2ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥናት መጽሔት ተመረቀ

ጥቅምት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

metshate 3በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል የተዘጋጀው 2ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥናት መጽሔት/Journal/ ጥቅምት 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ተመረቀ፡፡ በጥናት መጽሔቱ የምረቃ መርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ዑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል አማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ፤ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የሰሜን ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የጥናት መጽሔቱን በማዘጋጀት የተሳተፉ ምሁራን፤ ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምሁራን የተገኙ ሲሆን በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቡራኬ በጸሎት ተከፍቷል፡፡

 

የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ዲያቆን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያም የቀረበ ሲሆን በመልእክታቸውም “ማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል ሲያቋቁም ቤተ ክርስቲያን ያለፈችበትን ፈርጀ ብዙ ተግዳሮቶች መንፈሳዊና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አጥንቶ ትክክለኛ መፍትሔ ለመጠቆም፤ ርቀው ያሉትን  የቤተ ክርስቲያን ምሁራን ለማቅረብ፤ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ቀርበው በሙያቸው እንዲያገለግሉ ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ቤተ ክርስቲያን ቀመስ የሆነው የሀገሪቱ ሁለንተናዊ ሀብት በጥናትና ምርምር መሣሪያነት በመግለጽ፤ በመተንተንና በማሳተም ለዓለም ህዝብ ለማድረስ፤ በውጤቱም ቤተ ክርስቲያን የቁሳዊና መንፈሳዊ ግኝቶች ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል ነው፡፡” በማለት መልእክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የዕለቱን  ጉባኤ በንግግር እንዲከፍቱ በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል አማካሪ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ኀላፊ የሆኑትን ዶክተር ውዱ ጣፈጠን ጋብዘዋል፡፡

 

ዶክተር ውዱ ጣፈጠ ባደረጉት ንግግር “ቤተ ክርስቲያናችን የፍልስፍና ፤ የሥነ ጽሁፍ፤ የሥነ ሕንፃ፤ የሥነ ሥዕል፤ የሥነ ሰብዕ፤ የሥነ ማኅበረሰብ፤ የአስተዳደርና የሥነ ትምህርት . . . ወዘተ መድብለ ጸጋ ያላት ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ሀብት በአግባቡ እንድትጠቀምበት መመርመር፤ ለቀጣዩ ትውልድ የእውቀት ምንጭ በሚሆን መልኩ ማደራጀትና ማስተባበር የሚጠበቅ ሥራ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን ፈርጀ ሰፊ ሀብት ለልማት ለማዋል ወቅታዊና ነባራዊ ችግሮችን በጥናትና ምርምር በታገዘ መልኩ ለመፍታት መንቀሳቀሱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡” በማለት የገለጹ ሲሆን የጥናት መጽሔቱ ለኅትመት እንዲበቃ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱትን አካላት አመስግነዋል፡፡

 

መጽሔቱ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ዑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል አማካሪ ቦርድ ሰብሳቢmetshate አማካይነት ተባርኮ የተመረቀ ሲሆን በሰጡት ቃለ ምእዳን “የማር፣ የአትክልት፣ የገብስ ጭማቂ መጠጣት የተለመደ ነው፡፡ ትልቁ ጭማቂ ግን ከሰው አእምሮ የፈለቀውን መጠጣት ነው፡፡ ያውም ከሊቃውንቱ የመነጨውን፡፡ ታሪካችን እንዲጠበቅ ያደርጋልና፡፡ ይህ የጥናት መጽሔት ብዙ ምርምር የተደረገበትና ለቤተ ክርስቲያን፣ ለአገር እድገት፣ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት፣ ባሕል፣ ወግና እምነት ተጠብቆ እንዲሸጋገር የሚያደርግ፤ ለትውልዱ ለማስተላለፍ የሚጠቅም ነው” ብለዋል፡፡

 

የጥናት መጽሔቱን ለማዘጋጀት በተደረገው ጥረት ከፍተኛ ትብብር ሲያደርጉ የነበሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን እንዲሁም ተሳታፊዎች በጥናት መጽሔቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ሎሬት ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ የጥናት መጽሔቱ ስለሚኖረው ጠቀሜታ ሲገልጹ “ጥናትና ምርምር ለአንድ ሀገር መሠረት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ የእውቀት ክምችቶች አሉ፡፡ ከምሁራን ብዙ ጠይበቃል፡፡ የጥናት መጽሔቱም ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገራችን ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው፡፡ በእኛ በኩል ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁዎች ነን” በማለት ተናግረዋል፡፡

 

በጥናት መጽሔቱ ላይ በመሳተፍ ጊዜያቸውን፣ እውቀታቸውን በማካፈልና በማዘጋጀት ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው ወንድሞችና እኅቶች እንዲሁም ድርጅቶች ከብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ዑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል የአማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ፤ እንዲሁም ከብፁዕ አቡነ ኤልያስ የሰሜን ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እጅ ማእከሉ ያዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

 

በዚሁ ወቅት ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የሰሜን ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ ምእዳን “ይህች የጥናት መጽሔት ገና ካፊያ ናት፡፡  ኢትዮጵያ ያላት ሀብት እንደ ውቅያኖስ ተቀድቶ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሳንባ ነው የምትተነፍሰው፡፡ መኩሪያዋም መመኪያዋም ቤተ ክርስቲያን ናት ገና ብዙ ይቀራል ይቀጥላል” ብለዋል፡፡

 

metshate 2በመርሐ ግብሩ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን የመዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን የጥናትና ምርምር ማእከሉ ዋና ዳይሬክተር ዮሐንስ አድገ በጥናቱ ላይ የተሳተፉትን፤ የማማከር ሥራ ያከናወኑትን፤ መጽሔቱን በመገምገም ሙያዊ ድጋፋቸውን በመስጠት ለተባበሩት ምሁራን ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

 

በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ዑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል የአማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ ቡራኬና ጸሎት የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡