“አባታችን ሆይ” ክፍል አንድ

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

መግቢያ

አንባቢያን ሆይ ይህ ጽሑፍ የትርጉም ሥራ ሲሆን ትምህርቱም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የማቴዎስን ወንጌል ሲተረጉም ከጻፈው ላይ የተወሰደ ነው፡፡ የዚህ ቅዱስ አባት ሥራዎች ብዙ ከመሆናቸው የተነሣ ታላቁ ጸሐፊ /The great author/ ተብሎ ነው በሥነ መለኮት ምሁራን የሚታወቀው፡፡ “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን የጸሎት ሥርዐት ይህ ቅዱስ እንዴት አድርጎ ድንቅ በሚባል መልኩ እንደተረጎመው ትመለከቱ ዘንድ እነሆ ብለናል፡፡


ግብዞችን አትምሰሉአቸው

ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባና መዝጊያህንም ዘግተህ በሥውር ላለው አባትህ ጸልይ በሥውር የሚያይህ አባትህ በግልጽ ይከፍልሃል፡፡” /ማቴ.6÷1-6/

በዚህ ቦታ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ግብዞች ማለቱ አግባብነት ነበረው፡፡ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሐር ቤት ለጸሎት በሚመጡበት ጊዜ የሰዎችን ቀልብ ለመሳብ ሲሉ ከሥርዓት የወጣ አለባበስን ይለብሱ ነበር እንጂ ለጸሎት ተስማሚ የሆነውን የትሕትና አለባበስን አይለብሱም ነበርና ነው፡፡

ለጸሎት ወደ አምላኩ የሚቀርብ ሰው ሌሎች ጉዳዮቹን ሁሉ ወደ ኋላ ትቶና ከሰው ዘንድም ምስጋናንና ክብርን ሳይሻ ጸሎቱን ተቀብሎ ወደሚፈጽምለት አምላኩ ብቻ ትኩረቱን ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ይህን መፈጸም ትተህ ዐይኖችህን የትም የምታንከራትት ከሆነ ከእግዚአብሐር ቤት በባዶ እጅህ ምንም ሳታገኝ እንድትመለስ ዕወቅ፡፡ ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድ ዋጋ ማግኘትና ማጣት በእጅህ የተሰጠ የአንተ እድል ፈንታህ ነው፡፡ ስለዚህ ከንቱ ውዳሴን የሚሹ ሰዎች ከእኔ ዘንድ አንዳች አያገኙም አላለም፡፡ ነገር ግን “ዋጋቸውን ተቀብለዋል” አለ፡፡

በእርግጥ ከእግዚአብሐር ዘንድ ሳይሆን እነርሱን ከመሰሉ ሰዎች ምስጋናና አድናቆትን አግኝተው ይሆናል፡፡ ይህ ለእነርሱ ዋጋቸው ነው፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሐር ዘንድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለጸሎታቸው ብድራትን የጠበቁት ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሰዎች ነውና፡፡ ነገር ግን በዚህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር አምላክ ማንኛውንም እንደ ፈቃዱ ልመናና ጸሎት ብናቀርብ ልመናችንን ሊሰማን ጸሎታችንን ሊቀበል ቃል ኪዳን መግባቱም እናስተውላለን፡፡ ጌታችን ጻፎችና ፈሪሳውያን ለጸሎታቸው የመረጡት ሥፍራ ለከንቱ ውዳሴ የሚያጋልጥ መሆኑን ካስረዳ በኋላ እኛ ስንጸልይ ምን ማድረግ እንዳለብን አስተምሮናል፡፡
እንዲህም አለን “አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በሥውር ላለው አባትህ ጸልይ፡፡” ምንድን ነው ታዲያ? እንዲህ ሲለን በቤተ ክርስቲያን ጸሎትን አታድርጉ ሲለን ነውን? አይደለም ነገር ግን እንዲህ ማለቱ በየትኛውም ቦታ ሆነን ጸሎትን ብናደርግ በፍጹም ተመስጦ ሆነን ማቅረብ እንዳለብን ሲያሳስብ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በየትም ቦታ ማንኛውንም መልካም ሥራ ብንፈጽም ሁልጊዜም በማስተዋል ሆነን ብንፈጽማቸው የእርሱ ፈቃድ ነውና፡፡ ምንም እንኳን አንተ የእልፍኝህን በር ዘግተህ ብትጸልይ ይህን በማድረግህ ከሰው ዘንድ ምስጋናን ሽተህ ከሆነ የእልፍኝህን በር ዘግተህ በመጸለይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ አንዳች ዋጋን አገኛለሁ ብለህ አትጠብቅ፡፡

ይህንን ግልጽ ለማድረግም “ለሰው ትታዩ ዘንድ” የሚለውን ቃል ጨመረበት፡፡ ስለዚህም አንተን የእልፍኝህን ደጅ ዘግተህ ትጸልይ ዘንድ ማዘዙ ልቡናህን ሰብስበህ ትጸልይ ዘንድ ነው እንጂ በርህን ዘግተህ መጸለይ ዋጋ ያሰጥሃል እያለህ አይደለም፡፡ የእግዚአብሐር ፈቃድ የቤትህን ደጅ ዘግተህ ትጸልይ ዘንድ ሳይሆን የልብህን ደጆች በመዝጋት ትጸልይ ዘንድ ነው፡፡

ማንኛውንም የትሩፋት ሥራዎችን ስትሠራ ከከንቱ ውዳሴ ነፃ መሆን መልካም ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ስትጸልይ ራስህን ከከንቱ ውዳሴ መጠበቅ ይገባሃል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በጸሎታችን ሰዓት የምንቅበዘበዝና የምንባክን ከሆነና ከልባችን የማንጸልይ ከሆነ ለዚህ ክፉ ለሆነ በሽታ ማለትም ለከንቱ ውዳሴ እንጋለጣለን፡፡ እኛ በተመስጦ ሕሊናችንን ሰብስበን ካልሆነ የምንጸልየው እንዴት ጸሎታችንን እግዚአብሔር እንደሚሰማን እርግጠኛ እንሆናለን?

እንዲያም ሆኖ አንዳንድ ምዕመናን ከሥርዓት የወጣ ጩኸት በማሰማትና ያልተገባ ጠባይን በማሳየት የሌላውን ሰላም የሚያውኩ ከዚህም ባለፈ ራሳቸውን ለከንቱ ውዳሴ የሚያጋልጡ አሉ፡፡ በገበያ ቦታ እንኳ አንድ የእኔ ቢጤ ባልተገባ ጠባይ እና ለመስማት በማይመች ጩኸት ለአንዱ ባለጸጋ ልመና ቢያቀርብ ፈጥኖ ከፊቱ እንዲያባርረው በትሕትና በመሆን ቢለምነው ግን የባለጸጋውን ሆድ አባብቶ ያለውን እንዲሰጠው እንደሚያደርገው አትመለከትምን?

እኛም ስንጸልይ በማይገባና ፈር በለቀቀ ከሥርዐት በወጣ መልኩ አብዝተን በመጮኽ ሊሆን አይገባም፡፡ ነገር ግን በውጭ የምናሰማው አንዳች ጩኸት ሳይኖር ለከንቱ ውዳሴ ከሚያጋልጡ ያልተገቡ ጠባያት ርቀን አጠገባችን ያሉትን ሰዎች  ሳናውክ በፍጹም ትሕትና በውስጣዊ ማንነታችን ማለትም በነፍሳችን ወደ እግዚአብሐር ልንጮኽና ልመናችንን ልናቀርብ ይገባል፡፡

እንዲህ ስንል ሰው ከደረሰበት ታላቅ ኅዘን የተነሣ አምርሮ ሊጮኽ አይችልም ማለታችን ግን አይደለም፡፡ ቢሆንም አንድ ሰው ምንም እንኳ እጅግ ያዘነና የተከዘ ቢሆንም ይህን ታላቅ ኅዘን በነፍሱ ወደ እግዚአብሔር በመጮኽ ሊገልጸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሙሴ ወደ እግዚአብሐር አምላኩ በነፍሱ አብዝቶ ቃተተ ጮኸም፤ ጩኸቱም ከእግዚአብሐር ዘንድ ተሰማች፤ በዚህም ምክንያት እግዚአብሐር ሙሴን “ለምን ትጮኽብኛለህ” አለው፡፡ /ዘጸአ.14÷15/ የነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና ከከንፈሩዋ የወጣ አንዳችን ድምፅ ሳይኖር በነፍሷ ግን የልቧን ኅዘን ወደ እግዚአብሐር ታመለክት ነበር፡፡ ልመናዋንም እግዚአብሐር ተቀበላት የልቧንም መሻት ሁሉ ፈጸመላት፡፡ አቤል እንኳን በሞቱና በደሙ ከእግዚአብሐር አምላክ ዘንድ ከመለከት ድምፅ ይልቅ ጠርታ የምትሰማ ጩኸትን ወደ እግዚአብሐር ጮኾ ነበር፡፡ /ዘፍ.4÷10/

ነቢዩ ኢዩኤልም በእግዚአብሔርም ፊት የልባችንን ኅዘን ለመግለጽ ልብሳችንን ሳይሆን ልበችንን ለጸሎት ልናዋርድ እንዲገባን ሲያስረዳ “ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ” /ኢዩ.2÷13/ ብሎናል፡፡

መዝሙረኛውም “አቤቱ አንተን ከጥልቅ ጠራሁ” /መዝ.129፥1/ ብሏል፡፡ ከልባችን ጥግ ከጥልቁ የሚወጣው ጩኸታችን ድንቅ የሆነ ምላሽን ይዞልን ይመጣል፡፡ በምድራዊው ቤተ መንግሥት ትንሽ የሆነ ኮሽታ ወይንም ሹክሹክታ የግቢውን ጸጥታ ምን ያህል እንደሚያውከው አትመለከትምን? እንዴት ታዲያ ምድራዊ ባልሆነው እጅግም አስፈሪ በሆነው ሰማያዊው ቤተ መንግሥት ስትገባ የበለጠ ፀጥታን ገንዘብህ ማድረግ ይጠበቅብህ ይህን!!

አንተ አሁን በምስጋና ከትጉሃን መላእክት ጋር ተቆጥረሃል፡፡ ከሊቃነ መላእክት ጋርም ማኅበርተኛ ሆነሃል፡፡ ከሱራፌል ጋር ዝማሬን ለእግዚአብሐር ለማቅረብ ታድመሃል፡፡ በሰማያት ያሉ መላእክት ሁሉ በመልካም ሥርዓት በመሆን ለእግዚአብሔር ይገዛሉ፡፡ እርሱንም በመፍራት ሆነው ድንቅ የሆነ ዝማሬአቸውንና ቅዳሴአቸውን ለፍጥረት ሁሉ ገዢ ለሆነው አምላክ ያለማቋረጥ ያቀርባሉ፡፡

አንተም ከእነርሱ ጋር እግዚአብሐርን በማመስገን ስሙን በመቀደስ እነርሱን ትመስሏቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋርም በጥምቀት ማኅበርተኛ ሆነሃል፡፡ ስለዚህም በምትጸልይበት ጊዜ ለሰዎች ትታይ ዘንድ አትጸልይ ነገር ግን ወደ እግዚአብሐር ጸልይ፡፡ እርሱ በሁሉ ቦታ ይገኛልና እይታን ከፈለግህ በሁሉ ቦታ ያለ እርሱ ከሰው ይልቅ ያስተውልሃል፡፡ እርሱ በልብህ የታሰበውን እንኳ ያውቃል፡፡

በሥውር የሚያይህ አባትህ በግልጥ ይከፍልሃል፡፡” እንዲህ ሲል /Shall freely give thee “but shall reward thee”/  በነጻ ይሰጣሀል አላለም ነገር ግን እንደሚገባ ሆነህ በመጸለይህ ምክንያት በብድራት በግልጽ ይከፍልሃል ማለት ነው፡፡ አዎን እርሱ በአንተ ዘንድ እንደ ተበዳሪ ሆኖ ታየ፡፡ በዚህም አንተን ምን ያህል እንደወደደህና እንዳከበረህ አስተውል፡፡ እርሱ የማይታይ አምላክ እንደመሆኑ መጠን እንዲሁ እኛም ስንጸልይ በሥውር ላለው አባት ብለን እንጂ ከሰው ምስጋናን ለመቀበል ሽተን ሊሆን አይገባውም፡፡

በጸሎታችሁ አሕዛብን አትምሰሉአቸው

በመቀጠል ጸሎታችንን አንዴት ማቅረብ እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ “አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደነርሱ በከንቱ አትድከሙ” /ማቴ.6÷7/ አለ፡፡
ትመለከታለህ! አስቀድሞ ስለምጽዋት ሲያስተምር ወደ ከንቱ ውዳሴ የሚካተቱንን ነገሮች በማውጣት ከእነርሱ እንድንጠበቅ አዝዞን ነበር፡፡ ከእነዚህም ሌላ ግን ጨምሮ አላስተማረንም ወይንም ከድካማችን ካገኘነው እንጂ በአመፃ ካገኘነው ገንዘብ እንዳንመጸውት አስተማረን እንጂ ምጽዋቱ መቼ መፈጸም እንዳለበት ጊዜውን ለይቶ አላስተማረንም፡፡ ምክንያቱም “ስለጽድቅ የሚራቡ ብፁዓን ናቸው” በማለት ምጽዋታችን ምን መምሰል እንዳለበት አስቀድሞ አስተምሮ ነበርና ነው፡፡

ጸሎትን በተመለከተ ግን ደግሞ ደጋግሞ ነበር ያስተማረው፡፡ አስቀድሞ ጻፎችና ፈሪሳውያንን እንደወቀሳቸው ሁሉ “በከንቱ አትድከሙ” በማለት አሕዛብን ወቀሳቸው፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ ወገኖችንም አሳፈራቸው፡፡ጌታችን በትምህርቱ የምንሳብባቸውንና እኛም ልንፈጽማቸው የምንጓጓላቸውን ነገሮች ጎጂነት ነቅሶ በማውጣት ደጋግሞ አስተምሮናል፡፡ ምክንያቱም እኛ ሰዎች ስንባል በውጫዊ ገጽታቸው አምረውና አሽብርቀው በሚታዩ ነገሮች በቀላሉ ስለምንሳብ በውጭ ሲታዩ ጻድቃን የሚመስሉን ግብዞች መስሎ መመላለስን ስለምንመርጥ ነው፡፡

“በከንቱ አትድገሙ” በማለት እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች እጅግ የዘቀጠ አስተሳሰብ እንዳላቸው ገለጠ፡፡ እኛ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ሥልጣንን፣ ክብርን፣ የጠላት ነፍስን ባለጸግነትን እንዲሁም ሌላም እኛን የማይመለከቱን ነገሮችን በጸሎት ብንጠይቅ በከንቱ እንደመድገም ይቆጠርብናል፡፡

ስለዚህም “አትምሰሏቸው ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና” አለን፡፡ እዚህ ላይ ጌታችን እንዲህ ሲል ጸሎታችሁን አታርዝሙት ማለቱ አይደለም የጌታችን ዋናው የትምህርቱ ትኩረት ጊዜን በተመለከተ አይደለም ነገር ግን አስቀድመን እንዳስቀመጥነው የማይገቡ ጸሎታትን በማድረግ በከንቱ መድከም አብዝተንና አርዝመን የምንጸልየውን ጸሎት ነው፡፡

የሚገባ ጸሎት ከሆነ ደጋግመን መጸለይ እንዲገባ “በጸሎት ጽኑ” ተብለን ታዘናል፡፡ በኤፌ.6÷18 ላይም በጸሎት መጽናት እንዳለብን ተቀምጦልናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “ፊታችሁን ልናይ በእምነታችሁም የጎደለውን ልንሞላ ሌሊትና ቀን ከመጠን ይልቅ እንጸልያለን” /1ኛተሰሎ.3÷9-10/ በማለት በተግባር እየፈጸመ እንደነበር እናስተውላለን፡፡

ጌታችን ከጨካኙ ዳኛ ዘንድ ፍርድ ተጓደለብኝ በማለት በተደጋጋሚ ደጅ የጠናችውን መበለት ምሳሌ በማድረግ /ሉቃ.18÷1/ እንግዳ ስለመጣበት እንጀራ በእኩለ ሌሊት ከወዳጁ ይለምን ዘንድ የሄደውን ሰው ትጋት በማውሳትና ያም ወዳጁ የተጠየቀውን የሰጠበት ምክንያት ስናስተውል ስለወዳጅነቱ ሳይሆን ስለንዝነዛው ብዛት እንደሆነ አብራርቶ ገልጾልናል፡፡ በዚህም ያለማቋረጥ መጸለይ እንደሚገባ አስትምሮናል፡፡ በእርግጥ አጭር ስንኞችን ደጋግሞና አርዝሞ መጸለይ ይገባል አንልም ይህም እንደማይገባ ሲያስረዳ “በጸሎታቸው ብዛት የሚሰሙ ይመስላቸዋልና እነርሱን አትምሰሉአቸው” ብሎናልና፡፡

“ባትለምኑትም አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃል” ይላልና እርሱ የሚያስፈልገንን ካወቀ የእኛ መጸለይ ለምን አስፈለገ? ብሎ የሚጠይቅ ከእኛ መካከል አይጠፋም፡፡ አምላክን እንዲህ አድርግ ብለን አናዘውም ነገር ግን ከእርሱ ጋር የፍቃድ አንድነት ይኖረን ዘንድ ስለሚገባን ነው፡፡ /እግዚአብሔር ያለፈቃዳችን አንዳች ነገር ሊያደርግብን አይፈቅድም እርሱ ፈቃዳችንን ይጠይቃል/ ከዚህም በተጨማሪ ከእርሱም ጋር በጸሎት በምንመሠርተው የጠበቀ ግንኙነት ተጠቃሚዎች እንድንሆንና እንዲሆን የገዛ ኃጢአታችንን ዘወትር በማሰብ በትሕትና እንመላለስ ዘንድ ነው፡፡

“እናም ስትጸልዩ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር”/ማቴ.6÷9/

ይቀጥላል…