DSC02522

ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል ስለምትገኝበት ሁኔታ ዐውደ ጥናት ተካሄደ

ግንቦት 7/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

DSC02522የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል የምትገኝበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ቅዳሜ ግንቦት 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ተካሔደ፡፡ አውደ ጥናቱ በማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል አስተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን በዋና ክፍሉ ስር ከሚገኙት ዴስኮች መካከል የኦሮምኛ ትርጉም ዴስክ አማካይነት ቀርቧል፡፡

የኦሮምኛ ትርጉም ዴስክ በመደበኛና በኢመደበኛ አባላት የተጠናከረ ክፍል እንደመሆኑ በኦሮሚያ ክልል ቤተ ክርስቲያናችን ምን ላይ እንደምትገኝ የሚያሳይ ጥናት ይዞ እንዲቀርብ በተሰጠው ሓላፊነት መሠረት ጥናቱን ይዞ መቅረቡን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ሓላፊ ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ገልጸዋል፡፡ የጥናቱ ዋነኛ ዓላማን አስመልክተው ቤተ ክርስቲያናችን በኦሮሚያ ክልል ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ መዳሰስ፤ ችግሮቹን ለመፍታት ምን መደረግ እንደሚገባና ምዕመናን በአንዳንድ እምነቶች እንዳይወሰዱ በመረጃ የተደገፈ ምላሾችን መስጠት የሚያስችል ጥናት እንደሆነ ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኦሮምኛ ትርጉም ዴስክ ሓላፊ የሆኑት ቀሲስ ምስጋናው አገሳ እንደገለጹት ዴስኩ የትርጉም ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ፣ በተለይም ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞችና እኅቶችን በማሰባሰብ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከአማርኛ ወደ ኦሮምኛ በመተርጎም ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ በዚህ ዓመትም 5 መፃሕፍትን ተርጉመው ለምእመናን ለማድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝና ይህ ጥናት በእነዚሁ አባላት አማካይነት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጥናት አቅራቢዎቹ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ዋና ዋና የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ያሏቸውን የሚያሳይ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን ክልሉ ሰፊ እንደመሆኑ ችግሮቹም ስፋት ያላቸው ስለሆነ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው ያሏቸውንም በሁለት በመክፈል ውስጣዊ ችግሮችና ውጫዊ ችግሮች በማለት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ ምዕመናን ከኦሮምኛ ቋንቋ በቀር መስማትና መናገር ባለመቻላቸው በቋንቋቸው የሚገባውን አገልግሎት መስጠትና ማግኘት ያለመቻሉ፤ ንስሐ ለመግባት በአስተርጓሚ እስከማከናወን መድረሱ፣ በቋንቋው የተዘጋጁ የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትና የቋንቋው ተናጋሪ አገልጋይ ያለመኖር፣ የምዕመናን ባህልና አኗኗር ማዕከል ያደረገ ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት ያለመቻሉ፤ በተለያዩ እምነቶችና ባዕድ አምልኮዎች መጠመዱ…. የመሳሰሉት እንደሆኑ በጥናት አቅራቢዎቹ ተዳስሰዋል፡፡

DSC02521ከተለያዩ ዋና ዋና ክፍሎች የተገኙት የማኅበሩ አባላት በጥናቱ ላይ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን እንዲሁም የመፍትሔ ዐሳቦችን አቅርበዋል፡፡ ከጥናቱ አቅራቢዎችም ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም መፍትሔዎቹን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም  መካከል በክልሉ ምዕመናን በቋንቋቸው የሚገለገሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በተወላጆቹ /በቋንቋው ተናጋሪ አገልጋዮች/ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል፣ በኦሮምኛ ቋንቋ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማዘጋጀትና ማሰራጨት፣ አገልጋዮችን ለማፍራት ማሠልጠኛ ተቋም  መክፈት፣ በግቢ ጉባኤያት ለሚገኙ ተማሪዎች የአብነት ትምህርት መስጠት፣ ተጨባጭ ጥናቶችን በተጠናከረ ሁኔታ ማካሔድ…… የመሳሰሉትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የተገለጹት ችግሮችና ከአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች የቀረቡ ጥያቄዎችና የመፍትሔ ዐሳቦችን በማጠናከር ከማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አስፈጻሚ ጋር ተነጋግሮና አጽድቆ በአፋጣኝ ወደ ትግበራ እንደሚሸጋገር ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ የገለጹ ሲሆን ጥናት አቅራቢዎቹንና የየክፍሉ ተወካዩችን በአውደ ጥናቱ በመገኘታቸው አመስግነዋል፡፡

የአባ ማሩ ተረት /ለሕፃናት/

ግንቦት 7/2004 ዓ.ም.

በልያ አበበ

እንደምን አላችሁ ልጆች! እግዚአብሔር ይመስገን ደኅና ነን እንደምትሉ አልጠራጠርም፡፡ ዛሬ የምነግራችሁ ተረት ስለ አንበሳ፣ ጥንቸልና አሳማ ነው እሺ በጣም ጥሩ ልጆች ተረቱን ልንገራችሁ?  ግን እኮ ስለራሴ አላስተዋወኳችሁም፡፡ ስሜ አባ ማሩ ዘነበ ይባላል፡፡ ቁመቴ በጣም አጭር ነው፡፡ ፊቴ ደግሞ ልክ እንደ ብርቱካን ክብ ሆኖ ዓይኖቼ ትናንሽ ናቸው፡፡ ሁል ጊዜ የምለብሰው ነጭ ሱሪና ነጭ ሸሚዝ ነው፡፡ ከእጄ ነጭ ጭራ አይለይም፡፡ ለምን ነጭ ጭራ እንደምይዝ ታውቃላችሁ? በሰፈሬ የሚኖሩ እንደ እናንተ ያሉ ሕፃናት ወደ 12፡00 ሰዓት አካባቢ ፀሐይ ስትገባ ተሰብስበው ይመጡና “አባ ማሩ ዘነበ ተረት ይንገሩን?” እያሉ በዙሪያዬ ስብስብ ይላሉ፡፡ እኔም ልጆችን በጣም ስለምወዳቸው ትንሸን ወንበሬን ይዤ ከቤቴ እወጣና ከግቢያችን ካለው ሰፊ ሜዳ ቁጭ እላለሁ፡፡ ልጆችም በዙሪያዬ ይሰበሰባሉ እሳት እየሞቅን ተረቱን አጫውታቸዋለሁ ታዲያ ያን ጊዜ ትንኞች በአፌ ውስጥ እንዳይገቡ በነጩ ጭራዬ እከላከላቸዋለሁ፡፡ ስለራሴ ይኸን ያኽል ከነገርኳችሁ ወደ ተረቴ ልመለስ፡፡ ዝግጁ ናችሁ ልጆች? ጎበዞች፡፡

 

ተረት ተረት፤ “የመሠረት” አላችሁ፤ በአንድ ሰፊ ደን ውስጥ አንበሳ፣ ጥንቸልና አሳማ ይኖሩ ነበር፡፡ ከዕለታት በአንደኛው ቀን አንበሳው በጣም ስለራበው ምግብ ፍለጋ ከዋሻዋ ሲወጣ “እግዚአብሔር ሆይ ዛሬ በጣም ስለራበኝ እባክህን ምግብ ስጠኝ?” ብሎ ጸለየ፡፡ ጸሎቱን እንደጨረሰ ከፊት ለፊቱ ጥንቸልን ተመለከታት አንበሳውም “አምላኬ ሆይ ጸሎቴን ሰምተህ ምግብ እንድትሆነኝ ጥንቸልን ስላዘጋጀህልኝ አመሰግንሃለሁ” ብሎ አፉን ከፍቶ ዐይኑን አፍጥጦ ቆመ… ጥንቸልም አንበሳውን ስታይ በጣም ደነገጠችና “ወይኔ አምላኬ ይኼ አንበሳ በጣም ያስፈራል እባክህን የዛሬን ብቻ ከዚህ አንበሳ አፍ አውጣኝ” ብላ ጸለየች፡፡

 

አንበሳው፡- “እግዚአብሔር ሆይ አብላኝ” በማለት እየ ጸለየ ጥንቸሏም “እግዚአብሔር ሆይ ከዚህ አንበሳ አድነኝ” እያለች እየጸለየች ሁለቱም መሮጥ ጀመሩ፡፡ አንበሳው ከኋላ ሲያባርራት ጥንቸሏም ስትሮጥ አንድ ወንዝ አገኘች፡፡ ወንዙን ዘላ ስትሔድ ከወንዙ አጠገብ አንድ አሳማ በልቶ ጠጥቶ ጸሎት ሳያደርግ ተኝቶ ነበር፡፡ አንበሳውም ዞር ሲል የተኛ አሳማ ተመለከተ ወዲያው አንበሳው የተኛ አሳማ ከአጠገቤ እያለ ከጥንቸል ጋር ምን አሯሯጠኝ አለና ጥንቸሏን ትቶ አሳማውን በላ፡፡ ከዚያ በኋላ የጥንቸሏን መዳን የአንበሳውን መብላት የአሳማውን መበላት ያዩ አንድ ሽማግሌ

 

“ልብላም ያለ በላ፤ ልውጣም ያለ ወጣ ከመሐል የተኛ አሳማ ተበላ” ብለው ግጥም ገጠሙ ይባላል፡፡

 

ልጆች ከዚህ ታሪክ ምን ተማራችሁ? ጸሎት ከመጥፎ ነገር ያድናል ካላችሁ ትክክል ናችሁ፡፡ ስለዚህ እናንተም ምግብ ስትበሉ ማታ ስትተኙ ጠዋት ስትነሡ አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት ከጸለያችሁ ከመጥፎ ነገር ትድናላችሁ እሺ፡፡

 

ለዛሬው ተረቴን ከዚህ አቆማለሁ በሌላ ጊዜ በሌላ ተረት እስክንገናኝ ድረስ ደኅና ሁኑ ልጆች፡፡

የደጉዋ እናት ልደት/ለሕፃናት/

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በሊያ አበበ

በኢየሩሳሌም አገር የሚኖሩ ኢያቄምና ሃና የተባሉ በጣም ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ኢያቄምና ሃና ለእግዚአብሔር የታዘዘ  በተቀደሰ ጋብቻ ውስጥ በብዙ ዘመናት አብረው ቢኖሩም በነዚያ ጊዜያት ወስጥ አንድ ልጅ እንኳ ስላልነበራቸው እጅግ ያዝኑ ነበር፡፡ ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ አጥብቀው ይለምኑት ነበር፡፡

ከእለታት አንድ ቀን ኢያቄምና ሃና እርግቦች ጫጩቶቻቸውን ሲያጫውቱ ተመልክተው “ለነዚኽ ወፎች እንኳ ልጆችን የሰጠህ አምላክ ለእኛስ መች ይሆን ልጅ የምትሰጠን?” ብለው እጅግ አምርረው አለቀሱ፡፡ ከሐዘናቸውም ጽናት የተነሳ እንቅልፍ ያዛቸውና ተኙ፡፡

 

በተኙ ግዜም ለሁለቱም እግዚአብሔር መልካም ፈቃዱን በህልም ገለጠላቸው፡፡ ኢያቄም በህልሙ ሃና በእቅፍ ውስጥ ከፍሬዎች ሁሉ የምትበልጥ መልካም ጣፋጭ ፍሬ ይዛ ተመለከተ፡፡ ሃና የኢያቄም በትር ለምልማ፣ አብባና አፍርታ ተመለከተች፡፡ ከእንቅልፋቸውም ነቅተው ስለ ህልማቸው ተነጋገሩ፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆንላቸው በጸሎት ጠየቁ፡፡ እግዚአብሔር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ ቢሰጣቸው አድጎ እኛን ያገልግለን ይታዘዘን ሳይሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ እንዲሆን እንደሚሰጡት ቃል ገቡ፡፡

 

ከዚህ በኋላ ነሐሴ 7 ቀን ሃና ፀነሰች፡፡ ሃና በእርጅናዋ ጊዜ መፅነሷ የተመለከቱ ዘመዶቿና ያገሯ ሰዎች ተገርመው እየመጡ ይጠይቋት ነበር፡፡ ከነዚህም ሰዎች መካከል አንዱ ዐይነ ስውር የነበረችው የአርሳባን ልጅ ናት፡፡ የአርሳባን ልጅ ወደ ሃና መጥታ እውነትም ሃና መጽነሷን ለማረጋገጥ ሆዷን ዳሰሰቻት፡፡ በአድናቆትም ሳታስበው ዐይኗን ስትነካ ዐይኗ በራላት፡፡ በሌላ ግዜም የአጎቷ ልጅ በህመም ምክንያት ይሞትና ሃና ትወደው ስለነበር ልታለቅስ ወደአረፈበት ቤት ትሔዳለች፡፡ እንደደረሰችም አስክሬኑ በተቀመጠበት መካከል አልጋ ዙሪያ ስታለቅስ ሳለ ድንገት ጥላዋ ቢያርፍበት የሞተው ሰው ተነስቶ ሃና የአምላክ እናት የምትሆን እመቤታችንን እንደምልድና በዚህም ሃና እጅግ የከበረችና ምስጋና የሚገባት መሆኗን መሰከረ፡፡

 

ሃና በፀነሰች ግዜ የተደረጉ ብዙ ተአምራትን አይሁድ አይተው ገና በፅንስ ግዜ ይህን ያክል ተአምራት ያደረገ ሲወለድማ ብዙ ነገር ያደርጋል ብለው በምቀኝነት ተነሳስተው ኢያቅምና ሃናን ሊገድሏቸው ተነሱ፡፡ እግዚአብሔር ግን መልአኩን ልኮ ኢያቄምና ሃና ወደ ሊባኖስ ተራራ እንዲሸሹ አደረጋቸው፡፡ በዚያም ሆነው ግንቦት 1 ቀን ከንጋት ኮከብ ይልቅ የምታበራ እጅግ ያማረች የተቀደሰች የምትሆን ልጅን ወለዱ፡፡ ስሟንም ማርያም አሏት፡፡ ልጆች እኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡

የመጻሕትና የድምጽ ወምስል የምረቃ መርሐ ግብር ተካሔደ

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር ያሳተማቸውን መጻሕፍትና የድምጽ ወምስል የምረቃ መርሐ ግብር ሚያዚያ 27 ቀን 2004 ዓ.ም. በብሔራዊ ሙዚየም ትልቁ አዳራሽ አስመረቀ፡፡ ከተመረቁት መጻሕፍትና የድምጽ ወምስል ሥራዎች መካከል ዐስሩ የትርጉምና ወጥ መጻሕፍት ሲሆኑ በቪሲዲ እና በሲዲ የተዘጋጁ የአማርኛና የሞሮምኛ ስብከቶች ዘጋቢ ፊልሞች፣ ትርጉም ፊልሞችና መዝሙራት ይገኙበታል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም መርሐ ግብሩን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር በምረቃው ላይ የተገኙትን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችን በማመስገን ማኅበረ ቅዱሳን ከተሠረተ 20 ዓመታት አንስቶ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ከተጠቀመባቸው መንገዶች ዋነኛው መንፈሳዊ ጋዜጣ መጽሔትና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የተጻፉ መጻሕፍትንና የድምጽ ወምስል ውጤቶችን እያሳተመ ይገኛል፡፡ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ የልማት ተቋማት አስተዳደርን በሥሩ በመመሥሪት ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ ለማድረግ የኅትመት ውጤቶችን በማሳተምና በማሰራጨት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ከኅትመት ከበቁት የድምጽ ወመስል ሥራወች መካከል ከእያንዳንዱ የተቀነጨቡ ክፍሎች የቀረቡ ሲሆን የመጻሕፍት ደራሲያንና ተርጓሚያን ከመጻሕፍቱ አንድ አንድ አንቀጽ አንብበዋል፡፡ በዲ/ን ታደለ ፈንታው በኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል የመጻሕፍት ዝግጅት ክፍል አስተባባሪና በአቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ የልማት ተቋማት አስትዳደር ዳይሬክተር የመጻሕፍት ዝግጅት ክፍል እንቅስቃሴና የልማት ተቋማት አስተዳደር ልዩ ልዩ ክፍሎች ያከናወኗቸውን ተግባራት አጠር ያለ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

“የንስሓ ሸንጎ” የተሰኘ ወጥ መንፈሳዊ ልቦለድ የድርሰት ሥራቸውን ያቀረቡት ደራሲት ፀሐየ መላኩ ስለ ጥረታቸውና ሥራዎቻቸው ሲገልጹ አለማዊ ሕይወት መሠረቱና ማቃኛው መንፈሳዊ ሕይወት ነው ሁለቱንም ለማገናዘብ አጋጣሚው ነበረኝ ይላሉ፡፡ በተለይም አባታቸው ካህን ስለ ነበሩ ከለጅነት ጀምሮ መንፈሳዊ እውቀትን ለመቅሰም እድሉን አግኝተዋል፡፡ የኅብረተሰቡን ሕይወትና ፍላጎት፣ እምነት፣ ትዝብትና ገመና ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን ወደ ኅብረተሰቡ አድርሰዋል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ አለማዊውን ሕይወት ማስተካከልና የተሟላ ስብእና ማግኘት እንደሚቻል ማስተማር ስለፈለግሁ “የንስሓ ሸንጎ” የተሰኘውን ወጥ መንፈሳዊ ድርሰት አቅርቤያለሁ ብለዋል፡፡ ሙሉ ጊዜያቸውን ለሥነ ጽሑፍ እንደሚሰጡና የኢትዮጵያዊው ታላቁ የሃይማኖት አርበኛ የሆኑት የቅዱስ ጴጥሮስን ታሪክ ለመጻፍ ጥረት በማድረግ  ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ሕልውና እንዳይቋረጥ አጋዥነቱን እያሳየ ስለሆነ ይህንን የጀመረውን ጉዞ ሌሎችንም ጸሐፍት የሚያበረታታ ስለሆነ ቢቀጥልበት በማለት አሳስበዋል፡፡ ደራሲት፣ ገጣሚት፣ ሰዓሊት ፀሐይ መላኩ “እመምኔት” የተሰኘ መንፈሳዊ ልቦለድ መጽሐፍ ከዚህ በፊት ከጻፏቸው መጻሕፍት መካከል አንዱ ሲሆን አሁን ደግሞ “የንስሓ ሸንጎ”ን ይዘው ቀርበዋል፡፡ በመጽሐፉ ዙሪያ በዲ/ን ታደለ ፈንታው መጽሐፍ ያተኮረባቸው መሠረታዊ ነጥቦት ላይ ትንታኔ ተሰጥቷል፡፡

ለምረቃ ከበቁት መጻሕፍት 3ቱን የጻፉት ዲ/ን ታደለ ፈንኀታው ስለ መጻሕፍቱ እንደገለጹት መጻሕፍቱ ነገረ ቅዱሳንን የሚያወሱ ናቸው፡፡ አስቀድሞ የነበሩ አባቶቻችን አሁን ያለው ትውልድ እየተፈተነበት ያለውን ሕይወት እግዚአብሔርን በመያዝ በመንፈሳዊ ሕይወት እንዴት እንደተመላለሱ ስለሚያሳይ ትውልዱ ራሱን እንዲጠብቅ ታላቅ መልእክት ያስተላልፋሉ ብዬ ስለማስብ ትኩረቴ ነገረ ቅዱሳን ላይ አድርጌአለሁ” ብለዋል፡፡

በመጻሕፍቱና በድምጽ ወምስል ሥራዎቹ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን በተለይም ማኅበረ ቅዱሳን ማተማያ ቤት ቢኖረው በኅትመትና ሥርጭት ረገድ አገልግሎቱን ማስፋፋት ይችል እንደነበር ተገልጿል፡፡ በተሰጡ አስተያየቶች ዙሪያ በማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋመት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ደራሲያን የማተሚያ ቤት ሓላፊዎች ከተለያዩ ደራሲያን ማኅበራትና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራንም ያሬዳዊ ዝማሬን አቅርበዋል፡፡

Tserha Tsion Sebakian wongel

የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር ሰባኪያነ ወንጌልን አስመረቀ

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር በ14ኛው ዙር ለ3 ወራት ያሰለጠናቸውን 47 ሰባኪያነ ወንጌልን ሚያዚያ 21 ቀን 2004 ዓ.ም. አስመረቀ፡፡ በማኅበሩ የተመሠረተው የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የስብከተ ወንጌልTserha Tsion Sebakian wongel ማሰልጠኛ ተቋም በ12 የትምህርት ዓይነቶች ከጥር 21 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ከ16 ሀገረ ስብከቶች በተለይም ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ ተውጣጥተው የተመረጡና እያንዳንዳቸው ከሁለት እስከ ሦስት ቋንቋ መናገር የሚችሉ ሰባኪያነ ወንጌልን ቡራዩ አካባቢ በሚገኘው በተቋሙ ግቢ ውስጥ በደመቀ መንፈሳዊ መርሐ ግብር አስመርቋል፡፡ ከተመራቂ ደቀ መዛሙርት መካከል መነኮሳት፣ ካህናት፣ መሪጌቶች፣ ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት ያካተተ ሲሆን ‹‹ለቤተ ክርስቲያናችን እጣን፣ ጧፍና ንዋያተ ቅድሳት ብቻ ሳይሆን ሰውም እንስጥ›› የሚል መመሪያ ይዞ በመነሣት በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የመምህራን እጥረት ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ማናዬ አባተ የማኅበሩ መንፈሳዊ አገልግሎት መምሪያ ሓላፊ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እንዲሁም ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ የሊቃውንት ጉባኤ አባል ተገኝተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ‹‹ማኅበሩ እያደረገ ያለውን ጥረት ለሌሎች አርአያ የሚሆንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ደጋፊ አገኘች የምንልበት ነው” በማለት ገልጸዋል፡፡ ለተመራቂ ደቀBitsu Abune Epiphanios መዛሙርትም “ጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር እናንተን በወንጌሉ ቃል እንዳስታጠቃችሁ በሔዳችሁበትና በደረሳችሁበት ስፍራ ሁሉ የጠፉትን ወገኖቻችን የተበተኑትን አንድ በማድረግ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውለታ ለትመልሱ ይገባል” በማለት አደራቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ተመራቂ ደቀ መዛሙርቱን ካስተማሩ አባቶች መካከል አንዱ ሲሆኑ ባስተላለፉት መልእክት “ግራኝ መሐመድ እንደተሸነፈ ልክ እንደዛሬው ማኅበረ ቅዱሳንና ማኅበረ ጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ ኖረው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ አፍሪካን ታጠምቅ ነበር፡፡” በማለት የማኅበሩን ጥረት አበረታተዋል፡፡

የማኅበሩ አባላት ልጆቻቸው ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ በማድረግ ረገድ በየሰንበት ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ላይ የሚሳተፉ ሲሆን በዕለቱ በመድረክ ላይ ያሬዳዊ ዝማሬን አቅርበዋል፡፡ ተመራቂ ደቀ መዛሙርትም አስር በሚደርሱ ቋንቋዎች ያሬዳዊ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን የተማሩትን ትምህርት በተግባር ላይ እያዋሉ ስለመሆናቸው ምስክር ይሆን ዘንድ በአንድ ተመራቂ ደቀ መዝሙር ትምህርተ ወንጌል ተሰጠቷል፡፡

የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር ከሰንበት ትምህርት ቤቶች የተወጣጡና በአንድነት በመኖር ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፊት ጽኑ አላማ ባላቸው ምእመናን የካቲት 23 ቀን 1980 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ቀደም ሲል ከፍትህ ሚኒስቴር አሁን ደግሞ ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ መንፈሳዊ ማኅበር ነው፡፡ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ የመለከት መጽሔትን በማሣተምና በማሰራጨት፤ በአካባቢው ለሚገኙ ረዳት ለሌላቸው አረጋውያንና ወላጅ አልባ ለሆኑ ሕፃናት የዕለት ምግብ በመስጠት፤ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስና የትምህርት መሣሪያዎች ድጋፍ በማድረግ ፤አቅም ለሌላቸው በማኅበሩ ዘመናዊ ት/ቤት በአነስተኛ ክፍያ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡

በጎ አድራጊ ምዕመናንን በማስተባበር ባለ ሁለት ፎቅ ዘመናዊ ሕንፃ በማጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሔደውን የሰባኪያነ ወንጌል ሥልጠናን በአንደኛው ፎቅ ላይ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ አስር የማደሪያ ክፍሎች ሲኖሩት በአንድ ዓመት በ2 ዙር እስከ 120 ደቀ መዛሙርትን ማሰልጠን ያስችላል፡፡ የመጸዳጃ ቤት፣ የገላ መታጠቢያ፣ የምግብ ማብሰያና በአንድ ጊዜ ከ500 ሰው በላይ ማስተናገድ የሚያስችል አዳራሽ የያዘ ነው፡፡ ስልጣገኞቹ ሙሉ የሕክምና ወጪ፤ የትምህርት መሣሪያዎች ድጋፍ በቀን 3 ጊዜያት የሚመገቡት ምግብ በማኅበሩ ይሸፈናል፡፡ ሕንፃው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የሰባኪነ ወንጌል ማሰልጠኛ ተቋም በዓመት በ3 ዙር የሰባኪያነ ወንጌል ሥልጠና ለመስጠት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ማኅበሩ እስከ አሁን ድረስ በ14 ዙር ሥልጠናዎች 612 ሰባኪያነ ወንጌል ማሰልጠኑን መንፈሳዊ አገልግሎት መምሪያ ሓላፊው አቶ ማናዬ አባተ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ ሠልጣናቹ የዘመናዊ ትምህርት ተማሪ ከሆኑ 10ኛ ክፍልና ከዚያ በላይ፣ የአብነት ተማሪ ከሆኑ በዘመናዊው ትምህርት ስድስተኛ ክፍልና ከዚያ በላይ የሆኑትን ከየሀገረ ስብከቱ የሚመረጡበት መስፈርት ሲሆን በተጨማሪም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የወሰኑና የአካባቢውን ቋንቋ መስማትና መናገር የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡

ከደቡብ ኦሞ ጂንካ ሀገረ ስብከት አንቀጸ ብጹአን አቡነ ተክለ ሃይማሃት ቤተ ክርስቲያን የመጡት አባ ኃ/ሚካኤል በድሉ ከተመራቂ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ “አካባቢያችን በመናፍቃን የተከበበ ነው፡፡ ምዕመናንም ሆኑ ካህናት ብዙ እውቀት የለንም፡፡ መናፍቃንን የምናሸንፍበት ትምህርት አጥተን ብዙዎች ተወስደውብናል፡፡ በሥልጠናው በነፃ የተቀበልነውን እውቀት በነፃ ለወገኖቻችን እናስተምራለን” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከምዕመናን መካከል ከጉጂ ቦረናና ሊበን ሀገረ ስብከት ሜጋ ቅዱስ ሚካኤል ሰበካ ጉባኤ አባል የሆኑት አቶ ከበደ ተሰማ ርቀት ሳይገድባቸው እዚህ ድረስ የመጡት ከሚያገለግሉበት ቤተ ክርስቲያን ተመርጠው ለሰልጠናው የመጡትን ተመራቂ ደቀ መዛሙርትን ለመቀበል እንደሆነና አካባቢያቸውን አስመልክተው ባደረጉት ገለፃ “ያለንበት አካባቢ እጅግ ኋላ ቀር ነው፡፡ ኬንያ ድንበር ላይ ነው የምንገኘው፡፡ የአገልጋዮች እጥረት ያለበትና ቦታውም አመቺ ያልሆነ ነው፡፡ የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር ደርሶልን ከጭንቅ እየገላገለን ነው፡፡ ወደፊትም ትብብራችሁ እንዳይለየን” በማለት ተማጽነዋል፡፡

ተመራቂ ደቀ መዛሙርት ከብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ እጅ የምስክር ወረቀትና መጽሐፍ ቅዱስ ተቀብለዋል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ የደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ምክሐ ደናግል ማርያም ሰንበት ትምህርት ቤት በስጦታ የተገኘ ስለመሆኑ ከሓላፊዎቹ የተገለጸ ሲሆን  ደቀ መዛሙርቱን ለማፍራት በተደረገ ጥረት ውስጥ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሥልጠናውን ለሰጡ አካላት ማኅበሩ ምስጋናውን በእግዚአብሔር ስም አቅርቧል፡፡

የእግር ጉዞው መርሐ ግብር ተራዘመ

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ  የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት ምስረታን ምክንት በማድረግ ለሚያዚያ 27 ቀን 2004 ዓ.ም ተዘጋጅቶ የነበረው የእግር ጉዞ መርሐ ግብር ወደ ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም. ተራዘመ፡፡ የመርሐ ግበሩ አስተባባሪ ሰብሳቢ ዲ/ን ዋሲሁን በላይ ቀኑ የተቀየረበትን ምክንያት እንደገለጹት የእግር ጉዞው በታቀደለት ጊዜ ለማካሔድ ከፍተኛ ጥረቶች መደረጋቸውን፤ በርካታ ቲኬቶችና ካናቴራዎችን ማሰራጨታቸውን፤ ነገር ግን ከምእመናን በተደጋጋሚ በቀረቡ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች አንደኛ ከሰሙነ ሕማማት ጀምሮ በትንሳኤ በአል ምክንያት ምእመናን የተለያዩ ወጪዎችን ማውጣታቸውንና በጉዞው ላይ ለመሳተፍ ትኬቱን መግዛት ያለመቻላቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከትንሳኤ በአል በኋላ የቀኑ ማጠር፤ እንዲሁም በበአለ ሃምሳ ምክንያት የተለያ የማኅበራዊ ሕይወት ተሳትፎ ጎልቶ የሚታበት ወቅት በመሆኑ ቀኑ እንዲቀየርላቸው ከፍተኛ ግፊት በማድረጋቸው  ጥያቄያቸውን ተቀብለን የእግር ጉዞው መርሐ ግብር ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም. እንዲሆን ተወስኗል ብለዋል፡፡ ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም የተመረጠበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ ምእመናን ከትንሣኤ በአል ጋር ተያይዞ ከማኅበራዊ ሕይወት ፋታ ያገኙበታል ተብሎ መታሰቡና ቅድስት ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው በዓላት አንዱ የጰራቅሊጦስ ዕለት በመሆኑ ቀኑን በአንድነት ሆነን እግዚአብሔርን እያመሰገንን እንድንውል በማሰብ ነው ብለዋል፡፡

ለምእመናን ባስተላለፉት መልእክት ዋናው የጉዞው ዓላማ የማኅበራችን 20ኛ ዓመት ምሥረታ ነው፡፡ በ20 ዓመታት ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻውን ያደረገው ምንም ነገር የለም፡፡ ከቅዱስ ፓትርርኩ ጀምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያዩ አካላትና ጽ/ቤቶች፤ ከሠራተኛ ጉባኤያት፤ ከሰ/ት/ቤቶች፤ በተለይም ከምእመናን ጋር በኅብረት ሰርተናል፡፡ አብረን ከተጓዝናቸው እሰካሁንም ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በምክራቸው፤ በጸሎታቸው፤ በእውቀታቸው፤ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው እያገለገሉ ካሉ አካላትና ምእመናን ጋር በኅብረት እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ቀን ነው፡፡ ቀጣይ ጊዜያችን ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ጠንክረን አብረን ተያይዘን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ከእኛ የምትፈልገውን አገልግሎት የምንፈጽምበት እንዲሆን ቃል የምንገባበት ዕለት ስለሆነ ምእመናን የተዘጋጀውን ቲኬት በመግዛት በእግር ጉዞው እንዲሳተፉና የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

በእግር ጉዞው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የመምሪያ ሓላፊዎች፤ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፤ ሰበካ ጉባኤያት፤ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ምእመናን ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ መንፈሳዊና ምእመናንን ሊያስተምሩ የሚችሉ መርሐ ግብሮች ተዘጋጅተዋል፡፡

 

ጉዞው የሚደረገው፤ ወደ መንበረ ክብር ደብረ ታቦር ቅዱስ ሚካኤልና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ነው፡፡ የጉዞው መነሻ ቦታዎች፤ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፤ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል /አምስት ኪሎ/ እና ሰሜን ማዘጋጃ ቶታል ናቸው፡፡

 

የጉዞው መነሻ ስዓት፤ ከጠዋቱ 1፡00 ስዓት ሲሆን ከምእመናን የሚጠበቁ ጉዳዮች በተመለከተ ለመንፈሳዊ ቦታዎች የሚመች አለባበስ መልበስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የሩስያው ፕሬዝዳንት ለሀገራቸው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምስጋና አቀረቡ

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በስንሻው ወንድሙ

የሩስያ ፕሬዝዳንት ዴሚትሪ ሜድቬዴቭ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ ዜጎች ዘንድ መንፈሳዊ ሥርዐት እንዲጐለብት ለምታደርገው እንቅስቃሴ ከሁለት ሳምንት በፊት ምስጋና ማቅረባቸውን ዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

 

የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ሚያዝያ 7 ባደረጉት ንግግራቸው የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ሕዝቦች ባሕልና ወጋቸውን ከሃይማኖት ሥርዐት ጋር ጠብቀው እንዲቆዩ ለአደረገችው አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረባቸውን ዘገባው አመልክቶ ፕሬዝዳንቱ «ይህን የሐሴት ቀን ከእናንተ ጋር በማሳለፌ ደስታ ተሰምቶኛል፤ በሀገሪቱ ውስጥ ሃይማኖታዊ ሥርዐት እንዲሰፍን ለምታደርጉት እንዲሁም በሕዝቡ ዘንድ ሰላም እንዲሰፍንና መጪውን ትውልድ በበጐ ሥነ ምግባር ለመቅረጽ ለምታካሂዱት እንቅስቃሴ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እወዳለሁ» ሲሉ መናገራቸውንም ዘግቧል፡፡

 

ፕሬዝዳንቱ አክለው የበዓሉ መከበርና ሥርዐቱን የጠበቀ መሆን ለሰላምና ለመቻቻል እንዲሁም መንፈሳዊ እሴቶችን ከማጎልበት አንፃር አርአያ የሚሆን ተግባር ነው ማለታቸውን የዘገበው ጋዜጣ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ሕዝቦች ጠባቂ ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ ላለፉት በርካታ መቶ ዓመታት ጠብቃ ያቆየችውን የሀገር አንድነትን የመጠበቅ ሓላፊነት አሁንም አጠናክራ እንድትቀጥል መጠየቃቸውን ዘገባው አስፍሯል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከቤተ ክርስቲያኗ የተሰጠ ምላሽ አልተካተተም፡፡

ለሩስያና ቡልጋርያ ግንኙነት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የበኩሏን እንድትወጣ ተጠየቀ፡፡

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በስንሻው ወንድሙ

ሩስያ ከቡልጋርያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች በኦርቶዶክስ እምነት አባቶች በኩል ለማጠንከር የሀገሪቱ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በቡልጋርያ ለሁለት ቀናት ጉብኝት ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡

 

እንደ ዘጋርድያን ጋዜጣ ዘገባ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ክሪል ከቡልጋርያው አቻቸው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማክሲም ጋር ተገናኘተው ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ያላቸውን መልካም ግንኙነት በማጠንከር በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በድልድይነት በሚያገለግሉበት ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ፓትርያርክ ክሪል የቡልጋርያ ሁለተኛ ታላቅ ከተማ ፕሎቭዲቭ ሲደርሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን የተቀበሏቸው ሲሆን ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሮዜን ፕሌቭንሊቭና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦይብ በሪስቭን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ፓትርያርኩ በከተማዋ ቅድስት ማርያም ካቴድራል ባደረጉት ንግግር «ከቡልጋርያ ቤተ ክርስቲያን መልእክተኞች ጋር ተገናኝተናል፡፡ ቀደም ሲል የኛ መልእክተኞችን ቡልጋርያ ለመላክ ችለናል፡፡ በዚህ የጠበቀ ኦርቶዶክሳዊ ወንድማማችነት በመፍጠር ችግሮችን ለማስወገድ ጥረት ላይ ነን» ሲሉ ፓትርያርክ ክሪል መናገራቸው ተጠቁሟል፡፡

 

በጉብኝታቸውም በደቡብ ቡልጋርያ የሚገኘውንና እ.ኤ.አ ከ1877-1878 በሩስያ ቱርክ ጦርነት እንዲሁም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለሀገራቸው የተሰውትን ሩስያውያን መካነ መቃብርን ጎብኝተዋል፡፡ ፓትርያርክ ክሪል በቡልጋርያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ጉብኝታቸውን አስመልክቶና የሀገሪቱ ግንኙነት በሚጠናከርበት ላይ የሁለቱ ሃይማኖት አባቶች ሊያደርጉቸው የሚገቡ መሠረታዊ ነጥቦችን መጥቀሳቸውን ዘገባው ማስፈሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሀገሪቱ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የምታደርገውን እንቅስቃሴ መሠረት በማድረግ የሩስያ ኦርቶዶክስ በዓለም መድረክ ሊኖራት የሚገባውን ሥፍራ ለማጠንከርና የእምነቱ ተከታዮችን ለማጽናት ትልቅ እንቅስቃሴ ታደርጋለች፡፡ ቀደም ሲል ከሩስያው ፕሬዝዳንት ዴሞትሪ ሜድቬዴቭ ጋር በመሆን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የሩስያ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ በመጎብኘት ቅርሳቸውን በሚጠብቁበት ላይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

20 021

የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት ምሥረታ በመከበር ላይ ነው

ግንቦት 2/2004 ዓ.ም.

በ እንዳለ ደምስስ

20 021የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደትና የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት ምሥረታ እሑድ ሚያዚያ 28 ቀን 2004 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በድምቀት ተከበረ፡፡ “ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት አብረን እንሥራ በሚል መሪ ቃል በማኅበረ ቅዱሳን ህዝብ ግንኙነት ክፍል የተዘጋጀው መርሐ ግብር በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በጸሎት ተጀምሮ በዝማሬ በስብከተ ወንጌል አገልግሎትና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ምክር ተካሒዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የምዕራብ ትግራይ ሴቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የአዲስ አበባና የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሔኖክ የምዕራብ ወለጋ ጊምቢና አሶሳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡብ ትግራይ ማይጨው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተገኝተዋል፡፡

 

በዕለቱ የተጉኙት ሊቃነ ጳጳሳት ማኅበረ ቅዱሳን አስመልክቶ እንዲህ በማለት ገልጸው ነበር፡፡ “የፈተና ጊዜ ነው ፈተናውን የምናልፈው በእግዚአብሔር ረድኤት ነው እግዚአብሔርን በመከተል ነው፡፡ ሌላ ኀይል የለንም፡፡…. እናንተ እግዚአብሔርን መከተል መርጣችኋልና መጨረሻችሁን እግዚመብሔር ያሳመርላችሁ፡፡ በርቱ፡፡” ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፡፡/

 

“የዚህ ታላቅ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ሥርዓታዊ፣ መንፈሳዊና ሰዋዊ ማኅበር አካላት ሁሉ ሥራ እየሠራችሁ ነው እዚህ የደረሳችሁት ምርት እያመረታችሁ ያላችሁባቸው ዓመታት ምርታችሁንም እያያችሁና እየተጠቀማችሁበት የምትገኙበት ዕለት ነውና እንኳን አደረሳችሁ” /ብፁዕ አቡነ ሉቃስ/

 

ይህ ማኅበር 20 ዓመታት ሲጓዝ እግዚአብሔር ስለረዳው እግዚአብሔር ከማኅበሩ ጋር ስለሆነ እንደ ኤማሁስ መንገደኞች እግዚአብሔር ስለመራው ነው ዛሬ 20ኛውን ዓመት ለማክበር የበቃው በርቱ፡፡ /ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ/

 

20 037ብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ ሊሞቱ ሲሉ ካስተማሯቸው ተማሪዎቻቸው /ማኅበረ ቅዱሳንን ከመሠረቱት/ መካከል ሁለቱን፣ አንዱን በቀኝ አንዱን በግራ አቅፈው፣ ጸሎት አድርገው የሁለቱን ራስ አጋጭተው በመያዝ” በሉ ልጆቼ መቃብሬ ላይ እናንተ ናችሁ የምታለቅሱት እኔ ለኩሼዋለሁ እናንተ አንድዱት አሏቸው ለአትክልተ ጎርጎርዮስ፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ምንጭና ግንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆንም የማኅበረ ቅዱሳን ግንድ ደግሞ አቡነ ጎርጎርዮስ ናቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚገባውን ምግብ እያበላና እያጠጣ እዚህ ያደረሰው ማኅበር ነው፡፡” /ብፁዕ አቡነ ኤልያስ/

 

የማኅበሩ ሰብሳቢ  ሊቀትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዮም እንደገለጹት ከ1980 ዓ.ም. ጀምሮ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ20 022 ካልዕ በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ተተኪ ሰባኪያንን ለማፍራት ባደረጉት ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ ከግቢ ጉባኤያት 12 ተማሪዎችን በማሠልጠን ጀመረ፡፡ ዛሬ ይህ ጥረት አድጎ በጅማ፣ በአዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በባሕርዳርና በማይጨው ሥልጠናው ተጠናክሮ በመቀጠል በሺዎች የሚቆጠሩ መምህራንን ማፍራት ተችሏል፡፡ ብለዋል፡፡ አያይዘውም በመላው ዓለም በአገር ውስጥና በውጪ  የማኅበረ ቅዱሳንን እንቅስቃሴ ሲገልጹ ማኅበረ ቅዱሳን 44 ማዕከላት፣ 333 ወረዳ ማዕከላት 181 ግንኙነት ጣቢያዎች 325 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያትን በማስተባበርና በመምራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ከምዕመናን ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክቶ ለተጠየቁ ጥየቄዎች የማኅበሩ ዋና ጸሓፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ ከመምህር ቀሲስ እሸቱ ታደሰ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲሆን  የማኅበሩ መዝሙር ክፍል አባላት የአቡነ ጎርጎርዮስ የትምህርት ማዕከል ሕፃናት ተማሪዎች፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬ በየተራ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ኤልያስ ቡራኬ የመርሐ ግብሩ ፍፃሜ ሆኗል፡፡

የእመቤታችን በዓለ ልደት ተከበረ፡፡

ግንቦት 2/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኖአምላክ

በየዓመቱ ግንቦት አንድ ቀን በልዩ መንፈሳዊ ድምቀት የሚከበረው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል ትናንት በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ተከብሮ ዋለ፡፡

 

በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማዕከል አስተባባሪነት በማኅበሩ ሕንፃ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አዳራሽ በተከናወነው የእመቤታችን የልደት በዓል መርሐ ግብር ከስድስት መቶ በላይ የሚሆኑ የማኅበሩ አባላትና ሌሎች ተጋባዥ ምእመናንም ተገኝተዋል፡፡ የእመቤታችንን በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀውን መልእክት የአዲስ አበባ ማዕከል ሰብሳቢ ዲ/ን አንዱ ዓለም ኀይሉ አቅርበዋል፡፡

“የእመቤታችንን በዓል መንፈሳዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በማክበር ከእመቤታችን በረከተ ረድኤትን ለማግኘት፣ ለመማማር ለመመካከርና አገልግሎታችንም የተቃና እንዲሆን በጸሎት ለማሳሰብ እንዲረዳን ጭምር ነው፡- በዓለ ልደታን እንዲህ ባለ መልኩ ያከበርነው” ሲሉ የገለጹት የአዲስ አበባ ማዕከል ጸሓፊ አቶ ካሳሁን ኀይሌ ናቸው፡፡

 

በጸሎተ ኪዳንና በመዝሙረ ዳዊት በተከፈተው ጉባኤ ላይ ትምህርት፣ የግንቦት ልደታን እንዴት እናክብር? በሚል ምክርና ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከአገልግሎት ባልተለዩ  አባላት አማካኝነት የሕይወት ተሞክሮ የቀረበ ሲሆን በዓሉን ምክንያት በማድረግ በእመቤታችን ስም የተዘከረ ጸበል ጸዲቅ ቀርቧል፡፡

 

የማኅበረ ቅዱሳንን ሃያኛ ዓመት ምሥረታና የእመቤታችንን በዓል በጋራ እያከበርን በምንገኝበት በዚህ ወቅት ለአባላት የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድር ነው? የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ካሳሁን፡- የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮና መንፈሳዊ ይዘቱን የጠበቀ የበዓል አከባበር እሴታችንን በመጠበቅ ወደፊትም ማዕከሉ ተመሳሳይ መርሐ ግብራትን እንደሚያዘጋጅ ገልጸው፥ ምእመናንም በያሉበት ይህንኑ በጎ ትውፊት እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡