ለሩስያና ቡልጋርያ ግንኙነት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የበኩሏን እንድትወጣ ተጠየቀ፡፡

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በስንሻው ወንድሙ

ሩስያ ከቡልጋርያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች በኦርቶዶክስ እምነት አባቶች በኩል ለማጠንከር የሀገሪቱ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በቡልጋርያ ለሁለት ቀናት ጉብኝት ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡

 

እንደ ዘጋርድያን ጋዜጣ ዘገባ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ክሪል ከቡልጋርያው አቻቸው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማክሲም ጋር ተገናኘተው ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ያላቸውን መልካም ግንኙነት በማጠንከር በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በድልድይነት በሚያገለግሉበት ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ፓትርያርክ ክሪል የቡልጋርያ ሁለተኛ ታላቅ ከተማ ፕሎቭዲቭ ሲደርሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን የተቀበሏቸው ሲሆን ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሮዜን ፕሌቭንሊቭና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦይብ በሪስቭን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ፓትርያርኩ በከተማዋ ቅድስት ማርያም ካቴድራል ባደረጉት ንግግር «ከቡልጋርያ ቤተ ክርስቲያን መልእክተኞች ጋር ተገናኝተናል፡፡ ቀደም ሲል የኛ መልእክተኞችን ቡልጋርያ ለመላክ ችለናል፡፡ በዚህ የጠበቀ ኦርቶዶክሳዊ ወንድማማችነት በመፍጠር ችግሮችን ለማስወገድ ጥረት ላይ ነን» ሲሉ ፓትርያርክ ክሪል መናገራቸው ተጠቁሟል፡፡

 

በጉብኝታቸውም በደቡብ ቡልጋርያ የሚገኘውንና እ.ኤ.አ ከ1877-1878 በሩስያ ቱርክ ጦርነት እንዲሁም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለሀገራቸው የተሰውትን ሩስያውያን መካነ መቃብርን ጎብኝተዋል፡፡ ፓትርያርክ ክሪል በቡልጋርያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ጉብኝታቸውን አስመልክቶና የሀገሪቱ ግንኙነት በሚጠናከርበት ላይ የሁለቱ ሃይማኖት አባቶች ሊያደርጉቸው የሚገቡ መሠረታዊ ነጥቦችን መጥቀሳቸውን ዘገባው ማስፈሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሀገሪቱ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የምታደርገውን እንቅስቃሴ መሠረት በማድረግ የሩስያ ኦርቶዶክስ በዓለም መድረክ ሊኖራት የሚገባውን ሥፍራ ለማጠንከርና የእምነቱ ተከታዮችን ለማጽናት ትልቅ እንቅስቃሴ ታደርጋለች፡፡ ቀደም ሲል ከሩስያው ፕሬዝዳንት ዴሞትሪ ሜድቬዴቭ ጋር በመሆን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የሩስያ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ በመጎብኘት ቅርሳቸውን በሚጠብቁበት ላይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡