በሶዲቾ ዋሻ የእመቤታችን ጽላት በአገር ሽማግሌዎች እየተጠበቀ ነው

 

 

 መስከረም 9ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በከምባታ ጠምባሮ ዞን ልዩ ስሙ ሶዲቾ ዋሻ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ በ984 ዓ.ም. የነበረ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጽላት በአገር ሽማግሌዎች እየተጠበቀ ነው፡፡

 

በግንቦት ወር ላይ ቆሞስ አባ ኤልያስ የተባሉ አባት ወደ ሶዲቾ ዋሻ በመምጣት ከሚመለከታቸው የቤተክርስቲያንና የዞኑ የመንግስት አካላት ፈቃድ በማግኘት ከዋሻው ውስጥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግልማርያም ጽላት፤ የአንድ አባት አጽምና የእጅ መስቀል በቁፋሮ ማውጣታቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በሥፍራው በሚከናውነው የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ብዙዎች በጸበል እየተፈወሱ ሲሆን ኢ- አማንያንም ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡ ይህ ያሳሰባቸው አንዳንድ ግለሰቦች በቡድን በመደራጀት በቦታው ላይ የሚገኙትን አባት ቆሞስ አባ ኤልያስን ከአካባቢው እንዲለቁ በማስገደድ፤ በማስፈራራትና ድንጋይ በመወርወር ደብድበው ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸው የሚታወስ ነው፡፡ በርካታ ጸበል ሊጠመቁ የመጡ ምእመናንም በድንጋይ ድብደባ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የወረዳውና የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች ከምእመናን ጋር በመሆን ለሚመለከተው የወረዳ፤ ብሎም የዞኑ መንግስት ባለሥልጣናት ድረስ ጉዳዩን በመውሰድ እልባት እንዲያገኝ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ከወረዳው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ነገር ግን የወረዳው ካቢኔ በዋሻው ውስጥ የሚገኘውን ጽላት አቅራቢያው ወደሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ወስዳችሁ እንድታስገቡ፤ ቦታውንም እንድትለቁ በማለት መስከረም 3 ቀን 2005 ዓ.ም. የመጨረሻ የቀን ገደብ አስቀምጦ እንደነበር የወረዳው ቤተ ክህነት ሓላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ በዞን ደረጃ እንዲታይ ቢደረግም መፍትሔ ማግኘት ባለመቻሉ ወደ ክልል በመሔድ አቤቱታ በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡

 

ጽላቱን ያገኙት አባት ቆሞስ አባ ኤልያስ ማንንም እንዳያጠምቁ፤ እንዳያስተምሩ፤ የማዕጠንትም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንዳያከናውኑ ተከልክለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ቆሞስ አባ ኤልያስ ከዋሻው በመውጣት ወዳልታወቀ ሥፍራ በመሔድ ሱባኤ እንደገቡ የሚነገር ሲሆን ጽላቱ በአካባቢው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ በሆኑ የአገር ሽማግሌዎች ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑን የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ አባ ኃይለ ሚካኤል ገልጸዋል፡፡