ሰሙነ ሕማማት

በመ/ር መንግሥተአብ አበጋዝ

በነቢዩ ኢሳይያስ «ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ፤ በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ፣ ሕመማችንንም ተሸከመ፣ እኛ ግን እንደተመታ፣ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሰፈ፣ እንደተቸገረም ቆጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ፣ ስለ በደላችንም ደቀቀ፣ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡» /ኢሳ. 53፣4-7/ ተብሎ የተነገረው ቃል ተፈጽሞ፣ ጌታችን ለድኅነተ ዓለም ሲል በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለው ጸዋትወ መከራ የሚዘከርበት ሳምንት ነው፡፡ ከሆሣዕና ማግስት እስከ ትንሣኤ ያለው የጾመ እግዚእነ መዝጊያ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡

በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው፣ ከሐሜት፣ ከነገርና ከኃጢአት ርቀው፤ የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ ሲያዜሙ፣ ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍ ሲያነቡ፣ ሲሰሙ፣ ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፡፡ ካህናትና ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፣ በሠለስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት /በዘጠኝ/ ሰዓት፣ በሰርክ /በዐሥራ አንድ/ ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፣ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፣ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራ ሥቃይን እና 5ሺ 5መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከር ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማት የጌታችንን ሕማማት ከማሰብ ጋር በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸውንም የምናስታውስበት ሳም ንት ነው፡፡ በዕለት በዕለት ከፍለን በየትኛው ቀን ምን ተደረገ እያልን እንጠይቅ?

ሰኞ፡-ጌታችን የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ በምትባል መንደር ያድራል በማግስቱም ከቢታንያ ሲወጣ ተራበ /ማር. 11፣11-14/ ቅጠል ያላትን በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፣ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ ዕለት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል፡፡

ትርጓሜ፤ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች፣ ሃይማኖትና ምግባር ናት፡፡ ከእስራኤል ፍቅርን፣ ሃይማኖትን፣ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፡፡ እስራኤልን ሕዝበ እግዚአብሔር መባልን እንጂ፣ ነቢይነት፣ ካህንነት፣ መሥዋዕት አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡ በመርገሙ ምክንያት ትንቢት ክህነት መሥዋዕት ከቤተ እስራኤል ጠፉ፡፡

በለስ ኦሪት ናት፡- ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና ፍሬ ባንቺ አይሁን አላት፤ ድኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡ በአዲስ ኪዳን የድኅነት ዘመንም ተተካች፡፡

በለስ ኃጢአት ናት፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሠሩት ደስ ደስ ያሰኛል ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፡፡ በለሷም ስትረገም ፈጥና መድረቋ፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡

ከዚህ ቀጥሎ ወደ ቤተ መቅደስ ሔደ፤ ቤተ መቅደስ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምሥያጥ /የንግድ ቤት/ ሆኖ ቢያገኘው፤ «ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች… እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት» ማቴ.21፣13 ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸዉ፣ ገርፎም አስወጣቸዉ፣ ይህም የሚያሳየዉ ማደሪያው ቤቱ የነበርን እኛ የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ አንጽሖተ ቤተ መቅደስ የተፈጸመበት ሰኞም ይባላል፡፡

 ማክሰኞ፡- ሰኞ ባደረገው አንጽሖተ ቤተመቅደስ ምክንያት፣ ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን፣ ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና፤ የጥያቄ ቀን ይባላል፡፡

ጥያቄውም ከምድራውያን ነገሥታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን፣ በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? የሚል ነበር፡፡ /ማቴ. 21፣23-27፣ ማር. 11፣7-35፣ ሉቃ. 21፣23-27፣ ማር. 11፣27-33፣ ሉቃ. 20፣1-8/፤ እርሱም ሲመልስ፤ «እኔም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፣ እናንተም ብትነግሩኝ በማን ሥልጣን እነዚህን እዳደርግ እነግራችኋለሁ፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረ፣ ከሰማይን? ወይስ ከሰዉ? በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ወይስ በሰው ፈቃድ?» አላቸው፡፡ እነርሱም ከሰማይ ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም ይለናል፤ ከሰው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል፣ እንደ መምህርነቱ ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን፤ ተባብለው ከወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም አላቸው» ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተዉት አልነበረም፣ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ እንጂ፡፡

በማቴ. 21፣28፣ ምዕ. 25፣46፣ ማር. 12፣2፣ ምዕ. 13፣37፣ ሉቃ. 20፣9፣ ምዕ. 21፣38 የሚገኙት ትምህርቶች ሁሉም የማክሰኞ ትምህርት ይባላሉ፡፡ በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ፣ የትምህርት ቀንም ይባላል፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር ሲጠይቅ  መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡

ረቡዕ፡- ምክረ አይሁድ ይባላል፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር ያጠናቀቁበት ቀን ነውና፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት ቀን የተቃረበ በመሆኑ፣ ብዙው ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ፣ ተአምራቱንም የሚያደንቁ ስለ ነበር ሁከት እንዳይፈጠር ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ፣ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ /ማቴ. 26፣1-14፣ ማር. 14፣1-2፣ ቁ 10፣11፣ ሉቃ. 22፣1-6/፤ የሐዲስ ኪዳን ካህናትና ምእመናን በዚሁ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ፣ ሐዋርያት ከጌታችን መያዝ በኋላ በኀዘን በፍርሐት እንደነበሩ እያሰቡ መጻሕፍትን በማንበብ በጾም፣ በጸሎ ትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ከአሥራ ሁለት ሰዓት በኋላ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡

የመልካም መዓዛ ቀንም ይባላል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ፣ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት፣ /ባለሽቱዋ ማርያም/፤ «ከእንግዲህ ወዲህ በኃጢአት ተበላሽቶ ይኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚህ መልካም ሽቱ የሚያጣፍጥ፣ ኃጢአትን ይቅር የሚል አምላክ መጣ» ስትል ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ፣ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ፣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የተሞላ ሽቱ ይዛ በመሔድ በጠጉሩ /በራሱ/ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው ነው፡፡ ረቡዕ የመዓዛ ቀን የተባለው፡፡

ረቡዕ የእንባ ቀንም ይባላል፡፡ ማርያም እንተ እፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ፣ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና፤ በጠጉሯም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሳዋለችና፡፡ /ማቴ. 26፣6-13፣ ማር. 14፣.9፣ ዮሐ. 12፣8/ ኃጢአትን በማሰብ ማልቀስና ራስን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብን ከምታስተምረን ማርያም እንተ እፍረት እንባን ለንስሐ ሕይወት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ሐሙስ፡- በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስያሜዎች ያሏቸው በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ዕለት ነው፡፡

ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ፣ መሆኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ተባለ፡፡ /ማቴ. 26፣36-46 ዮሐ. 17/፡፡

ሕፅበተ ሐሙስ ይባላል፡፡ ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳትና የደብር አስተዳዳሪዎች፤ «በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ እኛም የአንተን አርአያ አንዘነጋም የሌላውን እግር እናጥባለን፤» ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙትን ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

የምስጢር ቀን ይባላል፡፡ ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፡፡ ይኸውም «ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ» ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ «ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱም ጠጡ» በማለት፤ እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምስጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀመዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ሥያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡ ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ «ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱ ጠጡ» በማለቱ ይታወቃል /ሉቃ. 22፣20/ ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለሆነ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ተባለ፡፡

የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡፡ ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር «ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባርያ ጌታዉ የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ» በማለት /ዮሐ. 15፣15/፤ ከባርነት የወጣንበት ልጆች የተባል በትን ቀን የምናስብበት በመሆኑ ሊቃውንቱ የነጻነት ሐሙስ አሉት፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት  ሕይወቱን መምራት ይኖርባታል፡፡ ባሮች አልላችሁም ተብለናልና፡፡

የጸሎተ ሐሙስ ምስጢራት በብሉይ ኪዳን

ለፋሲካ ዝግጅት ተደርጎበታል፡፡ ዝግጅቱም በሦስቱ ወንጌላት ላይ ተመዝግቧል /ማቴ. 26.7-13/፡፡ ፋሲካ ማለት ማለፍ ማለት ነው፡፡ ይኸውም እስራኤላውያን በግብፅ ምድር ሳሉ መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን በበሩ ወይም በመቃኑ እንዲቀባ ለሙሴ ነገረው፡፡ ሙሴም ለሕዝቡ ነገረ፣ ሁሉም እንደታዘዙት ፈጸሙ፡፡ መቅሰፍት ከእግዚአብሔር ታዞ መልአኩ የደም ምልክት የሌለበትን የግብፃውያንን ቤት በሞተ በኲር ሲመታ፣ የበጉ ደም ምልክት ያለበትን የእስራኤላውያንን ቤት ምልክቱን እያየ ማለፉን ለማመልከት ነው፡፡ /ዘጸ. 12፣1-20/፡፡ በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እስራኤላውያን በመጀመሪያ ወራቸው በ14ኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ ሀገራችንም አስቀድማ ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች ሀገር እንደመሆኗ ይህ ድርጊት ይፈጸምባት ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ፋሲካ ተብሎ የተጠራበት ምክንያት በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ደሙን ስላፈሰሰልን ነው፡፡ በደሙ መፍሰስ ሞተ በኲር የተባለ ሞተ ነፍስ ርቆልናልና፡፡ «ፋሲካችንም ክርስቶስ ነው» /1ቆሮ. 5፣7 1ጴጥ. 1፣18-19/

በዚህ ዕለት እንደ ማክሰኞ ሁሉ በዮሐ. 14፣16 የሚገኘውን ለደቀመዛሙርቱ ረጅም ትምህርት አስተምሯል፡፡ የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎች ምስጢረ ሥላሴ የሦስትነት ትምህርት፣ ምስጢረ ሥጋዌ /የአምላክ ሰው መሆን/፣ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን /የዳግም ምጽአቱን ነገር/ ነው፡፡ እነዚህን ትምህርቶች በስፋትና በጥልቀት መማር እንደሚገባ ሲያስረዳ፣ በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲችል በረጅም ትምህርት እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም እሱ እያስተማራቸው ሳለ ያልገባቸውንም እየጠየቁ ተረድ ተዋል፡፡ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቆ መረዳት እንደሚገባን እንማራለን፡፡ በዚሁ ዕለት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠበት ቀን ነው፡፡ ማቴ. 26፣47-58

ዓርብ-

የስቅለት ዓርብ ይባላል፡፡ የዓለም ሁሉ መድኃኒት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ መዋሉን ለማስታወስ ነው፡፡ /ማቴ. 27፣35/፡፡

መልካሙ ዓርብ ይባላል፡፡ ይህም የሚያስገነዝበን ከስቅለተ ክርስቶስ በፊት አንድ ሰው ሲያጠፋ ተሰቅሎ ይሞታል፡፡ በሮማውያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት ነበር፡፡ በዚህ ዕለት የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምሕረት ምልክት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስለ አደረገው፣ በሞቱ መልካሙን ሕይወትን ስለአገኘን መልካሙ ዓርብ ተብሏል፡፡

የትንሣኤን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የሚሔዱ ምእመናን ሁሉ በዕለተ ዓርብ መከራውን ለማሰብ ከቤተ ጲላጦስ እስከ ጎልጎታ መቃብረ ክርስቶስ ድረስ ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ጉዞ የሚደረግባቸውም አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል የተፈጸሙባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡

በዚህ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው መከራውን በማሰብ ሲሰግዱ የሚውሉ እንዳሉ ሁሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ በስም ክርስቲያን ተብለን ከምንጠራው መካከል፣ ተድላ ደስታ በሚፈጸምባ ቸው ሥፍራዎች ክፉ ሥራ ስንፈጽም የምንውል አንጠፋም፡፡ እንዲህ የምናደርግ ሁሉ በአለፈው ልንጸጸትና በቀሪ ዘመናችን ልንታረም ይገባል፡፡ በዓመት አንዴ የምናገኘው ይህ ዕለት ቀራንዮን የምናስብበት፤ ነገረ መስቀሉን የምናስተውልበት እንጂ ስለ ምድራዊ ኑሮአችን ስንባክን ኃጢአት ስንሠራ የምንውልበት ሊሆን አይገባም፡፡

ቅዳሜ-

ቀዳም ሥዑር ይባላል፡፡ በዚች ዕለት ከድሮው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምት ውል የተሻረችው ቅዳሜ ተብላለች፡፡

ለምለም ቅዳሜ ካህናቱ ለምእመ ናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለሆነ በዚህ ተሠይሟል፡፡ ቀጤ ማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል፡፡

ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል፡፡ ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው  ሁሉ ያረፈበት ሲሆን፤ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን  ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷ ታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘ ለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡ የዕለታ ቱን ክብርና ሥያሜ ከማወቅና ከመ ረዳት ጋር በዕለታቱ የታዘዙትን ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን መወጣት ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡

ምንጭ- መጽሐፈ ግብረ ሕማማት
-ሐመርና መለከት መጽሔቶች
ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በሰላም

Kepilatos_Adebabay_Eske_Litostra.JPG

ከጲላጦስ ዐደባባይ እስከ ሊቶስጥራ

Kepilatos_Adebabay_Eske_Litostra.JPG

ዕለታተ ሰሙነ ሕማማት ወምስጢራት

በዲ.ቸሬ አበበ

 

ከአባታችን አዳም በደል ወይንም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሰፍታት፣ ወዘተ በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የሆነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ጥሮ ግሮ ወጥቶ ወርዶ ለፍቶ ማስኖ የዕለት ጉርስ የቀን ልብስ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነበር፡፡ ሁልጊዜ የሰው ልጅ ቢያጠፋ ቢበድል ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳ የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የሆነ አምላክ የጠፋውን ሊፈለግ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ያጣውን ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላም ሊሰጥ፣ ተስፋ የሌለውን ተስፋ ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኃጡአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም ምሳሌ ሆነን፡፡ ዲያብሎስን ድል አድርጐ ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ሆነን፡፡
 
ሰሙነ ሕማማት ምንድን ነው?

ሰመነ ስምንት /ሳምንት/ አደረገ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከዕለተ ሆሣዕና ሰርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ሐመ ማለት ታመመ ማለት ሲሆን ይህም የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልእት አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡
መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም እግዚአብሔር ይፍታህ አይሉም የሳምንቱ ሥርዓተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምጽ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መሆናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡

በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜያት

ዕለተ ሰኑይ /ሰኞ/
ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ /የቤተ መቅደስ መንጻት/ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ /ማር.11-11፣ ማቴ.21-18-22 ሉቃ.13-6-9/፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ «ወመሰለ ሎሙ ወይቤሎሙ አሐዱ ብእሲ በለሰ ቦቱ ውስተ አጸደ ወይኑ ወየሐውር ይንሣእ ፍሬሃ ወኢይረክብ …»፤ ይህንም ምሳሌ አለ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም፡፡ በማለት በበለስ ስለተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ እንዲመለስ ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያጠይቃል፡፡ ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደጠወለገችና እንደተቆረጠች ሁሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቆረጡ እንዲሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባርን ነው፡፡ ሁላችን ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት ወምግባር አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንሆን ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም እንዳይጠወለግ እንዳይደርቅ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡
ዕለተ ሠሉስ /ማክሰኞ/
ይህ ቀን ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?» የሚል ነበር፡፡ /ማቴ.21-23-27/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ «ወይቤሎሙ ኢየሱስ አማን እብለክሙ ከመ መጸብሓውያን ወዘማውያት ይቀድሙክሙ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር»፤ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው እውነት እላችኋለሁ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል ሲል አስተምሯል፡፡ /ማቴ.21-28/
ዕለተ ረቡዕ

ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ የምክር ቀን በመባል ይጠራል፡፡

ዕለተ ሐሙስ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም «ወሶበ ኀፀቦሙ እገሪሆሙ ነሥአ አልባሲሁ ወረፈቀ ካዕበ ወይቤሎሙ አእመርክሙኑ ዘገበርኩ ለክሙ … ወሶበ አነ እንከ ሊቅክሙ ወእግዚእክሙ ኀፀብኩክሙ እገሪክሙ ከማሁኬ አንትሙኒ ይደልወክሙ ትኅፅቡ እግረ ቢጽክሙ፡፡»፤ «እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ እንዲህም አላቸው ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን?… እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል ሲል ተናግሯል፡፡ /ዮሐ.13-12-20/፡፡
ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ በማለት ምሥጢረ ቁርባንን የመሠረተበት ወይም ራሱ ምስጢረ ቁርባንን የጀመረበት ቀን በመሆኑ የምስጢር ቀን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው፡፡ /ማቴ.26-26-29/፡፡
አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ በእነርሱ ጥበብና ፍላጐት ቀስ ብለው መጥተው የያዙበት ቀን ስለሆነ በዚህ ዕለት በለሆሳስ /ብዙ የድምጽ ጩኸት ሳይሰማ/ የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ስለሆነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ የሕጽበት፣ የምስጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሓ ታጥበው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡
ዕለተ ዐርብ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» /1ቆሮ.1-18/፡፡ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ /ማቴ.27-35-75/፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ እነርሱ ግን እኛስ ምን አግዶን?  አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ፡፡ ተማክረውም የሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ፡፡ /ማቴ.27-3-9/
የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ አርማ ሆኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት መልካሙ ዓርብ በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡
ቀዳሜ ስዑር
ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈበት ዕለት ነች፡፡ ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት እግዚአብሔርን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ ስላረፈበት ሰንበት ዐባይ /ታላቋ ሰንበት/ ትባላለች ታላቋን ሰንበት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዘፍ.1፡3፡፡
ዕለተ ቀዳሚት /ሰንበት ዐባይ/ በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደ ተደረገባት ሁሉ የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ የሆነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በመቃብር አርፎባታል፡፡ ማቴ.27፡61፡፡
በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ «ቀዳሜ ስዑር » ትሰኛለች፡፡ ስዑር ቀዳሜ የተባለችው በዓመት አንድ ቀን ስለ ምትጾም ነው፡፡ ምክንያቱም እናቱ ድንግል ማርያም ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡
ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን በመጾምና በመጸለይ ዕለቷ እንዳከበሯት የተዋሕዶ ልጆች የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው የሚያከፍሉ /የሚጾሙ/ ለሁለት ቀን እህል ውኃ ሳይቀምሱ ያድራሉ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡
በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ካህናቱ «ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፡-በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ» የምሥራች እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡት ምእመናን ቄጠማ ይታደላል ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖህ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ዘፍ.9-1-29፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡
«ቄጠማ»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡
የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል /የሲኦል ቃጠሎ/ ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳሃን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡ 
 

ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡አሜን፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የሆሳዕና እሁድ

በዲ/ን በረከት አዝመራው
 
«አንች የጽዮን ልጅ አትፍሪ፤ እነሆ ንጉሥሽ በእህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል» ተብሎ እንደተጻፈ ኢየሱስ የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርሱ ተቀመጠ ዮሐ.12፥15፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመምጣቱ አስቀድሞ 1400 ዓመታት በፊት እግዚአብሔር በአብርሃም የእምነት ቃል ኪዳን ሕዝቡ ያደረጋቸውን እስራኤላውያንን በጽኑ  ክንድ ከባርነት ቀንበር አውጠቶ ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን አምድ እየመራ በመገናኛዋ ድንኳን ውስጥ አድሮ እርሱ ንጉሣቸው ሆኖ እነርሱ ደግሞ ህዝቡ ሆነው በምድረ በዳ መራቸው፤ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከነዓንም አገባቸው፡፡ እስራኤል ግን ምድራዊ ንጉሥ በመፈለግ ንጉሣቸው እግዚአብሔርን በመተዋቸው እግዚአብሔርን በደሉ፤ በምድር ላይ ያለች የመንግሥቱ ማሳያ ሊሆኑ የመረጣቸው ሕዝቡ ምድራዊ ንጉሥ ፈልገዋልና፡፡ መልከ መልካምና ያማረ የሆነው ሳኦል እስራኤል የመረጡት ምድራዊ ንጉሥ ውጫዊ ክብር ብቻ ያለው መሆኑን አስመስከረ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከዚህ ዓለም ያልሆነች በቁሳዊው ኅብር ያላጌጠች፣ የትህትናና የፍቅር የምሥጋና የሆነች መንግሥቱን ሊያመለክት ሲወድ ከወንድሞቹ ሁሉ ያነሰውንና በገና ደርደሪውን የእሴይን ልጅ ዳዊትን መረጠ፡፡ የዳዊት መንግሥት ብታልፍም « ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ» ያለውን ቃልኪዳን ግን አላጠፋም ፡፡ ስለዚህም በአምላክነቱ ለዘላለም የነገሥታት ንጉሥ የሆነ ወልድ ከዳዊት ዘር ሰው ሲሆን የዳዊት ተስፋ ተፈጸመ፤ በመለኮታዊ ስልጣኑ በእግዚአብሔር እሪና ያለው ወልደ እግዚአብሔር የዳዊት ልጅ ሆኗልና፡፡ ስለዚህም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበስራት «ካንቺ የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፡፡ እርሱም በያዕቆብ ወገን ላይ ለዘላለም ይነግሳል» በማለት የትንቢቱን ፍፃሜ አበሰረ፡፡ /ሉቃ.1/

  ንጉሥነ ክርስቶስ

ጌታችን ሲወለድ ስብዓሰገል «የተወለደው የእስራኤል ንጉሥ ወዴት ነው» በማለት ንጉሥነቱን ገልጠዋል፡፡ /ሉቃ. 2፥2/ ነገር ግን በምድራዊ ክብር ያጌጠ ሳይሆን በከብቶች ግርግም የተኛ፣ በእረኞችና በከብቶች የተከበበ ትሁት ንጉሥ ነው፡፡ መንግሥቱ ከዚህ ዓለም ያልሆነች ሰማያዊት ነችና መላእክት በዝማሬ አመሰገኑት፡፡ ጌታ ንጉሥ ያልሆነበት አንድ ጊዜም  ባይኖርም ይህች መንግሥቱ በምድራዊ ክብር ሳይሆን በትህትና በፍቅር ያጌጠች ሰማያዊት ስለሆነች በሃሳባቸው ምድራውያን የሆኑ ሰዎች ሊያውቋት አልቻሉም፡፡ ስለዚሀ የቀጠራት ሰዓት ስትደርሰ ሰማያዊትና መንፈሳዊት መንግሥቱን በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ በትህትና ገለጣት፡፡

«ሆሳዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው፡፡» ዮሐ.12፥13   

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአልዓዛር ቤት በቢታኒያ የመጨረሻውን ራት ከበላ በኋላ ሐዋርያቱን ልኮ የአህያ ውርንጫ አስመጥቶ በርሷ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በዚህም  የሚከተሉት ነገሮች ተገልጠዋል፡ ፣

1.    መንግሥቱ የትህትና እና የፈቃድ መሆኗን

አህያ ከእንሰሳት ሁሉ የማታስፈራ ናት፡፡ ጌታም እንደ ነገሥታቱ ስርዓት በከበረ ሰረገላና በፈረስ ሳይሆን በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ መንግሥቱ የትህትና መሆኗንና ሁሉም ሰው ተገዶ እና ፈርቶ ሳይሆን በፈቃዱ የሚገባባት መሆኗን ለማሳየት ነው፤ በአህያ ሰውን አባሮ መያዝ እንኳ አይቻልምና፡፡ ይህም በአጋጣሚ እንደ አንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ የሆነ ሳይሆን ነቢያት በትንቢት የተናገሩትና በእግዚአብሔር የድህነት ጉዞ የታሰበ ነው፡፡ ነቢዩ ዘካርያርስ ስለዚህ ሲናገር «አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንች የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዬ፤ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም  ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንች ይመጣል» በማለት ገልጦታል፡፡ ዘካ.9፥9፡፡

2.    የመገለጡ አላማ ለድህነት እንጅ ለክብር አለመሆኑ

 
እስራኤላውያን የፋሲካን በዓል ከማክበራቸው ከአምስት ቀን በፊት በዚህ ዕለት ለፋሲካ የሚሆኑት ጠቦቶችን ወደ ኢየሩሳሌም ይዘው ይገቡ ነበር፡፡ /ዘጸ.12፥1- 36/ ጌታችንም በዚህ ዕለት ወደ ኢየሩሳሌም መውጣቱ የመንግስቱን ምሥጢር በመስቀልና በመስዋዕትነት ፍቅር የሚገልጽ የእግዚአብሔር በግ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ከላይ በተጠቀሰው የዘካርያስ ትንቢት ላይ « እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው» የሚለው፡፡ ጌታችን ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ለመመስገን አስቦ ሳይሆን ይቀበሉት ዘንድ አለምን ለማዳን የመጣው ንጉሥ እርሱ መሆኑን በአደባባይ ለማወጅ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ምሥጋናን  ከህፃናት የተቀበለው፤ ሕፃናት ሁሉን ይቀበላሉና፡፡ ለዚህም ነው እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አትገቡም በማለት የተናገረው፡፡ / ሉቃ. 18፥17 / የመዳን ተስፋ የተነገረላቸው እስራኤላውያን ባልተቀበሉት ጊዜ ግን የመጣበት ዓላማ ይህ ስለነበር  ስለነርሱ አለቀሰ፡፡ ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፤ እንዲህም አለ «ለሰላምሸ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ እንኳ ብታወቂ አሁን ግን ከአይንሽ ተሰውሯል» ሉቃ. 19.41፡፡ የመምጣቱ ዓላማ ለዓለም ሰላምን የሚሰጥ /እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቅ/ አዳኝ ንጉሥ፣ የፋሲካ በግ መሆኑን ለማወጅ ነበርና ባልተቀበሉት ጊዜ አለቀሰላቸው፡፡ «ሆሳዕና» ማለት ግን «አሁን አድን» ማለት ስለሆነ አዳኝነቱ መቀበል ነበር፡፡ ንጉሥነቱን በአዳኝነቱ መግለጡም መንግሥቱ የፍቅር መሆኑንና ዙፋኑም መስቀል መሆኑን ለመግለጥ ነው፤ በጉ «የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ» ነውና፡፡ ራዕይ.19፥13- 16

  የሆሳዕና አከባበር በቅድስት ቤተክርስቲያናችን

ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሆሳዕና በታላቅ ክብር ታከብራለች፡፡ አከባበሯም እንደ አይሁድ እሁድ ሆሳዕና በእግዚአብሔር ስም የመጣች የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፣ ሆሳዕና በአርያም ካሉ በኋላ አርብ « ይሰቀል ይሰቀል» በማለት ሳይሆን እስከ መጨረሻው ድረስ ከእርሱ ጋር መሆንን በሚያሳይ አስደሳችና መንፈሳውያን ስርዓቶቿ ነው፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡

ዑደት

በቤተከርስቲያትን ሥርዓት መሰረት የሆሳዕና ጠዋት ቅዳሴ ከመገባቱ በፊት ዑደት ይደረጋል፡፡ ዑደቱም ከቤተመቅደስ ተጀምሮ በየአራት በሮች እየቆመ ምስባክ እየተሰበከ ወንጌል እየተነበበ ከተዞረ በኋላ በመጨረሻ ካህናቱና ዲያቆናቱ ወደ ቤተመቅደሱ ሲመለሱ ያልቃል፡፡ ዑደቱንም ዲያቆናት መስቀልና ስዕል /የእመቤታችን/ ይዘው፣ ካህኑ ማዕጠንት እያጠኑ ይመሩታል፡፡

 
ይህ ዑደት የቤተክርስቲያን ዘላለማዊው ጉዞዋ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ጉዞ ከእግዚአብሔር ይጀምራል፡፡ ክርስትና የእግዚአብሔር ጅማሬ እንጅ የሰው አይደለምና፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ ዑደት ከመሰዊያው ይጀምራል፤ መስዊያው ሰማያዊ ነውና፡፡ የዚህ የቤተክርስቲያን ጉዞ መሪ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር መርቶ ያደረሰ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ ካህኑ ዕጣን እያጠነ ይመራል፡፡ ይህ ጉዞ መከራ ያለበት መንገዱ ጠባብ ይሁን  እንጅ በደስታ የተሞላ ነው፡፡ ስለዚህ ዲያቆኑ መስቀል ሲይዝ ሕዝቡ ደግሞ ይዘምራሉ፡፡ ደስታና መስቀልን በአንድ ላይ ለመግለጥ ነው፡፡ የዚህ ጉዞ ፍጹም አርአያ ደግሞ እመቤታችን ናት ሁለቱንም ታሳያለችና፡፡ በአንድ በኩለ «ኅዘን በልቧ ያለፈ» ሲሆን በሌላ በኩል « ተአብዮ ነፍስዬ ለእግዚአብሔር ወትተሐሰይ መንፈስየ» ብላ ዘምራለችና፡፡ ዑደቱ በምዕራብ በር በኩል /በዋናው በር/ መጀመሩ እና በእያንዳንዱ በር መቆማችን የዘላለም ደጆች መከፈታቸውንና ሰማያውያንም የጉዞአችን /የማኅብራችን/ ተካፋዮች መሆናቸውን ያጠይቃል፡፡ በመጨረሻም ዑደቱ በካህናቱ ወደቤተ መቅደሱ መግባት መጠናቀቁ የክርስትና ጉዟችን ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም በመኖር መፈጸሙን ያሳያል ፡፡ በዚህ ጉዞዋ ቤተክርስቲያናችን እስከ መጨረሻው ከክርስቶስ የሚጸና ዘላለማው ጉዞዋን ትናገራለች፡፡

  ቅዳሴ

ከዑደት በኋላ ቅዳሴ ይቀጥላል፡፡ በቅዳሴም የክርስቶስን ሥጋና ደም እንቀበላለን በዚህም እስከሞት ድረስ የሚዘልቅ አንድነታችን እንገልጣለን፡፡ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ «ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሌ ይፈጸማል፡፡ ለአህዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና ይዘብቱበትማል፣ ያንገላቱትማል፣ ይተፉበታል፤ ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል በሦስተኛውም ቀን ይነሳል፡፡» እንዳለ የኢየሩሳሌም ጉዞው ወደሞት የተደረገ ጉዞ ነበር፡፡ ስለዚህ በሥጋወደሙ ከእርሱ ጋር የሆንን ምእመናንንም ከእርሱ ጋር ወደ ሙት እንሄዳለን፡፡   

ፍትሐት

ከቅዳሴ በኋላ ፍትሃት ይደረጋል፤ ይህም ለህዝቡ ሁሉ ነው፡፡ አንዳንዶች ይህ ፍትሃት ምናልባት በዚህ ሰሞን የሚሞቱ ካሉ በሚል የሚደረግ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ፍትሃት ለሁሉም ክርስቲያን ጭምር ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የጌታን ሞትና ትንሳኤ ማሰብ ሳይሆን አብረነው ሞቱን ትንሳኤውን እንካፈላለንና፡፡ ሰውነታችን በጸሎትና በስግደት ለዓለማዊ ፈቃዳችን ሁሉ ገድለን በእርሱ ትንሳኤ ትንሳኤ ልቦናን እንነሳለንና፡፡ ይህም ለመነኮሳት እንደሚደረግ ፍትሃት ያለ ነው፡፡ መነኮሳት ሲመነኩሱ ለዚህ ዓለም የሞቱ መሆናቸውንና የክርስቶስን መስቀል መሸከማቸውን ለማጠየቅ የሙታን ጸሎት እንደሚደረግላቸው ምእመናንንም የጌታን መስቀል በመሸከምና መከራውን በመካፈል ለዓለም ለመሞት በመወሰን ቤተክርስቲያን የሙታን ጸሎት ታደርግላቸዋለች፡፡ በዚህም ጌታችንን አብረን ወደ ሞቱ እንከተለዋለን፡፡

  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሀብዎሙ ዘይበልዑ/ክፍል ሁለት/

 የሚበሉትን ስጡአቸው /ማቴ. 14፣16 /

  በመ/ር አፈወርቅ ወ/አረጋዊ

ባለፈው ትምህርታችን «የሚበሉትን ስጡአቸው» በሚል ርእስ ቅዱሳን ሐዋርያት ለጌታችን ያቀረቡትን ጥያቄ፣ ጌታችን የመለሰላቸውን ድንቅ ነገር የሕብስቱ መባረክና መበርከትን በተመለከተ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ በዚህ እትም ደግሞ ካለፈው የቀጠለውን አቅርበናልና መልካም የሕይወትና የድኅነት ትምህርት ያድርግልን፡፡

በሊቀ ነቢያት ሙሴ መሪነት ወደ ምድረ ርስት ይጓዙ ለነበሩት ሕዝበ እስራኤል እግዚአብሔር እንዲህ አላቸው፡፡ «በሥርዓቴ ብትሔዱ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉትም ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፤ ምድሪቱም እህሏን ትሰጣለች፤ የሜዳውም ዛፎች ፍሬያቸውን ይሰጣሉ፤ የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቆረጥ ይደርሳል፤ የወይኑ መቆረጥም እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራን ትበላላችሁ. . .» ዘሌዋ. 26፣3-13፣ ዘዳ. 11፣13-17፡፡

 

በዚህ ርእሰ ትምህርት ላይ በትኩረት የምንመለከታቸው ዐበይት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ/ የእግዚአብሔርን ርኅራኄ፣ ቸርነትና መግቦት
ለ/ በመታዘዝ የሚገኘውን ታላቅ በረከት
ሐ/ ለጋስነትን
መ/ የችግር ተካፋይ መሆንን
ሠ/ ያለውን ማካፈልን
ረ/ የሥራ ድርሻን ማወቅ
 

በአጭሩ ለመረዳት ያህል እነዚህን አጉልተን ጠቀስን እንጂ፤ በዚህ ዐረፍተ ነገር ውስጥ እጅግ በርካታ ምስጢራት፣ ትምህርቶችና ትርጓሜዎች አሉ፡፡ ያቀረብናቸውን ነጥቦች በዝርዝር እንመልከት፡፡

መታዘዝ

የተራበውን ሕዝብ እንዲመግቡ ከጌታ የታዘዙት ደቀ መዛሙርቱ /ሐዋርያት/ ዓለምን በምግበ ሥጋ በምግበ ነፍስ እንዲጎበኙት ታዘዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም እንዲጠብቁት እንዲከባከቡት ቢታመም በተሰጣቸው ሥልጣን እንዲፈውሱት ሙሉ ሥልጣን ተሰጥቶአቸዋል፡፡ መታዘዝንም አስተምሮአቸዋል፡፡

ዓለም ይህን አውቆ ወደ መጋቢዎቹ ወደ ጠባቂዎቹ ቀርቦ ምግበ ሥጋውን ምግበ ነፍሱን ሊመገብ ይገባዋል፡፡ ከሚደርስበት መከራም ሊጠበቅና ሊፈወስ ይችል ዘንድ ወደ ጠባቂዎቹ ካህናት /ሐዋርያት/ በመቅረብ ጠባቂዎቹን አውቆ ከሌላው ሊሸሽ ግድ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ከመታዘዝ አንዱ ነውና፡፡

አበው ነቢያትና ሐዋርያት ለእውነት በመታዘዛቸው ጥቂቱን በማበርከት፣ መራራውን በማጣፈጥ፣ አስገራሚ ተአምራት በማድረግ፣ በጸሎታቸው የሕዝቡን ችግር አስወግደዋል፡፡
1. ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ለስራፕታዋ መበለት ትንሿን ዱቄት በማበርከት
2. ነቢየ እግዚአብሔር ኤልሳዕ ልጆቿ በዕዳ የተያዙባትን ሴት ጥቂቱን ዘይት በማብዛት፣ መካን ለነበረችው የሱነማይቱ ሴት ልጅ በመስጠት የአባትነት ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡

ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ነቢያቱም ሆነ ሐዋርያቱ በመጀመሪያ ታዛዦች ሆነው በመገኘታቸው ነው፡፡

የሚታዘዝ ይባረካል የማይታዘዝ ደግሞ ይረገማል፡፡ ሰው ለእግዚአብሔር ቢታዘዝ በረከትን ይቀበላል መርገሙ ከእርሱ ይርቃል፡፡

«እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉ ግን ብታምፁ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሯልና» ኢሳ. 1፣19፣ ዘዳ. 11፣27፡፡

ምግባራትን ሁሉ መታዘዝ ይቀድማቸዋል በክርስትናው ዓለም መታዘዝ ማለት፤

– ለእግዚአብሔርና ለሕጉ
– ለወላጅና ለቤተሰብ
– ለአካባቢና ለጎረቤት
– እግዚአብሔር ለሾማቸው ካህናት
– በዕድሜ ለገፉ አባቶችና እናቶች

እንደ አስፈላጊነቱ መታዘዝ ይገባል፡፡ ሐዋርያት በቅንነት በመታዘዛቸው በሥራቸው ፍሬ አፍርተዋል፡፡ የሐዋ. 10፣33፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ጌታችን ተከተሉኝ ሲላቸው ተከተሉት፡፡ ለሕዝቡ የሚበሉትን ስጡአቸው ሲላቸው ያላቸውን ያለንፍገት በማቅረብ  ሰጡ፡፡

ከእግዚአብሔር የመጣውን ትእዛዝ ሳንጠራጠር ሳንሟገት ጠቃሚ መሆኑን አውቀን በጽኑ እምነት ልንቀበል ያስፈልጋል፡፡

ሰማዕታት በእሳት፣ በስለት፣ በሰንሰለት በጅራፍ፣ በመገረፍ፣ በመስቀል በመሰቀል ይህንና ይህን በመሳሰለው መከራ ተፈትነው በሃይማኖታቸው ጸንተው ፈተናውን ድል አድርገው የተቀበሉትን ቃል ኪዳን ሳይጠራጠሩ መቀበል መታዘዝ ነው፡፡

ለጋስነት

ለጋስ ማለት ያልቅብኛል ይጎልብኛል ሳይል ሳይሳሳ በንፍገት ሳይሆን በቸርነት የሚሰጥ፤ ዘመድ ወገን ሳይል የሰው ወገን የሆነውን ሁሉ የሚረዳ፤ ለተራበው የሚያበላ፣ ለተጠማው የሚያጠጣ፣ ለተራቆተው የሚያለብስ ደግ ቸር የሆነ ሁሉ ለጋስ ይባላል፡፡

በዘመነ አበው በለጋስነት ከታወቁት አባቶች ታላቁን አብርሃምን ብንመለከት በየዕለቱ እንግዳ ይቀበል ነበር፡፡ በዚህ ግብሩም ታላቅ የበረከት አባት እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡ ዘፍ. 12፣2፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «የወንድማማቾች መዋደድ ይኑር እንግዶችን መቀበል አትርሱ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ተቀብለዋል» ዕብ.13፣1-2 በማለት በቸርነት በለጋስነት የተገኘውን ረድኤት በረከት አሳይቷል፡፡

እግዚአብሔር በሀብት በዕውቀት በመግቦት የጎበኛቸው ሁሉ ለጋሶች፣ ሳይነፍጉ ሀብታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ታማኝነታቸውን የሚሰጡ እንዲሆኑ ይህ ርእሰ ትምህርት ይናገራል፡፡ የሐዋርያት ለጋስነት ከብዙ ነገር ላይ ተነሥቶ ሳይሆን በትንሹ ላይ በመለገስ ለበረከት መብቃትን ያሳያል፡፡

ችግርን መጋራት

በዚች ምድር ላይ የተፈጠረ ፍጥረት ሁሉ በተለይም የሰው ልጅ ችግሩ ይለያይ እንጂ ችግር የማይደርስበት የለም፡፡

አንዱ የገንዘብ ችግር ባይኖርበት የጤና ችግር ይኖርበታል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ገንዘብና ጤንነት ተሟልተውለት በትዳር የሚቸገር፣ ትዳር ተሟልቶለት በልጅ እጦት የሚቸገር ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ በኩል የሚመጣውን ችግር መወጣት ያዳግተዋል፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከት ችግር ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ሁሉንም እንደየችግሩ ልንረዳና ልንረዳዳ፣ በችግሩ ልንጋራ፣ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ወደ ሰርግ ቤት ከመሔድ ይልቅ ወደ ልቅሶ ቤት መሔድ ይሻላል ያለው፤ የተቸገሩትን መርዳት ያዘኑትን ማጽናናት ማረጋጋትን ሲያስረዳን ነው፡፡

የሐዋርያት ጥያቄ የጌታችንም መልስ በችግርና በችግረኞች ላይ የተደረገ ውይይትና መፍትሔም የታየበት ነበር፡፡ የመፍትሔው አካላት ለመሆን ፈቃደኞች እንሁን፡፡ 

ሐዋርያው «በአሁኑ ዘመን ባለጠጎች የሆኑትን መልካም እንዲያደርጉ በበጎ ሥራ ባለጠጎች እንዲሆኑ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው» 1ጢሞ. 6፣17-19 ይላል፡፡ መርዳት የሚችሉ አካላት በመርዳታቸው የችግር ተካፋዮች መሆናቸውን ማመን ያስፈልጋል፡፡

ድርሻን ማወቅ

ከትንሽ እስከ ትልቅ ከአገልጋይ እስከ ተገልጋይ ከመጋቢ እስከ ተመጋቢ ያለው የሥራ ድርሻውን ማወቅ በእጅጉ  ጠቃሚ ነው፡፡ የሥራን ድርሻ ሳያውቁ መንቀሳቀስ ፍምን በእጅ ጨብጦ አልቃጠልም እንደማለት ነው፡፡ ጆሮ የዓይንን እግር የእጅን ሥራ ሊሠራ እንደማይችል ሁሉ የሥራ ድርሻውን የማያውቅ እንዲሁ ነው፡፡

ዳታንና አቤሮን በሊቀ ነቢያት ሙሴና በሊቀ ካህናት አሮን የሥራ ድርሻ ውስጥ በመግባት ክህነታዊ ሥራ እንሠራለን ብለው አደጋ ላይ ወድቀዋል፤ በእሳት ተበልተዋል፤ ምድር ተከፍታ ውጣቸዋለች፡፡

ንጉሡ ግዝያንም በማን አለብኝነት ተነሣሥቶ በሥጋዊ ሥልጣኑ ተመክቶ ክህነታዊ ሥራ እሠራለሁ በማለቱ በለምጽ ተመትቶ ሞቷል፡፡

የሐዋርያት ድርሻ የሕዝቡን ችግር ወደ ፈጣሪያቸው ማቅረብ፣ የታዘዙትን በቅንነት መፈጸም፣ ያላቸውን ይዘው መቅረብ ነበር፡፡ የጌታችን ድርሻ ለሐዋርያት መመሪያ መስጠት፣ የቀረበውን ማበርከት፣ የተቸገረው ሕዝብ ከችግሩ እንዲላቀቅ ሐዋርያት ድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ ነበር፡፡ ይህ ችግር ፈች አሠራር ለባለ ድርሻዎች ሁሉ አርአያነት አለው፡፡

በአጠቃላይ በየትኛውም የሥራና የአገልግሎት ድርሻ ሆነን ሕዝብን እንደምናገለግል በቅድሚያ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ «የሚያስተምር ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር» ሮሜ. 12፣7-8 ተብሎ ተጽፏል፡፡

«ሀብዎሙ ዘይበልዑ፤ የሚበሉትን ስጡአቸው» የተባሉ እነማን ናቸው? ለምን ተባሉ? መመሪያውንስ እንዴት ተወጡት? አሁን ከእኛ ምን ይጠበቃል? እንወያይበት፡፡

የሚመግብ ሆነ የሚመገብ ድርሻውን አውቆ ይሥራ፡፡ እንደተሰጠው ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢውም ተመጋቢውም ራሱን አሳልፎ ለፈጣሪው ይስጥ፡፡ መጋቢም ተመጋቢም የምግባቸው ዐውደ ማዕድ፤ ሲሳዮሙ ለቅዱሳን፤ የተባለ   እግዚአብሔር መሆኑን አምኖ መቀበል ብስለት ነው፡፡

የምንመገበውንና የሚመግቡንን ያዘዘልንና የሰጠን እግዚአብሔር ይመስገን አሜን፡፡

አለማመኔን እርዳው

በመ/ር ኃይለማርያም ላቀው

«እምነት፣ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረዳ ነው» ዕብ. 11፣1፡፡ የሰው ልጅ ተስፈኛ ወይም ተስፋ ያለው ፍጡር ነው፡፡ አዳም ቢበድልም እንኳን ቸሩ አምላክ በኋላ ዘመን ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ተስፋ ሰጥቶታል፡፡ አዳምም የመዳኑን ነገር በእምነት ተስፋ በማድረጉ በጊዜው አግኝቶታል፡፡ እምነት ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የምንገልጥበት፣ እርሱን ደስ የምናሰኝበት የሕይወት መሠረት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እምነት እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኝበት ጥበብ መሆኑን ሲያስረዳ «ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይ ቻልም» ብሏል፡፡ ዕብ. 11፣6፡፡

በዘመነ ብሉይ የነበሩ በእምነት ጥን ካሬአቸው የተመሰከረላቸው አበውና እመው በእግዚአብሔር በመታመናቸው በሚያቃጥል የእሳት ነበልባል ውስጥ በመጣል፣ ወደ አንበሳ ጉድጓድ በመወርወር፣ በሰይፍ በመተርተር እምነታቸውን ገልጠዋል፡፡ እግዚአብሔርም በቅዱሳን የእምነት ጥንካሬ የልበ ደንዳኖችን ልብ ማርኳል፡፡ «ንጉሡ ናቡከደነጾር ለጣዖት አንሰግድም ብለው እምነታቸውን የገለጡትን ሠለስቱ ደቂቅን ርዝማኔው አስራ ስድስት ክንድ ከሚደርስ የእሳት ነበልባል ውስጥ በሰንሰለት አስሮ ቢወርወራቸውም ከሰውነታቸው አንዳች ሳይቃጠል በመዳናቸው፤ «በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብ ደናጎ አምላክ ይባረክ» ዳን. 3፣25 ሲል የሠለስቱ ደቂቅን አምላክ አክብሯል፡፡

በዘመነ ሐዲስ በሰው ፍቅር ተስቦ ወደዚህ ዓለም የመጣው ቸሩ አምላክ ለአገልግሎት ከመረጣቸው ሰዎች አንዳንዶቹ ምንም ዓይነት መሠረታዊ የሃይማኖት ዕውቀት አልነበራቸውም፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን አላዋቂዎችን የመረጠው በዘመኑ በዕውቀታቸው የሚታበዩ ሰዎችን ዕውቀት ከንቱ ለማድረግ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጌታችን የዓለምን ጥበብ ከንቱ ለማድረግ አላዋቂዎችን እንደመረጠ ሲያስረዳ፤ «እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔር የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም መረጠ፡፡» ብሏል፡፡ 1ኛቆሮ.1፣26-29፡፡

እግዚአብሔር ለእምነት አገልግሎት ሰዎችን ሲመርጥ ሞኞች ጠቢባን ይሆናሉ፤ አላዋቂዎች ሀብተ እውቀት ያገኛሉ፤ ደካማዎች ብርቱዎች ይሆናሉ፡፡ አላዋቂ የነበሩት ተከታዮቹ ጠቢባን፤ ደካማ የነበሩት ብርቱዎች እስከሚሆኑ ድረስ ለቀጣይ የእምነት ሕይ ወታቸው ብርታት እንዲሆናቸው የተለያዩ ጥያቄዎችን ለጌታችን ያቀርቡ ነበር፡፡

ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይከተሉ ከነበሩ ሰዎች ለጌታችን ካቀረቡት ጥያቄ አንዱ «አለማመኔን እርዳው» የሚል ነው፡፡ ጌታችን የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው የተከተሉትን በሕይወት ሰጪ ትምህርቱ በነፍስ የተመሙትን ተስፋ የቆረጡትን፣ ባዶነት የሚሰማቸውን መንፈሳዊ ዝለት የገጠማቸውን ሲፈውስ፤ በተአምራቱ ደግሞ በሕማመ ሥጋ የታመሙትን ፈውሷል፡፡ የጌታችንን ሕይወት ሰጪ ትምህርት ፈልገው የተከተሉ አብዛኛዎች በተከፈለ ልብ ነበር፡፡ መድኃኒታችን የተከፈለ ልብ ያላቸውን ማረጋጋት፣ ያዘኑትን ማጽናናት ግብሩ በመሆኑ ድክመታቸውን ሳይሸሸጉ የሚቀርቡትን ፈጣን ምላሽ ይሰጣል፡፡

የጌታችን ደቀ መዛሙርት ልጁን እንዲፈውሱለት የወሰደው ሰው፤ ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ የእምነት ማነስ የተነሣ ፍቱን መፍትሔ ቢያጣም ከጌታችን ዘንድ መጥቶ የእምነቱ ጉድለት በጌታችን እንዲስተ ካክልለት የልጁን ሕማም ሁኔታ ከዘረዘረ በኋላ፤ «ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳን» ማር.9፣22 የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ «ቢቻልህ የሚለውን» የጥርጣሬ ቃል «ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሰው ሁሉ ይቻላል፡፡» በሚል ቃል ሲያርመው የተቸገረው ሰው አለማመኑ በእርሱ እንዲጠገንለት «በታላቅ ድምፅ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው» ብሎታል፡፡ ይህ ሰው አምናለሁ አለማመኔን እርዳው በማለት በእምነት ሕይወት ውስጥ ያለበትን ችግር ሳይሸሸግ መናገሩን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

ምክንያቱም እያመን የማናምን፣ ንስሐ እየገባን የማንፀፀት፣ እየቆረብን ለሥጋ ወደሙ ክብር የማንሰጥ፣ እየቀደስን ያልተቀደስን ብዙዎች ነን፡፡ እኛም እናምናለን ነገር ግን እምነታችን በአንተ ይታገዝ እርዳን ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ብዙ ሰዎች ክርስቶስ መወለዱን፣ መጠመቁን፣ ከሙታን መነሣቱን (ትንሣኤውን መግለጡን) ያምናሉ፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ድርሻ እና ተስፋ ግን ይጠራጠራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር እያመንን በእምነት ሕይወት ውስጥ አንኖርም ለዚህ ማለዘቢያ ግን እምነታችን፣ አለማወቃችንና ድካማችን በጌታችን እንዲደገፍ መማጸን ነው፡፡

በማቴዎስ ወንጌል ቅዱሳን ሐዋርያት የታመመውን ልጅ ለመፈወስ አቅም ያጡበትን ምክንያት ለመረዳት፤ «እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለምንድነው?» ሲሉ ጌታችንን ጠይቀውታል /ማቴ.17፣19/፡፡ ይህ ጥያቄ የእኛም ጥያቄ ነው፡፡ እኔ የተሰጠኝን ሓላፊነት ያልተወጣሁት ስለምንድነው? ያልቆረብኩት ስለምንድነው? ከልቤ ውስጥ የሚጉላላውን ቂም ያላወጣሁት ስለምንድነው? የበደልኩትን ያልካስኩት ስለምንድነው? የሚፈታተነኝን የሰይጣን ፈተና ማለፍ ያልቻልኩት ስለምንድነው? መንፈሳዊ ሕይወቴ ማደግ ያልቻለው፣ ራሴን ማወቅ መረዳት ያልቻልኩት ስለምንድነው? ብለን እንድንጠይቅ የቅዱሳን ሐዋርያት ጥያቄ ይጋብዘናል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት እግዚአብሔር ከጎናቸው እያለ የእምነት ጉድለት ስለታየባቸው ማድረግ የሚገባቸውን ለመፈጸም አልቻሉም፤ ነገር ግን ልባቸውን የፈነቀለውን አንገብጋቢ ጥያቄ መጠየቃቸው መልካም ነበር፡፡ ምክንያቱም በእምነት ሊያደርጉት የሚቻላቸውን ነገር ማድረግ የተሣናቸው ስለእምነታቸው ጉድለት መሆኑን ጌታችን አስረግጦ እንዲህ በማለት ነግሯቸዋል፡፡ «እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ሾላ ተነቅለህ በሌላ ቦታ ተተከል ብትሉት ይታዘዝላች ኋል» ሉቃ.17፣6 ብሏቸዋል፡፡ «ማመን፣ ያመኑትን ማድረግ» ከባድ ነገር ነው፡፡ ዛሬ ስለእምነት፣  በእምነት ሕይወት ስለመኖር፣ የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት በማድረግ የቅዱሳንን ገድልና ትሩፋት በመግለጥ ብዙ ነገር ተነግሮናል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛዎቻችን ቃሉ በጭንጫ ላይ የተዘራ ዘር ሆኖብናል፤ /ማቴ. 13፣20/ «ጌታችን በጭንጫ ላይ ዘር ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ደረቀ» ያለውን ሲፈታ «በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበል ነው፡፡ ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል፡፡» ብሏል፡፡

በእምነት መንፈሳዊ ሕይወታቸው አልጸና ብሎአቸው ይቸገሩ የነበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን ያቀረቡት ጥያቄ መሠረታዊ ምላሽ አግኝቶ፤ የሰውነ ታቸው ለልብሳቸው፤ የልብሳቸው ለጥላቸው አልፎ ሕሙም ከመፈወስ ሙት እስከ ማስነሣት ደርሰዋል፡፡ ይኸውም ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ በዚህም አገልግሎታቸው እንደ ሠመረላቸው መረዳት ይቻላል፡፡

እኛም «በሃይማኖት ስትኖሩ ራሳች ሁን መርምሩ» ተብሎ እንደተነገረን፤ በቅድሚያ መንፈሳዊ ሕይወቴ ያላደገው ለምንድ ነው? ብለን ያለንን የእምነት ጥንካሬና ድክመት መመዘን አለብን፡፡ በማስከተል እንደ ታመመው ልጅ አባት «አለማመኔን እርዳው» የሚል ጥያቄ አቅርበን፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል ፍጹም እምነት ሲኖረን ጌታችን እንዳለው ተራራ የሆነብን ትዕቢት፣ ከፊታችን የተደ ቀነው ክፋት፣ ምቀኝነት ከሕይወ ታችን ይነቀላል፡፡ እየወላወለ የሚያ ስቸግረን ልቡናችን ክት እንዲሆን ወይም እንዲሰበሰብልን «አለማመኔን እርዳው» ማለት አለብን፡፡ አለማመናችን በእግዚአብሔር ሲረዳ ባሕሩ እንደ የብስ ጸንቶልን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በባሕር ላይ እንረማመዳለን፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር አለማመናችንን ሲረዳው የሚሣነን ነገር የለም፡፡ «በእኔ የሚያምን ከእኔ የበለጠ ያደርጋል» ተብሎ ለቅዱሳን የተገባው ቃል የታመነ ነው፡፡ 

ያ በእምነት ያልጸናው ሰው ለእግዚአብሔር አምላኩ «አለማመ ኔን እርዳው» ሲል ያቀረበው ጥያቄ የሁላችንንም ሕይወት የሚወክል ነው፡፡ ዛሬ እምነቱ ሥርዓቱ፣ ትውፊቱ እያ ለን በፍጹም ልብ ያለማመን ችግር አለብን፡፡ ልጁ የታመመበት ሰው «አለማመኔን እርዳው ሲል» በአንተ ታምኜ የምኖርበትን ኃይል ለአንተ የሚገዛ ልብ እና ሕይወት ስጠኝ ማለቱ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ከአባቶቻችን የተቀበልነው እምነት የፈተና ጎርፍ ሳይሸረሽረው ነፋስ ሳያ ዘመው በዐለት ላይ ተመሥርቶ እን ዲጸናልን ዘወትር «ጌታ ሆይ አለማ መኔን እርዳው» ማለት አለብን፡፡ ያለማመናችን ችግር በእግዚአብሔር ካልተረዳ «ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ» በማለት ብቻ መንግሥተ ሰማያትን እንደማንወርስ ተነግሮናል፡፡ በመሆ ኑም ልባሞች ከመብራታቸው ጋር ዘይት ይዘው ሙሽራውን እንደጠበቁ፤ ባለማመን የጠወለገውን ሕይወታ ችንን በቃሉ ዝናምነት በማለምለም አለማመናችን በእግዚአብሔር ቃል መረዳት አለበት፡፡

ማንኛውም የሕይወት ውጣ ውረድ ቢያጋጥመን በእምነት ከጸናን የማናልፈው ነገር የለም፡፡ የማንዘለው የችግር እና የመከራ ግንብ፣ የማንሻገረው ባሕር እና መሰናክል የለም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በእምነት ከእግዚአብሔር ጋር ከኖርን የሚያስፈራን አንዳች ነገር አለመኖሩን ሲያስረዳ «በሞት ጥላ መካከል እንኳን ብሔድ፤ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል» መዝ. 22፣4 ብሏል፡፡

ነቢዩ እንደ ነገረን አፋችንን ሞልተን «በሞት ጥላ መካከል እንኳን ብሔድ ክፉን አልፈራም» በማለት በእምነት ማደግ አለብን፡፡ ቅዱስ ዳዊት በሕይወት ዘመኑ መውደቅ መነሣት ያጋጠመው ሰው ቢሆንም በእምነት በመጽናቱ ፍጻሜው ሠምሮ ልበ አምላክ ለመባል በቅቷል፡፡ በመሆኑም ዛሬ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የተደቀነብንን ፈተና የምናልፈው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኘው በእምነት ነው፡፡ የሚመጣውን ነገር በተስፋ የሚያስረዳንም እምነት በመ ሆኑ አለማመናችንን እርዳው እያልን መጮህ ይገባል፡፡

አለማመናችን በእግዚአብሔር ሲረዳ ወይም በእምነት ስንጸና ረድኤተ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ኃያላን የሆኑትን አራዊት ሳይቀር ገራም ያደርግልናል፡፡ በዘመነ ብሉይ ነቢዩ ዳንኤል ከአናብስት ጉድጓድ ሲወረወር የተራቡት አንበሶች ለነቢዩ ገራም የሆኑት የእምነት ሰው በመሆኑ ነው፡፡ በቅድስናቸው የተመሰከረላቸው ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አናምርት /ነብሮች/ እና አናብስት /አንበሶች/ የእግራቸውን ትቢያ እየላሱ የታዘዙላቸው በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን በእምነት ነው፡፡ ዛሬ ዲያብሎስ «እንደተራበ አንበሳ በፊታችን በሚያደባበት ዘመን የእምነትን ጥሩር መልበስ ያስፈልጋል፡፡ ለቀደሙት አባቶች ሥጋት የነበሩት ነገሮች ቀሊልና ታዛዥ እንደሆኑ ለእኛም ይሆኑልናል፡፡ ብዙ ጊዜ ፈቃደ ሥጋችን ፈቃደ ነፍሳችንን ሲጫነው የምንወደውን ሳይሆን የማንወደውን እናደርጋለን፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም» ሮሜ. 7፣19፡፡ ሲል እንደተናገረው፤ የሥጋችን ፈቃድ ብዙ ጊዜ «ነፍሴ ብይ፣ ጠጪ ደስ ይበልሽ» ወደ ማለት ቢያዘነብልም ቅሉ ወደ ፈቃደ ነፍስም መለስ ብሎ እኔ ማነኝ? ጉዞዬስ ወዴት ነው? ተስፋዬስ ማን ነው? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ፈቃደ ሥጋው እያየለ ሲያስቸግረው፤ በእንባው መኝታውን እያራሰ በእግዚአብሔር ፊት ቢያለቅስ፤ የኃጢአት አሽክላ እየተ ቆረጠለት በእምነቱ የሚደሰት ሰው ሆኗል፡፡

በእምነት ጉድለት በዲያብሎስ ሽንገላ የእምነት አቅም አጥተን ከቤተ ክርስቲያን ከቅድስና ሕይወት የራቅን ወገኖች፤ አለማመናችንን እግዚአብሔር እንዲረዳው ሳንሰለች ጥያቄ ማቅረብ አለብን፡፡ አስቀድመን እንደገለጽነው በእምነት ጉድለት ምክንያት ያጣነውን በረከት፣ ያጣነውን ጽናት እናገኛለን፡፡ ልባሞቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ይህን ለመፈጸም ለምን እኛን ተሳነን? ብለው እንደጠየቁ፤ እኛም ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡ በጎ መሥራት ለምን ተሳነን?

የሰው ልጅ ወደ እምነት ፍጹም ነት ውስጥ ሲገባ ሁሉ ነገር በእግዚአብሔር እጅ እንደሆነ ይረዳል፤ ከጭንቀትም ያርፋል፡፡

በአቅማችንና በፈቃዳችን የተቸገረን መርዳት፣ አምላክን ከልብ መውደድ፣ ማመስገን የእምነት ሰው መገለጫ ናቸው፡፡

በእምነት የጸኑ አባቶችን በአንበሳ ጉድጓድ፣ በእሳት ውስጥ፣ በወህኒ ቤት በተጣሉ ጊዜ የተረዳና የእምነታቸውን ዋጋ የከፈለ እግዚአብሔር ዛሬም አለ፡፡ በመሆኑም መንፈሳዊ ሕይወታችንን በእምነት አሳድገን ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ያብቃን፡፡

  

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Melakit_Yemegebuat_Blatena.jpg

መላእክት የመገቧት ብላቴና

መ/ር መንግሥተአብ አበጋዝ

  Melakit_Yemegebuat_Blatena.jpg

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? መላእክት በሰማይ የሚኖሩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናቸውን ታውቃላችሁ አይደል? በመጽሐፍ ቅዱስ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ዕብራውያን ሰዎች ምዕራፍ 1 ቁጥር 7 ላይ ይገኛል፡፡

 

በጣም ጥሩ ልጆች ከዚህ በተጨማሪ መላእክት በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 18 ቁጥር 10 ላይ እንደተገለጸው፤ እኛን የሰው ልጆችን ሁሉ ከክፉ የሚጠብቁ እና በእግዚአብሔር ፊት የሚጸልዩልን ናቸው፡፡

ዛሬ የምንነግራችሁ ከቅዱሳን መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ፋኑኤል የተባለው መልአክ የፈጸመውን ተግባር ነው፡፡

ኢያቄምና ሐና የተባሉ የእግዚአብሔር ሰዎች በስዕለት ያገኟትን ልጃቸውን ለእግዚአብሔር ቤት ሊሰጧት በሦስት ዓመቷ ወደ ቤተ መቅደስ ይዘዋት መጡ፡፡
የቤተ መቅደሱም አገልጋዮች /ካህናት/ በኢያቄምና ሐና አሳብ ተገርመው ሕጿኗን ምን እንመግባታለን እያሉም ተጨነቁ፡፡

በዚህ ወቅት ነበር አንድ አስደናቂ ነገር በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የታየው፡፡ ስሙ ፋኑኤል የተባለው መልአክ በእጁ ሕብስትና ወይን ይዞ መጥቶ ነበርና የቤተ መቅደሱ አካባቢ በብርሃን ተሞላ፡፡

የቤተ መቅደሱ ሓላፊ ካህኑ ዘካርያስ ለእርሱ መልእክት ሊያደርስ የመጣ መስሎት ወደ መልአኩ ተጠጋ፡፡ መልአኩ ግን ከእርሱ ራቀ፡፡ ደግሞም በየተራ ሕዝቡም ካህናቱም ወደ መልአኩ ቀረቡ መልአኩ ግን ከሁሉም እየራቀ ከፍ አለ፡፡

ከዚህ በኋላ ካህናቱ የእግዚአብሔር ጥበብ አይታወቅምና መልአኩ የመጣው ለብላቴናዋ /ለሕጻኗ/ ይሆናልና፤ ሐና ሆይ እስኪ ትተሻት እልፍ በይ አሏት፡፡ ሐናም ሕጻን ልጇን ትታት ራቅ አለች፡፡ በዚህ ጊዜ መልአኩ ብላቴናይቱን አንድ ክንፉን አንጥፎ አንድ ክንፉን ጋርዶ የሰው ቁመት ያህል ከመሬት ከፍ አደረጋትና መግቧት ወደ ሰማይ ተመለሰ፡፡

በእግዚአብሔር ሥራ ሕዝቡ ሁሉ ተደነቁ፡፡ ምን እንመግባታለን? እያሉ ይጨነቁ የነበሩት ካህናትም የምግቧን ነገር መልአኩ ከያዘልንማ ብለው ቤተ መቅደስ እንድትገባ አደረጓት፡፡ ብላቴናይቱም መላእክት እየመገቧት እስከ አሥራ አምስት ዓመቷ በቤተ መቅደስ ኖረች፡፡

ልጆች ይህች ብላቴና ማን ናት?

እናትና አባቷ ማን ይባላሉ? 

ይመግባት የነበረው መልአክ ስሙ ማን ነው? በሉ ደህና ሁኑ!
ወላጆች:- ለሕጻናት ተጨማሪ ጥያቄ በማቅረብ ታሪኩን በቃል እንዲያጠኑና እንዲነግሯችሁ አድርጉ፡፡

በደማቸው እንዳንጠየቅ ሥጋት አለን

በስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት የምናስተውለው ችግር በሕዝቦች መካከል ያለው የቋንቋ ልዩነትና በነዚህ ቋንቋዎች ሠልጥነው የተዘጋጁ ልኡካን ማነስ ነበር፡፡ ይህ ችግር ብዙ ማኅበረሰቦችን ከስብከተ ወንጌል ተለይተው እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህም ሌላ ሕዝቡ በተለያዩ የእምነት ድርጅቶች እንዲወሰድና ከበረት እንዲወጣም ሆኗል፡፡

 

አሁን አሁን በመጠኑም ቢሆን የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት፣ ሰባክያን፣ መዘምራን፣ ማኅበራት ወዘተ ምእመናን በሚያውቁትና በሚረዱት ቋንቋቸው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲያገኙ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

መዝሙሮች፣ የትምህርትና የጸሎት መጻሕፍት ወዘተ ወደ ልዩ ልዩ የሀገራችን ቋንቋዎች በመተርጐም ላይ ናቸው፡፡ ከዚህም አለፍ ብሎ በየቋንቋው ትምህርት የሚሰጡ፣ መዝሙር የሚያዘጋጁ፣ የሚቀድሱና የሚናዝዙ ካህናትም እየተገኙ ነው፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ በሰንበት ት/ቤቶች፣ በሰባክያን፣ በመዘምራን፣ በማኅበራት፣ በዲያቆናትና በካህናት የሚደረገው ጥረት በየአካባቢው ያለውን ሕዝብ ከመናፍቃን ቅሰጣ ታድጐ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲያውቅ እያደረገው መሆኑን በየጊዜው የሚሰሙት ዜናዎች ያስረዳሉ፡፡

በበቂ ሁኔታም ባይሆን ማኅበረ ቅዱሳንም ይህን ችግር ለመቅረፍና አገልግሎቱን ለማስፋፋት መዝሙራቱን፣ የትምህርትና የጸሎት መጻሕፍቱን በየቋንቋው ከመተርጐም እና ከማዘጋጀት ባለፈ በአካባቢያቸው /በአፍ መፍቻ/ ቋንቋቸው ትምህርተ ወንጌልን የሚያስተምሩና በመቅደስ አገልግሎት የሚሳተፉ ወገኖች ከየአህጉረ ስብከቱ በየደረጃው ካሉ የቤተክርስቲያን ሓላፊዎች ጋር በመተባበር በርቀት ከጠረፋማ እና ገጠራማ አካባቢዎች ሠልጣኞችን በማስመጣት እያስተማረ ይገኛል፡፡ ለዚህም በቅርቡ ከየካቲት 1 እስከ የካቲት 15 ቀን 2002 ዓ. ም. ድረስ ከጋምቤላ ሀገረ ስብከት ከሰባት የገጠር ወረዳዎች ለተውጣጡ አሥራ ስድስት ተተኪ ሰባክያን የሰጠውን ሥልጠና መጥቀስ ይቻላል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ስብከተ ወንጌል ካልተስፋፋባቸው የሀገሪቱ ገጠራማ እና ጠረፋማ የወረዳ ከተሞች የተተኪ ሰባክያን ሥልጠና ሲሰጥ ይሄኛው ለ11ኛ ጊዜ ሲሆን፤ እስከ አሁን ከየሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ጋር በመነጋገር ከ96 የሀገሪቱ ጠረፋማ ወረዳዎች ለተውጣጡ ከሁለት መቶ በላይ ተተኪ መምህራን መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ተምረው በቋንቋቸው ሕዝቡን እንዲያስተምሩ አሠልጥኖ አሰማርቷል፡፡

የሥልጠናውን ውጤት ለመዳሰስ እንደተሞከረው የተተኪ ሰባክያን ሥልጠና የወሰዱት ሰባክያን የአካባቢያቸውን ሕዝብ ከባዕድ አምልኮ በመመለስ፣ አስተምሮ በማስጠመቅ፣ አብያተ ክርስቲያናት በመትከልና የሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማደራጀት እና በማቋቅም ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ዓይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡

በመጠኑም ቢሆን ይህ ውጤት የተገኘው ለሥራው የየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት ድጋፍ፣ ከአጥቢያ ጀምሮ ሥልጠናውን ለመውሰድ የሚመጡትን ሠልጣኞች ከሚገኙበት ገጠራማና   ጠረፋማ ስብከተ ወንጌል ካልተዳረሰባቸው ወረዳዎች በመመልመል የየወረዳው ቤተ ክህነት ሓላፊዎች ቀናና የጋራ ትብብር ስለታከለበት ነው፡፡ ይህ ታላቅ ሥራ የቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ተልእኮ የሆነውን የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት የሚያስፋፋ በመሆኑ በየአካባቢው የሚሠሩትን መልካም ሥራዎች ብቻ በየራሳቸው እያዩ ከማመስገን ባሻገር አገልግሎቱ የሚስፋፋበትንና የሚጠነክርበትን ሥራ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ መጠቆም እንወዳለን፡፡

በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ የኅብረተሰብ ክፍሎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመናፈቅ እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ወገኖች ፈጽሞ በመናፍቃኑ ትምህርት ተጠራርገው ከመወሰዳቸው በፊት በቋንቋቸው በማስተማርም ሆነ በቋንቋቸው የሚያስተምሩ ሰዎችን ከየአካባቢያቸው በማሠልጠን ወንጌልን እንዲያስተምሯቸው ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

እነዚህን ወገኖች ወደተፈለገው የአገልግሎት ደረጃ ለማድረስ በቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ ሥልጠናዎች እነሱን መሠረት ያደረጉ እንዲሆኑ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ የአመላመል ሒደቱ፣ የትምህርት አሰጣጡ፣ የትምህርት መርጃ መሣሪያ አቅርቦቱ፣ ሥልጠናው የሚሰጥበት ማዕከላዊ ቦታ በዋናነት ሊታሰብበት የሚገባው ቁም ነገር መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወደካህናት ማሠልጠኛዎች፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት፣ የመቀሌ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ከሚገቡት ተማሪዎች መካከል በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ሊያስተምሩ ለሚችሉት እና በርቀት ለሚገኙት አካባቢዎች የተለየ ትኩረትና ቦታ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም የሥልጠናና የትምህርት ሒደቱን የሚከታተል የትምህርት ክፍል /ዲ¬ርትመንት/ ማቋቋም ይቻላል፡፡

እነዚህን ደቀ መዛሙርት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ ሥራ ለመሥራት በሚችሉበት መንገድ አሠልጥኖ ማሠማራቱ በሀገሪቱ የሚገኙትን ልዩ ልዩ ሕዝቦች በቀላሉ ለማስተማርና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር ያላቸውን የእናትነትና የልጅነት አንድነት ለማጠናከር ይረዳል፡፡ በየቦታው የሚደረገውን የትርጉምና የድርሰት ሥራ፤ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የሚሰጠውን   ሥልጠናና ትምህርትም ሥርዓት በማስያዝ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ከሆነ ዛሬ በደስታና ለቤተ ክርስቲያን በመቅናት የተጀመረው በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የማስተማር፣ የመዘመር፣ የማሠልጠን፣ የተለያዩ ጽሑፎችን የመድረስና የመተርጐም ሥራ ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶ ፍሬ ሊያፈራ በሚችልበት መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡

ይህ ካልሆነ ግን ዛሬ የቤተ ክርስቲያኒቱን እውነተኛና ቀጥተኛ ትምህርት በመናፈቅ    የሚጠብቁንን ሕዝቦች በኃጢአትና በክህደት ተጠልፈው በዲያብሎስ እጅ ወድቀው በሥጋም በነፍስም በመጐዳታቸው ምክንያት በደማቸው እንዳንጠየቅ እንሠጋለን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

Zimare_Mewasit.JPG

የዝማሬ መዋሥዕት አድራሾች ተመረቁ

በደረጀ ትዕዛዙ
 
Zimare_Mewasit.JPG
 
በዙር አባ አቡነ አረጋዊ ገዳም የዝማሬ መዋሥዕት ትምህርታቸውን ተከታትለው ተመረቁት ደቀ መዛሙርት ከአቡነ እንድርያስ ጋር

በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በላይ ጋይንት ወረዳ ሳሊ በተባለው ቀበሌ የሚገኘው የጽርሐ አርያም ዙር አባ አቡነ አረጋዊ ገዳም ዝማሬ መዋሥዕት ትምህርት ቤት ዐሥራ ሰባት የዝማሬ መዋሥዕት አድራሾችን አስመረቀ፡፡

የአብነት ትምህርት ቤቱ ጥር 30 ቀን 2002 ዓ.ም አድራሾችን ባስመረቀበት ወቅት ብፁዕ አቡነ እንድ ርያስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልእክት፤ «በብዙ ጥረት እና ድካም፤ በረጅም ጊዜ ያካበታችሁትን ዕውቀት በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንድታውሉት አደራ እላለሁ» ብለዋል፡፡

ምሩቃኑ ተግተው ቤተክርስቲያንን በማገልገል ሌሎችንም ተተኪ ደቀመዛሙርት ማፍራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ብፁዕነታቸው፤ ሀገረ ስብከታቸው ለዚህ ቅዱስ ተግባር ስኬታማነት የበኩሉን የሓላፊነት ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተመራቂ ቤተሰቦች፣ ካህናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፤ ዝማሬ፣ ቅኔ መወድስ የአማርኛ እና የግእዝ ቅኔ ግጥሞች በተመራቂዎች መቅረቡን ከደብረ ታቦር ማእከል የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ «አድራሽ» ማለት በቤተ ክርስቲያን የአብነት ት/ቤቶች ለመምህርነት የሚያበቃቸውን ሙያ ተምረው ያጠናቀቁ ደቀመዛሙርት ማለት ነው፡፡