«ወአድኀነ ሕዝቦ በመስቀሉ»

መስከረም 2002 ዓ.ም.

ክፍል አንድ

«ሕዝቡን በመስቀሉ አዳነ»
ዲ/ን ዘላለም ቻላቸው

በቤተክርስቲያናችን መስከረም 17 ቀን የመስቀል በዓል ይከበራል፡፡ እኛም በዚህ ትምህርት የመስቀሉን ነገር እና የበዓሉን ታሪክና አከባበር እንመለከታለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን የነገረ መስቀሉ መነሻው ነገረ ድኅነት ነውና ጥቂት ነገሮችን ስለዚያ እንበል፡፡

1.ነገረ ድኅነት

ነገረ ድኅነት አምላካችን እግዚአብሔር ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ሰው ሆኖ ተወልዶ እንዳዳነን የምንማርበት የትምህርት ክፍል ነው፡፡ ይህ ትምህርት በውስጡ አራት ዋና ዋና ነገሮች አካቷል፡፡በአጭር በአጭሩ እንመልከታቸው፤

1. እግዚአብሔር በቸርነቱ አዳምንና ሔዋንን ከፍጥረቱ ሁሉ አልቆ በራሱ አርአያና አምሳል ፈጥሮ ገነትን ያህል ቦታ አዘጋጅቶ በተድላ በደስታ እንዲኖሩ ሌሎችንም ፍጥረታት ሁሉ እንዲገዙ ሥልጣንንም ጭምር ሰጣቸው፡፡ /ዘፍ.1.25/፡፡ አዳምና ሔዋንም በገነት በነበሩባቸው ዓመታት ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገሩ በፍጥረታት ላይ ነግሠው አዳም ካህን ሆኖ በደስታ ይኖሩ ነበር፡፡ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ለ40 ቀናት ተነጋግሮ ሲመጣ እስራኤል «ፊትህን ሸፍንልን» እስኪሉት ድረስ ፊቱ ካበራ ዘወትር ከእግዚአብሔር ጋር ይኖሩ የነበሩት አዳምና ሔዋን ምን ያህል ብርሃናዊ ነበሩ ይሆን? አባቶቻችን «ከፀሐይ ሰባት እጅ ያበሩ ነበር» በማለት ክብራቸውን ይገልጡታል፡፡

2. አዳምና ሔዋን አትብሉ የተባሉትን ዕፅ በልተው የእግዚአብሔርን ሕግ በማፍረስ በደሉ፡፡ ከፈጣሪያቸው ጋር ራሳቸውን ለማስተካከል /አምላክ ለመሆን/ በማሰብና በመመኘታቸው ይቅርታ የማይገባውን ዓመጽ ፈፀሙ፡፡ በዚህም ምክንያት «ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ» /ዘፍ. 2:18 / ተብሎ አስቀድሞ በተነገራቸው ሕግ መሠረትም «በፀነሰሽ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛዋለሁ፣ በጭንቅ ትወልጃለሽ፣ . . .  ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፣ በሕይወት ዘመንህ ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህና አሜከላ ታበቅልብሃለች. . . »/ዘፍ.3.15-19/ ተብለው ተረገሙ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣሉ፤ ከገነት ተባረሩ፤ የሞት ሞት ተፈረደባቸው፤ ሞት ሰለጠነባቸው፡፡ አዳምና ሔዋን ከእግዚአብሔር የተለዩና የተዋረዱ ባሕርይ ያላቸው ስለነበሩ የሚወልዷቸው ልጆችም እንዲሁ ከእግዚአብሔር የተለዩና ባሕርያቸው የተዋረደ እነዚህ መከራዎች ሁሉ የሚደርሱባቸው ሆኑ፡፡

3. አዳምና ሔዋንም ሆኑ ልጆቻቸው ከዚህ ውድቀት ራሳቸውን ማዳን አልቻሉም ነበር፤ ምክንያቱም   አዳም፣ ሔዋንና ልጆቻቸው እንዲድኑ የበደሉን ካሣ በሞት የሚከፍል ሰው ያስፈልግ ነበር፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛና ትክክለኛ ስለነበር ካሣ ሳይከፈል ፍርዱ ስለማይሻር ነው፡፡ ከአቤል ጀምሮ የፈሰሰው የሰዎችና የነቢያት ደምም ካሣ መሆን አልቻለም፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ሁሉ ራሳቸው የተዋረደ ባሕርይ ያላቸውና ለመስዋዕትነት የማይበቁ በመሆናቸው ነው፡፡

4. እግዚአብሔር ቸርና ሩህሩህ ስለሆነ የፍጡሩ የሰው ሥቃይ ስላሳዘነው ከራሱ ጋር የሚታረቅበትን መንገድ አዘጋጀ፡፡ እግዚአብሔር በመለኮታዊ ባሕርይው መሞት ስለማይችል ሁኖና ሙቶ ካሣውን ለመክፈል ወስኖ ለአዳምና ለሔዋን ቃል ኪዳን ገባላቸው፡፡ ቀጠሮ ሰጣቸው፡፡ የዘመኑ ፍጻሜ /የቀጠሮው ቀን/ በደረሰ ጊዜ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል የእግዚአብሔር ቃል /ወልድ/ መጣ፤ ከነፍሷ ነፍስ ከሥጋዋ ሥጋ ነሥቶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ፡፡ ሰው ሆኖ ተወለደ፡፡ ነቢዩ አሳይያስ «በሰዎች ዘንድ የተናቀና የተጠላ የሕማም ሰውና ሥቃይ ያልተለየው ነበር፤ በእርግጥ እርሱ ደዌአችንን ወሰደ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ. . »/ኢሳ.53.3-4/ እንዳለው ከልደቱ እስከ ስቅለቱ እና ሞቱ ድረስ በርካታ መከራዎችን በመቀበል የበደላችንን ዋጋ ከፈለ፡፡ በመስቀል ላይ የሕይወት መሥዋዕትነት በመክፈል የሰው ልጆችን ከራሱ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አስታረቀ፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ያሬድ «ወሪዶ እመስቀሉ ቀጥቀጠ ኃይሎ በፀላኢ አርአየ ሥልጣኖ ለዕለ ሞት፤»  «ከመስቀሉ ወርዶ የጠላትን ኃይል ቀጠቀጠ፤ በሞትም ላይ ሥልጣኑን አሳየ» በማለት እንደተናገረው በሲኦል ለ5500 ዘመናት ተይዘው የነበሩ ነፍሳትን ነጻ አወጣቸው፡፡

 

2.ነገረ መስቀል

ከላይ እንደተመለከትነው ዓለም የዳነው ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ በተቀበለው ጸዋትወ መከራ እና በሞቱ የበደላችንን ዋጋ በመክፈሉ ከሆነ መስቀል ቤዛችን ነው፤መስቀል የነፍሳችን መድኅኒት ነው፤ ሕዝቡን በመስቀሉ አዳነ፤ በመስቀሉ ዳንን ስንል ምን ማለታችን ነው? ይህንን የምንለው ከሁለት ነገሮች አንጻር ነው፤

2.1. መስቀል እንደ ነገረ ድኅነት ዓርማ /ምልክት/

በመጀመሪያ ደረጃ መስቀል የክርስቶሰ የማዳኑ ሥራ እና የክርስቶስ መከራ ዓርማ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ «. . . መስቀል የህማም ምልክት ነው. . .» እንዳለው መስቀል የክርስቶስን ሕማም፣ መከራ ሞት እና የማዳን ሥራ የሚወክል ዓርማ ነው፡፡

ይህንን ለመረዳት ከሌላ ቀላል እና ግልጽ ከሆነ ነገር እንነሣ፡፡ ሀገር የሚለው ቃል /ጽንሰ ሐሳብ/ በጣም ሰፊና በርካታ በዓይን የሚታዩና በዓይን የማይታዩ ነገሮች የተካተቱበት ነው፡፡ ይህ እጅግ ሰፊና ረቂቅ የሆነ ነገር ግን በአንድ ነገር ይወከላል፤ በባንዲራ፡፡ ባንዲራ ሀገር በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ውስጥ የተካተቱትን ነገሮች ሁሉ ይወክላል፡፡ እንደ ቁብ ጨርቅ ቢሆንም ትርጉሙ ግን ሀገር ማለት ነው፡፡ ባንዲራን መውደድ፣ ለንዲራ መሞት ስንልም እንዲሁ ሀገርን መውደድ፣ ለሀገር መሞት ማለት ነው፡፡ ድርጅቶችም እንዲሁ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ዓርማ አላቸው፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በመጀመሪያ ደረጃ መስቀል የክርስቶስ የማዳኑ ሥራ የመከራው፣ የመስቀሉ፣ የመሞቱ ወካይ ዓርማ ምልክት ነው፡፡ መስቀሉን ስናየው፣ ስናማትብ፣ ስሙን ስንሰማው እነዚህ የጌታችንን መከራዎች የሚያስታውሰን ምልክት፣ ሁሉንም በመስቀል ላይ የተደረገውን ነገር ሁሉ የሚወክል ዓርማ ነው፡፡ በመስቀሉ አዳነን ስንልም በመስቀሉ ላይ በፈጸመው ቤዛነት አዳነን ማለታችን ነው፡፡

 

ይህ ምልክት እንዲኖር ያስፈለገበት ምክንያት ሰዎች እግዚአብሔርን ማምለክ ይችሉ ዘንድ ለመርዳት ነው፡፡ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የነበሩትን የመሥዋዕት ሥርዓቶች ያዘጋጀው፤ በሕዝቡ መካከል ለመገኘቱ ምልክት የሆነውን ታቦት የሰጠው. . . ሰዎች አምልኮታቸውን ለመፈጸም የሚታይ የሚዳሰስ ነገር ስላስፈለጋቸው ነው፡፡

በሐዲስ ኪዳንም በቤተክርስቲያን ያሉት ልዩ ልዩ ሥርዓቶች፣ ንዋያተ ቅዱሳት፣ ከዚሁ አንጻር የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን የሚገኘው የማይታይ ጸጋም በሚታይ አገልግሎት የሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በአጠቃላይ እግዚአብሔርን የምናመልከው ሰዎች ነንና ሁሉም የተደረገው ለሰዎች በሚሆን፣ ለሰዎች በሚረዳ መልኩ ነው፡፡

 

የመስቀሉም ነገር እንዲሁ ነው፡፡ የጌታችንን መከራ ስቅለት እና ሞት ክርስቲያኖች ሁል ጊዜ ማሰብ አለብን፡፡ ይህንን እንድናደርግ የሚያስችል፣ የረቀቀውን ጉልህ፣ የራቀውን ቀረብ የሚያደርግ እና ህሊናችንን የሚሰበስብ ዓርማ ተዘጋጀ፤ ይኸውም መስቀል ነው፡፡

ጌታም «መስቀሌን ተሸክማቸሁ ተከተሉኝ» ሲልም ከዚህ አንጻር ነው፤ መከራዬን፣ ስቃዬን፣ ሞቴን ተጋርታችሁ ማለቱ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል «ጥልን በመስቀሉ ገደለ» /ኤፌ. 2.16/ እኛም «መስቀል ቤዛነ፣ መስቀለ ጽንዕነ፣ መስቀል መድኀኒተ ነፍስነ አይሁድ ክህዱ፣ ንሠነሰ አመነ፣ እለ አመነ በኀይለ መስቀለ ደኀነ» ስንል የክርስቶስን መከራውን፣ መስቀሉን፣ ሞቱን እናምናለን፤ በዚህም ድነናል ማለታችን ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድም ከዚሁ አንጻር እንዲህ ይላል፡-

–    «መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም መሠረተ ቤተ ክርስቲየን» «መስቀል ለዓለሙ ሁሉ ብርሃን ነው፤ የቤተ ክርስቲያንም መሠረት ነው»

–    «በቀራንዮ ሐፍረተ መስቀል  ተዓገሰ ፣ ጊዜ ተፀልበቱ አዕረቅዎ ልብሰ በአፈ ኩናት ረገዝዎ  ከርሠ በዕፀ መስቀሉ……. መርዔተ ሐደሰ» «በቀራንዮ የመስቀል ሀፍረት ታገሰ፣ በስቅለቱ ጊዜ ከልብሱ ራቁቱን አደረጉት፣ በጦር ጐኑን ወጉት፣ በመስቀሉ መንጋውን አደሰ /አዲስ አደረገ/»

–    «በመስቀሉ አርሃወ ገነተ፤ መተሞዓ ኃይለ ሥልጣኑ ለሞት» «በመስቀሉ ገነትን ከፈተ፤ የሞተ ኃይልም ድል ተደረገ»

 

–    «ትዌድሶ መርዓት ቤተ ክርስቲያን እንዘ ትብል በመስቀልከ አብራህከ ሊተ እንዘ ግድፍተ ወኀድግት አነ ምራቀ ርኩሳን ተዓገስከ በእንቲአየ ሕይወተ ርከብኩ በትንሳኤከ ጸጋ ነሣዕኩ ወደቂቅየኒ ገብኡ ውስተ ህጽንየ በመስቀልከ አብራኀከ ሊተ በመስቀልከ አድኅንከ ኩሎ ዓለመ» «ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን /ጌታን/ እንዲህ እያለች ታመሰግነዋለች የተተውኩና የተጣልኩ ሁኜ ሳለ አብርተህልኛል፤ ስለ እኔ ብለህ የርኩሳንን ምራቅ ታግሰሃል፤ ከትንሳኤህ ህይወት አገኘሁ፤ ፀጋንም አገኘሁ፤ ልጆቼም ወደ እቅፌ ገቡ፤ በመስቀልህ አበራህልኝ፤ በመስቀልህም ዓለምን ሁሉ አዳንህ»

በእነዚህ ሁሉ ‹‹… በመስቀልህ…›› ስንል ‹‹… መከራ በመቀበልህ፣ በመሰቀልህ፣ በሞትህ…›› ማለታችን ነው፡፡

መስቀል ምንን ያስታውሰናል?

መስቀልን ስናይ፣ መስቀልን ሰናስብ፣ ስሙንም ስንጠራ የሚከተሉትን ነገሮች እናስታውሳለን፡-

ሀ. በመስቀል አምላክን ለእኛ ያለውን ፍቅር እናስታውሳለን

 

ነቢዩ ኢሳይያስ «እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጎድን» /ኢሳ. 53-6/ እንዳለው እኛ የሰው ልጆች በሀጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይተን፣ በሞት ጥላ ስር በመከራና በችግር እንኖር ነበር፡፡

 

«በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን ወዷል» /ዮሐ. 3-16/ እንደተባለው አምላካችን እኛን ለማዳን አንድያ ልጁን ወደዚህ ምድር ልኮና የሞት መስዋዕትነት ከፍሎ አድኖናል፡፡ «ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል» /ሮሜ. 5.8/ ምክንያቱም «ስለ ወዳጆቹ ህይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም፡፡» /ዮሐ. 15-13/

ስለዚህ መስቀል ስለ እኛ ሲል በመስቀል ላይ የሞትን ጽዋ የተቀበለው አምላካችን ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያስታውሰን ምልክት ነው፡፡

 

ለ. በመስቀል ኀጢአታችንን እናስታውሳለን፤

ጌታችን በመስቀል የተሰቀለው እኛ ኃጢአተኞች በመሆናችን ነው፡፡ ስለዚህ መስቀል ኀጢአታችንን የሚያስታውሰን ምልክት ነው፡፡ ይህንን ስናስብም ቅዱስ ጳውሎስ «በዋጋ ተገዝታችኋልና የራሳችሁ አይደላችሁም፤» እንዳለው /1ኛ ቆሮ.6-20/ ከኀጢአት ባርነት ነጻ የወጣነው ዋጋ ተከፍሎብን እንደሆነ አስበን እግዚአብሔርን በማመስገን፣ በትህትና እና ራስን ዝቅ በማድረግ እንሞላለን፡፡

 

ሐ. መስቀል የእግዚአብሔርን ቅን ፈራጅነት ያስታውሰናል፤

መስቀል የእግዚአብሔር ፍቅር እና ቅን ፍርድ በአንድ ላይ የተደረጉበት አደባባይ ነው፡፡ አዳም በበደለ ጊዜ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ሞት ተፈረደበት፤ እግዚአብሔር የሰው ልጆች ወዳጅ ስለሆነ ሊያድነው ቢወድም፣ ፍርዱ ሁል ጊዜ ትክክለኛ ስለነበረ ደግሞ ስለ በደሉ ካሳ ሳይከፈል አላዳነውም፡፡ ስለዚህ ራሱ መጥቶ መስዋዕት በመሆን የበደሉን ሳካ በመስቀል ላይ ከፈለ፤ ፍቅሩና ቅን ፍርዱ በአንድ ላይ ተገለጠ፡፡

መ. መስቀል የጌታችንን ሕማማትና ሞት ያስታውሰናል፤

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበደላችንን ዋጋ የከፈለው ሊነገሩ የማይችሉ ሕማማትን ተቀብሎ፣ ተሰዶ፣ ተሰድቦ፣ ተዋርዶ፣ ተገርፎ፣ የሃጢአተኞች ምራቅ ተተፍቶበት፣ መስቀል ተሸክሞ ተራራ ወጥቶ፣ እጆቹና እግሮቹ ተቸንክረው ከመስቀል ላይ በሕይወቱ ለ3 ሰዓታት በሞቱ ለ2 ሰዓታት ቆይቶ፣ የሞትንም ጽዋ ቀምሶ ነው፡፡

መስቀል እነዚህን ሁሉ የጌታችንን ሕማማትና ሞቱን የሚያስታውሰን ምልክት ነው፡፡

 

ሠ. መስቀልን ስናይ ይቅር መባላችንን እና ድኅነታችንን እናስባለን፡፡

መስቀልን ስንመለከት ኀጢአቶቻችን እንዴት ይቅር እንደተባሉና ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ «አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁም ይቅር በላቸው» ማለቱን እናስታውሳለን፡፡ /ሉቃ.13-34/

ዳግመኛም መስቀልን ስንመለከት ጌታችን በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ በዲያብሎስ አገዛዝ ስር የነበሩ ነፍሳትን ነጻ እንዳወጣቸው፣ እኛንም በአዳም በደል ምክንያት ከመጣብን የባሕርይ ድካም እንዳዳነን እናስባለን፡፡

አሁንም መስቀልን ስንመለከት በጌታ ቀኝ ተሰቅሎ የነበረውንና ድኅነትን ያገኘውን ወንበዴ፤ ጌታችን በፍቅሩ ወደ እርሱ እንደሳበው፣ በቸርነቱ በደሉን ሁሉ ይቅር ብሎ ወደ ገነት እንዳስገባው እናስባለን፣ እኛም በተስፋ እንሞላለን፡፡

ረ. መስቀል የኀጢአት ደመወዝ ሞት መሆኑን ያስታውሰናል፤

«በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ በክርስቶስ ህያዋን ሆንን» /ኤፌ.2-51/ እንደተባለው ጌታችን እኛን ከሞት ለማዳን በመስቀል ተሰቅሎ ለመሞት ያበቃው እኛ በመበደላችን፣ የበደል /የኀጢአት/ ደመወዝ ደግሞ ሞት በመሆኑ ነው፡፡ መስቀል ይህንን ያስታውሰናል፡፡

 

ሰ. መስቀል ትንሳኤንና ዳግም ምጽአትን ያሳስበናል፤

የጌታችን መስቀልና ሞት ስናስታውስ አብረን ትንሳኤውን እናስባን፤ በእርሱ ትንሳኤ ደግሞ የእኛን ትንሳኤ እናስባለን፡፡

መስቀል ዳግም ምጽአትንም ያስታውሰናል፡፡ ጌታችን ስለ ህልፈተ ዓለምና ዳግም ምፅአት ሲያስተምር እንዲህ ብሏል «የዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት /መስቀል/ በሰማይ ይታያል…. የሰው ልጅም በሰማይ ደመና ሁኖ በኀይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል» /ማቴ.24-30/ ዳግም ምጽአትን ስናስብ ለፍርድ በፊቱ እንደምንቆምም እናስታውሳለን፡፡

 

ሸ. መስቀል መስቀልን እንድንሸከም መታዘዛችንን ያስታውሰናል፤

መስቀል ጌታችን «ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ» /ማቴ.16-24/፣ «የራሱንም መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ደቀመዝሙሬ ሊሆን አይችልም» /ሉቃ.14-27/ ብሎ ያስተማረንን ትምህርት ያስታውሰናል፡፡

2.2. መስቀሉ እንደ የማዳኑ ሥራ መሣርያ

በሁለተኛ ደረጃ መስቀል ስንል ጌታችን ዓለሙን ባዳነበት ጊዜ እንደ መሣሪያ የተጠቀመበትን ዕፀ መስቀል /የእንጨት መስቀል/ ማለታችን ነው፡፡ በዚህ ሥር ሁለት ዓይነት መስቀሎችን እንመለከታለን፡፡

2.2.1 በቀራንዮ የተተከለው ጌታ የተሰቀለበት የመጀመሪያው መስቀል

 

በዓለም ታሪክ የተለያዩ አስደናቂ ታሪኮች የተሰሩባቸው ቁሶች /የነገስታት የጦር ዕቃዎች፣የታላላቅ ሰዎች አልባሳት፣ መኪናዎች፣ ዙፋኖች፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣…./ በክብር በቤተ መዘክሮች ይቀመጣሉ፤ ከበድ ያለ ዋጋም አላቸው፡፡

ዕፀ መስቀል ጌታ የሰው ልጆችን ያዳነበት መሳርያ፤ ክርስቶስ የተሰዋበት መሠዊያ፣ ድኅነት የተፈፀመበት አደባባይ ነው፡፡ የጌታችን ደም የፈሰሰበትና በደሙ የተቀደሰ፣ የከበረ፣ የተለየ ንዋይ /ሃብት/ ነው፡፡ እንግዲህ በዓለም ታሪክ የተሰራባቸው ዕቃዎች ከተከበሩ ይህ ድኅነት ነፍስ የተገኘበት ንዋይ ምን ያህል ይከብር?

ስለዚህ ዕፀ መስቀሉ ድኅነት የተፈፀመበት መሣሪያ ነውና እናከብረዋለን፣ እንሳለመዋለን፡፡ይህ መስቀል በክርስቶስ ደም የተባረከና የከበረ ስለሆነ የበረከት ምንጭ ሆኗል፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር /በመጋቢት 10 ቀን/  እንደተጻፈውም ድውያንን ፈውሷል፤ ሙታንን አስነስቷል፡፡

2.2.2 ዛሬ ከእንጨት /ዕፅ/፣ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከብረት እና ከተለያዩ ነገሮች የሚዘጋጁ መስቀሎች

 

እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው አንድ ታቦት ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ታቦታትን እንዴት እንደሚሠራና እንደሚባርካቸው ግን ነግሮታል፡፡ ይኸውም ሰዎች እየበዙ ሲሄዱ በተለያዩ ቦታዎች ታቦታት ማስፈለጋቸው ስለማይቀር ለሁሉም የሚሆን ይሆን ዘንድ ነው፡፡ ዛሬም በዚሁ መሠረት እንሰራለን፡፡

የመስቀልም ነገር እንዲሁ ነው፡፡ ጌታ የተሰቀለበትን የመጀመሪያ መስቀል ሁሉም ሊያገኘው አይችልም፤ ስለዚህ በየቦታው ያሉ ምዕመናን ከመስቀል የሚገኙ ጥቅሞችን ያገኙ ዘንድ መስቀሎች በየቦታው የሚገኙበት መንገድ ተፈጠረ፡፡

 

በዚህ መሠረት መስቀሎች ከተለያዩ ቁሳቁሶች ይዘጋጃሉ፡፡ ጌታችን የተሰቀለበት መስቀል የተቀደሰው በላዩ ላይ በፈሰሰው ደመ መለኮት ነው፡፡ ዛሬ ያሉት መስቀሎች ደግሞ ይህንን ነገር መስቀል በሚያወሱ ጸሎቶች ይበረኩና ይከብራሉ፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው መስቀል የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ይሰጣሉ፡፡ ማለትም አንድም የመከራ መስቀሉና ዓመቱ አርማ ይሆናሉ፤ አንድም የበረከት ምንጭ ይሆናሉ፤ አጋንንትን ያወጣሉ፤ ድውያንን ይፈውሳሉ፡፡