የእግር ጉዞው መርሐ ግብር ተራዘመ

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ  የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት ምስረታን ምክንት በማድረግ ለሚያዚያ 27 ቀን 2004 ዓ.ም ተዘጋጅቶ የነበረው የእግር ጉዞ መርሐ ግብር ወደ ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም. ተራዘመ፡፡ የመርሐ ግበሩ አስተባባሪ ሰብሳቢ ዲ/ን ዋሲሁን በላይ ቀኑ የተቀየረበትን ምክንያት እንደገለጹት የእግር ጉዞው በታቀደለት ጊዜ ለማካሔድ ከፍተኛ ጥረቶች መደረጋቸውን፤ በርካታ ቲኬቶችና ካናቴራዎችን ማሰራጨታቸውን፤ ነገር ግን ከምእመናን በተደጋጋሚ በቀረቡ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች አንደኛ ከሰሙነ ሕማማት ጀምሮ በትንሳኤ በአል ምክንያት ምእመናን የተለያዩ ወጪዎችን ማውጣታቸውንና በጉዞው ላይ ለመሳተፍ ትኬቱን መግዛት ያለመቻላቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከትንሳኤ በአል በኋላ የቀኑ ማጠር፤ እንዲሁም በበአለ ሃምሳ ምክንያት የተለያ የማኅበራዊ ሕይወት ተሳትፎ ጎልቶ የሚታበት ወቅት በመሆኑ ቀኑ እንዲቀየርላቸው ከፍተኛ ግፊት በማድረጋቸው  ጥያቄያቸውን ተቀብለን የእግር ጉዞው መርሐ ግብር ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም. እንዲሆን ተወስኗል ብለዋል፡፡ ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም የተመረጠበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ ምእመናን ከትንሣኤ በአል ጋር ተያይዞ ከማኅበራዊ ሕይወት ፋታ ያገኙበታል ተብሎ መታሰቡና ቅድስት ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው በዓላት አንዱ የጰራቅሊጦስ ዕለት በመሆኑ ቀኑን በአንድነት ሆነን እግዚአብሔርን እያመሰገንን እንድንውል በማሰብ ነው ብለዋል፡፡

ለምእመናን ባስተላለፉት መልእክት ዋናው የጉዞው ዓላማ የማኅበራችን 20ኛ ዓመት ምሥረታ ነው፡፡ በ20 ዓመታት ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻውን ያደረገው ምንም ነገር የለም፡፡ ከቅዱስ ፓትርርኩ ጀምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያዩ አካላትና ጽ/ቤቶች፤ ከሠራተኛ ጉባኤያት፤ ከሰ/ት/ቤቶች፤ በተለይም ከምእመናን ጋር በኅብረት ሰርተናል፡፡ አብረን ከተጓዝናቸው እሰካሁንም ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በምክራቸው፤ በጸሎታቸው፤ በእውቀታቸው፤ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው እያገለገሉ ካሉ አካላትና ምእመናን ጋር በኅብረት እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ቀን ነው፡፡ ቀጣይ ጊዜያችን ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ጠንክረን አብረን ተያይዘን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ከእኛ የምትፈልገውን አገልግሎት የምንፈጽምበት እንዲሆን ቃል የምንገባበት ዕለት ስለሆነ ምእመናን የተዘጋጀውን ቲኬት በመግዛት በእግር ጉዞው እንዲሳተፉና የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

በእግር ጉዞው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የመምሪያ ሓላፊዎች፤ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፤ ሰበካ ጉባኤያት፤ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ምእመናን ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ መንፈሳዊና ምእመናንን ሊያስተምሩ የሚችሉ መርሐ ግብሮች ተዘጋጅተዋል፡፡

 

ጉዞው የሚደረገው፤ ወደ መንበረ ክብር ደብረ ታቦር ቅዱስ ሚካኤልና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ነው፡፡ የጉዞው መነሻ ቦታዎች፤ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፤ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል /አምስት ኪሎ/ እና ሰሜን ማዘጋጃ ቶታል ናቸው፡፡

 

የጉዞው መነሻ ስዓት፤ ከጠዋቱ 1፡00 ስዓት ሲሆን ከምእመናን የሚጠበቁ ጉዳዮች በተመለከተ ለመንፈሳዊ ቦታዎች የሚመች አለባበስ መልበስ ይጠበቅባቸዋል፡፡