weddingpic

ሰርግ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

ኅዳር 06/2004 ዓ.ም.

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች በላከው መልእክት ም.፬፥፲፪ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል በተረጎመበት ፲፪ኛው ድርሳኑ በዘመኑ የሚፈጸመውን የሰርግ ሥርዐት መሠረት በማድረግ ሰርግን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ትምህርትን ሰጥቶአል ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሰርግ ምክንያት የሚወጡትን ወጪዎችና ግርግርና ሁካታ አጥብቆ የሚቃወም አባት ነው ፡፡ በዚህም ጽሑፍ ይህን ወደማስተዋል ልንመጣም እንችላልን ፡፡ መልካም ንባብ

ስለዚህ እንዲህ ብሎ ያስተምራል ፡- ትዳር ምንድን ነው? ትዕይንት(ትያትር) ነውን ? አይደለም፡፡  ምንም እንኳ እናንተ ለትዳርና ለምሳሌውweddingpic አክብሮት ባይኖራችሁ ትዳር ግሩም ምሥጢርና የታላቅ መንፈሳዊ ምሥጢር ምሳሌ ነው ፡፡ ቅዱስ    ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስተምር “ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው”   ይልና ጨምሮ “እኔ ግን ስለ ክርስቶስና    ስለ  ቤተ ክርስቲያን እላለሁ” ይላል   ፡፡(ኤፌ.፭፥፴፪) ጋብቻ የቤተ ክርስቲያንና   የክርስቶስ ምሳሌ ነው ፤  እንዲህ በከበረ    ምሥጢር ላይ ዳንኪረኞችን በመጋበዝ   ዝሙትን ታስተዋውቁበታላችሁን ? ነገር   ግን  ከእናንተ መካከል አንዱ እኔን፡- እንዲህ ስትል ደናግል ወይም ያገቡት አይጨፍሩ እያልክ ነው ፤  እንግዲያ እነርሱ በዚህ ሰርግ ላይ ካልጨፈሩ ማን ሊጨፍር ነው ? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል ፡፡ ማንም  አይጨፍር ነው መልሴ ፡፡

በአሕዛብ ዘንድ ይህን በመሰሉ ሥርዐቶቻቸው ዳንኪረኞች ዳንኪራቸውን ያቀርባሉ፡፡ በእኛ ግን ማንኛውም ምሥጢራት ሲከናወኑ በጸጥታ፣ በትሕትናና  በጥሩ ሥነምግባር እንዲሁም በመልካም ሥርዐት ነው፡፡ ይህ የጋብቻ ሥርዐት አመንዝሮች ከተጠሩበት እግዚብሔርን የማይፈሩ ከተጋበዙበት እንዴት ብለን ነው መንፈሳዊ ጋብቻ ብለን ልንጠራው የምንችለው ? እንዲህ ከሆነ እንዴት ተብሎ ነው ሁለቱ አካላት አንድ ሆነዋል ልንል የምንችለው ?

ክርስቶስ በተገኘበት ጋብቻ ግን ዳንኪራ የለም የእምቢልታም ድምፅ አይሰማበትም፡፡ ነገር ግን ግሩም የሆነ ጸጥታ የሰፈነበት፣ በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዐት የሚከናወን ነው፡፡ በዚህ ሥርዐት  አንድ አካል ወደመሆን ሲመጡ አንድነታቸው ሕይወት አልባ ፍጥረታት እንደሚኖራቸው አንድነት ወይም በዚህ ምድር የሚታየውን ዓይነት አንድነት አይደለም፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ሆነው አንድ ይሆናሉ፡፡ ይህ ታላቅ የሆነ ምሥጢር በሚከናወንበት ሥፍራ እንደ አራዊት ታላቅ ሁካታና ረብሻ እንዲሁም ነፍስን የሚያሳድፉ ታላቅ የሆነ በደል ይፈጸማልን ?

ሁለቱ አንድ አካል በመሆናቸው በዚህ ያለውን የፍቅርን ምሥጢር አስተውል ፡፡ እነዚህ ሁለት አካላት ሁለትነታቸውን ይዘው የሚቀጥሉ ከሆነ ብዙ ሊሆኑ አይችሉም ፡፡ ነገር ግን አንድ ወደመሆን ሲመጡ ብዙዎች ይሆናሉ ፡፡ ከዚህ ምን እንማራለን ? የትዳርን ታላቅነት አይደለምን ? ሥላሴ ሁለት የሆነው አካል አንድ አድርጎ ፈጠረው ስሙንም ሰው አለው፡፡ ይህን አንድ የሆነው አካልንም ሁለት በማድረግ ገለጠው ፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ አካላት ሁለት ቢሆኑ የእግዚአብሔር ፈቃድ  ግን አንድ ይሆኑ ዘንድ ነበር ፡፡

በዚህም ምክንያት አንዱ አምሳሉን ለመውለድ ብቻውን ብቁ እንዲሆን አላደረገውም ፡፡ ስለዚህ ከተቃራኒው አካል ጋር አንድነትን ላልመሠረተ ሰው አንድ አካል የሚባለው ስያሜው አይሰጠውም ነገር ግን የሌላኛው ግማሽ አካል ይባላል ፡፡ ለዚህም ምስክሩ ልጅን መውለድ አለመቻሉ ነው ፡፡ ይህ እግዚአብሔር አስቀድሞ የሠራው ሥርዐት ነው፡፡ የጋብቻን ምሥጢር አስተዋላችሁን ? አስቀድሞ አንድ አድርጎ ፈጠራቸው በኋላም ነጣጠላቸው ፤ እንደገና ሁለት የነበሩትን እነዚህን ወገኖች ወደ አንድነት አመጣቸው ፡፡ እንዲህም አድርጎ ስለሠራው ሰው በትዳር አንድ ከሆኑ ወገኖች እንዲፈጠር ሆነ ፡፡

ባልና ሚስት ሁለት አካላት አይደሉም ነገር ግን አንድ አካል ናቸው ፡፡…. ይህን “ሰውን በአርዓያችንና በአምሳላችን እንፍጠር …ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍ.1፡27) በሚለው ቃል ማረጋገጥ ይቻላል  ፡፡ ባል ራስ ነው ፤ ሚስት ደግሞ ቀሪው አካል ናት ፡፡ ስለዚህ አንዱ የደቀመዝሙርነት ማዕረግ ሲኖረው አንዱ የመምህርነት ቦታ ይይዛል አንዱ መሪ ሲሆን ሌላው ደግሞ ታዛዥ አደረገው ፡፡ ሔዋን ከአዳም ጎን ትገኝ እንጂ ወደ ኋላ መለስ ብለን የእርሱዋን ልደት ስንመረምረው አንድ አካል እንደነበሩ ማስተዋል እንችላለን  ፡፡በዚህ ምክንያት አንድ አካል እንደሆኑ ለማስረዳት ሲል እግዚአብሔር አምላክ ሴቲቱን ረዳት አላት፡፡ (ዘፍ.2፡18) በአንድነት ከመኖራቸውና አባትና እናት ከመሆን ባለፈ አንድ አካል በማድረግ አከበራቸው፡፡ (ዘፍ.2፡24)

በሌላ መልኩ ደግሞ አባት ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ የራሳቸውን አካል አግኝተው በመጣመራቸው እጅግ ደስ ይሰኛል፡፡ አባት ምንም ሀብት የተረፈው ባለጠጋ ቢሆን ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ ያላገቡ  ከሆኑ ውስጡ ምንም ዓይነት መረጋጋት አይኖረውም፡፡ ይህን ታግሶ መኖርም አይቻለውም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ልጅ ከእናቱ አካል ተከፍሎ የተወለደ ቢሆን በዚህ ምድር ዘሩ እንዲቀጥል ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ስለዚህም በራሱ ሙሉ አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ነቢዩ ሚልክያስ “እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው ምንድን ነው? ዘር አይደለምን? (ሚል.፪፥፲፭) ይለናል፡፡

እንዴት ነው ታዲያ አንድ ሥጋ ወደ መሆን የሚመጡት ? እጅግ ንጹሕ የሆነን ወርቅን ማግኘት ከፈለግህ ወርቅህን ከሌላ ወርቅ ጋር ትቀይጠዋለህ፤ ከእነዚህም አንድነት ልዩ የሆነ ወርቅ ይገኛል፡፡ በዚሁ መልክ እናት በደስታ ዘርን ተቀብላ ከራሱዋ ጋር በማዋሐድ፣ ፅንሱን በመመገብና እንክብካቤ በማድረግ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም እንዲመጣ የራሱዋን ድርሻ ትወጣለች፡፡ልጅ እንደ ድልድይ ነው ፡፡ በእርሱም ምክንያት ሦስቱ አንድ ሥጋ ይባላሉ ፡፡ ልጅ ሁለቱ አካላት ፍጹም አንድ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ፡፡ በመካከላቸው ባለው ታላቅ ወንዝ ምክንያት የተለያዩ ከተሞች በወንዙ ላይ በሚሠራው ድልድይ ምክንያት ሁለት መሆናቸው ቀርቶ አንድ እንዲሆኑ እንዲሁም ልጅም እንዲህ ነው ፡፡

ልጅ በፊት በባልና በሚስት መካከል የተፈጠረውን አንድነት ይበልጥ ያጠናክረዋል ፡፡ ለባልና ሚስት ድልድይ የሆነው ልጅ የሁለቱ ተዋሕዶ ውጤት ነውና ፡፡ ራስና ቀሪው አካል በአንገት አንድ እንዲሆን ፣ እንዲሁ ልጅም በባልና በሚስት መካከል ሆኖ በእነርሱ መካከል ያለውን አንድነት ይበልጥ ያጠብቀዋል ፡፡ ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸውን በልጅ ምክንያት ይበልጥ እየጠበቀ ይመጣል ፡፡

እንዲሁም ዘማርያን በአንድነት ሲዘምሩ ዝማሬው አንድ ሆኖ ይወጣል ፡፡ ወይም ሁለት ወገኖች እጃቸውን እርስ በእርሳቸው ቢያቆላልፉ ከእንግዲህ አንድ እንጂ ሁለት አይደለንም ማለታቸው እንደሆነ እንዲሁ ባልና ሚስትም በአንድነታቸው በሚፈጠሩት በልጅ በኩል ፍጹም የሆነ አንድነትን ይመሠርታሉ ፡፡ ስለዚህ ጌታችን ግሩም በሆነ ቃሉ “ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ አለ” በተለይ በልጆቻቸው ፡፡ እንዲህ ሲባል ባልና ሚስት ልጅ ካልወለዱ ሁለት እንደሆኑ አይቀጥሉም ማለት ነውን ? በፍጹም አይደለም ፤ ሁለቱ በሥጋ ሲተባበሩ አንድ አካል ወደ መሆን ይመጣሉ ፡፡ የሽቶ ዘይትን ከሌላ የሽቶ ዘይት ጋር ሲደባልቁት አንድ እንዲሆኑ ከተቀየጡም በኋላ አንድ የሽቶ ዘይት እንዲሆኑ እንዲሁ በዚህም እንዲሁ ነው ፡፡

እኔ አሁን እንዲህ በግልጽ ስለዚህ ጉዳይ በመናገሬ አንዳንዶች ነውር ነው በማለት ትምህርቴን እንደሚጠየፉት እረዳለሁ ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው ? ይህን አሁን የምናገረውን እንደ ብልግና ንግግር ስለሚቆጥሩት ነው ፡፡እነዚህ ወገኖች በትዳር ውስጥ የሚፈጠረውን እንደዚህ ላለው አንድነት ልዩ የነቀፋ ስም ይሰጡታል (ብልግና ይሉታል) ፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን”(ዕብ.፲፫፥፬) ብሎ አስተምሮናል ፡፡

ስለምን እናንተ ክቡር የሆነውን እንደ ነውር ፣ ንጹሕ የሆነውን እንደ ርኩስ ትቆጥሩታላችሁ ? ይህ ጋብቻን እንደ ርኩሰት የሚቆጥሩትና በራሳቸው አካል ላይ ዝሙትን የሚፈጽሙ የከሃድያን አመለካከት ነው፡፡ ስለዚህም ነው ይህን ክፉ አስተሳሰብ ለማጥራትና ወደ ቀድሞው ክብሩ ለመመለስ ስል በዚህ መልክ ያስተማርኩት፡፡ በዚህም እስተምህሮ የከሃድያን አፍ ይዘጋል፡፡

እነርሱ የእግዚአብሔርን ድንቅ ስጦታንና የልደታችን መሠረት የሆነውን ተራክቦን ሲነቅፉት ይሰማሉ፡፡

ይህን የመገኛችን ምንጭ የሆነውን ተራክቦ እንደ ቆሻሻና እንደማይጠቅም ረብ የለሽ ከንቱ ነገር አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ስለዚህ እኛ ይህን አስተምህሮ ከዚህ ዓይነት አመለካከት ንጹሕ ልናደርገው ይገባናል፡፡ተወዳጆች ሆይ ይህ ጉዳይ ሲነሣ እንደሚጠየፉት ከሃዲያን እንድንሆን አልሻም፤ ይልቁንስ ከእነርሱ አጸያፊ ሥራ ትሸሹ ዘንድ እመክራችኋለሁ፡፡ ነገር ግን በዚህ እነርሱን የምትመስሉዋቸው ከሆነ በቀጥታ እግዚአብሔርን እየተሳደባችሁ ነው፡፡

ትዳር ለቤተ ክርስቲያን የተፈጸመላት ምሥጢር ምሳሌ እንደሆነ ላስረዳችሁን? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የራሱ ሲያደርጋትና በመንፈሳዊ ተዋሕዶ ከእርሱዋ ጋር አንድ ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ “እንደ ንጽሕት ድንግል” ይልና “እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለውና” ይለናል፡፡ (፪ቆሮ.፲፪፥፪) ታዲያ እኛ ምን ሆንን ? የእርሱ የአካል ሕዋሳቶችና “ሥጋው” ሆንን፡፡ ይህን ሁሉ በማስተዋል ታላቅ ምሥጢር የሆነውን ትዳርን ከማቃለል እንቆጠብ፡፡ ሰርግ ማለት የክርስቶስ በሰዎች መካከል ሰለመገኘቱ የሚመሰልበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ ታላቅ የሆነው ይህ ምሥጢር በሚፈጸምበት ቦታ ስካር የሚገባ ነውን? ንገረኝ  የንጉሥ ምስል በቆመበት ስፍራ ሆነህ እርሱን ማዋረድ ትጀምራለህን? ይህን ፈጽሞ አታደርገውም፡፡

አሁን ግን ሰርግ ሲሲረግ  ሰርጉ ለተመሰለበት ምሳሌ ተገቢውን አክብሮት ከመስጠት ይልቅ ቦታውን የኃጢአት መፍለቂያ ምንጭ አድርገነዋል፡፡ ሥርዐቱ ሙሉ ለሙሉ ተለውጦ ሕገወጥ ሥራዎች የሚፈጸሙት ሥርዐት ሆኗል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸው” አላለንምን? እንዲሁም “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ፡፡” (ኤፌ.፭፥፬፤፬፥፳፱) ብሎ አላስተማረንምን? አሁን ግን በዚህ ታላቅ በሆነ ምሥጢር ላይ የስንፍና ንግግር፣ ዋዛ ፈዛዛ ነገሮች፣ ፌዝና ቀልዶች ሞልተውበታል፡፡

እነዚህ ከንቱ ነገሮች በቀላሉ የሚቀርቡም አይደሉም  እኮ እነዚህ ከንቱ ነገሮች እንደ ጥበብ ተቆጥረው በአቅራቢዎቻቸው ተቀናብረው በሰርጉ ለታደሙት ይቀርባሉ፡፡ ይህንንም ለሚያቀርቡ ሰዎችም ታላቅ ክብርና  ምስጋና ይሰጣቸዋል፡፡ ይገርማል  ኃጢአት እንደ ጥበብ ተቆጠረ፡፡ ከዚህም በላይ ኃጢአትን ለእኛ የሚያስተዋውቁንን ወገኖች ትዕይንት የምንከታተለው  ትኩረት ሰጥተንና በጸጥታ ነው፤ ከአንደበታቸው የሚያወጡትንም ቃል በአጽንዖት በመስማት ጭምር እንጂ እንዲያው በከንቱ አናዳምጣቸውም፡፡ ስለዚህ ዲያብሎስ በዚህ የሰርግ ቤት ለእርሱ ወታደሮች ይሆኑ ዘንድ ሠራዊቶችን ይመለምላል፡፡ ስካር ባለበት ቦታ ዝሙት አለ፡፡ ከንቱ ንግግር ባለበት ቦታ ሰይጣን የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ ይመቸዋል፡፡ እስቲ ንገረኝ እንዲህ በሆነ ቦታ ሰይጣን እንዲገኝ እየጋበዝህ ክርስቶስ የሚገኝበትን ምሥጢር እየፈጸምኩ ነው ትላለህን?

አንተ እኔን ለዚህ ነገር ጠንካራ ተቃዋሚ እንደሆንኩ አድርገህ ትቆጥረኛለህ ፡፡ ከዚህ ጥመትህ ትድን ዘንድ አንተን በጽኑ የሚገሥጽህንም ሰው እንዲህ እንድትመለከተው አውቃለሁ ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ አንተን “የምትበሉም የምትጠጡም ብትሆኑ ወይም ማናቸውም ተግባር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት”(፩ቆሮ.፲፥፴፩) አላለህምን ? አንተ ግን ሥራዎችህን ሁሉን ራስህን ለማዋረድና የሰውን ልጅ ለሚጎዱ ነገሮች ታውላዋለህ ፡፡ ነቢዩስ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ በረዓድም ደስ ይበላችሁ”(መዝ.፪፥፲፩) አላለህምን ? አንተ ግን ሥርዐት አልባ ሆነህ ትመላለሳለህ ፡፡

በአንድ ጊዜ ደስታውንና ጥንቃቄውንም ማስኬድ ትፈልጋላችሁን? አጥንትን የሚያለመልም መዝሙርን መስማትስ ትሻላችሁን? በእርግጥ ከመዝሙሮች ሁሉ የሚልቅ መዝሙርን ልትሰሙ ትችላላችሁ፡፡ እናንተ ግን አትፈቅዱም፤ ብትፈቅዱ ግን  ሰይጣናዊ ዘፈኖች ከመስማት ይልቅ መንፈሳዊ ዝማሬን ለመስማት ትበቃላችሁ፡፡ የመዘምራንን ግሩም የሆነ መጓደድ መመልከት ትሻላችሁ? እነሆ የመላእክት ዝማሬና መጓደድ፡፡ እንዴት ሆኖ ነው የእነርሱን ዝማሬን መስማት በልዑል ፊት መጓደዳቸው መመልከት የሚቻለው ብሎ የሚጠይቀኝ ካለ “እነዚህን ግሳንግሶችን ከነአካቴው ከተውክና በሰርግህ ክርስቶስ እንዲገኝ ከፈቀድክ ይህ ይሆናል፡፡  ክርስቶስ በሰርግህ የታደመ ከሆነ መላእክትም ከእርሱ ጋር በሰርግህ ይገኙልሃል፡፡

ከአንተ ዘንድ ፈቃዱ ካለ እርሱ በአንተ ሰርግ መገኘት ብቻ አይደለም  ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት በመቀየርም ሰርግህን ያደምቅልሃል፡፡ እንደ ውኃ ቀዝቃዛና ወራጅ የሆነውን የዚህን ዓለም ደስታና ፈንጠዝያ አጥፍቶ መንፈሳዊ ደስታን ከሚያጎናጽፈው ከዚህ ተአምር በላይ ምን ድንቅ ተአምር አለ!! ይህ ነው ውኃውን ወደ ወይንነት የመቀየሩ ትርጉም፡፡ እንቢልታ ነፊዎች ባሉበት ክርስቶስ ፈጽሞ አይገኝም፡፡ እርሱ በዚህ ሰርግ ቢገኝ እንኳ መጀመሪያ ይህንን አስወግዶ ነው፡፡ ከዚያም የራሱን ተአምርን ይፈጽማል፡፡ ከዚህ የሰይጣን መሳሪያ ከሆነ እቢልታ በላይ ምን የሚጠላ ነገር አለ? ሁሉ በሥርዐት ካልሆነ ምንም ነገር ያለጥቅም ይሆናል፡፡ ድካማችን ሁሉ ያለፍሬ ይቀራል እኛንም ወደ ውርደት ይጥለናል፡፡

ከመልካም ሥነምግባር የበለጠ አስደሳች ነገር የለም፣ ሥርዐት ወዳድ ከመሆን የበለጠ ጣፋጭ የሆነ ነገር የለም፣ ጽድቅ ለመፈጸም ቆራጥ ከመሆን የበለጠ ተወዳጅ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ሥርዐቶቻችን ልክ እኔ ስለጋብቻ ሥነ ሥርዐት ባስተማርኩት መልክ ይሁኑ፡፡ እንዲህ ከሆነ ደስተኛ ልንሆን እንችላለን፡፡

ነገር ግን ጋብቻን ሊያደርግ የሚሻ ሰው ከማን ጋር ጋብቻውን መፈጸም እንዳለበት ይጠንቀቅ፡፡ ሴት ልጅ ያለችው ሰው   አስቀድሞ እውነተኛና እርሱዋን ሊንከባከባት የሚችል ባልን ሊፈልግላት ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ወንድ ለአካል ራስ እንዲሆን ሊመረጥ ይገባዋል፡፡ ለእርሱ ስትሰጥም እንደ ባሪያ አድርጎ ሊይዛት ሳይሆን እንደ ልጁ ሊያያት ሊሆን ይገባል፡፡

ሀብት ስላለው ወይም ከከበረ ቤተሰብ በመሆኑ ወይም ሰፊ ግዛት ስላለው እርሱን ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ አትምረጡ፡፡ ነገር ግን በነፍሱ ትሑት፣ አስተዋይ፣ ቅንነት ያለውና እግዚአብሔርን የሚፈራ የሆነን ሰው ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ምረጡ፡፡ እንዲህ ከሆነ የምታፈቅሩዋት ልጃችሁ በደስታ ልትኖር ትችላለች፡፡ ባለጠጋ ሆኖ በምግባሩ ግን ብልሹ የሆነን ሰው ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ያጫችሁት ከሆነ እርሱዋን አለመጥቀማችሁ ብቻ ሳይሆን እርሱዋን ነጻ ሰው ከማድረግ ይልቅ የእርሱ ባሪያ በማድረግ ትጎዱአታላችሁ፡፡ ልጃችሁ የእርሱ ሚስት በመሆኑዋ ምክንያት በምታገኛቸው ሀብት ደስ ከመሰኘት ይልቅ እርሱዋን እንደ ባሪያ ቆጥሮ በእርሱዋ ላይ የሚያደርስባት በደል የከፋ ይሆናል፡፡

እንዲህ ዓይነት ድርጊትን ከመፈጸም ትቆጠቡ ዘንድ እለምናችኋለሁ ፡፡  ነገር ግን ከእርሱዋ ጋር ተቀራራቢ ኑሮ ያለውን ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ታጩ ዘንድ እመክራችኋለሁ ፡፡ ይህ ባይሆን ምንም ሀብት ለሌለው ነገር ግን በጎ ሕሊና ላለው ሰው ትድሩዋት ዘንድ አሳስባችኋለሁ ፡፡ እንዲህ በማድረጋችሁ ልጃችሁን ሌላው ቢቀር ለአንድ ጌታ ልጃችሁን እንደባሪያ ከመሸጥ ተቆጥባችሁ በትክክለኛው ትርጉም እንደ ባል ሊሆናት ለሚችል ሰው መስጠት ይቻላችኋል ፡፡

ለልጅህ ባል የሚሆናትን ጥሩ ሥነ ምግባር የተላበሰውን ሰው በጥንቃቄ መርምረህ በማግኘት  ልትድራት ስትዘጋጅ ክርስቶስ ኢየሱስ በጋብቻው ሥነ ሥርዐት ላይ  እንዲገኝልህ ጥራው፡፡  በዚህ የደስታ ቀንህ እርሱን በእንግድነት እንዲገኝ  ስለጋበዝከው ቅር አይሰኝም፡፡ ምክንያቱም እርሱ የሚገኝበት ምሥጢር ነውና፡፡ አዎን ከዚሀ ይልቅ ግን አስቀድመህ ለልጅህ ባል አድርገህ ያጨኸውን ሰው  እርሱ እግዚአብሔር ተወዳጅ ባል ያደርገው ዘንድ ለምነው፡፡

የአብርሃም ባሪያ እንኳ ያላደረገውን አስከፊ ድርጊት ከማድረግ ግን ራስህን ጠብቅ፡፡ እርሱ በጌታው በአብርሃም በተላከ ጊዜ እግዚአብሔርን መንገዱን ያቀናለት ዘንድ ለምኖት ነበር፡፡ እንዲህ በማድረጉም ሁሉን ነገር ሰመረለት፡፡ እንዲሁ አንተም ለልጅህ ባልን በመፈለግ አእምሮ ቢባክን ወደ እግዚአብሔር  “ጌታ ሆይ አንተ የፈቀድከውን አድርግ”  ብለህ ጸልይ፡፡ ለእርሱን እንዲህ በማለት ፈቃድህን አሳልፈህ ስጠው፡፡ በዚህ መልክ ለእርሱ ክብርን ስጥ፤ እርሱም በምላሹ ፈቃድህን በመፈጸም ያከብርሃል፡፡ በእርግጥ አንተን ሁለት ሥራዎች ይጠብቁሃል፡፡ እነርሱም ፈቃድህን ለእርሱ ሙሉ ለሙሉ መስጠትና፣  እርሱ የመሰከረለትን በጥሩ ሥነ ምግባር የታነጸውን ሰው መሻት ናቸው፡፡

የልጅህን ሰርግ ለመሰረግ በምትዘጋጅበትም ጊዜ እቃዎችንና ልብሶችን ለመዋስ ስትል ቤት ለቤት አትዙር፡፡ ምክንያቱም ሰርጉ የሚፈጸመው ትዕይንትን ልታቀርብ ወይም የልጅህን ቁንጅና ልታሳይበት አይደለምና፡፡ በመሆኑም ሰርግህን ልትፈጽም በምትዘጋጅበት ጊዜ ባለህ ነገር ብቻ ቤትህ ለማስዋብ ሞክር፡፡ በመቀጠል ጎረቤቶችህን ወዳጆችህንና የቅርብ ዘመዶችህን ጥራ፡፡ እንዲሁም ጥሩ ባሕርይ አላቸው የምትላቸውን ሰዎች በሰርጉ እንዲታደሙልህ ጋብዝ፡፡ ሙዚቀኞችን ግን ፈጽመህ አትጥራ ለእነርሱ የምታወጣው ወጪ በራሱ ከፍተኛና ሊሆን የማይገባ ነው፡፡

ከእነዚህ ሁሉ አስቀድሞ ግን ክርስቶስን በሰርግህ እንዲገኝ ጋብዘው፡፡ እርሱን እንዴት አድርገህ እንደምትጋብዘው ታውቃለህን ? “ንጉሡም መልሶ፡- እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል”(ማቴ.፳፭፥፵) እንዲል ድሆችን በሰርግ እንዲገኙ በማድረግ ክርስቶስን በሰርግህ እንዲገኝ ማደረግ ይቻልሃል፡፡ ስለክርስቶስ ብለህ ድሆች በሰርግህ እንዲገኙ ስላደረግህ ሰርግህ የተበላሸ አድርገህ አትቁጠር፤ ነገር ግን ሴሰኞችን በሰርግህ ብትጋብዝ ሰርግህ በእርግጥ የረከሰ ይሆናል፡፡ ድሆችን ወደ ሰርግህ መጥራትህ ሀብት ወደ ቤትህ እንዲገባ መጥራትህ ነው፡፡ ቅምጥሎችን ከሰርጉ እንዲታደሙ የጠራህ እንደሆነ ግን ውርደትን እየጠራህ ነው፡፡

ሙሽሪትን በወርቅ ጌጣ ጌጦች አታስጊጣት ነገር ግን በጥሩ ሥነ ምግባርና በጭምትነት አስጊጣት እነዚያን ነገሮች ፈጽመህ አትፈልጋቸው፡፡ ግርግርና ሁካት በሰርግህ ፈጽሞ አይኑር፡፡ ሙሽራውን ጥራና ሚስቱን ይዞ ወደ ቤቱ ይግባ፡፡ በምሳና በራት ግብዣህ ላይ አስካሪ  መጠጦች አይገኙ፡፡ ነገር ግን ሰርግህ በደስታ የሞላበት ይሁን፡፡

እንዲህ አድርገህ ሰርግህን በመከወንህ ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሆንክ ለማስተዋል እንድትችል በዘመኑ ሰርግ ተብለው ከሚቆጠሩት ጋር ያንተን የሰርግ ሥነ ሥርዐት አስተያይ፡፡ ሌላው ይቅርና ያንተን ሰርግ የተመለከተ ሰው ሁሉ የቁንጅና ውድድር ሳይሆን በእውነተኛ ትርጉም ሰርግን እንዳየ ምስክርነትን ይሰጥሃል፡፡ በዘመኑ ሰርግ ተብለው ከሚጠሩት ውስጥ ግን እጅግ የበዙ ክፋቶች ታጭቀው ይገኙበታል፡፡ በአዳራሽ የሚፈጸመው ሰርግ በጥንቃቄና እግዚአብሔርን በመፍራት ከሚደረገው ጋር ሲነጻጸሩ በቶሎ የሚጠናቀቁ ሰርጎች አይደሉም ፡፡ ከዚህም ባለፈ በውሰት የመጡት እቃዎች ሊጠፉም ስለሚችሉ ፍጻሜው ከደስታ ይልቅ ሊቋቋሙ ከማይችሉት ከባድ ሃዘን ውስጥ ሊጥል ይችላል ፡፡ ይህ የከበደ ሃዘን በአማች ላይ የሚታይ ነው ፡፡ ነገር ግን ሙሽሪትም ከዚህ ሃዘን ነጻ ልትሆን አትችልም ፡፡ በሰርጉም ፍጻሜም የቤቱ ውበቱ ጠፍቶ በሃዘን ታወሮ ይታያል ፡፡

በጥንቃቄና እግዚአብሔርን በመፍራት በሚከናወነው ሰርግና በአሕዛብ ልማድ በሚፈጸመው ሰርግ መካከል ሰፊ የሆነ ልዩነት አለ፡፡ በዚህ ክርስቶስ ሲገኝ በዚያ ግን ሰይጣን ነግሦ ይታይበታል ፡፡ በዚህ ፍጽም የሆነ ፍስሐ ሲታይ በዚያ ደግሞ ጥቅ ያጣ አለባበስ ይተዋወቅበታል ፡፡ በዚህ ፍጹም ደስታ ሲኖር በዚያ ግን ሕማምና ሰቆቃ ይተርፈዋል ፡፡ በዚያ የወጣው ወጪ ታላቅ ሲሆን በዚህ ግን እዚህ ግባ የማይባል ወጪ ብቻ ያስተናግዳል ፡፡ በዚያ ግርግርና ሁካታ ሲታይ በዚህ ግን ግብረ ገብነት ጎልቶ ይንጸባረቅበታል፡፡ በዚያ ኃጢአት ሠልጥና ስትታይ በዚህ ግን ኃጢአት ፈጽማ አትኖርም ፡፡ በዚያ ስካሮች ሲኖሩባት በዚህ ግን ሰላም ወዳዶች ይታዩባታል ፡፡ በዚያ ሁካታና ጠብ ሲኖር በዚህ ግን እርጋትና ሰላም ሰፍነው ይታዩበታል ፡፡

እነዚህን ሁሉ ልብ በሉ ፡፡ እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘት እርሱን ለሚያፈቅሩት ካዘጋጀው ከመንግሥቱ ተካፋዮች እንድንሆን ከዚህ ቀን ጀምረን ይህን ክፉ ልማድ ከራሳችን አርቀነው እናስወግደው ፡፡ የሰውን ልጅ ከመውደዱ የተነሣ ሰው በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር አብ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር ምስጋና ዛሬም ዘወትርም እስከዘለዓለሙ ይሁን አሜን !!