‹‹ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው›› (ማቴ.፯፥፲፪)
ግንቦት ፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
በሕይወታችን ውስጥ ለአምላካችን እንዲሁም ለሌሎች ፍቅራችንን የምንገልጽበት መንገድ ለራሳችን እንደምናደርገውን ሁሉ ከልብ ከመነጨ ፍቃድ ለባልንጀሮቻችን ማድረግ ነው፡፡ መሠረታዊ ነገሮች እንዲሟሉልን ብቻ ሳይሆን ለምድራዊ ኑሮአችን የሚያስፈልጉንን ሁሉ ስናደርግ እንዲሁ ለቤተ ሰቦቻችን፣ ለወዳጆቻችን፣ ለዘመዶቻችን እና ለጎረቤቶቻችን ማድረግን መርሳት የለብንም፡፡ ይህም ማዕድ ከመጋራት ጀምሮ አብሮ እስከ መቸገር፣ መራቆትና ኅዝንንም ሆነ ደስታን እስከ መካፈል ይደርሳል፡፡
ሰውን እንደራስ አድርጎ መውደድ እንደራስ አድርጎ ከማሰብ ጨምሮ ለራስ የሚያደርጉትን ሁሉ ለሰው ማድረግን እንደሚያካትት ከጌታችን ቃል እንማራለን፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ ምሳሌዎችን እናገኛለን፡፡ ከሁሉም የበለጠ ግን የሚነሣ አንድ ታሪክ አለ፤ ይህም በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል የተመዘገበው የደጉ ሳምራዊ ታሪክ ነው፡፡
አንድ ቀን አንድ የሕግ ባለሙያ ጌታችንን ሊፈትነው ቀርቦ «መምህር ሆይ የዘለዓለም ሕይወትን እንድወርስ ምን ልሥራ (ላድርግ)? ሲል ጠየቀው፡፡» ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕግ ዐዋቂው «በሕግ በመጽሐፍ የተጻፋውን አንተ እንዴት ታነባለህ? ብሎ ጠየቀው፤ ሕግ ዐዋቂውም ለጌታችን ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም ፣ በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደራስህ ውደድ» በማለት መለሰለት፡፡
ጌታችንም ለሕግ ዐዋቂው «እውነት መለስህ፡፡ የዘለዓለም ሕይወትን ለማግኘት በሕይወትም ለመኖር ከፈለክ ጌታ አምላክህን በፍጹም ነፍስህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደራስህ አድርገህ ውደድ» አለው፡፡
በዚህን ጊዜ ጌታችን ራሱን ከፍ አድርጎ ሌላውን ንቆ ጥያቄ ላቀረበው ሕግ ዐዋቂ ባልንጀራው ማን እንደሆነ እንዲረዳ እና ምን ማድረግ እንዳለበት የሚከተለውን ታሪክ በምሳሌ ሊነግረው እንዲህ በማለት ጀመረ፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ፤ ተጓዘ፡፡ ይህ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በመንገድ ላይ እየተጓዝ ሳለ በድንገት ወንበዴዎችና ሽፍቶች አገኝተውት መጥተዉ አስቆሙት፡፡ ገንዘቡን ወሰዱ፤ ልብሱንም ገፈፉበት:: ደብድበውም አቁስለው ሊሞት ሲቃረብ በመንገድ ላይ ጥለውት ሄዱ፡፡
አንድ ካህን በዚያ መንገድ ሲሄድ ያን ተደብድቦ የወደቀውን ሰው ቀርቦም ቢያየው ተጎድቷል፤ ነገር ግን ሳይረዳው አልፎ ጥሎት ሄደ፡፡ ከካህኑ ቀጥሎ ደግሞ አንድ ከሌዊ ወገን የሆነ ሰው በዚያ መንገድ ሲያልፍ በወንበዴዎች ተደብድቦ የወደቀውን ሰው አገኘው እና አየው:: ነገር ግን እርሱም ሳይረዳው ዝም ብሎ በመንገድ ላይ እንዳየው እንደቀደመው ሌዋዊውም ካህን ገለል ብሎ አልፎት ሄደ፡፡
አንድ ሳምራዊ ግን በዚያች መንገድ ሲሄድ አገኘው፤ አይቶም አዘነለት፤ ወደ ቆሰለው ቀርቦ በቁስሉ ላይ እንዲያደርቅለት ወይን አደረገለት፤ እንዲያለሰልስለት ደግሞ ዘይት በቁስሉ ላይ አፈሰሰለት፡፡ ደጉ ሳምራዊው የተደበደበውን ተጓዠ ሰው ቅርብ ወዳለው እንግዳ ማረፊያ ስፍራም ከአስገባው በኋላ እየተንከባከበውና እያስታመመው የሚፈልገውን እያደረገለት አብሮት በሰላም አደሩ፡፡ (ሉቃ.፲፥፳፭-፴፯)
በዚህ ታሪክ ላይ በደጉ ሳምራዊ የተመሰለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ አምላካችን እርሱ የወደቁትን የሚያነሣ፣ የተራቆቱትን የሚያለብስ፣ የተበዱለትን የሚክስ፣ የተጨቆኑትን የማይረሳ ለችግራቸውም የሚደርስ ነውና፤ ቸርነቱንና ፍቀሩን በምሳሌ አስረድቶናል፡፡ ይህም ብቻም ሳይሆን እርሱ እንዳደረገውም እንዲሁ እኛም ለሌሎች እንድናደርግ አሳስቦናል፡፡ አምላካችን እኛን እንደወደደን እንዲሁ እኛም ባልንጀሮቻችን እንድንወድ፣እርሱን ለእኛ እንደሚያዝን እኛም ለሰዎች እንድናዝን፣ ማንም የሌለውንና ተንቆ፣ ተትቶ እና ወድቆ የነበውረን ሰው ከወደቀበት አንሥቶና አክሞ እንዳዳነው እኛም የታመሙትን ማስታመም፣ የተራቆቱትንና የወደቁትን ማስንሣትና ለችግራቸው መድረስ እንዳለብን ከደጉ ሳምራዊ እንማራለን፡፡
የአምላካችን ፍቅር ቃላት ከሚገለጹት በላይ ቢሆንም በቅዱሳን ልጆቹ እንዲሁም በቅዱስ መስቀሉ ላይ ተሰቅሎ አሳይቶናል፡፡ እኛም ባልንጀሮቻችን በቃልም በተግባርም እንድንወድ አዞናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ሲያስተምር እንዲህ ብሏል፤ ‹‹እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና።›› (ማቴ.፯፥፲፪)
ሲርበን መብላት፣ ሲጠማን መጠጣት፣ ሲበርደን ሙቀት፣ ሲከፋን መደሰት፣ ሲቸግረን ችግራችንን መወጣት እንዲሁም ስንራቆት መልበስ እንደምንፈልገው ሁሉ ሌላውም “ይርበዋል፤ ይጠማዋል፤ ይበርደዋል፤ ይቸገራል፤ ይራቆታል” ብሎ በማሰብ አስፈላጊውን ነገር እንደ ዓቅማችን ካለን አካፍለን ማድረግ እንዳለብን ጌታችን በቃልም በተግባርም አስተምሮናል፡፡ ‹‹ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና›› በማለት እንደተናገረውም አምላካችን በሊቀ ነቢያት ሙሴ በኩል በደብረ ሲና ተራራ ላይ ከሰጠን ከዐሥርቱ ሕግጋት መካከል ይህ ሕግ ይገኝበታል፡፡ ‹‹ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ›› እንዲል፡፡ (ዘሌ.፲፱፥፲፰)
ሰዎች ሊያደርጉልን የምንፈልገውን እኛም ለሰዎች እንድናደርግ እንዲሁም ራሳችንን እንደምንወደው ባልንጀሮቻችንን እንድወድ አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን!!!