«ወአድኀነ ሕዝቦ በመስቀሉ»

ክፍል ሁለት

 

3. ክብረ መስቀል

እኛ ኦርቶዶክሳውያን የመስቀልን መንፈሳዊ ትርጉም ከመረዳትና በልባችን ከመያዝ በተጨማሪ ለመስቀል ያለንን ክብር እና ፍቅር ለመግለፅ የምናደርጋቸው በርካታ ነገሮች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን እንጠቁማለን፡-

3.1 መስቀልን በቤተ ክርስቲያን፣ በንዋያተ ቅዱሳት፣ በሰውነት ላይ ማድረግ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ የመስቀልን በዓል አስመልክተው ባስተማሩት ትምህርት ላይ እንዲህ ይላሉ፤

«መስቀል ባሉት መንፈሳዊና ትምህርተ ሃይማኖታዊ ትርጉሞች ምክንያት ክርስቲያኖች ሁሉ የሙጥኝ ብለን እንይዘዋለን፡፡ በአብያተ ክርስቲያናት ላይ እናደርገዋለን፤ በተለያየ መስክ እንቀርፀዋለን፤ በደረታችን ላይ እናንጠለጥለዋለን፣ በምልክቱ እናማትባለን፤ ፀሎታችንን እንጀምርበታለን፤ ካህናትም በእጃቸው ይይዙታል፣ ሰዎችንም ይባርኩበታል፣ የሐዲስ ኪዳን በረከቶች ሁሉ ምንጭ መስቀል እንዲሆን በማመን መስቀል በሁሉም ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጸም ላይ እንጠቀምበታለን፤ በካህናቱ ልብሶች ላይ እናደርገዋለን ይኸውም ለጌጥ ሳይሆን ስለ ኃይሉ እና ስለ ቡራኬው ነው፡፡»

3.2. መስቀልን በመሳለም መባረክ

በጥንት ጊዜ መስቀል የመርገም ምልክት ነበር፡፡ ነገር ግን ጌታችን በመስቀል ላይ መርገማችንን ሁሉ ተሸክሞ ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቅንና የአዲስ ሕይወትን በረከት ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህም የሐዲስ ኪዳን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ የተገኙት ከመስቀል ነው፡፡

ስለዚህ ካህናት ቡራኬን ለመስጠት መስቀልን ይጠቀማሉ፤ ይህም በረከቱ የሚመጣው /የሚመነጨው/ ከራሳቸው ሳይሆን በረከትን እንዲሰጡበት የሰጣቸው ጌታችን ከተሰቀለበት መስቀል መሆኑን እና በሐዲስ ኪዳን ያሉ በረከቶች ሁሉ ምንጭ መስቀል መሆኑን ላይ ለማመልከት ነው፡፡

እግዚአብሔር የማይታዩ ፀጋዎችን ለሰዎች የሚሰጠው በሚታዩ አገልግሎቶች ነው፡፡ ይኸውም ነገሮችን ለሰው ልጅ ህሊና በሚረዳ መልኩ ለማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ከተወለደ ጀምሮ ዓይን ያልነበረውን ዓይን የፈጠረለት በሚታይ መልኩ በምድር አፈርና በምራቁ ጭቃ ሰርቶ ነው፡፡ ጥምቀትንም በውሃ ውስጥ በመነከር አድርጎታል፡፡ በዚሁ መሰረት በመስቀልን በመባረክ የማይታዩ በረከቶች እና ፀጋዎችን እናገኛለን፡፡ እነዚህ በረከቶችም ደስታ፣ የመስቀሉ ፍቅር፣ ጥብአት /ድፍረት/ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

3.3. ማማተብ

አተበ ማለተ አመለከተ ማለት ነው፡፡ ማማተብ ማለት ደግሞ ማመልከት ማለት ነው፡፡ ማማተብ ማለት ከአውራ ጣት ቀጥሎ ባለው ጣትና በቀሪዎቹ ሦስት ጣቶች የመስቀል ምልክት ሰርቶ እጅን ከግንባር ጀምሮ ከላይ ወደ ታች ከዚያም ከግራ ወደ ቀኝ «በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ» እያሉ ስመ ሥላሴን እየጠሩ ሰውነትን ማመልከት ማለት ነው፡፡

እጃችንን ከላይ ወደታች ማውረዳችን እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወረዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው መሆኑን እንዲያሳስበን ነው፡፡

ከግራ ወደ ቀኝ ማድረጋችን በመከራውና በሞቱ ከግራ /ከሞት/ ወደ ቀኝ / ወደ ሕይወት / እንዳሸጋገረን እንዲያሳስበን ነው፡፡ የመስቀል ቅርጹ ደግሞ መከራ መስቀሉን ያሳስበናል፡፡

ስናማትብ ራሳችንን እንባርካን፣ አጋንንት እኩያት መናፍስት ይርቁልናል፣ መከራ መስቀሉንም እናስባለን፤ መስቀሉን እንሸከማለን፡፡ ስለዚህ ጠዋት ስንነሳ፣ በፀሎታችን ወቅት፣ ክፉ ሀሳብ ሲመጣብን፣ የማያስፈራ ነገር ሲገጥመን፣ ደስ ሲለን፣…. እናማትባን፡፡

3.4. ለመስቀል መስገድና መገዛት

እኛ ኦርቶዶክሳውያን በመስቀል ፊት እንሰግዳለን፡፡ በመስቀል ፊት የምንሰግደው ስግደት ከሁለቱ የመስቀል ትርጉሞች አንጻር ሁለት ዓይነት መልኮች አሉት

ሀ. መስቀል የክርስቶስ መከራ ስቅለት እና ሞት የሚወክል አርማ እንደመሆኑ መጠን በመስቀለ ፊት ስንሰግድ ጌታችንን እያሰብን ለአምላክ ብቻ የሚገባውን የአምልኮ ስግደት ለአምላካችን እንሰግዳለን፤ ይህም ልክ በጌታችን ስዕለ አድኅኖ ፊት እንደመስገድ ያለ ነው፡፡

ለ. መስቀል የተከበረ ንዋይ ስለሆነ ለመስቀሉ ያለንን ፍቅር እና አክብሮት ለመግለጽ የፀጋ የአክብሮት ስግደት እንሰግድለታን፡፡ እንገዛለታን /እናከብረዋለን/ ቅዱስ ያሬድ ይህንን ሁለተኛውን ስግደት አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡፡ «ሀለው እለ ይቤሉ ለዕፅኑ ታመልኩ፣ ለለዕፅኑ ትገብሩ በዓለ፣ አቀደሶኑ በደሙ ክቡር ለዕፀ መስቀሉ፣ ወእንተዝ ንሕነ ናመልኮ» «የምታመልኩት ዕፅን/ የምትገዙት ለዕፅ/ ነውን? በዓልስ የምታደርጉት ለዕንጨት ነውን? የሚሉ አሉ፡፡ በክቡር ደሙ መስቀሉን ቀድሶት የለምን? ስለዚህ እኛ እናመልከዋለን /እንገዛለታለን/»

መለከ ማለት ገዛ ማለት ነው፡፡ ናመልከ ማለት እንገዛለታለን፤ እናከብረዋለን፣ ከፊቱ ራሳችንን ዝቅ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡ ክቡር መስቀል ክርስቶስ ማዳኑን የፈፀበት፣ በደሙ ያከበረው ንዋይ ቅዱስ ስለሆነ የፀጋ ስግደት እንሰግድለታለን፡፡ እንገዛለታለንም፡፡

ከዚህም በተጨሪ በመስቀል ስም ታቦታትን በመቅረጽና አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ፣ የመስቀልን በዓላት በማክበር፣ ስመ ክርስትናን ወልደ መስቀል፣ ወለተ መስቀል፣ ገብረ መስቀል እያልን በመሰየም ለመስቀሉ ያለንን ክብር እና ፍቅር እንገልጣለን፡፡

እነዚህን ነገሮች ከማድረግም በተጨማሪ መስቀልን እንዲህ እያልን በቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች እናመሰግነዋለን፡-

– «መስቀል ኃይልነ ወፀወንነ መድኃኒተ ነፍስነ ፍጽምን ወከዋላን ምጽንአተ ቅጽርነ መስቀል ቤዛነ ኃይልነ ወፀወንነ ዮም ፍስሓ ለነ» «መስቀል ኃይላችን፣ መመኪያችን፣ የነፍሳችን መድኃኒት ነው፡፡ የአጥራችን መጽኛ፣ ቤዛችን ነው፡፡ ዛሬ ለእኛ ደስታ ሆነ»

– «ወሀለወት አሐቲ ሀገር ብርሐት ከመ ፀሐይ ሕንፄነ ወሱራሬሃ አዳም የዓውደ ሐጹር በትእምርተ መስቀል» «አንዲት እንደ ፀሐይ የምታበራና ህንጻዋና አስራሯ ያማረ ሀገር አለች /ቤተ ክርስቲያንን ነው/፡፡ በመስቀል ምልክት የሆነ አጥር ይከባታል»

– «መስቀልከ ተስፋ ቅቡጻን መስቀልከ ልብስ ለዕሩቃን አንቅዕት ለፅሙዓን መርሶ መድኃኒቶሙ ለአሕዛብ» «መስቀልህ ተስፋ ለቆረጡ ተስፋ፣ ለተራቆቱ ልብስ፣ ለተጠሙ ምንጭ፣ ለአህዛብ ደግሞ የመድኃኒታቸው ወደብ /መጠጊያ/ ነው»

– «መስቀል ዘኀኑ ለባሕር፣ መርሶሙ ለአሕማር መስቀል ብርሃን ወሃቤ ሰላም ብርሃነ ዓለም» «መስቀል የባሕር ፀጥታ፣ የመርከቦች ወደብ፣ የዓለም ብርሃን እና ሰላምን ሰጪ ነው፡፡»  

4. የመስቀሉ ኃይል

ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶሳውያን በላከው የመጀመሪያ መልዕክቱ እንዲህ ይላል፡- «የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው፤ ለእኛ ለምንድነው ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፡፡» /1ኛ ቆሮ.1-18/

መስቀል ከሁለቱ ትርጉሞቹ /መልዕክቶቹ/ አንጻር ኃይልነቱም በሁለት መልኩ ሊታይ ይችላል፤

ሀ/ መስቀል ኀጢአታችንንና በኀጢአታችን ምክንያት የደረሰብንን ሞት፣ የጌታችንን ሕማማት፣ መስቀል እና ሞት፣ ትንሳኤውንና ዳግም ምፅአቱንና እኛም ከሞት ተነስተን ለፍርድ የምንቆም መሆናችንንና ሌሎች ተያያዥ ነገሮችን የሚወክልና የሚያስታውሰን ምልክት ነው፡፡

እነዚህን ነገሮች ማሰባችንና ማስታወሳችን ሁል ጊዜ በመንፈሳዊ ሃሳብ ውስጥ እንድንሆንና ዓለምንና የዓለም የሆነውን በሚያስንቅ የክርስቶስ ፍቅር፣ እንድንሞላ ስለሚያደርገን መስቀል ኃይላችን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስለ ሚደርስብን ፈተና እና ስለ እግዚአብሔር ብለን ስለምንተወው ነገር ሁሉ የምንቀበለውን አክሊልም እያስታወሰ ብርታት ስለሚሆነን መስቀል ኀይላችን ነው፡፡

ለ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ይህንን ሁለተኛውን የመስቀል ኀይልነት ሰያብራሩ እንዲህ ይላሉ፣ «የመስቀል ምልክት ሰይጣናት ሁሉ የሚፈሩት ኀይል እንደሆነ እናያለን፤ ሰይጣን የሰው ልጆችን ለማጥፋት ያደረገው ጥረትና የደከመው ድካም የከሸፈው በመስቀል ላይ በተደረገው ነጻ ማውጣት ነው፡፡ ስለዚህ ሰይጣን የመስቀልን ምልክት ይፈራል፤ ስለዚህ በእምነት ከተደረገ በመስቀልና በመስቀል ምልክት እጋንንትን ማራቅ፣ ማውጣትና ማሳደድ ይቻላል፡፡ እኛም የእግዚአብሔር ልጆች የድል ምልክት አድርገን እንይዘዋለን፤ አጋንንትን ድል ለማድረግ እንጠቀምበታለን፡፡

ስለዚህ በዘወትር ጸሎታችን «መስቀል ኃይላችን ነው» እንላለን፤ ስለ መስቀሉና ስለ አምላካችን ውለታና ስለ ዘለዓለማዊ ህይወታችን በማሰብ ክፉ ሃሳብና ፍትወታትን ድል እናደርግበታለን፤ በመስቀል ምልክት በማማተብና በዕፀ መስቀል በመባረክ /ባ ይጠብቀል/ እና በመባረክ /ለካህናት/ አጋንንትን እናርቃለን፤ ከሰዎችም እናስወጣለን፡፡

5. ጌታችን የተሰቀለበት ዕፅ መስቀል መገኘት

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ተአምራትን ማድረግ ሙታንን ማስነሣት፣ በሽተኞችን መፈወስ፣ አጋንንትን ማውጣት ስለጀመረ በቅንአታቸውና ባለማወቃቸው ጌታን የሰቀሉት አይሁድ መስቀሉ በኢየሩሳሌም አካባቢ ባለው የቀራንዮ ተራራ ላይ ቀብረው ቦታውን የቆሻሻ መጣያ አደረጉት፡፡ ሁሉም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ቆሻሻቸውን በዚያ መጣል ጀመሩ፡፡ በጊዜ ብዛትም የቆሻሻው ክምር አድጎ ትልቅ ኮረብታ አከለ፡፡

ክርስቲያኖች መስቀሉ ያለበትን ቦታ ቢያውቁም ሊያወጡት ግን አልቻሉም ነበር፡፡ ነገር ግን በ70 ዓ.ም የሮማው የጦር ጀነራል /በኋላ ንጉሠ ነገሥት/ ቬስፓስያንና ልጁ ጥጦስ ኢየሩሳሌምን ሊያጠፋ ጥቂት ጊዜ ሲቀራቸው ክርስቲያኖች ከተማውን ለቀው ስለወጡና የነበሩት አይሁድ ስለተገደሉ፣ የቀሩትም ስለሸሹና ከተማዋ ባዶ ስለሆነችና ከዚያ በኋላ የነበረውም ዘመን ለክርስቲያኖች የሰማእትነት፣ የስደትና የመከራ ዘመን ስለነበር መስቀሉን ማውጣት አልተቻለም ነበር፡፡ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ሳይቀር ተረሳ /ጠፋ/፡፡

ከ300 ዓመታት ያህል በኋላ እግዚአብሔር ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን አስነሣ፡፡ ቆስጠንጢኖስ መክስምያኖስ ከሚባል ጠላቱ ጋር አስጨናቂ የሆነ ጦርነት ላይ በነበረበት ወቅት በሰማይ ላይ ብርሃናዊ የመስቀል ምልክት ታየው፤ «ከዚያም በዚህ ምልክት ጠላትህን ታሸንፋለህ፡፡» የሚል ድምፅ ከሰማይ ሰማ፡፡ /ይህ የሆነው ቆስጠንጢኖስ ለብቻው ሁኖ በተመስጦ እያሰበ ሳለ ነው፡፡/ ወዲያውም የክርስትናን እምነት ተቀበለ፡፡ /የተጠመቀው ግን ሊሞት ጥቂት ሲቀረው ነው፡፡ መስቀልን የመንግሥቱና የሠራዊቱ አርማ አደረገ፡፡ በሠራዊቱ ልብሶች፣ የጦር ዕቃዎች፣ ፈረሶች ሁሉ ላይ የመስቀልን ምልክት አድርጎ ጠላቱን በመዋጋት ድል አደረገ፤ ለክርስቲያኖች ነጻነትን ሰጠ የዘመነ ሰማዕታት ፍጻሜ ሆነ፤ ክርስቲያናዊ መንግሥት መሠረተ፡፡

የቆስጠንጢኖስ እናት ቅድስት እሌኒ ትባላለች፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ስለ ቅድስት እሌኒ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፡- «ልጇ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ንግሥት በማድረግ አከበራት፤ በቤተ መንግሥቱ ንዋይም ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጣት፤ እርሷም ይህንን ገንዘብ በደግነት በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ሠራችበት፤ ድሆችንና የተቸገሩትንም ረዳችበት፡፡ ከቦታ ቦታ ስትዘዋወርም ሰዎችን ትረዳና ከባርነት ነጻ ታወጣ ነበር፡፡

«በጣም ሃይማኖተኛም ነበረች፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን የምትሔደው ንግሥት ብትሆንም እንኳን ቀላል እና ተራ ልብሶችን ለብሳ ነበር፡፡ ጸሎቷን ያለ ማስታጐል /ያለማቋረጥ/ ትጸልይ ነበር፡፡ ከመንፈሳዊ መርሐ ግብሮችንም አትቀርም ነበር፡፡ እንደ ንግሥት ከኖረችው በላይ እንደ አማኝ ኖራለች፡፡ ቅዱሳት መካናትን ትጎበኝና በእርጅናዋ ወራት የረጅም ጉዞን ድካም ትቀበል ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን እንድታወጣ በራእይ ነገራት፡፡ እሌኒም የታዘዘችውን ለመፈጸም ወደ ኢየሩሳሌም ብትሔድም መስቀሉን ግን ማግኘት አልቻለችም፡፡ በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር ቅዱስ ያሬድ በድጓው ጽፎታል፤

«ሖረት ዕሌኒ በሰላም ከመ ትኀስስ ዕፅ መስቀል ወረከበት መሐይምናነ እምዘመደ ዕብራውያን ወትቤሎሙ በአይቴ ሰቀሉ ወልደ ዋህደ ወይቤልዋ በቀራንዮ በበህየ ሰቀልዎ፤ ዕሌኒ መስቀሉን ትፈልግ ዘንድ በሰላም ሔደች፤ ከዕብራውያን ወገኖች መካከል ምዕመናንን አገኘችና ጌታን የሰቀሉት የት ነው ብላ ጠየቀቻቸው፤ እነርሱም በቀራንዮ ነው የሰቀሉት አሏት፡፡» ከጠየቀቻቸው ሰዎች መካከልም ኪራኮስ አሚኖስ የሚባሉ ሰዎች እንዳሉበት ቅዱስ ያሬድ እንዲህ እያለ ይነግረናል፡፡

«ትቤሎ ዕሌኒ ለኪራኮስ ምዕመን ንግረኒ አፍጥን ኀበ ሀሎ መስቀሎ ለኢየሱስ ክርስቶስ፤ ዕሌኒ ኪራኮስን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የት እንዳለ ቶሎ ብለህ ንገረኝ አለችው፡፡»

ትቤሎሙ ዕሌኒ ለኪራኮስ ወለ አሚኖሰ ንግሩኒ ኀበ ሰቀሉ ወልደ ዋህደ፤ ዕሌኒ ኪራከስንና አሚኖስን አይሁድ ጌታን የት እንደሰቀሉት ንገሩኝ አለቻቸው፡፡»

ኪራኮስም እንዲህ አላት፡- እኔ ዘመኑ ሩቅ ስለሆነ አላውቀውም፤ አባቴ ግን የቦታው ስም ቀራንዮ መሆኑን ነግሮኛል፡፡»

ይሁን እንጂ በቀራንዮ ተራራ ላይ ቁፋሮ ቢጀመርም መስቀሉ ሊገኝ አልቻለም፡፡ በኋላ አባ መቃርስ የተባለው የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ አይሁድ መስቀሉን አስቀብረው ቦታውን የቆሻሻ መጣያ እንዳደረጉትና ቦታውም በተራራው ላይ ባሉት ኮረብታ መሰል ክምሮች አንዱ እንደሆነ ነገራት፡፡ ይሁን እንጂ በቀራንዮ ተራራ ላይ በርካታ ትናንሽ ኮረብታዎች ክምሮችን በመኖራቸው መስቀሉ ያለበት ሊታወቅ አልቻለም፡፡

ከዚህ በኋላ «ወትቤ ዕሌኒ አንሰ ኢይለብስ አልበሰ መንግሥትየ ለእመ ኢተረክበ ዕፅ መስቀል ወፀርሐት ኀበ እግዚአብሔር በዐቢይ ቃል፤ ዕሌኒም ዕፅ መስቀሉ ካልተገኘ የመንግሥቴን ልብስ አልለብስም አለች፤ በታላቅ ቃልም ወደ እግዚአብሔር ጮኸች» እንዳለው ዕሌኒ ሱባኤ ገብታ ጸሎት ማድረግ ጀመረች፡፡ በሱባኤዋም ወቅት መልአክ ተገልጦ ደመራ አስደምራ ዕጣን ብትጨምርበት ጢሱ መስቀሉ ያለበትን እንደሚያመለክታት ነገራት፡፡

በዚህም መሠረት መስከረም 16 ቀን ታላቅ ደመራ አስደምራ እሳት አስለኩሳ በጣም ብዙ ዕጣን ጨመረችበት የዕጣኑ ጢስም ወደ ሰማይ ወጥቶ ተመልሶ መስቀሉ ወዳለበት ኮረብታ ተመለሰና መስቀሉ ያለበትን አመለከተ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ይህንን አስደናቂ ክስተት «ዘዕጣን አንዳረ ሰገደ ጢስ»፣ «ዕጣኑ መስቀሉ ያለበትን አመለከተ፣ ጡሱም ለመስቀል ሰገደ» በማለት ገልጾታል፡፡

ወዲያውም ቁፋሮ ተጀመረ፡፡ ከስድስት ወራት በኋላም በመጋቢት 1ዐ ቀን ስንክሳር እንደተገለጠው ሦስት መስቀሎች /የጌታችንና አብረውት የተሰቀሉት ሁለት ወንበዴዎች/ ተገኙ፡፡ የጌታችን መስቀል ሙት በማስነሣቱና ድውያንን በመፈወሱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ ከመስቀሉ ጋርም አክሊለ ሶኩና ጌታችን የተቸነከረባቸው ችንካሮች እንደተገኙ መጽሐፈ ስንክሳርና መጽሐፈ ድጓ ይናገራሉ፡፡

ዕሌኒም በጣም ተደሰተችና በቀራንዮ ተራራ ላይ በመስቀል ስም ቤተ ክርስቲያን አሠራች፡፡ ቤተ ክርስቲያኑም መስከረም 16 ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከብሮ መስከረም 17 ቀን ተቀደሰበት፡፡ የጌታችን መስቀልም በወርቅ ሳጥን ውስጥ በዚያው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀመጠ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በዚህ ምክንያት የመስቀሉን በዓል ቅዳሴ ቤቱ በተከበረበት መስከረም 16 ቀን ዳመራ ደምራ ታከብራለች፡፡ መጋቢት 1ዐ ቀንም መስቀሉ የተገኘበትን ዕለት ታስባለች፡፡

የመስቀሉ በረከት ይደርብን፤ አሜን፡፡