ክብረ ድንግል ማርያም

ነሐሴ ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ታደለ ፈንታው

mariam[1]

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ጋር

እግዚአብሔር ዘላለማዊ ኃይሉንና አምላክነቱን ለዓለም ከገለጸበት ታላቅ ሥራ መካከል በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የገለጸው ድንቅ ሥራው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ይህንን ኹኔታ ድንግል ማርያም ‹‹ብርቱ የኾነ እርሱ ታላቅ ሥራን በእኔ አድርጓል፤ ስለዚህም ፍጥረት ኹሉ ያመሰግኑኛል›› /ሉቃ.፩፥፵፱/ በማለት ገለጸችው፡፡

ቅድስት ኤልሳቤጥም ‹‹የጌታዬ እናት›› አለቻት /ሉቃ.፩፥፵፫/፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ›› አላት /ሉቃ.፩፥፳፰/፡፡ ቅዱስ ዳዊት ደግሞ ‹‹ልጄ›› ይላታል /መዝ.፵፬፥፱/፡፡ ሰሎሞንም ‹‹እኅቴ›› ይላታል /መኃ.፭፥፩/፡፡ ለወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም እናት ኾና ተሰጥታዋለች /ዮሐ.፲፱፥፳፮/፡፡ ይህን ድንቅ ምሥጢር ውስንና ደካማ የኾነ አእምሮ ሊገነዘበው ከሚችለው በላይ ነው፡፡

ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንደገለጸው ‹‹የቅድስት ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና፤ አማኑኤልን መውለዷና የማይሞተው ጌታ መሞቱ›› እነዚህ ሦስቱ ከዚህ ዓለም ጥበበኞችና ገዢዎች የተሰወሩ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹እነዚህ ድንቅ ምሥጢራት በራሳቸው ከንግግርና ከቋንቋዎች ኹሉ በላይ ኾነው የሚነገሩ በእግዚአብሔር የዝምታ መጐናጸፊያ የተጠቀለሉ ድብቅና ጣፋጭ ምሥጢሮች ናቸው›› ይላል፡፡

የእመቤታችን ምስጋናዋ የበዛለት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም ‹‹አቤቱ መሰንቆ ልቡናዬን አነቃቃ፤ የልቤንም እንዚራ፡፡ ድምፁን ከፍ አድርጎ የዳዊት ልጅ የኾነችውን፣ የጌታውን እናት ድንግል ማርያምን ያመሰግናት ዘንድ፤ ለዓለም ሕይወት የሚሰጠውን የወለደች እናቱ የኾነች እርሷን ከፍ ከፍ ያደርጋት ዘንድ›› ብሏል፡፡ በሌላም አንቀጽ ደግሞ ‹‹ከሕሊናት ኹሉ በላይ ለኾነ ለዚህ ነገር አንክሮ ይገባል፡፡ ምድራዊት ሴት ፈጣሪዋን ወለደችው፤ እርሱም እናቱን ፈጠረ›› አለ፡፡ ስለእነዚህ ነገሮች ኹሉ ምን ማለትን እንችላለን? እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስለ ድንግል ማርያም ያልተናገረበት ጊዜ፤ ያላናገረው ቅዱስ እንደሌለ እንመለከታለን፡፡

‹‹በእግዚአብሔር፣ በመላእክትና በሰው ፊት የከበረ ሰው መታሰቢያው ለዘለዓለም ነው፡፡ በቤቱ በቅጥሩ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምን ይቀበላልና›› /ኢሳ.፶፭፥፫/፡፡ ይህንን ታላቅ በረከት እንደሚሰጣቸው የተናገረው የማይዋሸው ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ወልድ እናት ከድንግል ማርያም የበለጠ በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ማንን ልንጠራ እንችላለን? እንደ እርሷስ ሊታሰብ፣ ሊከበርም የሚችል በቅድስና ሕይወት ያለፈ ማን ይኖራል?

ቅዱስ እግዚአብሔር ፍጥረቱንና ዓለሙን ለማዳን የወሰነው ጊዜ በደረሰ ጊዜ ከድንግል ማርያም በድንግልና ተወለደ፡፡ አስቀድሞ በመልአኩ አፍ እንዳናገረ ክብሩ በእርሷ ላይ ታየ /ኢሳ.፷፥፪/፡፡ ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በእርስዋ አደረ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእመቤታችን ላይ የማደሩ ምሥጢር ያነጻቸው፤ ይቀድሳቸው፤ በሥጋም በነፍስም መርቶ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ያገባቸው ዘንድ በነቢያት፣ በሐዋርያት ላይ እንዳደረው ዓይነት አይደለም፡፡ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ (ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ) ከሥጋዋ ሥጋን፣ ከነፍስዋ ነፍስን ነስቶ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ ኾነ እንጂ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ይህን ዘለዓለማዊ እውነት ‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል፡፡ ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል›› በማለት ገልጾታል /ሉቃ.፩፥፵፭/፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ደራሲና ገጣሚ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም ‹‹የእስራኤል ንጉሥ በእስራኤል ልጅ አደረ፤ የዳዊት አምላክ ከዳዊት ልጅ ሥጋን ለበሰ፡፡ የዕብራውያን ጌታ በዕብራውያን ልጅ ማኅፀን ተወሰነ፡፡ ለአብርሃም የዕብራይስጥ ልሳን ያስተማረው ከቀድሞም ያልሰማውን ልሳን እንዲናገር አፉን ጆሮውን የከፈተለት ከዕብራዊት ድንግል ተወለደ፤ በድንግልና ወተት ጥቂት ጥቂት እያለ አደገ፡፡ የሕፃናትን ሥርዓት እንዳያጎድል አፉን የሚፈታባት ዘመን እስኪፈጸም ጥቂት ጥቂት እያለ በዕብራይስጥ ልሳን ሲናገር ኖረ፡፡ ለሙሴ በዕብራይስጥ ልሳን በጣቶቹ የተጻፉትን ዐሠርቱ ቃላትን የሰጠ የዕብራይስጥ ፊደል ለመማር ከመምህር እግር በታች ተቀመጠ፡፡ የባቢሎን አውራጃ በምትኾን ሰናዖርም የፍጥረትን ሁሉ ቋንቋ የበተነ እርሱ የአሕዛብን ቋንቋ እንደማያውቅ ኹሉ እናቱ አፍ በፈታችበት ልሳን በዕብራይስጥ ልሳን ሲናገር ኖረ፡፡ ጆሮ ይህንን ነገር ከመስማት የተነሣ የሚለመልምበት ይህ ነገር ዕፁብ ድንቅ ነው፡፡ ለዚህ አንክሮ ይገባል›› አለ፡፡ ይህ በሰው ጥበብ በብራናና በቀለም የተጻፈ እውነት ሳይኾን ለድኅነት በተጠሩ ሰዎች ሁሉ ልቡና በአምላክ ጥበብ የተጻፈ እውነት ነው፡፡

የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ይደርብን፤ የልጇ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክረስቶስ ጸጋ ይብዛልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡