ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ፥ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ» (ማቴ. 2፥13)
«ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ፥ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ» (ማቴ. 2፥13)
ክፍል ፪
በመምህር አሰበልኝ
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንደምን ሰነበታችሁ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ለአባቶቻችን የሰጠውን የተስፋ ቃል አጽንቶ ላዳነን ለጠበቀን ለእርሱ ምስጋና ይሁን።
በክፍል ፩ የወርኃ ጽጌ ጽሑፋችን የጽጌን ምንነትና በዘመነ መፀው የመከበሩን ምክንያት አይተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ መንፈሳዊ አስተምህሮውንና ምሥጢሩን እንመለከታለን። በዚህ በወርኃ ጽጌ ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን እመቤታችን ቅድስት ደንግል ማርያም የተወደደ ልጇን ይዛ ከቅዱስ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር የተቀበሉትን ስደትና መከራ በማሰብ ቤተ ክርስቲያን በሠራችው ሥርዐተ ማሕሌት ካህናትና ምእመናን በመሳተፍ የበረከቱ ተሳታፊ ይሆናሉ።
ይህ ወርኃ ጽጌ ወቅት ምድር በጽጌያት (በአበባዎች) የምታጌጥበት እንደ መሆኑ መጠን፣ የእኛም መንፈሳዊ ሕይወት በእመቤታችንና በልጇ ፍቅር፣ በቅዱስ ዮሴፍና በሰሎሜ ተጋድሎ ተደግፈን መዓዛው እንዳማረ አበባ አብበን መንፈሳዊ ፍሬ እንድናፈራ የሚያሳስበንና የሚያስተምረን ልዩ ወቅት ነው። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ስደት በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው ሕፃኑ ከእናቱ ጋር መሰደዱና የእርሱ ቸርነት የሚያስደንቅ ነው።
የሰማይና የምድር ፈጣሪ፣ አእላፍ መላእክት የሚሰግዱለት የክብር ንጉሥ ሕፃን ሆኖ ወደ ግብፅ ተሰደደ። ለምን ተሰደደ?
፩.ትሕትናውን ለማስተማር፦ በኃይልና በሥልጣን ጠላትን ማጥፋት ሲችል እንደ ሕፃን ልጅ በእናቱ እቅፍ ስደትን ተሰዶ በትሕትና አልፎ ለሰው ልጆች አሳየ።
፪.የትንቢቱን ቃል ይፈጽም ዘንድ፦ ነቢዩ ሆሴዕ “ልጄን ከግብፅ ጠራሁት” (ሆሴ. 11፥1) ብሎ ነቢዩ የተናገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ሕፃኑ ከእናቱና ከቅዱሳን ጋር ወደ ግብፅ ተሰደደ።
፫.ስደትን ለመባረክ፦ በዓለም ላይ በስደት፣ በችግርና በመከራ ውስጥ ያሉትን ሁሉ ለማጽናትና የስደት መንገድን በእግሩ ባርኮ ለመቀደስ ፈጣሬ ዓለማት እርሱ ተሰደደ።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕፃኑን ይዛ ከቅዱስ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ወደ ግብፅ በተሰደዱበት ጊዜ የነበረው መከራ በሰው አእምሮ የሚለካ አይደለም። በእግር የተሰደዱት ስደት በበረሃው በቀን ሐሩርና በሌሊቱ ቁር፣ ምንም የሌላቸው ደካሞች መስለው የተጓዙት ለእኛ በረከትና በተጋድሎ እንድንኖር የሚያደርግ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። እመቤታችን ከተወደደ ልጅዋ ጋር ስትሰደድ የሕይወት ፍሬ (ክርስቶስን) አቅፋ፣ ረሃቡንና ጥሙን ችላ በጽናት ነበር፤ ይኸውም ምእመናን በመከራ ጊዜም በሃይማኖት መጽናት እንደሚገባን የሚያመለከት ነው።
ቅዱስ ዮሴፍም የእግዚአብሔር መልአክ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ፡፡” (ማቴ. 2፥13) ያለውን ትእዛዝ ሰምቶ ‘አልችልም’ አላለም። ዕድሜው የገፋ አረጋዊ ቢሆንም የቤተሰቡ ጠባቂ ሆኖ ሌሊት ተነሥቶ ወጣ። እግዚአብሔር አምላክ የሰጠውን ኃላፊነት በታማኝነት መወጣት ምን ማለት እንደሆነ አሳየን።
ሰሎሜም በጉዞው ሁሉ አብራ በመሆን በስደት በመሳተፍ እሜታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ስታግዛት ነበር፤ ሕፃኑንም ተንከባክባለች። ይህም በመከራ ጊዜ አብሮ የመቆም፣ የፍቅርና የእውነተኛ አገልጋይነት ምሳሌ ሆናለች ዛሬም መከራ እና ስደት ከሚደርስባቸው ጋር መቆም እንደሚገባ በዚህም በረከት እንደምናገኝ መገንዘብ ይገባል፡፡
ስለሆነም ከእመቤታችን ከቅድሰት ድንግል ማርያም ስደት የምንማረው በሕይወታችን የሚገጥሙን ፈተናዎች፣ የኑሮ ውጣ ውረዶች፣ ስደትና መከራዎች ጊዜያዊ መሆናቸውን በማሰብ በእመቤታችን ስደት እግዚአብሔር እንደነበረ ሁሉ፣ ከእኛ ጋርም የሚጠብቀን የሚያጸናን እንደሆነ በማሰብ ቅዱስ ዮሴፍ፣ እመቤታችንና ሰሎሜ በችግር ጊዜ አንድ ሆነው መከራን በፍቅር እንዳለፉት ዛሬ በክርስቲያኖች በሚደርሰው መከራና ስደት እኛም እንደ ቅዱሳኑ ስለስሙ ከሚሰደዱት ጋር ኅብረት በማድረግ በክርስቲያናዊ ኅበረታችን ውስጥ አንድነትን በመገንዘብ የሚገባውን ሁሉ በማድረግ በእውነተኛ ፍቅር ይህን የመከራና የሥቃይ ጊዜ ልናሳልፈው ይገባል።
ምክንያቱም እመቤታችን አንድያ ልጇን ይዛ ከቅዱስ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ወደ ግብፅ ቢሰደዱም ስደታቸው ለበረከት ሆኗል፤ የሕፃኑ መሰደድ ዲያብሎስን አሳደደው፣ ጣዖታትን አጠፋቸው፣ ገዳማትን ባረከ “ጉየተ ሕፃን ዘአጕየዮ ለሰይጣን/ለዲያብሎስ” “የሕፃኑ (የኢየሱስ ክርስቶስ) መሰደድ ሰይጣንን ከሰዎች ልቦና አሳደደው” እንዲል የግብፅ ስደት በደስታና በድል እንደተጠናቀቀ እኛም በሃይማኖትና በትዕግሥት ከጸናን የፈተናችን መጨረሻ በክብርና በበረከት የተሞላ ይሆናል። የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! በዚህ በወርኃ ጽጌ ወቅት፣ የእመቤታችንን የስደት መከራ ስናስብ፣ ልባችንን ለበጎ ሥራና ለፍቅር በመክፈት የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ ይልቁንም በክርስትናቸው ሞት፣ መከራ ሥቃይና ስደት እየደረሰባቸው ያሉትን ኦርቶዶክሳውያን በማሰብ የእመቤታችንን ፍቅር በሥራ ልንገልጸው ይገባል።
በዚህ በወርኃ ጽጌ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ምእመናን ህፃናት አበባ በመያዝ በማሕሌት እመቤታችንን በፍቅር ስናመሰግን ኀለፈ ክረምት ብለን ጀምረን እንሆ ተመየጢ ተመየጢ ለማለት በቃን ደራሲው የእመቤታችን ፍቅር አልጠገብ ቢለው
“ኢየኃፍር ቀዊመ ቅድመ ሥዕልኪ ወርኃ ጽጌ ረዳ አመ ኃልቀ
ዘኢየኃልቅ ስብሐተኪ እንዘ እሴብሐኪ ጥቀ”
(አበባ ወቅት ባለቀ ጊዜ የማያልቅ ምስጋናሽን ፈጽሜ እያመሰገንኩሽ ከሥዕልሽ ፊት መቆምን አላፍርም) በማለት ይገልጻል። እኛም ተመየጢ(ተመለሽ) በማለት በኃጢያት ከልቡናችን የራቀው ፍቅሯ እንዲመለስልን ልንማጸን ይገባናል።
አምላካችን እግዚአብሔር በቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ በጻድቁ ቅዱስ ዮሴፍና በቅድስት ሰሎሜ ጸሎትና በረከት ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን፤ ሕዝባችንን ይጠብቅልን፤ በስደትና በችግር ያሉትን ሁሉ በምሕረቱ ይጎብኝልን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር፣
ወለወላዲቱ ድንግል፣
ወለመስቀሉ ክቡር
አሜን!
