‹‹የእግዚአብሔር ምሕረቱ ብዙ ነው እያልክ በኃጢአት ላይ ኃጢአት አትሥራ››
(ሲራክ ፭፥፭) 

በለሜሳ ጉተታ

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በመጽሐፈ ሲራክ ላይ ይህንን ኃይለ ቃል ተመዝግቦ እናገኘዋለን፤ መነሻውም በምዕራፍ ፭ ላይ ያለው ቃል  ነው፡፡ ቃሉም ስለ እግዚአብሔር ምሕረትና ስለ ኃጢአት ክፋት ያስተምራል፡፡ እግዚአብሔር መልካም ደግና በጎ ነገርን ፈጠረ፡፡ ሰይጣንና የሰው ልጅ ግን በራሳቸው ሀሳብ፣ ፍላጎትና ክፉ ሀሳብ ሲመሩ ክፋትን ሠሩ፡፡ ይህንንም መጽሐፉ ‹‹ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብ እና ሲታለል ይፈተናል፡፡ ምኞትም ከፀነሰች ኃጢአትን ትወልዳለች፣ ኃጢአትም ከተፈጸመች ሞትን ትወልዳለች›› በማለት ጠቅሶታል፡፡ (ያዕ. ፩፥፲፫)

እግዚአብሔር በባሕርይ መሐሪ፣ ይቅር ባይና ቸር አምላክ ነው፡፡ ተጸጽቶ ለተመለሱና ከልብ ለተማጸኑት ኃጢአትን ይቅር ይላል፤ የንስሓ ጊዜም ይሰጣል፤ ሆኖም የንስሓን ትርጉም ሳይረዱ ኃጢአትን በድፍረት እየሠሩ በስንፍና ወድቀው አምላክን ዘወትር በሐሰት አንደበት ከንቱ ውዳሴን የሚያድርጉትን ግን አይወድም፤ ይጸየፋቸዋልም፡፡

ኃጢአት መዘዙ ብዙ ነው፡፡ የሰዶምና የጎሞራ ሰዎች በኃጢአታቸውም ምክንያት ጠፍተዋል፤ የሎጥ ሚስትም የጨው ሐውልት ሆና የቀረችው በኃጢአቷ ምክንያት ነው፡፡ ኃጢአት ሰላምን ይነሳል፤ የእግዚአብሔር ምሕረትና ቸርነትን እንድናጣ ያደርጋል፡፡ የባቢሎን ሰዎች አንድ የነበረው ቋንቋቸው የተለወጠባቸው ኃጢአትን ስለሠሩ፣ ክፋትን ስላበዙ፣ እግዚአብሔርንም ስለተዳፋሩ ነው፡፡ በኃጢአት ምክንያት በምድር ላይ የነበሩ ሕዝቦችና ሀገሮች ጠፍተዋል፡፡ ዛሬም እኛ ሰላምን፣ አንድነትን፣ ፍቅርንና ጤንነትን ያጣነው፣ በረከት የራቀን፣ ጭካኔና ክፋት መገለጫችን የሆነው በኃጢአታችን የተነሳ ነው፡፡

እግዚአብሔርን በመፍራት መኖር ሲገባ በየዕለት ተግባራችን በአዕምሮአችን ክፋት በማሰብና ተንኮል ለመሥራት በመሻት፣ ከሰብአዊነት ይልቅ ጭካኔ በልባችን ሞልቶ ጥቅምን በማስበለጥ ኃጢአትንና ክፋትና እየሠራን እንውላን፡፡ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌላቸው ሰዎች ፈጣሪን ስለሚረሱ ባዕድነትን ይላመዳሉ፤ ግብዝም ይሆናሉ፤ ይህም ማንነታቸውን አስለውጦ ወደ ርኩስነት ይለውጣቸዋል፡፡ መጥፎ መንፈስ በውስጣቸው በሚገባበትም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ስለሚርቃቸው ጥሩውን በመጥላት ክፋትን ይወዳሉ፤ በመጥፎነታቸውም ይመካሉ፡፡  እግዚአብሔር አምላክን መዳፈር ይጀምራሉ፤ ሕጉን በተላለፉና ሥርዓቱን በጣሱ ቁጥርም በዓለማዊ ኑሮአቸው፣ በአምልኮት እና በተቀደሱ ሥፍራዎች ጭምር ኃጢአትን ይፈጽማሉ፡፡ ይህም አምላክን ያስቆጣል፤ ለመቅሰፍትም ይዳርጋል፤ ለመርገምና ለመከራ አሳልፎ ይሰጣል፤ በአገልግሎት፣ በክርስትናና በመንፈሳዊ ሕይወትም ዝለትን፤ በሃይማኖትና በምግባር ጉድለትን ያመጣል፤ ከእግዚአብሔር መንግሥት ይለያል፤ ለዘላለም ሞትም አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው›› የሚለን፡፡ (ሮሜ.፮፥፳፫)

እናም ይህን የሚያውቅና መዳን የሚፈልግ ሰው ኃጢአት በመሥራቱ ተጸጽቶ ይቅርታን እና ምሕረትን በመሻት ከልብ ሊማጸን ይገባል እንጂ ‹‹የእግዚአብሔር ምሕረቱ ብዙ ነው፤ ምንም ያህል ኃጢአት ብሠራ እንኳን ይቅር ይለኛል›› ብሎ ከኃጢአት ላይ ኃጢአት መሥራቱ ለዘለዓለም ቅጣት ይዳርገዋል፡፡ንስሓ ከኃጢአት ለመንጻት፣ ንጽሕናንና ቅድስናን ገንዘብ ለማድረግ ይረዳልና በንስሓ ነፍሳችንና ሥጋችንን ማጽዳት ይጠበቅብናል፡፡ ከበደልና ኃጢአት መመለስ ክፋትን መተው፣ ንስሓም መግባት ከእኛ ይጠበቃል፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ለማግኘት፣ መንፈሳዊ ፍሬዎችን ለማፍራት፣ ከሥጋ ፍሬና ተግባር ለመላቀቅ፣ ከኃጢአት ራስን ለመጠበቅ፣ በጥምቀት ያገኘነውን የሥላሴ የጸጋ ልጅነትን እንዳናጣ፣ ከጸጋ እግዘአብሔርም እንዳንለይ እና የእግዚአብሔር በረከት እንዳይጎድልብንም ይረደል፡፡ ለዚህ ደግሞ በየዕለቱ ንስሓ መግባትና በንስሓ ሕይወትም መመላለስ ያስፈልጋል፡፡ የኃጢአት ጥፋቱ ብዙ በመሆኑ ጸጋንና ክብር አንዲሁም ማንነትን ያሳጣል፡፡ ከእግዚአብሔር መንግሥትና አንድነቱም ይለያል፡፡ በመንፈሰዊ ሕይወትና በአገልግሎት ላይም ያዳክማል፤ የመንፈስ ዝለትንም ያመጣል፤ ለዘለዓለም ሞትም አሳልፎ ይሰጣል፤ ስለዚህም ራሳችንን ከዚህ ልንጠብቅ ይገባል፡፡

የሰው ልጅ ለሕይወት እንጅ ለሞት የተፈጠረ ፍጡር አይደለም፡፡ አፈጣጠሩም ከሌሎች ፍጥረታት ድንቅ ሆኖ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል ነው፡፡ አምላካችን ሲፈጥረን በምክንያት ነውና ዘለዓለማዊ ሕይወት እናገኛለን፡፡ ለዚህ ክብር ለመብቃት ደግሞ ራስን ከኃጢአት፣ ከክፋት፣ ከተንኮል እና ከምቀኝነት መጠበቅ አለብን፡፡ ኃጢአት ከእግዚአብሔር መንግሥት ይለያል፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ›› የሚለን (ሮሜ. ፮፥፲፪)፤ በንሰሓ ግን ከዚህ መንጻት ይቻላል፡፡

እግዚአብሔር በባሕርይ መሐሪና ይቅር ባይ ነው፤ ትዕግስቱም የበዛ አምላክ ነው፤ መአትን ወደ ምሕረት፤ ቁጣን ወደ ትዕግስት ይለውጣል፤ የሰውን ልጅ መዳን እንጂ ጥፋት አይፈልግም፡፡ ለዚህ ደግሞ የንስሓ ሕይወትን ሰጥቶናል፡፡ እርሱ በደልን የማይቆጥር ኃጢአትንም የሚያስተሰርይ የይቅርታ አምላክ ነው፡፡ ሥጋን ተዋሕዶ መከራንም የተቀበለውና የተሰቀለው ለእኛ ድኅነት እንዲሁም ፍቅሩንም ሊገልጽልን ስለፈቀደ ነው፡፡ የበደሉትን፣ ያጠፉትን፣ እርሱን ያሳዘኑትንም ይቅር ያላቸው፣ ምሕረትና ቸርነትንም ያደረገላቸው ወደ እርሱ ተመልሰው፣ ለሕጉ ለመገዛትና ትእዛዛቱን ለመፈጸም በመፈለጋቸው ነው፡፡  ወንበዴውን ይቅር ያለው፣ የጴጥሮስን እንባ የተቀበለው፣ ለሞት አሳልፎ የሰጠውን ይሁዳን ከሞት እንዲመለስ በዛፍ ያናገረው፣ ዘማዊቷንም ይቅር ያላት በጸጸትና በለቅሶ ስለተማጸኑት ነው፡፡ በንስሓ ከጥፋታቸው የሚመለሱ ይድናሉ፤ እምቢ ያሉት ግን በክፋታቸው ይጠፋሉ፤ ለዚህ ነው ‹‹እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ÷ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉ ግን ብታምፁም ሰይፍ ይበላችኋል›› ያለን፡፡ (ኢሳ. ፩፥፲፱)

የእግዚአብሔር አምላካችንን ምሕረት ለማግኘት መጾም፣ መጸለይና በንስሓ ሕይወት ውስጥ መኖር ያስፈልጋል፡፡ ንስሓ ከኃአጢአት ያነጻል፤ ለመንግሥቱ ያበቃል፡፡ ካልሆነ ግን ‹‹መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል›› (ማቴ. ፯፥፲፱) የሚለው ቃል ይፈጸምብናል፡፡ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ለዚህም እራሱን ከኃጢአት ጠብቆ መኖር ይገባዋል፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ብሏል ‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ›› (ዘካ.፩፥፫)፡፡

ንስሓ እንዳንገባ የሚያደርገን አንዱ ነገር ሰበብ ነው፡፡ ሰበብ ያሰንፋል፤ ወደ ኋላ ይጎትታል፤ ተስፋም እንድንቆርጥ ያደርጋል፤ ለበለጠ ኃጢአትም ይገፋፋል፤ ዓለማዊ ሰውም ያደርጋል፤ ጊዜ የተሰጠን ለንስሓ እንጂ ለጥፋት አለመሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ስለዚህም ኃጢአት በመሥራታችን በመጸጸትና ተስፋ ሳንቆርጥ ዛሬ ንስሓ ልንገባ ይገባል፤ ምክንያቱም የመዳን ቀን ዛሬ ነውና፡፡