“ወአርአየ ስብሐቲሁ ወአምኑ ቦቱ አርዳኢሁ” ዮሐ. 2፤11

ጥር 12 ቀን 2005 ዓ.ም

መ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ


“ጌትነቱን ገለጠ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበዐላት አከባበር ቀመር ከበዓለ ልደት ፤ግዝረት፤ ጥምቀት ቀጥሎ ቃና ዘገሊላ ይከበራል፡፡ ምክንያቱም ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ወደዚህ ዓለም በመጣበት ወቅት ልዩ ልዩ የሆኑ ድንቅ ተአምራት አድርጓል፡፡ ከእነዚህም የመጀመሪያው በቃና ዘገሊላ በሰርግ ቤት ተገኝቶ ያደረገው ተአምር ተጠቃሽ ነው፡፡

 

ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ እንዲህ ጽፎታል፡፡ “በሦስተኛው ቀን በገሊላ ቃና ሠርግ ሆነ” ምን በሆነ በሦስተኛው ቀን የሚል ጥያቄ በሁላችንም እዕምሮ እንደሚመላለስ አያጠያይቅም፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ጥር 11 ቀን ተጠምቆ ሳይውል ሳያድር ዕለቱን ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሞ ፤ዲያብሎስን ድል ነስቶ፤ መዋዕለ ጾሙን ፈጽሞ ለእኛም ዲያብሎስን ደል የምንነሳበትን መንገድ አሳይቶን ከገዳመ ቆሮንቶስ መልስ ደቀ መዛሙርቱን መረጠ፡፡ ከጥር አሥራ አንድ እስከ የካቲት ሃያ አርባ ቀን ይሆናል፡፡ መዋዕለ ጾሙን የካቲት ሃያ ፈጽሞ በወጣ በሦስተኛው ቀን ገሊላ አውራጃ ቃና በተባለች መንደር ሰርግ ሆነ፡፡ በዚህ ሰርግ ብዙ ሰዎች የታደሙ መሆኑን የወይን ጠጁ ማለቅ ያስረዳል፡፡ በእርግጥም የተጠሩት ሰዎች ብዙ ቢሆንም ብዙዎች መመገብ የሚችል አምላክ በሰርግ ቤት መጠራቱ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ሰርግ ከሠዎች በተጨማሪ ሦስት አካላት ተጠርተዋል፡፡

1. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም

“ወሀለወት ህየ እሙ ለእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ” የጌታ እናት ከዚያ ነበረች እንዲል እንዲያው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ በደግ ሰው ልማድ ተጠርታ እንጂ እመቤታችን በማኅበራዊ ሕይወት የነበራትን ተሳትፎ እና በሰዎች ዘነድ የነበራትን ተዋቂነት ያመለክታል፡፡ በሌላ መልኩ በቤተ ዘመድ ልማድ ማንኛውም ዘመድ እንደተጠራው ሁሉ እርሷም በገሊላ በነበሩት ሰዎች ዘንድ ታላቅና ተዋቂ ስለበረች እና ቤተ ዘመድ በመሆኗ በዚህ ሠርግ ተጠርታ ነበር፡፡የተገኘችው የሰው ሰውኛው ይህ ቢሆንም በዚያ ሠርግ ቤት ማንም ሊሠራው የማይችል የሥራ ድርሻ ነበራት፡፡ይህ በሰዎች ዘንድ የማይታወቅ በእግዚአብሔርና በእርሷ መካከል ያለ አማላጅነት ነው፡፡ የጎደለውን መሙላት ለሚችል ውድ ልጇ የጎደለውን እንዲሞላ ማማለድ ነው ፡፡ እመቤታችን ከሰው ልጆች የተለየች ክብርት ቅድስት ንፅህት ልዩ በመሆኗ የምታውቀውም ምሥጢር ከሰው የተለየ ነው፡፡ “ወእሙሰ ተአቀብ ዘንተ ኩሎ ነገር ወትወድዮ ውስተ ልበ” ማርያም ግን ይህንን ሁሉ ትጠብቀው በልቧም ታኖረው ነበር ሉ.2፤19 ይህን ሁሉ ያለው ድንግል ማርያም አምላክን በመውለዷ ከሰው ልጆች የራቀ ምስጢር የተገለጠላት መሆኑን ያስረዳል፡፡ ይህንን ሁሉ ብሎ እንደ ሸማ ጠቅልሎ እንደ ወርቅ አንከብሎ የተናገረው የተገለጠላት ምስጢር በሰው አንደበት ተነግሮ የማያልቅ እንደሆነ ነው የሚገልጠው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሁለት ብለን የምንቆጥረው አይደለምና መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እንደዚሁ “ፀጋን የተሞላሽ” በማለት የገለጠው ለእርሷ የተሰጠው ባለሟልነት ልዩ መሆኑን ለማስረገጥ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ በሠርጉ ቤት የምትሰራውን ሥራ በውል ታውቅ ነበርና፡፡

 

2. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠርቶ ነበር

“ወፀውእዎ ለእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ” ጌታ ኢየሱስንም ጠሩት” ዮሐ.2፤2 እናትን ጠርቶ ልጅን መተው ተገቢ አይደለምና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጠርተው ልጇም ጠርተውታል፡፡ ይህም ፍፁም ሰው መሆኑን ያስረዳል፡፡ ሰው ነውና እንደ ሰውነቱ ወደ ሰርግ ቤት ተጠራ፤አምላክ ነውና ጌትነቱን ገለጠ፡፡

 

ከሚደሰቱት ጋር መደሰት ከሚያዝኑ ጋር ማዘን ተገቢ መሆን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር አስተማረ፡፡ በቃና ዘገሊላ ከሠርግ ቤት እንደሄደ በአልአዛር ቤት ለለቅሶ መገኘቱን ልብ ይሏል፡፡ወደ ሠርግ ቤት የሄደው በደስታ ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ እንደገለጠው “ሖረ ኢየሱስ በትፍስህት ውስተ ከብካብ እንዘ ይገብር ተአምረ ወመንክረ በውስተ አህዛብ፤ ኢየሱስ በአህዛብ ፊት ተአምራትንና ድንቆችን እያደረገ በደስታ ወደ ሠርግ ሄደ” ወደ አልአዛር ቤት ሲሄድ ግን “ጌታች ኢየሱስ ክርስቶስም እርሷ (ማርታ) ስታለቅስ ባየ ጊዜ በልቡ አዘነ፡፡በራሱም ታወከ(ራሱን ነቀነቀ፡-የሀዘን ነው) ጌታችን ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ ፡፡አይሁድም ምን ያህል ይወደው እንደነበር እዩ አሉ” ዮሐ.11÷33-38

 

ከዚህ እንደ ምንመለከተው ከኀጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ መሥራቱን የሰውን የተፈጥሮ ሕግ ምን ያህል እንደ ከበረ እና እንደፈጸመ ያሳያል በመደሰት እና በማዘን ፍጹም ሰው መሆኑን ሲያስረዳን ፍጹም አምላክ መሆኑን በሰርጉ ቤት ውኃውን የወይን ጠጅ በማድረግ በልቅሶ ቤትም ዓልዓዛርን ከአራት ቀናት በኋላ በማስነሣት አስረዳን፡፡ አምላክ ነኝ ከሠርግ ቤት አልሄድም ከልቅሶም ቤት አልገኝም አላለም በትሕትና ራሱን ዝቅ አድርጎ በሰርግ ቤት እንዲሁም የሚያዝኑትን ለማጽናት በልቅሶ ቤት በመገኘቱ ሁሉንም የሰውነት ሥራ አከናወነ፡፡ አምላክ ነው በሰርግ ቤት የጎደለውን መላ፡፡ አምላክ ነውና የሞተውን አልዓዛርን መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱኝ ሳይል እንዲነሣ አደረገ፡፡

 

በዚህ የሰርግ ቤት ባይገኝሰዎች ምን ያህል ሀፍረት ይሰማቸው ይሆን? የእርሱ እንዲሁም የእናቱ በሰርጉ ቤት መገኘት ለባለሰርጉና ለታዳሚዎች ሙላት ነበር እርሱ ባይኖር የሰርጉ ቤት የሃዘን ቤት ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም በዚህ ሰርግ ቤት ተመላጅነት የአምላክ አማላጅነት ደግሞ የፍጡራን መሆኑን አስተምሯል፡፡

“ወሶበ ሀልቀ ወይኖ ወይትቤሎ እሙ ወይንኬ አልቦሙ” ዮሐ.3÷3 “የወይን ጠጅ ባለቀባቸው ጊዜ እመቤታችን የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው አማላጅነት የፍጡራን ገንዘብ ነው፡፡ እርሱ አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ÷ ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ አንቺ ያልሽውን ልፈጽም አይደለም ሰው የሆንኩት አላት ጊዜ ገና አልደረሰም የሚለው ሥራውን ያለ ጊዜው አይሠራውምና ነው፡፡ ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ አለው” እንዲል፡፡ መዝ.118÷126 በሌላ መልኩ በአምላክነቱ ማንም የማያዝዘው ግድ ይህን አድርግ ብሎ ማንም ሊያሰገድደው የሚችል የወደደውን የሚያደርግ ቢፈልግ የሚያዘገይ ሲፈልግ በዐይን ጥቅሻ በፈጠነ መልኩ መፈጸም የሚችል በራሱ ፈቃድ እንጂ በሰምች ፈቃድ የማይመራ መሆኑን ያስተምረናል፡፡

 

“ፈቃድ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ማቴ.6÷ ብላችሁ ለምኑኝ ያለው ለዚህ ነው በሌላ መንገድ የወይን ጠጅ በሙሉ አላላቀም፡፡

 

ያለውን ቢያበረክተው ተአምራቱን አናደቅም፥ ፈጽሞ ጭል ብሎ እስከሚያልቅ “ጊዜ ገና አልደረሰም” አለ፡፡ሰው ቢለምን ቢማልድ በእርሱ ፈቃድ ጊዜው ሲደርስ ነው የሚፈጸመው፡፡ምልጃው አልተስማም ተቀባይነት አላገኝም ማለት ግን አይደለም ተቀባይነት ያገኘ መሆኑ የሚታወቀው በመደረጉ ነው፡፡

 

አማላጅ ያስፈለገው እርሱ የሚያውቀው ነገር ኖሮት በስምአ በለው ለመንገር አይደለም ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ይታወቅ ዘንድ እና የሰው ልጆችን ከችግር የሚያወጣበት መንገዱ ብዙ መሆኑን ለማስረዳት ነው እንጂ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሚዜዎችን “ኩሎ ዘይቤለክሙ ግበሩ፤ያዘዛችሁን ሁሉ አድርጉ፡፡” ማለቷ “አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ” የሚለው የጌታችን መልስ “እሺታ ይሁንታን” የሚገልጽ መሆኑን ያስረዳል፡፡ “እሱም ውኃ ቅዱና ጋኖችን ምሏቸው” አለ፡፡ እነርሱም በታዘዙት መሠረት እመቤታችን ያላችሁን አድርጉ እንዳለቻቸው ውኃውን ቀድተው ጋኖችን ሞሏቸው፡፡ ውኃውንም ክብር ይግባውና በአምላካዊ ችሎታው ወደ ወይን ጠጅ ለወጠው፡፡ ለአሳዳሪውም ሰጠው አሳዳሪው የወይን ጠጅ የሆነውን ውኃ ቀምሶ አደነቀ ከወዴት እንደመጣ ግን አላወቀም ድንቅ በሆነ አምላክ ሥራ እንደተለወጠም አልተረዳም፡፡ ያን ምስጢር የሚያቀው ባለሰርጉ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ውኃውን የቀዱ ሰዎች ናቸውና፡፡

 

ታዳሚዎችም “ሰው ሁሉ የተሻለውን ወይን አስቀድሞ ያቀርባል በኋላም ተራውን የወይን ጠጅ በኋላ ያቀርባል አንተስ መናኛውን ከፊት አስቀድመህ ያማረውን ከኋላ ታመጣለህን” ብለው አድንቀዋል፡፡ ድሮም የአምላክ ሥራ እንደዚያ ነው ብርሃን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ጨለማን ፈጥሯል ከጨለማ ቀጥሎ “ብርሃን ይሁን” በማለት ብርሃንን ፈጥሯል፡፡ መጀመሪያ ብርሃን ተፈጥሮ ኋላ ጨለማ ቢፈጠር ይከብድ ነበርና መጀመሪያ 21 ፍጥረታት ፈጥሯል፡፡ በመጨረሻም በአርዓያውና በአምሳሉ የሥነ ፍጥረት የሆነውን የሰው ልጅ ፈጥሯል፡፡ ናትናኤልንም እንዲህ ብሎታል፡፡ “ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የሚባልጥ ታያለህ” ማለቱ የእግዚብሔር ሥራ እየቆየ ውብ ያማረ መሆኑን ያመለክታል ሰው ግን ጥሩ ነው፡፡ ያለውን ያስቀድማል ያ ሲያልቅ የናቀውን ይፈልጋል፡፡ “የወደዱትን ቢያጡ ያጡትን ይቀላውጡ” እንዲሉ እግዚብሔር ልማዱ ነው፡፡ ተራውን ከፊት ታላቁን ከኋላ ማድረግ ለሰው መጀመሪያ የተሰጠው የሚያልፈው ዓለም ነው በኋላ የማያልፈው መንግሥተ ሰማያት ይሰጠዋል ሰው መጀመሪያ ይሞታል በመጨረሻ ትንሣኤ አለው፡፡ ሰው መጀመሪያ ሲወለድ ርቀቱን ነው፡፡ ኋላ ልብስ ያገኛል፡፡ ሁብታም ይሆናል፡፡ ሰው ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ዓለምን የሚያገኛት የሚተዋወቃት በልቅሶ ነው፤ ኋላ ግን ይደሰታል በሀሳር በልቅሶ ወደመቃብር ይወርዳል፡፡ በደስታ “መቃብር ክፈቱልኛ፥ መግነዝ ፍቱልኝ” ሳይል ይነሣል ይህን የአምላክ ሥራ አድንቆ መቀበል እንጂ መቃወም አይችልም፡፡

 

3. ቅዱሳን ሐዋርያት በዚህ ሠርግ ነበሩ

“ወለአርዳኢሁ ውስተ ከብካብ” እንዲል፡፡ ዮሐ.2፥2 “ደቀመዛሙርቱንም ጠሯቸው” መምህርን ጠርቶ ደቀ መዝሙርን መተው ተገቢ አይደለምና፤ ደቀ መዛሙርቱ ከመምህራቸው ከክርስቶስ ጋር አብረው በሠርግ ቤት ተገኝተው በተደረገው ተአምር ጌትነቱን አምነዋል፡፡ ተአምራቱን ተመልክተዋል፣ ከዋለበት የሚውሉ፥ ከአደረበት የሚያድሩ፥ ተአምራት የማይከፈልባቸው፥ ይህን ዓለም ለማስተማር የተመረጡ ናቸውና፤ አየን ብለው እንጂ ሰማን ብለው አያስተምሩምና፡፡በጠቅላላው የእነርሱ በሰርጉ ቤት መገኘት የሚያስተምርና ካህናት የሌሉበት ሰርግ ሊደረግ እንደማይገባው ነው፡፡ በሰርግ ቤት የካህናት መገኘት እና ቡራኬ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ያስተምራል፡፡ በፍትሐ ነገሥት አን.24 የተገለጸውም ይህ ነው “ወማዕሰረ ተዋሰቦሶ ኢይትፌጸም ወኢይከውን ዘእንበለ በሀልዎተ ካህናት ወጸሎት ዘለዕሌሆሙ” የጋብቻ አንድነት ካህናት ቢኖሩ እንጂ ያለእነርሱ አይጸናም ጸሎት ቢያደርጉ እንጂ ያለ ጸሎት አይፈጸምም” እን. በቃና ዘገሊላው ሰርግ ጋብቻን በጥንተ ፍጥረት “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ረዳት እንፍጠርለት” ዘፍ.2፥19 ያለ አምላክ የሐዲስ ኪዳን ጋብቻ በካህናት ቡራኬና ጸሎት መከናወን እንደሚገባው ሲያስተምረን ቅዱሳን ሐዋርያትን ይዞ ተገኝቷል፡፡ የቃና ዘገሊላ ሰርግ እና በሰርጉ ላይ የታዩ ተአምራት ምልጃዎች ሁሉ ሌላም ምሥጢር ያዘሉ ናቸው፡፡ እመቤታችን “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” ማለቷ “ወይን” በተባለው የክርስቶስ ደም ዓለም እንዲድን ያስረዳል፡፡ ደምህን አፍሰህ ሥጋህን ቆርሰህ አጽናቸው ማለቷ ሲሆን “ጊዜዪ ገና ነው” የሚለው የጌታ መልስ “ደሙ በዕለተ ዓርብ የሚፈስበት ጊዜ ገና መሆኑን ያስረዳል” ጥንቱን ዓለምን ለማዳን አይደለምን፣ ሰው የሆንኩት ሥጋ የለበስኩት ለዚህ ዓለምን ለማዳን አይደለምን ሲል ነው፡፡

ይቆየን፡፡

ጥምቀት በቅዱስ ኤፍሬም

ጥር 9 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ


ቅዱስ ኤፍሬም በጥምቀት ላይ እጅግ ጥልቅ የሆነ አስተምህሮ ያለው አባት ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በጥምቀት የገሃነም እሳት ይጠፋል ይለናል፡፡ “የሰውነት ትኩሳት ከሰውነታችን በሚመነጨው ላቦት እንዲቀዘቅዝ እንዲሁ በጥምቀት የገሃነም እሳት ይጠፋል፡፡”

 

ከዚህ ተነሥተን እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ምልከታ የገሃነም ቦታዋ ከሰውነታችን ውስጥ ናት ማለት ነው፡፡ እሳቱ የማይጠፋ መባሉም ከእኛ ዘለዓለማዊነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን መረዳት እንችላልን ፡፡ እኛ ዘለዓለማውያን ሆነን ስለተፈጠርን እሳቱም በሰውነታችን ውስጥ ዳግም አይቀጣጠልም፡፡ ይህ የሚያስረዳን ከጥምቀት በኋላ በራሳችን ፈቃድና ምርጫ በድርጊትም ይሁን በቃል ጌታችንን እስካልካድነው ድረስ የገሃነም እሳት በሰውነታችን ውስጥ እንደማይኖር ነው፡፡

 

ስለዚህ መዳን አለመዳን በእጃችን እንደተያዘች መረዳት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ይህን መብታችንን የማንጠቀምበት ጊዜ ይመጣል፡፡ እርሱም በምጽአትና በሞት ወደ እግዚአብሔር ለፍርድ የተወሰድንበት ወቅት ነው፡፡ እስከዛው ድረስ ግን የገሃነምን እሳት በሰውነታችን ላይ ማቀጣጠልም ይሁን ማጥፋት ወይም ሰውነታችንን የጌታ ቤተመቅደስ ማድረግ ወይም አለማድረግ የእኛ ፈንታ ይሆናል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ጥምቀትን ወደሰማያት የምንወጣጣበት መሰላል ብሎም ይጠራዋል፡፡

 

“እርሱ ወደ ጥምቀት በመውረድ ጥምቀትን መሠረተልን እርሱም በሠራልን ጥምቀት ወደ ሰማየ ሰማያት ተነጠቅን ፡፡”

¨ ቅዱስ ኤፍሬም መጠመቂያ ገንዳውን በክርስቶስ መስቀል ይመስለዋል፡፡ በውስጡም ክርስቶስን

 

ለብሰን እንወለዳለን ሲለን እንዲህ ይላል፡፡

“የክርስቶስ መንጎች እጅግ ደስ ተሰኝተው የእርሱን አርዓያ የነሡበትን ሕያውና ቅዱስ የሆነውን መስቀል ከበው ቆመዋል፡፡ በዚያ ውስጥ ፍጥረታት እንደገና ተፈጥረው ይታያሉ፡፡ ሁሉም ሕያውና ቅዱስ በሆነው መስቀሉ ታትመዋል፡፡”

 

¨ ቅዱስ ጴጥሮስ በጌታ ትእዛዝ በቀኝ በኩል የጣለው መረብ ፻፶፫ ዓሣት ይዞለት ነበር፡፡ ይህ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡

 

“ከባህር ውስጥ በቅዱስ ጴጥሮስ መረብ ፻፶፫ ዓሣት ተሠግረው ነበር፡፡ እንዲሁ በእርሱ ስብከት በጥምቀት እቅፍ ዐሥር ሺሕና ከዚያም በላይ የሆኑትን በማጥመድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ማረካቸው” ይለናል፡፡

 

¨ “በምድር ላይ እሳትን ልጥል መጣሁ አሁን የእነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ” (ሉቃ.፲፪፥፵፰) የሚለውን የጌታ ቃል ለመንፈስ ቅዱስ በመስጠት እንዲህ ብሎ ያስተምራል፡፡

 

“ጌታችን “በምድር ላይ እሳትን ልጥል መጣሁ” ሲል እኔ የማጠምቀው ጥምቀት በዚህ ነው ሲለን ነው፡፡ እሳት ያለውም መንፈስ ቅዱስን ነው፡፡”

 

“በጥምቀት እሳት በክፉው ሰይጣን የተቀጣጠለውን እሳት አጠፋለሁ፡፡ ንጹሕ የሆነው በተጠማቂያን ነፍስ ውስጥ የተቀጣጠለው መለኮታዊው እሳት መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በእርሱ እሳትነት በኀጢአታችንና በመተላለፋችን ምክንያት የተቀጣጠለውን የገሃነም እሳትን ይጠፋልናል፡፡

 

“ይህ እሳት በምሳሌ በሲና ምድረ በዳ በእሾኽ ቁጥቋጦ ውስጥ ለሙሴ የታየው እሳት ነው ፡፡ ሙሴ ያየው እሳት እሾኹንና ቁጥቋጦውን አላቃጠለውም ነበር፡፡ ነገር ግን በጥምቀት በእናንተ ውስጥ የተቀጣጠለው መለኮታዊ እሳት የኀጢአት ቁጥቋጦውን አቃጥሎ ያጠፋዋል ፡፡ ስለዚህም እርሻው እስከሰማይ የሚደርስ ፍሬን ያፈራል፡፡

 

¨ ቅዱስ ኤፍሬም ጥምቀትን ነቢዩ ኤርምያስን በፀነሰችው ማኅፀን መስሎ ያስተምራል፡፡

“ነቢዩ ኤርምያስ ገና ከእናቱ ማኅፀን ሳለ ተቀደሰ ተማረ፡፡ ደካማ የሆነችው ማኅፀን የፀነሰችውን ቀድሳ የወለደች ከሆነ እንዴት ጥምቀት ከእርሷ ማኅፀን የተፀነሱትን ይበልጥ ቀድሳ አትወልዳቸው ይሆን? ጥምቀት ተጠማቅያንን ንጹሐንና መንፈሳውያን አድርጋ ትወልዳቸዋለች፡፡”

 

የውኃንም ተፈጥሮ በማንሣት ጥምቀትን በውሃ ተፈጥሮአዊ ጠባይ መስሎ ያስረዳል፡፡ “ውኃ በተፈጥሮው እንደመስታወት ነው ፡፡ አንድ ሰው በውኃው መስታወትነት እርሱ ምን እንደሚመስል ተረድቶ እራሱን ያስተካክላል ፡፡ ወደ ጥምቀት ተመልከት በእርሱ ውስጥ ያለውን ውበትን ልበሰው፡፡”

 

በሥነ ፍጥረት የመንፈስ ቅዱስ በውኃ ላይ መስፈፍን ለጥምቀት ሰጥቶ ይተረጉመዋል “በሥነ ፍጥረት መንፈስ ቅዱስ በውኃ ላይ በመስፈፉ ምክንያት ውኃ ፀንሳ ዓሣትንና አእዋፋትን እባብንም አስገኝታ ነበር፡፡ እንዲሁ በጥምቀት መንፈስ ቅዱስ ውኃ ላይ በመስፈፉ ምክንያት በንስር የሚመሰሉትን ደናግላንንና ጳጳሳትን ወለደች፡፡ በዓሣት የተመሰሉትን ራሳቸውን ለመንግሥተ ሰማያት ጃንደረቦች ያደረጉትንና ቅዱሳንን ወለደች፡፡ አስቀድሞ ተንኮለኞች የነበሩትን በእባብ የሚመሰሉትን ወገኖች ደግሞ የዋሃን ርግቦች እንዲሆኑ አድርጋ ወለደቻቸው፡፡”

 

ቅዱስ ኤፍሬም አዳም በክርስቶስ አካል ተጠምቆአል ብሎ ያስተምራል፡፡

“በጌታ ጥምቀት አዳም በገነት ዛፎች መካከል ያጣውን የጸጋውን ልብስ አገኘው፡፡ እርሱ ወደ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ በውኃ ውስጥ ያንን የጸጋ ልብስ ለብሰው በእርሱም አጌጦና ተውቦ ወጣ፡፡ ምኅረቱን ሙሉ ለሙሉ የሰጠን አምላካችን እርሱ የተመሰገነ ይሁን፡፡”

 

በጥምቀት የምንለብሰው መንፈስ ቅዱስን ቅዱስ ኤፍሬም ያዕቆብ በፎኖተ ሎዛ በሕልም ባየው መሰላል መስሎ ይገልጸዋል፡፡

 

“ወንድሞች ሆይ ዐይኖቻችሁን ክፈቱና ተመልከቱ ልክ ያዕቆብ እንደተመለከተው መሰላል ዓይነት በአየሩ ላይ በዐይን የማይታይ አምድ ተተክሎ ይታያችኋል፡፡ የዚህ አምድ መሠረቱ በመጠመቂያው ውኃው መካከል ሲሆን ጫፉም የሰማይን ደጆች ይነካል፡፡ በእርሱም ወደ መጠመቂያው ገንዳ ብርሃን ይወርዳል ፡፡ በእዚህም አምደ ብርሃን በኩል ተጠማቂያን ወደ ሰማያት ይነጠቃሉ ፡፡ በዚያም በአንድ ፍቅር ይገለጣሉ፡፡”

 

ስለጌታ ጥምቀት አስፈላጊነት ሲያስተምር እንዲህ ይላል ፡-

“ ውኆች በእኔ ጥምቀት ይቀደሳሉ፡፡ ከዚህ ውኃ የሚጠመቁ በእኔም ምክንያት እሳታውያንና መንፈሳውያን ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ካልተጠመቁ በቀር ፍጹማን አይሆኑም፤ እኔም ከመሠረትኩት ጥምቀት የሚጠመቅ ሰውም የሲኦል ሞት አይኖርበትም”

 

“እኔ በመሠረትኩት ጥምቀት እስረኞች ነጻ ይወጣሉ፡፡ የተጻፈውም የእዳ ደብዳቤ ይሰረዛል፡፡ በጥምቀት ውኃ ውስጥም ተጠማቅያን እኔን ለማገልገል ሥልጣንን ይረከባሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሚሆነው እኔ ተጠምቄ ጥምቀትን ከባረኩዋት በኋላ ነው፡፡”

 

ጥምቀትን ሲያመሰግናትም እንዲህ ይላል፡፡

“ በልቡናችን ዐይኖች ጥምቀት እንዴት ውብ ናት ፡፡ ሁላችን ወደ እርሱዋ እናስተውል፡፡ ማኅተም እንዲቀረጽ እንዲሁ እኛም በጥምቀት አርዓያውን እንመስል ዘንድ ተቀርጸናል፡፡ የበጎቹ ልብ እንደ ወተት ነጭ ነው፡፡”

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ጥምቀት

ጥር 9 ቀን 2005 ዓ.ም

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


በሰው ልጅ ዘላለማዊ ድኅነት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ሥርዓተ ጥምቀት ከሌሎቹ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በቀዳሚነት የሚፈጸምና የማይደገም ሥርዓት ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “አንዲት ጥመቀት” በማለት የሥርዓተ ጥምቀትን አለመደገምና አለመሠለስ ገልጦ ተናግሯል /ኤፌ.4፥5/፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቦ እንደሚገኘውና፥ የታናሽ እስያ ክፍል በሆነችው ቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም. የተሰበሰቡ 150 የሃይማኖት አባቶቻችን “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፣ ለኀጢአት ማስተሥረያ /ኀጢአትን በምታስተሠርይ/ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” በማለት የጥምቀትን አንድ መሆንና ኀጢአትን በደልን የምታርቅ፣ የምታስወግድ ስለመሆኗ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናግረዋል፡፡ ሃይማኖታቸውንም ገልጠዋል፡፡

 

ጥምቀት የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲተረጉሙ “ጥምቀት” በቁሙ፡- “ማጥመቅ፣ መጠመቅ፣ አጠማመቅ፣ ጠመቃ፣ የማጥመቅና የመጠመቅ ሥራ፣ ኅፅበት፣ በጥሩ ውኃ የሚፈጸም” በማለት ተርጉመውታል፡፡ ምሥጢረ ጥምቀትን የመሠረተው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን ሥርዓተ ጥምቀትን የመሠረተው በሦስት ዓይነት መንገዶች እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡

 

ሦስቱ መንገዶች የሚባሉትም ትምህርት፣ ትዕዛዝና ተግባር ናቸው፡፡ ይኸውም ሊታወቅ በዮሐንስ ወንጌል ምዕ.3 ቁጥር 5 ላይ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው፡፡ ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አትደነቅ፡፡” በማለት የአይሁድ አለቃ ለነበረው ለኒቆዲሞስ ጌታችን ያስተማረውን ትምህርት ልብ ላለው ጥምቀት በጌታችን ትምህርት መመሥረቷን ይረዳል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትዕዛዝም ጭምር ጥምቀትን መሥርቷል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ የጌታችንን ትዕዛዝ እንዲህ ያስነብበናል፡- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡” /ማቴ.28፥19/ መምህረ ትሕትና የሆነው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተግባር መምህር ነውና ተጠመቁ ብሎ ካስተማረውና ካዘዘው በተጨማሪ ሥርዓተ ጥምቀትን በተግባር ጭምር መሥርቷል፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 3 በማርቆስ ምዕራፍ 1 እና በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ላይ በስፋት እንደተመዘገበው ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ባሕረ ዮርደኖስ ሄዶ ከባሪያው ከዮሐንስ እጅ ሥርዓተ ጥምቀትን ፈጽሟል፡፡ በዚህም ትሕትናንና የትሕትናን አሠራር ፈጣሪያችን አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በበዓላት አከባበር ሥርዓት መሠረት በየዓመቱ ጥር 10 ቀን /የከተራ ዕለት/ ታቦታተ ሕጉ ከመንበረ ክብራቸው በመነሣት ወደ ጥምቀተ ባሕሩ ይጓዛሉ፡፡ ይህም ጌታችን በኪደተ እግሩ እየተመላለሰ ምድርን እንደቀደሳት በማሰብና እርሱኑ አርዓያ በማድረግ ሀገሩን መንደሩን ለመቀደስና ለመባረክ የሚፈጸም ዑደት ነው፡፡

 

ሥርዓተ ጥመቀት በአጋጣሚ ወይም በድንገት የተጀመረ /የተመሠረተ/ አይደለም፡፡ በዘመነ ብሉይ በርካታ ምሳሌዎች የተመሰሉለት፣ በርካታ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት ነው እንጂ፡፡ በነቢዩ ሕዝቅኤል እግዚአብሔር አምላካችን አድሮ ሲናገር “ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፣ እናንተም ትጠራላችሁ ከርኲሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ፡፡” ብሏል፡፡ /ሕዝ.36፥25/ ከኀጢአት የሚያነጻ ከርኲሰት የሚቀድስ ለመንግሥተ ሰማያት የሚያዘጋጅ የሚያበቃ ጥሩ ውኃ ተብሎ የተገለጸ ጥምቀት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

 

ሥርዓተ ጥምቀትን የመሠረተው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሆኑ በአጭሩ ከገለጽን፤ ጌታችን የተጠመቀው ለምንድር ነው? የሚል ጥያቄ ቢነሣ፡-

 

ጌታችን እርሱ ባወቀ ጥምቀትን የፈጸመበት ዋነኛ ምክንያቶች እንደ ሊቃውንት አባቶቻችን አስተምህሮ በሦስት መንገዶች ይታያል፡፡ እነዚህም

 

1ኛ ምሥጢረ ሥላሴን /ሦስትነቱን ያስረዳን ዘንድ ነው/ ማቴ.3፥13-17 በዘመነ ብሉይ በነበሩ ሰዎች በረቂቅና በምሳሌ ይታወቅ የነበረውን የልዩ ሦስትነቱንና አንድነቱን ምሥጢር በተረዳ በታወቀና በጎላ ሁኔታ እንረዳ ዘንድ ጌታችን ተጠምቋል፡፡ በቅዱስ ወንጌላችን በግልጽ እንደሚታየው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የስም፣ የአካል፣ የአካለ ግብር ሦስትነት እንዳላቸው በጊዜ ጥምቀቱ ለክርስቶስ እንረዳለን፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ፡- “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት እኔ ባይ አካል እንዳለው ገልጿል፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሰውነት በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በዮሐንስ እጅ በመጠመቅ እርሱም እንደ ባሕርይ አባቱ የራሱ እኔ ባይ አካል እንዳለው ገልጦ አሳይቶናል፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሆኖ ከሰማይ በመውረድ ታይቷል፤ በዚህም መንፈስ ቅዱስ እንደ አብና ወልድ እኔ ባይ አካል እንዳለው ተረድተናል፡፡ ስለሆነም ጌታችን ጥምቀትን የፈጸመው የሦስትነቱን ምሥጢር ይገልጽልን ዘንድ ነው፡፡

 

2ኛ ለትምህርት ለትሕትና ለአርዓያነት

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥርዓተ ጥምቀትን የፈጸመው እንደእኛ የሰው ልጆች የልጅነትን ጸጋ ለማግኘት አይደለም፡፡ እርሱ አብን በመልክ የሚመስለው በባሕርይ የሚተካከለው፤ ተቀዳሚም ተከታይም የሌለው የአብ የባሕርይ ልጁ ነውና፡፡ /ዮሐ.1፥18፣ ዮሐ.3፥16/ እንዲሁም እንደ ንዑስ ክርስቲያን ሥረየት ኃጢአትንም ለማግኘት አይደለም፡፡ ነውርም ኀጢአትም በደልም ምንም ምን ክፋት የሌለበት ንጹሐ ባሕርይ ነውና ነቢዩ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም እንዳለ /ኢሳ.53፥9፤ ማር.2፥10፣ ሉቃ.7፥49/ ነገር ግን በርዕሳችን እንደተገለጠው ጌታችን ሥርዓተ ጥምቀትን የፈጸመው ለትምህርት፣ ለትሐትናና ለአርአያነት ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትን የሚሰጥ እርሱ እንደ ደካማ ሰው ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ሄዶ ከዮሐንስ ዘንድ ሲጠመቅ ትሕትናን አስተምሮናል፡፡ ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ሳይል ፤ ከዮሐንስ ዘንድ ሄዶ ተጠመቀ፡፡ የቱንም ያህል ክብር ሥልጦን…. ቢኖረን እኛም ከካህናት ዘንድ መሄድ እንዳለብን ሲያስተምረን ነው፤ /ዮሐ.131-17 እና 1ኛ ጴጥ.2፥26/

 

3ኛ. ጥምቀታችንን ይባርክልን ዘንድ

እንፈጽመው ዘንድ የሚገባንንና የሚያስፈልገንን ሥርዓት ሁሉ የሠራልን ፈጣሪያችን ነው፡፡ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀን አርባ ሌሊት በመጾም ጾማችንን እንደባረከልን /ማቴ.4፥1-10/ በጥምቀቱ ጥምቀታችንን ይባርክልን ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሉቃስ በወርኀ ጥር በ11ኛው ቀን ማክሰኞ ሌሊት 10 ሰዓት ተጠምቋል፡፡

 

እኛ የሰው ልጆች ሥርዓተ ጥምቀት እንዲፈጸምልን የሚያስፈልገው፡-

የልጅነት ጸጋን እናገኝ ዘንድ ነው፡፡ ዮሐ.1፥5

አስቀድመን ከሥጋ እናት አባታችን በዘር በሩካቤ እንደተወለድንና የሥጋ ልጅነትን እንዳገኘን ሁሉ በማየ ገቦ ስንጠመቅ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ እንወለዳለን፡፡ ይህንን አስመልክቶ ጌታችን “ከሥጋ የሚወለድ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስ የሚወለድ መንፈስ ነው” ብሎ ከማስተማሩ በፊት “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ያለው፡፡ /ዮሐ.3፥3 እና 6/ በምሥጢረ ጥምቀት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ስለመገኘቱ አስተምሯል፡፡ ሐዋርያውም በጥምቀት ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ አስመልክቶ ሲናገር “አባ አባት ብለን የምንጮኸበትን /የምንጣራበትን/ የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈስ ጋር ይመሰክራል፡፡” ብሏል፡፡ /ሮሜ.8፥15-16/ ጌታችንንም ለተቀበሉት ሁሉ በስሙም ላመኑበት በጠቅላላው የእግዚአብሔር ልጆች ይሁኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አለመወለዳቸው ተገልጿል፡፡ /ዮሐ.1፥11-13/

 

እንግዲህ እኛ ክርስቲያኖች ሁለት ልደታት እንዳሉን እናስብ፡፡ ይኸውም መጀመሪያው ከሥጋ እናትና አባታችን የተወለድነው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከእግዚአብሔር የምንወለደው ነው፡፡ ከተወለድን በኋላ እድገታችን በሁለቱም ወገን መሆን ያስፈልጋዋል፡፡ ሰው ሥጋዊም መንፈሳዊም ነውና፡፡

 

ሥርየተ ኀጢአትን ለማግኘት

በአምልኮ ባዕድና በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ከጥምቀት በአፍአ ሆነው የቆዩ ሰዎች ከነበረባቸው ኀጢአት ይነፁ ዘንድ ሥርዓተ ጥምቀት ተሠርታለች፡፡ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በ50ኛው ቀን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሀብቱ በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ ማደሩን የሰሙ አይሁድ፤ ከቅዱሳን ሐዋርየት ዘንድ ቀርበው የሚናገሩትን ቃለ እግዚአብሔር መስማት ጀመሩ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነቱን፣ በኃይለ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱንና ወደ ሰማይ ማረጉን ነገሯቸው፡፡ አይሁድም ይህንን በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት “ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?” አሏቸው፡፡ ጴጥሮስም “ንስሐ ግቡ ኀጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡….” አላቸው /ሐዋ.2፥37-38/ ይህ የሐዋርያው ቃል የሚያስረዳን የጥምቀትን መድኀኒትነት ነው፡፡ አስቀድመን እንደገለጥነው አባቶቻችን በሃይማኖት መግለጫቸው “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፥ ኀጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” ማለታቸው ጥምቀት ከደዌ ነፍስ የምታድን መሆኗን መመስከራቸው ነው፡፡ /ጸሎተ ሃይማኖት/

 

ዘላለማዊ ድኅነት

የሰው ልጅ ድኅነት ቅጽበታዊ አለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይሁንና የድኅነት በር ከፋችና ሌሎችን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ለመፈጸም የሚያበቃን ምሥጢር ምሥጢረ ጥምቀት ነው፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱ በሰጣቸው ሐዋርያዊ መመሪያ ውስጥ “ሑሩ ውስተ ኩሉ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኲሉ ፍጥረት፡፡ ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን ወዘሰ ኢአምነ ይደየን፡፡ ወደ ዓለም ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፡፡ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል፡፡” በማለት ተናግሯል፡፡ /ማር.16፥15-16/

 

እንግዲህ በጥምቀት ያገኘነውን ጸጋና ክብር ሁላችን ልናስብ ያስፈልገናል፡፡ ይህንንም ክብራችንን መጠበቅ ያሻናል፡፡

ፈጣሪያችን በዓሉን የበረክት የረድኤት ያድርግልን፡፡

ketera 2 1

ከተራ ምንድን ነው?

ጥር 9 ቀን 2005 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

ketera 2 1

ጥያቄ

በየዓመቱ የጥምቀት በዓል በድመቀት ይከበራል፡፡ ከበዓሉ በፊት የከተራ በዓል የሚከበርበትን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ፋይዳውን ብታብራሩልን

ዮስቲና ከአዲስ አበባ

መልሱ

ከተራ ከበበ ካለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ፍችው ውኃ መከተር፣ መገደብ ማለት ነው፡፡  የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡ ድንኳንም ከሌለ ዳስ ሲጥል ይውላል፡፡ የምንጮች ውኃ ደካማ በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል ጉድጓድ እየተቆፈረ ውኃው እንዳይሄድ ይገደባል፡፡

ketera 2 2“ከተራ” በመባል የሚታወቀው – ዋዜማው” ሠርግው /1981፣8/ እንደገለጹት “ከተራ” የሚለው ቃል “ከተረ ከበበ ካለው የግዕዝ ግስ የወጣ ነው፡፡ ከተራ ፍቺውም ውኃ መከተር፣ ወይም መገደብ ማለት ነው፡፡” ብለው ሲፈቱ፣ ደስታ ተከለ ወልድ /1962፣ 694/ ደግሞ  የጥምቀት ዋዜማ፣ ጥር 10 የጠራ ወራጅ ውኃ የሚከተርበት ታቦትና ሰው ወደ ዠማ ወንዝ የሚወርዱበት ጊዜ” ነው በማለት ይፈቱታል፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም /1948፣ 555/ ከተረ የሚለውን ቃል በቁሙ፣  “ዘጋ፣ አቆመ፣ አገደ፣ ከለከለ፡፡” ማለት ነው ብለው ይፈቱታል፡፡ በየዓመቱ ጥር 10 ቀን የምእመናኑ አብዛኛው ሥራ ውኃውን መከተርና መገደብ በመሆኑ ዕለቱ ከተራ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ውኃው የሚከተረው በማግሥቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲሆን ነው፡፡

 

በየሰበካው ቦታ ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው የሚከተሩበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ስፍራ ‹‹ባሕረ ጥምቀት››፣ ‹‹የታቦት ማደርያ›› እየተባለ ይጠራል፡ ባሕር፡- የውኃ መሰብሰቢያ (ምእላደ ማይ፣ የውኃ መከማቻ (ምቋመ ማይ) ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ‹‹የውኃ አገር›› /መካነ ማይ፣ ዓለመ ማይ/ ነው፡፡

 

ከዚህም በተጨማሪ በቅዱስ ላልይበላ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር እየተመላለሱ በብሕትውና እና በስብከተ ወንጌል  ያገለግሉ የነበሩት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአክሱም፣ በመቐለና በመርጡለ ማርያም እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን ባርከዋል፡፡ በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት (1260-1275 ዓ.ም) በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (1203-1204 ዓ.ም) አሳሳቢነት የተጀመረው ሥርዐተ በዓል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዐዋጅ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ ታቦታቱም በሕዝብ ጥበቃና ክብካቤ ተደርጎላቸው በየጥምቀተ ባሕሩ እንዲያድሩ ወስነዋል፡፡ የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና አድማሱ ብሔራዊነትን እየያዘ መጣ፡፡

 

ከዐፄ ገብረ መስቀል ጀምሮ የአደባባይ በዓል የሆነው የጥምቀት በዓል በ15ኛው ክ/ዘመን በደገኛው ኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ(1426-1460 ዓ.ም)  አማካኝነት ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በዚያ ፈንታ በጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው እንዲያድሩ፣ አገሩን በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ በዐዋጅ ወሰኑ፡፡ ይህን ታሪክ በመከተል ዐፄ ናዖድ (1486-1500) ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመን ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወርድበት እና ከባሕረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ አውርዶ፣ አጅቦ መመለስ እንዳለበት በዐዋጅ አስነግረው ነበር፡፡ ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታና በእልልታ ከቤተ መቅደስ አጅቦ ከአወጣ በኋላ በባሕረ ጥምቀት ከትሞ ማደር ጀመረ ።/ሐመር ጥር/የካቲት 1998 ዓ.ም/

 

ketera 3ታቦታት ከአንድ በላይ ሆነው ወደ ከተራው ስለሚሄዱ እግዚአብሔር አምላክ ለነብዩ ሙሴ “የታቦት መኖር ከእናንተ ጋር የመኖሬ ምልክት ነው” ዘፀ 25÷1 እንዳለው ታቦተ ሕጉን ተሸክመው ዮርዳኖስን እንደ ተሻገሩት ካህናተ ኦሪት፤ ካህናቱ የማይለወጠውን ታቦተ ሕጉን በራሳቸው ተሸክመው የብሉዩን ሥርዓት ከሐዲስ ኪዳን ጋር አንድ አድርገው የሐዲስ ኪዳን መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰቡ፤  ካህናተ ሐዲስም ወደ ከተራ (ዮርዳኖስ) ይጓዛሉ፡፡ ሊቃውንቱም እንዲሁ ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ እግዚአብሔር እያደረሱ እንደሚያድሩ ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘ ያስረዳሉ።

 

ሊቀ ጠበብት አያይዘውም የከተራ ዕለት ጥር 10 ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የሄደበትን ለማዘከር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ኃዳፌ ነፍስ ለጻድቃን የሚለውን ዋዜማ ይቆማሉ፡፡  የዋዜማው ቀለም  ከቀኑ በአራት ሰዓት በመላው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይጀመራል ከዚያም የዋዜማው ሥርዐት ቅዱስ ተብሎ እስከ ሰላም ያለው ቀለም ይደርሳል፡፡ በዕለቱም ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ ታቦተ ሕጉን የሚያነሡት ሰሞነኛ ካህን ከምግበ ሥጋ ተከልክለው ለዕለቱ የሚገባውን ጸሎት ያደርሳሉ፡፡

 

በከተራው ዕለት ድንኳን ተተክሎ፣ ዳሱ ተጥሎና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ ታቦተ ሕጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ መቅደሱ ታቦታት  በወርቅና በብር መጎናጸፊያ እየተሸፈኑ በተለያየ ኅብር በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ ካህናትና የመጾር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ አብሕርት /ምጥማቃት/ ለመሄድ ሲነሡ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደወል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምእመናን ከልጅ እስከ ዐዋቂ በዐጸደ ቤተ ክርስቲንና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ‘’ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ …’’ እንደሚባለው ያማረ ልብሳቸውን ለብሰው በዓሉን ያደምቃሉ፡፡

 

ሊቀ ጠበብት የበዓሉን ሂደት ሲገልጹ ታቦቱ ከመንበረ ክብሩ ሲነœ ‹‹ዮም ፍስሀ ኮነ›› ተብሎ ከተጸነጸለ በኋላ ታቦቱ ወጥቶ ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት የሚለው ሰላም በሊቃውንቱ  ይዘመራል፣ ይጸነጸላል፣ ይመላለሳል፡፡ የወርቅ ካባና ላንቃ የለበሱ ቀሳውስት፣ መነኮሳት ጥላ የያዙት ከታቦቱ ጎን መስቀልና ጽና የያዙት ከታቦቱ ፊት ይሄዳሉ፡፡ እንደ ቀሳውስቱ ተመሳሳይ ልብሰ ተክህኖ የለበሱት ዲያቆናት ጥላ፣ መስቀልና ቃጭል ይዘው እያቃጨሉ ከቀሳውስቱ ፊት በመሆን ያጅቧቸዋል፡፡ ከነዚህም ሌላ ካባ፣ ላንቃ ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን የብር፣ የነሐስ መቋሚያና ጸናጽል ይዘው ‹‹ወረደ ወልድ›› የሚለውን አመላለስ እያሸበሸቡ ዲያቆናቱን ቀድመው ይሄዳሉ፡፡

 

የደብር አለቆችና አበው ካህናት ታቦቱን ተከትለው ይጓዛሉ፡፡ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችም በተለያዩ ቀለማት ባሸበረቁ አልባሳት ተውበው ትርዒት እያሳዩ “ወረደ ወልድ፣ እግዚኡ መርሐ፣ ሆረ ኢየሱስ” እና ሌሎችንም የአማርኛ መዝሙራትን እየዘመሩ፣ እናቶች “ነይ ነይ እምዬ ማርያም” እያሉ ሌሎችም ምስጋናዎችም እየቀረቡ ጉዞ በዝግታ ወደ ጥምቀተ ባሕር ይሆናል፡፡

 

የከተራ በዓል ማክበሪያ ቦታ እንደደረሱ ታቦታቱ በድንኳኑ አጠገብ ቆመው ‹‹ወረደ ወልድ›› የሚለው ሰላም ተመርቶ በአግባቡ ከተለዘበ በኋላ ጸሎት ተደርጎ የዕለቱ ትምህርተ ወንጌልና ዝማሬ  ከቀረበ በኋላ ውዳሴ ማርያም፣ መልክዐ ኢየሱስ ተደግሞ  ታቦታ ሕጉ  ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳን ይገባሉ /ሠርግው፤ 1981፣ 9/፡፡ በሁለተኛ የአገልግሎት ክፍል  ካህናቱ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያድራሉ፡፡ በመንፈቀ ሌሊትም ሥርዐተ ቅዳሴው ተጀምሮ ከሌሊቱ በ9፡00 ሠርሆተ ሕዝብ ይሆናል፡፡ በነጋታው የሥርዐተ ጥምቀቱ መርሐ ግብር ይቀጥላል፡፡

 

የከተራ በዓል ምሳሌያት

በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድና የባሕረ ጥምቀቱ መዘጋጀት  ሃይማኖታዊ ታሪክና ምሳሌ አለው፡፡የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብሮ መጓዝና ወደ ወንዝ መወረድ የተጀመረው በአሮን ልጅ በአልዓዛር ጊዜ ነው፡፡ ኢያሱ በሙሴ እግር ተተክቶ ሕዝበ እስራኤልን እየመራ ከዮርዳኖስ ወንዝ ሲደርስ ባሕሩ ከሁለት ይከፈልና ወራጁም ይቆም/ይከተር/ ነበር፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ወደ ምድረ ርስት ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ሲሻገሩ፡- ድንኳን ጥለው የቃል ኪዳኑን ታቦት በድንኳን ውስጥ አድርገው ሌዋውያኑ በዙሪያው፣ ካህናቱ ደግሞ በውስጥ ኾነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አድረው በማለዳ ተሻግረዋል /ኢያሱ 3÷8-9/፡፡  ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብረው  የወንዙን ዳርቻ በረገጡት ጊዜ እንደ ክረምት ማዕበል ይወርድ የነበረው ውኃ ግራና ቀኝ ተከፍሎ እንደ ግድግዳ ወደ ላይ ቆሟል፡፡ ሕዝቡ ተሻግሮ እስከሚያበቃ ታቦተ ጽዮንን ያከበሩት  ካህናት ከወንዙ መሀል ይቆሙ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት›› ይህም ‹‹የካህናት እግሮቻቸው የዮርዳኖስን ውኃ በመርገጣቸው እንደ ጥምቀት ሆናቸው›› በሐዲስ ኪዳነ ጌታችን ለመሠረተው ሥርዐተ ጥምቀት ምሳሌ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የጥምቀትን ዋዜማ ከተራ ብላ የጠራችው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡

 

ጌታችን በተጠመቀ  ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ የላይኛው ሸሽቶ ወደ ላይ ተመልሶ ሽቅብ ፈሷል፡፡ የታቹም ወደ ታች ሸሽቷል፡፡ የላይኛው ፈሳሽ ተቋርጦ እንደ ክምር ተቆልሎ ቀርቷል።ቅዱስ ዳዊት የተመለከተውም ይህንኑ ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ በዘር ይወርድ የነበረው ፍዳ መርገም በክርስቶስ ቤዛነት ተቋርጦ ፤ የታቹም ፈጽሞ መድረቁ ኃጢአተ አዳም የመጥፋቱ ምሳሌ ነው፡፡ እስራኤል ፈለገ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ  መሔዳቸው ምእመናን በጥምቀት ከኃጢአት ቍራኝነት ተላቀው እግራቸውን ወደ ልምላሜ ገነት ወደ ዕረፍት መንግሥተ ሰማያት አቅንተው ለመሔዳቸው ምሳሌ ነው፡፡  ኢያሱ የጌታ፣ እስራኤል  የምእመናን፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ ምድረ ርስት የገነት መንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡

 

ታቦቱን አክብሮ  የሚሔደው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ፣ታቦቱ የጌታችን፣  ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ታቦታቱን አጅበው የሚሔዱትና በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩት ሰዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ታቦታቱ በጥምቀት ዋዜማ ከመንበራቸው ወደ ጥምቀተ ባሕር መውረዳቸውና በዚያ ማደራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱንና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ያጠይቃል፡፡ ‹‹ጥምቀት የሞቱና  የትንሣኤው ምሳሌ ነው፡፡ ከኃጥአን ጋር ተቆጥሮ እንዲጠመቅና እንዲሰቀል የተጻፈውን ቃል ንስሐና ጥምቀት የማያስፈልገው ሲሆን ነገር ግን  ፍጹም ኃጥእ መስሎ በዮሐንስ እጅ ጥምቀትን ለመፈጸም በማየ ዮርዳኖስ እግር ተጠመቀ፡፡›› /ኪ.ወ.ክ ፤517/፡፡

 

ጌታችን የተጠመቀበት ወርኀ ጥር በእስራኤላውያን ዘንድ የዝናብ፣ የበረዶ ወራት ነው፡፡ ከወንዝ ዳር ያለ መጠለያ መዋልና ማደር አይቻልም፡፡ በመኾኑም ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ ነበር፡፡ በዚህ አንጻር ዛሬም በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ ድንኳኖች ዳሶች ይጣላሉ፡፡

 

በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በአክሱም የንግሥት ሳባ መዋኛን ‹‹ማይ ሹም›› በጎንደር የዐፄ ፋሲል መዋኛን፣ በላስታ የላሊበላ መዋኛን፣ በሸዋ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ፍርድ መስጫ አደባባይን፣ አርባ አራት ታቦታት የሚያድሩበትን የሸንኮራ ሜዳን “ራቡቴ ወንዝ” በአዲስ አበባ ደግሞ ጃንሆይ ሜዳን /ጃንሜዳን/ ወዘተ ለአብሕርተ ምጥማቃት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኒህ ቦታዎች ዛሬም ድረስ ተከብረው ይገኛሉ፡፡እኛ በዚህ ወቅት ታቦት ይዘን፣ ከወንዝ ወርደን፣ ድንኳን ተክለን በማክበራችን ይፈጸማል፡፡

ሐመር 19ኛ ዓመት ቁጥር 9 ጥር 2004 ዓ.ም.

christmas 1

ጥበብ ዘየዓቢ እምነ ኩሉ ጥበብ ከጥበብ ሁሉ የሚበልጥ ጥበብ

ጥር 1 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን እሱባለው

christmas 1

ከሰማይ በታች ባሉት ፍጥረታት ላይ በገዢነት የተሾመው የዕለተ ዓርብ ፍጥረት የሰው ልጅ በምክረ ከይሲ ተታልሎ ከፈቃደ እግዚአብሔር ፈቀቅ በማለቱ ሞትን ወደ ዓለም አስገብቷል፡፡ በዚህም የተሰጠውን ነጻነት በገዛ ፈቃዱ አሳልፎ ሰጠ በምትኩም ወደ ሰይጣን ምርኮኝነት እና ጽኑ አገዛዙ ፈጽሞ ሄደ፡፡

 

መፍቀሬ ሰብእ አምላካችንም እንደ ወጣን እንቀር ዘንድ ተቅበዝባዦች እንድንሆንም አልወደደም፤ ባማረ በተወደደ ቸርነቱ ጎበኘን እንጂ፡፡ ወኢኃደጎሙ ውስተ ኃጕል ለዝሉፉ በዕደ ሰይጣን – በሰይጣን እጅ እንደተያዙ ሊቀሩ  በጥፋት ውስጥ አልተዋቸውም እንዲል፡፡ ከነበርንበት ጉስቁልና ያድነን ዘንድ የሰይጣን ምክሩን ያፈረሰው በአምላክነቱ፣ በከሃሊነቱ፣ ከጌትነቱ ወገን በምንም በምን ድል አልነሣውም ወኢሞኦ በኃይሉ መዋኢት ወኢኃየሎ በክሂሎቱ ወኢበምንትኒ እምዕበዩ አላ በትሕትናሁ ወፍትሐ ጽድቁ በትሩፋተ ምሥጢር እንግዳ- እንግዳ በሚሆን ተዋርዶ(ትሕትና) በሠራው ሥራ ድል ነሣው እንጂ፡፡

ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ አዳምንና ሔዋንን ለማሳት በእባብ ሥጋ ተሠውሮ የሞት ምክርን በመምከር ምክንያተ ስህተት ቢሆንም የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ግን በልዩ ጥበቡ የጠላትን ምክር ያጠፋ ዘንድ አምላክም ሰው ሆነ በዚህም ከነበርንበት ውድቀት አነሣን፣ የጎሰቆለ ባሕሪያችንን አደሰልን አዲስ የሕይወት መንገድን ከፈተልን፡፡ ሰይጣን በእባብ ሥጋ ሲሰወር  ከአዳም ተሰውሮበት እንደ ነበረ ሁሉ የቃል ሥጋ መሆንም ከሰይጣን ዕውቀት በላይ ነበር፡፡ ሊቃውንት ይህንን ሲያብራሩ አምላክ እርሱ ባወቀ ጥበቡ ጽንሰቱንና ልደቱን ከሰይጣን ባይሰውር ኖሮ ጌታን አገኛለሁ በማለት በሄሮድስ አድሮ የገሊላን ሕጻናት እንዳስፈጀው ቀድሞ በርካታ ጽንሶችን ባጨናገፈ ነበር፡፡ የሰውን ነገድ ሊያድን ወድዶ በሰማያዊ ቤቱ ካሉ መላእክት ተሠውሮ በድንግል ማኅጸን ተወሰነ፤ሥልጣኑን የሚቃወሙ አጋንንትን ባለማወቅ ሰወራቸው (እንዳያውቁ አደረገ) እንዲል ትምህርተ ኅቡዓት፡፡

ይህን የአምላክ ሰው መሆን በተመለከተ ሊቃውንት ሲናገሩ “እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰው ሆኖ እኛን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል(እጅግ ይደንቃል) ይላሉ፡፡ እንደ አምላክነቱ ፍጥረታትን መፍጠር የባሕርይ ገንዘቡ ናት፤ ነገር ግን አምላክ ከብቻዋ ከኃጢአት በስተቀር ሰው ሆኖ የቤዛነት ሥራ መሥራት ከኅሊናት ሁሉ  በላይ የሆነ ነገር በመሆኑ ከጥበብ ሁሉ የሚበልጥ ጥበብ ተብሏል፡፡ በዚህ ልዩ የጥበብ ጉዞ ውስጥ ኁልቈ መሣፍርት የሌላቸው ልብን የሚነኩ ምድራውያን ፍጥረታት በምንሆን በእኛ እውቀት የማይመረመሩ የጌትነቱን ሥራ እና ትሕትና ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ በቅዱስ በዝርዝር ጽፎት እናገኛለን፡፡/ሉቃ.2/

የማኅበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት የሰው ልጅ ፍላጎት ወሰን ገደብ የለውም /Human needs are unlimited/ ሲሉ ይደመጣሉ፤ታዲያ ይህን  ወሰን አልባ መሻቱን እንኳ በገቢር በመሻት እንኳ አያረካውም ፡፡ ዘውትር አንድ የሚጎድለው ነገር እንዳለ ይሰማዋል ይህንንም ለማሟላት ጊዜውና አቅሙ የፈቀደለትን ነገሮች ሁሉ በማድረግ ይጠመዳል፡፡ ከማይገደቡ ፍላጎቶች መካከል ክብርን ዝናን መፈለግ ይገኙበታል፡፡ ክብርና ዝናን የማይሻ ሰው ካለ፥ እርሱ እግዚአብሔር ረድቶት፣ ባሕርያት ተስማምተውለት፥ ራሱን በፈጣሪው ፊት ባዶ ያደረገ ትሁት ሰው ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በርካቶች በዚህ ጾር ተወግተው እንደ ወደቁ ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል፡፡ ሕንጻና ልጆች ስምን ያስጠራሉ  በማለት ክብርን ሲሹ ውርደትን የተጎናጸፉ ናምሩዳውያን/ባቢሎናውያንን  ማስታወስ ይችላል ዘፍ፲፩፥፩-፭ ይመለከቷል፡፡

አውግስጦስ ቄሳርም እንዲህ ባለ መሻት ተጠምዶ ስሙ በታሪክ መዝገብ ውስጥ በጉልህ ይጻፍለት ዘንድ  በግዛቱ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ይቆጠሩ ዘንድ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ ትእዛዙም ከሚፈጸሙባቸው የሮማ ግዛት መካከል በገሊላ አውራጃ የምትገኘው የናዝሬት ከተማ አንዷ ነበረች ፡፡በአይሁድ ባሕል እንደ ተለመደው በየነገዳቸው ይቆጠሩ ዘንድ ሁሉም ነገዶች ወደ ዳዊት ከተማ ይተሙ ነበር፡፡ ወደ ከተማዋ ለቆጠራ ከወጡት መካከል ወንጌላዊው ለይቶ ሲናገር …ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበር ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተልሔም ወደ ምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ፡፡ ሉቃ ፪፥፬-፮፡፡ ብሏል፡፡

 

እኛን በሕይወት መዝገብ ይጽፈን ዘንድ ወደዚህ ዓለም የመጣው ፍጥረቱ ጋር የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ አውግስጦስ ቄሣር ባዘጋጀው መዝገብ ለመመዝገብ /ለመቆጠር/ ከእናቱ ጋር ወጣ፡፡ሉቃ ፲፥፳፣ ፊሊጵ ፬፥፫ ይመለከቷል፡፡

አዋጁ ለአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ከባድ ነበር በእርግና ዕድሜ ላይ ነበርና መውጣት መውረዱ እንዲህ በቀላል የሚወጣው ተግባር አልነበረም፡፡ በተጨማሪም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የመውለጃ ጊዜዋ ተቃርቧል፣ ይህ በእንዲህ እንዳለ ያንን ረጅም ጉዞ በድካም አጠናቅቀው ወደ ከተማዋ ሲገቡ ጠንከር ያሉት ተመዝጋቢዎች ቀድመው በመድረስ ከተማዋን አጣብበዋታል፡፡ የዳዊት ከተማም የዳዊትን ልጅ የምታስተናግድበት ሥፍራ አልነበራትም፡፡ ሉቃ ፪፥፭-፯፡፡

ጌታችን የዳዊት ከተማ በተባለች ቤተልሔም የተወለደው ያለምክንያትና  በአጋጣሚ አልነበረም፡፡ እርሱ ባወቀ አስቀድሞ ምሳሌውን አስመስሎ ትንቢቱን አስነግሮ ቆይቷል እንጂ፡፡ ይህም ሊታወቅ “አንቺ ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል፡፡” የሚለው የነቢዩ ሚኪያስ ቃለ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ሚክ 5፥2 ከ4ቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነ ነቢዩ ኢሳይያስም በትንቢቱ 1፥3 በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም፡፡ በማለት በመንፈሰ እግዚአብሔር እንደተናገረ፣ እረኛና ሰብሳቢ ይሆነው ዘንድ የአብ ልጅ የማርያም ልጅ  ሥጋን ይዋኻድ ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡

 

ይህን የወልድን ትሕትና ስናስብ ፍጻሜ ወደሌለው አግራሞት ይመራናል፡፡ ከግሩማን ፍጥረታት ይልቅ ግሩም የሆነ ገናናነቱ፣ ተቆጥረው የማያልቁ ብዙ የብዙ ብዙ የሚሆኑ ትጉሃን መላእክት የሚያመሰግኑት ፈጣሪ እንደ ምስኪን ድሃ በግርግም መወለዱን ስናስብ ዕፁብ ዕፁብ ብሎ ከማድነቅ የበለጠ ምን ቋንቋ ሊኖረን ይችላል?

መጠንና መመርመር በሌላት ፍቅሩ ስለወደደን በከብቶች ግርግም ተወለደ፣ ጒስቈልናችንን  ያርቅልን ዘንድ ስለ እኛ ጒሰቈለ፤ መርገማችንን አስወገደ ፡፡ ዘፍ ፫፥፲፮፡፡ ሰው መሆን ቢያቅተን ሰው ሆኖ ያድነን ዘንድ ወደደ ተወልደ “በአምሳሊከ ከመ ይለድከ በአምሳሊሁ-በራሱ አምሳል ይወልድህ  አንተን መስሎ ተወለደ” እንዳለው፡፡  አረጋዊ መንፈሳዊ፡፡

ከአበው አንዱ ይህን ሲተረጉም፡- ወደ ሰማያት ከፍ ከፍ ያደርገን ዘንድ፥ ከሰማያት ወረደ፤ ወደ ምስዋዕ(መሰውያ) ከፍ ከፍ ያደርገን ዘንድ በበረት ተወለደ፤ ለራሱ ከበረት በቀር ሌላ ማደሪያ ሳያዘጋጅ፥ ለእኛ በአባቱ ዘንድ ብዙ ማደሪያን ያዘጋጅ ዘንድ፥ ከልዕልና ወደ ትሕትና ወረደ” ብሏል፡፡ ዮሐ፲፬፥፪፡፡

በሰዎች ዘንድ ማደሪያን ቢፈልግ አላገኘም፤ ግእዛን የሌላቸው እንስሳት ግን ያላቸውን አልነፈጉትም፡፡ ቅዱስ ያሬድ እንዳለው እስትንፋሳቸውን በመገበር ጌታቸውን እንዳወቁ መሰከሩ፡፡ የነቢዩ የኢሳይያስ ትንቢትም ተፈጸመ፡፡ኢሳ ፩፥፫ በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም፡፡ ማደሪያዎቹ የሆን እኛ ሰውነታችንን ምን ያህል ለእርሱ አዘጋጅተን ይሆን ወይስ እንደ ዳዊት ከተማ በእንግዶች ብዛት ሥፍራ ነሥተነው ይሆን? በመጽሐፍ ልጄ ሆይ ልብህን ስጠኝ እንደ ተባለ ልባችንን መስጠት ያስፈልገናል፡፡ ከደጅ ቆሞ ሲያንኳኳ በራችንን የከፈትንለት ስንቶቻችን ነን?

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ  በነገሥታት፣ በሠራዊቱ እና በጻሕፍት ዘንድ ማደሪያን እንዳላገኘ፣  በዚያም እንዳላደረ፥ ዓለምና ፈቃዷ በሚናኝበት ሰው ዘንድም እንዲሁ ሥፍራ ስለማይኖረው በዚያ አያድርም፡፡ ይልቁንም …የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እንደርጋለን፡፡ ዮሐ ፲፬፥፳፫ ፡፡ እንዳለው ልደቱን ስናስብና  በዓሉንም ስናከብር የእግዚአብሔር ማደሪያ ለመሆን መሠራት ይጠበቅብናል፡፡.. “መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ፡፡” እንዲል ፩ጴጥ ፪፥፭፡፡

ልደቱንም ወዲያው ንጉሡ እና ሠራዊቱ  እንዲሁም ኦሪትንና ነቢያትን ጠንቅቀን እናውቃለን ይሉ የነበሩት ጸሐፍት ፈሪሳውያን ሌሎቹም ወገኖች በሙሉ ይህንን ታላቅ የምስራች ለመስማት አልበቁም፡፡ ዓለም እንዲህ ባለ ዝምታ ታላቁን  የነገሥታት ንጉሥ ተቀበለች፡፡ ሰማያውያን ቅዱሳን መላእክት ግን ዝምታን አልመረጡም፥ በብርሃን ጐርፍ ተጥለቅልቀው፣ በአንክሮ ተውጠው ምስጋናን ጀምሩ፡፡ ዓይናቸውን ወደ ሰማይ አቅንተው፥ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሐርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ሳይለይ በግርግም በግእዘ ሕፃናት የተገለጠውን እግዚአብሔር ወልድን አይተው “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት” በማለት አመሰገኑት ዳግመኛ ወደ ምድር ሲመለከቱ በእመቤታችን እቅፍ ሥጋን ተዋኽዶ አገኙት በዚህን ጊዜ እየሰገዱ “ወሰላም በምድር  ለዕጓለ እመሕያው” በማለት አመሰገኑት እንጂ፡፡ መንጋቸውን በትጋት በመጠበቅ ላይ ለነበሩት ኖሎትም ዓለም ያልተረዳውን እውነት አበሠሩ፡፡ ትጉኅ እና እውነተኛ እረኛ መድኀኔዓለም ልደቱን በበረት ገለጠላቸው፡፡

የተመሰገነ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ከጥበብ ሁሉ የሚበልጠውን ይህን የአምላካችንን ጥበብ ለምን እንዲህ ባለ ሁኔታ እንደ ፈጸመው ሲገልጽ ሀብታም ሲሆን እናንተ በእርሱ ድህነት ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድኃ ሆነ” ፪ቆሮ፰፥፱ ብሏል፡፡

መላእክት ቀድመው ትስብእቱን በደስታ እንዳበሰሩት አሁን ደግሞ ልደቱን በልዩ ደስታ አወጁ፡፡ ከዚያ በፊት በርካታ ነቢያት፣ካህናት፣ መሳፍንትና ነገሥታት ተወልደው ነበር፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የተሰማ የምስጋና ቃል አልነበረም፤ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ግን ልዩ ቃለ ማኅሌት ተሰምቷል፡፡ ምክንያቱም የተወለደው ነቢያትና ካህናት ለሰው ልጆች ይሰጡ ዘንደ ያልተቻላቸውን ድኅነት ይሰጥ ዘንድ የመጣ እግዚአ ነቢያት/የነቢያት ጌታ/፣ ሰያሜ ካህናት/የካህናት ሿሚ/እና የነገሥታት ንጉሥ  በመሆኑ ልዩ ምስጋናን አቅርበዋል፡፡እግዚአብሔርን በሰማይ የሚተካከለው ማን ነው ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል? በቅዱሳን ምክር እግዚአብሔር ክቡር ነው፡፡ መዝ፹፰፥፮-፯ እንዲል፡፡

ጌታ በተወለደባት ሌሊት ታላቁን የደስታ ምስራች ከመላእክት በመስማት መንጋቸውን በትጋት በመጠበቅ ላይ ከነበሩት ኖሎት የቀደመ አልነበረም፡፡ በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ፡፡እነሆም የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ፡፡መልአኩም እንዲህ አላቸው እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና፡፡ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፥ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ፡፡ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ ፡፡እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር  በአርያም ይሁን፥ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ፡፡ሉቃ፪፥፰-፲፬፡፡

እነዚህ እረኞች የሌሊቱ ግርማ ያላስፈራቸው ስለ መንጋቸው በትጋት የቆሙ፣የተሰጣቸውን ሓላፊነት ከመወጣት ቸል ያላሉ በመሆናቸው፥ የታማኝ አገልጋዮች ምሳሌ ናቸው፡፡መንጋውን በትጋት የሚጠብቁ እረኞች ሁሌም ዋጋቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ለዚህም ነው መልአኩ ዜና ልደቱን ለማብሠር ወደ ምኵራብ ወይም ወደ ንጉሡ ያልሄደው ይልቁንም ወደ ተጉት እረኞች ሄደ እንጂ፡፡

ሁላችንም ዛሬ እንደ እረኞቹ በቤተ ክርስቲያን የየራሳችን ድርሻ ይኖረናል፡፡ የእረኝነት ሓላፊነት የተሰጠን መንጋውን በመጠበቅ፣ የተቀረነው ደግሞ ከመንጋው አንዱ  እንደመሆናችን ራሳችንን  ለማስጠበቅ መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ስንታመን የደስታው ተካፋዮች እንሆናለን፡፡

እረኞቹ ከመላእክት ጋር አመሰገኑ፥ ዮም አሐደ መርዔተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን፥ እነሆ በአንድ የምስጋና  ቃል ክርስቶስን ያመሰግኑ ዘንድ መላእክትና ሰዎች አንድ መንጋ ሆኑ፡፡” እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም “እነሆ ቤተልሔም ጽርሐ አርያም ሆነች” በማለት ተናግሯል፡፡

ይህቺን ዕለት ያዩ ዘንድ ብዙ ነቢያት ሽተው፣ በትንቢታቸው በርካታ ነገርን ተናግረዋል ክንድህን ላክልን፣ ብርሃንህን ላክልን፣ ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ እያሉ ተማጽነዋል፡፡ ሁሉም ነቢያት በአንድ መንፈስ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ በትንቢት ቃል ተንብየዋል፡፡ይህ ሁሉ ትንቢት ሲከናወን እያንዳንዱን ነገር ትመለከት የነበረችው  የነቢያት ትንቢታቸው የተባለች፣ በሰው ልጅ የመዳን ሂደት(ነገረ ድኅነት) ውስጥ ምክንያተ ድኂን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ከጥበብ ሁሉ  በላይ የሆነውን ይህን የአምላክ ሰው ሆኖ መገለጥ ጥበብ በልቧ ትጠብቀው ነበር፡፡

በጾሙ እንደ ነቢያት የጌታን መወለድ ናፍቀናል፡፡ እኛ ግን ነቢያት ያላገኙትን ዕድል አግኝተናል፡፡ ይኸውም በዐይናችን ዐይተነዋል፣ በጆሮአችንም ሰምተነዋል፡፡ ስለዚህ ካየነው ከሰማነው ዘንዳ ሰውነታችንን ለእርሱ እንዲመች አድርገን ወደ ሕይወታችን እንዲመጣ ልንፈልግ፣ ልንፈቅድ ይገባናል፡፡ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ወደ ሕይወታችን ይገባልና፡፡

የሕይወታችን መሪ እርሱ ነውና፥ በዓለም ማዕበል ተነድተን ከጽድቅ ወደብ ሳንደርስ ወድቀን እንዳንጠፋ በእመቤታችን አማጅነት በቅዱሳን ሁሉ ቃል ኪዳን በልዩ ጥበቡ በጽድቅ ጎዳና እንዲመራን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን

እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀኒት ተወልዶላችኋል ሉቃ.2፥11

ታኅሣሥ 27 ቀን 2005 ዓ.ም.

መጋቤ ብሉይ አእምሮ ዘውዴ

እንኳን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡


የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ  አይደለም፡፡ ከጥንት ከመሠረት ጀምሮ በመላእክት፤ በነቢያት  ሲነገር፤ ሲሰበክ የመጣ ነው እንጂ፡፡ ማቴ.1፥18፡፡

 

ሰው የመሆኑን ምሥጢር ለመጀመሪያ ጊዜ በማእከለ ገነት የተናገረ እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

yeledeteአባታችን አዳም ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ወጥቶ ዕፀ በለስን በልቶ ከጸጋ እግዚአብሔር በተራቆተ ጊዜ /አዳም ኮነ ከመ አሐዱ እምኔነ/ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ዘፍ.3፥22 ብሎ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው እንደሚሆን ተናግሯል፡፡ በዚህ ቃል መሠረት /መሪነት/ ቅዱሳን መላእክት ምሥጢረ ትንቢት ተገልጾላቸዋል፡፡ እነሱም የተገለጸላቸውን ምሥጢረ ትንቢት ኀላፍያትንና መጻእያትን ለሚናገሩ ነቢያት ነግረዋቸዋል፡፡ ቅዱሳን ነቢያትም ከእግዚአብሔር ያገኙትን ከመላእክት የሰሙትን መነሻ አድርገው በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ምሳሌያት በተለያዩ ዘመናት የወልደ እግዚአብሔርን ሥጋዌ ሰብከዋል /ገልጸዋል/ ዕብ.1፥1፡፡ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፡፡

የጌታችን ልደት በትንቢተ ነቢያት

ከዓበይት ነቢያት መካከል አንዱ የሆነው ነብየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፡፡

እነሆ ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች ኢሳ.7፥14፣ ሕዝ.44፥1/ ፡፡ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወልደው አማኑኤል ጌታ ነው፡፡ ትርጉሙም  እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው፡፡ነቢዩ  በጎላና በተረዳ ነገር “ሕፃን ተወልዶልናል ወልድም ተሰጥቶናል አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፡ ስሙም ድንቅ መካር ኀያል አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል“ በማለት የሚወለደው ሕፃን የባሕርይ አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ሥልጣን የባሕርይ ገንዘቡ እንደሆነ እና ለሥልጣኑም ወሰን ድንበር እንደሌለው ተናግሯል፡፡

 

ከደቂቀ ነቢያት መካከል አንዱ ሚክያስም በቤተልሔም ስለመወለዱ፡-

  • የኤፍራታ ምድር አንቺ ቤተልሔም ከይሁዳ አለቆች ከቶ አታንሽም ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና ሚክ.5፥2፣ ማቴ.2፥6/ ብሏል፡፡

  • ነቢየ እግዚብሔር ቅዱስ ዳዊትም እነሆ በኤፍራታ ሰማነው ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው እንግዲህስ ወደ እግዚአብሔር ማደሪዎች እንገባለን ብሎ የወመለዱን ምሥጢር ተናግሯል መዝ.131፥6

  • ነቢዩ ዕንባቆምም አቤቱ ድምፅህን ሰምቼ ፈራሁ ሥራህንም ዐይቼ አደነቅሁ በሁለት እንስሶች መካከል አየሁህ ዘመኑ እንደደረሰ አድርጌ አውቅህአለሁ ዘመኑም በደረሰ ጊዜ ተገለጥክ ብሎ በቤተልሔም በረት በተወለደ ጊዜ አድግና ላኅም እስትንፋሳቸውን እንደሚገብሩለት ዕንባቆም 3፥1 ተናግሯል፡፡

 

christmas 1ከዚህ በኋላ የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ድንግል ማርያም በመላክ አብሥሯታል፡፡ “ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል” በማለት፡፡ ሉቃ. 1፡32

 

እመቤታችንም በብዙ ኅብረ አምሳል ትንቢት ሲነገርለት፤ ምሳሌ ሲመሰልለት፤ ሱባኤ ሲቆጠርለት የነበረውን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በቤተልሔም ግርግም /ዋሻ/ ወለደችው፡፡

 

ይህንንም ብስራት በቤተልሔም ዋሻ መንጋቸውን ነቅተውና ተግተው ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች መጋቤ ሐዲስ አብሣሬ ትስብዕት ቅዱስ ገብርኤል ፤ እነሆ ዛሬ መድኀኒት በዳዊት ከተማ ተወልዶላችኋል ይኸውም ቡሩክ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሚያርቅ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል ከዓለም በፊት ንጉሥ የነበረ ዛሬም ከዳዊት ባሕርይ /ዘር/ በቤተልሔም ዋሻ ዓለምን ለማዳን የተወለደ የዳዊት ልጅ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ ሲል አበሰራቸው፡፡ መዝ.73፥12

 

የጌታችንን ልደት ስናነሣ ሁለት ልደታት እንዳሉት እናምናለን፡፡ እኒሁም ልደታት /ልደት ቀደሚዊና/ /ልደት ደኃራዊ/ ናቸው፡፡

ልደት ቀዳማዊ፡ ቅድመ ዓለም ከአብ አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት የተወለደው ልደት ሲሆን /ነቢዩ ዳዊት እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽ    ባህ መዝ.109፥3 ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ወለድኩህ ፤አንተ ልጄ ነህ እኔም ዛሬ ወለድኩህ መዝ.2፥7

 

ልደት ደኃራዊ ፤ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈፀም በሀሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ እንዲል ቃሉ፡፡ ቅድስት ድንግል ከምትሆን ከእመቤታችን እንበለ ዘርዓ ብዕሲ ያለ አባት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም የተወለደው ልደት ነው፡፡

 

ቀዳማዊ ልደቱ ጥንትና ፍጻሜ የሌለው የማይመረመር ስለሆነ ቀዳማዊ ልደቱን ለመግለፅ ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ እንደ ተወለደ ድኅረ ዓለምም ከእመቤታችን /እንበለ ዘርዓ ብዕሲ/ ያለ አባት ተወለደ፡፡ እሱም እመቤታችን ያለ አባት የወለደችው ፤ እግዚአብሔርም ያለ እናት የወለደው ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ

 

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሰባቱ መስተጻርራን /ተቃራኒ ነገሮች አንድ ሆነዋል

ሕዝብና አሕዛብ፤ በጠብና በክርክር ይፈላለጉ የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ በጌታችን ልደት ታርቀዋል፡፡ ይኸውም ሊታወቅ ከዚህ አስቀድሞ ቤተ መቅደሱን ለማፍረስ ንዋየ ቅድሳቱን ለመዝረፍ ሕዝቡን ለመማረክ ምታ ነገሪት ብለው ይመጡ የነበሩ  የሩቅ ምስራቅ /የፋርስ የባቢሎን ሰዎች በጌታችን ልደት ምክንያት ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ አይቴ ሀሎ ዘተወልደ ንጉሠ አይሁድ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው ማቴ.2፥4 እያሉ መጥተው ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ ገብረውለታል፡፡

 

ነፍስና ሥጋ፡- በሲዖልና በመቃብር ተለያይተው የነበሩ ነፍስና ሥጋ ከእመቤታችን ከነፍሷ ነፍስ ከሥጋዋ ሥጋ ነሥቶ በተዋሕዶ ሰው በሆነ ጊዜ ነፍስና ሥጋን አስታርቋል፡፡

 

ሰውና እግዚአብሔር፡- አባታችን አዳም አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ በልቶ የሰውና የእግዚአብሔር የፍቅር ግንኙነት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተቋርጦ ነበርና ጌታችን የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ በተወለደ ጊዜ እርቀ ሰላም ተገኝቷል፡፡

 

ሰውና መላእክት፡- አባታችን አዳም ከእግዚአብሔር ጋር በተጣላ ጊዜ ቅዱሳን መላእክትም ስለተጣሉት በምትገለባበጥ ሰይፈ እሳት አስፈራርተው ከገነት ከአስወጡት በኋላ ወደ ገነትም እንዳይገባ ገነትን ይጠብቁ ነበር፡፡ ጌታችን በተወለደ ጊዜ አንድ ሆነው ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ ይኸውም ዮም አሐደ መርኤተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብህዎ ለክርስቶስ እንዲል፡፡ ሰውና መላእክት ክርስቶስን ለማመስገን አንድ ሆኑ  እንዳለ ሊቁ፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን ጌታችን የተወለደባት እና ሰባቱ መስተጻርራን አንድ የሆኑባት፤ ሰውና መላእክት የዘመሩባት የብርሃን ጎርፍ የጎረፈባት እንስሳት እስትንፋሳቸውን የገበሩባት ቤተልሔም በቤተ ክርስቲያን ትመሰላለች፡፡

 

ቤተልሔም፡- ተለያይተው የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ ፤ሰውና እግዚአብሔር፤ ነፍስና ሥጋ ፤ሰውና መላእክት አንድ ሆነው በቤተልሔም እንደዘመሩ ዛሬም የፍቅር ተምሳሌትና የአማኞች ሁሉ እናት በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዘር፣ በጎሣ፣ በጥቅም፣ በሥልጣን ሳንከፋፈል አንዲት ቤተ ክርስቲያንን በፍቅር እንድናገለግል በቤተልሔም የተደረገው የልደቱ ምሥጢር ይህን ያስተምረናል፡፡

ክርስቲያኖች የጌታን መወለድ የምናስበው በዚህ መንፈስ ነው፡፡

st. tekela

“ወብዙኀን ይትፌሥሑ በልደቱ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል” ሉቃ.1፥14

ታኅሣሥ 25 ቀን 2005 ዓ.ም.

ዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

st. tekela

  • በዘመነ ብሉይ የእግዚአብሔር ድምፅና የመልአክ ብሥራት ብርቅ በነበረበት ወቅት ካህኑ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ ልጅ መውለድ አጥተው ባረጁበት ዘመን የእግዚአብሔር መልአክ ካህኑ ዘካርያስን እንዲህ አለው፡፡

መልአኩም እንዲህ አለው “ዘካርያስ ሆይ፥ አትፍራ፤ ጸሎትህ በእግዚአብሔር ፊት ተሰምቶአልና፤ ሚስትህ ኤልሣቤጥም ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፡፡ ደስታና ሐሤትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናልና የወይን ጠጅና የሚያሰክርም መጠጥ ሁሉ አይጠጣም፤ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮም መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል፡፡ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ይመልሳቸዋል፡፡ እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የከሓድያንንም ዐሳብ ወደ ጻድቃን ዕውቀት ይመልስ ዘንድ፥ ሕዝብንም ለእግዚአብሔር የተዘጋጀ ያደርግ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኀይል በፊቱ ይሄዳል፡፡”ሉቃ1፥13-18 ይህ ለመጥምቁ ዮሐንስ የተነገረ ቃል ቢሆንም ወላጆቹ (ካህኑ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ) በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን እንደነበሩ በቅዱስ ወንጌል ተገልጿል /ሉቃ.1፥6-7/ እንደዚሁ ሁሉ ካህኑ ጸጋዘአብና ሚስቱ እግዚእ ሐረያ በእግዚአብሔር ሕግና ሥርዓት ይመሩ የነበሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ ይህም ሊታወቅ በትሩፋት ሥራ፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋት የታወቁ ነበር፡፡ በተለይም የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል በዓልን ምክንያት በማድረግ ይመጸውቱ ነበር፡፡ የመልአኩም ጥበቃ ባለ ዘመናቸው ሁሉ አልተለያቸውም ነበር፡፡ ጌታችን በቅዱስ ወንጌል ላይ “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፣” /ማቴ.7፥17/ እንዳለ፣ ለዓለም ሁሉ የወንጌልን ብርሃን የሚያበስር ሐዲስ ሐዋርያ በቅድስናና በክብሩ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ሃያ አምስተኛ ሆኖ ያመሰገነውን ጻድቅ ወለዱ፡፡ በሰሜን ሸዋ ጽላልሽ ልዩ ስሙ ኢቲሳ በተባለ ቦታ የተወለዱት ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሡና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከየመን እስከ ኬንያ ከሶማሌ እስከ ሱዳን ድረስ የተስፋፋበትን ወርቃማ ዘመንን ያስገኙ ጻድቅ አባት ናቸው፡፡

“ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ” እንዲሉ የጻድቁን ታሪክ በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡


ቅዱሳኑ በትሩፋት ሥራ የተጠመዱ ነበሩ

ልጅ አጥተው ሲያዝኑ ይኖሩ የነበሩት ካህኑ ፀጋ ዘአብና ቅድስት እግዚእ ሐረያ፣ በየወሩ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል ያከብሩ ነበርና መጋቢት 12 ቀን የተራበን ሲያበሉ ሞቶሎሚ ንጉሠ ዳሞት ሀገራቸውን ወርሮ ከእነርሱ ደረሰ፡፡ ጸጋ ዘአብም እንደማይምራቸው አውቀው አንከርት ወደሚባለው ባሕር ሮጡ፡፡ ከሞተሎሚ ጭፍሮች አንዱ ተከተላቸው፣ የማይደርስባቸው ሲሆን ሰይፉን ሊወረውርባቸው ቃጣ፡፡ ሰይፉ ከእጁ ተጠቅልላ ቀረች፡፡ በሌላ እጁ ሁለተኛ ሊወረውር ቢቃጣ አሁንም ተጠቅልላ ቀረች፡፡ እሳቸውም እንዳልተዋቸው አይተው ዘለው ከባሕር ገቡ፡፡ ከባሕር ውስጥ ሆነው እንዲህ አያሉ ይጮሁ ጀመረ…” ኀይል የምትሆነኝ ቅዱስ ሚካኤል፣ አምባ መጠጊያ የምትሆነኝ ቅዱስ ሚካኤል፣ ኀይልህ ወዴት ነው? ከኃሊነትህ ወዴት ነው? ተአምራት ማድረግህ ወዴት ነው? እንሆ መሞቻዬ ደረሰ፡፡ ዛሬ የሽብር ቀን ነው፡፡ ዛሬ የመከራ ቀን ነው፡፡ ዛሬ ጥፋት ተፈርዶብኝ፡፡ በበዓልህ ደስ ሳታሰኘኝ ታሳዝነኛለህን? እያሉ ያለቅሱ ጀመረ፡፡ እስመ ለመላእክቲሁ ይኤዝዞሙ በእንቲአከ ከመ ኢትትዐቀፍ በዕብን፤ እግርከ በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዛቸዋልና፣ እግርህ በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸውም ያነሡሃል፡፡ እንዲል /መዝ.90፥11/ ቅዱስ ሚካኤል በውስጥ ሆኖ ተቀብሏቸዋል፡፡ “ወባሕርኒ ኮነቶ ከመ ደብተራ ዘድለት ለማኅደር” ይላል ባሕርም እንደ ድንኳን ሆነላቸው “ኦ ፍቁርየ ጸጋ ዘአብ አስመ አነ አዐቅበከ በይነ ዘይወጽእ እምሐቁከ፤ ወዳጄ ጸጋ ዘአብ ሆይ፥ ከአብራክህ ስለሚከፈለው ቅዱስ እጠብቅሃለሁና አትፍራ” አላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ በሦስተኛው ቀን አውጥቶ ቤተ ክርስቲያን አድርሷቸዋል፡፡

 

በሌላ በኩል በሞቶሎሚ ወታደሮች የተማረኩት እግዚእ ሐረያ ለንጉሡ ሚስት ሊያደርጓቸው፣ ከቤተ መንግሥቱ አገቧቸው፡፡ ቅድስት እግዚእ ሐረያ ግን “ጌታዬ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስንፍናዬን ለምን ተመለከትክ፡፡ በንጹሕ ሆኖ የሚያገለግል ባሪያህ ጸጋ ዘአብን ለምን አላሰብከውም አንተን ለሚክዱ ኃጥአን ለሚሆኑ ጠላቶች አሳልፈህ ለምን ሰጠኸኝ ሕግህን ሥርዓትህን ከማያውቅ ከሚያጸይፍ ባሪያ ልጅ ትሰጠኝ ዘንድ ወደድክን? ከዚያም ከንጹሕ አገልጋይህም ቢሆን አንተን ደስ የማያሰኝ ልጅ ካለሆነ ማኅፀኔን ዝጋው እልሃለሁ፡፡ አቤቱ የትድግና ባለቤት ዛሬ በእኔ ላይ ትድግናህን ግለጽ” በማለት ያመለክቱ ነበር፡፡ ጠባቂ መልአካቸው፡- ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦ ከሠራዊት ሞቶሎሚ በመንጠቅ በክንፉ ታቅፎ ከዳሞት ዞረሬ በሦስት ሰዓት አደረሳቸው፡፡ በመጋቢት ሃያ ሁለት ቀን ጸጋ ዘአብ ከቤተ መቅደስ ገብተው ሲያጥኑና ስለ እግዚእ ሐረያ ሲለምኑ፣ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ከቤተ መቅደስ አግብቶ ከዚያ ትቷቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ገድለ ተክለሃይማኖት ምዕ.12

 

በዚህ ሁኔታ በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ደግም የተገናኙት ሁለቱ ቅዱሳን /ጸጋ ዘአብና እግዚእ ሐረያ/ መጋቢት ሃያ አራት ቀን ከአብራካቸው የሚከፈለውን ጻድቁ ተክለሃይማኖትን ፀነሱ፡፡ እነሆም ታኅሣሥ 24 ቀን ቅዱስ አባታችን ተወለዱ፡፡

 

“ገድለ ተክለሃይማኖት” የተባለው መጽሐፍ አባታችን ተክለሃይማኖት በተፀነሱበት መጋቢት 24 ቀን ለእናትና አባታቸው እግዚአብሔር ራእይ እንዳሳያቸው ይገልፃል፡፡ ቅድስት እግዚእ ሐረያ ያዩት ራእይ “የብርሃን ምሰሶ ከቤታቸው ውስጥ ቁሞ የሞሶሶው ራስ ከሰማይ ደርሶ በዓለም ያሉ ሕዝብ ሁሉ ነገሥታቱም ጳጳሳቱም በዙሪያው ቁመው እኩሌቶቹም ይሰግዱለታል፤ እኩሌቱቹም እሱን ጥግ አድርገው ይቀመጣሉ፡፡ በሱም ላይ ብዙ አዕዋፍ ተቀምጠውበታል፡፡እኩሌቶቹ ነጫጮች፣ እኩሌቶቹም ቀያዮች፣ እኩሌቶቹ አመድ አመድ ይመስላሉ፡፡ ዝጉርጉርም ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ካህኑ ጸጋ ዘአብ ደግሞ በዚሁ ሌሊት ስላዩት ሕልም ለእግዚእ ሐረያ ሲነግሩ እንዲህ ብለዋል፡- “ከምንተኛበት አጎበር ሥር ፀሐይ ሲወጣ፥ስፍር ቁጥር የሌላቸው ብሩሃን ከዋክብት በክንፉ ላይ ተቀምጠው ለዓለሙ ሁሉ ሲያበሩ፣ ከብርሃኑም ብዛት የተነሣ ሀገሩ ሁሉ አበራ፡፡ ይህን ራእይ ዐይቼ ደንግጬ አለቀስኩ”

 

ከዚህ በኋላ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል የሁለቱንም ህልም ይተረጉሙላቸው ዘንድ ከእግዚአብሔር ተልኳል፡፡ በትርጓሜውም፡- “ከጸጋ ዘአብ ቤት ሲወጣ የታየው ፀሐይ ከአብራኩ የሚከፈለው ልጁ ተክለ ሃይማኖት ነው፡፡ በብርሃኑ ከምእመናን ላይ የኃጢአትን ጨለማ የሚያርቅ ይሆናል፤ በክንፉም ላይ ታዝለው፥የታዩት ከዋክብት በመንፈስ ቅዱስ በእርሱ ትምህርት ይወለዱ ዘንድ ያላቸው ልጆቹ ናቸው፡፡ የእግዚእ ሐረያ ሕልም ትርጉሙ እንዲህ ነው በቤታቸው የብርሃን ምሶሶ ቁሞ ራሱ ከሰማይ ደርሶ ያያቸው ልጅህ ነው፡፡ ነገሥታቱ ጳጳሳቱ ሲገዙለት ያየችውም በእውነት ነገሥታቱ ይሰግዱለታል፡፡ አሕዛብም ይገዙለታል፡፡ ለሁሉም መጠጊያ ይሆናል፡፡ ከነገሥታቱ በላይ ሆኖ ይኖራል፡፡ ተአምራቱ ከዛፍ ፍሬ ይበዛል ሥፍር ቁጥር የለውም፡፡ እንደሣዕረ ምድር ጸንቶ ይኖራል፡፡ ስሙም ለዘለዓለም ሲመሰገን ይኖራል፡፡ ሰማይ ከምድር በላይ እንደሆነ የሱም ስም አጠራሩ እንደሱ ካሉ ከቅዱሳን ምእመናን በላይ ሆኖ ይኖራል፡፡ የሕልማችሁ ትርጓሜ ይህ ነው፡፡” በማለት የሕልሙን ፍች አስታውቋቸዋል፡፡

 

በሚያስደንቅ ልዩ ልዩ ተአምራት በቅዱስ ሚካኤል ጥበቃና በእግዚአብሔር ቸርነት ከብዙ መከራ ተጠብቀው የኖሩት ሁለቱ ቅዱሳን ባልና ሚስት /ካህኑ ጸጋ ዘአብና ቅድስት እግዚእ ሐረያ/ ታኅሣሥ 24 ቀን ፃድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ወለዱ፡፡

 

ከሠተ አፉሁ

ታኅሣሥ 26 ቀን /በተወለዱ ሦስተኛው ቀን/ በዕለተ ሰንበት ከጧቱ ሦስት ሰዓት ላይ እጆቻቸውን አንሥተው ወደ ሰማይ እየተመለከከቱ “አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ ማለትም፦ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በባሕርይ በሕልውና አንድ የሚሆን አብ በአካል በስም ልዩ ነው፣ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በባሕርይ በህልውና አንድ የሚሆን ወልድ በአካል በስም ልዩ ነው፣ በህልውና አንድ የሚሆን መንፈስ ቅዱስ በአካል በስም ልዩ ነው” በማለት ሰማያዊያን  መላእክት ምድራውያን ጻድቃን ፈጣሪን በሚያመሰግኑበት ሥርዓት ሆነው አመሰገኑ፡፡ እናትየው እግዚእ ሐረያ ግን ይህንን በልባቸው እያደነቁ “ልጄ ፍሥሐ ጽዮን ምን ትላለህ ይህ ቃል የአባትህ ሥራ ነው፡፡ ላንተ ግን የሚገባህ ጡት መጥባት ነው” በማለት ተናገሩ፡፡ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ግን ክቡር ዳዊት “እም አፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስትዳሎከ ስብሐት፡፡ በእንተ ጸላዒ ከመ ትንሥቶ ለጸላኢ ወለገፋዒ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት” በማለት የተናገረው ቃል ተፈጽሞላቸዋል፡፡ መዝ.8፥2

 

“በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል” ተብሎ በመጋቢ ሐዲስ በቅዱስ ገብርኤል የተነገረለት ዮሐንስ መጥምቅ /ሉቃ.1፥14/ ከእናት አባቱ አልፎ ብዙዎችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያገናኘ የደስታ ምንጭ የሆነ ነቢይም ሐዋርያም ነው፡፡ በጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት መወለድም፣ ለጊዜው ልጅ ባለማግኘት ለብዙ ዓመታት ሲያዝኑ ለነበሩ ወላጆቻቸው ታላቅ የምሥራችና ደስታ ሆኗል፡፡በፍጻሜው ግን ፈጣሪያቸውን ባለማወቅ በአጋንንት አገዛዝ ሥር ወድቀው የነበሩ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በጸሎታቸው ኀይልና ግሩም በሆነው ትምህርታቸው ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስን ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብና፣ ከባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት አውቀው ተረድተው ለስሙ እንዲገዙ አድርገዋል፡፡

 

ነቢዩ ኤርሚያስን ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔር ከእናቱ ሆድ ጀምሮ ለቅድስና ለክብር በነቢይነት እንደጠራው በመጻሕፋችን ተገልጦአል፡፡ /ኤር.1፥5/ ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖትም ለኢትዮጵያ ሰዎች ሐዋርያ ሆነው ያገለግሉ ዘንድ በባለቤቱ በመድኀኔዓለም በኢየሱስ ክርስቶስ አንደበት “እስመ ረሰይኩከ ሐዲስ ሐዋርያ፤ አዲስ ሐዋርያ አድርጌ ሾሜሃለሁ” ተብሎ የተነገረላቸው ናቸው፡፡ በዚህም በጌታችን ቃል “በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ እርሱም ይሠራል ከዚያም የሚበልጥ ይሠራል” /ዮሐ.14፥12/ ተብሎ በተነገረው ቃል መሠረት፤ በሰው ሰውኛ ሊደረጉ የማይችሉ ታላላቅ ተአምራትን በመፈጸም ኢ-አማንያንን ወደ ሃይማኖት መልሰዋል፡፡ ተጋድሏቸውን የመዘገበው መጽሐፍ /ገድለ ተክለ ሃይማኖት/ እንደተመዘገበው በዛፍ ላይ አድሮ ሲያሰግዳቸውና ሲያስመልካቸው የነበረ ጋኔኑን አዋርደው እርሱን ከኢትዮጵያ ምድር አርቀው በአምልኮተ ባዕድ የነበሩ ሰዎችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ቀላቅለዋል፡፡

 

ባለብዙ ገድል ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት “ዳግማዊ ዮሐንስ” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ሐዋርያ ናቸው፡፡ ዮሐንስ መጥምቁ በተፀነሰ ጊዜ የአባቱን አንደበት የዘጋ፣ ሲወለድ ደግሞ የአባቱን አንደበት ዳግመኛ የከፈተ ነው፡፡ (ሉቃ.1፥62-66) መምህር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገድ የተባለለት፥ ዮሐንስ መጥምቁ ንጉሥ ሔሮድስን ሳይፈራና ሳያፍር የገሰጸ እንደሆነ ሁሉ፤ አባታችን ተክለ ሃይማኖትም  እንደ ሞቶሎሚ ያሉ ጣዖት አምላኪና አስመላኪ ነገሥታትና ኀያላንን ሳይፈራ የተጠራለትን አገልግሎት በጽኑ መታመን የፈጸመ ነው፡፡

 

ፈጣሪያችን ከጻድቁ አባታችን ከተክለሃይማኖት በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡ አሜን

ST. Gebreale

እኛ የምናመልከው አምላክ ኪሚነደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፡፡ ት.ዳን.3፥17

ታኅሣሥ 18 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ኀይለ ኢየሱስ ቢያ

 

ST. Gebrealeንጉሡ ናቡከደነጾር በዱራ ሜዳ ላቆምኩት የወርቅ ምስል ካልሰገዳችሁ ከእጄ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ በኀይልና በዛቻ በጠየቃቸው ጊዜ ሠለስቱ ደቂቅ በልበ ሙሉነት፥ በፍጹም እምነት፥ መልስ የሰጡበት ኀይለ ቃል ነው፡፡ ከኀይለ ቃሉ ቅዱስ ዳዊት አመንኩ በዘነበብኩ /በተናገርሁት አመንሁ፤ እንዳለ መዝ.115፥1 ፍጹም እምነታቸውንና ታማኝነታቸውን፣ ጽናታቸውን እንረዳለን፡፡ ዛሬ የምናከብረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓል ሠለስቱ ደቂቅን ከባቢሎን እሳት ያዳነበት ነው፡፡ ታሪኩ የተፈጸመው በብሉይ ኪዳን ዘመን ከ605-562 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በነገሠው በናቡከደነጾር ዘመን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ከጣዖት አምላኪና አስመላኪ ኀያላን ነገሥታት መካከል አንዱ ናቡከደነጾር ነበር፡፡ ምስሉ የቆመው በ587 ቅ/ል/ክ እንደሆነ መተርጎማን ያስረዳሉ፡፡ ዳን.3፥1 ናቡከደነጾር እስራኤላውያንን በማረከበት ዘመን ዳንኤልንና ሦስቱን ሕፃናት በልዩ ሁኔታ አክብሯቸው ነበር፡፡

 
 
            • ዳንኤልን ብርጣሶር አለው አሰበ በል አምኃ ቤል ሲል ነው
            • አናንያንም ሲድራቅ አለው ወልደ ሰቃየ አትክልት /አትክልተኛ/ ማለት ነው
            • ሚሳኤልንም ሚሳቅ አለው ፀሐቂ ተጋሂ ፍንው ለግብር መልእክት  /ትጉህ ፈጣን መልእክተኛ/ ማለት ነው፡፡
            • አዛርያንም አብደናጎም አለው ገብረ ዳጎን /የጣዖት አገልጋይ/ ማለት ነው፡፡ የቀድሞ ስማቸው ትርጉም ግን
            • ዳንኤል ማለት ፍትሕ እግዚአብሔር ዳኛ እግዚአብሔር
            • አናንያ ማለት ደመና
            • ሚሳኤል ማለት ሰምዓኒ እግዚአብሔር /እግዚአብሔር ስማኝ/
            • አዛርያ ማለት ረድኤት ማለት ነበር፡፡ ት.ዳን.1፥7

            ንጉሡ እነዚህን ሕፃናት ለሦስት ዓመት በቤተ መንግሠት ጥሩ ምግብ እየተመገቡ የከለዳውያንን ትምህርትና ቋንቋ ያጠኑ ዘንድ አዝዞ ነበር፡፡ እነርሱ ግን ትምህርቱን እየተማሩ በንጉሡ ቤት የተዘጋጀውን ምግብና መጠጥ ሳይመገቡ ጥራጥሬና ውኃ እየተመገቡ በፈተና ያለፉ ነበሩ፡፡ ዳን.1፥8-21

            ጠቢባንና አስተዋዮች በመሆናቸው በባቢሎን አውራጃዎች ላይ ተሾሙ፡፡ ዳን.2፥46-49 የሠለስቱ ደቂቅ በንጉሡ ዘንድ መወደድና መሾም ያስቀናቸው ባቢሎናውያን ለናቡከደነጾር “በባቢሎን ሀገሮች ለሚሠራ ሥራ የሸምካቸው ከአይሁድ ወገን የሚሆኑ ትእዛዝህን እምቢ ያሉ አምላክህን ያላመለኩ ለሠራኸውም ለወርቁ ምስል ያልሰገዱ ሚሳቅና ሲድራቅ አብደናጎም የሚባሉ ሦስት ሰዎች አሉ” ብለው ከሰሷቸው ያን ጊዜም ንጉሡ ተቆጣና እንዲሰግዱ አዘዘ፡፡ እነርሱም አንሰግድም አሉ፡፡ “ያን ጊዜም …… ዳን.3፥13-19”

            ናቡከደነጾር ሦስት ዓይነት መንገዶችን ተጠቅሞ ለምስሉ ለማሰገድ ጥረት አድርጓል

            1. በመጀመሪያ ዐዋጅ በማወጅ ነው ይህ ዐወጅ ከተራው እስከ ባለሥልጣናቱ ያሉትን የሚመለከት ነበር፡፡ በተለይም ባለሥልጣናቱ ቀድመው በመስገድ አርአያ እንዲሆኑ ተጋብዘዋል፡፡
            2. ሁለተኛው የሕዝቡን ልብ በሙዚቃ እንዲደሰቱ በደስታው ተውጠው ሳያስቡት እንዲሰግዱ ማድረግ
            3. የመጨረሻው በማስፈራራት /ወደ እሳት ትጣላላችሁ እያለ/ እንዲሰግዱ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን የቱንም ያህል ቢያባብልና ቢጥር ሠለስቱን ደቂቅ ለማሰገድ ያደረገው ሙከራ  አልተሳካለትም፡፡

            ሠለስቱ ደቂቅ ጣዖት አናመልክም ካሉ ለምን ወደ ጣዖቱ መጡ? ቢሉ

            1. ለምስክርነት፡- የአምልኮ ጣዖትን ከንቱነትና የእግዚአብሔርን ክብር ለመመስከር
            2. ለአርአያነት፡- በምርኮ ያሉት እስራኤላውያን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ አርአያ ለመሆን ነው፡፡

            ሠለስቱ ደቂቅ ለንጉሡ የትእዛዝ ለመቀበል ምክንያት አላቸው፡፡ ግን ተቃወሙት

            1. ወጣቶችና ምርኮኞች ናቸው
            2. በንጉሡ ሥልጣን ሥር ናቸው፡፡
            3. አንዴ ብቻ ስገዱ ተባሉ እንጂ እግዚአብሔርን ተው አልተባሉም ስለዚህም፡- “ለዛሬ  ተመሳስለን እንለፍ” ማለት ይችላሉ፡፡
            4. “የንጉሡ ውለታ ይዞን ነው” ማለት ይችላሉ
            5. “በባዕድ ሀገር ስለሆንን ነው፡፡”
            6. እንኳስ እኛ በባዕድ ምድር በሰው እጅ ያለነው ቀደመቶቻችን በራሳቸው ፈቃድ ጣዖት አምልከዋል፡፡
            7. “ከሰው ጋር ሲኖሩ ሞኝ ሆኖ አህያ ሲጭኑ ሦስት ሆኖ ነው” በማለት ምክንያት መፍጠር ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ምክንያት አልሰጡም፡፡

            ከሠለስቱ ደቂቅ ሦስት ነገር እንማራለን

            ማመን፣ መቁረጥ እና ማድረግን፡፡ ሃይማኖት እነዚህን 3 ነገሮች ይፈልጋል፡፡ ሦስቱ ሕፃናት በእግዚአብሔር ፍጹም አመኑ፣ ይህንንም እምነታቸውን ሲገልጡ “የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል” በማለት ተናግረዋል፡፡ የመጣባቸውን ሁሉ ለመቀበል ወሰኑ ቆረጡ “አምላካችን እኛን ማዳን ይችላል ነገር ግን ፈቃዱ ከዚህ እሳት ገብተን ሠማዕትነትን እንድንቀበል ቢሆን ከእሳት እንገባለን” በማለት አንድ ልብ፣ አንድ ቃል ሆነው አቋማቸውን ገለጡ፡፡ የቆረጡትን ነገር አደረጉት፤ ወደ እሳት ውስጥ ተወረወሩ ሦስቱም ነገሮች ስለተፈጸሙ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ እሳቱን አብርዶ አዳናቸው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል” በማለት የተናገረው ቃልም ተፈጽሞላቸዋል፡፡ /መዝ.33፥7/ ጠባቂ መልአካቸው ቅዱስ ገብርኤል በእሳት ውስጥ ገብቶ ከመከራ ሥጋ አድኖአቸዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራና መልአኩል ልኮ የፈጸመውን ትድግና ያየው ናቡከደነጾር “ናቡከደነፆርም መልሶ፡- መልአኩን የላከ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይባረክ፡፡ እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብድናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቆረጣሉ ቤቶቻቸውም የጉድፍ መጣያ ያደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ፡፡ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብድናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፡፡” ዳን.3፥28-30

            ናቡከደነጾር ሦስት ነገሮችን አስተውሏል

            1. ሠለስቱ ደቂቅ ፈጣሪያቸውን በመዝሙር ሲያመሰግኑ ሰምቷል፡፡
            2. እሳቱ በወጣቶች ላይ ምንም ጉዳት እንዳላደረሰባቸው አስተውሏል
            3. ሰው ያልሆነ ፍጡር አብሯቸው መኖሩን አውቋል ከዚህ የተነሣ አማኞችንም ፈጣሪያቸውንም አመስግኗል፡፡ “መልአኩን የላከ…. የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይመስገን” ብሏል፡፡ ዳን.3፥28

            የእግዚአብሔርን ጥበቃ ስናነሣ ጥበቃው በብዙ ዓይነት /መንገድ ነው፡፡

            1. የእግዚአብሔር ጥበቃ፡- እግዚአብሔር በመግቦቱ ዓለምን ይጠብቃል ይመራል፡፡ መዝ.22፥1፣ ማቴ.5፥45፣ ማቴ.6፥25፣ 1ኛ ጴጥ.5፥7
            2. የቅዱሳን መላእክት ጥበቃ፡- ቅዱሳን መላእክት በተልእኮ ይጠብቃሉ ይራዳሉ ያማልዳሉ፡፡ መዝ.33፥7 “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል፡፡” ይላል
            3. የካህናት ጥበቃ በማስተማርና በምክር በጸሎት ይጠበቃሉ ዮሐ.21፥15፣ 1ኛ ጴጥ.5፥2፣ ዕብ.13፥17 “ለመምህሮቻችሁ ታዘዙ… ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉና”
            4. የሕግ ጥበቃ ሕግ ሲያከብሩት ሰውን ይጠበቃል ይመራል፡፡ መዝ.118፥105 “ሕግህ ለእግሬ ብሥራት ለመንገዴም ብርሃን ነው”

            ከዚህም ውስጥ የቅዱሳን መላእክትን ጥበቃ ብንመለከት

            ቅዱሳን መላእክት ምንድን ናቸው? አገልግሎታቸው ምንድ ነው ብንል

            • የቅዱሳን መላእክት ተፈጥሮ እግዚአብሔር አምላክ በዕለተ እሑድ እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ/ካለመኖር ወደመኖር አምጥቶ የፈጠራቸው ንጹሐን ቅዱሳን ረቂቃን ፍጥረታት ናቸው፡፡ ኩፋ.2፥5-9፣ መዝ.103፥4፣ ቈላ.1፥16-17
            • ቅዱሳን መላእክት በነገድ መቶ ናቸው ማቴ.18፥11-14 ሳጥናኤል በመሳቱ 99 ነገደ መላእክት ሲሆኑ 100ኛ ነገድ አዳም ሆኗል፡፡
            • ቅዱሳን መላአክት ቁጥራቸው አይታወቅም ት.ኤር.33፥22
            • ቅዱሳን መልእክት ሕያዋን ናቸው ሞት የለባቸውም ማቴ.22፥30

            የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት በሁለት ይከፈላል

            1ኛ. እግዚአብሔርን ያለ ዕረፍት ማመስገን

            ራዕ.4፥6-11፣ ራዕ. 5፥6-14፣ ኢሳ.6፥1፣ መዝ.102፥20፣ ሄኖክ 11፥16 “ለእነርሱ ዕረፈታቸው ምስጋናቸው ነውና ያመሰግናሉ ያከብራሉም አያርፉም”

            2ኛ. ሰውን ያለ ዕረፍት ማገልገል /መጠበቅ/ ነው ማቴ.18፥10፣ ዕብ.1፥14፣ ዘፀ.13፥21፣ ዳን.6፥22 /”አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ”/፣ ዳን.12፥1

            • ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወትን እንዲወርሱ ያግዛሉ ይራዳሉ፡፡ ዕብ.1፥14
            • ቅዱሳን መላእክት ከእግዚአብሔር ወደ ፍጥረታት ለምሕረትም ለመዓትመ ይላካሉ፡፡

            ለምሕረት ሲላኩ

            ት.ዘካ.1፥12 “የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ “አቤቱ ሁሉን የምትችል ሆይ እነዚህን ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና ይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” እያሉ እግዚአብሔርን ይለምናሉ፡፡ ሮሜ.9፥23፣ ዘፍ.19፥12-23 “….ራስህን አድን” አሉት

            ለመዓት ሲላኩ

            2ኛ ነገ.19፥35 “በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ መጣ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ ማለዳም በተነሡ ጊዜ እነሆ ሁሉ በድኖች ነበሩ” 2ኛ ሳሙ.24፥16

            • ቅዱሳን መላእክት ከሰው ወደ እግዚአብሔር ልመናን ምልጃን ያቀርባሉ /የምዕመናንን ጸሎት ያሳርጋሉ/ ራዕ.5፥8፣ ራዕ.8፥2-5፣ ማቴ.18፥10፣ ዮሐ.1፥52
            • ቅዱሳን መላእክት ከክፉ ነገር ሁሉ ይመልሳሉ /ወደ በጎ ይመራሉ/ ዘኁ.22፥32 የእግዚአብሔር መልአክ “መንገድህ በፊቴ ቀና አልነበረምና አቋቁምህ ዘንድ መጥቼአለሁ አለው፤ ለክፋት ተነሥቶ የነበረውን ለበጎ አደረገው፡፡
            • ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን ያጽናናሉ ያበረታታሉ፡፡ 1ኛ ነገ.19፥5፣ ዳን.10፥13-21፣ ሉቃ.22፥43 “የሚያበረታታው የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ታየው” ማቴ.4፥11 “እነሆም መላእክት ሊያገለግሉት መጡ” እኛንም በችግራችን ጊዜ ሊያገለግሉን ይመጣሉ፡፡
            • ቅዱሳን መላእክት ከሰይጣን ተንኮልና ስሕተት ይጠበቃሉ ይታደጋሉ ዘፀ.23፥20-23፣ መዝ.90/91፥11-12
            • ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን ለሚገዳደሩና ለሚጠረጠሩ ይቀስፋሉ  መዝ.34፥5-6

            በአጠቃላይ ስለ ቅዱሳን ምልጃ ስናነሣ 3 ነገሮች መኖራቸውን ማወቅ መረዳት ይገባናል፡፡

            1. የሚለመነው የሚማለደው እግዚአብሔር ይቅር ባይ መኖሩን ዘፀ.32፥11-15
            2. የሚለምን/ የሚማልድ አስታራቂ መልአክ/ጻድቅ መኖሩን ት.ዘካ.1፥12
            3. የሚለመንለት ሰው/ ተነሣሂ ይቅርታ ጠያቂ/ መሆን አለበት ሉቃ.18፥13፣ ዘፍ.20፥7
            • የሚለመንለት ሰው አማኝ ተነሣሂ መሆን አለበት ት.ሕዝ.14፥14፣ መዝ.33፥7
            • ለማስታረቅ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ፣ ብቃት መመረጥ መወደድ ያስፈልጋል የሐዋ.19፥11-20፣ ዘኁ12፥1
            • ለማስታረቅ በሰው ፊትም ቢሆን መወደድ መከበር ተሰሚነት ያስፈልጋል፡፡
            • በአጠቃላይ ሠለስቱ ደቂቅ በእምነታቸው ጽናት የእግዚአብሔርን ቸርነት የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልን ጠባቂነት በግልጽ አሳየተው አስረድተዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ ነው ንጉሡ “መልአኩን የላከ.. የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የሲድራቅና የሚሳቅ፣ የአብደናጎም አምላክ ይመስገን” ያለው፡፡
            • እኛም በክርስትናችን ጸንተን በሥነ ምግባራችን ለሌሎች ምሳሌ በመሆን ከዚህ ክፉ ዓለም በእግዚአብሔር ቸርነት በቅዱሳን ጸሎትና ተራዳኢነት በወላዲተ አምላክ አማላጅነት ንስሐ ገብተን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን የስሙ ቀዳሽ የመንግሠቱ ወራሽ ለመሆን ያብቃን፡፡

            የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አይለየን

            ወስብሐት ለእግዚአብሔር

            አሜን

            ምንጭ፡- ድርሳነ ቅዱስ ገብርኤል

            • ስንክሳር ግንቦት 10 ቀን
            • መዝገበ ታሪክ
            • ትንቢተ ዳንኤል ከዘመነ ባቢሎን እስከ ዓለም ፍጻሜ፡፡
            dn tewedreose getachew

            ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ምን ይላሉ?

            ታኅሣሥ 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

            • “በቤተ ክርስቲያን ነጻነት ያለበት አመራር ሊኖር ይገባል”

            ዲ/ን ቴዎድሮስ ጌታቸው

            በደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል

            ከሐመረ ብርሃን ሰንበት ት/ቤት

            dn tewedreose getachewየቅዱስ አባታችን ዕረፍት ምክንያት በማድረግ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ፓትርያርክ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ እንደ እኔ አመለካከት የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ለማስጠበቅ ዕርቁን አስቀድሞ  መካሔድ ያስፈልጋል፡፡  ምርጫውም መፈጸም ያለበት ከዕርቁ በኋላ ቢሆን ተገቢ ይመስለኛል፡፡

             

            ምርጫውን በማስመልከት በተለይ በዚህ ዘመን እርስ በእርስ የሚጣረሱ ወሬዎች እየወጡ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባለን ሰዎች፣ በካህናቱም ዘንድ እየተወራ፣ እየታየም ያለው “እገሌ ይመረጥልን፤ ምርጫው ከእገሌ አይ ወጣም” በማለት አላስፈላጊ የቲፎዞ ነገር ነው፡፡ ብፁዓን አባቶቻችን የፓትርያርክ ምርጫውን ተረጋግተው ማካሔድ አለባቸው፡፡ አንዳንዶች ምርጫው በጎጥ፣ በጎሣ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን፤ በቡድን የሚንቀሳቀሱ አሉ ይባላል፡፡ ይህ ክርስቲያናዊ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አባቶቻችን እነዚህን እኩይ ሤራ የሚያራምዱትን ሰዎች በንቃት ሊከታተሏቸውና ሤራቸውንም ከምንጩ ሊያደርቁት ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የፈቀደው፣ መንፈስ ቅዱስ ያዘጋጀውን ሰው ለመመረጥ ተረጋግቶ ሁኔታዎችን ማጤን የሚያስፈልግበት ወቅት በመሆኑ፤ አባቶቻችን በዚህ ላይ ጥንቃቄ ሊያ ደርጉ ይገባል እላለሁ፡፡ ከዛ ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጃት ማነው? የሚለውን ነው መመልከት ያለብን፡፡ የዘር ጉዳይ በካህናቱ ብቻ ሳይሆን ወደ አንዳንድ ምእመናንም ወርዶ ይታያል፡፡ ብፁዓን አባቶች እነዚህ አላስፈላጊ ግፊት ከሚያደርጉ ሰዎች ሊጠነቀቁ፣  ምእመ ናንም ከዚህ ዓይነት ድርጊት ሊቆጠቡ ይገባል፡፡

             

            ምርጫው የተሳካ ይሆን ዘንድም ጳጳሳቱ፣ ሊቃውንቱ፣ ካህናቱና ምእመናኑ በአንድነት ጸሎት ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጃትን አባት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንዲያዘጋጅልን ቅድሚያ ጸሎት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችም ከአባቶች እግር ሥር ሆነን የጸሎቱ ተካፋይ በመሆን እግዚአብሔር ጥሩ አባት እንዲሰጠን ተግተን መጸለይ አለብን፡፡

             

            ፓትርያርኩ ከተመረጡ በኋላ በቤተ ክርስቲያን የሚጠብቃቸው ተግዳሮቶች በእኔ ዕይታ የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳደር የሚመለከት ነው፡፡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ድረስ ያለው አስተዳደሯን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ከሚታዩት አስተዳደራዊ ችግሮች የተነሣ፤ የተለያዩ በደሎች እየተፈጸሙ ነው፡፡ ምእመናንም ይህን በመመልከት ከቤተ ክርስቲያን እየራቁ ያሉ፣ ጥቂት አይደሉም፡፡ ‹‹ተሐድሶዎች›› በስውር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴም ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡ ሌላው በቤተ ክርስቲያኗ ሥር ሰዶ የሚታየው የጎጥና የጎሳ ችግር ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን የሚሾመው መስፈርቱ ዕውቀቱ፣ በመንፈሳዊ ሕይወቱ እንጂ ከየትኛው ዘር የመጣ ነው የሚለው መቅደም የለበትም፡፡ ስለዚህ ተመራጩ ፓትርያርክ እነዚህን ሥር የሰደዱ ጉዳዮች የማስተካከል ትልቅ ሓላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡

             

            ሌላው ቃለ ዓዋዲው በሥራ እንዲተረጐም መሥራት ያለባቸው ይመስለኛል፤ በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያን  ከቃለ ዓዋዲው ውጭ የሚሠሩ ሥራዎች እየበዙ መጥተዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን አምባገነናዊ አሠራር መወገድ አለበት፡፡ አምባገነናዊ አሠራር ጥሩ ሙያ ያላቸውን፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚያስቡ ቅን አገልጋዮችን ያርቃል፡፡ ተመራጩ ፓትርያርክም ሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ ለተዘረዘሩት ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት፤ ቤተ ክርስቲያን ነጻነት ያለበት አመራር እንዲኖራት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

             

            በሰንበት ትምህርት ቤት የተሰባሰብንም ወጣቶች የቤተ ክርስቲያናችንን ወቅታዊ ጉዳይ እየተወያየን ነው፡፡ ዘመኑ የቴክኖሎጂ በመሆኑ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ስለ ቤተ ክርስቲያን  የተለያዩ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ በዚህም  ምንማድረግ አለብን? የሚለው መወያያችን ሆኗል፡፡ የውይይታችን ጭብጥም እግዚአብሔር ጥሩ አባት እንዲሰጠን ከመመኘት አንጻር በመሆኑ በግልም፣ በጉባኤም ጸሎት እያደረግን ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም በሐመር መጽሔት ይህን መድረክ ከፍቶ ወጣቶች፣ ምእመናን፣ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ቅን የሚያስቡ ሁሉ አስተያየት እንድንሰጥ በማድረጉ በጣም እናመሰግናለን፡፡ ወደፊትም በዚሁ ይቀጥል እላለሁ፡፡

             

            • “በተፈጠረው ክፍተት ክፉዎች እየተጠቀሙበት ስለሆነ ዕርቁ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ”

            ዘሪሁን መንግሥቱ

            በመንበረ መንግሥት /ግቢ/ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም

            ከዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት

            ቤተ ክርስቲያናችን ፓትርያርክ እንዴት መመረጥ እንዳለበት ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን የሚያውቀው መመሪያ ሊzerehune mengestueኖራት ይገባል፡፡ ሰዎች በዘር፣ በጐጥ፣ በአካባቢ ፓትርያርክ ለማስመረጥ ጥረት እንደሚያደርጉ  አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም አይደለም፡፡ ሐዋርያትን የመረጣቸው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም የሚመሩ አባቶች የሚመርጥ እግዚአብሔር ነው፡፡

             

            ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ገጥሟት የማያውቀው ፈተና በዘመናችን ተከስቷል፡፡ ከምርጫው በፊት ዕርቁ መፈጸም አለበት፡፡  እንዲያውም ዕርቁ ዘግይቷል ነው የምለው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አሐቲ ሆና ልጆቿ  በአመለካከት የተነሣ ተከፋፍለው “እኔ እገሌን ነው የምከተለው” የማለት አስተሳሰብ ተፈጥሯል፡፡ አባቶቻችን በአሁኑ ወቅት አንድ መሆን አለባቸው፡፡ ሐዋርያት በይሁዳ ምትክ ማትያስን ሲመርጡት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው እንጂ ተከፋፍለው አልነበረም፡፡

             

            ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ በሁለቱም በኩል አባቶች  ወደ አንድ መምጣት አለባቸው፡፡  እዚህ ላይ መታየት ያለበት እስከ ዛሬ ዕርቅ ባለመፈጸሙ ምክንያት ጵጵስና የማይገባቸው ሰዎች ጵጵስና እንዲያገኙ ሆነዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከመመሪያዋ፣ ከቃለ ዓዋዲዋ ከምትመራበት ሕግና ሥርዐት ውጪ እንድትመራ አድርገዋል፡፡ ይህ ክፍተት በመፈጠሩ የእኛን እምነት የማያምኑ ነገር ግን አማኝ መስለው ምእመናንን የሚያሳስቱ የተለያየ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ተጠቅመውበታል፡፡

             

            በምርጫው ላይ ትልቁ ድርሻ የጳጳሳቱ ነው፡፡ አባቶቻችን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ማድረግ የሚገባቸው ብዬ የማስበው ምርጫው እንደ ሐዋርያት መሆን አለበት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያዘው መሠረት ተተኪው ፓትርያርክ እንዲመረጥ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለባቸው፡፡ ሊቃውንት አባቶችም በፓትርያርክ ምርጫ ላይ የራሳቸው የሆነ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ሲገጥማት በችግሯ ጊዜ ሊሆን የሚገባውን ከመግለጽ ዝም ብለው በኋላ “እንዲህ አደረጉት፣ እኛ እኮ እንዲህ ብለን ነበር” ከማለት ይልቅ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ለምእመናኑ ግልጽ የሆነ ነገር ማስረዳት፣ ውዥንብሮችን ማጽዳት፣ ፓትርያርክ ለመምረጥ ከሕዝቡ ምን ይጠበቃል? የሚለውን ማስተማር አለባቸው፡፡ ይህን መሥራት ከሊቃውንቱ በተጓዳኝ ከሊቃነ ጳጳሳቱም ይጠበቃል፡፡ ካህናቱም “እገሌ ስለሚጠቅመኝ ይሾምልኝ፤ ነገ ዕድገት ይሰጠኛል” ብለው ለመሾም፣ ለመሸለም፤ የተለየ ነገር ለማግኘት ብለው ሳይሆን፤ በትክክለኛው ሥርዐት እንዲመረጥ እገዛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለንስሐ ልጆቻቸው በአገልግሎት ለሚያገኟቸው በርካታ ምእመናን  ከአሉባልታ በጸዳ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዐት ለምእመናን የመንገር ሓላፊነት አለባቸው፡፡

             

            ሰንበት ትምህርት ቤት በርካታ ወጣቶችን የያዘ ተቋም በመሆኑ፤ ወጣቱ ከምንም በላይ በፓትርያርክ ምርጫው ሂደት ላይ በንቃት እየተከታተለ ይገኛል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤት ያሉ ወጣቶች ከሊቃውንቱ እግር ሥር ቁጭ ብሎ በመማር ከአባቶች የወረደውን መመሪያ ብዥታ ባልፈጠረ መልኩ ምእመናን የሚያውቁበትን መንገድ ማመቻቸት፤ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ለምእመናን ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት ሂደት ላይ ሙያዊ እገዛ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

            ፓትርያርኩ ከተመረጡ በኋላ በመጀመሪያ የሚጠብቃቸው ሥራ ቤተ ክርስቲያኒቱን አንድ ማድረግነው፡፡ ሌላው መረጃን በተመለከተ ዛሬ የተለያዩ ወሬዎች እየተናፈሱ ነው፡፡ “እገሌ እንዲህ ነው፤ እገሌ እንዲህ ስለሆነ ነው…” የሚሉ ወሬዎችን ምእመናኑ ከማይመለከታቸው አካላት መረጃ እየሰሙ ነው፡፡  ለምሳሌ፡- ቤተ ክርስቲያንን የማያውቀው  ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲጽፍ ይታያል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ስም ለማጉደፍና አባቶቻችን የሌሉበትን ስም እየሰጡ ለማጥፋት የሚጥሩ አካላት አሉ፡፡ ከዚያ ጐንም የተሰለፉ ምእመናንም አሉ፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን አደረጃጀቷ ምን እንደሚመስል፣ ምእመናኖቿ  ምን ዓይነት አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው፣ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት ተቋሞቹ እንዴት መደራጀት አለባቸው፤ ገዳማቶቿ እንዴት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም መገናኘት አለባቸው? የሚሉ ጉዳዮች መልስ ከሚመረጡት አባት ይጠበቃል፡፡

             

            ሲኖዶሱም ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ውሳኔዎችን ከሥር ከሥር እየተከታተለ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በእያንዳንዱ ሥራ አባቶች እታች እየወረዱ ማስፈጸም ላይጠበቅባቸው ይችላል፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ቀጥሎ አህጉረ ስብከቶች በተዋረድ የሚያስፈጽሙበትና ክትትል የሚደረጉበትን መንገድ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል፡፡

             

            ተመራጩ ፓትርያርክ ይህን ትልቅ ሓላፊነት ለመወጣት በመጀመሪያ ያልተሠሩ ሥራዎችን መለየት፣ ቤተ ክርስቲያኗን ተጭነው ያሉ በዘልማድ የተቀመጡ አሠራሮችን ነቅሰው ማውጣት አለባቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቢሮክራሲውን ማስወገድ፣ አስተዳደራዊ ቦታዎች በተማሩ እና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው አርአያ በሚሆኑ  ሰዎች መተካት አለባቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ባስተማረቻቸው ልጆቿ ነው መተዳደር ያለበት እንጂ፤ እንደ ፓርላማ ኮታ “ከእገሌ ብሔር መቅረት የለበትም” በሚል ስሜት ቤተ ክርስቲያን መመራት የለባትም፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት በየገዳማቱ፣ በየአድባራቱ የሚሾሙ በትክክል ተምረው ነው ወይ? የሚለውም መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

             

            ሰንበት ት/ቤቶች በፓትርያርክ ምርጫው ላይ “የእኛ ሱታፌ ምንድን ነው?” በማለት እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን መወያየት፣ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ይጠበቃል፡፡

             

            • “ ‘እነ እገሌ ይመረጡልን’   የሚሉ ቡድኖችን ቅዱስ ሲኖዶስ ማዳመጥ የለበትም”

             

            ወጣት አንተነህ ዐወቀ

            በደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል

            ከእግዚአብሔር ምስሌነ ሰንበት ት/ቤት

            antenehe awekeምርጫው ከመደረጉ በፊት፤ መቅደም ያለበት ዕርቁ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ተከፍላለች፡፡ እዚህ ባለው ሲኖዶስ የምትመራ ቤተ ክርስቲያን፣ ውጭ ባለው ሲኖዶስ የሚመራና እንዲሁም ገለልተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ የሚታወቅ አለ፡፡ በዚህ ወቅት እነዚህ ሦስት ወገኖች ወደ አንድ መምጣት አለባቸው፡፡

             

            ቤተ ክርስቲያን መለያየት የለባትም፤ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ለሀገር አንድነት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ለምሳሌ፡- የኒቂያ ጉባኤ ስንመለከት፤ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የአርዮስ ክህደት ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን፤ ለሀገርም ችግር ይፈጥራል ብሎ በማሰቡ አባቶች ተሰባስበው  ችግሩን እንዲፈቱ ያደረገበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ አሁንም በውጭና በሀገር ውስጥ ባሉት አባቶች መካከል የተፈጠረው ችግር ሰላማዊ በሆነ ነገር መፈታት አለበት፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንድ ስትሆን ነው በአንድነት መሥራት የሚቻለው፡፡ ስለዚህ ዕርቁ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡

             

            ለፓትርያርክ ምርጫው የጳጳሳቱ፣ የካህናቱ፣ የሊቃውንቱ፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ የምእመናኑ፣ የምሁራኑ ቤተ ክርስቲያኗ ጥሩ መሪ እንዲኖራት፣ ምእመናንን በአግባቡ መምራት እንድትችል የድርሻችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ወጣቱ ስለ ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት መረጃ የሚያገኝበት ቤተ ክርስቲያን ምን መሆን አለባት? የቀድሞ አባቶች ያሳለፉት ነገር ምንድን ነው? አሁንስ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ያሳያል? ወደፊትስ ምን መሆን አለበት? የሚለው ነገር በደንብ እየተረዳን ያለንበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል፣ ይጠቅማል የሚለውን  እንደየ ችሎታችን፣ እንደየ ዕውቀታችን፣ እንደየ አቅማችን ማድረግ የሚጠበቅብንን ነገር ሁሉ ማድረግ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡

             

            በሰንበት ትምህርት ቤት እርስ በእርስም ቢሆን ስለ ፓትርያርክ ምርጫ እንወያያለን፡፡ ዛሬ ወጣቱ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ላይ በርካታ መረጃዎች በኢንተርኔት፣ በፌስ ቡክ፣ በተለያዩ ብሎጐች ያገኛል፡፡ ትናንት በነበሩ አባቶች ምን ተሠራ? ዛሬስ ያሉት ምን እየሠሩ ነው? የሚለውን እየተመለከትን ነው፡፡ ትናንት በቤተ ክርስቲያን ላይ ተፈጥሮ የነበረው ችግር ነገ እንዳይቀጥል የድርሻችንን አስተዋጽኦ እንዴት ማበርከት እንዳለብን ሁሌም በተገናኘን ቁጥር እናወራለን፡፡ ምናልባትም ይህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ራእይ ይዛ ለአገልግሎት የምትነሣበት ጊዜ ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶና ወዶ አሁን የታሰበው ምርጫ ወደ ግቡ ደርሶ በጆሮአችን የምንሰማበት ደረጃ ከደረሰን ትልቅ ለውጥ ይኖራል፤ ከበፊቱም የተሻለ ነገር አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ ወጣቱ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ በአትኩሮት እንዲከታተል ያደረገው የሚሰማቸው፣ የሚያያቸው፣ እየተደረጉ ያሉ ትንሽም ቢሆን ፍንጭ የሚሰጡ ነገሮች ስላሉ ነው፡፡

             

            ፓትርያርኩም ከተመረጡ በኋላ ብዙ ከሚጠብቃቸው ሥራዎች ዋና ዋናዎቹ፡- በመጀመሪያ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ችግር ሆነው ያሉ ነገሮችን ለመቅረፍ መነሣት አለባቸው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ፈተና ሆኖ ያለው የዘረኝነትና የገንዘብ ጉዳይ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ክህነት በዘር ነበር፤ የሌዊ ወገን የሆነ ነበር የሚያገኘው፡፡ በሐዲስ ኪዳን ግን ክርስቶስ ራሱ ሊቅ ካህናት ሆኖ ያለ ዘር ሁሉም ለዚህ አገልግሎት የታጨና ብቁ ሆኖ የቀረበውን ቤተ ክርስቲያን በምትሰጠው መስፈርት የሚያሟላ ከሆነ ይሾማል፡፡ ስለዚህ ተመራጩ ፓትርያርክ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ የዘረኝነት መንፈስ ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ዘመን መነኩሴው የመነኮሰው ከየት ነው? የት ነው የተማረው? ምንኩስናውን የሰጠው ማነው? የሚለውን ሊመለከቱ ይገባል፡፡ እነዚህ ነገሮች ዛሬ ካልጠሩ፣ ነገ እነዚህ መነኮሳት ናቸው አድገው የጵጵስናን ማዕረግ የሚያገኙት፡፡ ስለዚህ ምንጩና መነሻው ያልታወቀ መነኩሴ ነገ የጵጵስናውን መዓርግ አግኝቶ ለቤተ ክርስቲያን አደጋ የሚሆንበት ነገር እንዳይፈጠር በመነኮሳት አሿሿምና አገልግሎት ላይ ክትትል ሊያደርጉ ይገባል፡፡

             

            ዛሬ  በቤተ ክርስቲያን  ገንዘብ የዘረፈ፣ የአስተዳደር በደል ያደረሰ፣ መንጋውን ሳይመራ  በቤተ ክርስቲያን ላይ ችግር ሲፈጥር የነበረውን አባት ወደ ሌላ ቦታ ተወስዶ ይሾማል፡፡ ይህ የሚያሳየው በቀድሞው ቦታ ሲያጠፋ የነበረውን ጥፋት ሌላ ቦታ ሔዶ ይደግመዋል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት አሠራሮች መቅረት መቻል አለባቸው፡፡ ዛሬ መንግሥት በሥራ ብልሹነት፣ በሙስና፣ በእምነት ማጉደል ከሓላፊነት የሚያነሣቸውን ሰዎች በሌላ ቦታ በሓላፊነት አይመድባቸውም እንዲቀጡ ያደርጋል እንጂ፤ በእኛም ቤተ ክርስቲያን እነዚህ ነገሮች መለመድ አለባቸው፡፡

             

            በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያን ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የአንድ ክርስቶስ አካል እንደሆኑ ታስቦ ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ ንዋየ ቅድሳትና በቂ መተዳደሪ ሀብት በእኩል መጠን ማግኘት ባለመቻላቸው ዕጣን፣ ጧፍ…፣ እንዲሁም አገልጋይ ካህናትም በማጣት እስከ መዘጋት የደረሱ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ጥሩ ገቢ ኖሯቸው፣ ጥሩ ደመወዝ የሚያገኙ ገዳማት አድባራት አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ የፋይናንስ አሠራሯን ማስተካከል ይጠበቅባታል፡፡ ተመራጩ ቅዱስ ፓትርያርክ ቤተ ክርስቲያን አንድ ወጥ የሆነ የፋይናንስ አያያዝ ሊኖራት እንደ ሚገባና የተቸገሩት እንዲረዱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

             

            ሌላው ቤተ ክርስቲያን የምታደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ የምንሰማው ከቤተ ክርስቲያን ሳይሆን፤ ከውጭ አካላት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በፓርላማ ስብሰባ ጊዜ “በፓርላማው እንዲህ፣ እንዲህ አንኳር ነገሮች ተነግረዋል፤ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡ በማለት መገናኛ ብዙኃኑ ለሕዝቡ መረጃ ያቀብላሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ግን በየጊዜው ምን እየተደረገ?  ምን እየተሠራ? እንዳለ አናውቅም፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ግን ቤተ ክርስቲያኗ የሠራቻቸውን መስማት፣ ማወቅ ያለብን ከቤተ ክርስቲያኗ ነው፡፡ ተመራጩ ፓትርያርኩም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ወቅታዊ መረጃዎች ለምእመናን የሚደርሱበትን መንገድ ሊያመቻቹ ይገባል፡፡

             

            ስለ ነገዋ ቤተ ክርስቲያን ዕድገት ወጣቶችን የሚመለከተን በመሆኑ፤ በምን አቅጣጫ መሔድ፣ አስተዋጽኦአችንንም እንዴት ማበርከት እንዳለብን ከአባቶቻችን ጋር በመመካከር የድርሻችንን እንወጣ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል የምንለውን ገንቢ የሆኑ አስተያየቶች አሁን በሐመር መጽሔት በሚሰጥበት አግባብ እንስጥ፡፡

            • ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 20ኛ ዓመት ቁጥር 7 ኅዳር 2005 ዓ.ም.

            like kahenate hayle selasa

            ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ምን ይላሉ?

            ታኅሣሥ  11 ቀን 2005 ዓ.ም.

            • “እግዚአብሔር ከእኛ በላይ የሚመለከታቸው አባቶች አሉ”

            ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ

            ከሰሜን አሜሪካ ከኮሎራዶ ስቴት

            like kahenate hayle selasaቤተ ክርስቲያን የሚጠብቅ የሚመራ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ቅዱስ አባታችን በማረፋቸው የተነሣ ሀገራችን ትልቅ ሐዘን ላይ ናት፡፡ በዚህ ወቅት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው  የጸሎቱ ጉዳይ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመንበሩ ደግ አባት እንዲያስቀምጥ በጸሎት ሊለመን ይገባል፡፡ አሁን ቤተ ክርስቲያን ጥንቃቄ ልታደርግበት ይገባል ብዬ የማስበው በሰው ሰውኛ መንገድ በመጓዝ ለቤተ ክርስቲያን የሚሆነውን አባት ለመምረጥ ከተሞከረ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሙሴን፣ አሮንን እንደጠራቸው ሁሉ የሚመረጡት አባት እግዚአብሔር የጠራቸው አባት እንዲሆኑ መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን፤ ሁላችንም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ነን፤ ሁሉም አባቶቻችን የቤተክርስቲያን አባቶች ናቸው፡፡ «እገሌ ከእገሌ» ሳይባል መንፈስ ቅዱስ የጠራው አባት ለዚህች ቤተ ክርስቲያን መሪ እንዲሆን መጸለይ ያስፈልጋል፡፡

             

            በሰው ሰውኛውን ተመልክተን “አቡነ እገሌ” ቢሆኑ ይሻላል የምንለው የሚጠቅም አይሆንም፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ በላይ የሚመለከታቸው አባቶች ስለሚኖሩ “እገሌ ከእገሌ” ይሻላል ብሎ መምረጥ ያለበት እግዚአብሔር ነው፡፡ መብቱን ለመንፈስ ቅዱስ ከሰጠነው ትክክለኛ አባት ሊመርጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በኅብረት ሆነን ሥራው ውጤታማ እንዲሆን መተባበር በምንችለው አቅም ማገልገል፣ መጸለይ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሥራ የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ ነገ ሊጸጽተን የሚችል ሥራ መሥራት የለብንም፡፡ ነገ የሚጸጽተን ሥራ መሥራት ቤተ ክርስቲያናችንን ሊጎዳ ይችላል፡፡ ሰው ይጠቅመኛል ብሎ የሚያስቀምጠው ሰው ሰውኛውን ይሆንና ቤተ ክርስቲያንን ሊጎዳ ይችላል፡፡ ትልቁ ነገር ቤተ ክርስቲያንን የማይጎዳ ሥራ መሥራት ነው፡፡ ይህ ሲሆን ነው እግዚአብሔር የሚያግዘን፣ በረከቱን የሚያበዛልን፡፡

             

            እግዚአብሔር ፈቅዶ በዚህ መንበር የሚያስቀምጣቸው አባት ቀዳሚ ሥራቸው እግዚአብሔር የሰጣቸውን መንጋ መሰብሰብ ነው፡፡ የትናንትናው ዘመን ከዛሬው ዘመን የተለየ ስለሆነ ዘመኑን መዋጀት ያስፈልጋል፡፡ ዘመኑን መዋጀት ሲባል አንድ አባት ብቻቸውን የሚሠሩት ነገር አይደለም፡፡ የመንፈሳዊ አባታችን እጅ፣ እግር፣ ዐይን እኛ ልጆቻቸው ስለሆን ልጆቻቸውን አስተባብረው አንድ አድርገው ሊመሩ ይገባል፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን የአንድነት፣ የሰላም ምሳሌ ናት፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነቷ፣ ሰላሟ፣ መሠረቷ ይህች ቤተ ክርስቲያን ስለሆነች፤ ሰላሙ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ማንም ቢሆን ከዚህች ቤተ ክርስቲያን እንዲወጣ የሚፈልግ የለም፡፡ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው፣ መሥዋዕት የሆነው፣ ቀራንዮ ላይ የዋለው ለዓለሙ ሁሉ እንጂ ለተወሰኑ ሰዎች አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጠላቶች የሏትም ሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጠላት የሆኑ ካሉ ደግሞ በተቻለ መጠን ማስተማር ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡

             

            ተመራጩ ፓትርያርክ ቅዱስ  ሲኖዶስን አስተባብረው ቤተ ክርስቲያንን የሚጠብቁ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዛሬ የምትጠብቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱ የውጪ መንጋ ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ስብከተ ወንጌል አገልግሎት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ወዘተ የመጠበቅ ትልቅ ሓላፊነት አለባቸው፡፡ ፓትርያርኩ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ተባብረው ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው ሕገ ደንብ መሠረት በመገዛት የቅዱስ ሲኖዶስ ወሳኔ አስፈጻሚ እየሆኑ ይህን ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለዚህ ተመራጩ አባት ያለባቸው ሓላፊነት ቀላል አይደለም፡፡ ይህንንም ከአንድ ሰው ብቻ የምንጠብቀው ነገር አይደለም፡፡ ሁላችንም ተባብረን የድርሻችንን ስንወጣ የሚመረጡት አባት ሓላፊነታቸውን መወጣት ይችላሉ፤ ትልቁ ሓላፊነት የቅዱስ ሲኖዶስ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

             

            • “በሁለቱም አባቶች ዘንድ እርቁ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል”

            መላከ ጽዮን በላቸው ወርቁ

            በሰሜን አሜሪካ በኒዮርክና

            አካባቢው ሀገረ ስብከት የራችስተር

            ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም

            ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ

            የቤተ ክርስቲያኒቱ የእርቅና የሰላም ጉዳይ እጅግ በጣም አንገብጋቢና ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አባቶች በአስተዳደራዊmelake tsyone ምክንያት ተለያይተው በተፈጠረው ችግር በአሜሪካን በሚኖሩ ካህናት፣ ወጣቶች ምእመናን ዘንድ እጅግ በጣም ከፍ ያለ የመለያየት መንፈስ ፈጥሯል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መጠናከር በአንድነት መሥራት ሲገባ፤ በአንጻሩ ክፍተት ተፈጥሮ እርስ በርስ ካለመግባባት የተነሣ ለቤተ ክርስቲያን ጠላቶች በር የከፈተ ጉዳይ ሆኗል፡፡ እርቀ ሰላሙን ለመፈጸም የማንም ተፅዕኖ ሳይኖር በአባቶች ተነሣሽነት ቁርጥ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ለትውልድ፣ ለታሪክ ሲባል በፍቅር፣ በሰላም፣ በአንድነት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ ሕዝቡን ለማዋሐድ በአባቶቻችን በኩል የተፈጠረውን ችግር በእነርሱ በኩል መፍትሔ እንዲያመጣ መከናወን አለበት፡፡

             

            በአሜሪካን ሀገር በእርቅ ኮሚቴው የሚሳተፉ ሰዎች በአቀረቡልን ጥያቄ መሠረት የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፣ በየቀጠና ማእከላቱ በየአጥቢያው የገንዘብም የዐሳብም አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡  ባለን ሚዲያ፣ በድረ ገጽም ሆነ በሌሎች ለእርቁ ትኩረት በመስጠት ጽሑፎችን በማዘጋጀት፤ በትምህርተ ወንጌሉም በዚሁ ርእሰ ጉዳይ ላይ አተኩረን  እየሠራን ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በማረፋቸው በዐቃቤ መንበር የሚመራ በቅዱስ ሲኖዶስ ተሠይሟል፡፡ በዚህ ሂደትም ውስጥ ተጀምሮ የነበረው እርቅ ትኩረት ተሰጥቶት በሁለቱም አባቶች ዘንድ የመጀመሪያ አጀንዳ ሆኖ እርቁ ቢፈጸም ሁላችንንም የሚያስደስት ነው፡፡

             

            ቤተ ክርስቲያን የራሷ ቀኖና አላት፡፡ መንፈሳዊ አባቷን በቀኖናዋ መሠረት ምርጫዋን ትፈጽማለች፡፡ ከምርጫው በፊት ሊታዩ የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም የቤተ ክርስቲያን ሕግ፣ ደንብና መመሪያው ለምርጫው በግልጽ ተቀምጦ (መስተካከል ካለበት የሚስተካከለው ታይቶ) በአግባቡ ምሉዕ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ኖሮበት ምርጫው እንዲከናወን ቢደረግ፡፡ ሌላው ከምርጫው በፊት ሌሎች ሊከናወኑ የሚገባቸው ሂደቶችም ካለፈው የተማርናቸው ስሕተቶች ምንድን ናቸው) ብሎ ቅዱስ ሲኖዶስ ሊያያቸው የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የቅዱስ ፓትርያርኩ የሥራ ሓላፊነት ዝርዝራቸው በቀኖናው ላይ ተጠቅሷል፡፡ በግልጽ ያልሰፈረ ካለ ከምርጫው በፊት የቤተ ክርስቲያኒቷ ሕግ ከመንበረ ፓትርያርኩ ጀምሮ በአደረጃጀቱ፣ በአወቃቀሩ ታች ድረስ ምሉዕ ሆኖ የሥራ ሓላፊነቱ ጭምር በግልጽ ተዘጋጅቶ ቢጸድቅ፤ የማንም ተፅዕኖ ሳይኖርበት የሚመረጠው አባት እግዚአብሔር ያስቀመጠው ስለሚሆን ሊፈጠሩ ይችላሉ ብለን የምንሰጋቸው ክፍተቶች  ይቀንሳሉ፡፡ በዚህም በኩል የምእመናን ተሳትፎ የጎላ መሆን አለበት፡፡ ቃለ  ዐዋዲው በአጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ምእመናን ያላቸውን ቦታ ያመለክታል፡፡ ከሁሉም በላይ ምርጫው እስኪከናወን ድረስ ሱባኤ ገብተው ለእግዚአብሔር ጸሎት ማድረስ አለባቸው፡፡ እግዚአብሔር ምርጫውን ሙሉ በሙሉ ገብቶ እንዲያከናውነው፣ እንዲያስፈጽመው መደረግ አለበት፡፡

             

            ቀጣዩ ተሿሚ ፓትርያርክም ቦታ መንፈሳዊ ልጆቹን  በሰላም፣ በፍቅር፣ በአንድነት የሚያስተሳስር፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማና ቀኖና በትክክል ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ የሚያደርግ፣ ትምህርተ ወንጌልን የሚያስፋፋ፣ ስብከተ ወንጌልን የሚያጠናክር የቀደሙት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጀምረዋቸው የነበሩ ሥራዎች ማጠናከር በተለይም ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች መርዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡

             

            በገጠር በካህን እጥረት ምክንያት ብዙ አብያተ ክርስቲ ያናት እየተዘጉ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በከተማ አካባቢ በርካታ ካህናት ተከማችተው ይታያሉ፡፡ የገጠሯ ቤተ ክርስቲያን እንዳትዘጋ ትኩረት መስጠት ካህናቱ ማእከላዊ በሆነ አስተዳደር እንዲተዳደሩ ማድረግ፤ ተተኪው ትውልድ ወጣት ከመሆኑ አንጻር ጊዜውን፣ ጉልበቱን፣ ሕይወቱን ሰጥቶ ቤተ ክርስቲያን ላገልግል የሚለውን በመምራት፣ መንገድ ማሳየት ይጠቅቸዋል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላት የሆኑ መናፍቃን፣ ተሐድሶዎች  ቀዳዳ፣ ክፍተት ፈልገው የበግ ለምድ ለብሰው ቤተ ክርስቲያን በመግባት ሃይማኖቷን፣ ዶጋማዋን እንዳይቆነጻጽሉ ሥርዐቷን እንዳያፈርሱ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

             

            ዘመኑን በተከተለ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንዲኖራት ትኩረት ሰጥቶ የገንዘብና የንብረት አስተዳደሯን በአግባቡ በሕግና በሥርዐት የሚመራ ባለሙያዎችን በየደረጃው ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱትንና ቤተ ክርስቲያኒቱንና አሁን የጀመረቻቸውን መልካም እሴቶች የሚያበረታታ፤ ካህናቱ ከምእመናኑ ጋር ያላቸው ውሕደትና ጥምረት አጣጥሞ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የማሻገር ሓላፊነት ከአዲሱ ቅዱስ ፓትርያርክ የሚጠበቁ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

             

            • “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን በገጠር የሚያስፋፋት አባት እንጠብቃለን”

            ቀሲስ ታምራት

            ከጎሬ

            kesis tamerateየፓትርያርክ ምርጫ ቤተ ክርስቲያናችን በመንፈስ ቅዱስ ስለምትመራ ነገሮቹን ሁሉ ለመንፈስ ቅዱስ አሳልፎ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ያ ማለት ደግሞ ከካህናት አባቶች፣ ከእያንዳንዳዱ ክርስቲያን፣ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ከሰባክያን ብሎም ከሲኖዶስ ምርጫው የተሳካ ይሆን ዘንድ በጸሎት ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

             

            በዚህ ዘመን ለቤተ ክርስቲያን የሚበጃት ዓለሙን ሊዋጅ የሚችል ታሪኳን፣ ትውፊቷን፣ ሃይማኖቷን  ጠብቆ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ የሚችል አባት እንዲመረጥ እያንዳንዱ ሰው ገንቢ ያልሆነ አስተያየት ከመስጠትና ከዘረኝነት ነጻ ሆኖ እግዚአብሔርን ብቻ አስቦ ምርጫው በተስፋ ሊጠብቅ ይገባል፡፡

             

            አሁን የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የሚመሩ አባት ፓትርያርክ እንደሚታወቀው ከፊት ለፊታችንጠ እግዚአብሔር ቢፈቅድ ይመረጣል፡፡ የሚመረጡት አባት ደግሞ ምን ማድረግ አለባቸው) ከሚመረጡት አባት ምን ይጠበቃል) የሚለውን ጉዳይ  እኔ በሁለት መልኩ ነው የማየው፡፡ የመጀመሪያው በሞት ያለፉት ቅዱስነታቸው ጀምረዋቸው ያሉ መልካም እሴቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱ ቤተ ክርስቲያናችንን በዓለም ደረጃ ዕውቅና እንድታገኝ አድርገዋታል፡፡ የሚመረጡት ፓትርያርክ ይህንኑ ተግባር ለዓለም የማሳወቅ፣ የማስቀጠል ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሁለተኛው ቤተ ክርስቲያኒቱ ባሳለፈችው ሁለት ሺሕ  ዓመታት ውስጥ ሐዋርያዊ ተልእኮዋ ስንመለከት እንደ ዕድ ሜዋ የሚያረካ አገልግሎት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያደረሰ አይደለም፡፡ ያም ከተለያዩ ምክንያቶች  የተነሣ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ አሁን ተመራጩ ፓትርያርክ ይህንን ክፍተት ለመሙላት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚችሉትን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

             

            በገጠር አካባቢ የሚገኙ ምእመናን የተጠናከረ አገልግሎት አላገኙም፡፡ የገጠሯ ቤተ ክርስቲያንም ተዘግታ ያለችበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በሰፊው እየተካሔደ ያለው በከተማ አካባቢ በመሆኑ፤ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የከተማ ሃይማኖት እየሆነች አገልግሎቷ በከተማ ብቻ እንዲወስን የሚያደርጋት አጋጣሚ እየመጣ ነው፡፡ እኛ ከተማ ከተማውን  እየሠራን ሌሎች ቤተ እምነቶች ደግሞ ገጠር ገጠሩን እየሠሩ ቤተ ክርስቲያናችን ከተማ ላይ እየቀረች ገጠሩን ለሌሎች አሳልፈን እየሰጠን ነው፡፡

             

            ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ አሁን የሚመረጡት አባት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር አስተካክለው ቤተ ክርስቲያን ያላትን የገንዘብም ሆነ የሰው ሀብት ልማት በትክክል በሥራ ላይ ማዋል፤ አገልግሎቷም በገጠር እንዲስፋፋ የሚያደርጉ አባት ቢሆኑና ሲኖዶሱም ሕገ ደንቡን አክብሮ የሚመራ መሆን አለበት፡፡ ይህን የሚያደርግ አባት እግዚአብሔር እንደሚሰጠን አምናለሁ፡፡

             

            • “ጥሩ አሠራር የሚዘረጋ አባት ያስፈልገናል”

            ኅብስተ ኪዳነ ማርያም

            ከደሴ

            hebesta kidanemaryameቅዱስ አባታችን በማረፋቸው ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ ፓትርያርክ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሂደት ምእመናንና ካህናቱን የሚያስተዳድር አባት እግዚአብሔር እንዲሰጠን መጸለይ አለብን፡፡

             

            በፓትርያርክ ምርጫ ላይ ወገንተኛ መሆን ተገቢ አይደለም፡፡ ምእመናን፣ ወጣቶችም አንዱን ወገን መደገፍ ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን የትኛው ይጠቅማል የሚለውን ማሰብ አለብን፡፡ ስለዚህ ችግሮችን የሚፈቱ ጥሩ አሠራር የሚዘረጉ አባት እንዲመረጡ እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቃለን፡፡

             

            ስለ ግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የተጻፉ መጻሕፍትን ስናነብ ግብፃውያን  አባቶችና ምእመናኑ ያላቸው ግንኙነት፣ አባቶች ያላቸው ትጋት፣ ምእመናኑ እንዴት እንደሚጠብቁትና እንደሚንከባከቡት  ስናነብ በጣም ያስቀናል፡፡ እኛስ መቼ ነው እንደዚህ የምንሆነው የሚል ቁጭት በውስጤ አለ፡፡ የእኛም አባቶች ለወጣቱ ትውልድ ቤተ ክርስቲያን በደንብ የማሳወቅ፣ አባቶችና የንስሐ ልጆች ግንኙነት እንዲጠናከር፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ያለው አሠራር ግልጽ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚመረጠው ፓትርያርክ ከላይ እስከታች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለው ምእመናን ቤተ ክርስቲያን በቂ አገልግሎት እንዲያገኝ ምእመኑም በመንፈሳዊ ሕይወቱ አዲስ አሠራር መዘርጋት አለባቸው፡፡ ይህን ያህል ፐርሰንት አስገብተዋል፣ ይህን ያህል አማኞች አሉ የሚለው የቁጥር ሪፖርት በቂ አይደለም፡፡ በእውነት የተመዘገቡ ቤተ ክርስቲያን የምታውቃቸው ምእመናን፣ አስተዋጽኦቸው በአግባቡ እያበረከቱ ያሉ ምን ያህል ክርስቲያኖች አሉ? ስንቶችን ካለማመን ወደ ማመን አምጥተናል? የሚሉ ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ናቸው፡፡

             

            ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር፣ ሰበካ ጉባኤ በልማት እንዲሳተፉ፣ ትምህርት ቤቶች፣ አጸደ ሕፃናት እንዲስፋፋ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች አብነት ትምህርት ቤቶች እየተዘጉ፤ መምህራኑ ጉባኤያቱን እያጠፉ ወደ ከተማ እየተሰደዱ ነው፡፡ ይህን በደንብ አጥንቶ ሊሟሉ የሚገባቸውን ነገሮች በማሟላት ጉባኤያቱ እንዳይፈቱ ማድረግ ከተመራጩ ፓትርያርክና ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

            • ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 20ኛ ዓመት ቁጥር 5 መሰከረም 2005 ዓ.ም.