የቅዱስ ሲኖዶስ የአራት ቀናት ውሎና ውሳኔዎች

ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስና

በዲ/ን ዩሴፍ ይኲኖ አምላክ


  • አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለአስተዳደር እንዲመች በአራት አህጉረ ስብከት ተከፈለ፡፡

 

ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በተካሔደው ሥርዓተ ጸሎት የተከፈተው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባሳለፍናቸው አራት ቀናት በስድስት ጠቃሚና ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

 

በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግኑኝነት ሓላፊ የሆኑት አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ዛሬ ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኖች በሰጡት መግለጫ ቅዱስ ሲኖዶስ፡-

  • በሕገ ቤተ ክርስቲያን

  • በቤቶችና ሕንጻ አስተዳደር

  • በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጉዳይ

  • በጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደራዊ ጉዳዮች

  • በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ስለሚወከሉ አባቶች

  • የቤተ ክርስቲያንን የውጭ ግኑኝነት

 

በተመለከተ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መወያየቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት፡-

  1. ቤተ ክርስቲያን የምትመራበት ቃለ ዓዋዲ ወቅቱን ባገናዘበ ሁኔታ ለአስተዳደርና ለአሠራር አመቺ ይሆን ዘንድ ማሻሻያ እንዲደረግበት፡፡

  2. በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር የሚገኙ ሕንፃዎች በአግባቡ እንዲያዙ፣ ልዩ ልዩ ጉዳት የደረሰባቸው እድሳት እንዲደረግላቸው፣ ባሉት ባዶ ቦታዎች ላይ ተጨማሪ ቤቶች እንዲሠሩና በመንግሥት ተወርሰው ያልተመለሱትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕንፃዎች የማስመለሱ ጥረት እንዲቀጥል፡፡

  3. በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚታየውን ነባራዊ ሁኔታ ለአስተዳደርና ለአሠራር ምቹ ባለመሆኑ ምክንያት አዲስ አበባ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምእራብ፣ ምስራቅ ተብሎ ለአራት አህጉረ ስብከቶች እንድትከፈል ውሳኔ ተላልፏል፡፡

  4. የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ምቹና ቀልጣፋ እንዲሆን በባለሙያ ጥናት ተካሂዶ ለግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ፡፡

  5. የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 117ኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ ሳልሳዊ ሞት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱ 118ኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ በተዘጋጀችበት በአሁኑ ጊዜ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚወክሉ ጳጳሳት እንዲገኙ በተላለፈው ጥሪ መሠረት አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው እንዲገኙ ተወስኗል፡፡

  6. በቤተ ክርስቲያናችን የውጭ ግንኙነት ዙሪያ ሰፊ ሥራ ለመሥራትና ስብከተ ወንጌልን አጠናክራ ለመቀጠል ይቻላት ዘንድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለመላው ዓለም ለማዳረስ እንዲቻል ወርኀዊ መጽሔት እንዲዘጋጅ ተወስኗል በማለት የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ገልጸዋል፡፡

 

የህዝብ ግንኙነት ሓላፊው ከዚሁ ጋር በማያያዝ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በቀጣይነት ስለሚወያይባቸው አጀንዳዎች ሲገልጹ፤

  • ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ዓመታዊ በጀት

  • የሦስት ዓመት ሥልታዊ እቅድ

  • ስለ ሙስናና ተያያዥ ችግሮች

  • ስለ ሀብትና ንብረት አጠባበቅ

  • ስለ አብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት

  • ስለ ፓትርያርክ ምርጫና የምርጫውን ሕግ ስለመወሰን  እንደሚነጋገር አስታውቀዋል፡፡

 

የህዝብ ግንኙነት ሓላፊው አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ይህንን መግለጫ ለመስጠት ያስፈለገበት ምክንያት ሲገልጹም አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠላቶች የተለያዩ አሉባልታዎችን በመንዛት ምእመናንን በማደነጋገር ላይ ስለሚገኙ ምእመናን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚተላለፈውን ውሳኔና መልእክት ብቻ እንዲከታተሉና እውነታውን እንዲረዱ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  በቀጣይነትም ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች ተከታትለው ለምእመናን ይፋ እንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡

 

አራተኛ ቀኑን የያዘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡