የቅድስት ምንባብ 3(ሐዋ.10÷17-30 )

ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደሆነ ሲያወጣና ሲያወርድ ከቆርኔሌዎስ ተልከው የመጡ ሰዎች የስምዖንን ቤት እየጠየቁ በደጅ ቁመው ነበር፡፡

ተጣርተውም፡- ጴጥሮስ የተባለ ስምዖን በእንግድነት በዚያ ይኖር እንደሆነ ጠየቁ፡፡ ጴጥሮስም ስለ ታየው ራእይ ሲያወጣ ሲያወርድ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው÷ “እነሆ÷ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፡፡ ተነሥና ውረድ፤ ምንም ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬአቸዋለሁና፡፡” ጴጥሮስም ወደ እነዚያ ሰዎች ወረደና÷ “እነሆ÷ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ ለምን መጥታችኋል?” አላቸው፡፡ እነርሱም÷ “የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ጻድቅ ሰው ነው፤ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አንተን ወደ ቤቱ እንዲጠራህ የምታስተምረውንም እንዲሰማ አዝዞታል፤” አሉት፡፡ እርሱም ተቀብሎ አሳደራቸው፤ በማግሥቱም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በኢዮጴ ከተማ ከሚኖሩት ወንድሞችም አብረውት የሄዱ ነበሩ፡፡ በማግሥቱም ወደ ቂሳርያ ከተማ ገባ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ ከእግሩ በታችም ወድቆ ሰገደለት፡፡ ጴጥሮስም÷ “ተነሥ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” ብሎ አነሣው፡፡ ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ወደ እርሱም የመጡ ብዙ ሰዎችን አገኘ፡፡ ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው÷”ለአይሁዳዊ ሰው ሄዶ ከባዕድ ወገን ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን ከሰው ማንንም ቢሆን እንዳልጸየፍና ርኩስ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳየኝ፡፡ አሁንም ስለ ላካችሁብኝ ሳልጠራጠር ወደ እናንተ መጣሁ፤ በምን ምክንያት እንደ ጠራችሁኝ እጠይቃችኋለሁ፡፡”

የቅድስት ምንባብ 2(1ኛጴጥ.1÷13-ፍጻ. )

ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡

እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ክፉ ምኞት አትከተሉ፡፡ ነገር ግን የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡ “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ” የሚል ተጽፎአልና፡፡ ለሰው ፊትም ሳያዳላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርድ አብን የምትጠሩት ከሆነ በሕይወታችሁ ዘመን ሁሉ በፍርሀት ኑሩ፡፡

ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ፡፡ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ፡፡ ዓለም ሳይፈጠር የታወቀ÷ በኋላ ዘመን ስለ እናንተ የተገለጠ፡፡ ከሙታን ለይቶ በአስነሣው÷ ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ቃል ያመናችሁ÷ አሁንም እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሁን፡፡

ሳትጠራጠሩ በፍጹም ልቡናችሁ ወንድሞቻችሁን ትወድዱ ዘንድ÷ ለእውነት በመታዘዝ ሰውነታችሁን አንጹ፤ እርስ በእርሳችሁም ተፋቀሩ፡፡ ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ለዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፡፡

የቅድስት ምንባብ1(1ኛ ተሰ.4÷1-13)

አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ÷ በእኛ ዘንድ እንደ ታዘዛችሁ በሚገባ ትሄዱ ዘንድ÷ እግዚአብሔርንም ደስ ታሰኙ ዘንድ÷ ደግሞ እንደ ሄዳችሁ ከፊት ይልቅ በዚሁ ታበዙና ትጨምሩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንነግራችኋለን፤ እንማልዳችኋለንም፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ያዘዝናችሁን ትእዛዝ ታውቃላችሁ፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ነውና፤ እርሱም ከዝሙት ትርቁ ዘንድ መቀደሳችሁ ነው፡፡ ሁሉም እያንዳንዱ ገንዘቡን ይወቅ፤ በንጽሕናና በክብርም ይጠብቀው፡፡ እግዚአብሔርን እንደማያውቁት እንደ አረማውያንም በፍትወት ድል አትነሡ፡፡ ይህንም ለማድረግ አትደፋፈሩ፤ በሁሉም ወንድሞቻችሁን አትበድሉ፤ አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁና እንደ አዳኘሁባችሁ÷ በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር የሚበቀል ነውና፡፡ እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኲሰት አልጠራንምና፡፡ አሁንም የሚክድ÷ መንፈስ ቅዱስን የሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን የካደ አይደለም፡፡

ባልንጀሮቻችሁን ስለ መውደድ ግን ልንጽፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ራሳችሁ በእግዚአብሔር የተማራችሁ ናችሁና፡፡ በመቄዶንያ ሁሉ ካሉት ወንድሞቻችን ሁሉ ጋር እንዲሁ ታደርጋላችሁ፤ ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ÷ ትበዙና ትጨምሩ ዘንድ÷ ሥራችሁንም ታከናውኑ ዘንድ እንደ አዘዝናችሁም በእጃችሁ ትሠሩ ዘንድ÷ በውጭ ባሉት ሰዎችንም ዘንድ ከማንም አንዳች ሳትሹ በሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናችኋለን፡፡

የዘወረደ ወንጌል (ዮሐ.3÷10-24)

ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፤ ነገር ግን አንዴት ይህን አታውቅም?” አለው፡፡

እውነት እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ ነገር ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉንም፡፡ በምድር ያለውን ስነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁን ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው፡፡ ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ አንጂ ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና፡፡ ዓለም በእርሱ ይድን ዘንድ ነው እንጂ በዓለም አንዲፈርድ እግዚአአብሔር ልጁን ወደዚህ ዓለም አልላከውምና፡፡ በእርሱ ያመነ አይፈረድበትም፤ በእርሱ ያላመነ ግን ፈጽሞ ተፈርዶበታል፤ በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም አላመነምና፡፡ ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጥቶአልና፤ ሰውም ሥራው ክፉ ስለሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መርጦአልና፡፡ ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደብርሃን አይመጣም፡፡ አውነትን የሚሠራ ግን ሥራው ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራልና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ፤ በዚያም እያጠመቀ አብሮአቸው ተቀመጠ፡፡ ዮሐንስም በዮርዳኖስ ማዶ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን ያጠምቅ ነበር፤ በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ እየመጡ ያጠምቃቸው ነበር፡፡ ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ ቤት አልገባም ነበርና፡፡

የዘወረደ ምንባብ 3 (ሐዋ.25÷13-ፍጻ. )

ከጥቂት ቀን በኋላም ንጉሥ አግሪጳና በር ኒቄ ወደ ቂሣርያ ወርደው ፊስጦስን ተገናኙት፡፡

ተገናኙት፡፡በእርሱ ዘንድ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ ነገረው፤ እንዲህም አለው÷ “ፊልክስ በእስር ቤት ትቶት የሄደ አንድ እስረኛ ሰው በእዚህ አለ፡፡ በኢየሩሳሌም ሳለሁም ሊቃነ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች ወደ እኔ መጥተው እንድፈርድበት ማለዱኝ፡፡ አኔም፡- ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ሳይቆም÷ ለተከሰሰበትም ምላሽ ይሰጥ ዘንድ ፋንታ ሳያገኝ ማንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሕግ አይደለም ብየ መለስሁላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ፤ በዚሁ በተሰበሰቡ ጊዜ ሳልዘገይ በማለዳ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ÷ ያን ሰው እንዲያመጡት አዘዝሁ፡፡ የከሰሱትም በቆሙ ጊዜ÷ እኔ እንደ አሰብሁት በከሰሱት ክስ የሠራው ምንም ነገር የለም፡፡ ስለ ሃይማኖታቸው ከሆነው ክርክርና ስለ ሞተው÷ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው ስለ ኢየሱስ ከሆነው ክርክር በቀር፤ ስለ ክርክራቸውም የማደርገውን አጥቼ ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም  ሄደህ በዚያ ልትከራከር ትወዳለህን? አልሁት፡፡” አግሪጳም ፊስጦስን÷ “እኔም ያን ሰው ልሰማው እወደለሁ” አለው፤ ፊስጦስም÷ “እንግደያስ ነገ ትሰማዋለህ” አለው፡፡

በማግሥቱም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጡ፤ ከመሳፍንቱና ከከተማው ታላላቅ ሰዎች ጋርም ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ፊስጦስም እንዲህ አለ÷ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ÷ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ወንድሞቻችን ሁላችሁ÷ ስሙ፤ አይሁድ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው በኢየሩሳሌምም ሆነ በዚህ እየጮሁ የለመኑኝ ይህ የምታዩት ሰው እነሆ፡፡ እኔ ግን ለሞት የሚያደርሰው በደል እንዳልሠራ እጅግ መርምሬ÷ እርሱም ራሱ ወደ ቄሣር ይግባኝ ማለትን ስለወደደ እንግዲህ ልልከው ቈርጫለሁ፡፡ ለገር ግን ስለ እርሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው የታወቀ ነገር የለኝም፡፡ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን አገኝ ዘንድ ወደ እናንተ ይልቁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ ወደ አንተ አመጣሁት፡፡ የበደሉ ደብዳበቤ ሳይኖር እስረኛን ወደ ንጉሥ መላክ አይገባምና፤ ለእኔም ነገሩም ሆነ አስሮ መላኩ አስቸግሮኛል፡፡”

የዘወረደ ምንባብ 2 (ያዕ.4÷6-ፍጻ. )

ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡

እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡

የዘወረደ ምንባብ 1 (ዕብ.13÷7-17)

የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘለዓለምም የሚኖር እርሱ ነውና፡፡ ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና፡፡ ድንኳኒቱን ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት ከእርሱ ሊበሉ የማይቻላቸው መሠዊያ አለን፤ ሊቀ ካህናቱ የሚሠዉትን እንስሳ ደም ስለ ኀጢአት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያቀርብ ነበርና፤ ሥጋውንም ከሰፈር ውጭ ያቃጥሉት ነበር፡፡ ስለዚህም ኢየሱስ ሕዝቡን በደሙ ይቀድሳቸው ዘንድ ከከተማ ውጭ ተሰቀለ፡፡ አሁንም ተግዳሮቱን ተሸክመን÷ ወደ እርሱ ወደ ከተማው ውጭ እንውጣ፡፡ በዚህ የሚኖር ከተማ ያለን አይደለም የምትመጣውን እንሻለን እንጂ፡፡ በውኑ እንግዲህ በሰሙ አናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን÷ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡