉም መጣር ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ከዚህ የሚያደናቅፍ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ አንድነትን የሚጠላ ፍቅርን የሚጠላ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ለዚህ ጉዳይ መትጋት ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡