የሆሣዕና ምንባብ9(ማቴ. 9፥26-ፍጻ.)

የተአምራቱም ዝና በሀገሩ ሁሉ ተሰማ፡፡ ጌታችን ኢየስስም ከዚያ በአለፈ ጊዜ ሁለት ዕውራን÷ “የዳዊት ልጅ ሆይ÷ ራራልን” ብለው እየጮኹ ተከተሉት፡፡ ወደ ቤትም በገባ ጊዜ እነዚያ ዕውራን ወደ እርሱ መጡ፤ ጌታችን ኢየሱስም “ይህን ማድረግ እንዲቻለኝ ታምናላችሁን?” አላቸው፤ እነርሱም÷ “አዎን ጌታ ሆይ!” አሉት፡፡ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” ብሎ ዐይኖቻቸውን ዳሰሳቸው፡፡ ያንጊዜም ዐይኖቻቸው ተገለጡ፤ ጌታችን ኢየሱስም÷ “ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ” ብሎ አዘዛቸው፡፡ እነርሱ ግን÷ ወጥተው በዚያ ሀገር ሁሉ ስለእርሱ ተናገሩ፡፡

እነዚያም ከወጡ በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዲዳ ወደ እርሱ አመጡ፡፡ ያደረበትም ጋኔን በወጣ ጊዜ ዲዳ የነበረው ተናገረ፤ ሰዎችም “በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ያለ ከቶ አልተየም” እያሉ አደነቁ፡፡ ፈሪሳውያን ግን “በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” አሉ፡፡

ጌታችን ኢየሱስም በምኲራቦቻቸው እያስተማረ÷ የመንግሥት ወንጌልንም እየሰበከ÷ በሕዝቡም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በየከተማውና በየመንደሩ ሁሉ ተመላለሰ፡፡ ብዙ ሰዎችንም አይቶ አዘነላቸው፤ ደክመው ነበርና÷ እረኛ እንደሌላቸው በጎችም ተበትነው ነበርና፡፡ ያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “መከሩሰ ብዙ ነው፤ ሠራተኛው ግን ጥቂት ነው፡፡ እንግዲህ ለመከሩ ሠራተኛን ይጨምር ዘንድ የመከሩን ባለቤት ለምኑት፡፡”

 

የሆሣዕና ምንባብ10(ማቴ.21÷1-18)

ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦ÷ ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ፡፡ እንዲህም አላቸው፤ “በፊታችሁ ወደ አለችው መንደር ሂዱ፤ ያንጊዜም የታሰረች አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፍቱና አምጡልኝ፡፡ ምን ታደርጋላችሁ? የሚላችሁ ቢኖርም ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ÷ ያንጊዜ ይሰዱአችኋል፡፡” ይህም ሁሉ የሆነው በነቢይ እንዲህተብሎ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ “ለጽዮን ልጅ፡- እነሆ÷ የዋህ ንጉሥሽ በአህያይቱና በአህያይቱ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት”፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ጌታችን ኢየሱስ እንደ አዘዛቸው አደረጉ፡፡ አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፤ ልብሳቸውንም በላያቸው ጫኑ፤ ጌታችን ኢየሱስም በእነርሱ ላይ ተቀመጠ፡፡ ብዙ ሕዝብም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎችም ከዛፎች ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፡፡ በፊቱ የሚሄዱትና የሚከተሉት ሕዝብም÷ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ይጮሁ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ÷ “ከተማዪቱ ይህ ማነው?” እያለች ታወከች፡፡ ሕዝቡም÷ “ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ፡፡

ጌታችን ኢየሱስም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አባረረ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም መደርደሪያ÷ የርግብ ሻጮችንም ወንበር ገለበጠ፡፡ “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላይ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የሌባና የቀማኛ ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው፡፡ በቤተ መቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡ፤ አዳናቸውም፡፡ ያን ጊዜም የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ተአምራት÷ ልጆችንም በቤተ መቅደስ÷ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ” እያሉ ሲጮሁ ባዩ ጊዜ ደስ አላላቸውም፡፡ እነርሱም÷ “እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን?” አሉት፤ ጌታችን ኢየሱስም÷ “አዎን÷ እሰማለሁ÷ ከልጆችና ከሕፃናት አንደበት ምስጋናን አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ ያነበባችሁበት ጊዜ የለምን?” አላቸው፡፡ ትቶአቸውም ከከተማው ወደ ቢታንያ ሄደ፤ በዚያም አደረ፡፡

 

የሆሣዕና ምንባብ8(ሉቃ. 18፥35-ፍጻ.)

ከዚህም በኋላ ኢያሪኮ በደረሱ ጊዜ አንድ ዕውር በጎዳና ተቀምጦ ይለምን ነበር፡፡ የሚያልፈውንም ሰው ድምፅ ሰምቶ÷ “ይህ የምሰማው ምንድን ነው?” አለ፡፡ እነርሱም÷ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ያልፋል” ብለው ነገሩት፡፡ ድምፁንም ከፍ አድርጎ÷ “የዳዊት ልጅ ኢሱስ ሆይ÷ ማረኝ” አለ፡፡ የሚመሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን በጣም ጮኾ÷ “የዳዊት ልጅ ሆይ÷ ማረኝ” አለ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ቆመና ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ወደ እርሱም በደረሰ ጊዜ÷ “ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም÷ “ጌታ ሆይ÷ ዐይኖቼ እንዲያዩ ነው” አለው፡፡ ጌታችን ኢየስስም÷ “እይ፤ እምነትህ አዳነችህ” አለው፡፡ በዚያን ጊዜም አየ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ፤ ተከተለውም፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡

የሆሣዕና ምንባብ7(ማር. 10፥46-ፍጻ.)

 ወደ ኢያሪኮም ገባ፤ ከኢያሪኮም በወጣ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ብዙ ሰውም ነበረ፤ የጤሜዎስ ልጅ ዕውሩ በርጤሜዎስም በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር፡፡ የናዝሬቱ ኢየሱስ እንደ ሆነም ሰምቶ፥ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ” ብሎ ጮኸ፡፡ ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን ድምፁን ከፍ አደረገና፥ “የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ” አለ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ቆመና፥ “ጥሩት” አለ እነርሱም ዕውሩን ጠሩት፤ “በርታና ተነሥ፥ መምህር ይጠራሀል” አሉት፡፡ እርሱም ተነሥቶ ልብሱን ትቶ ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጣ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ምን ላደርግልህ ትሻለህ?” አለው፤ ዕውሩም፥ “መምህር ሆይ፥ እንዳይ ነው” አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም፥ “ሂድ፤ እምነትህ አዳነችህ” አለው፤ ወዲያውም አየ፤ በመንገድም ተከተለው፡፡

የሆሣዕና ምንባብ6(ማቴ. 20፥29-ፍጻ.

ከኢያሪኮም በወጣ ጊዜ ብዙ ሰዎች ተከተሉት፡፡ እነሆ÷ ሁለት ዕውራን በመንገድ አጠገብ ተቀምጠው ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስም ሲያልፍ ሰምተው፥ “አቤቱ፥ የዳዊት ልጅ፥ ይቅር በለን” እያሉ ጮኹ፡፡ ሕዝቡ ግን ዝም እንዲሉ ይቈጡአቸው ነበር፤ እነርሱ ግን፥ “አቤቱ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን” እያሉ አብዝተው ጮኹ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና፥ “ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ?” አላቸው፡፡ እነርሱም፥ “አቤቱ፥ ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ ነው” አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም አዘነላቸው፤ ዐይኖቻቸውንም ዳሰሳቸው፤ ወዲያውም አዩና ተከተሉት፡፡

የሆሣዕና ምንባብ5(ሉቃ.19÷1-11)

ጌታችን ኢየስስም ወደ ኢያራኮ ገብቶ በዚያ ያልፍ ነበር፡፡ እነሆ÷ የቀራጮች አለቃ ስሙ ዘኬዎስ የተባለ አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ባለጸጋ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስንም ያየው ዘንድ÷ ማን እንደ ሆነም ያውቅ ዘንድ ይሻ ነበር፤ የሰው ብዛትም ይከለክለው ነበር፤ ቁመቱ አጭር ነበርና፡፡ ወደ ፊቱም ሮጠ፤ ያየው ዘንድም በሾላ ላይ ወጣ፤ በዚያች መንገድ ያልፍ ዘንድ አለውና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ወደዚያ በደረሰ ጊዜ አሻቅቦ አየውና÷ “ዘኬዎስ ሆይ÷ ፈጥነህ ውረድ፤ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ አለኝና” አለው፡፡ ፈጥኖም ወረደ፤ ደስ እያለውም ወደ ቤቱ ይዞት ገባ፡፡ ሁሉም አይተው “ወደ ኀጢኣተኛ ሰው ቤት ሊውል ገባ” ብለው አንጐራጐሩ፡፡ ዘኬዎስም ቆመና ጌታችንን እንዲህ አለው÷ “ጌታዬ ሆይ÷ አሁን የገንዘቤን እኩሌታ ለነዳያን እሰጣለሁ፤ የበደልሁትም ቢኖር ስለ አንድ ፋንታ አራት እጥፍ እከፍለዋለሁ፡፡” ጌታችን ኢየሱሱም እንዲህ አለው÷ “ዛሬ ለዚህ ቤት ሕይወት ሆነ፤ እርሱ የአብርሃም ልጅ ነውና፡፡ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና፡፡” ይህንም ሲሰሙ፤ ምሳሌ መስሎ ነገራቸው፤ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦ ነበርና፤ እነርሱም የእግዚአብሔር መንግሥት ወዲያውኑ የምትገለጥ መስሎአቸው ነበርና፡፡

 

መፃጉዕ

                                           
                                                                                                                                                                                                                  በእመቤት ፈለገ
ልጆች በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት የዓብይ ጾም አረተኛ እሑድ መጻጉዕ
 ይባላል፡፡ ታሪኩም እንደዚህ ነው፡፡ በኢየሩሳሌም በር አጠገብ ቤተሳይዳ የምትባል የመጠመቂያ ቦታ ነበረች በዚያም ማየት የተሳናቸው፣ መራመድ የማይችሉ ብዙ በሽተኞች በመጠመቂያው ቦታ ተኝተው የውሃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ ልጆች የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃውን በሚያናውጠው ጊዜ÷ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ /ይድን/ ነበር፡፡ በዚያ ቦታም ከታመመ ሰላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር፡፡ ስሙም መጻጉዕ ይባላል፡፡ ልጆች መጻጉዕ እንዴት በሕመም እንደተሰቃየ አያችሁ?

ታዲያ ልጆች ጌታችን ኢየሱስ ያሰው በአልጋው ተኝቶ ባየ ጊዜ በበሽታ ብዙ ዘመን እንደቆየ አውቆ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ መጻጉዕም “አዎን ጌታዬ ሆይ ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያው የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም “ተነስና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያውኑ ያሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፡፡ ልጆች ታሪኩን በደንብ አነበባችሁ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጻጉዕን ከበሽታው እንደፈወሰው አነበባችሁ አይደል? ጎበዞች! እኛም በታመምን ጊዜ እንደመጻዕጉም የሚረዳን ሰው ባጣን ጊዜ እግዚአብሔር አምላካችን ይረዳናል፡፡
ደህና ሰንብቱ!

የመፃጉዕ ወንጌል(ዮሐ. 5÷1-24)

ከዚህም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል፤ አምስት እርከኖችም ነበሩአት፡፡ በዚያም ዕውሮችና አንካሶች÷ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃዉን በሚያናውጠው ጊዜ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበርና፡፡ በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ይህን ሰው በአልጋዉ ተኝቶ ባየ ጊዜ በደዌ ብዙ ዘመን እንደ ቆየ ዐውቆ÷ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ ድውዩም መልሶ÷ “አዎን ጌታዬ ሆይ÷ ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያዉ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው፡፡ ጌታችን ኢየስስም÷ “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያውኑም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ያች ቀንም ሰንበት ነበረች፡፡

አይሁድም የዳነውን ሰው÷ “ዛሬ ሰንበት ነው፤ አልጋህን ልትሸከም አይገባህም” አሉት፡፡ እርሱም መልሶ÷ “ያዳነኝ እርሱ፡- አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” አላቸው፡፡

አይሁድም÷ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?” ብለው ጠየቁት፡፡ ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና÷ “እነሆ÷ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” አለው፡፡ ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ” አላቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፤ “ሰንበትን የሚሽር ነው” በማለት ብቻ አይደለም፤ ደግሞም እግዚአብሔርን “አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል” በማለት ነው እንጂ፡፡

ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል፡፡ አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል፡፡ አብ ሙታንን እንደሚያስነሳቸው÷ ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል፡፡ አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ፡፡ ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም፡፡

የመፃጉዕ ምንባብ3(የሐዋ.3÷1-11)

ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት በአንድነት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ ከእናቱ ማኅፀንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው ነበር፤ ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሁል ጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚልዋት በመቅደስ ደጃፍ ያስቀምጡት ነበር፡፡ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም ወደ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው፡፡ ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኩር ብሎ ተመለከተውና “ወደ እኛ ተመልከት” አለው፤ ወደ እነርሱም ተመለከተ፤ ምጽዋት እንደሚሰጡትም ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ ጴጥሮስም÷ “ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ÷ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ” አለው፡፡ በቀኝ አጁም ይዞ አስነሣው፤ ያን ጊዜም እግሩና ቊርጭምጭምቱ ጸና፡፡ ዘሎም ቆመ፤ እየሮጠና እየተራመደም ሄደ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፡፡ ሕዝቡም ሁሉ እግዝአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፡፡ እርሱም መልካም በምትባለው በመቅደስ ደጃፍ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እንደ ሆነ ዐወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መገረምና መደነቅ ሞላባቸው፡፡

የመፃጉዕ ምንባብ2(ያዕ.5÷14- ፍጻሜ ምዕ.)

ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉ ቀሳውስትን ይጥራና ይጸልዩለት፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቅቡት፡፡

የሃይማኖት ጸሎትም ድውዩን ይፈውሰዋል፤ እግዚአብሔርም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል፡፡ እርስ በርሳችሁ ኀጢአታችሁን ተናዘዙ፤ እንድትድኑም ለወንድሞቻችሁ ጸልዩ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎቱ ብዙ ትረዳለች፤ ግዳጅም ትፈጽማለች፡፡ ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበር፤ እንደምንታመምም ይታመም ነበር፤ ዝናም እንዳይዘንም ጸሎትን ጸለየ፤ ሦስት ዓመት ከስድስት ወርም በምድር ላይ አልዘነመም፡፡ ዳግመኛም ጸለየ፤ ሰማይም ዝናሙን ሰጠ፤ ምድርም ፍሬዋን አበቀለች፡፡ ወንድሞቻችን ሆይ÷ ከእናንተ ከጽድቅ የሳተ ቢኖር÷ ከኀጢአቱ የመለሰውም ቢኖር÷ ኀጢአተኛውን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ራሱን ከሞት እንደ አዳነ÷ ብዙ ኀጢአቱንም እንደ አስትሰረየ ይወቅ፡፡

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድም የሐዋርያው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት ተፈጸመች፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡