DSC02522

ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል ስለምትገኝበት ሁኔታ ዐውደ ጥናት ተካሄደ

ግንቦት 7/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

DSC02522የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል የምትገኝበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ቅዳሜ ግንቦት 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ተካሔደ፡፡ አውደ ጥናቱ በማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል አስተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን በዋና ክፍሉ ስር ከሚገኙት ዴስኮች መካከል የኦሮምኛ ትርጉም ዴስክ አማካይነት ቀርቧል፡፡

የኦሮምኛ ትርጉም ዴስክ በመደበኛና በኢመደበኛ አባላት የተጠናከረ ክፍል እንደመሆኑ በኦሮሚያ ክልል ቤተ ክርስቲያናችን ምን ላይ እንደምትገኝ የሚያሳይ ጥናት ይዞ እንዲቀርብ በተሰጠው ሓላፊነት መሠረት ጥናቱን ይዞ መቅረቡን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ሓላፊ ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ገልጸዋል፡፡ የጥናቱ ዋነኛ ዓላማን አስመልክተው ቤተ ክርስቲያናችን በኦሮሚያ ክልል ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ መዳሰስ፤ ችግሮቹን ለመፍታት ምን መደረግ እንደሚገባና ምዕመናን በአንዳንድ እምነቶች እንዳይወሰዱ በመረጃ የተደገፈ ምላሾችን መስጠት የሚያስችል ጥናት እንደሆነ ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኦሮምኛ ትርጉም ዴስክ ሓላፊ የሆኑት ቀሲስ ምስጋናው አገሳ እንደገለጹት ዴስኩ የትርጉም ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ፣ በተለይም ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞችና እኅቶችን በማሰባሰብ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከአማርኛ ወደ ኦሮምኛ በመተርጎም ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ በዚህ ዓመትም 5 መፃሕፍትን ተርጉመው ለምእመናን ለማድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝና ይህ ጥናት በእነዚሁ አባላት አማካይነት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጥናት አቅራቢዎቹ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ዋና ዋና የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ያሏቸውን የሚያሳይ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን ክልሉ ሰፊ እንደመሆኑ ችግሮቹም ስፋት ያላቸው ስለሆነ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው ያሏቸውንም በሁለት በመክፈል ውስጣዊ ችግሮችና ውጫዊ ችግሮች በማለት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ ምዕመናን ከኦሮምኛ ቋንቋ በቀር መስማትና መናገር ባለመቻላቸው በቋንቋቸው የሚገባውን አገልግሎት መስጠትና ማግኘት ያለመቻሉ፤ ንስሐ ለመግባት በአስተርጓሚ እስከማከናወን መድረሱ፣ በቋንቋው የተዘጋጁ የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትና የቋንቋው ተናጋሪ አገልጋይ ያለመኖር፣ የምዕመናን ባህልና አኗኗር ማዕከል ያደረገ ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት ያለመቻሉ፤ በተለያዩ እምነቶችና ባዕድ አምልኮዎች መጠመዱ…. የመሳሰሉት እንደሆኑ በጥናት አቅራቢዎቹ ተዳስሰዋል፡፡

DSC02521ከተለያዩ ዋና ዋና ክፍሎች የተገኙት የማኅበሩ አባላት በጥናቱ ላይ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን እንዲሁም የመፍትሔ ዐሳቦችን አቅርበዋል፡፡ ከጥናቱ አቅራቢዎችም ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም መፍትሔዎቹን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም  መካከል በክልሉ ምዕመናን በቋንቋቸው የሚገለገሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በተወላጆቹ /በቋንቋው ተናጋሪ አገልጋዮች/ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል፣ በኦሮምኛ ቋንቋ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማዘጋጀትና ማሰራጨት፣ አገልጋዮችን ለማፍራት ማሠልጠኛ ተቋም  መክፈት፣ በግቢ ጉባኤያት ለሚገኙ ተማሪዎች የአብነት ትምህርት መስጠት፣ ተጨባጭ ጥናቶችን በተጠናከረ ሁኔታ ማካሔድ…… የመሳሰሉትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የተገለጹት ችግሮችና ከአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች የቀረቡ ጥያቄዎችና የመፍትሔ ዐሳቦችን በማጠናከር ከማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አስፈጻሚ ጋር ተነጋግሮና አጽድቆ በአፋጣኝ ወደ ትግበራ እንደሚሸጋገር ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ የገለጹ ሲሆን ጥናት አቅራቢዎቹንና የየክፍሉ ተወካዩችን በአውደ ጥናቱ በመገኘታቸው አመስግነዋል፡፡