ቅዱሳን መላእክት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ቅዱሳን መላእክት
በመምህር ሳምሶን ንጋቱ
✝️ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ምሕረትና ርኅራኄን በሚያደርግበት ጊዜ በተደረገልን ነገር ተሳታፊ ከመሆናቸውም በላይ ደስተኛ እና አመስጋኞች መሆናቸውን መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ ”ድንገት ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት መጡ እግዚአብሔርንም ሲያመሰግኑ በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ለሰው ልጅ በጎ ፍቃድ አሉ፡፡” ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጸጋ አምላክ የተራቆትነውን መልሶ ሊያለብሰን በከብቶች በረት በጨርቅ በተጠቀለለ ጊዜ መላእክቱ በትሕትናው ቢደነቁም ለሰው ልጆች የተገባው ቃል ሲፈጸም ደስታቸውን በምስጋና ገልጸዋል (ሉቃ ፪፤ ፲፫)፡፡
እግዚአብሔርን ለሚያመልኩ ምእመናን በዙሪያቸው የሚከትሙና ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ የማዳን ታላቅ ሥልጣን የተሰጣቸው ቅዱሳን መላእክት ዘወትር ከሕይወታችን የማይርቁ መሆናቸው በነቢዩ ቅዱስ ዳዊት አንደበት እንዲህ ተዘምሯል፡፡ ”ይትአየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ ጠዐሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር”፤የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸዉማል እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱ ዕወቁም” እንዲል (መዝ ፴፫ ፤ ፯)፡፡
ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለምልጃ ከሚቆሙ ቅዱሳን መላእክት አንዱ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር (፲፪) ዓሥራ ሁለት ቀን በዓሉ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ “ በሰማይም ሰልፍ ሆነ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉት ዘንዶውም ከነሰራዊቱ ተዋጋቸው አልቻላቸውምም ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም…” እኔ ፈጣሪያችሁ ነኝ የሚል ትዕቢትና ትምክሕት ልቡን ሠወረበት ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ጭፍራውን ይዞ ላይመለስ ወደ ጥልቁ ሲወርድ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል የመላእክት አለቃ በመሆን ተሾመ (ራእ፲፪፤፯)፡፡
ለነዌ ልጅ ኢያሱ በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በታላቅ ክብር ሲገለጥ ኢያሱም “ከእኛ ወገን ነህን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ” ባለው ጊዜ እኔስ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ” በማለት አለቅነቱም በዓለመ መላእክት ብቻ ሳይሆን በሕዝበ እስራኤል (እግዚአብሔርን በሚያመልኩ ሰዎች) ላይ ጭምር መሆኑን ተናግሯል፡፡
መጋቤ ብሉይ የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ቅዱስ ሚካኤል እስራኤል ዘሥጋን ከግብፅ የባርነት ኑሮ እግዚአብሔር ነፃ ሲያወጣቸው መና አውርዶ፣ ደመናን ጋርዶ፣ ከዓለት ውኃን አፍልቆ እያበላ እያጠጣ የእግራቸው ጫማ እንኳ ሳያልቅ ሲመራቸው የነበረ መልአክ መሆኑን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሲመሰክር “መርሖሙ መዓልተ በደመና ወኩሎ ሌሊተ በብርሃነ እሳት ወአውፅኦሙ ለሕዝቡ በትፍሥሕት ፈነወ መልአኮ ወአድኀኖሙ እንዘ ሚካኤል የሐውር ቅድመ ትዕይንቶሙ፤ እስራኤልን ቅዱስ ሚካኤል ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን እሳት መራቸው በእስራኤል በጎዳናቸው ፊት ፊት እየሔደ ሕዝቡን በደስታ አወጣቸው መልአኩን ልኮ አወጣቸው፡፡” በማለት የእግዚአብሔርን ነፃ አውጭነት የቅዱስ ሚካኤልን ረዳትነት በዝማሬው ገንጧል(ድጓ ዘቅዱስ ሚካኤል)፡፡
ቅዱስ ሚካኤል ሕዝበ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ወደ ከነዓን በሚመራቸው ጊዜ እግዚብሔር ለሙሴ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ነበር “ በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክን በፊትህ እልካለሁ በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት፡፡ ” በማለት ቅዱስ ሚካኤል እኛን እስራኤል ዘነፍስን ጭምር ከምድር ወደ ሰማይ፣ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከመከራ ወደ ዕረፍት የሚመራን መልአክ መሆኑን እና መንገድ በተባለች ሃይማኖት ስንኖር እግዚአብሔርን እየበደልን የመልአኩን ቃል ባለማድመጥ ካስመረርነው መልአኩ ይቅር እንደማይለን በግልጽ አስጠንቅቋል (ዘፀ፳፫፣፳)፡፡
✝️በዚህ መከራ ለይቶ ኦርቶዶክሳውያን ላይ በበዛበት ዘመን ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለእነ ዱራታዎስ፣ ለእነ አፎሚያ ወዳጅነቱን በመግለጥ ፈጥኖ እንደደረሰላቸው ለእኛም በስደት በመከራ ላሉ ወገኖቻችንም በማያሳፍር ምልጃው ይድረስልን አሜን፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮችን ይቀላቀሉ።
👇ቴሌግራም፡-👇
http://t.me/mkpublicrelation
👇ፌስ ቡክ👇
:-https://www.facebook.com/mahiberekidusan.mkusa/
👇ዩ ቲዩብ፡-👇
http://www.youtube.com/user/EOTCMK
ማኅበረ ቅዱሳን
