ፅንሰተ ማርያም ድንግል

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል …፤ ልዑል እግዚአብሔር ማደሪያውን መረጠ፤ አከበረ፤ ለየ፤ ቀደሰ …›› /መዝ.፵፭፥፬/ በማለት እንደተናገረው፣ አምላክን በማኅፀኗ ለመሸከም የተመረጠችው ማኅደረ ማለኮት፤ የዓለሙን ቤዛ በመውለዷ ‹‹ቤዛዊተ ዓለም›› እየተባለች የምትጠራው፤ በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር የነበረችው የድኅነታችን ምክንያት የኾነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማኅፀን የተቋጠረችው ነሐሴ ፯ ቀን ነው፡፡ ፅንሰቷም እግዚአብሔር በባረከውና ባከበረው ቅዱስ ጋብቻ በተወሰኑት ወላጆቿ በቅዱስ ኢያቄምና በቅድስት ሐና ሥርዓት ያለው ግንኙነት አማካይነት ነው፡፡ ‹‹ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በሥጋዊ ፈቃድ የተፀንሽ አይደለሽም፤ ሕጋዊ በኾነ ሥርዓት ከሐና እና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ›› እንዲል /ቅዳሴ ማርያም/፡፡

ታሪኩን ለማስታዎስ ያህል የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ቴክታ እና በጥሪቃ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለጠጎች እና መካኖች ነበሩ፡፡ በጥሪቃ ሚስቱ ቴክታን ‹‹አንቺ መካን፤ እኔ መካን፡፡ ይህ ኹሉ ገንዘብ ለማን ይኾናል?›› አላት፡፡ ቴክታም ‹‹እግዚአብሔር ከእኔ ልጅ ባይሰጥህ ከሌላ ይሰጥህ ይኾናል፡፡ ሌላ ሚስት አግብተህ ልጅ አትወልድምን?›› ብትለው ‹‹ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃል›› አላት፡፡ ኹለቱም እያዘኑ ሲኖሩ አንድ ቀን ነጭ እንቦሳ (ጥጃ) ከበረታቸው ስትወጣ፤ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ልጅ ስትደርስና ስድስተኛዪቱ እንቦሳም ጨረቃን፣ ጨረቃም ፀሐይን ስትወልድ ራእይ አዩ፡፡

ራእያቸውን ለሕልም ተርጓሚ ሲነግሩም ‹‹የጨረቃዪቱ ትርጕም ከፍጡራን በላይ የምትኾን ልጅ እንደምታገኙ የሚያመለክት ነው፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጠልኝም፡፡ እንደ ነቢይ፣ እንደ ንጉሥ ያለ ይኾናል፤›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ጊዜ ይተርጕመው ብለው›› ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ቴክታ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ሄኤሜን አለቻት፡፡ ትርጕሙም ስእለቴን (ምኞቴን) አገኘሁ ማለት ነው፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና ለዓቅመ ሄዋን ስትደርስም ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡ እነርሱም እንደ በጥሪቃና ቴክታ መካኖች ነበሩ፡፡ በእስራኤላውያን ባህል መካንነት የእርግማን ምልክት ተደርጎ ይቈጠር ነበርና ሐና እና ኢያቄም ብዙ ዘለፋና ሽሙጥ ይደርስባቸው ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደስ ቢሔዱ የዘመኑ ሊቀ ካህናት ሮቤል መካን መኾናቸውን ያውቅ ነበርና ‹‹እናንተማ ‹ብዙ ተባዙ› ብሎ እግዚአብሔር ለአዳም የነገረውን ያስቀረባችሁ ርጉማን አይደላችሁምን? እግዚአብሔር ቢጠላችሁ እንጂ ቢወዳችሁማ ልጅ ይሰጣችሁ አልነበረምን?›› ብሎ መሥዋዕታቸውን ሳይቀበላቸው በመቅረቱ፤ አንድም ከአዕሩገ እስራኤል (ከአረጋውያን እስራኤላውያን) የተወለዱ ሰዎች የሚመገቡትን ተረፈ መሥዋዕት እንዳይመገቡ በመከልከሉ እያዘኑ ሲመለሱ ከልጆቻቸው ጋር የሚጫወቱ ርግቦችንና አብበው ያፈሩ ዕፀዋትን ሐና ተመለከተች፡፡ እርሷም ‹‹ርግቦችን በባሕርያቸው መራባት እንዲችሉ፤ ዕፀዋትን አብበው እንዲያፈሩ የምታደርግ ጌታ እኔን ለምን ልጅ ነሳኸኝ?›› ብላ አዘነች፡፡

ከቤታቸው ሲደርሱም ‹‹እግዚአብሔር ልጅ ቢሰጠን ወንድ ከኾነ ለቤተ እግዚአብሔር ምንጣፍ አንጣፊ፣ መጋረጃ ጋራጅ ኾኖ ሲያገለግል ይኑር፤ ሴት ብትኾንም መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ መጋረጃ ፈትላ ስታገለግል ትኑር›› ብለው ከተሳሉ በኋላ ሐምሌ ፴ ቀን ሐና ለኢያቄም ‹‹በሕልሜ ፀምር (መጋረጃ) ሲያስታጥቁህ፤ በትርህ አፍርታ ፍጥረት ኹሉ ሲመገባት አየሁ›› ብላ ያየቸውን ራእይ ነገረችው፡፡ ኢያቄም ደግሞ ለሐና ‹‹ጸዓዳ ረግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በራስሽ ላይ ስታርፍ፣ በቀኝ ጆሮሽ ገብታ በማኅፀንሽ ስታድር አየሁ›› ብሎ ያየውን ራእይ ነገራት፡፡ ሕልም ተርጓሚው ‹‹ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› ባላቸው ጊዜም ‹‹አንተ አልፈታኸውም፤ ጊዜ ይፍታው›› ብለው ተመልሰዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ‹‹ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› ብሎ ነግሯቸው ሐዲስ ኪዳን ሊበሠር፤ ጌታችን ሊፀነስ ፲፬ ያህል ዓመታት ሲቀሩ ነሐሴ ፯ ቀን በፈቃደ እግዚአብሔር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀንሳለች፡፡ እመቤታችን በሐና ማኅፀን ውስጥ ሳለች ከተደረጉ ተአምራት መካከልም በርሴባ የምትባል አንድ ዓይና ሴት (አክስቷ) ሐናን ‹‹እግዚአብሔር በረድኤት ጐበኘሽ መሰለኝ ጡቶችሽ ጠቁረዋል፤ ከንፈሮችሽ አረዋል›› ብላ ማኅፀኗን በዳሰሰችበት እጇ ብታሸው ዓይኗ በርቶላታል፡፡ ይህንን አብነት አድርገውም ብዙ ሕሙማን ከደዌያቸው ተፈውሰዋል፡፡

ዳግመኛም ሳምናስ የሚባል ያጎቷ ልጅ በሞተ ጊዜ ሐና የአልጋውን ሸንኮር ይዛ ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት ከሞት ተነሥቶ ‹‹ሰላም ለኪ ኦ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ፤ ሰማይና ምድርን የፈጠረው አምላክ አያቱ ሐና ሆይ ሰላም ላንቺ ይኹን›› ብሎ ሕልም ተርጓሚው ያልፈታውን ራእይ በመተርጐም ከሐና እመቤታችን፤ ከእመቤታችን ደግሞ እውነተኛ ፀሐይ የተባለው ክርስቶስ እንሚወለድ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ /ምንጭ፡- ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ ፭፥፴፰/፡፡

በአጠቃላይ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹‹ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን፤ ማርያም ሆይ እውነተኛውን ምግብ፣ እውነተኛውን መጠጥ አስገኝተሽልናልና እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፤›› በማለት እንደ አመሰገናት እኛም ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠውን፤ ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ ማዳን የሚቻለውን፤ እውነተኛውን ምግበ ሥጋ ወነፍስ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለወለደችልን ‹‹እናታችን፣ አማላጃችን፣ የድኅነታችን ምክንያት፣ ወዘተ›› እያልን እመቤታችንን እናከብራታለን፤ እናገናታለን፤ እናመሰግናታለን፡፡ እናቱን በአማላጅነት፤ ራሱን በቤዛነት ለሰጠን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው፤ የእመቤታችን በረከት አይለየን፡፡