በስመ አብ ወወልድ ወመንፈሰድ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በመላው ዓለም የተስፋፋውን የኮኖና ወረርሽኝ ለመግታት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

በሀገራችን ኢትዮጵያ በገጠር፣ በከተማና በመላው ዓለም ለምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን በሙሉ!

ወቅታዊ የሰው ልጅ ሥጋት በመሆን በመላው ዓለም በፍጥነት በተስፋፋው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም አቀፍ ሥጋት ስለተከሰተ መንግሥታት ሀገርን ከጥፋት፣ ሕዝብን ከሞት ለመጠበቅ አዋጆችን እያወጡ ይገኛሉ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ለመታደግ እምነትና ቀኖናን ጠብቆ ሃይማኖታዊ መመሪያ የመስጠት ሐዋርያዊ ኃላፊነት አለባት፡፡

ስለዚህ ቋሚ ሲኖዶስ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሠረት እምነትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጠብቆ ለሁሉም ካህናትና ለሕዝበ እግዚአብሔር ደኅንነት ሲባል የሚከተሉትን መመሪያዎች አስተላልፏል፡-

  1. በሰሙነ ሕማማት እንደምናደርገው የእርስ በርስ መሳሳም ቀርቶ ራስን በማድረግ፣ እጅ በመንሳት ወይም በእማሄ ሰላምታ በማቅረብ እንዲፈጸም፣
  2. ወረርሽኙ በሰዎች መሰብሰብ የሚስፋፋ ስለሆነ ማናቸውም መንፈሳዊ ጉባኤያት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት፣ ወደ ገዳማትና አድባራት የሚደረጉ ጉዞዎች እና ምእማናን የሚሳተፍባቸው ታላላቅ መርሐ ግብሮች ለጊዜው እንዲቋረጡ፣
  3. ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባም ሆነ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ እጆቻንን በመታጠብና ዘርዘር ብሎ በመቆም ሥርዓተ አምልኮ እንዲፈጸም፣
  4. ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓላት በቅዳሴና በማኀሌት ታስበው ክብረ በዓላቱ በሌላ ጊዜ እንዲከበሩ፣
  5. የጉንፋን ምልክት ያለባቸው ለሌሎች እንዳያስተላልፉ በቤታቸው በጥንቃቄ ተለይተው በጸሎትና በሕክምና እንዲቆዩ፣ ከቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊ አገልግሎት በልዩ ሁኔታ እንዲያገኙ፣
  6. በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የተስፋ ልዑክ በመሆን እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ተደራጅቶ ተልዕኮውን በአስቸኳይ እንዲጀምር
  7. ሥርዓተ ቅዳሴን በተመለለተ፡-
  • በቤተ መቅደስ ቀዳሲያን በሆኑት ልዑካን ብቻ ሥርዓተ ቅዳሴው እንዲፈጸምና ሌሎች አገልጋዮች በቅድስቱ ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያገለግሉ፣
  • በዕለቱ ለሚቀርቡ ምእመናን ለአረጋዊያን፣ ለወጣቶችና ሕፃናት የፈረቃ ተራ በማዘጋጀት ቆራቢዎች ብቻ ወደ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያስቅድሱ
  • ሌሎች ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ቢያንስ ሁለት የትልቅ ሰው እርምጃ ያህል በመራራቅ ቆመው እንዲያስቀድሱ፣
  • የቅዳሴ ጠበል በየግል መጠቀሚያ ምእመናን በየቆሙበት ቦታ በጥንቃቄ እንዲሰጥ፣
  • ሌሎች ከቅዳሴ ጋር የተያያዙ ዝርዝር የአፈፃጸም ጉዳዮችን ግብረ ኃይሉ አዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ በማጸደቅ ለአህጉረ ስብከት በሚልከው መመሪያ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ፣
  1. ከሥርዓተ ቅዳሴ በተጨማሪ እንደ ስብሐት ነግሕ፣ ሰዓታት፣ ቁመተ ማኅሌት፣ ጥምቀተ ክርስትና፣ ጸሎተ ፍትሐት፣ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለሥርዓቱ በሚያስፈልገው ቁጥር ብቻ እና በውስን ሊቃውንት በተራ እንዲፈፀም፣
  2. ወረርሽኙ ከዓለም እንዲጠፋ ካህናት ብቻ በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምሕረትና በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጸሎተ እጣን በማድረስ ማዕጠንት እንዲፈጽሙ፣
  3. በማኅበራዊ ግንኙነት በደስታ፣ በሀዘን፣ በእድር፣ በሥርዓተ ቀብር አፈጻጸምና በመሳሰሉት መሰባሰቦች በሽታው እንዳይሰራጭ አገልግሎቱ በውስን የሰው ቁጥር በጥንቃቄ እንዲፈጸም፤
  4. ምእመናን ራሳቸውን እየጠበቁ በቫይረሱ የተጠቁና አገግመው የወጡ ወገኖችን፣ እንዲሁም በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ከሃይማኖት እና ከምግባር የወጣ መገለልና ጥቃት እንዳይደርስባቸው በክርስቲያናዊ ፍቅር እና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንክብካቤ እንዲደረግላቸው፣
  5. ለነዳያን እና ለተቸገሩ ወገኖች አስፈላጊው ማኅበራዊ እና ቁሳዊ እገዛ በሁሉም አጥቢያዎች እንዲደረግ፣
  6. ቤተ ክርስቲያንን ከማይወክሉና ቀኖናዊ ካልሆነ አሳሳች መጃዎች በመቆጠብ ሊቃውንት፣ ካህናት ፣ መምህራን፣ ሰባኪያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጡ መመሪያዎችን በየአጥቢያችሁ እና አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንድትጽሙ እና እንድታስፈጽሙ ተወስኗል፡፡

በአጠቃላይ በበሽታው እስከ አሁን ለተያዙት፣ በጊዜያዊ ማቆያ ለሚገኙት በሙሉ እግዚአብሔር አምላካችን ምሕረት እንዲሰጥልን እንጸልያለን፤

በመላው ዓለም የምትገኙ ወገኖቻችን የራሳችሁና የሌሎች ሕይወት ከወረርሽኙ እንዲጠበቅ እንዲሁም የበሽታው ሥርጭት እንዲቆም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እያሳሰብን የተሰጡት መመሪያዎች ወረርሽኙ እስኪጠፋ ድረስ የጸኑ እንዲሆኑ በጥብቅ እናስታውቃለን፡፡

ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱና በይቅርታው ብዛት ዓለማችንን ከጥፋት የሰውን ልጅ ሁሉ ከመከራ ሞት ይጠብቅልን አሜን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ/ም አዲስ አበባ