tena 3

5ኛው ሀገር አቀፍ ዓመታዊ ዐውደ ጥናት ተካሔደ

 

መስከረም 3 ቀን 2006 ዓ.ም.

 
በእንዳለ ደምስስ

tena 3በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው 5ኛው ሀገረ አቀፍ ዓመታዊ ዐውደ ጥናት “ጥናትና ምርምር ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ መጠናከር” በሚል ጳጉሜ 2 እና 3 ቀን 2005 ዓ.ም. በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ተካሄደ፡፡

በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “እግዚአብሔር ሲፈቅድ ልጆቹን ለመልካም ነገር ያውላቸዋል፡፡ የዚህ ጉባኤ ዓላማም ለመልካም ሥራ ነው፡፡ መልካም ሰዎች ለመልካም ነገር ይውላሉና፡፡ ሰው ሰውን አፍቃሪ፤ ረጂ፤ ለሀገሩም ለእግዚአብሔር የተመቸ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የዘመኑ የፈጠራ ትምህርት ከመንፈሳዊ ትምህርት ጋር በተያያዘ መመራመርን ይጠይቃል፡፡ ሰው ካወቀ ለሌላው ያሳውቃል፤ ለሌላው ያስረዳል፤ መልካም መሳሪያም ይሆናል፡፡ ይህ የተጀመረው ምርምርና ጥናት እኛንም የበለጠ ያፋቅረናል፤ በሃይማኖት እንድንቆም፤ የበለጠም እንድንሠራ ያደርገናል፡፡ የተሸሸገውን ታሪካችንን፤ያሳውቀናል፤ ልጆቻችንንም ተረካቢ ያደርጋቸዋል፡፡ ጥሩ ጅምር በመሆኑ በዚሁ እንድንቀጥል ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው ዐውደ ጥናት ስምንት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል “ጥንታዊ ቅርሶችን ከመጠበቅና ከማሰባሰብ አንጻር የካህናት ሚና” በፕሮፌሰር አየለ በክሪ በመቀሌtena 3 2 ዩኒቨርስቲ የታሪክና ባህል ጥናት መምህር፤ “ልማትና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በአቶ ፀጋዬ አስገለ እና በመምህር ካኽሳዬ ገብረ እግዚአብሔር፤ “ሥርዓተ ፆታና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በወ/ሮ ሐረገወይን ቸርነት በፐብሊክ ሣይንስና ምግብ ዋስትና የሥርዓተ ፆታ አማካሪ፤ “የሕይወት ምህንድስና፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በአቶ ኃይለ ማርያም ላቀው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤሌክትሪካል ኢንጂነር ቅዳሜ ጳጉሜ 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በዐውደ ጥናቱ ላይ የቀረቡ አራት ጥናታዊ ጽሑፎች ናቸው፡፡

እሑድ በተካሄደው ቀጣይ ዐውደ ጥናትም አራት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ “የበዓላት አከባበር፤ ቱሪዝምና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በአቶ ባንታለም ታደሰ በጎንደር ዩኒቨርቲ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር፤ “የሃይማኖት ቱሪዝም ልማት ተግዳሮት እና ትንበያ” በአቶ ኤርሚያስ ክፍሌ በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ወንዶ ገነት ስኩል ኦፍ ዋይልድ ላይፍ እና ቱሪዝም መምህር፤ “ሳይንስና ሃይማኖት እንዴት ይለያያሉ” በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ መምህር፤ “ሃይማኖታዊ እሳቤዎች በሳይንስ እይታ” በዶክተር አብርሃም አምኃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው ዐውደ ጥናት ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በጥናት አቅራቢዎች ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ሰፊ ውይይትም ተካሂዶባቸዋል፡፡ ዐውደ ጥናቱ ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት የቀጥታ ስርጭት ሽፋን የነበረው ሲሆን በርካታ በተለያዩ አህጉራት የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ተከታትለውታል፡፡ ጥያቄዎቻቸውንም በማቅረብ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡