ኩኑ ቅዱሳን እስመ ቅዱስ አነ” ዘሌ.19፡2

 የካቲት 12ቀን 2007 ዓ.ም.

 ፲ቱ ማዕረጋት

ቅዱሳን ማለት የተቀደሱ፣ የከበሩ፣ የተመሰገኑ፣ የተለዩ፣ የተመረጡ፣ ንጹሐንየሆኑ፣ የጠሩ….. ወዘተ ማለት ነው፡፡ ቅዱሳን በዚህ ስም የሚጠሩበት ከሰው ወይም ከምድራዊ ባለሥልጣን የተቸሩት አይደለም፡፡ በሃይማኖት ጸንተው በምግባር ጐልምሰው የሥጋ ምኞታቸውን ጥለው አፍርሰው ሲገኙ የቅድስና ባለቤት ቅዱስ እግዚአብሔር እነሱን /ቅዱሳንን/ መሣሪያ አድርጐ ኃይሉንና ሥልጣኑን ቢገልጽባቸው ማኅደረ እግዚአብሔር መሆናቸው ይገለጻል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡

እሱ እግዚአብሐር ቅዱስ ተብሏልና የጌትነቱ መገለጫ የሆኑ ሁሉ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ ጻድቃን እንደመላእክት ውሉደ እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡ /ኢዮ.1፡6/፣ ሮሜ.8፡14/ ቅዱሳን ጻድቃን በግብር መላእክትን መስለው ሆነው የፈጣሪአቸውን ፈቃድ ፈጽመው በመገኘታቸው ከዚህ ዓለም በመለየታቸው ቅዱሳን ሲባሉ የፈጣሪአቸውን ሕያው መንግሥት ወራሾች ናቸውና ውሉደ እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡ በሌላም ቃል ውሉደ ብርሃን ይባላሉ፡፡ /ሉቃ.16፡8/ በዓለማቸው ይራቀቃሉና ይህን ዓለም ይጠሉታል፡፡ ውሉደ ሕይወት ይባላሉ ሞትንና የሞት ከተማ ይህን ዓለም ይንቃሉና በክብር ተነሥተው ዳግመኛ ሲሞቱ የማይገባቸው ስለሆነ /ሉቃ.10፡30/ ውሉደ ጥምቀት ተብለዋል ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትናን ተጐናጽፈዋልና፡፡ ውሉደ መንግሥትም ተብለዋል የመንግሥተ ሰማያት ባለቤቶች ናቸውና፡፡ በጸጋ እግዚአብሔር የበለጸጉ በመሆናቸው የእግዚአብሔር አዕይንተ እግዚአብሔር ተብለዋል /መዝ.33፡15/

 

የፈጣሪአቸው ፈቃድ በተግባራቸው ስለሚታይ የእግዚአብሔር አዝነ ፈቃድ ወደ ጻድቃን ነው፡፡ ልመናቸው ጾማቸው እንዲሁም ምጽዋታቸው ሁሉ የተወደደ መሥዋዕት ነው፡፡ ቅዱሳን በዓላማቸው ጾምን ግብዣ /ድግስ/፣ ለቅሶን ዘፈን፣ ደስታን ሐዘን አድርገው በመኖራቸው ይህ ተለዋዋጭ ዓለም በየጊዜው የሚአቀርብላቸው መርዶ በእነሱ ዘንድ ዋጋ የለውም ወይም ዋጋ አይሰጡትም፡፡ ዓለምም ለእነሱ የሚያቀርበው ዓለማዊ የምኞት ስጦታ እንደ ኢምንት የተቆጠረ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ገጸ መዓቱ ወደ ዓለማውያን ሰነፎች እንደሆነ ገጸ ምሕረቱ ወደ ቅዱሳን ነው፡፡ ስለዚህ አማላጅነታቸው ጸሎታቸው በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ “አፍቅርዎ ለእግዚአብሔር ኲልክሙ ጻድቃኑ” ቅዱሳን እውነትን ይዛችሁ ትሕትናን ተላብሳችሁ እግዚአብሔርን ውደዱት “እስመ ጻድቅ የሐስስ እግዚአብሔር” እግዚአብሔር እውነትን ትሕትናን ይወዳልና፡፡ /መዝ.30፡23/ የቅዱሳን ፍሬ ትሕትና ነው፡፡ በዓይነ ሕሊናቸው ፈጣሪአቸውን በዓይነ ሥጋቸው የእነሱን ምንነት እንዲሁም የዓለምን ከንቱነት ይመለከታሉ፡፡

 

ፍሬ የያዘ ተክል ሁሉ ቁልቁል የተደፋ ነው፤ ትሕትናን ያስተምራል፣ የጻድቃን ምሳሌ ነው፡፡ በፈሪሃ እግዚአብሔር ልቡ የተሰበረ እሱነቱን /ምንነቱን/ የመረመረ ሰው በዓይነ ሕሊናው የፈጣሪውን ቸርነት በዓይነ ሥጋው የራሱን ውድቀት ይመለከታል፡፡ ይህ አመለካከት ለጸጋ እግዚአብሔርና ለፍሬ ክብር ያደርሱታል፡፡ በመቅረዝ ላይ ያለች መብራት መሰወር እንዳይቻላት የመቅረዙ ከፍታ የግድ እንደሚገልጻት በተራራ ላይ ያለች ቤትም በእይታ እንደማትሰወር የተራራው ከፍታ እንደሚገልጻት በጥበበ እግዚአብሔር ከብረው በጸጋ እግዚአብሔር ተውበው የሚኖሩ ቅዱሳን ጻድቃንም ደረጃ በደረጃ ማዕረጋትን አልፈው ከመለኮት ባሕርይ ተካፍለው የተአምራት መገለጫ ተካፍለው የተአምራት መገለጫ ይሆናሉ፡፡

 

“መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኑ” /መዝ.67፡35/ “እግዚአብሔር በቅዱሳኑ በወዳጆቹ አድሮ የሚሠራው ሥራ ድንቅ ነውን፡፡ /2ኛጴጥ.1፡3/ ቅዱሳን የጸጋ ተዋሕዶ ተዋሕደው ሲገኙ ሙት ሲሆኑ ሙታንን ማስነሳት እውር ሲሆነ እውርን ማብራት፣ በዓለም ላይ ድንቅ ሥራቸው ይሆናል፡፡ የጸጋና የክብር ተሸላሚዎች ሆነዋልና በዓለም ላይ ሳሉ የሚመጣባቸውን ፈተና ሁሉ ከምንም ባለመቁጠር ተቋቁመው የጸጋ መቅረዝ ተቋሞች ይሆናሉ፡፡ በዚህም በአላሰለሰው ሕይወታቸው የአንበሳ አፍ ዘጉ /ዳን.7፡1-28/ ውኃውን ወደ ኋላው መለሱ /ዘጸ.14፡22/ ሰማይን አዘዙ /1ኛ ነገ.17፡1፣ ያዕ.5፡17/ ነበለባለ እዥሰት አበረዱ /ዳን.3፡1-13/ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ ወዳጅ እግዚአብሔር ከዘመድ ባዕድ ከሀገር የሚኖሩትን በረድኤት ይቀበላል፣ ሥጋዊ ሀገረ ተድላን ጥለው ሓላፊ ጠፊ ምድራዊ ምቾታቸውን ንቀው ጸጋውን የሚጠባበቁትን ሁሉ አብሮአቸው ይኖራል፡፡ ትዕግስትን የጥዋት ቁርስ የቀን ምሳ የማታ እራት አድርገው የሚመገቡትን ሁሉ ቤተ መቅደስ አድርጓቸው ይገኛል፡፡

 

 

ቅዱሳን በዚህ ዓለም ይጠበቡበታል፣ ወጥተው ወርደው እነሱነታቸውን ከስስት ኃጢአት ጠብቀው ለወዲያኛው ዓለም ደግሞ በትዕግሥት ደጅ ይጠኑበታል፡፡ “አሪሃ እግዚአብሔር ትፍስህተ ልብ ውእቱ ወይሁብ ሐሴተ ወያስተፌስህ ወያነውሀ መዋዕለ ሕይወት፤ እግዚአብሔርን መፍራት የልብ ደስታ ነው፡፡ ፍጹም የሥጋና የነፍስን ደስታ ይሰጣል በሕይወትም ያኖራል፡፡” “ለፈሪሃ እግዚአብሔር ይሴኒ ድሐሪቱ ወይትባረክ አመ እለተ ሞቱ እግዚአብሐርን የሢፈራ ሰው ፍጻሜው ያምርለታል እንደ ኢዮብ ከደዌው ተፈውሶ ልጅ ልጅ አይቶ ይሞታል /ኢዮብ.31፡16/ ይህ ሁሉ በረከት የቅዱሳን የሁልጊዜ ፍሬ ነው፡፡

 

ቅዱሳን ሁል ጊዜ የሚሠሩት ሰማያዊ ድርብ ድርብርብ /እንደ ሐመረ ኖኅ/ በጸጋ ላይ ጸጋ እየተጨመረላቸው ወደ 10ሩ መእረጋት ይወጣሉ፡፡ በያዙት ቀን መንገድም ኢዮባዊ ትዕግስት አብርሃማዊ ሂሩት ይስሐቃዊ ፈቃደኛነት ያዕቆባዊ ቅን አገልግሎት ጠሴፋዊ ሀዳጌ በቀልነት ሙሴአዊ ለወገን ተቆርቋሪነት እየጨመሩ በመኖራቸው ሳያውቁት የፈጣሪአቸውን ኃይል የጌትነቱ የመለኮትነቱን ድንቅ ሥራ መገለጫዎች ይሆናሉ፡፡

 

ማዕረጋቸውን ከዚህ ይናገሩታል፡-

 

የንጽሐ ሥጋ ማዕረጋት 3 ናቸ ው እነሱም፡-

1. ጽማዌ
2. ልባዌ
3. ጣዕመ ዝማሬ ይባላሉ፡፡

 

የንጽሐ ነፍስ ማዕረጋት 4 ናቸው

1. አንብዕ
2. ኲነኔ
3. ፍቅር
4. ሁለት ናቸው፡፡

 

የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት ናቸው እነሱም
1. ንጻሬ መላእክት
2. ተሰጥሞ
3. ከዊነ እሳት ናቸው፡፡

የንጽሐ ሥጋ ማዕረጋት

1. ማዕረገ ጽማዌ፡- ይህ ማዕረግ የመጀመሪያው ነውና ማስተዋል ውስጣዊ ትዕግስትን ውስጣዊ ትህትና ውስጣዊ የራስ ሚዛንን ይዞ ማሰላሰል…… ወዘተ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ እግዚአብሔርን ብቻ መዘከር ይችሉ ዘንድ የዚህን ዓለም ውጣ ውረድ ከማውራት ይከለከላሉ፡፡ በዚህ ማዕረግ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ያያሉ፡፡ ነገር ግን ለምን እንደሚወጡና እንደሚወርዱ አያውቁም፡፡ ዮሐንስ ሐጺር የሰፋውን ስፌት ገበያ ላይ ለመሸጥ ተቀምጦ እያለ እርሱ ግን በተመስጦ እነ ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን እንዲሁም ሌሎችን መላእክት በየማዕረጋቸው እያየ ሲያደንቅ ስፌቱን የሚገዛ ሰው ቁሞ እንቅቡ ዋጋው ስንት ነው ብሎ ሲጠይቀው እርሱ የሚያየውን የሚያይ መስሎት “ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ አኮ ገብርኤል ሚካኤል ይበልጣል ወይስ ገብርኤል” ብሎ በአንክሮ ጠየቀው፡፡ ይህን ሲለው ሰውየው ይሄስ እብድ ነው ብሎ ትቶት ሄዷል፡፡

 

2. ማዕረገ ልባዌ፡– ደግሞ ማስተዋል ልብ ማድረግ አሰሙኝ እንጂ ስሙኝ አለማለት ልማር እንጂ ላስተምር አለማለት የተነገረው ትንቢትና ተግጻጽ ምዕዳን ሁሉ የራሱ እንደሆኑ መገመት መመርመር ዓይነ ሥጋን ከመጽሐፍ ከስነ ፍጥረት ዓይነ ነፍስን ከምስጢር….. ወዘተ ማዋል ነው፡፡ ወይም የእግዚአብሔርን ቸርነት ማድነቅ ስለሰው ያደረገውን ውለታ ማሰላሰል ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከሰው መወለዱን በገዳም መጾሙን መገረፉን ሥጋውን መቁረሱን ደሙን ማፍሰሱን መሰቀሉን መሞቱን መቀበር መነሳቱን እያሰቡ ልብን በፍቅረ እግዚአበሔር መሰበር አንደበትን በመንፈሳዊ ሕይወት መስበር ዓላማን በገጸ መስቀል/ትዕግሥት/ ማስተካከል የመሳሰሉት ናቸው፡፡

 

3. ማዕረገ ጣዕመ ዝማሬ፡- ከዚህ ደረጃ ሲደርስ አንደበትን ከንባብ ልቡናን ከምስጢር ማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱሳን ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ አንደበታቸው ምንም ዝም ቢል በልባቸው ውስጥ ዝም አይሉም፡፡ ከአፍ እስትንፋስ ከአፋፍ ላይ ነፋስ እንደማይለይ ሁሉ ከአንደበታቸው ትዕግስት ከእጃዋው ምጽዋት ከልቡናቸው ትሕትና ከሰውነታቸው ንጽሕና አይለይም፡፡

 

4. የሚጸልዩትና የሚይነቡት ምስጢሩ እየገባቸው ስለሚያደርጉት አይሰለቻቸውም፡፡ ከዚህ ማዕረግ የደረሰ አንደ ባሕታዊ ለብዙ ዘመናት አቡነ ዘበሰማያት /አባታችን ሆይ/ እያለ ብቻ ሲኖር መልአክ መጥቶ ይትቀደስ ስምከ በል እንጁ ቢለው ኧረ ጌታዬ እኔስ አቡነ የሚለው ኃይለ ቃል ምስጢሩና ጣዕሙ በአፌ እንደ ጨሙ እየሟሟ አልጠገበኝ ብሏል እንዴት አድርጌ ወደፊት ልሂድ ብሎታል፡፡

 

የንጽሐ ነፍስ ማዕረጋት

 

1. ማዕረገ አንብዕ፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ቅዱሳን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ያደረገውን ፍቅር እስከ ሞትና መቃብር የተጓዘውን የመከራ ጉዞ እያሰቡ በአንጻሩም ምረረ ገሃነመ እሳትን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን እያሰላሰሉ ውሉደ አዳም ይህን ሁሉ መከራ ባለ መገንዘብ ወደ ሰፊው የፈቃደ ሥጋ ሲጓዝ በማየታቸው ሲአለቅሱ ይታያል፡፡ ያለምንም መሰቀቅ ሲአለቅሱ እንባቸው እንደ ምንጭ ይፈሳል፡፡ እንደ ሰን ውኃ ይወርዳል ይኸውም ለዚህ ዓለም ብለው የሚአለቅሱት ልቅሶ ፊትን ያንጣጣል ዓይንን ይመልጣል የቅዱሳን ልቅሶ ግን ፊትን ያበራል ኃጢአትን ያስወግዳል እርጥብ እንጨት ከእሳት ጋር በተያያዘ ጊዜ እንጨቱ ከነበልባለ እሳት ሲዋሐድ እንጨቱ እርጥብነቱን ትቶ ውኃውን በአረፋ መልክ እያስወገደ ይነዳል፡፡ ቅዱሳንም በግብር/በሥራ/ ከመለኮት ጋር ሲዋሐዱ የዚህ ዓለም ምስቅልቅል ሥራ በሰማያዊ የረጋ ሕይወት ተለውጦ አሠራራቸው አካሄዳቸው ፍጹም ሕይወታቸው መልአካዊ ይሆናል፡፡

 

2. ማዕረገ ኲነኔ፡- ከዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ ሥጋዊ ፈቃድ ሁሉ ለነፍስ ፈቃድ ይገዛል ነፍስ በሥጋ ባሕርያት ላይ ትሰለጥናለች ምድራዊ /ሥጋዊ/ ምኞት ሁሉ ይጠፋና መንፈሳዊ /ነፍሳዊ/ ተግባር ሁሉ ቦታውን ይወርሳል ያለምንም ማወላወል መንፈሳዊ ተግባር ሁሉ ይከናወናል፡፡

3. ማዕረገ ፍቅር፡– ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ውሉደ እግዚአብሔር ቅዱሳን እንደ ፈጣሪአቸው ሁሉን አስተካክለው በመውደድ ይመሳሰላሉ አማኒ መናፍቅ ኃጥእ ጻድቅ ዘመድ ባእድ ታላቅ ታናሽ መሃይም መምህር ሳይሉ አስተካክለው በመውደድ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

4. ማዕረገ ሁለት፡- ቅዱሳን ከዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ ባሉበት ሆነው ሁሉን ማየት መረዳት ይችላሉ፡፡ ጠፈር ደፈር ሳይከለክላቸው ርቀት ሳያግዳቸው ሁሉን በሁሉ ይመለከታሉ፡፡

 

የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት

1. ንጻሬ መላእክት
2. ተሰጥሞ
3. ከዊነ እሳት ናቸው፡፡

 

 ማዕረገ ንጻሬ መላእክት፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ የመላእክት መውጣት መውረድ ማየት ተልእኮአቸውን ያለምንም አስተርጓሚ መረዳት ማነጋገርና ማማከር የመሳሰሉትን መፈጸም፤ ለምሳሌ እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ መልአኩን 10 ዓመት ማቆም ነው፡፡
 ማዕረገ ተሰጥሞ፡– ከዚህ ማዕረግ ሲደረስ በባህረ ብርሃን መዋኘት ባሉበት ሆኖ ወደ ላይም ወደታችም መመልከት መቻል….. ወዘተ ናቸው፡፡
 ማዕረገ ከዊነ እሳት /ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ/፡- የፈጣሪ ቤተ መቅደስ ሆኖ ጸጋ በተዋሕዶ ከመላእክት ጋር ሆኖ ረቆ ማመስገን ያሉበትን ሥጋ በብቻው ማየት በአካለ ነፍስ ሰማየ ሰማያትን መጐብኘት ገነት ውስጥ መግባት ናቸው፡፡

 

እነዚህም የቅዱሳን ማዕረጋት 10 ናቸው፡፡ /2ኛ ጴጥ.1፡4-10፣ ዮሐ.1፡40/ የአስሩ ማዕረጋት ምሳሌዎች የአስሩ ቃላት፡፡ /ዘጸ.20፡3-12፣ ዮሐ.13፡17/ በመጨረሻም ቅዱሳን የቅዱስ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች ናቸው ኑሮአቸውም ቅዱስ ነው፡፡

      የቅዱሳን በረከታቸው አይለየን፡፡ አሜን፡፡

• ምንጭ፡- ዝክረ ቅዱሳን ኅዳር ፮ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.

 

የነነዌ ሰዎች የንስሐ ምስክሮች

 

ጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም.

በዲ/ን በረከት አዝመራው

የነነዌ ጾም ከሰባቱ የቤተ ክርስቲያን አጽዋማት አንዱና የዐቢይ ጾም ማዘጋጃ ደወል ነው፡፡ ይህ የነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ በቤተ ክርስቲያናችን በጣም ታላቅ ዋጋ ያለውና የራሱ መዝሙር የሚዘመርለት፣ ቅዳሴ የሚቀደስበት ታላቅ መታሰቢያ ያለው ታሪክ ነው፡፡

 

ራሱ ጌታችንም የነነዌ ሰዎችን የንስሐ ታሪክ በመጥቀስ አይሁድን ገስጾበታል፤ በፍርድ ቀንም በዚያ ትውልድ ዘንድ እንደሚፈርዱበት ተናግሯል፡፡ ይህም የሆነበት የነነዌ ሰዎች ደስ የሚያሰኝ የንስሐ ታሪክ ስላላቸው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ይህን አስደሳች የንስሐ ታሪክ በጾመ ነነዌ ከሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባት አንጻር ለመመርመር እንሞከራለን፡፡

 

ኃጢአት ከእግዚአብሔር መለየት እንደሆነ ሁሉ ንስሐ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡  በዚህ ከእግዚአብሔር ሊለዩ የሚችሉ ብዙ ፈተናዎች ባለቡት ዓለም እስካለን ድረስ ሕይወታችን ሁሉ የንስሐ ጊዜ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሁሉም ጊዜ በተለየ ወደ እግዚአብሔር የምንመለስባቸው የጾም ወቅቶች ሲሆኑ ከእነዚህም ታላቁና ዋነኛው ዐቢይ ጾም ነው፡፡

 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዐቢይ ጾም ከእያንዳንዱ ምእመን ልቦና የንስሐ ፍሬን ትፈልጋለች፤ ያለ ትንሣኤ ልቦና /ንስሐ/ የክርስቶስን ትንሣኤ በእውነትና በደስታ ማክበር አይቻልምና፡፡ ለመሆኑ ከንስሐ የሚያሰናክሉን ነገሮች ምን ምን ናቸው? የነነዌ ሰዎች ታሪክ ስለዚህ ምን ያስተምረናል?

 

1.    ቅንጦትን መውደድ
ምንም እንኳን በደፈናው ገንዘብ የኃጢአት ምንጭ ነው ባንልም እንደ ወንጌል ትእዛዝ በክርስቲያናዊ መንገድ ካልተያዘ ግን እግዚአብሔርን ሊያስረሳና የኃጢአት ማስፈጸሚያና ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜም ገንዘብና ባለጸግነት ከእግዚአብሔር በመለየታችን ያጣነውን ሰላምና ደስታ ለማግኘት ተስፋ የምንጥልበት ጣኦት ሆኖ ሊቀየር ይችላል፡፡ በሀብታችን በምናገኘው ጊዜያዊ ደስታና ሰላም ዘላለማዊውንና ፍጹምን የእግዚአብሔር ስጦታ መፈለግ፣ ወደ እግዚአብሔር መመለስን መናፈቅ ልናቆም እንችላለን፡፡ በዚህ መልኩ ብልጽግና ከንስሐ የሚያሰናክል ወጥመድ ይሆናል ማለት ነው፡፡

 

እግዚአብሔር ሀብት እንኳ ቢሰጠን ለተቸገረ በመመጽወት፣ ልጆቻችን በክርስቲያናዊ መንገድ በማሳደግ፣ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በማፋጠን የእውነተኛ ደስታና የጽድቅ መንገድ እንድናደርገው እንጂ እግዚአብሔርን የተጠማች ነፍሳችንን ጥሪዋን በማደናቀፍና ጩኸቷን በማፈን በሥጋ ድሎት ውስጥ የምንደበቅበት መሣሪያ እንድናደረገው አይደለም፡፡ ለ«ታላቂቷ ከተማ» ነነዌም የጥፋት መንገድ የሆናት በብልጽግናዋና በታላቅነቷ እግዚአብሔርን ረስታ የኃጢአት ከተማ መሆኗ ነው፡፡ በነቢዩ በዮናስ ታሪክ ውስጥ ገንዘብ ለዮናስ ከእግዚአብሔር የመከለያ መሣሪያ ሲሆን እናገኘዋልን፡፡ «. ..  ከእግዚአብሔርም ፊት ኮብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሔድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርሷ /ወደ መርከቧ/ ገባ» እንዲል /ዮና፤1-3/፡፡

 

በዚህ ሰዓት ለዮናስ ገንዘብ ባይኖረው ይሻል ነበር፡፡ እኛም ቢሆን ከንስሐ የሚመልስ፣ ለኃጢአት መሣሪያ የሚሆን ሀብት ከሚኖረን በድኅነት ብንኖር ይሻለናል፡፡ ምንም እንኳ በቤተክርስቲያናችን ትውፊት ዐቢይ ጾም አብዝተን የምንጸልይበት፣ በጾም በስግደትና በምጽዋት ልናሳልፈው የሚገባ ወቅት ቢሆንም ፤ አሁን አሁን ግን ገንዘብ ማግበስበሻ እየሆነ እንደሆነ እናያለን፡፡ በመሠረቱ በጾም ወቅት ከሆዳችን የምንቀንሰው ገንዘብ እንድናጠራቅመው ሳይሆን እንድንመጸወተው የሚገባ ነው፡፡ ለማጠራቀምማ የማያምኑ ሰዎችስ ምግብ ይቀንሱ የለ? ለዚህ ነው በነነዌ ጾም በመጀመሪያው ቀን /ሰኞ/ የሚነበበው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት “አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ፡፡ ሀብታችሁ ተበላሽቷል፣ ልብሳችሁም በብል ተበልቷ፡፡ ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጓል፤ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል፡፡ ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል፡፡ እነሆ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፣የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ጸባዖት ጆሮ ገብቷል፡፡ በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል፤ በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል”  በማለት አስፈሪ ተግሳጽ የሚያስተላልፈው፡፡ ስለዚህ በዐቢይ ጾም አብዝተን የምንመጸውትበት፣ ከእግዚአብሔር የሆነውን ስጦታ የምንፈልግበት፣ የንስሐ ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡

 

2.    ለኃጢአት ሌላ ተጠያቂ መፈለግ
ሌላው ከንስሐ ሲያርቀን የሚገኘው ምክንያት በሰዎች መፍረድ ነው፡፡ በሰዎች የሚፈርድ ሰው ራሱን የሚያጸድቅ ነው፡፡ ራሱን ያጸደቀ ደግሞ ንስሐ መግባትና ከኃጢአት መመለስ ዳገት ይሆንበታል፡፡ ከነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ ውስጥ ለንስሐ በጣም አስቸጋሪ የነበረው ነቢዩ ዮናስ ነው፡፡ መርከበኞቹና የነነዌ ሰዎች በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ ዮናስ ግን ከታሪኩ መጀመሪያ እስከ መጨረሻዋ ጊዜ ድረስ በእግዚአብሔር ያጉረመርም ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ከእግዚአብሔር መኮብለሉና የነነዌ ሰዎችን ድኅነት መቃወሙን እንደ  ስህተት እንጂ እንደራሱ ስህተት አለመቁጠሩ ነው፡፡  ለዚህ ነበር ከእግዚአብሔር ኮብልሎ ሲሔድ እንኳ ምንም ዓይነት ጭንቀት ሳይሰማው «በከባድ እንቅልፍ» ተኝቶ የነበረው /ዮና.1-5/፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንዳንድ ሰዎች ለራሳቸው ኃጢአት እግዚአብሔርን ተጠያቂ ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ ሰዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም በራሳቸው ከመፍረድ ይልቅ በሰዎች መፍረድ ይጀምራሉ፤ ወይም የኃጢአታቸው ምክንያት እግዚአብሔርን አድርገው ይገኛሉ፡፡ ነቢዩ ዮናስ የራሱን ክብር ፈላጊነት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ምሕረት የኃጢአቱ ምክንያት ማድረጉ የሚያስገርም ነው፡፡ ይህም ለብዙ ጊዜ ከንስሐ እንዳዘገየው ከታሪኩ እንማራለን፡፡ በተቃራኒው ለንስሐ ቅርብ የሆኑት መርከበኞች በዮናስ ላይ ለመፍረድ ምን ያህል እንደተጨነቁ ስናይ ቀድሞውኑ በዮናስ አለመታዘዝ ምክንያትም ቢሆን እግዚአብሔር ወደ ንስሐ ሊመልሳቸው የፈለገ ይህን አይቶ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

 

በጾመ ነነዌ የመጀመሪያው ቀን /ሰኞ/ የሚነበበው የቅዱስ ጳዉሎስ መልእክትም የሚያስተምረን ይህንኑ ነው፡- “ስለዚህ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፣ የምታመካኘው የለህም በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኮንናለህና፡፡ አንተም ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና፡፡ እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደሆነ እናውቃለንና፡፡ . . . ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ስታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን ቁጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ” /ሮሜ.2-1-5/፡፡ በተቃራኒው ግን በሰው ላይ ከመፍረድ በራሳቸው ላይ መፍረድን የሚመርጡ ሰዎች ለንስሐ ቅርብ ናቸው፡፡ በሚቀጥለው ቀን ማክሰኞ የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክትም የሚያብራራው ይህንኑ ነው/1ቆሮ.4-1/፡፡

 

3.    የእግዚአብሔርን ተግሳጽ አለመቀበል
በነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ሰዎችን ሲገስጽ እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ዮናስን በማዕበል፣ ወደባሕር እንዲወረወር በማድረግ፣ አሳ አንበሪ እንዲውጠው በማድረግ እግዚአብሔር ወደ ትክክለኛ መንገዱ ሊመልሰው ቢጥርም በዚህ ሁሉ ሊመለስ አልቻለም፤ ከአሳ አንበሪ አፍ ወጥቶ ሔዶ ቢሰብክም እግዚአብሔር ይቅር ሲላቸው ግን በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረም ጀምሯልና፡፡ ድሮም ቢሆን በፍርሃት እንጂ ስህተቱን ተቀብሎ አልነበረም ወደ ነነዌ ሔዶ የሰበከው፡፡ ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት /ነፋስ፣ አሳ አንበሪ፣ ትል፣ ፀሐይ/ እንዴት እንደሚታዘዙለት እርሱ ግን ታላቅ ነቢይ ሲሆን አልታዘዝም ማለቱን በማሳየትም ገስጾታል፡፡ በመጨረሻም ለንስሐ በቅቷል፡፡ መርከበኞቹም በመርከባቸው ላይ የተነሣው ማዕበል ተግሳጽ ሆኗቸው ወደ ንስሐ ተመልሰዋል፡፡ ከዘላለም ሕይወት እንዳንለይ አጥብቆ የሚፈልገው እግዚአብሔር ልዩ ልዩ መከራዎችንም በማምጣት ወደ ንስሐ እንድንመለስ ያደርጋል፡፡ ለዚህ ተግሳጽ ግን በትክክለኛ ወይም በተሳሳተ መንገድ መልስ ልንሰጥ እንችላለን፡፡ ካወቅንባቸውና ከተጠቀምንባቸው ችግሮችና መከራዎች ወደ ንስሐ የሚመሩ መንገዶች ናቸው፡፡ የነነዌ ታሪክም የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡ በነነዌ ጾም በቅዳሴ የሚነበቡት የሚከተሉት ምንባባትም በአጽንኦት የሚገልጹት ይህንኑ ነው፡፡
 

ምስባክ:- “ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፈ፡፡
እግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዛል በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል
የእኔ ስዕለት ለሕይወቴ አምላክ ነው፡፡” /መዝ.41-7-8/

መልእክት:- “. .  . ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል. . .” /ሐዋ.14-22/፡፡
 

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አሳዛኙ ነገር ሰው ካለፈ ሕይወቱ አለመማሩ ነው፡፡ በነቢዩ በዮናስ ታሪክም የምናገኘው ይህንኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር የተሳፈረበትን መርከብ ካናወጠ፣ ዮናስ በአሳ አንበሪ እንዲዋጥ ካደረገ በኋላ እንኳ እግዚአብሔር በነነዌ ሰዎች ላይ ያሳየው ምሕረት ዮናስ ሞትን እስኪመኝ ድረስ እንዲያዝንና በእግዚአብሔር ላይ እንዲያጉረመርም አድርጎታልና፡፡ በእኛም ሕይወት ተመሳሳይ ተግሳጻት ከእግዚአብሔር ዘንድ ቢመጣም ከኃጢአት ባለመመለስ ከዮናስ ያልተለየ መልስ ነው የምንሰጠው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ራሳችንን የምናይበት፣ በሕይወታችን ያደረጋቸውን የእግዚአብሔር ሥራዎች የምንመረምርበት፣ በውስጣችን ያደፈጡትን አውሬዎች የምናድንበት የተረጋጋና ሰፋ ያለ ጊዜ ስለሌለን ነው፡፡ ይህን አጥብቃ የተረዳችው ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በልዩ ልዩ መንገድ የሚጠራንን የእግዚአብሔር ድምፅ የምናዳምጥበት፣ በመልካም ምክንያቶች የተሸፈኑ ነገር ግን መልካም ያልሆኑና መልካም ልንሠራበት የምንችለውን የሕይወት ጊዜዎችን የሚያቃጥሉ ከንቱ ምኞቶቻችን፣ የማይጨበጡና የማይደረስባቸው “ክፉ ተስፋዎቻችን” ሁሉ የምንመረምርበት፣ መልካሟንና እውነተኛዋን ነገር ግን አስቸጋሪዋንና ጠባቧን የሕይወት መንገዳችን አጉልተን “የምናስምርበት” ሰፋ ያለ ጊዜ ሰጥታናለች፤ ይህም ዐቢይ ጾም ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በአግባቡ ከተጠቀምንበትም የዚህን አስቸጋሪና አወናባጅ ዓለም በድል የተወጡ ሰዎች የሚያዩትን የዘለዓለማዊን ሕይወት «ቀብድ» የትንሣኤውን ብርሃን እናያለን፡፡ ዐቢይ ጾምን እንደሚገባ ያላሳለፈ ክርስቲያን ግን የትንሣኤን ድግስ በልቶ ሆዱን ይሞላ እንደሆነ እንጂ የትንሣኤን ታላቅ ደስታ መቅመስ አይችልም፡፡ ስለዚህም ዐቢይ ጾም ለክርስቲያን ታላቅ ስጦታ መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ስለጾም በጻፉት መጽሐፋቸው “በዐቢይ ጾም ሕይወቱን ያልቀየረ ክርስቲያን በሌሎች አጽዋማት ይቀይራል ማለት ይከብዳል” በማለት የጻፉት፡፡

 

4.    ክፉ እኔነት
በዮናስ ታሪክ ውስጥ ከብዙ የዮናስ ስህተቶች ጀርባ የነበረውና ንስሐውን ያዘገየበት ታላቁ መሰናከል ክፉ እኔነት ነው፡፡ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ የነነዌ ሰዎችን ድኀነት ሳይሆን የራሱን ክብር እንዲመለከት ያደረገው በዮናስ ሕይወት ውስጥ በጥልቅ የተተከለ ክፉ እኔነቱ ነው፡፡ በዚያ ሁሉ ታሪክ ውስጥ በርግጥም ዮናስ ስለራሱ እንጂ ስለሰዎች ሲያስብ አልታየም፡፡ ነቢዩ ዮናስ “እኔ ሐሰተኛ ነቢይ ከምባል የነነዌ ሰዎች መጥፋት ይሻላል” “የዮናስ አምላክ ቃሉን ይቀይራል ከምባል የነነዌ ሰዎች ይጥፉ” ብሎ ያስብ እንጂ እግዚአብሔር ግን አላለም፡፡ አመድና ትቢያ የሆነው የሰው ልጅ ስለክብሩ ሲጨነቅ ክብር የባሕሪዩ የሆነ ሩህሩህ አምላክ ግን ማንም እንዲጠፋ አልፈቀደም፡፡

 

በርግጥ የነነዌ ሰዎች በመዳናቸው የዮናስም የእግዚአብሔርም ቃለ አልታበለም፡፡ ዮናስ “ነነዌ በሦስት ቀን ውስጥ ትጠፋለች” ብሎ ሰበከ፡፡ አመጸኛዋ ነነዌ ግን በቁጣ እሳት ከመጥፋቷ በፊት በንስሐ ራሷን አዋረደች፡፡ በዚያን ጊዜ ነነዌ በንስሐ አዲስ ፍጥረት የሆነች፣ እግዚአብሔር የሚያጠፋት ሳትሆን የሚወዳት ሌላ ነነዌ ሆነች፡፡ ዮናስ ሆይ በንስሐ የታደሰችው ነነዌ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ እንደማያጠፋስ ለምን አላሰብክም? ታላቁ

 

የእግዚአብሔር ነቢይ ሆይ ንስሐ የገባችዋን ነነዌን ማጥፋት አምላክህን አያስነቅፈውምን? በነቢዩ በዮናስ ውስጥ ያለው እኔነቱ በርግጥም እግዚአብሔርንም፣ የነነዌ ሰዎችንም እንዳያስብ መጋረጃ ሆኖበት ነበር፡፡

 

በነቢዩ በዮናስ ሕይወት ውስጥ ክፉ እኔነቱ በዚህ መልክ ቢገለጥም፣ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ግን በተለያየ መንገድ ሊገለጥ ይችላል፡፡ አንዳንዶቻችን “እኔ ቅዱስ ነኝ” የማለት ክፉ እኔነት ተጠናውቶናል፡፡ ኃጢአታችን ለንስሐ አባታችንና ለጓደኞቻችን ስንናገር እንኳ “ኃጢአትን የመናገር ቅድስና” እንጂ ኃጢአተኝነታችን አይሰማንም፡፡ “እኔ ርኩስ ነኝ” ስንልም ራስን በፈቃድ ኃጢአተኛ የማድረግ “ቅድስና” እንጂ ልባዊ የሆነ ንስሐ አይሰማንም፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ “እኔ አዋቂ ነኝ” የማለት ክፉ እኔነት ይዞናል፡፡ “እኔ እኮ ምንም አላውቅም” ብለን ስንናገር እንኳን በልባችን ራስን ዝቅ ማድረግን “እያስተማርን” ነው በፍቅር ከተሰባሰቡ መንፈሳውያን ወንድሞችና እኅቶች መካከል እንኳን “ወርቃማ መንፈሳዊ ምክሮችን” ለመለገስ እንጂ መች ፍቅርን ‘ከታናናሾቻችን’ ለመማር እንቀመጣለንና፡፡ በዚህም በባዶነታችን እንኖራለን፡፡

 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን “ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች መድኃኒት አያስፈልጋቸውም” ብሏል፡፡ ሕመምተኞች መሆናችን አውቀን በንስሐ ብንቀርብ መድኃንኒት ይሆነናል፤ ራሳችንን አጽድቀንና «ቅዱስ ነኝ» ብለን በውሸት የጤንነት ስሜት መድኃኒት መፈለግ ከተውን ግን ከነኃጢአታችን እንሞታለን፡፡ ጌታችን ለእውራን ብርሃን፣ ዕውቀት ለሌላቸው ሰማያዊ ጥበብን የሚሰጥ ራሱ የእግዚአብሔር ጥበብ መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን ራሳችን በአዋቂዎች ተራ ከመደብን መምህር አልፎን ይሔዳል፡፡ ጌታ አለማወቃቸውን ያወቁትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰማያዊ ጥበብን የሚፈልጉትን ሲያስተምር እንጂ «ምሁራንን» ሊያስተምር አልመጣምና፡፡ በኃጢአት መኖር እንደ ሀሞት መሮት፣ እንደጨለማ ከብዶት ከልቡ የሚጮኽን ተነሣሒ ለመቀደስ፣ እግዚአብሔር የዕውቀት ምንጭ የሕሊና ብርሃን መሆኑን አውቀው ከጥልቅ ከልቦናቸው ዕውቀትን የሚፈልጉትን ለማስተማር መጥቷልና እንደዚሁ ካልሆንን ከዚህ ጸጋ ዕድል ፈንታ አይኖረንም፡፡

 

ይህን ሁሉ የሕይወታችን ውጥንቅጥ እንመረምርበት ዘንድ ታላቁ የቤተክርስቲያን ስጦታ ዐቢይ ጾም እነሆ፡፡

የእውነተኛ ንስሐ ውጤቶች በነነዌ ሰዎች ታሪክ

1.    የዘላለም ሕይወት ተስፋ
ነነዌ የጥፋት ፍርድ ከተፈረደባት በኋላ የመኖር ተስፋ የተሰጣት ከተማ ናት፡፡ በሌላ አነጋገር ነነዌ ሞታ የተነሣች ከተማ ናት ማለት ይቻላል፡፡ ነቢዩ ዮናስም ወደ ባሕር ከተጣለ፣ በአሳ አንበሪ ሆድ ውስጥ ካደረ በኋላ የመኖር ተስፋ የተሰጠው ሰው ነው፡፡ መርከበኞችም መርከባቸው በማዕበል ከተመታች በኋላ፣ ማዕበሉ ካሸነፋቸው በኋላ በእግዚአብሔር ምሕረት ሌላ የመኖር ተስፋ የተሰጣቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የነነዌ ታሪክ የተስፋ ታሪክ ነው፡፡

 

ንስሐም በኃጢአት ከሞቱ በኋላ እንደገና የመኖር ተስፋ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የዘለዓለም ሕይወትን ተስፋ ማድረግ ይከብዳቸዋል፤ ለዚህም ምክንያቱ በንስሐ አለመኖራቸው ነው፡፡ ሰው ያላየውን ነገር እንዴት ይናፍቃል? የማያውቀውን ነገርስ እንዴት ተስፋ ያደርጋል? በንስሐ የሚኖር ሰው ግን የዘለዓለም ሕይወት ቀብድ የሆነ ትንሣኤ ልቦናን ይነሣልና የዘለዓለም ሕይወትን በተስፋ ይናፈቃሉ፡፡ ዐቢይ ጾምንም በንስሐና ራስን በመመርመር ያሳለፈ ሰው በትንሣኤው ትንሣኤን ይቀምሳልና ዘለዓለማዊውን ትንሣኤ በተሰፋ ይናፍቃል፡፡

በነነዌ ጾም የሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባትም ይህን እንደሚከተለው ይገልጻሉ፡-

“. . .  ትዕግሥትም ፈተናን፣ ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን፡፡ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም” /ሮሜ.5-4-5/፡፡

“እናንተ ግን፣ ወዳጆች ሆይ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፣ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን  ጠብቁ” /ይሁዳ.1-20/፡፡

 

2.    በእግዚአብሔር ዘንድ መከበር
በንስሐ የተመለሰችው ነነዌ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ከብራለች፡፡ የነነዌ ሰዎች ንስሐ በማይገቡ ዘንድ በትውልዱ ሁሉ ምስክር ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቅዷል፡፡ «የነነዌ ሰዎች በፍርድ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፣ እነሆም “ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ” እንዲል /ሉቃ.11-32/፡፡ የነቢዩ የዮናስ ታሪክም እንደዚሁ ነው፡፡ የንስሐ ሰባኪ የሆነው ራሱም ከብዙ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኋላ በንስሐ የተመለሰው ዮናስ የክርስቶስ ምልክት እንዲሆን እግዚአብሔር መፍቀዱ እግዚአብሔር ለተነሳሕያን የሚሰውን ክብር ያሳያል፡፡

 

ምንም እንኳን በዚህ ምድር ያለን ሰዎች የተነሣሕያንን ክብር ባናውቅም በሰማይ ያሉ መላእክት ግን በአንድ ኃጢአተኛ ንስሐ መግባት ታላቅ ደስታ ማድረጋቸው የንስሐን ክብር ያሳያል፡፡ ለዚህ ነው ለንስሐ የተዘጋጀ ልብን በማየት እግዚአብሔር አስቀድሞ ነነዌን “ታላቂቷ ከተማ” ብሎ የጠራት /ዮናስ.1-2/፡፡ ተነሣሕያን የእግዚአብሔር ይቅርታና ፍቅር የሚገለጥባቸው ሰዎች ናቸውና በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ዘንድ የከበሩ ሰዎች ናቸው፡፡

 

3.    የእግዚአብሔርን ኃይል ማየት
በነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔር ኃያልነት በግልጥ ተገልጧል፡፡ የእግዚአብሔር ኃያልነትም በትዕግሥቱ፣ በፍቅሩ፣ ፍጥረትን በመግዛቱ፣ ለሰው ልጆች በሰጠው ድንቅ ነፃነት ወዘተ ተገልጧል፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ አንዲትም ነፍስ ሳትጠፋ ሁሉም ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር ያሳየው የትዕግሥቱ ኃያልነት እንዴት ድንቅ ነው! የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያስተምር ዘንድ ነቢይ የሆነው ዮናስ እንኳ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ትቶ ሲኮበልል በሔደበት ሁሉ እየተከተለ በተለያየ መንገድ ወደ መንገዱ እንዲመለስ ይሠራ ነበር፡፡ ምናልባትም ሰው ዮናስን ይህን ያህል አይታገሰውም፡፡ ሰዎች እግዚአብሔርን ‘የመምከር’ ዕድል ቢሰጠን “ጌታ ሆይ አንተ ሁሉን ማድረግ ትችላለህ፤ ከነዚህ ድንጋዮት እንኳ ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት ትችላለህ፡፡ ለምን ዮናስን ትለምነዋለህ? ተወው ሌላ ነቢይ ወደ ነነዌ ላክ፡፡ ዮናስን ርግፍ አድርገህ ተወው ከነነዌ ሰዎች የራሱን ክብር አስቀድሟልና” እንል ይሆናል፡፡ በባሕሪዩ ታጋሽ የሆነው እግዚአብሔር ግን ዮናስ በንስሐ ይመለስ ዘንድ ጠብቆታል፤ በመጨረሻም ለክርስቶስ ምሳሌ የሚሆን ታላቅ ነቢይ አድርጎታል፡፡

 

በነነዌ ታሪክ የእግዚአብሔር የፍቅሩ ታላቅነትም ተገልጧል፡፡ የእስራኤል አምላክ ይባል እንጂ ከአሕዛብ መካከል ለንስሐ የተዘጋጀ ሕዝብ ሲያይ ነቢዩን ልኮ ሕዝቡ አድርጓቸዋል፡፡ ቀና ልብ ያላቸው፣ ዮናስ ሲተኛ እንኳ ለማያውቁት አምላክ ሲጸልዩ የነበሩትን መርከበኞችንም በዮናስ  ምክንያት እንዲያውቁት አድርጓል፡፡ በርግጥም እግዚአብሔር ወደርሱ የምታይን ነፍስ፣ እርሱን የተጠማችን ልቦና አይተዋትም፡፡

 

በነነዌ ሰዎች ታሪክ የታየው ሌላው የእግዚአብሔር ኃይል በፍጥረቱ ላይ ያለው ሥልጣን ነው፡፡ ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት /ፀሐይ፣ ማዕበል፣ ትል፣ ዛፍ፣ አሳ አንበሪ. . . / የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያለምንም ተቃውሞ ሲፈጽሙ እናያለን፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠውን ታላቅ ስጦታ ‘ነፃነትን’ እናደንቃለን፡፡ ፍጥረታት የሚታዘዙለት ኃይል እግዚአብሔር በነፃነት የፈጠረው የሰው ልጅ ፈቃዱን ሲጥስ ይመለስ ዘንድ በሚታዘዙት ፍጥረታት፣ በነቢያት. . . ይናገራል እንጂ ልቦናን በኃይሉ ቀይሮ እንደፈቃዱ እንዲኖር አያደርግም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መቀየር የፈለገን ልብ መቀየር የሚችል የሁሉ ፈጣሪ መሆኑን ፍጥረታቱን በማዘዝ አሳይቷል፡፡

 

ከዚህ ታሪክ ለእኛ የሚሆን ብዙ ነገሮችን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው በንስሐ የምንኖር ከሆነ ወደዚህ ሕይወት እንደርስ ዘንድ እግዚአብሔር የታገሰባቸውን ያለፉትን የኃጢአት ዘመናት አስተውለን የእግዚአብሔርን የትዕግሥቱን ብርታት በሕይወታችን እናውቃለን፡፡ ከዚህ በኋላ ስለ እግዚአብሔር ታጋሽነት ሰዎች ሊነግሩን አያስፈልግም፤ በሕይወታችን አይተነዋልና፡፡

 

ከዚህም በተጨማሪ ወደ እርሱ እንመለስ ዘንድ በሕይወታችን ውስጥ የሠራውን የፍቅሩን ብርታትም እናውቃለን፡፡ ምንም እንኳ በዚህ ምድር ላይ ከቢሊዮኖች መካከል አንድ ብንሆንም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን በንስሐ መመለሳችን ሁሌ በእግዚአብሔር ሕሊና ውስጥ ሲታሰብ የኖረ፣ በሰማያት ካሉ ቅዱሳን ይልቅ የአንድ ኃጢአተኛ መመለስ ለሰማያትና ለእግዚአብሔር ደስታ የሚሰጥ መሆኑን ስናውቅ በርግጥም እግዚአብሔር እንዴት ሰውን ወዳጅ ነው? ነፍሳችንስ በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል የምትወደድ ናት? እንላለን፡፡

 

ከዚህ ሌላ ፍጥረታት የእግዚአብሔር ሁሉን የማድረግ ሥልጣን በመታዘዝ እንዳሳዩ ሁሉ በንስሐ የተመለሰ ኃጢአተኛም የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት የሚታይበት ይሆናል፡፡ በኃጢአት የኖረን፣ አያሌ ዘመናትን በዲያብሎስ ምክር በጠማማ መንገድ የኖረን ልቦና መቀየር ከኃያሉ ከእግዚአብሔር በቀር ለማን ይቻለዋል? ኃጢአተኛን ‘ቅዱስ’ ማድረግ የእግዚአብሔር የብቻው የኃያልነቱ ውጤት ነውና፡፡ ለዚህ ነው ‘ተነሳሕያን’ ሰማዕታት ናቸው የሚባለው፤ የእግዚአብሔርን ሥራ በሕይወታቸው ይመሰክራሉና፡፡ ጥንታውያን ክርስቲያኖች በደማቸው የእግዚአብሔርን ክብር መስክረው ከሆነ ለዚህ ትውልድ ደግሞ “የንስሐ” ሰማዕትነት ቀርቶለታል፡፡

 

በአጠቃላይ ከነነዌ ሰዎች ታሪክ ስለንስሐ ብዙ እንማራለን፡፡ ለዚህም ነው ከብዙ የንስሐ ታሪኮች መርጣ ቅድስት ቤተክርስቲያን በተለየ ክብር የምታስበው፡፡ ለዚህም ነው ለታላቁ የንስሐ ወቅት ለዐቢይ ጾም ማዘጋጃ መግቢያ ያደረገችው፡፡ እኛም ከዚህ ታሪክ ተምረን፣ የተማረነውንም በንስሐ ወቅታችን /በአሁኑ ጾም/ በተግባር ልናውለው ይገባል፡፡ ለዚህም የተነሳሕያን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን፡፡
 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

timket 01-07

ወተጠሚቆ ሶቤሃ ወጽአ እማይ ጌታችን … ከተጠመቀ በኋላ ከውሃው ወጣ

ጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም.

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ 
የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የጎንደር መ/መ/መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ

timket 01-07በነቢያት የተነገረው ትንቢት በወንጌል የተጻፈው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ከተሥአቱ ከዘጠኙ ታላላቅ በዓላት አንዱ ነው፡፡ጥምቀት ተጠምቀ ተጠመቀ ካለው ግሥ የወጣ ሲሆን ጥምቀት ማለት በውሃ መጠመቅና በወራጅ ወንዝ በሐይቅ ውስጥ በምንጭ የሚፈጸም ነው:: በካህናት እጅ የሚፈጸመው ጥምቀት ከሌላው ጥምቀት ልዩ ነው::

በዘመነ ብሉይ ይፈጸም የነበረው ጥምቀት የንስሓ ጥምቀት ሲሆን በዘመነ ሐዲስ የሚፈጸመው ግን የልጅነት ጥምቀት ነው:: የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ከሁለቱም ልዩ ነው:: እሱ ሰውን ያከብራል እንጅ ከሰው ክብርን የማይፈልግ የባሕርይ አምላክ ነው:: ለኛ አርአያና አብነት ለመሆን በሰላሳ ዓመቱ በእደ ዮሐንስ በዮሐንስ እጅ በማየ ዮርዳኖስ ተጠምቆ የባሕርይ ልጅነቱንና አምላክነቱነን ከአብና ከመንፈሰ ቅዱስ አስመሥክሮ ዕለቱን ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ጾምን ጀምሯል፡፡

 

በሠላሳ ዓመቱ የተጠመቀበት ምሥጢር አዳም የሰላሳ ዓመት፤ ሔዋን የአሥራ አምስት ዓመት ሰው ሁነው ተፈጥረው አዳም በአርባ ቀን ሄዋን በሰማንያ ቀን ከሥላሴ የተቀበሉትን ልጅነት በምክረ ከይሲ ዕፀ በለስን በልተው አስወስደው ነበረና በሰላሳ ዓመቱ ተጠምቆ መልሶላቸዋል፡፡

 

ወየአክል ሠላሳ ክረምቱ ለእግዚእ ኢየሱስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ሠላሳ ዓመት ሁኖት ነበር፡፡ ሉቃ ፫-፳፫ በሰላሳ ዓመት የመጠመቁ ምስጢር ይህ ሲሆን እኛ ዛሬ ወንዶች በአርባ ቀን ሴቶች በሰማንያ ቀን በዕለተ ዓርብ ከቀኝ ጎኑ በፈሰሰው ማየ ገቦ ተጠምቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕጸነ ዮርዳኖስ ሁለተኛ የምንወለድበት ምሥጢር ግን አዳም በአርባ ቀኑ ሄዋን በሰማንያ ቀን ከሥላሴ ልጅነትን አግኝተው ሁለተኛ የተወለዱበትን ምሥጢር የያዘና የጠበቀ ምሥጢረጥምቀትና ሥርዓተ ጥምቀት ነው፡፡ ኩፋ ፬-፱

 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመው ሕግና የሠራው ሥርዓት እንደእንግዳ ደራሽ እንደውሃ ፈሳሽ አይደለም ቅድመ ዓለም በልብ የመከረውን ኋላም በነቢያት ያናገረውን ትንቢትና ምሳሌ ያስቆጠረውን የዘመን ሱባዔ ለአዳም የሰጠውን የመዳን ተስፋ ለመፈጸም ነው እንጅ፡፡ የተነገረውን ትንቢት የተመሰለውን ምሳሌ እንደሚከተለው መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡

 

ወአሜሃ መጽአ እግዚእ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ከመ ይጠመቅ እምኀበ ዮሐንስ ማቴ ፫-፲፫ ማር፩-፱ ሉቃ ፫-፳፩ ዮሐ ፩-፴፪ ለጌታ ሰላሳ ዓመት ሲመላው ለዮሐንስ መንፈቅ ሲተርፈው ያን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ አብ በደመና ሁኖ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ብሎ ሲመሠክር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አንዱ አካል ወልድ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ታወቋል፡፡

 

ያን ጊዜ ጌታ ከገሊላ ወደዮርዳኖስ መጣ አለ፡፡ ምነው አገልጋይ ወደጌታው ይሄዳል እንጅ ጌታ ወደአገልጋዩ ይሄዳልን? አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጅ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን? ቢሉ ጌታ መምጣቱ ለትሕትና ነው እንጅ ለልዕልና አይደለምና ዳግመኛም ለአብነት ነው ጌታ ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ብሎት ቢሆን ዛሬ ነገሥታት መኳንንት ካህናትን ከቤታችን መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበርና፡፡ ካህናት ካሉበት ከቤተ ክርስቲያን ሂዳችሁ ተጠመቁ ለማለት አብነት ለመሆን ነው፡፡

 

ያውስ ቢሆን ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለምን ነው ቢሉ ትንቢቱን ምሳሌውን ለመፈጸም ትንቢት ባሕርኒ ርእየት ወጐየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ ባሕር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ ርእዩከ ማያት እግዚኦ ርእዩከ ማያት ወፈርሁ አቤቱ ውሃዎች አንተን አይተው ሸሹ ተብሎ ተነግሯል መዝ ፸፮-፲፮፣ ፻፲፫-፫

 

 ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ(ምንጩ) አንድ ነው ዝቅ ብሎ በደሴት ይከፈላል ከታች ወርዶ ይገናኛል ዮርዳኖስ ከላይ (ነቁ)ምንጩ አንድ እንደሆነ የሰውም መገኛው (ምንጩ)አንድ አዳም ነውና ዝቅ ብሎ በደሴት እንዲከፈል እስራኤል በግዝረት አሕዛብ በቍልፈት ተለያይተዋል ከታች በወደብ እንዲገናኝ በክርስቶስ ጥምቀት ሕዝብና አሕዛብ አንድ ሁነዋልና ዳግመኛም አብርሃም ለአምስቱ ነገሥተ ሰዶም ረድቶ አራቱን ነገሥተ ኮሎዶጎሞር ድል ነሥቶ በተመለሰ ጊዜ ደስ ቢለው በመዋዕልየኑ ትፌኑ ቃልከ ወሚመርዕየኒሁ ኪያሃ ዕለተ አው አልቦ አለው፡፡ምሳሌውን ታያለህና ሑር ዕድዎ ለዮርዳኖስ፡፡ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ሒድአለው፡፡ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ቢሔድ መልከ ጼዲቅ ኅብስተ አኮቴት ጽዋዓ በረከት ይዞ ተቀብሎታልና፡፡ አብርሃም የምእመን ዮርዳኖስ የጥምቀት መልከ ጼዴቅ የካህናት፡፡ ኅብስተ አኰቴት ጽዋዓ በረከት የሥጋው የደሙ ምሳሌ ነውና ያን ለመፈጸም ዘፍ ፲፬-፲፫-፳፬፡፡

 

ዳግመኛም ኢዮብና ንዕማን በዮርዳኖስ ተጠምቀው ከደዌያቸው ድነዋል ኢዮብና ንዕማን የአዳምና የልጆቹ ነገ ካልዕ ፭ ፰-፲፱ ደዌ የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ ነውና ያን ለመፈጸም ነው፡፡ ዳግመኛም እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በኋላ በኢያሱ ጊዜ ወደምድረ ርስት ሲሄዱ ከዮርዳኖስ ወንዝ ደረሱ ታቦቱን የተሸከሙና ልብሰ ተክህኖ የለበሱት ሌዋውያን ካህናት በፊት በፊት ሲሄዱ ታቦቱን የሚያጅቡ ሕዝበ እስራኤል ከታቦቱና ከሌዋውያን ካህናት ሁለት ሽህ ክንድ ርቀው ዮርዳኖስ ከላይና ከታች ተከፍሎላቸው በየብስ ተሻግረው ኢየሩሳሌም ገብተዋል ምእመናንም በማየ ገቦ ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማያት ለመግባታቸው ምሳሌ ነው፡፡

 

ዛሬም ታቦታቱን ወደጥምቀተ ባሕር በማውረድ በዓለ ጥምቀቱን ለሚያከብሩ ክርስቲያኖች በሙሉ ከታቦታቱ ሁለት ሽህ ክንድ ርቀው መከተል እንዲገባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈ አምላካዊ ትዕዛዝ መሆኑ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል “ሕዝቡን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሽህ ክንድ ይሁን በዚህ መንገድ በፊት አልሄዳችሁበትምና የምትሁዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደታቦቱ አትቅረቡ ብለው አዘዙ” ኢያ፫-፩–፲፯፡፡

 

ዛሬ ሌዋውያን ካህናትና ሊቃውንት በዝማሬ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዕልልታና ሆታ ታቦታቱን አጅበው ወደጥምቀተ ባሕር ለሚወርዱ ታቦታት በመጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ ሦስት ቁጥር ሦስት ላይ የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ዛሬ ታቦታቱ ወደጥምቀተ ባሕር ወርደው ለማደራቸውና ለበዓለ ጥምቀቱ መነሻ አምላካዊ ሕግና ሥርዓት ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደዮርዳኖስ መጥቶ በዮሐንስ እጅ መጠመቁም በዘመነ ወንጌል ክርስቶስ ከተጠመቀበት ሠላሳ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ በየዓመቱ ጥር አሥራ አንድ ቀን ለሚከበረው በዓለ ጥምቀት አምላካዊ ታሪካዊ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ ክርስቲያናዊ ሕግና ሥርዓት ያለው በዓል ስለሆነ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሲከበር የሚኖርታላቅ በዓል መሆኑን ያስረዳል፡፡

 

ኤልያስም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ብሔረ ሕያዋን ገብቷል፡፡ የኤልያስ ደቀ መዝሙር ኤልሳዕም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዮርዳኖስ ዳር እንጨት ሲቆርጡ መጥረቢያው ከውሃው ውስጥ ወደቀ ኤልሳዕ የእንጨት ቅርፊት በትዕምርተ መስቀል ከወደቀበት ላይ ቢጥልበት የማይዘግጠው ቅርፊት ዘግጦ የዘገጠውን ብረት አንሳፎ አውጥቶታል እንደዚሁም ሁሉ በባሕርዩ ሕማም ሞት የሌለበት አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርም ተወልዶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በዮርዳኖስ ተጠምቆ በቀራንዮ በቅዱስ መስቀል ተሰቀሎ ከጎኑ ጥሩ ውሃና ትኩስ ደም አፍስሶ በሲኦል የወደቀ አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው ነገ ካልዕ ፮-፩–፯፡፡

 

መጠመቁም ለሱ ክብር የሚጨመርለት ሁኖ አይደለም ዮርዳኖስን ብርህት ማሕጸን ለማድረግ እኛ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕጸነ ዮርዳኖስ ተወልደን መንግሥተ ሰማያት እንድንገባ ሥርዓተ ጥምቀትን ለማስተማርና አብነት ለመሆን ነው እንጅ ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይሬእያ ለመንግሥተ እግዚአብሔር ዳግመኛ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕጸነ ዮርዳኖስ ያልተወለደ ማለትም ያልተጠመቀ ወደእግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን ወዘሰ ኢአምነ ወኢተጠምቀ ይደየን ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል እንዲል፡፡ ዮሐ ፫-፫ ማር፲፮-፲፮

 

እኛም ስንጠመቅ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው ፡፡ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ስታጠምቋቸውም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው እንዲል ማቴ ፳፰-፲፱ ኢዮብ ንዕማን ጌታ የተጠመቁበት ዮርዳኖስ ወደቡ አንድ ነው፡፡

 

ትንቢቱን አስቀድሞ በነቢያት አናግሯል ምሳለውንም አስመስሏል ሱባዔውንም አስቆጥሯል በዮርዳኖስ የተጠመቀበት ምስጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ አገዛዝ ስቃይ አጸናባቸው ፡፡ሲጨነቁ አይቶ አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ ማለትም አዳም የዲያብሎስ ተገዥ ሔዋንም የዲያብሎስ ተገዥ አገልጋዮች ነን ብላችሁ ስመ ግብርናታችሁን የተገዥነታችሁን ስም ጽፋችሁ ብትሰጡኝ መከራውን አቀልላችሁ ነበር አላቸው ፡፡

 

እነሱም የሚቀልላቸው መስሏቸው ፈቀዱለት እነሱም አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ ብሎ በወረቀት ብጽፈው ይጠፋብኛል ሲል በማይጠፋ በሁለት ዕብነ(ሩካም)በረድ ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጥሎት ይኖር ነበር በዮርዳኖስ የጣለውን ሲጠመቅ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ እንደሰውነቱ ተረግጦ አጥፍቶልናል በሲኦል የጣለውንም በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ አጥፍቶልናልእና በዮርዳኖስ የተጠመቀበት ምሥጢር ይህ ነው፡፡

 

ወዮሐንስሰ ዐበዮ እንዘ ይብል አንሰ እፈቅድ እምኃቤከ እጠመቅ ዮሐንስ ግን አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጅ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን ብሎ አይሆንም አለው ወአንተኑ ትመጽእ ኀቤየ አገልጋይ ወደጌታው ይሄዳል እንጅ ጌታ ወደአገልጋዩ ይሄዳልን አለው እናቱ ኤልሳቤጥ ምንትኑ አነ ከመ ትምጽኢ ኀቤየ እሙ ለእግዚእየ እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከናዝሬት ወደዓይነ ከርም ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ በመጣች ጊዜ ኤልሳቤጥ የጌታየ እናቱ እኔ ወደአንች እመጣለሁ እንጅ አንቺ ወደኔ ትመጭ ዘንድ ይገባኛልን ብላ ነበርና ከዚያ አያይዞ ተናገረው ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎ ኅድግ ምዕረሰ ጌታም መልሶ አንድ ጊዜስ ተው አለው አንድ ጊዜ ቢጠመቅ ሁለተኛ በፈቃድ ቢጠመቅ በግድ በሰውነቱ ቢጠመቅ በአምላክነቱ መጠመቅ አያሻውምና፡፡

 

እስመ ከመዝ ተድላ ውእቱ ለነ ይህ ለኛ ተድላ ደስታችን ነውና አንተ መጥምቀ መለኮት ተብለህ ክብርህ ይነገራልና እኔም በአገልጋዩ እጅ ተጠመቀ ተብየ ትሕትናየ ሲነገር ይኖራልና ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኵሎ ጽድቀ ትንቢተ ነቢያትንም ልንፈጽምይገባናልና፡፡

 

ዮሐንስ እንዲያጠምቅ ጌታ እንዲጠመቅ ትንቢት ተነግሯልና ዳግመኛም ይህ ለምእመናን ተድላ ነውና እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት ዳግመኛም ይህ ለባሕርይ አባቴ ለአብ ለባሕርይ ልጁ ለኔ ለባሕርይ ሕይወቴ ለመንፈስ ቅዱስ ተድላ ለነ ተድላ ደስታችን ነውና አብ በደመና ሁኖ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ብሎ ሲመሠክር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ይገለጣልና የጀመርነውንም የቸርነት ሥራ ልንፈጽም ይገባናልና ወእምዝ ኀደጎ ከዚህ በኋላ ተወው፡፡

 

ስመ አብ ብከ ወስመ ወልድ ለሊከ ወስመ መንፈስ ቅዱስ ህልው ውስቴትከ ባዕደ አጠምቅ በስምከ ወበስመ መኑ አጠምቅ ኪያከ አብ በአንተ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፡፡ አንተም በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነህ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በአንተና በአብ ህልው ነው፡፡ ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለው አንተን በማን ስም ላጥምቅህ ቢለው ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጼዴቅ ብለህ አጥምቀኝ አለው ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደባሕር ወርደዋል፡፡

 

ወተጠሚቆ እግዚእ ኢየሱስ ሶቤሃ ወጽአ እማይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ከውሃው ወጣ ጥምቀቱን በውሃ ያደረገው በሌላ ያላደረገው ስለምንድን ነው ቢሉ ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም ትንቢት ወእነዝሐክሙ በማይ ወትነጽሑ ተብሎ ተነግሯል ምሳሌ ውሃ ለሁሉ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለውሃ መኖር የሚችል የለም፡፡ ጥምቀትም ለሁሉ የሚገባ ነው ያለጥምቀት ወደእግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይቻልምና ውሃ መልክ ያሳያል መልክ ያለመልማል ጥምቀትም መልክዐ ነፍስ ያሳያል መልክዐ ነፍስ ያለመልማልና፡፡

 

ወናሁ ተርኅወ ሎቱ ሰማይ ሰማይ ተከፈተለት አሁን በሰማይ መከፈት መዘጋት ኑሮበት አይደለም የተዘጋ በር በተከፈተ ጊዜ በውስጡ ያለው እቃ እንዲታይ ከዚህ በፊት ያልተገለጸ ምሥጢር ተገለጸ ሲል ነው ይኸውም የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ነው፡፡

 

ወርእየ መንፈሰ እግዚአብሔር እንዘ ይወርድ ከመ ርግብ ወነበረ ላዕሌሁ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥበት አየ፡፡ መንፈስ ቅዱስን ርግብ አለው፡፡ ርግብ ኃዳጊተ በቀል ናት፡፡ መንፈስ ቅዱስም ኃዳጌ በቀል ነውና፡፡ ርግብ በኖኅ ጊዜ ሐጸማየ አይኅ ነትገ ማየ አይኅ ስትል ቆጽለ ዕፀ ዘይት ይዛ ተገኝታለች፡፡ መንፈስ ቅዱስም ተስፋ መስቀልን ያበሥራልና ፡፡ ጥምቀቱን በቀን ያላደረገው በሌሊት ያደረገው ስለምን ነው ቢሉ በቀን አድርጎት ቢሆን መንፈስ ቅዱስ በቁሙ ርግብ ነው፡፡ በተባለ ነበርና አሁንስ ርግብ አለመሆኑ መንፈስ ቅዱስ መሆኑ በምን ይታወቃል ቢሉ ጌታ የተጠመቀ ከሌሊቱ በአሥረኛው ሰዓት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ተሐዋስያን ወፎች ርግቦች ከየቦታቸው አይወጡምና ርግብ አለመሆኑ መንፈስ ቅዱስ መሆኑ በዚህ ይታወቃል፡፡

 

መንፈስ ቅዱስም መውረዱ ከውሃው ከወጣ ከዮሐንስ ከተለየ በኋላ ነው ከውሃው ሳለ ወርዶ ቢሆን ለቀድሶተ ማያት የወረደ ነው ባሉት ነበርና ከዮሐንስ ጋርም ሳለ ወርዶ ቢሆን ለክብረ ዮሐንስ የወረደ ነው ባሉት ነበርና ረቦ ወርዷል ያሉ እንደሆነ አብ ምሉዕ ነው አንተም ምሉዕ ነህ እኔም ምሉዕ ነኝ ሲል፡፡ አሰይፎ ወርዷል ያሉ እንደሆነ የብሉየ መዋዕል የአብ ሕይወት ነኝ የአንተም ሕይወት ነኝ እኔም ብሉየ መዋዕል ነኝ ሲል ወርዶ ራሱን ቆንጠጥ አድርጎ ይዞታል ቢሉ አብ አኃዜ ዓለም ነው፡፡ አንተም አኃዜ ዓለም ነህ እኔም አኃዜ ዓለም ነኝ ሲል ምሥጢሩ ግን እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት አብነትለመሆን ነው፡፡

 

ወናሁ መጽአ ቃል እምሰማይ ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ ለተዋሕዶ የመረጥኩት በሱ ህልው ሁኜ ልገለጥበት የወደድኩት የባሕርይ ልጄ ይህ ነው የሚል ቃል ከወደሰማይ ተሰማ፡፡ይህም አብ የተናገረበት ቃል ያው የሚጠመቀው አካላዊ ቃል ነው እንጅ ሌላ ቃል አይደለም የሥላሴ ልብ ቃል እስትንፋስ አንድ ነውና አብ ልብ ወልድ ቃል መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ በመሆን አንድ አምላክ ነውና አብኒ ልቡናሆሙ ለወልድ ወለመንፈስ ቅዱስ ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ ወመንፈስ ቅዱስኒ እስትንፋሶሙ ለአብ፡ወለወልድ አብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ልቡናቸው ነው ወልድም ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው መንፈስ ቅዱስም ለአብ ለወልድ ሕይወታቸው ነው ሲል ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት እንደተናገረው ነው፡፡

ከበዓለ ጥምቀቱ ረድኤት በረከት ይክፈለን

 

“ወኩኑ ታቦተ መንፈሳዌ ለክህነት ቅድስት ወንጽሕት፤ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ” /፩ኛ ጴጥ. ፪፥፭/

 

 

ታኅሣሥ 14ቀን 2007 ዓ.ም.

መምህር ኅሩይ ባዬ

የዲያቆናት አለቃ የመጀመሪያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በሠላሳ አምስት ዓመተ ምሕረት በድንጋይ ተወግሮ ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡ ያን ጊዜም በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነው ክርስቲያን የሆኑ የአይሁድ ወገኖች ተበተኑ፡፡

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም መከራ ውን ሳይሠቀቁ እምነታቸውን ጠብቀው በሃይ ማኖት እንዲጸኑ በስድሳ ዓመተ ምሕረት መጀ መሪያይቱን መልእክት ለተበተኑ ምእመናን ጽፎላ ቸዋል፡፡

 

ወኩኑ ታቦተ መንፈሳዌ ለክህነት ቅድስት ወንጽሕት፤ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈ ሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ ሲል ሰማያዊ ጥቅም ከማያሰጥ ከክህነተ ኦሪት በተለየ ለክህነተ ወን ጌል መንፈሳዊ ማደሪያ ለመሆን ተዘጋጁ ማለቱ ነው፡፡ ቅድስት ማለቱም ምሳሌያዊ ከሆነው የኦ ሪት ክህነት ተለይቶ አማናዊ ክህነትን ለመ ያዝ የእግዚአብሔር ማደሪያ መንፈሳዊ ቤት ሆኖ መሠራት ስለሚያስፈልግ “ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ” እያለ ይጽፋል፡፡

 

በዚህ ትምህርታዊ ስብከት ካህን የሚለውን ቃል በመተርጐም የካህናትን ተልእኮ በማመልከት የሓላፊነቱን ታላቅነትና ክቡርነት እንመለከታለን፡፡ በሁለተኛው ክፍልም ክህነት ከእግዚአብሔር የተቀበልነው፣ የታደልንለት እና የተጠራንለት አደራ በመሆኑ ሥልጣነ ክህነታችንን ጠብቀን ራሳችንን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን፣ እምነታችንን፣ እና ምእመናንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን እንማራለን፡፡

 

“ተክህነ” የሚለው ቃል ተካነ አገለገለ ክህነትን ተሾመ /ተቀበለ/፤ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ቆሞ ለማገልገል ካህን ተባለ የሚለውን ትርጓሜ ያመለክታል፡፡ “ክሂን” ከሹመት በኋላ ማገልገልን፤ “ተክህኖ” ከማገልገል በፊት መሾምን የሹመትን ጊዜ የተቀበሉበትን ዕለትና ሰዓት ያሳያል፡፡

 

ክህነት ቢልም መካን ማስካን ካህንነት ተክኖ ማገልገልን ያሳያል፡፡ ካህን የሚለውን ቃል ሶርያ ውያን “ኮሄን”፣ ዕብራውያን “ካህን”፣ ሲሉት ዐረ ቦች ደግሞ ካህና በማለት ይጠሩታል፡፡ ካህን የሚ ለውን ቃል በቁሙ ቄስ ጳጳስ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሕዝብ መሪ አስተማሪ መንፈሳዊ ሀብት ብለው አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይተረጉሙ ታል፡፡

 

እነዚህን የመዝገበ ቃላት ትርጓሜዎች እንደ ዋልታ አቁመን ጠቅላላ ትርጓሜ መስጠት ይቻ ላል፡፡ ክህነት “ተክህነ” አገለገለ ከሚለው የግእዝ ግስ ይወጣል፡፡ ክህነት የሥልጣኑ ስም ሲሆን አገልጋዮቹ ካህናት ይባላሉ፡፡ ክህነቱ የሚገኝበት መንፈሳዊ ምሥጢርም ምሥጢረ ክህነት ይባላል፡፡ በሚታይ የአንብሮተ እድ አገልግሎት የማይታይ የሥልጣነ ክህነት ሐብት ይገኝበታልና ምሥጢር የተባለበት ምክን ያትም በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ስለሚገኝበት ሲሆን ምሥጢረ ክህነትን የጀመረው /የመሠረተው/ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

 

በክቡር ደሙ የዋጃትንና የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን እንዲያገለግሉ ካህናትን የለየ፣ የጠራና የሰየመ አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ከትንሣኤው በኋላ የመነሣቱን አዋጅ ለማብሰር ወደ ዓለም ሲላኩ በክህነታቸው ታላላቅ ተአምራትን አድርገዋል፡፡ /ማር. ፲፮፥፲፮/ ያስሩም ይፈቱም ነበር፡፡ /ማቴ. ፲፰፥፲፰/ ይህ የማሰርና የመፍታት ሥልጣን እስከ ኅልፈተ ዓለም የሚቀጥል መሆኑን አምላካችን በቅዱስ ወንጌል አስተም ሯል፡፡ /ማቴ. ፳፰፥፳/

 

ክህነት በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ሦስት ደረጃዎች አሉት፡፡ እነርሱም ዲያቆን፣ ቄስ፣ ኤጲስ ቆጶስ በመባል ይታወቃሉ፡፡ የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አግናጥዮስ እነዚህን ሦስት የክህነት ደረጃ ዎች እንዲህ በማለት ገልጿቸዋል፤ “ለእግዚአብሔር የሚገባችሁን ሁሉ ለማድረግ ፍጠኑ፤ የሚመ ራችሁ ኤጲስ ቆጶስ የእግዚአብሔር እንደራሴ ነው፡፡ ቄሱም እንደሐዋርያት ዲያቆናትም ለክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ባለአደራዎች ናቸውና”

 

በሌላ አገላለጥ ከሦስቱ ጾታ ምእመናን /ወንዶች፣ ሴቶችና ካህናት/ አንዱ ካህን ነው፡፡ ካህን ከወንዶችና ከሴቶች ምእመናን በተለየ ከፍ ያለ ሓላፊነት አለው፡፡ ይህ ሓላፊነት ምድ ራዊ ሳይሆን ሰማያዊ፤ ሥጋዊ ሳይሆን መንፈ ሳዊ ሓላፊነት ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ አንድ ወጣት ቅስና ለመቀበል ፈልጐ ወደ እርሳ ቸው ሔደ፡፡ ቅዱስነታቸውም አሁን የምሰጥህ የክ ህነት ሥልጣን ሹመት ሳይሆን ሓላፊነት ነው በማለት ተናግረዋል፡፡

 

ሹመት ደረት ያቀላል፤ ሆድን ይሞላል፤ ሓላ ፊነት ግን ያሳስባል፣ ያስጨንቃል፣ እንቅልፍ ያሳ ጣል፣ ክህነት ሓላፊነት በመሆኑ አንድ ካህን ሳይ ታክትና ሳይሰለች በጸሎት በጾምና በስግደት ስለ ራሱ ኃጢአት እና ስለ መንፈሳዊ ልጆቹ ክርስቲ ያናዊ ሕይወት ስለሚጨነቅ ምንጊዜም ቢሆን ዕረ ፍት የለውም፡፡ አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ግልገሎቼን አሠማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሠማራ” /ዮሐ. ፳፩፥፲፮/ ብሎ ለካህናት የኖላዊነትን ሓላፊነት የሰጠበት የአደራ ቃልም እንደዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡

 

 

ካህን ካህን ከመሆኑ አስቀድሞ ምእመናንን የማስተማር ብቃቱ፣ ቤተሰቡን የመምራት ችሎ ታው፣ የአንድ ሴት ባል መሆኑ፣ ቤተሰባዊ ሓላፊ ነቱን የመወጣት አቅሙ፣ ልጆቹን የማስተዳደር ክሂሎቱ እና ከሰዎች ጋር ያለው የሠመረ ግንኙ ነቱ ጤናማ ሊሆን እንደሚገባ ቅዱሳት መጻሕ ፍት ያስረዳሉ፡፡

 

ካህን ከሕይወቱ ሊያስወግዳቸው የሚገቡ ክፉ የሆኑ ጠባያትም በመጽሐፍ ተዘርዝረዋል፡፡ ካህን ለብዙ የወይን ጠጅ የማይጎመጅ /የማይ ሰክር/፣ በሁለት ቃል የማይናገር፣ ከፍቅረ ንዋይ የራቀ፣ አጥብቆ ገንዘብን የማይወድ፣ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚጠብቅ፣ ግልፍተኛ ያልሆነ፤ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በአንጻሩም ትሑት፣ የማይጋጭ፣ ይቅር የሚል፣ ትዕግሥተኛ የሆነ እንደሆነ ለሚመራቸው ምእመናን ትክክለኛ አርአያ መሆን ይችላል፡፡

 

ካህናት በሐዋርያት መንበር ተቀምጠው የማሠርና የመፍታትን ሓላፊነት ይወጣሉ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደጻፈልን “ካህናት በምድር የፈጸሙትን ጌታ በሰማይ ያጸናላቸ ዋል፤ የባሮቹን /የካህናትን/ አሳብ ጌታ ይቀበለ ዋል” በመሆኑም ካህናት በምድር ላይ የሚፈጽሙአ ቸውን ምሥጢራት እግዚአብሔር በሰማያዊ ምሥ ጢር ተቀብሎ ያከብራቸዋል፡፡
ኤጲስ ቆጶሳት መዓርገ ክህነቱን ለሚመለከ ታቸው ወገኖች ከመስጠታቸው በፊት የቅድ ሚያ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ፤ ምእመናንም በጉዳዩ ላይ አሳብና አስተያየታቸውን ለኤጲስ ቆጶሱ ቢናገሩ መልካም እንደሆኑ የሚደነግጉ መጻ ሕፍት አሉ፡፡ ስለሆነም

 

ካህኑ ከመሾሙ በፊት፡

 

1. የሃይማኖትን ምሥጢር ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆን እንዳለበት ሐዋርያት በጉባኤ ኒቅያ ደንግገዋል፡፡ /ጉባኤ ኒቅያ ፫፻፳፭ ቀኖና ፲፱/
2. አዲስ አማኒ ያልሆነ /ጉባኤ ኒቅያ ፫፻፳፭ ቀኖና ፪-፱/
3. የመንፈስ ጤንነት ያለው /የሐዋ. ቀኖና ፸፰/
4. ዕድሜው ከሠላሳ ዓመት ያላነሰ፤ ሊሆን እንደ ሚገባ /ስድስተኛው ሲኖዶስ ቀኖና ፲፫/ በግልጥ ያስቀምጣል፡፡

 

የካህናት ተልእኮ

 

የኤጲስ ቆጶሳት ተልእኮ ቀሳውስትን እና ዲያቆናትን ይሾማሉ፣ ያስተምራሉ፣ ያጠምቃሉ፣ ያቆርባሉ፡፡ በሀገረ ስብከታቸው ያሉት ምእመናን ማኅበራዊና መንፈሳዊ ችግር ሲደርስባቸው ይመክ ራሉ፣ ያጽናናሉ “ሕዝቡን ጠዋትና ማታ ለነግህና ለሠርክ ጸሎት በቤተ ክርስቲያን ይገኙ ዘንድ” ያዝዟቸዋል፡፡

 

የቀሳውስት ተልእኮ፡- እንደ ኤጲስ ቆጶሱ ያስተ ምራሉ፤ ያጠምቃሉ፣ ያቆርባሉ፡፡

 

የዲያቆናት ተልእኮ፡– ለኤጲስ ቆጶሱና ለካህኑ ይላላካሉ፤ ምሥጢራትን ግን የመፈጸም ሓላፊነት የላቸውም፡፡
ከእነዚህ መሠረታዊ የክህነት ደረጃዎች ሌላ በቤተ ክርስቲያን የሚታወቁ መዓርጋት አሉ፡፡ እነርሱም ንፍቅ ዲያቆን፣ አንባቢ /አናጉንስጢስ/ መዘምር፣ ኀፃዌ ኆኅት /በረኛ/ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ንፍቅ ዲያቆን ዋናውን ዲያቆን ይረዳል፡፡ አንባቢ /

 

አናጉንስጢስ/ በቅዳሴ ጊዜ መልእክታትን ያነብ ባል፡፡ መዘምር ደግሞ የመዝሙር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ኀፃዌ ኆኅት ቤተ ክርስቲያንን ይጠር ጋል፣ ያጸዳል፣ ያነጥፋል፣ ደወል ይደውላል፣ በጸሎት ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ይከፍታል ይዘጋል፡፡
ከእነዚህ የተቀብዖ ስያሜዎች ውስጥ ፓትር ያርክ የሚባለው መዓርግ ከሊቃነ ጳጳሳት መካከል ለአንዱ በፈቃደ እግዚብሔር በምርጫ ይሰየ ማል፡፡

 

ይህ የመዓርግ ስም የተጀመረው በአምስተ ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን በዚህ የመዓርግ ስም ይጠሩ የነበሩት የሮም፣ የእስክንድርያና የአን ጾኪያ ታላላቅ ከተሞች አባቶች /መጥሮ ፖሊሶች/ ነበሩ፡፡ በኋላ ግን ራሳቸውን ችለው የሚተዳደሩ አገሮች ሁሉ የየራሳቸውን ፓትርያርክ ሹመዋል፡፡ ፓትርያርክ ማለት በግሪኩ ቋንቋ ርእሰ አበው /አባት/ ማለት ነው፡፡

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስ ቲያን ሥርዐት ሦስቱ ዐበይት የክህነት መዓርጋት ዲቁና ቅስና ኤጲስ ቆጶስ ናቸው፡፡ ንፍቀ ዲቁና አንባቢ፣ መዘምርና ኀጻዌ ኆኅት በመባል የሚታ ወቁት አራቱ ንኡሳን መዓርጋት በአገልግሎት ውስጥ በግልጽ የሚታዩና በዲቁና ወስጥ የሚጠ ቃለሉ መዓርጋት ናቸው፡፡
ሥልጣነ ክህነት የነፍስ ሕክምና አገልግሎት በመሆኑ ልዩ ጥንቃቄና ክብካቤ ያሻዋል፡፡ ሥልጣነ ክህነት በዘመድ፣ በዘር፣ በአገር ልጅነት በገንዘብ አይሰጥም፡፡ ለመሾም ተብሎም እጅ መንሻ መስ ጠትና መቀበል ፈጽሞ የቤተ ክርስቲያን ትው ፊት፣ ሥርዐትና ቀኖና አይደለም፡፡

 

የካህናትን ክብር ካስተማሩን አበው መካከል አንዱ ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው “ኦ ካህናት አንትሙ ውእቱ አዕይንተ እግዚአብሔር ብሩሃት ተናጸሩ በበይናቲክሙ አሐዱ ምስለ ካልዑ፤ ካህ ናት ሆይ ብሩሃን የእግዚአብሔር ዓይኖች እናንተ ናችሁ እርስ በርሳችሁ አንዱ ካንዱ ጋራ /ተያዩ/ ተመለካከቱ” ይላል፡፡ ይህም በችግሮቻችን ዙርያ መወያየት፤ መነጋገርና መደማመጥ የሚያስፈልግ መሆኑን ያስረዳናል፡፡

 

“የኩነኔ አገልግሎት ክብር ከሆነ ይልቅ የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣልና” /፪ኛ ቆሮ. ፫፥፱/ እንዳለው ሐዋርያው የክህነት አገልግሎት የተለየ እና ክቡር መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ክህ ነት ከእግዚአብሔር የተገኘ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔርም የሚያደርስ ታላቅ መሰላል ነው፡፡

 

የሥርዐተ ጥምቀት፤ የሥርዐተ ቁርባን፤ የሥርዐተ ተክሊልና የምሥጢረ ንስሐ መፈጸሚያና ማስፈጸሚያ መንፈሳዊ መሣሪያ ሥልጣነ ክህነት መሆኑን ስንረዳ የምንሰጠው ክብርም የተለየ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ “ወወሀቦሙ ሥልጣነ ዘከማሁ ይእስሩ ወይፍትሑ ኲሎ ማእሠረ አመጻ፤ እንደ እርሱ የኃጢአትን ማሠሪያ ያሥሩና ይፈቱ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” /ዮሐ. ፳፥፳፪-፳፫/ መዓርጉ ክቡር በመሆኑ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ክቡር የሆነውን ክህነት አክብረን እንድንከብርበት መለኮ ታዊ ኃይሉ ይርዳን፡፡

 

 

St.Mary

ጼዴንያ ማርያም

መስከረም 9 ቀን 2007 ዓ.ም.

St.Mary“ሰላም ለሥዕልኪ እንተ ሠዓላ በእዱ፡፡ ሉቃስ ጠቢብ እምወንጌላውያን አሐዱ፡፡ አመ ተቀብዑ ማርያም እምሐፈ ሥዕልኪ ቅብዐ ናርዱ፡፡ በሕማም እኩይ እለ ደወዩ ወውሕዱ፡፡ ፅዑራነ ዓለም ጥዕዩ ወጥቀ ፈድፈዱ፡፡” አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ዐሥር በዚች ቀን ጼዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ተአምር ተገለጠ፡፡

ይቺንም ሥዕል የሣላት ወንጌላዊ ሉቃስ ነው፡፡ ወደ ጼዴንያ አገርም የመጣችበት ምክንያት አንዲት ስሟ ማርታ የሚባል መበለት ሴት ነበረችና ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች ናት አምላክን የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያምንም እጅግ ትወዳት ነበር፡፡ በሚቻላትም ሁሉ ታገለግላታለች፡፡

በአንዲት ቀንም ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል መነኲሴ ከእርሷ ዘንድ እንግድነት አደረ በመልካም አቀባበልም ተቀበለችው በማግሥቱም ስትሸኘው አባት ሆይ የምትሔደው ወዴት ነው አለችው፡፡ እርሱም በከበሩ ቦታዎች ውስጥ ልሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም እሔዳለሁ አላት እርሷም ከአኔ ገንዘብ ወስደህ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል ግዛልኝና በመመለሻህ ጊዜ አምጣልኝ አለችው፡፡ እርሱም በራሴ ገንዘብ ገዝቼ አመጣልሻለሁ አላት፡፡

ከዚህም በኋላ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከቅዱሳት መካናት ተባረከና ሥዕሏን ሳይገዛ ወደ ጐዳናው ተመለሰ፡፡ ያን ጊዜም ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰማ ወደ ገበያም ተመልሶ ላሕይዋና መልኳ ያማረና የተወደደ የሆነ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል አግኝቶ ገዛት በሐርና በንጹሕ ልብስም ጠቀለላት፡፡

በጐዳናውም እየተጓዘ ሳለ ከማያስፈራ ዱር ውስጥ ወንበደዎች ተነሡበት ሊሸሽም ወደደ ከዚያቺም ሥዕል መንገድህን ሒድ የሚል ቃል ወጣ የተከተለውም ሳይኖር መንገዱን ተጓዘ፡፡ ሁለተኛም ነጥቆ ሊበላው አንበሳ ተነሣበት ያን ጊዜም ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረው፡፡

አባ ቴዎድሮስም ይህን ሁሉ ድንቅ ተአምር በአየ ጊዜ ያቺን ሥዕል ወደ አገሩ ሊወስዳት ወደደ ግዛልኝ ላለችው መበለት ይሰጣት ዘንድ አልፈለገም፡፡ ከዚህም በኋላ በመርከብ ተሳፍሮ በሌላ አቅጣጫ ሲጓዝ ታላቅ ነፋስ ተነሣበት ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያም ወሰደው ከመርከብም ወርዶ ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ሔደ ማንነቱንም አልገለጣላትም እርሷም አላወቀችውም፡፡

በማግሥቱም ተሰውሮ ወጥቶ ወደ አገሩ ሊሔድ በፈለገ ጊዜ የቅጽሩን ደጃፍ አጥቶ ሲያጥመሰምስ ዋለ በመሸ ጊዜም ወደ ማደሪያው ተመለሰ፡፡ ያቺም መበለት በአየችው ጊዜ ታደንቃለች እንዲህም ሁኖ እስከ ሦስት ቀን ኖረ በመሸ ጊዜ በሩን ያየዋል ነግቶ መሔድን ሲሻ የበሩ መንገድ ይሠወረዋል፡፡ ያቺም መበለት ያዝ አድርጋ አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን ስትቅበዘበዝ አይሀለሁና ምን ሁነህ ነው አለችው፡፡

ከዚህም በኋላ ከዚያች ሥዕል የሆነውን ሁሉ ነገራት ራሱንም ገለጠላት፡፡ ያቺንም ሥዕል ሰጣት ተቀብላም የተጠቀለለችበትን ልብስ ፈታች ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች፡፡ ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የዚያን መነኲሴ እጆቹንና እግሮቹን ሳመች፡፡

ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር የምትቀመጥበትን አዘጋጅታ አኖረቻት ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት በቀንና በሌሊትም የሚበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች ከመቅረዞም ውጭ የሐር መጋረጃን ጋረደች፡፡ ከሥዕሊቱ በታችም ከሥዕሊቱ እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች ያም መነኰስ እስከሚሞትበት ቀን ድረስ የእመቤታችንን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገለ ኖረ፡፡

የሀገሩም ሊቀ ጳጳሳት የዚያችን ሥዕል ዜና በሰማ ጊዜ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከካህናት ከሕዝቡም ሁሉ ጋር መጣ፡፡ በሠሌዳዋም ውስጥ በአዩዋት ጊዜ ሥጋ የለበሰች ሁና አገኙዋት ከዚህ ከአምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ ከዚያም ቅባት ቀድተው ለበረከት በተካፈሉ ጊዜ ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ ይመላል፡፡

ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜ ንውጽውጽታ ሁኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ በዚያች አገር ትኖራለች፡፡ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእናቱ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡

  • ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ከመስከረም እስከ የካቲት

 

የ2007 አጽዋማትና በዓላት

ጳጉሜን 5 ቀን 2006 ዓ.ም.

  • መስከረም 1 ሐሙስ፣

  • ነነዌ ጥር 25፣

  • ዓብይ ጾም የካቲት 9፣

  • ደብረ ዘይት መጋቢት 6፣

  • ሆሣዕና መጋቢት 27፣

  • ስቅለት ሚያዚያ 2፣

  • ትንሣኤ ሚያዚያ 4፣

  • ርክበ ካህናት ያዚያ 28፣

  • ዕርገት ግንቦት 13፣

  • ጰራቅሊጦስ ግንቦት 23፣

  • ጾመ ሐዋርያት ግንቦት 24፣

  • ምሕላ ድኅነት ግንቦት 26፣

Emebetachin-Eriget

“አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” /መዝ.131፥8/

ነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

Emebetachin-Erigetሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሐ ምጡቀ ፤ በአእባነ ባህርይ ዘተነድቀ ፤ማርያም ደብተራ እንተ ኢትትከደኒሠቀ፤እመቤቴ ማርያም ሆይ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል ፡፡ ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት በማይቻል ዕንቊ የታነፀ ሕንፃ ይገኝበታል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አዳም አባታችን እግዚአብሔርን በድሎ፣ ክብሩን አጥቶ፣ ሞተ ሥጋ ሞተ ነብስ ተፈርዶበት፣ ከገነት ሲባረር ፤ ምህረትና ቸርነት የባህሪው የሆነው አምላክ ይቅር ይለው፣ ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ ተማጽኗል፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የአዳምን ማዘን፣ መጸጸት ፣ ንስሀ መግባት ተመልክቶ 5500 ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ስደትህን በስደቴ፣ ሞትህን በሞቴ አጥፍቼ የቀደመ ክብርህን መልሼ ያጣኸውን ርስት ገነት መንግስተ ሰማያት አወርስሃለሁ፡፡ገላ4፡4 በማለት ቃል ኪዳን ገብቶለታል፡፡

አዳም አባታችን ቃል ኪዳን በተገባለት መሠረት የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ለእግዚአብሔር ወልድ ማደሪያነት የተመረጠች፣ ለአዳም እና ዘሩ መዳን ምክንያት የሆነች የልጅ ልጅ የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዳ 15 ዓመት ሲሆናት በቅዱስ ገብርኤል ብስራት የእግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ማደሪያ ሆነች፡፡ ልጇን በወለደች ወቅት የሰብዓ ሰገልን “የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት አለ” የሚለውን ዜና የሰማ ሄሮድስ የተወለደውን ህጻን ለመግደል አዋጅ አወጀ ፡፡ እመቤታችንም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማዳን ወደ ግብጽ ይዛው ተሰደደች ማቴ.2፡12፡፡

የስደት ዘመኑ አልቆ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ 30 ዘመን ሲሆነው ስለመንግስተ እግዚአብሔር ስለ ሰው ልጆች ነጻነት ይሰብክ ጀመር፡፡ ኃላም የአዳም ዘር ሞት ለማጥፋት ፣ባርነትን አጥፍቶ ነጻነትን ለማወጅ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ ፡፡ በሦስተኛው ቀን ተነስቶ ነጻነትን አወጀ፡፡ በዚህ ሁሉ የድኅነት ጉዞ ውስጥ ያልተለየችና ምክንያተ ድኂን የሆነችው እመቤታችን የሰው ልጆች ድኅነት ሲረጋገጥ በተወለደች በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን አረፈች፡፡

a ergete mariam 2006 1ሐዋርያት መጽናኛቸው እናታቸው ቅድስት ድንግል ማርያም ብታርፍባቸው ሥጋዋን ባጎበር አድርገው ወደ ጌቴ ሴማኒ ይዘዋት ሄዱ አይሁድ “ቀድሞ ልጇን ሰቅለን ብንገድለው ደቀ መዛሙርቱ ተነሣ፣ ዐረገ” እያሉ ሲያውኩን ኖሩ፤ ዛሬ ደግሞ እርሷን ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? በእሳት እናቃጥላታለን” ብለው ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል የታውፋንያን ሁለት እጁን በሰይፍ መትቶ ቀጣው፡፡ በዚህም የታውፋንያ ሁለት እጁ ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ፡፡

ከዚያ በኋላ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌላዊውን ቅዱስ ዮሐንስ ጨምሮ በደመና ነጥቆ ከገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት፡፡ዮሐንስ ከገነት ሲመለስ ለሐዋርያት “ የእመቤታችንን ሥጋ ወደ ገነት መወሰድ ነገራቸው፡፡ “ዮሐንስ የእመቤታችንን ሥጋ ገነት ማረፍ አይቶ እኛ ሳናይ” ብለው፤ ከነሐሴ 1 ቀን – ነሐሴ 14 ቀን ጾመዋል፡፡ “ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሓ ወኑዛዜ፡ ኀበ ኢይሬእይዎ ለላህ ወኢይሔይልዎ ለትካዜ፡ ማርያም ህሉት ዉስተ ልበ ኣምላክ እምቅድመ ግዜ፡ ትፍሥሕትሰ ተፈሣሕኩ ብፍልሰትኪ ይእዜ፣ ገጸ ዚኣኪ እሬኢ ማዕዜ”ይላል መልክዓ ፍልሰታ፡፡

እግዚአብሔር ሀዘናቸውን ተመልክቶ መጽናናትን ይሰጣቸው ዘንድ ከነሐሴ 1 ቀን -ነሐሴ 14 ቀን ሐዋርያት በአንድ ልብ ሆነው ሱባኤ ያዙ (በጾም በጸሎት ተወስነው ) እግዚአብሔርም የልብ መሻታቸውን አይቶ ነሐሴ 14 ቀን ጌታ የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከዕፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ሐዋርያት ገንዘው በክብር ቀብረዋታል፡፡ ስለ ግንዘቷም “ሰላም ለግንዘተ ሥጋኪ ብእደ ሓዋርያት ኣርጋብ፤ ብአፈወ ዕፍረት ቅዱው ዘሐሳብ ሴቱ ዕጹብ፤ ማርያም ድንግል ውለተ ህሩያን ሕዝብ፤ ረሰይኩኪ እግዝእትየ ህየንተ እም ወኣብ፤ ይኅጽነኒ ከመ ጥብ ፍቅርኪ ሓሊብ።” ያለው ለዚህ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ በዝማሬ ድርሰቱ “በስብሐት ውስተ ሰማያት መላእክት ወሊቃነ መላእክት ወረዱ ለተቀብሎታ፣ እብለኪ ወእሙ ለእግዚእየ እብለኪ ዳዊት አቡሃ ምስለ መሰንቆሁ ሙሴኒ እንዘ ይፀውር ኤፉደ መጽኡ ሃቤሃ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ሐዋርያት አጠኑ ሥጋሃ በማዕጠንተ ወርቅ፣ ሱራፌል ወኪሩቤል ሰፍሑ ከነፊሆሙ ላዕሌሃ፣ ወረደ ብርሃን እምሰማያት ወመብረቀ ስብሐት እምውስተ ደመናት፣ ተለዓለት እምድር ውስተ አርያም በስብሐት ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ” ብሏል፡፡

ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማዕታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡ ንጉሥ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እንዳለ /መዝ 44¸9/፡፡ ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፡፡ ሐዋርያት ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋም በታላቅ ክብር ማረጉን ነገራቸው፡፡

መላእክትና ሊቃነ መላእክት ቅዱስ ሥጋዋን ለማሳረግ በታላቅ ምሥጋና ከሰማይ ወረዱ፤ አባቷ ዳዊት ከመሰንቆው ጋር ሙሴም የአገልግሎት ልብሱን ለብሶ፣ ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስም ወደ እርሷ መጡ ሥጋዋንም በወርቅ ማዕጠንት አጠኑ፡፡ ሱራፌልና ኪሩቤልም በላይዋ ክንፎቻቸውን ዘረጉ /ጋረዱ/፡፡ ከሰማያት ብርሃን የምስጋና መብረቅም ከደመናት ውስጥ ወጣ፡፡ ከምድር ወደ ሰማያት በምስጋና ከፍ ከፍ አለች ከልጇ ጋርም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች” ማለት ነው፡፡ ይህም “በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች፡፡” መዝ.44፥9 ተብሎ የተነገረላትን ቃለ ትንቢት የተፈጸመላት መሆኑን ያመለክታል፡፡

ከሐዋርያት ወገን የሆነው ቅዱስ ቶማስ ለወንጌል አገልግሎት ሄዶ በወቅቱ አልነበረም፡፡ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሕንድ ሲመጣ ስታርግ አገኛት፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” ይላል፤ ተበሳጨ፡፡ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁኝ” አለ፡፡ በዚህ ጊዜ የልቡናን ሐዘን የምታቀል እመቤታችን፡- አይዞህ አትዘን እኒያ ትንሣኤዬን ዕርገቴን አላዩም፡፡ አንተ አይተሃል፡፡ ተነሣች፣ ዐረገች ብለህ ንገራቸው፡፡” ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡

ከዚህ በኋላ ሄዶ፤ “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” አላቸው “ሥጋዋን አግኝተን ቀበርናት” አሉት፡፡ እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተዉ ይህ ነገር አይመስለኝም” አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ እንጂ ልማድህ ነው፡፡ አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም፤ አንተ እየተጠራጠርህ ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራለህ” አለው፡፡ እርሱም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ ይሰማቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ተቆጥቶ ሂዶ መቃብሩን ቢከፍተው የእመቤታችን ሥጋዋን አጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ደንግጦ ቆመ፡፡ ይህን ጊዜ ቅዱስ ቶማስ “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሣች ዐረገች” አላቸው፡፡

a ergete mariam 2006 2ቅዱስ ቶማስ የያዘውንም ሰበን እያሳያቸው፡- “ቅዱስ ሥጋዋን የገነዛችሁበት ጨርቅ /ሰበን/ ይህ አይደለምን” ብሎ ሰበኑን ሰጣቸው፡፡ ይህንንም ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ከዚህ በኋላ በዓመቱ “ቶማስ ትንሣኤሽን ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ በማለት ጾም ጀመሩ፡፡

በ16ኛው ቀን አምልካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ እመቤታችንን መንበር ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ ቄስ፣ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ራሱ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡ሐዋርያት ከዚህ በኋላ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በብቃት ለመወጣት ቻሉ፡፡ ይህንን ዐቢይ ምሥጢር አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ተንሥአ እግዚኦ” ውስተ ዕረፍትከ፡፡ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” /መዝ.131፡8/፡፡

“ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” /መዝ.44፡9/ ሲል በ ቅዱስ ዳዊት የተናገረው ቃለ ትንቢት በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና የጸናች የቅድስት ድንግል እመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ እንዲሁም ፍለሰት /ዕርገት/ በምሥጢር ከማሳየቱም ሌላ ወላዲተ አምላክ በልጇ በወዳጇ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት በክብርመኖሯንም ያስረዳል /ራእ.11፡19/፡፡

 

a ledeta mariam 2006 01

አድርሺኝ

ነሐሴ 12 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

a ledeta mariam 2006 01በጎንደር ከተማ በፍልሰታ ለማርያም ጾም ወቅት በካህናቱ፤ በሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና በምእመናን አማካይነት በየዓመቱ የሚከናወን የተለመደ ሥርዓት አለ፡፡ ይህም ሥርዓት “አድርሺኝ” በመባል ይታወቃል፡፡

በጎንደር ከነገሡት ነገሥታት መካከል ከ1703-1708 ዓ.ም. ለአምስት አመታት በንግሥና የቆዩት ዐፄ ዮስጦስ የጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን በመትከል የሚታወቁ ሲሆን፤ አድርሽኝ የተሠኘውንም ሥርዓት በእርሳቸው እንደተጀመረ ይነገራል፡፡

ስለ ሥርዓቱ አጀማመር አባቶች ሲናገሩ፣ ዐፄ ዮስጦስ ተቀናቃኞቻቸው የከፈቱባቸውን ጦርነት ለመመከት ወደ ጦርነት ሲዘምቱ “ልደታ ለማርያም ሳትለዪኝ በድል ብትመልሺኝ፤ ለዚህም ታላቅ ክብር ብታደርሺኝ በየዓመቱ በፍልሰታ ለማርያም ሱባኤ ካህናቱን፤ መኳንንቱንና ምእመናንን ሰብስቤ ግብዣ አደርጋለሁ” በማለት ብፅዐት ይገባሉ፡፡ እርሳቸውም ድል አድርገው በመመለሳቸው በቃላቸው መሠረት በጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ደጀ ሰላም ሕዝቡን ሰብስበው ግብዣ ማድረጋቸውን ቀጠሉ፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑም እርሳቸውን ተከትሎ በየዓመቱ በጾመ ፍልሰታ ወቅት ይህንን ሥርዓት ይተገብሩት ጀመር፤ ስያሜውም “አድርሺኝ” ተባለ፡፡

አድርሺኝ በመላው ጎንደር በየአብያተ ክርስቲያናቱና በየአካባቢው በፍልሰታ ጾም ወቅት ይከናወናል፡፡ ምእመናን ከቅዳሴ መልስ ሱባኤው እስኪጠናቀቅ በመረጡት አንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ቆሎና ጠላ አዘጋጅተው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ጽዋ ይጠጣሉ። በተለይም መነኮሳይያት እናቶች በሚታደሙበት ጽዋ ላይ “ኦ! ማርያም” የሚለውን የተማጽኖ መዝሙር ይዘምራሉ። ይህ መዝሙር በሚዘመርበት ጊዜ ያለ ምንም ጥርጥር እመቤታችን ፊት ለፊት ትቆማለች ተብሎ ስለሚታሰብ በፍጹም ተመሥጦና በመንበርከክ ያከናውኑታል።

የጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ-ኤስድሮስ ሰንበት ት/ቤት ወጥነት እንዲኖረው በማሰብ ይህንን የእናቶች የምሕላ ዝማሬ ለተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል አሰባስቦ አዘጋጅቶታል፡-

ኦ! ማርያም

ኦ! ማርያም እለምንሻለሁ ባሪያሽ፤

እስኪ አንድ ጊዜ ስሚኝ ቀርበሽ፤ ከአጠገቤ ቆመሽ፤

ፅኑ ጉዳይ አለኝ ላንቺ የምነግርሽ፤

የዓለሙን መከራ ያየሽ፤

በእናትሽ በአባችሽ ሀገር፤

በምድረ ግብፅ ዞረሽ ውሃ የለመንሽ፡፡

ከሁሉ ሁሉ ጤፍ ታንሳለች፤

ከጭቃ ወድቃ ትነሳለች፤

ስትነሳ /2/ የአዳም ልጅ ሁሉ ሞትን ረሳ፤

የአዳም ልጅ ሁሉ ሰነፈና የኑሮ ቤቱን ረሳና፤

ተው አትርሳ /2/ ተሠርቶልሃል የእሳት ሳንቃ፡፡

ያን የእሳት ሳንቃ፤ የእሳት በር፤

እንደምን ብዬ ልሻገር፤

ተሻገሩት አሉ የሠሩ ምግባር፤

እኔ ባሪያሽ እንዴት ልሁን? ሰላም ሰጊድ /2/

በመሥቀሉ ሥር ያያትን ተሰናበታት እናቱን፤

እናትዬ ለምን ታለቅሻለሽ ተሰቅዬ፤

ይስቀሉኝ ሐሰት በቃሌ ሣይገኝ፡፡

ንፅሕት የወልደ እግዚአብሔር እናት፤

ንፅህት በፍቅሯ ወዳጆቿን ስትመራ፤

ንፅሕት በቀኝ ወዳጆቿን ስትጎበኝ፤

የእኛስ እመቤት ያች ሩኅሩኅ፤

ከለላችን ናት እንደ ጎጆ፤

እርሷን ብለው ጤዛ ልሰው ኖሩ ትቢያ ለብሰው /2/

ኪዳነ ምሕረት ሩኅሩኅ ተይ አታቁሚኝ ከበሩ፤

የገነሃም እሣት መራራ ነው አሉ፤

እኔ ባሪያሽ እንዴት ልሁን? ሰላም ሰጊድ /2/

ድንግል ማርያም ንፅሕት፤

የምክንያት ድኅነት መሠረት፤

እንለምንሻለን ወደ አንቺ አንጋጠን፤

ከፈጣሪ በይ አማልጅን ሰላም ሰጊድ /2/

ኃያል /2/ ቅዱስ ሚካኤል ኃያል፤

የለበሰው ልብሱ የወርቅ ሐመልማል፤

ይህም ተጽፏል በቅዱስ ቃል ሰላም ሰጊድ /2/

ጊዮርጊስ ስልህ ዘንዶ ሰገደ ከእግርህ፤

እፁብ ድንቅ ይላሉ ገድልህን የሰሙ፤

አንተ አማልደኝ ከሥልጣኑ ሰላም ሰጊድ /2/

አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ደግ አባት፤

መጥቼልሃለሁ ከደጋ፤

ስንቄንም አድርጌ አጋምና ቀጋ፤

አንተ አማልደኝ ከፈጣሪ ሰላም ሰጊድ /2/

ፃድቅስ ባያችሁ ተክለ ሃይማኖት፤

በአንድ እግር ቆመው ሰባት ዓመት፤

በተአምኖ ሰባት ባቄላ ምግብ ሆኖት /2/

ተክለ ሃይማኖት አባቴ፤

መሠላሌ ነህ ለሕይወቴ፤

የዓለሙን ኑሮ መጥፎነቱን፤

የፈጣሪያችን ቤዛነቱን፤

አስተውለኸው አጥንተኸው፤

ደብረ ሊባኖስ የተሰዋኸው፡፡

ክርስቶስ ሠምራ እናታችን፤

ከአምላካችን ፊት መቅረቢያችን፤

ሣጥናኤልን አሸንፈሽ፤

ከግዛቱ ውስጥ ነፍስን ማረክሽ፡፡

ክርስቶስ ሠምራ ቅድስቷ፤

ለጽድቅ ሕይወት አማላጇ፤

እንለምንሻለን ወደ አንቺ አንጋጠን፤

ከፈጣሪ በይ አማልጅን ሰላም ሰጊድ /2/

ኦ! አባቴ አንተ ረኃቤ ነህ ጥማቴ፤

የኔ መድኃኒት ኃያል ተመልከተን ዝቅ በል፤

የነገሩህን የማትረሳ፤

የለመኑህን የማትነሳ፤

አምላኬ አንተ ነህ አምባዬ፤

የሕይወት ብርሃን ጋሻዬ፡፡

ማርያም ስሚን ወደ ሕይወት መንገድ ምሪን፤

ከአጠገባችን ቁጭ ብለሽ አድምጭን፤

ይደረግልን ልመናሽ ስትመጪ /2/

አንቺ እናቴ ሆይ /2/ የሔድሽበትን ትቢያ ቅሜ፤

ያረፍሽበትን ተሳልሜ፤

በሞትኩኝ /2/ የኋላ ኋላ ላይቀር ሞት፡፡ /2/

 

በፍልሰታ ለማርያም ጾም ወቅት ዘወትር ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በቤተ-ኤስድሮስ ሰንበት ት/ቤት ካለፉት 21 ዓመታት ጀምሮ ጸሎት ዘዘወትር፣ ውዳሴ ማርያም፣ ይዌድስዋ መላእክት፣ መዝሙረ ዳዊት 50 እና 135፣ ጸሎተ ምናሴ፣ መሐረነ አብ ጸሎት በዜማ ከተጸለየ በኋላ ኦ! ማርያም የምሕላ መዝሙር ይዘመራል፡፡

  • ማስታወሻ፡- መረጃውን በመስጠት የተባበሩንን ዲያቆን ሙሉቀን ብርሃኑ እና የጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ- ኤስድሮስ ሰንበት ትምህርት ቤትን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡

 

ክረምት

ነሐሴ 7 ቀን 2006 ዓ.ም.

ዕጉለ ቋዓት፥ ደስያት

ይህ ወቅት ከነሐሴ 10 እስከ ነሐሴ 27 ቀን ድረስ ያሉት 17 ዕለታት የሚጠሩበት ነው፡፡ ፍጥረታትና በባሕር የተከበቡ ደሴቶች የሚታወሱበት ጊዜ ሲሆን ወቅቱም ዕጓለ ቋዓት ደስያት ዐይነ ኩሉ ይባላል፡፡ ዕጓለ ቋዓት የሚለው ቃል ቁራን ሲያመለክት፣ ቁራ ሲወለድ ያለ ፀጉር በሥጋው ብቻ ይወለዳል፡፡

 

እናትና አባቱም እነርሱን ባለመምሰሉ ደንግጠው ይሸሻሉ፤ በዚህ ጊዜ የሚንከባከበው ሲያጣ እግዚአብሔር በረድኤት አፉን ከፍቶ ምግብ ሲሻ ተሐዋስያንን ብር ብር እየደረገ ከአፉ ያስገባለታል፡፡ “ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፥ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘብዙ፥ ለቁራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው? ” (ኢዮ.38፥41) ተብሎ እንደ ተገለጠው እግዚአብሔር የሰጠውን እየተመገበ ቆይቶ ሲጠነክር እንደ እናትና አባቱ ያለ ፀጉር ያወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ እናትና አባቱ ቀርበው ይንከባከቡታል፡፡ በሥነ ፍጥረት አቆጣጠር ግን በክንፍ የሚበሩ አዕዋፍን ሁሉ ይወክላል፡፡

 

ይህም አምላካችን እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ሁሉ የሚያስብ በመሆኑ ይህን ዘመን ርኅርሔ ለተመላው አምላክነቱ ሥራው መታሰቢያ እንዲሆን ቤተ ክርስቲያን ዕጓለ ቋዓት በማለት ታስታውሰዋለች፡፡

ደስያት ማለት በውኃ የተከበቡ ቦታዎች ማለት ነው፡፡ እነዚህን ቦታዎች በውኃ እንዲሸፈኑ አድርጎ በውስጣቸው ያሉትን ሰዎች እንስሳት አራዊት አዕዋፍ ሁሉ የሚጠብቃቸው፣ በተስፋና በእምነት አበርትቶ የሚያኖራቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህን ድንቅ ሥራ ያዩ በውስጥ በውጭ ያሉት ሰዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፡፡ በደሴት (በቤተ ክርስቲያን) የተጠጉ ሁሉ ከሞተ ሥጋና ከሞተ ነፍስ ይጠበቃሉ፡፡

በዚህ ወቅት፡- ክፍለ ክረምቱ እንደተገባደደ፥ ውኃው እየጠራ፣ መሬቱ እየረጋ፣ ደመናውና ጉሙ እየተቃለለ፣ የወንዞች ሙላት እየቀነሰ፣ የክረምት ምግባቸውን ይዘው በየዋሻው የከረሙ ጭልፊቶችን አሞራዎች ድምፃቸውን እየሰሙ ምግብ ፍለጋ ሲወጡ የሚታዩበት ወቅት ነው፡፡

በተጨማሪም ከነሐሴ 27-29 ያለው ጊዜን “ሞተ አበው” በመባል ይታወቃል፡፡ ከ22ቱ አርእስተ አበው የአብርሃም ይስሐቅና ያዕቆብ ቤተሰቦቻቸው ዕረፍት ይታሰባል፡፡ ቅዱስ መጽሐፋችንም “አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ሊሰዋ ወጣ፤ እግዚአብሔር ቤዛ አድርጎ ቀንዱ በዕፀ ሳቤቅ የተያዘ በግ አወረደለት” በማለት የአብርሃምን ታዛዥነት የይስሐቅን ቤዛነት ያወሳል፡፡ የተቀበሉትም ቃል ኪዳን “ወተዘከረ ሣህሎ ዘለዓለም ዘሠርዓ ለአብርሃም ወመሐለ ለይስሐቅ ወዐቀመ ስምዐ ለያዕቆብ ያርኁ ክረምተ ይገብር ምሕረተ እም ሰማይ ይሁብ ወእምድር በረከተ ያጸግብ ነፍስ ርኅብት” በማለት ይዘመራል፡፡

 

ፍልሰታና ሻደይ

ነሐሴ 5 ቀን 2006 ዓ.ም.

ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ በመላው ዓለም የክርስትና እምነት በሐዋርያቱ መሰበክ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሀገራችን የክርስትና እምነት ተሰብኳል፡፡  በተለይም ሀገራችን የሰሜኑ ክፍል  ህዝበ ክርስቲያኑ ለረጅም ዘመናት ሥርዓተ አምልኮ ሲፈጽምባቸው እንደነበሩና አሁንም አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ በአካባቢው የሚገኙ በርካታ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትና መንፈሳዊ ቁሶች ያስረዳሉ። እነዚህም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ መንፈሳዊ ቅርሶች ናቸው። ከማይዳሰሱ መንፈሳዊ ቅርሶች መካከል የተለያዩ መንፈሳዊ በዓላት የሚከበሩበት ሥርዓት አንዱ ነው።

asendya 01በዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ከሚከበሩ በዓላት መካከል የሻደይ ምስጋና / ጨዋታ አንዱ ሲሆን ልጃገረዶች በአማረ ልብስ ደምቀው አሸንድዬ በሚባል ቄጠማ ጉንጉን ወገባቸውን አስረው የሚያከብሩት ነው። በዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃማኖታዊ ይዘት አለው። በዓሉ ከነሐሴ 16 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 21 ቀን ድረስ ይከበራል። ይህ በዓል በዋግ ኽምራ ሻደይ፣ በላስታ አሸንድዬ፣ በትግራይ አሸንዳ፣ በቆቦ አካባቢ ሶለል፣ በአክሱም አካባቢ ደግሞ ዓይነ ዋሪ እየተባለ ይጠራል።

የሻደይ በዓል ከኦርቶዶክስ ተዋሐዶ እምነት ጋር እየተያያዘ የመጣ ሲሆን አጀማመሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ አለው፡፡ ከነዚህም መካከል የአዳም ከገነት መባረር፣ የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ፣ ከዘመን መለወጫ፣ ከመጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንገት መቆረጥ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ (ፍልስታ) እና ከመስፍኑ ዮፍታሔ ልጅ ታሪክ ጋር በማስተሳሰር የሚያስቀምጡት ሲሆን በማኅበረስቡ አባቶችና ሊቃውንቱ ዘንድ ጎልቶ የሚነገረውና የሚተረከው ግን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ (ፍልስታ) በዓልን መሠረት ያደረገ ነው።

አባታችን አዳም በገነት ሳለ ሕግ በመተላለፉ ጸጋ እግዚአብሔር ርቆት እርቃኑን በሆነ ጊዜ አካሉን ለመሸፈን ቅጠል መጠቀሙን ለማሰብ ያች አዳምና ሔዋን ክብራቸውን ተገፈው ከገነት የተባረሩባትን ዕለት በማሰብ በወቅቱ ያገለደሙትን ቅጠል በምልክትነት በመውሰድ የሻደይ ቅጠልን በገመድ ላይ ጎንጉነው በወገባቸው አገልድመው/አስረው/ አዳምና ሔዋን ከገነት ከመውጣታቸው በፊት ግብረ ሥጋ ግንኙነት ያልጀመሩ ደናግላን ስለነበሩ ያንን በመከተልና በምሳሌነት በመውሰድ ያላገቡ የአገው ልጃገረዶች ተሰባስበው ያችን ዕለት ወይም ቀን በመታሰቢያነት ለመቁጠር ወይም ለመዘከር የሻደይ ጨዋታን መጫወት ወይም ማክበር እንደጀመሩ ይናገራሉ።

ከኖኅ ዘመን ታሪክ ጋር ያለው ግንኙነት ደግሞ ከጥፋት ውኃ በኋላ ውኃው የመጉደሉን ምልክት ርግብ ለኖኅ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ በመምጣት በምድር ሰላም እነደሆነ የምሥራች አብሥራለች። ከዚሁ ጋር በተገናኘ በዓሉን ያንን ለምለም ቅጠል ወገባቸው ላይ በማሰር ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋገርን ሲሉ ማክበር እንደጀመሩ ከታሪኩ ጋር አያይዘው ያስቀምጡታል።

ከመስፍኑ ዮፍታሔ ታሪክ ጋርም ቢሆን የሻደይ በዓል እንዴት ግንኙነት እንዳለው ሲያስቀምጡ ዮፍታሔ ወደ ጦርነት በሔደ ጊዜ በድል ከተመለስ ለአምላኩ መሥዋዕትን ለማቅረብ ስዕለት ገበቶ ነበር። ይህም ከቤቱ ሲመለስ መጀመሪያ የሚቀበለውን እንደሚሠዋ ሲሆን በዚህ ጊዜ ያለ ወትሮዋ ልጁ እየዘፈነች ልትቀበለው ወጣች በዚህም በጣም አዘነ። ልጁም ለአምላኩ የገባውን ስዕለት እንዳያስቀር ሁለት ወር ስለ ድንግልናዋ አልቅሳ ስዕለቱን እንዲፈጽም ጠይቃው ከሁለት ወር በኋላ ስዕለቱን የፈጸመ ሲሆን አባቷ የገባውን ቃል ኪዳን እንዳያጥፍ ያበረታታችውንና መሥዋዕትነትን ለሀገር፣ ለህዝብ፣ ለአባትና ለፈጣሪዋ የከፈለችውን የዮፍታሔን ልጅ በየዓመቱ ለአራት ቀናት ሙሾ በማውጣት አስበው ይውላሉ፡፡ በዚህ መሠረት በበዓሉ ላይ ከሚፈጸሙ ተግበራት ጋር አዛምደው መነሻው ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደሆነ ይናገራሉ። “ጽዮንን ክበቡዋት በዙሪያዋም ተመላለሱ…በብርታትዋ ልባችሁን አኑሩ፣ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ” መዝ 48፥12

 

የሻደይ በዓል አጀማመርን በተመለክተ ከላይ ከተቀመጡት ታሪኮች በተጨማሪ በአካባቢው ሕዝብና በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንቶች ዘንድ ተደጋግሞ የሚነሣው ታሪክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ በዓል ሲሆን ይኸውም እግዚአብሔር አምላክ ለአዳምና ሔዋን ከ5500 ዘመን በኋላ ወደዚህ ዓለም አንድያ ልጁን ልኮ ከኃጢያት እሥራት ነጻ እንደሚያወጣቸው በገበላቸው ቃልኪዳን መሠረት አምላክ የተወለደባት እና ትንቢቱ የተፈጸመባት፣ በሔዋን ስህተት ከገነት የተባረረው የሰው ልጅ በእርሷ ምክንያት ከኃጢያት ባርነት ነጻ የወጣባትና ወደ ቀድሞ ቤቱ ገነት እንዲመለስ ምክንያት የሆነችው የሰው ልጅ መመኪያ የተባለች እመቤት፣ እንደማንኛውም ሰው የተፈቀደላትን እድሜ በምድር ከኖረች በኋላ ሞተ ሥጋን እንደ ሞተች ከመጽሐፍት እንረዳለን፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ በኋላ ሞትን ድል አድርጋ ከመቃብር ተነሥታ ወደ ሰማይ አረገች፡፡

በፍልሰታ ወቅት በዓሉ መከበሩም ለሻደይ ተጨዋቾች ተምሳሌትና የድንግልናቸው አርዓያ የሚያደርጓት ድንግል ማርያም አካላዊ ሥጋዋ ከጌቴሰማኔ ወደ ገነት መፍለሱን እንዲሁም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል መምሪያ ሓላፊ የሆኑት መጋቢ ምስጢር ገብረ ሕይወት ኪዳነ ማርያም “በዓሉ በልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው በሄዋን ምክንያት የተዘጋው ገነት በእመቤታችን አማካኝነት በመከፈቱ ነው። መመኪያቸው ስለሆነች ልጃገረዶች በዓሉን ያከብሩታል ድንግልናቸውንም አደራ የሚሉት በእርሷ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

ዕርገቷን መላዕክት በእልልታ፣ በሽብሸባና በዝማሬ ነጫጭ ልብስ ለብሰው አጅበዋት ነበር፡፡ ዕለቱን ፍስለታ ብለን የምንጠራውም ማርያም ከሞት ተነሥታ ማረጓን፣ ሙስና መቃብር አፍልሳ መነሣትዋን ወይም ዕርገቷን በማሰብ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን በነሐሴ 16 ቀን እንደ አዲስ በመላዕክት ሽብሸባ፣ እልልታ፣ ዝማሬና ዝማሜ ታጅባ ከምድር ወደ ሰማይ ስታርግ እንዳዩ፡፡ በታላቅ ፍስሃ ይመለከቱና በታዓምራቱ ይደነቁም ነበር፡፡ ከዛን ዕለት ጀምሮ ደናግል ቅዱሳን ከመላእክቱ በተመለከቱት ሥርዓት መነሻነት ባህላዊ ነጫጭ ልብሶችን ለብሰው፣ አምረውና አጊጠው፣ የወቅቱ መታሰቢየ የሆነውን ለምለሟን ከምድር ሳሮች ሁሉ ረዘም ያለችውን የሻደይ ቅጠል በወገባቸው አስረው እንደ መላአክቱ አክናፍ ወገባቸውን ከግራ ወደ ቀኝ እያመላለሱ በማሽከርከር እያሸበሸቡ፣ በአንደበታቸው እየዘመሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ በአንድነት ተሰባሰባስበው በፍቅርና በሐሴት ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ በመጾም ጾሙ ከሚፈታበት ከዳግም ዕርገቷ ነሐሴ 16 ጸሎታቸው ተሰምቶላቸው የፈለጉትን ማየታቸውን ምክንያት በማድረግ እስከ ነሐሴ 21 ቀን ድረስ በየዓመቱ ማክበር እንደተጀመረ ይነገራል፡፡

እናቶችና እኅቶች በአደባባይ ወጥተው የድንግል ማርያምን ሞትን ድል አርጎ መነሣት ትንሣኤዋንና ዕርገቷን እንደ ነጻነታቸው ቀን ቆጥረው የተለያዩ አልባሳትን በማድረግና ለበዓሉ ክብር በመስጠት ከበሮ አዘጋጅተው አሸነድዬ የተባለውን ቄጠማ በወገባቸው ታጥቀው ምስጋና በማቅረብ በዓሉን ይዘክራሉ፡፡ በዚህም መሠረት የሻደይ ጨዋታ የፍስልታ በዓል መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ እንደተጀመረና በምእመኑ ለረጅም ጊዜ እየተከበረ የኖረ ሃይማኖታዊ በዓል እንደሆነ ይታመናል፡፡

የሻደይ ልጃገረዶች የቡድን አመሠራረት ደብርን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የሻደይ ጨዋታ በዓል በሚያከብሩበት ጊዜ ልጃገረዶች የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትን ለብሰው ከበሮ እና ለምስጋናው የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማሟላት ተጠራርተው በመጀመሪያ ወደ አጥቢያቸው በመሄድ የቤተ ክርስቲያኑን ደጁን አልፈው ይዘልቃሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያኑን ደጅ ከተሳለሙ በኋላ የተለያዩ ጣዕመ ዝማሬ እያሰሙ ሦስት ጊዜ ይዞሩና ደጃፉን ተሳልመው በቅጥር ግቢው አመቺ ቦታ ፈልገው ምስጋናቸውን ይጀምራሉ፡፡ ከበሮአቸውን እየመቱ፣ የታቦቱን ስም እየጠሩ በሚያምር ድምፃቸው፣ ሽብሻቦ፣ ውዝዋዜ፣ ጥልቅ መልእክትን በያዙ ግጥሞች፣ ለዚህ ያደረሳቸውን አምላክና ታቦት ያወድሳሉ፣ ያሞግሳሉ፣ ያከብራሉ፣ ይለማመናሉ፡፡ ምስጋናው ለዚህ ዓመት ያደረሳቸውን አምላክ የሚያመስግኑበት እና ቀጣዩ ዓመትም እንደዚሁ የሰላም፣ የጤና የተድላ እንዲሆን የሚማጸኑበት፣ ተስፋቸውን የሚገልጹበትና ስለት የሚሳሉበት በመሆኑ ምስጋናውን ሞቅ፣ ደመቅ አድርገው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በፍቅር፣ በደስታ፣ በመተሳሰብና በሰላም ይጫወታሉ፡፡ እያንዳንዱ አባል ለእግዚአብሔርና ለደብራቸን ታቦት ያልሆነ እያሉ ጉልበታቸውን፣ ችሎታውንና ልምዳቸውን ሳይቆጥቡ በምስጋናው ይሳተፋሉ።

ከቤተ ክርስቲያን መልስ በአካባቢው ወዳሉት ትልልቅ አባቶች ዘንድ ሄደው በመዘመር ምርቃን ይቀበላሉ። ከዚያ መልስ ወደ ተራራማ ስፍራ በመውጣት ክብ ሠርተው ይዘምራሉ፡፡ ከዝማሬያቸው ውስጥ ግጥሞቹ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው ግጥሞች ከግለሰባዊ ስሜት ወይም ከግለሰብ ውዳሴ የራቁ ናቸው፡፡ የቡድን አመሠራረታቸው ደብርን መሠረት ያደረገ በመሆኑ አንዱ ቡድን ከሌላው ቡድን የተሻለ መሆኑን ለማሳየት ፣ የደብሩን ኃያልነት፣ ደብራቸውን እንደማያስደፍሩና እንደሚጠብቁ በምስጋናቸው ይገልጻሉ፡፡

የወከሉትን ደብር ታቦት ስም እየጠሩ ለአባት እናት፣ ለቤተሰብ ጤና፣ ጸጋ፣ ሀብት፣ ሰላም በአጠቃላይ መልካሙን ሁሉ እንዲያድላቸው ይማጸናሉ፡፡ አደራውን ለታቦቱ ይሰጣሉ፡፡ ለዚህም ዜማውና ግጥሙ ተመሳሳይ ቢሆንም የወከሉትን ደብር ስም ብቻ በማቀያየር በተመሳሳይ ዜማና መወደስ እና መማጸን በሁሉም የሻደይ ተጨዋች ቡድኖች ይታይል፡፡ ልጃገረዶቹ በዚህ የምስጋና ጊዜ የሚሰበሰቡትን ሥጦታዎች ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣሉ።

የሻደይ ምስጋና/ጨዋታ በዚህ መልኩ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በማመስገን ከፍከፍ በማድረግ ዕርገቷን በማሰብ የአምላክ እናት አማልጅን እያሉ ስሟን በመጥራትና በማክበር የሚከናወን በመሆኑ ይህንን ሃይማኖታዊ መሠረትነት ያለውን ትውፊት የመጠበቅና የማስጠበቅ ሓላፊነት ከሁላችን ይጠበቃል። የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን፡፡

  • ምንጭ፡-ሰቆጣ ማእከል ሚዲያ ክፍል