ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ኅዳር 06/2004 ዓ.ም.
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች በላከው መልእክት ም.፬፥፲፪ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል በተረጎመበት ፲፪ኛው ድርሳኑ በዘመኑ የሚፈጸመውን የሰርግ ሥርዐት መሠረት በማድረግ ሰርግን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ትምህርትን ሰጥቶአል ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሰርግ ምክንያት የሚወጡትን ወጪዎችና ግርግርና ሁካታ አጥብቆ የሚቃወም አባት ነው ፡፡ በዚህም ጽሑፍ ይህን ወደማስተዋል ልንመጣም እንችላልን ፡፡ መልካም ንባብ
ስለዚህ እንዲህ ብሎ ያስተምራል ፡- ትዳር ምንድን ነው? ትዕይንት(ትያትር) ነውን ? አይደለም፡፡ ምንም እንኳ እናንተ ለትዳርና ለምሳሌው አክብሮት ባይኖራችሁ ትዳር ግሩም ምሥጢርና የታላቅ መንፈሳዊ ምሥጢር ምሳሌ ነው ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስተምር “ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው” ይልና ጨምሮ “እኔ ግን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ” ይላል ፡፡(ኤፌ.፭፥፴፪) ጋብቻ የቤተ ክርስቲያንና የክርስቶስ ምሳሌ ነው ፤ እንዲህ በከበረ ምሥጢር ላይ ዳንኪረኞችን በመጋበዝ ዝሙትን ታስተዋውቁበታላችሁን ? ነገር ግን ከእናንተ መካከል አንዱ እኔን፡- እንዲህ ስትል ደናግል ወይም ያገቡት አይጨፍሩ እያልክ ነው ፤ እንግዲያ እነርሱ በዚህ ሰርግ ላይ ካልጨፈሩ ማን ሊጨፍር ነው ? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል ፡፡ ማንም አይጨፍር ነው መልሴ ፡፡