ከሶዲቾ ዋሻ ጽላት ያገኙት አባት ከፍተኛ ድብደባ ደረሰባቸው

በከምባታ ጠምባሮ ዞን በሶዲቾ ዋሻ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጽላትና ንዋያተ ቅድሳት በቁፋሮ እንዲወጣ ያደረጉት አባት ቆሞስ አባ ኤልያስ ጳጉሜ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. ከፍተኛ ድብደባ ደረሰባቸው፡፡
ዋሻው በ1998 ዓ.ም. የተገኘና የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቅርስነት ከያዛቸው የመስህብ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ በአካባቢው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ቁጥር አነስተኛ ሲሆን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች እንደሚበዙ ይታወቃል፡፡ ከዋሻው መገኘት በኋላ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች በዋሻው ውስጥ በዓመት 2 እና 3 ጊዜያት ጉባኤ ያካሒዱበት እንደነበር ይነገራል፡፡ በቅርቡ በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. ቆሞስ አባ ኤልያስ የተባሉ አባት ወደ ሥፍራው በመምጣት በቦታው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳትና ቅርሶች እንዲሁም ጽላት እንደሚገኝ፤ ይህንንም ማውጣት እንዲችሉ ከዞኑ የመንግስት አካላት፤ ከሀገረ ስብከቱና ከወረዳው ቤተ ክህነት ፈቃድ ማግኘታቸውን አባ ኤልያስ ይገልጻሉ፡፡ ሀገረ ስብከቱም ሆነ ወረዳ ቤተ ክህነቱ ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡
ቆሞስ አባ ኤልያስ በዋሻው ውስጥ ቁፋሮ በማካሔድም የአንድ አባት አጽም፤ የእጅ መስቀልና በ984 ዓ.ም. /ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት/ የነበረ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጽላት አግኝተዋል፡፡ በቦታው የነበረውንም ጸበል ባርከው በርካታ ምእመናንና ኢ-አማንያንን በማጥመቅ እየተፈወሱ እንደሚገኙ ቆሞስ አባ ኤልያስ ይገልጻሉ፡፡ ወደ ሥፍራው በሔድንበት ወቅት ለአራት ዓመታት ሙሉ ሰውነታቸው የማይንቀሳቀስና የአልጋ ቁራኛ የነበሩ አባት ሙሉ ለሙሉ መዳናቸውን በአካል ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡ በቁጥር 38 የሚሆኑ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች አምነው ለመጠመቅ መቻላቸውንም ቆሞስ አባ ኤልያስ ይናገራሉ፡፡
ጉዳዩ ያሳሰባቸው አንዳንድ ግለሰቦች በቡድን በመሆን ድንጋይ በመወርወርና በመዛት ከቦታው እንዲለቁ ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ሙከራዎች ማድረጋቸውን ቆሞስ አባ ኤልያስ እና የዓይን እማኞች ያረጋግጣሉ፡፡
ጳጉሜ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. ግን የግለሰቦቹ የኃይል እርምጃ ተጠናክሮ ድንጋይ በመወርወር ቆሞስ አባ ኤልያስን በመደብደብ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱባቸው ከወረዳው ቤተ ክህነት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ለወረዳው አቅራቢያ ወደሆነ የህክምና መስጫ ጣቢያ በመውሰድም ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛሉ፡፡ ጉዳዩን ለመፍታትና ዘላቂ እልባት ለመስጠትም የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ከሚመለከታቸው የዞኑ የመንግስት አካላት ጋር እየተነጋገሩ እንደሚገኙ ከወረዳው ቤተ ክህነት ያገኘነው የመረጃ ምንጭ ያመለክታል፡፡