የሆሣዕና ምንባብ8(ሉቃ. 18፥35-ፍጻ.)

ከዚህም በኋላ ኢያሪኮ በደረሱ ጊዜ አንድ ዕውር በጎዳና ተቀምጦ ይለምን ነበር፡፡ የሚያልፈውንም ሰው ድምፅ ሰምቶ÷ “ይህ የምሰማው ምንድን ነው?” አለ፡፡ እነርሱም÷ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ያልፋል” ብለው ነገሩት፡፡ ድምፁንም ከፍ አድርጎ÷ “የዳዊት ልጅ ኢሱስ ሆይ÷ ማረኝ” አለ፡፡ የሚመሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን በጣም ጮኾ÷ “የዳዊት ልጅ ሆይ÷ ማረኝ” አለ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ቆመና ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ወደ እርሱም በደረሰ ጊዜ÷ “ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም÷ “ጌታ ሆይ÷ ዐይኖቼ እንዲያዩ ነው” አለው፡፡ ጌታችን ኢየስስም÷ “እይ፤ እምነትህ አዳነችህ” አለው፡፡ በዚያን ጊዜም አየ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ፤ ተከተለውም፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡