መጋቢት 19/2004 ዓ.ም.
ከዓመታት በፊት ፓስተር እንደነበሩ በሚነገርላቸው ግለሰብ ተዘጋጅተው በጀርመን ሀገር ለታተሙት የቅሰጣ መጻሕፍት ምላሽ የሰጠ መጽሐፍ መታተሙ ታወቀ፡፡ ገዳሙ ደምሳሽ በተባሉትና በአሁኑ ወቅት በጀርመን ቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በተሾሙ ግለሰብ ተዘጋጅተው ለታተሙት ሦስት መጻሕፍት ምላሽ የሰጡት መምህር ኅሩይ ኤርምያስ የተባሉ በዚያው በጀርመን የሚኖሩ ሊቅ ሲኾኑ፤ የመጽሐፋቸው ርእስ «መጻሕፍትን መርምሩ በእልቅና ካባ ፓስተር መቅደስ ገባ ?» የሚል እንደኾነ ከቦታው የደረሰን ሪፖርት ያስረዳል፡፡ መጽሐፉ 219 ገጾች ያሉት ሲኾን አዘጋጁ በመጽሐፉ መግቢያ እንደገለጹት መልስ የሰጡባቸው መጻሕፍት “የመናፍቃን ሰፊ የቅሰጣ ማስፈጸሚያ ወጥመዶች አካል፤ በውጭ ሳይኾን በውስጥ ተጠምደው ምእመናንን በገዛ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው አደባባይ የሚያጠምዱ ናቸው ” ብለዋል፡፡ አክለውም መልስ የሰጡባቸው መጻሕፍት «ቤተ ክርስቲያንን ይሳደባሉ፣ ይተቻሉ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያንቋሽሻሉ» ካሉ በኋላ የእሳቸው መልስ የኑፋቄ መጻሕፍቱን ደራሲ ተደራሽ ያደረገ ቢመስልም ዋና «ዓላማው መላው ምእመናን ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁና የተሳሳተ ትምህርት ሰርጎ እንዳይገባ ማንቃትና ማዘጋጀት ነው» ብለዋል፡፡ በመጻሕፍቱ ይዘትና በአዘጋጁ ወቅታዊ አስተምሕሮ በመደናገር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መፍትሔ እንድትሰጣቸው ከአካባቢው አስተዳደር ጀምሮ እስከ ሊቃውንት ጉባኤና ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ አቤት ሲሉ የቆዩት ምእመናን በመምህር ኅሩይ መጽሐፍ መጽናናታቸውንና መደሰታቸውን ከቦታው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
መልስ የተሰጠባቸውን መጻሕፍት አዘጋጅ አስመልክቶ ከአካባቢው ምእመናን በደረሰን አቤቱታ መሠረት፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ምእራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከትን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስንና በቤተ ክርስቲያኗ የሀገረ ጀርመን ሊቀ ካህናት የኾኑትን ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዐዊ ተበጀን በማነጋገር ሰፋ ያለ ዘገባ በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በኅዳር ወር፣ ቅጽ 19፣ ቁጥር 236 እትማችን ሰፋ ያለ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ አንባብያን ጉዳዩን ከስሩ ይረዱት ዘንድ በወቅቱ የታተመውን ዘገባ ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡
– – – – – – – – – –
• በጀርመን አገር በሚገኙ አብያተ ከርስቲያናት የሚፈፀሙ ሃይማኖታዊ ሕፀፆች እና በደሎች ተገቢው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የምእመናን ሕብረት ጠየቀ
በጀርመን አገር በኑፋቄ ትምሕርታቸው የሚታወቁት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ አስተዳዳሪ የሆኑት የ«ቀሲስ» ገዳሙ ደምሳሽ እና ከአንድ መቶ ሥልሳ ሺሕ ዩሮ በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ ለግል ጥቅም ባዋሉ ግለሰብ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ መእመናን ጠየቁ፡፡
በጀርመን አገር የሚገኘው የምእመናን ኅብረት ይህንኑ በማስመልከት ሰሞኑን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ለጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊ እና ለሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ባሰራጨው ደብዳቤ ከቤተ ከርስቲያኒቱ ሥርዐትና ደንብ ውጪ የተፈጸመው በደል ተጣርቶ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡
ኅብረቱ ባሰራጨው ደብዳቤ እንዳመለከተው የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በማገልገል ላይ ያሉት «ቀሲስ» ገዳሙ ከአሁን ቀደም በመናፍቃን የእምነት ድርጅት ውስጥ በሰባኪነት አገልግሎታቸው በተጨማሪ፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጪ ሦስት የኑፋቄ መጻሕፍትን አዘጋጅተው አሰራጭተዋል፡፡ በቅርቡም አራተኛ መጽሐፍ አዘጋጅተው ያሳተሙ ሲሆን ሌሎች ኑፋቄ አዘል ሦስት መጻሕፍት በማዘጋጀት ላይ እንዳሉ ጠቁሟል፡፡
መጻሐፍቶቹ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማ ውጪ የሆኑ መልእክት የሚያስተላልፉ መሆናቸውን የጠቀሰው ይህ ደብዳቤ ከዚህ ውጪ የተለያዩ የኑፋቄ ትምህርቶችን በማስተማር እና በካሴት በማሳተም ምእመናንን እያሳቱ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ባለፈው ዓመት ብቻ በግልጽ የታወቁ አምስት የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ያገለግሉ እና ከእርሳቸው እግር ሥር የማይጠፉ የነበሩ ምእምናን እና የሰበካ ጉባኤው አባላት ወደ ሌላ እምነት ተቋም ሔደው እንዲጠመቁ ማድጋቸውን ጠቅሰው፤ ከአሁን ቀደም ለፃፏቸው መጻሕፍት እና የኑፋቄ ትምህርቶችን ሳያስተካክሉ እና እርማት ሳይሰጡ እንዲሁም የፀፀት ምላሽ ሳይሰጡ በ1997 ዓ.ም የአስተርዩ ማርያም በዓል ዕለት በጀርመን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊ በሆኑት ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርአዊ ተበጀ አማካኝነት «ቀሲስ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰዋል» የሚል ማደናገሪያ መልእክት መተላለፉ እንዳሳዘነው ኅብረቱ በጻፈው ማመልከቻ ጠቅሷል፡፡
እኚሁ ግለሰብ ቀደም ሲል በኅቡዕ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ያለምንም ፍራቻ በግላጭ ስለሚዘሩት ኑፋቄ ጀርመን ሀገር ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በመጠቆም አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም አስተዳደሩ ለጥያቄው መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ነገሩን ወደ ጎን በመተው እና በማለባበስ ላይ መሆኑን ደብዳቤው ጠቅሷል፡፡ ግለሰቡ በተለያዩ አድባራት እየተገፉ ትምህርት እንዲያስተምሩ ከዚህም አልፎ ለሚያደርጉት ተፃራሪ ድርጊት አስተዳደሩ ድጋፍ እየሰጡ እንደሚገኝ በቅሬታ ደብዳቤው ገልጧል፡፡
ይህ ድርጊት በርካታ ምእመናንን ያሳዘነ እና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲርቅ ምክንያት እየሆነ ስለሆነ የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት መፍትሔ እንዲሰጡ የምእመናን ኅብረቱ በአፅንኦት አሳስቧል፡፡
ኅብረቱ ባቀረበው አቤቱታ በሙኒክ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከመቶ ሠላሳ ሺሕ ዩሮ በላይ ገንዘብ አጥፍተው በሊቀ ጳጳሱ የታገዱት ካህን ጉዳይ ተጣርቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንደትወስድ ጠይቀዋል፡፡
«በሃይማኖታችን እና በመላው ምእመናን ላይ የተቃጣውን ከባድ የእምነት ፈተና ለመቋቋም እንድንችል ጉዳዩን በጥልቀት መርምራችሁ ተገቢውን ውሳኔ በአፋጣኝ እንድትሰጡበት በልዑል እግዚአብሔር ስም እንማፀናለን» ሲል የምእመናን ኅብረቱ ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ባሠራጨው የአቤቱታ ደብዳቤ አመልክቷል፡፡
ጉዳዩ የሚመለከታቸው በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርአዊ ተበጀ በአቤቱታው ላይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ «ቀሲሰ» ገዳሙ ከአሁን ቀደም የሌላ እምነት ተከታይ ቢሆኑም ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመመለሳቸው በክህነታቸው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
«ቅዱስ ቤተ ክርስትያን ወደ እርሷ የመጡትን ትቀበላለች፣ አታገልም፡፡ የቀሲስ ገዳሙም ጉዳይ ይኸው ነው፡፡ ሊቃነ ጳጳሳትም አቡነ ዮሴፍ እና አቡነ እንጦንስ በፈቀዱት መሠረት አገልግሎቱን እንዲሰጡ እየተደረገ ነው፡፡» ያሉት ሓላፊው፤ አሳተሙት ስለተባለው የኑፋቄ መጻሕፍት እና ትምህርት በሊቃውንት ጉባኤ ተመርምሮ ውሳኔ እንዲሰጥበት ሒደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ሚያዝያ ጊዮርጊስ የንግስ ዕለት የሰሜን አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ «ቀሲስ» ገዳሙ በዓውደ ምሕረት ላይ ባስተማሩትን ትምህርት በመደሰት «መጋቢ ሐዲስ» የሚል ሹመት መስጠታቸውንም ሓላፊው ተናግረዋል፡፡
ሓላፊው እንዳሉት የቀሲስ ገዳሙን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በአገልግሎት እንዲቀጥሉ የሚቃወሙ በርካታ ምእመናን እንዳሉ ሁሉ የሚደግፏቸውም የዛን ያህል የበዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለያየ አቅጣጫ የሚመጣውን ቅሬታ አጣርቶ ውሳኔ ለመስጠት በሚደረገው ሒደት የቤተ ክርስቲያኒቱ ትክክለኛ አካሔድ በመከተል ውሳኔውን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እና የምእመናን ኅብረቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት በየጠየቀው በሙኒክ ቅዱስ ቤተ ጊዮርጊስ ቤተ ከርስቲያን ገንዘብ ምዝበራ ጉዳይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ «ይህ ጉዳይ በሀገሪቱ ፍ/ቤት በሕግ የተያዘ በመሆኑ ምንም የምለው ነገር የለኝም፤ በተፈፀመው ወንጀል ግን አዝኛለሁ» ብለዋል፡፡ ድርጊቱ እንዴት እና መቼ እንደተፈፀመ እንዲሁም ማን እንደፈፀመው ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ ውሳኔ ሲያገኝ በይፋ እንደሚገለጽም አስረድተዋል፡፡
«በጥምቀት አንድ ነን» በሚል ከአሁን ቀደም ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር ስለፈረሙት ጉዳይ ማስተካከያ ስለመሰጠቱ እና ስለአለመሰጠቱ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ጉዳዩ የቆየ በመሆኑ መነሳት እንደሌለበት ቿቅሰው፣ ሆኖም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክለው መፈራረማቸው ዛሬም ስሕተት ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
«በመፈራረማችን ያጣነውም ያገኘነውም ነገር የለም፡፡ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መሥራች ከመሆናችን አንፃር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር እንጂ ከዛ ውጪ የተደረገ ስምምነት አይደለም» ያሉት ሓላፊው፤ «በዚህ በኩል ከማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አካል ‘ትክክል አላደረክም’ ያለኝ የለም» ብለዋል፡፡
«በመፈራረሜ የፈፀምኩት ስሕተት ባለመኖሩ አልፀፀትም ይቅርታም አልጠይቅም፣ የምፀፀተው ስፈራረም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ ባለመጠየቄ ነው፤ እንዲህ ሰዎችን የሚያሳዝን መሆኑን አላወኩም፡፡ ፈቃድ ብጠይቅ ትልቅ ቁም ነገር ነበረው» ሲሉ ሓላፊው ተናግረዋል፡፡
የመገናኛ አውታሮች በሰፉበት፣ ዘመኑን ዋጁ በሚባልበት በዚህ ወቅት ከዓለም ተገልለን ብቻችንን ከመሆን እንዲህ ያለ ኅብረት መፍጠር ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸውም ሓላፊው አስረድተዋል፡፡
በምእመናኑ ኅብረት ጥያቄ እና በሊቀ ካህናት ዶ/ር መርአዊ ተበጀ ምላሽ ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ጥያቄ የቀረበላቸው የሰሜን ምእራብ አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ በጀርመን የሚነሱ የምእመናን ጥያቄዎችን ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከቀሲስ ገዳሙ ጉዳይ የጠራ መረጃ ስላልተገኘ እስካሁን በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት እርምጃ ለመውሰድ ያስቸገረ መሆኑን ጠቅሰው ጉዳዮቹ ተጣርተው በቅርቡ ውሳኔ እንደሚሰጥባቸው ተናግረዋል፡፡
የተፃፉት የኑፋቄ መጻሕፍት ላይ ወደ ፮ የሚሆኑ ነጥቦችን አውጥተው ማብራሪያ እንዲሰጡ በጠየቋቸው ጊዜ «ቀሲሱ» ‘አማርኛ ችግር ስላለብኝ ነው’ ማለታቸውን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው መጻሕፍቶቹ በሊቃውንት ጉባኤ እና በቅዱስ ሲኖዶስ በተቋቋመው የሃይማኖት ጉዳይ አጣሪ ኮሚቴ ተመርምረው ስሕተት እንዳለባቸው ከታመነ ቤተ ክርስቲያኒቱ እርምጃ እንደምትወስድ ተናግረዋል፡፡ ወደ ጀርመን ተመልሰው ከሌሎች ካህናት ጋር ስለ ጉዳዩ በመወያየት ተጨማሪ የማጣራት ሥራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡
የኑፋቄ ትምህርት ለሚያስተምሩ ግለሰብ እንዴት መጋቢ ሐዲስ የሚል ማዕረግ ሰጡ) የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፤ «ቀደም ሲል በሌላ እምነት እስከ ፓስትርነት ደረጃ የደረሰ ማዕረግ እንደነበረው ባለማወቄ እና በትምህርቱም ምእመናንን ጥሩ እውቀት ማስጨበጡን በመገንዘብ ይህንኑ ማዕረግ በቃል ሰጥቼዋለሁ፡፡ በጽሑፍ ያረጋገጥኩበት እና እውቅና የሰጠሁበት ሁኔታ ግን የለም» ብለዋል፡፡ ያ ማዕረግ የቤተ ክርስቲያኒቱ እውቅና እንደሌለው፣ ባለማወቅ በቃል የተፈፀመ ስሕተት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የተፃፈው መጽሐፍ እንግሊዝ ሀገር ለሚገኙ ሊቃውንት ሰጥተው ስሕተቱ እየተነቀሰ እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑን ብፁዕነታቸው ጠቅሰው፤ ከአሁን ቀደም ‘አቡነ ዮሴፍ ፈቅደው አገልግሎት እንዲሰጥ አደረጉ’ የተባለውን እና ማን አለቃ አድርጎ እንደሾማቸው በማጣራት ወደ ጀርመን ተመልሰው ከካህናቱ ጋር የመወያየት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በሙኒክ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ስለተፈፀመው ምዝበራ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ከ19 ዓመት በላይ በዛው ቤተ ክርስቲያን በሓላፊነት ሲያገለግሉ በነበሩ ቄስ መስፍን ድርጊቱ መፈፀሙን ጠቅሰው፤ ጉዳዩ በሀገሪቱ ፍ/ቤት ለመከሰስ በአቃቢ ሕግ እየተመረመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እዛ ያሉት ሰበካ ጉባኤ እና ምእመናን ባደረጉት የኦዲት ምርመራ በሰነድ ብቻ 166 ሺሕ ዩሮ መጉደሉን እንዳረጋገጡ ጠቅሰው፤ ከሰነድ ውጪ ያለ ደረሰኝ ከምእመናን የገባ በርካታ ገንዘብም ይጎድላል የሚል እምነት መኖሩን አስረድተዋል፡፡
የገንዘብ አሰባሰብና አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ብፁዕነታቸው ቿቅሰው፤ ይህን ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ግለሰቡ ለፈፀሙት ተግባር ቤተ ክርስቲያኒቱ የራሱን ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ለመውሰድ እንድትችል አህጉረ ስብከቱ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በጥምቀት አንድ ስለመሆኗ ስለተፈረመው ሰነድ ጉዳይ በሰጡት ቃል ፍርርሙ እርሳቸው ወደዛ ሀገር ከመሔዳቸው 2 ዓመት ቀድሞ የተፈፀመ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፍርርሙ ለአንድ ግለሰብ ለጥቅም ሲባል የተፈፀመ እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ እውቅና የሰጠችው አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ከፊርማ ያለፈ በተግባር የተፈፀመ ምንም ዓይነት ነገር እንደሌለ ያመለከቱት ብፁዕነታቸው፤ ጉዳዩን ከምእምናን በደረሳቸው ጥቆማ መሠረት ለቅዱስነታቸው ጭምር ማሳወቃቸውን አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ የምእመናን ኅብረትም ሆነ ሌሎች የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወዳጆች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ተቀብሎና መርምሮ ተገቢውን እርማት ለመስጠት ጥረቱ እንደሚቀጥል ብፁዕነታቸው ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ የደቡብ፣ ደቡብ ምእራብ እና ደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ሐምሌ 2 ቀን 2003 ዓ.ም «ለሚመለከተው ሁሉ» በሚል በጻፉት ደብዳቤ «ቀሲስ ገዳሙ ደምሳሽ በመባል የሚጠሩት ግለሰብ በፍራንክፈርት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ክብረ በዓል ላይ ታቦተ ሕጉ በቆመበትና ማኅበረ ምእመናን በተሰበሰቡበት ከስሕተቴ ተመልሻለሁ ሀገር ቤት ሔጄ ንስሐ ገብቻለሁ በማለት ለሕዝቡ በአስታወቁበት ወቅት ከስሕተት መመለስዋና ንስሐ መግባትዎ መልካም ነው ሆኖም ግን ቤተ ክርስቲያን መጠቀም የሚችሉት እንደማንኛውም ማኅበረ ምእመናን ነው ከማለት በስተቀር በቤተ ክርስቲያን ክህነት አገልግሎት ተመድበው እንዲሠሩ በቃልም ሆነ በጽሐፍ ያስተላለፍኩት ምንም ዓይት ትዕዛዝ የሌለ መሆኑን እገልፃለሁኝ» ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት እንዳልነው አሁንም ጉዳዩን እየተከታተልን የምንዘግብ መኾኑን እንገልጻለን፡፡
ምንጭ፡- /ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ 19ኛ ዓመት ቁ.236 ኅዳር 2004 ዓ.ም./