ከትርፍ ነፃ የሆኑ የምስልና የድምጽ ሲዲዎች እንደሚሠራጩ ተገለጠ፡፡

በዲ/ን ኅሩይ ባየ
ቀን 05/03/2004ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል የተዘጋጁ 3 ሺህ የሚሆኑ የምስልና የድምጽ ሲዲዎች ኅዳር 8 ቀን 2004 ዓ.ም በማኅበሩ ጽ/ቤት እንደሚሠራጭ የምክረ ሐሳቡ አስተባባሪ ኢንጂነር ሙሉጌታ ጌትነት አስታወቁ፡፡

ኢንጅነር ሙሉጌታ እንደገለጡት የምስልና የድምጽ ሲዲዎችን ለማግኘትና ለማሠራጨት ምንም ዐይነት ትርፍ ታሳቢ ሳይደረግ የሲዲውን ዋጋ ብቻ በመሸፈን ማግኘት ይቻላል፡፡ በማያያዝም የሥርጭቱ ዋና ዓላማ ስብከተ ወንጌልን በተፋጠነ መንገድ ለምእመናን ማዳረስ ሲሆን በገበያ ላይ የሚገኙት የምስልና የድምጽ ሲዲዎች የምእመናንን ምጣኔ ሀብት የሚጎዱ በመሆናቸው በቀላሉ ቃለ እግዚአብሔር የሚስፋፋበትን መንገድ ለማመቻቸት፣ የተሐድሶ መናፍቃን ስሑት ትምህርቶች በሕዝበ ክርስቲያኑ ሰርገው ስለገቡ ትክክለኛ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ያላቸውን የስብከት ሲዲዎች ምእመናን እንዲያገኙና ስለ ሃይማኖታቸው እንዲያውቁ ለመደገፍ፣ በከተማ የሚኖሩ ጥቂት ምእመናን የመካነ ድር አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቢሆኑም አገልግሎቱ ውድና ዝቅተኛ ፍጥነት ስላለው የምስልና የድምጽ ዝግጅቶችን መመልከትና መስማት ስለማይችሉ ችግሩን አስወግዶ ተደራሽነትን ለማስፋፋት እንዲቻልና የቪሲዲ አገልግሎት ከገጠር እስከ ከተማ እየተስፋፋ በመምጣቱ ንጹህ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችን ለሁሉም እንዲዳረስ ለማድረግ እንደሆነ አስተባባሪው አስገንዝበዋል፡፡

ስርጭቱ እስከ ሦስት ዙር የሚቀጥል ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ለአዲስ አበባ ምእመናን ይከፋፈላል፡፡ በሁለተኛውና በሦስተኛው ዙር የሚከናወኑት ስርጭቶች ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጭ ወደ ማእከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች እንደሚላኩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስርጭቱን በተመለከተ ራሱን የቻለ ኮሚቴ እንደተዋቀረም ተጠቁሟል፡፡

የምስልና የድምጽ ትምህርቶች የተዘጋጁት በማኅበረ ቅዱሳን የምስልና የድምጽ ክምችት ክፍል በተለያዩ ዘመናት የተቀረጹ የሊቃውንት ትምህርቶች፣ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል በተለያዩ መርሐ ግብሮች የተቀረጹና በአዲስ አበባ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤት የተቀረጹ ትምህርቶች እንደሆኑ ተገልጧል፡፡ ዝግጅቱ ከትርፍ ነፃ በሆነ መልኩ ተዘጋጅቶ የሚሠራጭ በመሆኑ ምእመናን በቀላሉ እንዲጠቀሙበት ማኅበሩ ጥሪውን ያስተላልፋል ሲሉ አስተባባሪው አሳስበዋል፡፡