Semera_Kidus_Yohanes_Church.jpg

በአፋር ሰመራ ከተማ የመጥምቁ ዮሐንስ ገዳም ቅዳሴ ቤት ተከበረ

ሎጊያ ወረዳ ማዕከል
    Semera_Kidus_Yohanes_Church.jpg
 
 
 
 
 
 
 
በሰመራ ከተማ የተሰራዉ የቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን

በአፋር ሀገረ ስብከት ሰመራ ከተማ በሀገረ ስብከቱና በአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ጥረት የተሠራው የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ገዳም መቃኞ ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ግንባታው የተጀመረው ይኸው መቃኞ ቤተ ክርስቲያን፤ ቤተልሔም፣ የግብር ቤት፣ የዕቃ ቤት እና የውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳ እንዲሁም የካህናት ማረፊያ ቤቶችም ጭምር እንደተሠሩለት ታውቋል፡፡

ጥር 30 ቀን 2002 ዓ.ም በርካታ የአካባቢው ምእመናን፤ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች፣ ካህናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር ከቀረበው መግለጫ ለመረዳት እንደተቻለው፤ 2001 ዓ.ም በሰመራ ከተማ የተቋቋመው ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ሲቀበል የክርስቲያኖች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ይሁንና በከተማው በወቅቱ ምንም ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ ማስቀደስ፣ ቃለ እግዚአብሔርን መስማት እንዲሁም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶችን ማግኘት አልተቻለም ነበር፡፡

በዕለቱ ቡራኬ የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮናስ እንደገለጹት፤ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የአምልኮ ቦታ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው በአፋር ክልላዊ መንግሥት መልካም ፈቃድ 29 ሺሕ 830 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቦታው የመንበረ ጵጵስና፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሥሪያን ያካተተ ማስተር ፕላን /የይዞታ ማረጋገጫ/ የተሠራለት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

«ይህ ቦታ በረሃማ ስለሆነ፤ በበረሃ የገደመው ዘ ንብረቱ ገዳም በተባለለት በቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ስም፤ ቅሩበ ሳሌም ዮሐንስ መጥምቅ ገዳም ተብሎ እንዲጠራ ይሁን» ያሉት ብፁዕነታቸው፤ ቅሩበ ሳሌም የሚለው ሥያሜ ዮሐንስ መጥምቅ የንስሐ ጥምቀት ያጠምቅበት የነበረው አካባቢ እንዲታወስ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የገዳሙ ሕንፃ ቤተክርስቲያን /መቃኞ/ መሠራት እጅግ ያስደሰታቸው መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው ለሥራው የተባበሩትን ሁሉ በማመስገን ምእመናኑን እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡

ከሁለት ዓመት  በኋላ  ዋናውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ዕቅድ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

በሰመራ ከተማ ምንም ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች የእምነት ሥርዓታቸውን ማከናወን ይቸገሩ እንደ ነበር የጠቀሰው የግቢ ጉባኤው ሰብሳቢ ዲ/ን ደጀን፤ ያም ሆኖ ተማሪው ከዩኒቨርስቲው መደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን መንፈሳዊ ትምህርት የመቀበል ፍላጎቱ ከፍተኛ ስለነበረ ግቢ ጉባኤ ተቋቁሞ ትምህርቱ ይሰጥ እንደነበር አስረድቷል፡፡

«ቦታው ምድረ በዳ ከመሆኑ አንፃር በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው እጅ ተሠራ ለማለት አያስደፍርም» ያለው ሥራውን በሓላፊነት ሲከታተል የነበረው ዲ/ን ናሁሠናይ ደስታ በበኩሉ፤ «የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ከጀምሩ አንሥቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፍ ያደረጉ የሰመራ ዩኒቨርስቲ መምህራንና ሠራተኞች፣ የዱብቲ ውኃ ሥራዎች ድርጅት ሠራተኞች፣ የእመቤታችን ጽዋ ማኅበር፣ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችና የአካባቢው ምእመናን ምስጋና ይገባቸዋል» ብሏል፡፡

በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮናስ ከተለያዩ ምእመናን ያገኙዋቸውን ንዋያተ ቅድሳት ለቤተ ክርስቲያኑ መገልገያ ማስረከባቸውንም ከማኅበረ ቅዱሳን የሎግያ ወረዳ ማእከል የተላከልን ዘገባ ያስረዳል፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቶቹ የልምድ ልውውጥ አደረጉ

በይብረሁ ይጥና

ከሲዳማ ሀገረ ስብከት ሀዋሳ ከተማና አካባቢዋ የተውጣጡ የስድስት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮች በአዲስ አበባ የአምስት ሰንበት ትምህርት ቤቶችን እንቅስቃሴ በመጎብኘት የልምድ ልውውጥ አደረጉ፡፡

ሃያ ዘጠኝ አባላትን ያቀፈው የልኡካን ቡድን፤ በሰንበት ትምህርት ቤቶች መዋቅር አደረጃጀትና አሠራር፣ መዝሙራት፣ የአባላት ክትትልና አያያዝ፣ ሥነ ምግባርና የልማት ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግም የጋራ ግንዛቤ አግኝቷል፡፡

የልኡካን ቡድኑ አስተባባሪና የሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰንበት ትምህርት ቤት አባል ወጣት ብስራት ጌታቸው ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ እንዳስታወቀው፤ «ከየካቲት 19 እስከ 21 ቀን 2002 ዓ.ም ድረስ ከመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት፣ መናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል፣ ጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን እና ከልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተክለ ሳዊሮስ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር የልምድ ልውውጥና ውይይት በማድረግ ሰፊ ትምህርት ቀስመናል፡፡» ብሏል፡፡ እንዲሁም፤ «በተለይ የቤተክርስቲያንን ሥርዓት ለማስጠበቅና የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ሰንበት ትምህርት ቤቶች በኅብረት ሆነው መሥራት ጠቃሚ መሆኑን ተረድተናል» በማለት አመልክቷል፡፡

ከአባላቱ መካከል የሀዋሳ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ዋና ጸሐፊ ወጣት ሥላስ አዲስ በሰጠችው አስተያየት፤ «ለሦስት ቀናት ባደረግነው ውይይት ጠቃሚና መሠረታዊ የሆነ ነገር አግኝተናል፡፡ ካገኘነውም ተሞክሮ ከተኛንበት እንድንነቃና ሥራዎቻችንን እንደገና እንድንፈትሽ አድርጎናል» ስትል ተናግራለች፡፡

ሌላው በሀዋሳ ደብረ ሰላም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ምክትል ሰብሳቢ ወጣት ይድነቃቸው ጥላሁንም፤ «በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙ የአሠራር ልዩነትና ክፍተቶች መኖራቸውን ተረድቻለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር እኛ ብዙ መሥራት እንዳለብን ተገንዝቤያለሁ፡፡ በይበልጥ መዝሙራትን በሚመለከት ችግሮች ስላሉ ከጉብኝታትን ባገኘነው ትምህርት ካለፈው በተሻለ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተን እንድንሠራ ያደርገናል፡፡ በጠቅላይ ቤተክህነትም አንድ ወጥ በሆነ አሠራር አፈጻጸሙን ለመከታተል ጥረት ቢደረግ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን ለመቆጣጠር ይመቻል፡፡» ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በአዲስ አበባ የመንበረ መንግሥት ግቢ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት አባል ደነቀ ማሞ በበኩሉ ውይይቱን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት፤ «ከሀዋሳ ከመጡ ስድስት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር የልምድ ልውውጥ መደረጉ በሰንበት ትምህርት ቤቶች መካከል የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ያስችላል፡፡ ስለሆነም ሌሎች ሰንበት ትምህርት ቤቶችም ይህን አርአያ ቢከተሉ ጠቀሜታው የጎላ ነው» ሲል ተናግሯል፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቶች በአንድነት ሆነው መወያየታቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና ትውፊት ለመጠበቅ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታመናል፡፡

የሐይቅ ቅዱስ ዮሐንስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ እንዲጠናቀቅ የድጋፍ ጥሪ ቀረበ

በደረጀ ትዕዛዙ

በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሐይቅ ከተማ የሚገኘው የደብረ ናግራን ቅዱስ ዮሐንስ ፍቅረ እግዚእ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታን ለማስፈጸም የምእመናን ድጋፍ ተጠየቀ፡፡

በ1879 ዓ.ም እንደተሠራ የሚነገርለት ይኸው ቤተ ክርስቲያን ለበርካታ ዘመናት እድሳት ባለማግኘቱ አዲስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ፈቃድ ከሰባት ዓመት በፊት ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ኮሚቴው ምእመናንን በማስተባበር፣ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን በመጠቀምና ጉባኤያትን በማዘጋጀት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በማሠራት የተሻለ ደረጃ ላይ እንዳደረሰው የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አባ ወልደ ትንሣኤ አሳምነው ተናግረዋል፡፡

የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ገንዘብ ያዥ አቶ ካሳሁን መብራቱ በበኩላቸው፤ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማነፅ ምእመናን ያደረጉት ትብብር የሚያበረታታ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የግንባታ ዕቃ መወደድ የተነሣ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ግንባታ ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡

ስለዚህ የቆርቆሮ፣ የበርና የመስኮት የመሳሰሉት ቀሪ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ቤተ ክርስቲያኑ  ለምእመናን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ድጋፍ መጠየቅ አስፈልጓል ያሉት አቶ ካሳሁን፤ ለዚህም ምእመናን የተቻላቸው ትብብር እንዲያደርጉ ተማጽነዋል፡፡

ዐቢይ ጾም፤ ወደ ትንሣኤ የሚደረግ ጉዞ

ዲ/ን ዘላለም ቻላቸው

አንድ ሰው ለጉዞ ሲነሣ ወዴት እንደሚሄድ ማወቅ አለበት፡፡ በዐቢይ ጾምም እንዲሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ዐቢይ ጾም መንፈሳዊ ጉዞ ነው፤ መድረሻውም ትንሣኤ ነው፡፡ ለእውነተኛው መገለጥ ለፋሲካ መሟላት የሚደረግ ዝግጅት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም አስፈላጊ የሆነና ስለ ክርስትና እምነታችንና ሕይወታችን በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር ስለሚገልጥልን ይህን በዐቢይ ጾም እና በትንሣኤ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመረዳት በመሞከር መጀመር አለብን፡፡

የትንሣኤ በዓል ከበዓላት አንዱ ከመሆን እና የአንድ ያለፈ ክስተት መታሰቢያ ከመሆን በላይ ሊታሰብ ያስፈልገዋል፡፡ አንድ ጊዜም ብቻ እንኳን ቢሆን የትንሣኤን በዓል በሚገባው መልኩ አክብሮ በዚያም ከቀን ይልቅ በሚያበራው ሌሊት የተሳተፈና ያንን ልዩ ደስታ የቀመሰ ማንም ሰው ያውቀዋል፡፡ ያ ደስታ ግን ስለ ምንድን ነው? በትንሣኤ በዓል ዕለት እንደምናደርገው «ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሀጺባ በደመ ክርስቶስ»፤ «ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ»፣ «ዛሬ ሁሉም ነገር፣ ሰማይም፣ ምድርም፣ ከምድር በታች ያሉ ነገሮችም በብርሃን ተሞሉ» እያልን መዘመር የምንችለው ለምንድነው? «የሞት መሞት፤ የሲኦል መበዝበዝ፣ የአዲስና የዘለዓለማዊ ሕይወት መጀመሪያ…» እያልን ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?

ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልሱ ይህ ነው፡፡ ከሁለት ሺሕ ዓመታት በፊት ከመቃብር ወጥቶ ያበራው አዲስ ሕይወት በክርስቶስ ለምናምን ለሁላችንም ተሰጥቶናል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ «በሞቱም እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን፤ እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደተነሣ እኛም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን» /ሮሜ.6-4/ እንዳለው ይህ አዲስ ሕይወት እና ብርሃን ለእኛ የተሰጠን በጥምቀታችን ዕለት ነው፡፡

ስለዚህ የትንሣኤን በዓል ስናከብር፣ የክርስቶስን ትንሣኤ በእኛ ላይ እንደተደረገ እና አሁንም እንደሚደረግ አድርገን እናከብራለን፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዳችን የዚያን የአዲስ ሕይወት ስጦታ እና ያንን የምንቀበልበት እና በእርሱም የምንኖርበትን ኃይል ተቀብለናል፡፡ ይህ ስጦታ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር ሁሉ ስለ ሞትም ጭምር ያለንን አመለካከት የሚቀይር ነው፡፡ በደስታ «ሞት የለም» ብለን በእር ግጠኝነትም መናገር እንድንችል የሚያደርገን ነው፡፡

ኦ! ሞት ግን አሁንም አለ፤ በእርግጠኝነት አንጋፈጠዋለን፤ አንድ ቀንም መጥቶ ይወስደናል፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ በራሱ ሞት፣ የሞትን ባሕርይ /ምንነት/ እንደቀየረው ይህ ሙሉ እምነታችን ነው፤ ሞትን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት መሸጋገሪያ፣ ማለፊያ፣ ፋሲካ አድርጎታል፤ ከአሳዛኝ ነገሮች ሁሉ የበለጠ አሳዛኝ የነበረውን ሞት ወደ ፍጹም ድልነት ቀይሮታል፡፡ «ሞትን በሞቱ ደምስሶ» የትን ሣኤው ተካፋዮች አድርጎናል፡፡ ለዚህም ነው «ክርስቶስ ተነሥቷል፣ ሕይወትም ሆኗል፤ ማንም በመቃብር አይቀርም» የምንለው፡፡

ቁጥር በሌላቸው በቅዱሳኖቿ የተረጋገጠውና ግልጽ የተደረገው የቤተክርስቲያን እምነት ይህ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ እምነት በእኛ ውስጥ ሁልጊዜ አለመኖሩ [ይህንን ሁል ጊዜ አለማሰባችን]፤ እንዲሁም እንደ ስጦታ የተቀበልነውን አዲስ ሕይወት ሁልጊዜ መጣላችንና መካዳችን እንዲሁም ክርስቶስ ከሞት እንዳልተነሣ ሆነን የመኖራችን ነገር እና ያ ልዩ ክስተት ለእኛ ምንም ዓይነት ትርጉም የሌለው መሆኑ የዕለት ተዕለት ተሞክሮአችን አይደለምን?

ይህ ሁሉ የሆነው በድካማችን ምክንያት ነው፡፡ ማለትም ጌታ «አስቀድማችሁ መንግሥቱንና ጽድቁን ፈልጉ» ባለን ጊዜ በወሰነልን ደረጃ «በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር» መኖር ለእኛ የማይቻለን በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ በቀላሉ እንረሳዋለን፤ ምክንያቱም ሁልጊዜም በተለያዩ ሥራዎች የተጠመድን እና በዕለት ተዕለት ተግባሮቻችን የተዋጥን ነን፤ ስለ ምንረሳም እንወድቃለን፤ በጥምቀት የተቀበልነውን አዲስ ሕይወት እና ብርሃንም እንጥላለን፡፡

በዚህ በመርሳት፣ በመውደቅ እና ኃጢአት በመሥራት በኩልም ሕይወታችን በድጋሚ «አሮጌ» ይሆናል፤ ጥቅም /ረብ/ የሌለው፤ ጨለማ እና ትርጉም አልባ፤ ትርጉም የሌለው ጉዞ፤ ትርጉም ወደሌለው ፍጻሜ ይሆናል፡፡ሞትን እንኳን ሳይቀር ረስተነው ከቆየን በኋላ በድንገት «ደስታ በሞላበት ሕይወታችን» መሐል አስፈሪ፣ ሊያመልጡት የማይችሉት እና አስጨናቂ ሆኖ ወደ እኛ ይመጣል፡፡

በየጊዜው ኃጢአታችንን ልንናዘዝ እንችላለን፤ ነገር ግን ሕይወታችንን ከዚያ ክርስቶስ ለእኛ ከገለጠውና ከሰጠው ከአዲሱ ሕይወት ጋር ማዛመድና ሕይወታችንን በዚያ ላይ መመሥረት እናቆማለን፡፡ ትልቁና እውነተኛው ኃጢአት፣ የኃጢአቶች ሁሉ ኃጢአት፣ የስም ብቻ የሆነው ክርስትናችን በጣም አሳዛኝ ገጽታ ይህ ነው፡፡ የሕይወታችንን ትርጉም በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ አለመመሥረት፡፡

ይህንን ልብ ካልን፣ የትንሣኤ በዓል ምን እንደሆነና ዐቢይ ጾም ለምን ከእርሱ በፊት እንዲኖር እንዳስፈለገ እንረዳለን፡፡

በዐቢይ ጾም በቤተክርስቲያን የሚደረገው ሥርዓተ አምልኮ ዓላማም በቀላሉ የምንጥለውንና የምንወስደውን የዚያን የአዲስ ሕይወት ርእይ እና ጣዕም በውስጣችን እንድናድሰው ለመርዳት እና ተጸጽተን ወደ እርሱ እንድንመለስ ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም የማናውቀውን ነገር እንዴት ልንወድና ልንፈልግ እንችላለን? አይተነው እና አጣጥመነው የማናውቀውን ነገር እንዴት በሕይወታችን ካሉ ነገሮች ሁሉ በላይ ልናደርገው እንችላለን? በአጭሩ ስለ እርሱ ምንም አሳብ የሌለንን መንግሥት እንዴት ልንፈልግ እንችላለን? አንችልም፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያን በእነዚህ ሥርዓተ አምልኮዎች ይህን እንድናደርግ ትረዳናለች፡፡

በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ወዳለው ሕይወት መግቢያችን፤ ከዚያም ጋር ያለን ኅብረት መሠረት በቤተክርስቲያን ያለው አምልኮ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን «ጆሮ ያልሰማውን፣ ዓይንም ያላየውን በሰው ልብም ያልታሰበውን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እርሱን ለሚወዱት ያዘጋጀውን» ከዚያ ነገር ጥቂቱን ለእኛ የምትገልጥልን በአምልኮ ሕይወቷ አማካኝነት /through her liturgical life/ ነው፡፡ በዚያ በአምልኮ ሕይወት መሐል ላይ ደግሞ፣ እንደ ጠቅላላው የአምልኮ ሥርዓት ልብ እና ከፍታ፣ እንዲሁም ጨረሮቿ ሁሉም ቦታ እንደሚደርሰው ፀሐይ ሆኖ የትንሣኤ በዓል ይቆማል፡፡

የትንሣኤ በዓል በየዓመቱ ወደ ክርስቶስ መንግሥት ግርማ እና ውበት ለማሳየት የሚከፈት በር ነው፡፡ የሚጠብቀን ዘለዓለማዊ ደስታ ቅምሻ ነው፡፡ ምንም እንኳን በስውር ቢሆንም ፍጥረትን ሁሉ የሞላው፣ «ሞት የለም!» የሚለው የዚያ ድል ክብር መገለጫ ነው፡፡

አጠቃላይ የቤተክርስቲያን የአምልኮ ሕይወት ዓመታዊው የአምልኮ መርኀ ግብር / liturgical year/ የተደራጀው በትንሣኤ ዙሪያ ነው፤ ማለትም በዓመቱ በተከታታይ የሚመጡት ወቅቶች እና በዓላት ወደ ፋሲካ፣ ወደ ፍጻሜው የሚደረጉ ጉዞዎች ይሆናሉ፡፡ ፋሲካ ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን ጅማሬም ነው፤ «አሮጌ» የሆነው ነገር ሁሉ ፍጻሜ እና የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ፤ ከዚህ ዓለም በክርስቶስ ወደ ተገለጠው መንግሥት መሸጋገሪያ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የኃጢአት እና የማይረቡ ነገሮች መንገድ የሆነው «አሮጌው» ሕይወት ግን በቀላሉ የሚሸነፍ እና የሚቀየር አይደለም፡፡ የሰው ልጅ አሁን ባለበት ሁኔታ ሊፈጽመው የማይችለውን ነገር የወንጌል ሕግ ትጠብቅበታለች፡፡ ከአቅማችን እና ከምንችለው እጅግ በጣም በሚበልጥ ርእይ፣ ግብ እና የሕይወት መንገድ እንፈተናለን ምክንያቱም ሐዋርያት እንኳን ሳይቀሩ የጌታን ትምህርት ሲሰሙ ተስፋ በመቁረጥ «ይህ እንዴት ይቻላል?» ብለው ጠይቀውታል፡፡ በእርግጥም በየዕለቱ በሚያስፈልጉን ነገሮች በመጨነቅ፣ ቀላል ነገሮችን፣ ዋስትናን እና ደስታን በመፈለግ የተሞላን የማይረባ የሕይወት እሳቤ ትቶ «ሰማያዊ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ» የተባለለትንና ከፍጽምና በቀር ሌላ ምንም ግቡ ያልሆነውን የሕይወት እሳቤ መያዝ ቀላል አይደለም፡፡

ዓለም በመገናኛ ብዙኃኖቿ በሙሉ «ተደሰቱ፣ ቀለል አድርጋችሁ እዩት / take it easy/፣ ሰፊውን መንገድ ተከተሉ» ትለናለች፡፡ ክርስቶስ ደግሞ በወንጌል «ጠባቡን መንገድ ምረጡ፣ ተዋጉና መከራን ተቀበሉ፤ ይህ ወደ እውነተኛው ደስታ የሚያደርስ ብቸኛው መንገድ ነውና» ይለናል፡፡ ቤተክርስቲያን ካልረዳችን ካልደገፈችን እንዴት ያንን አስጨናቂ ምርጫ መምረጥ እንችላልን? እንዴትስ መጸጸት /ንስሐ መግባት/ እና በየዓመቱ በትንሣኤ በዓል ዕለት ወደሚሰጠው የከበረ ቃል ኪዳን መመለስ እንችላለን? የዐቢይ ጾም አስፈላጊነቱ እዚህ ላይ ነው ይህ በቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀልን ዕርዳታ፣ የትንሣኤ በዓልን የመብላት የመጠጣት እና የመዝናናት ፈቃድ የሚገኝበት ዕለት ነው ብለን ሳይሆን፣ በውስጣችን ያለው የአሮጌው መጨረሻ እና የእኛ ወደ አዲሱ መግቢያ አድርገን እንድንቀበለው የሚያስችለን የንስሐ ትምህርት ቤት ነው፡፡

በጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን የዐቢይ ጾም ዋና ዓላማ ንኡሰ ክርስቲያንን ማለትም አዳዲስ አማንያንን በዚያን ጊዜ በትንሣኤ ዕለት ለሚፈጸመው ጥምቀት ማዘጋጀት ነበር፡፡ ነገር ግን /ክርስትና ከተስፋፋና/ የሚጠመቁ ሰዎች ቁጥር ከቀነሰ በኋላም ግን ቢሆን የዐቢይ ጾም መሠረታዊ ትርጉም በዚያው ጸንቷል፡፡ ስለዚህም ትንሣኤ በየዓመቱ ወደ ጥምቀታችን መመለሻ ሲሆን ዐቢይ ጾም ደግሞ ለመመለስ መዘጋጃችን ነው፤ በክርስቶስ ወደሆነው አዲስ ሕይወት ለመተላለፍ የምናደርገው ትጋትና ጥረታችን ነው፡፡

ዐቢይ ጾም ጉዞ ነው፤ መንፈሳዊ ጉዞ ነው፡፡ ገና ስንጀምረው፣ በዐቢይ ጾም ብሩህ ሐዘን /bright sadness/ ውስጥ የመጀመሪያውን እርምጃ ስንራመድ ከር. . . ቀት ፍጻሜውን /መጨረሻውን/ እናያለን፡፡ ይህም የትንሣኤ በዓል ደስታ ነው፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ክብር መግባት ነው፡፡ የዐቢይ ጾምን ሐዘን ብሩህ የሚያደርገውና በወቅቱ የምናደርገውን ጥረት «መንፈሳዊ ምንጭ» የሚያደርገውም ይህ የትንሣኤ በዓል ቅምሻ የሆነው ብሩህ ርእይ ነው፡፡

ሌሊቱ ጨለማ እና ረጅም ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በመንገዱ ሁሉ ምስጢራዊ የሆነ ብሩህ ወገግታ በአድማሱ ላይ ያንፀባርቃል፡፡
«ሰውን ወዳጅ /መፍቀሬ ሰብእ/ ሆይ! አቤቱ ተስፋ ያደረግነውን ነገር አታስቀርብን» አሜን፡፡

ምንጭ፡- [The Lent, Father Alexander Schemaman, St. vladmir’s Seminary Press,].

የክርስትና መሠረተ እምነት በጸሎተ ሃይማኖት (አራተኛ መጽሐፍ)

በሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ
 
የሕይወት ብርሃን የሚያጠፋው ሞት የተባለው ጠላታችን በመጨረሻው ዘመን በእግዚአብሔር ኃይል አንዲጠፋና ሰውም የማይጠፋና ሰውም የማይጠፋውን የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኝ ፣ ተድላ ደስታ ያለበትን መንግሥተ ሰማያትንም እንደሚወርስ በቅዱሳት መጻሕፍት ተገልጿል ፤ በወንጌሉ የምሥራች ቃል ተረጋግጧል፡፡

የክርስትና መሠረተ እምነት በጸሎተ ሃይማኖት (ሦስተኛ መጽሐፍ)

በሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ
 
‹‹ ጌታ ማኅየዊ ›› የተባሉት ቃላት ለአምላክ ብቻ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ስለዚህም መንፈስ ቅዱስ ‹‹ ጌታ ማኅየዊ ›› መሆኑንና አምላክነቱንም በቅዱሳት መጻሕፍት ቃል በማረጋገጥ ፣ የመንፈስ ቅዱስ ተቃዋሚዎችን የረቱት የጥንቶቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በአንቀጸ ሃይማኖታቸው ደንግገውልናል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ከወልድ ጋር እኩል ስለሆነ ከእነርሱ ጋር ልንሰግድለትና ልናመሰግነው እነደሚገባን አስተምረውናል፡፡

የክርስትና መሠረተ እምነት በጸሎተ ሃይማኖት (ሁለተኛ መጽሐፍ)

በሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ
 
ሰው ባጠፋው ጥፋት ከደስታ ሕይወት ወጥቶ፣ ከክብሩ ተዋርዶና ወድቆ በችግርና በመከራ ኖሮ በመጨረሻ ሥጋው በመቃብር በስብሶ ሲቀር፣ ነፍሱ ደግሞ በሲዖል ስትሠቃይ በማየቱ ወልደ እግዚአብሔር ሰውን ከዚህ ክፉ ነገር ለማዳን ሰው ሆኖ ሕማምና ሞትን ተቀብሎ እንዳዳነው እናምናለን፡፡

የክርስትና መሠረተ እምነት በጸሎተ ሃይማኖት (አንደኛ መጽሐፍ)

በሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ
እግዚአብሔር አምላክ የሁሉም አባት ነው መባሉ እርሱ ለፍጥረታት ሁሉ ማለት ለዓለም ሁሉ ሠራኢና መጋቢ ፣ ለሕዝብና ለአሕዛብ ሁሉ መሪና ጠባቂ በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና በጻድቃንና በኃጢያተኞችም ላይ ዝናቡና ያዘንባልና››(ማቴ.5፣45)፡፡ እርሱ የሰማይ ወፎችን ይመጋባቸዋል ፤ የሜዳ አበቦችንና የሜዳውን ሣር ሁሉ በልዩ ልዩ ኅብረ ቀለም ያስጌጣቸዋል ፣ ያለብሳቸዋልም (ማቴ. 6፣26-30)፡፡

የትምህርተ ሃይማኖት መቅድም

በሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ
አሚንሰ መሰረት ይእቲ ወካልአኒሃ ሕንጻ ወንድቅ እሙንቱ- እምነት መሠረት ናት ፤ ሌሎቹ ግን ሕንጻና ግንብ ናቸው:: በማለት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሚያስገነዝበን እንደ ሕንጻና ግንብ ከሚቆጠሩት ከምግባርና ከትሩፋት ሁሉ በፊት የሃይማኖትን ቀዳሚነትና መሠረትነት ነው፡፡ መሠረት ሕንጻውን ሁሉ እንደሚሸከም እምነትም ምግባራትን ሁሉ ትይዛለች ፤ ሕንጻ ያለ መሠረት እንደማይቆም ምግባርም ያለ ሃይማኖት አይኖርም፡፡ ስለሆነም ከሁሉ በፊት የሃይማኖትን ትርጉም በማስቀደም ትምህርታችንን እንጀምራለን፡፡

ሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን

በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዓይ
 
ቤተ ክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ የጸጋው ግምጃ ቤት ስለሆነች መስቀል ላይ የተሰጠውን አምላካዊ ጸጋ በእምነት ለሚቀርቧት ሁሉ ታድላለች ፣ ትምህርቷን አምነው የተቀበሉ ሁሉ የዚህ ጸጋ ተካፋዮች ናቸው፡፡ ይህን ጸጋ ለምዕመናን የምታድልባቸውን መሳሪያዎች ምሥጢራት ትላቸዋለች፡፡