ተረፈ አይሁዳዊነት በኤልያሳዊነት ስም ሲበቅል

ዲ/ን ማለደ ዋስይሁን

ሚያዝያ 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ አንዲት ሴት ”መሲህን ልወልድ ነው” እያለች ሰዎችን ታስከትል ነበር፡፡ ይህቺ ሴት አስገራሚ በሆነ ሁኔታ በየገዳማቱ እየዞረች ካህናቱን ሁሉ ለማንበርከክ ተንቀሳቅሳለች፡፡ ለዚህም ወንጪ ቂርቆስ ላይ ያደረገችውን ማስታወስ በቂ ነው፡፡

የዚህች ሴት አካሔድ አነጋጋሪ የሚሆነው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በደሙ በመሠረታት፣ ሥጋውና ደሙም በሚፈተትበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአይሁድ ወገኖች አስተምህሮ የሚመስል ሰበካ ይዛ መገኘቷ ነው፡፡ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት በምትጠባበቅ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክርስቶስ ገና እንደሚወለድ ያለ አስተምህሮ ሲነገር መስማት ማሳፈሩ ብቻ ሳይሆን በጊዜው ቤተ ክርስቲያን ትንሹም ትልቁም በወደደ ጊዜ የሚሻውን የሚፈጽምባት፣ የሚናገርባት ተቋም ሆና እንደ ነበር የሚያሳይ ነው፡፡ ሴቲቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊታሰብ የማይችል በማሰቧ፣ ሊነገር የማይችል በመናገሯ በአብዛኛው የክርስቲያን ወገን ይታሰብ የነበረው የአንዲት ሴት ከንቱ ቅዠት ተደርጎ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ተመሳሳይ ዝንባሌዎች ያቆጠቁጣሉ ብሎ ያሰበ የለም፡፡

 

እነሆ ዛሬ ደግሞ ሌላ የአይሁዳዊነት ዝንባሌ ያለው አስተምህሮ በኤልያስ ስም በተደራጀ ቡድን አማካኝነት ማብቀል ጀምሮ እስከ አራት መቶ ተከታዮች እንዳሉት እየተነገረ ነው፡፡ አስገራሚው ይኸው አስተምህሮ ተለጥፎ የመጣው በዚህችው በመከራ ውስጥ በምትጓዝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ ስሙንም በተዋሕዶነት ሰይሞ ሲጓዝ አላፈረም፡፡ መከፋፈል፣ ማሰለፍ የሚፈልገውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ነው፡፡ አስተምህሮው የተደበላለቀና ወጥ ያልሆነ ዘርፍ፣ መልክ፣ መነሻም መድረሻም የሌለው ክርስትና ይሁን አይሁዳዊነት ፖለቲካ ይሁን ሃይማኖት ጥንቆላ ይሁን እብደት ያለየለት እንቅስቃሴ ነው፡፡

 

ይህ ቡድን አውቆም ሆነ ሳያውቅ ጥለን ወደመጣነው እርሾ ወደ አይሁዳዊነት ያዘነበለ አስተምህሮ ይዞ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈል አንዱን አንሥቶ ሌላውን ለመጣል የሚሞክር አፍራሽ አካሔድም የያዘ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ላይ ባለፉት ዘመናት ከተወረወሩት ፍላጻዎች ተከትሎ የመጣ በአቅሙ ፍላጻ ሆኖ ለማደግ የሚተጋ ነው፡፡

 

በዚህች ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ዘመናት በብሕትውና ስም በአጥማቂነት ስም ብዙዎች የተለያዩ ፍላጎቶቻቸውን ለማስተጋባት ምእመናንን ግራ በማጋባት ተሰልፈው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ሁሉም እየታዩ መጥፋታቸው እንዳለ ሆኖ ያጠፉት፣ ተስፋ ያስቆረጡት ያሰናከሉት መንጋ እንዳለም አይረሳም፡፡ በአብዛኛው ግን አሁን አሁን እንደሚታዩት መሠረት የለሽ ከክርስትና ሃይማኖት እሳቤ ፍጹም የወጣ ጽንፍ ይዘው ግን ታይተዋል ማለት አይቻልም፡፡ አብዛኛውም ምእመናን እርካታ ሊሰጣቸው ያልቻለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር በመንቀፍ ስለሚመሠረቱ ተከታዮችን በቀላሉ ለማግኘት አስችሏቸው ነበር፡፡ በአብዛኛው የባሕታውያኑና የአጥማቂዎቹ ትኩረት አስተዳደሩን፣ አገልጋይ ማኅበራትን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን፣ ግለሰቦችን መንቀፍ ላይ የሚያተኩርና ከዚያ አለፍ ሲል የራሳቸውን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ለመደንገግ ሲጥሩ መታየታቸው ነው፡፡

 

እነዚህ የአሁኖቹ የአይሁዳዊነት ዝንባሌ ያላቸው እንቅስቃሴዎች ግን የተናቁ ቢመስሉም የአካሔድ ሚዛኑ ፍጹም ፀረ ክርስትና ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን የሚሠሩ እንደሆነ ይናገሩ እንጂ የሚያሳስባቸው የስብከተ ወንጌል ሥርጭት አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት አቅም ስለማደግ አለማደጉ አይደለም፡፡ አስተዳደራዊ መሻሻል ስለማምጣት አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ውስጥ ለውስጥ ለማዳከምና ለመከ ፋፈል ስለሚሠራው የተሐድሶ ቡድን አይደለም፡፡ ወይም በሀገሪቱ እየተስፋፋ ስላለው ዓለማዊነት አይደለም፡፡ በሀገሪቱ እየተስፋፋ እንደሆነ ስለሚነገርለት ግብረሰዶምና እጅግ የከፋ የኃጢአት ሥራ አይደለም፡፡ ስለ ሰላም ስለ ዕርቅ አይደለም፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚያሳስቧቸው ነገሮች ሲመረመሩ የጸሐፍት ፈሪሳውያን እርሾ ከቤተ ክርስቲያን የመወገዱ ጉዳይ ያንገበገባቸውና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን ሊያሳድጉ ሊያሰፉ ሊያጠናክሩ የሚችሉ ፍንጮች መታየታቸው ያበሳጫቸው መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡ እነዚህ ወገኖች ነግቶ በመሸ ቁጥር የሚናገሯችው የተደበላለቁ ያልሰከኑ ገና እየተደራጁ ያሉ ዝብርቅርቅ ሐሳቦች ያሏቸው ስለሆኑ በሚያነሡት ነጥብ ላይ መልስ በመስጠት ጊዜን ማጥፋት ለጊዜው አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ነገር ግን ይህን የሚወዛወዝ አስተምህሯቸውን ዝንባሌ መጠቆም አግባብ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክስ መባል የለባትም 
እነዚህ ወገኖች ክርስትና ማለት ሀበሾች ብቻ ተጠምቀው ይዘውት የሚገኙ ሃይማኖት አድርገው የማሰብ ያህል አጥብበው ያያሉ፡፡ የአሐቲ ቤተ ክርስቲያን እሳቤ የሌላቸውና ለሁሉም ወገን የተሰጠች መሆኗን በመዘንጋት “ተዋሕዶ ብቻ ነን” ይላሉ፡፡ ኦርቶዶክስ መባልን ሲኮንኑ ከኒቅያ ጉባኤ ጀምሮ ያሉ ሊቃው ንትን ከዚያም ለብዙ ምዕተ ዓመታት የነበሩ ሊቃውንትና ምእመናንን አኀት አብያተ ክርስቲያናትን ወዘተ እየኮነኑ መሆኑን እንኳ አላስተዋሉም፡፡ ሃይማኖታችን አንዲት/one/ ኩላዊት/catholic/ ሐዋርያዊት /apostolic/ ቅድስት /holy/ መሆኗን አያውቁም ወይም ብለን እንደምናስተምር ስናስተምርም እንደኖርን ረስተዋል፡፡

 

የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ተቀብ ለው የቅዱሳን ሐዋርያትን ትምህርትና ትውፊት የተቀበሉ፣ ያቆዩ፣ ያጸኑ፣ በኒቅያ፣ በቁስጥንጥንያ፣ በኤፌሶን የተደረጉ መንፈ ሳዊ ጉባኤያትን የተቀበሉ፣ ሐዋርያዊ ውርስ ያላቸው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን ምስጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምስጢረ ቁርባንና ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን ትምህርትን እነርሱም የሚያስተምሩ አኅት አብያተ ክርስቲያናትን ሁሉ ኦርቶዶክስ እንደሚባሉ ማወቅ መረዳት ያለመቻልና ክርስትናን ከብሔርተኛ ስሜት /nationalism/ አስተሳሰብ ጋር አቆራኝተው ማየታቸው ነው፡፡

 

እነዚህ ሰዎች ይህን ለማለት እንደመነሻ የሚያሳብቡት “የቅባት እምነት ተከታይ የሆኑ ካህናት በጎጃም አሉ፤ ዘጠኝ መለኮት የሚሉ በዋልድባ አሉ የሚልና ተሸፍነው የሚኖሩት በኦርቶዶክስ ስም ነውና ኦርቶዶክስ የሚለውን አንቀበልም” የሚል ነው፡፡ እነዚህን አለመቀበላቸው መልካም ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሲታገሏቸው እንደኖሩ አሁንም ያንንኑ መንገድ ተከትለው ቢታገሉ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ያ አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትጠራበት ስም በራሱ ከእነዚህ የኑፋቄ ወገኖች የተለየች ሆና “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን” ተብላ እንደሆነ እያወቁ “ተዋሕዶ” መባል አለብን የሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ያነሣሉ፡፡ “ተዋሕዶ” የሆነውን እኛን መልሰው “ተዋሕዶ እንሁን” ሲሉን ነገር እንዳለው ሁሉም ወገን መገንዘብ ይገባዋል፡፡ “ተዋሕዶ ነን” ብለን በይፋ የምንጠራበት ስም ካለን፣ ቅባትና ዘጠኝ መለኮትን የሚያነሣ መጠሪያ ከሌለን፣ በእምነትም ተዋሕዶ እምነትን እንደ ምንከተል ከታወቀ የሚፈለገው ምንድነው፡፡ ከዚህ ከሚያነሡት ክርክር ጋር ኦርቶዶክስ መባልንስ የሚያስጥል ምን መነሻ አለ፡፡

 
ኦርቶዶክሳዊነት እጅግ በስፋት ተተንትኖ መታየት የሚችል ለእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን የተገባ ስም መሆኑን ማሳየት ቢቻልም በዚህ ጽሑፍ ማሳወቅ የተፈለገው ግን የእነዚህ ወገኖች የአለማወቅ ደረጃ በዚህ ላይ ያለ መሆኑን ነው፡፡ ኦርቶዶክስ መባልን ደባ ነው፣ ሸክም ነው ወዘተ እያሉ መለፈፋቸው ብዙ እርምጃ የማያስኬድ መሆኑን አውቀው ሊታረሙበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ “ኦርቶዶክስ” የሚለውን ቃል መለካውያን ተጠቅመውበታል ይላሉ፡፡ እነርሱ በመጠቀማቸውም እኛ እንድንጥለው ይመክሩናል፡፡ እነርሱ ክርስቲያን ተብለው እንደሚጠሩ ቤተክርስቲያን ብለው እንደሚጠሩም መገንዘብ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ቆይተው ደግሞ እነርሱ ክርስቲያን ተብለው ተጠርተዋልና እኛ ክርስቲያን መባልን እንድንተው፣ ቤተ ክርስቲያን መባልን እንድናስቀር ሊመክሩን ይነሣሉ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ሐሳባቸው የአይሁዳዊነት እርሾ አለው የምንለው፡፡

 
ስም አጠራራችን “አይሁዳዊ” የሚል ነው
እነዚህ ወገኖች ኦርቶዶክሳዊ መባልን ኮንነው ሲያበቁ ሊያሻግሩን የሚጥሩት አይሁዳዊ ወደሚለው መጠሪያ ነው፡፡ ለማስተማር ብለው በበተኑት ወረቀት ላይ ”አይሁዳዊ የሚለውን የጌታን የእመቤታችንን የንጹሐን ኢትዮጵያውያንን የከበረ ስም አጠራር ለዐመፀኛ አሕዛብ አሳልፎ መስጠት ፈጽሞ አይገባም ነበር” ይላሉ፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ከሚለው የክርስቲያኖች ስም ሲነጥሉን ያልራሩ ሰዎች በስያሜ ከአይሁድ ጋር ተቀራረቡ በማለት ጭካኔያቸው ሲያይል ያሳዩናል፡፡ ኦርቶዶክሳዊነት የክርስትና ስም ነው፡፡ አይሁዳዊ፣ ግሪክ፣ ኢትዮጵያዊ ወዘተ የሚለው ግን የወገን፣ የብሔር ስም መሆኑን እንኳን አላስተዋሉም፡፡ ለዚህ ነው ዝንባሌው ወደ ጸሐፍት ፈሪሳውያን እርሾ ነው የምንለው፡፡

ሰንበተ አይሁድ እንጂ ሰንበተ ክርስቲያን እሑድ የሚባል የለም
እነዚህ ወገኖች የተረፈ አይሁዳውያን ትምህርት አላቸው ስንል ለዝንባሌያቸው ሌላው መነሻ ስለ ሰንበተ ክርስቲያን መስማት አለመፈለጋቸውና ሰንበተ አይሁድ እንድትነግሥ ማነሣሣታቸው ነው፡፡ “ብዙዎች በየዋሕነት ጌታ ያዘዘው ሐዋርያት የደነገጉት ነው ብለው ዕለተ እሑድን ሰንበት ነች እያሉ እንደሚያስቡ ይታወቃል፤ ነገር ግን እሑድ መቼ እነማን ለምን ዓላማ ሰንበት ተብላ ልትሰየም ቻለች ብለን ስንመረምር የሰይጣንን ተንኮል እናስተውላለን…” እያሉ እሑድ ሰንበት መባሏን የሰይጣን ሥራ ያደርጉታል፡፡

   

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበተ አይሁድን ቀዳሚት ሰንበት ብላ እንደ ክርስትናው ሕግና ሥርዓት ተገቢውን ክብር እንደምትሰጥ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ እስከ አሁን የክርስቲያን ወገን ሁሉ ሲቀድሳት የነበረችን ሰንበተ ክርስቲያንን ግን ገናና፣ ክብርት፣ ልዕልት ሆና የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ሲዘከርባት የኖረችና የምትኖር ናት፡፡ እነዚህ ወገኖች ግን የተረፈ አይሁድን ሐሳብ ዳግም ለማራገብ በመነሣት መከራከሪያ እንድትሆን ጥረት ማድረጋቸው ወደ ኋላ የሚስባቸውን አሮጌ እርሾ ያሳያል፡፡

የዳዊት ኮከብ መሠረቱ የሆነ ትእምርተ መስቀል መለያችን ይሁን
የዳዊት ኮከብ የአይሁድ ምኩራቦች መለያ ምልክት ነው፡፡ የዳዊት ኮከብ ሰሎሞናዊ እንደሆኑ በሚነገርላቸው በኢትዮጵያ ነገሥታት ዘንድ የቤተ መንግሥቱ ትእምርት ሆኖ እንደኖረ እስከ አሁን ድረስ በቤተ መንግሥትና በዩኒቨርሲቲዎቻችን አጥሮች በሚታዩት ምልክቶች እንረዳለን፡፡ ይሁን እንጂ ክርስትናውን አሽቀንጥሮ ለመጣል መሠረቱን ለመናድ ያዋሉት ሳይሆን የቤተ መንግሥቱ ምልክት ሆኖ የመንግሥቱን የትመጣ ለማጠየቅ የተገለገሉበት ትእምርት ነው፤ ከዚህ ባለፈ ግን እኛ ሁላችን ከዳንበት ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀሉ ትእምርት ጋር ቁርኝት የምንፈጥርበት አይደለም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ወገኖች አሁንም ክርስትናችንን ከአይሁዳዊነት ጋር የመቀላቀል አሳብ ወይም ሌላ በሃይማኖት ስም ሊተክሉ የሚፈልጉት የፖለቲካ ርእዮት አለ ማለት ነው፡፡ እኛ ሃይማኖታችን ትእምርት የሚያደርገው የዳዊትን ኮከብ ሳይሆን ዳዊትን ጨምሮ ሰዎች ሁሉ የዳኑበትን የክርስቶስን መስቀል መሆኑን በመረዳት ሊታረሙ ይገባል፡፡

 

በሌላም በኩል “ቶ” እንደ ብቸኛ የመስቀል ምልክት አድርጎ ለመጠቀምና በዳዊት ኮከብ ምልክት ላይ ተቀጽሎ እንዲቀርብ ይሰብካሉ፡፡ በአልባሳቶቻቸው አትመው ወይም ቀርጸው ያሳያሉ፡፡ የ “ቶ” ቅርጽ በተለያዩ ዘመናት በተለያዩ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች እንደሚታየው በሆነ ዘመንና ሁኔታ ወስጥ የመስቀል ምልክት ሆኖ አገልግሎ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ በመለስ ግን የሆነ የቤተ ክርስቲያናችን መለያ እንዲሆን አድርጎ የመቀሰቀስ ሥልጣን ግን ለዚህ ቡድን የሰጠው የለም፡፡ ካልሆነ ግን የሚኖረው ፋይዳ በእነ ዴርቶጋዳ፣ ራማቶሐራ፣ ዣንቶዣራ ከሚነገረን ልቦለዳዊ የርእዮተ ዓለም መግባቢያነት ያለፈ አይሆንም፡፡ በዚያም ልቦለዳዊ ታሪክ እንኳ ቢሆን ይህን የምስጢር መልእክት መቀባበያ አድርጎ ሲጠቀምበት የነበረው ገጸ ባህርይ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚኖር አባ ፊንሐንስ የተባለ የይሁዲ እምነት ተከታይ ነበር፡፡ ታሪኩን ስናነብ የሌላዋን ገጸ ባሕርይ የልጁን የሲጳራን ክርስቲያናዊ ሕይወት ለማስጣል የአንገቷን መስቀል ለመበጠስ ሲታገል የነበረ አስመሳይ መነኩሴ ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ወስጥ ታዲያ “ቶ” የዚህ አስመሳይ መጠቀሚያ ነበር፡፡ ታዲያ እነዚህ በእውኑ ዓለም ያሉ ወገኖች “ቶ”ን ካልተጠቀመን ሞተን እንገኛለን ሲሉ በክርስትና ስም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየኖሩ የራሳቸውን ተልእኮ ለማሳካት የሚሮጡ ተረፈ አይሁዳውያን ናቸው አያስብል ይሆን!  

ዮዲት ጉዲት ስሟ ታሪኳ ተዛብቷል
“ደቂቀ ኤልያስ” ብለው ራሳቸውን የሚጠሩት እነዚህ ወገኖች አይሁዳዊ እንደሆነች ታሪክ የጻፈላትን ዮዲት ወይም ጉዲት ወይም እሳቶ የሠራችውን ሥራ እንደበጎ ተቆጥሮ ታሪክ እንዲገለበጥ ይሠራሉ፡፡ ዮዲት ጉዲት አብያተ ክርስቲያናትን ስታጠፋ ክርስቲያኖችን ስታርድ መኖሯን ታሪክ እየመሰከረ ነቢዩ ኤልያስ ነገረን በሚል ማስረጃ እውነታው ተገልብጦ ጠንቋዮችን ዐመፀኛ ካህናትን ወዘተ እንዳጠፋች እንዲታሰብ ሊያግባቡን ይጥራሉ፡፡ ሰልፋቸው የአይሁድን ገጽታ የመገንባት ከተቻለም ከይሁዲነት የሃይማኖት እሳቤዎች እየሸራረፉ ለማጉረስ በመሆኑ እንቅስቃሴው የተረፈ አይሁድ ነው፡፡
 
 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መዋቅር በአውሬው መንፈስ የሚመራ ነው
እነዚህ ወገኖች ያዘሉት ጭፍንነት የተሞላበት አካሔድ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደሚጠሏት ያሳብቃል፡፡ በታሪክ ረገድ ከንግሥተ ሳባ እስከ ደቂቀ እስጢፋ፣ በአስተዳደር ዘማዊና መናፍቅ ከሚሏቸው ጳጳሳት እስከ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ በሃይማኖት ከኦርቶዶክስ አይደለንም እስከ ሰንበተ ክርስቲያንን መሻር ድረስ የተመሰቃቀለ መሠረት የለሽ ቅዠትን ይዘው ተከታይ ለማፍራት መንቀሳቀሳቸው፣ ሊያውም በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ መሆኑ ለሃይማኖት ቤተሰቡ ያላቸውን ንቀትና የድፍረት አሠራራቸውን ያስረዳል፡፡ ስለዚህ ሲቀሰቅሱም ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደፈረሰች አደርገው ነው፡፡ ለዚህም “የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተባለው መዋቅር ማንንም ሊደግፍና ሊጠልል ቀርቶ እራሱን እንኳን ማቆም ያልቻለ በገዛ ራሱ የፈረሰ የእንቧይ ካብ መሆኑን እንረዳለን” ይሉናል፡፡ ተስፋ ማስቆረጥ ይፈልጋሉ፤ መንጋውን መበተን ይሻሉ፤ ለማን ሊሰጡት እንደሆነ አይታወቅም፤ ግን ምእመኑ እንዲሸሽ ይመክራሉ፡፡ የሆነውም ያልሆነውም በካህናትና መነኮሳት ተሠሩ የሚሏቸውን የሥነ ምግባር ችግሮች መቀስቀሻ ያደርጉታል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ አስተዳደራዊ ችግሮችን የሃይማኖታዊ አስተምህሮ ችግር ያህል አድርገው ይሰብካሉ፡፡ በእነርሱ እሳቤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዲያቆናት ቀሳውስት ጳጳሳትም ሁሉ የቅባት፣ የዘጠኝ መለኮት ወልድ ፍጡር የሚሉ አሪዮሳውያን ወዘተ ኑፋቄ ተከታዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእነርሱ መስቀል መሳለም፣ በእነርሱ እጅ መቁ ረብ የማይገባ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክህነቱ መንጋውን እንዲሰበስብ አይፈልጉም፡፡

 

ቤተ ክህነቱ መንጋውን መሰብሰብ እንዳይችል ሆነ ማለት የክህነትን ሥልጣን እንደሌሎች መናፍቃን ካድን ማለት ነው፡፡ እንደውም በኢትዮጵያዊው መልከጼዴቅ ሥርዓተ ክህነት የሆነ አዲስ ሊቀካህን ይኖርና ክህነት እንደ አዲስ ኤልያስ ለመረጣቸው ይሰጣል፤ ይላሉ፡፡ ልብ በሉ “ሊቀ ካህን” የሚለው እሳቤ ዳግም ወደ አይሁድ ዓለም የሚስብ ነው፡፡ ለአንዳንዶችም መስቀል ከሰማይ እንደተላከ ሆኖ ሲሰጣቸው የታየበት መድረክም አለ፡፡ ስለዚህ በእነሱ እሳቤ ሐዋርያዊ ውርስ የሚባል ነገር በክህነት አይታሰብም፡፡ ስለዚህ ክህነቱ ተክዷል፡፡ ይህንን ካላመንን ደግሞ የሚያጠምቀን የሚያቆርበን የሚናዝዘን የሚያመነኩሰን የሚያጋባን የሚፈውሰን በቅብዐ ሜሮን ለእግዚአብሔር የሚለየን ማን ይሆናል፡፡ እንዳትቆርቡ ብለው ሲቀሰቅሱ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ እየለዩን ነው፡፡ ስለዚህ እርሱን እንዳንቀበል የሚሠ ሩትስ ለምንድነው፡፡ ካህን ከግብጽ ይመጣል እንዳይሉን ግብፆችም ለእነዚህ ወገኖች መሰሪና ተንኮለኞች ናቸው፡፡

 

“ካህናቱ የበኣል የጣዖት ካህናት ሆነዋልና አትቀበሏቸው” በሚለው በእነዚህ ሰዎች ልፈፋ የሚከሰሰው ሁሉም ከሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለችው ከእነማን ጋር ነው፡፡ ማኅበራቱ፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶቹ ሁሉ በዚህ ቡድን እሳቤ የአውሬው ወገኖች ናቸውና፡፡ ታዲያ ያለክህነት እና ካህናት ያለ አገልጋይ መምህራን ሰባክያነ ወንጌል የምትኖር የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ያለች ናት፡፡ ስለዚህ ያላችሁት ያለሰብሳቢ ነው እያሉን ነው፡፡ ታዲያ የሚፈልጉት እንድንበተን ብቻ ከሆነ “ደቀ መዛሙርቱ ሰርቀውታል እንጂ አልተነሣም” እያሉ በክርስቶስ አምነው የነበሩትን ክርስቲያኖች ተስፋ አስቆርጠው ሊበትኑ ከተነሡት አይሁድ አሠራር በምን ይለያል፡፡ መንገዳቸው ቅስቀሳቸው ሁሉ የማፍረስና የጭካኔ ነውና፡፡

 

ከመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት እንለይ
ለእነዚህ ወገኖች በክርስትና ስም ካሉ ከሁሉም ወገኖች ጋር መጎራበታችንን አይወዱም፡፡ ስለዚህ ከሃምሳ ዓመታት ያላነሰ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ ለማድረግ አስተርጉሞ አሳትሞ በማከፋፈል አገልግሎት እየሰጠ ያለውንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በዋናነት ተሳትፎ ከምታደርግበት ማኅበር እንድንርቅ ይመክራል፡፡ ሰዎችን ያነሣሣል፡፡ እነርሱን ጨምሮ ብዙዎች በሀገራችን በአማርኛና በሌሎችም ቋንቋዎች ተተርጉመው የቀረቡ መጻሕፍት በቀላሉ ማግኘት እንዲቻል ድጋፍ እየሰጠ ያለውን ማኅበር የጥፋት መልእክተኛ ማድረግ ሚዛናዊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ስልታዊ በሆነ መልኩ የማዳከም ፍላጎት ነው፡፡

በመሠረቱ እነዚህ ወገኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርን ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን የእምነት መሠረት ማድረግን የሚቀበሉ አይደሉም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉ በተንኮልና በአውሬው አሠራር ተለውጧል ብለው ያስባሉ፡፡ የዚህ ምክንያት ግን ግልጽ ነው እነርሱ ለሚነዟቸው ልፍለፋዎች ሁሉ ደጋፊ የሚያደርጉት መጽሐፋዊ መነሻ አለመኖሩ ነው፡፡ ስለዚህ ሲመቻቸው “በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገረው የዓለም የፍጻሜ ዘመን ተቃርቧል” ይላሉ፤ ሳያስፈልጋቸው ደግሞ “መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርን አትመኑ” እያሉ ይቀሰቅሳሉ፡፡ ለእነርሱ ታማኙ የእምነታቸው መጽሐፍ “የኤልያስ ዐዋጅ ነው” የሚሉት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚሠራውን ደባ እያቀነባበረ ያለው የእነርሱ “አባትዬ” ተራ ድርሰት ነው፡፡ እርሱ ለዘመናት ተሻግሮ ከመጣው ቃለ እግዚአብሔር በላይ ታማኝ ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጥላል፡፡  

 

ከዚህም ተሻግሮ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አባል መሆን ገንዘብ መውደድ እንደሆነ አድርጎ አጥብቦ ለማሳሰብ ይሠራሉ፡፡ ከኅብረቱ ወጥቶ እነርሱን መሳብ እንጂ መተባበር ሃይማኖት ያጠፋል ብለው ያስባሉ፡፡ ሃይማኖትን ማስፋፋት ከማይፈቅዱ ወገኖች ጋር ቤተ ክርስቲያን የተባበረች አድርጎ በማሳሰብ የክርስትና ሽታ ካላቸው ኦርቶዶክስ የሚባሉ አኀት አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ ቤተ ክርስቲያን አጠገባቸው እንድትደርስ አይሹም፡፡ ክርስትናን መሸሹ እንዳለ ሆኖ እንድንጠነቀቅ ከማሳሰብ የሚነሣ ሳይሆን አጠገባቸው እንዳንደርስ በፍርሃትና በጥርጣሬ ተሞልተን፣ ራሳችንን ብቻ አጽድቀን እንድንነሣ ስለሚገፉ አካሔዱ አይሁዳዊ እርሾ የተቆራኘው ነው፡፡ ሌላውን የኃጢአት ጎተራ አድርጎ ከመፍረድ ያልፍና አይሁድ ጌታን በሚከሱበት “የአብሮ በላ አብሮ ጠጣ” ክስ ቤተ ክርስቲያንንም ሊከሱ ይነሣሉ፡፡

 
ሰንበት ትምህርት ቤቶች አያስፈልጉም
እነዚህ ወገኖች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለማዳከም የሚሠሩ ሤረኞች መሆናቸውን በቀላሉ የምንረዳው በዚህ ዘመን ያሉ የቤተ ክርስቲያንን የአገልግሎት ምሰሶዎች ለመነቅነቅ መቋመጣቸው ነው፡፡ ለዚህ ማሳያው ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማመስገን ፈንታ ሲወቅሷቸው፣ በማበረታታት ፈንታ ሲሰደቧቸው መታየታቸው ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች በረጩት ጽሑፍ ላይ ያስነበቡንን ስናይ “ሰንበት ትምህርት ቤት አውሬው የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ለማጥመድ የመሠረተው ረቂቅ ስውር ወጥመድ ነው” ይላሉ፡፡ ሴቶችን ከሊቃውንት በላይ አድርጎ ወረብ ያስወርባል፤ የአውሮፓ ባህል ነው፣ አስነዋሪ ሥራዎች ይሠሩበታል…ወዘተ እያሉ ተራና ጽንፈኛ ቅስቀሳ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ክርስትናን ሃይማኖቴ ነው ብሎ ከሚከተል ወገን የሚሰነዘር አይደለም፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምእመናንን ከመናፍቃን ለመጠበቅ የሠሩትን፣ ሕፃናትና ወጣቶች ቤተ ክርስቲያንን እንዲያውቋት፣ የፈጸሙትን አገልግሎትና ቤተ ክርስቲያንም የአገልግሎት ውጤቱን አይታ አንድ መምሪያ ያቋቋመችለት መሆኑን እያወቁ፤ ካላቸው የተረፈ አይሁዳዊነት ስውር ተልእኮ አንጻር ሰንበት ትምህርት ቤቶች በሠሩት አገልግሎት ተቆጥተው የሚያስተጋቡት ስም ማጥፋት ነው፡፡ አካሔዳቸው ፀረ ስብከተ ወንጌል ነው፤ ስለዚህ ፀረ ክርስትና ነው፤ ስለዚህም የአይሁድ ቅናትን ያዘለ ነው፡፡

 
ማኅበረ ቅዱሳን አጥማጅ ስለሆነ ይጥፋ
የእነዚህ ወገኖች ሌላው ዒላማ ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ ለብዙ መናፍቃን ራስ ምታት የሚሆንባቸው የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ለዚህም ኃይል ራስ ምታት ሆኗል፡፡ በዚህ ቡድን ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን የሚነቀፈው እንዲህ እየተባለ ነው “የኢትዮጵያ ቅዱሳን ያዘኑበት፣ የዐመፀኞች ስብስብ፣ ምን ያህል ያጌጠ ሽፋን እንደተከናነበ በውስጥ ግን ምን እንደሚያካሒድ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ካለ እኔ ለቤተ ክርስቲያን ማንም የለም እያለ ከመናፍቃንና ከዘማውያን ጳጳሳት ጋር ሽር ጉድ የሚል የኢትዮጵያ ቅዱሳንን ቃል የሚያስተሐቅር ትእቢተኛ ጎራ ጌታ የተለሰኑ መቃብራት ናቸው ሲል የተናገረበት ነው” ብለዋል፡፡ መናፍቃን የቅዱሳንን ገድል ብቻ የሚሰብክ እያሉ የሚተቹትን ማኅበረ ቅዱሳንን እነዚህ ወገኖች ደግሞ የቅዱሳንን ቃል ያስተሐቅራል በማለት በሌላ ጽንፍ ስም ለማጥፋት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የዚህ ሰልፍ መሠረት የተቃውሞው መነሻ ግን የአይሁድ ቅናት ነው፡፡ ማኅበሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላሉ ክርስቲያን ተማሪዎች የሚሰጠው አገልግሎት፣ በሚዲያዎቹና በመምህራኑ የሚሰጠው አገልግሎት፣ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር ተስማምቶ የመሔዱ ነገር፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚያደርገው ጥረት፣ መናፍቃንን ለማስታገስ የሚጥረው ጥረት፣ ገዳማትና አድባራት እንዳይዳከሙ የሚተጋው ትጋት ወዘተ ሰይጣንን ማስቀናቱ ያመጣው ስድብ ነው፡፡ ቢያንስ ወጣቶች የክርስትና የሞራል ሰብእና ወይም ሥነ ኅሊና እንዲኖራቸው ያደረገው ጥረት አልታሰባቸውም፡፡ ይህ በመሆኑ እነዚህ ወገኖች የሚደሰቱት በተቃራኒው ሲሆን ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ተቃራኒ ሲቆሙ የሚቆሙት የኢትዮጵያ ክርስትናን በመቃረን ነው፡፡ ሰለዚህ ክርስትናን በማጥላላት ወደ ቀደመ በሰው ወግ ወደ ተፈጠረ አሮጌ እርሾ ሊወስዱን መዳዳታቸውን ብንጠረጥር ያስኬዳል፡፡

 
ኤልያስ መጥቷል
ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መምጣቱንም ሊያበስሩን ይሞክራሉ፡፡ አስገራሚው ነገር ከላይ የተነሡ ሁሉንም ጉዳዮች የገለጠው ያወጀው የፈረጀው የለወጠው የሻረው ያጸደቀው የኮነነው ነቢዩ ኤልያስ እንደሆነ በየምዕራፉ ይነግሩናል፡፡

 

ነቢዩ ኤልያስና ሄኖክ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መሠረት በምድር ላይ እንደሰው ተመላልሰው በኋላ ግን ሞትን ሳይቀምሱ በማረግና በመሰወር በብሔረ ሕያዋን እስከ አሁን እንደሚኖሩ ይታመናል፡፡ ሰው ሆኖ ተፈጥሮ በለበሱት ሥጋ መሞት ለማንም አይቀርምና ወደዚህ ዓለም መጥተው በሰማዕትነት እንደሚያርፉ የቤተ ክርስቲያናችን ነገረ ሃይማኖት ያትታል፡፡ ከዚያም በመነሣት ስለኤልያስ መምጣት የተነገሩባቸው ሁለት የትንቢት ቃሎች በመጽሐፍ ቅዱሳችን አሉ፡፡ የመጀመሪያው ከመሲሑ ከክርስቶስ መምጣት አስቀድሞ እንደሚመጣ የተነገረው ምጽአት ነው፡፡ ይህም በነቢዩ ሚልክያስ “እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ፡፡ መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል፡፡” ተብሎ የተነገረው ነው /ሚል. 4፥5/፡፡

ሌላው የትንቢት ቃል ደግሞ በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ላይ የተነገረው የሚከተለው የትንቢት ቃል የተተረጎመበት ክፍል ነው፡፡ “ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺሕ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ፡፡ እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው፡፡ ማንምም ሊጎዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል፡፡ ጠላቶቻ ቸውንም ይበላል፡፡ ማንም ሊጎዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል፡፡ እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳ ይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፤ ውኃዎችንም ወደደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሰፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው፡፡ ምስክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ያሸንፋቸውማል፡፡ ይገድላቸውማል፡፡ በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል፡፡ እርሷም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብፅ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት፡፡ ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኩል በድናቸውን ይመለከታሉ፡፡ በድናቸውም ወደ መቃብር ሊገባ አይፈቅዱም እነዚህ ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስለ ሣቀዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል፡፡ በደስታም ይኖራሉ እርስ በእርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ፤ ከሦስት ቀን ተኩልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤ በእግሮቻቸውም ቆሙ፡፡ ታላቅም ፍርሐት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው፤ በሰማይም ወደዚህ ውጡ የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፡፡ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቷቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ፡፡…” /ራእ. 11፥3-03/ በዚህ ቃለ እግዚአብሔር ውስጥ “ሁለቱ ምስክሮቼ”፣ “ሁለቱ ወይራዎች”“ሁለቱ መቅረዞች”፣ “ሁለት ነቢያት” እያለ የሚጠራቸው በዚህ ዓለም ሞትን ያልቀመሱ ሁለቱ የእግዚአብሔር ወዳጆች ሄኖክና ኤልያስ እንደሆኑ ሊቃውንቱ በትርጓሜ ያስቀምጣሉ፡፡ እነዚህም ቅዱሳን የሚገለጹት ከጥልቁ የሚወጣውን አውሬ ሊዋጉ ነው እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ሊዋጉ አይደለም፡፡

 

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ትንቢቶች ትንቢት እንደመሆናቸው መጠን የተፈጸሙበትን ጊዜና ሁኔታ ሊረዱ የሚችሉት ቅዱሳን ናቸው፡፡ “በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም” /2ጴጥ.1፥21/ እንደተባለ በሥጋና ደም ሰዎች የሚረዷቸው አይደሉም፡፡ ይህ አካሔድ አይሁድን ከሃይማኖት መንገድ ያስወጣቸው ነው፡፡

አይሁድ በኤልያስ መምጣት ጉዳይም ስተዋልና፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ለጌታችን “እንግዲህ ጻፎች ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል ስለምን ይላሉ ብለው ጠየቁት” የነቢያት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናል፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ የወደዱትንም ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም” አላቸው፡፡ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንደነገራቸው አስተዋሉ፡፡/ማቴ.17፥11/ አይሁድ ግን በሥጋና ደም ለትንቢቱ ትርጓሜ አበጅተው ይጠባበቁ ነበር፡፡ በግብሩ፣ በመንፈሱ፣ በአኗኗሩ ኤልያስን መስሎ ንስሐ ግቡ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኸው ድምፅ ኤልያስ የተባለው ዮሐንስ መሆኑን አላስተዋሉምና እርሱንም መሲሁንም ሳይቀበሉ ቀሩ፡፡ ለዚህም ነው እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የአይሁድ በመሆኑ የአሁኖቹ “ኤልያሳውያን” አካሔድ ተረፈ አይሁዳዊነት ነው የምንለው፡፡

 

በአንድ በኩል ይህንን የነቢዩ ሚልክያስን ቃል ይዘው እየሞገቱን ከሆነ ዮሐንስ መጥምቅን በኤልያስ መንፈስ መምጣቱን አለመቀበልና ብሎም መሲሁን ኢየሱስ ክርስቶስንም እንዳለመቀበል ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ነገ ከነገወዲያ ባለፉት ዓመታት በየአደባባዩ ስታውከን እንደነበረችው ሴት መሲሁ ተወልዷል ወይም ሊወለድ ነው ሊሉን ተዘጋጅተዋል ማለት ነው፡፡ ይህ በግልፅ የመጣ የይሁዲ እምነት አራማጅነት ነው፡፡

 

በሌላ በኩል ደግሞ በዮሐንስ ራእይ የተቀመጠውን የትንቢት ቃል መነሻ አድርገው እየሞገቱን ከሆነ ደግሞ አስተሳሰቡ አሁንም ትንቢትን ለገዛ ራስ መተርጎም እንዳይሆን ልንጠነቀቅበት የሚገባ ነው፡፡ ለገዛ ራስ መተርጎም የጸሐፍት ፈሪሳውያን እርሾ ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች አካሔድ ሃይማኖትን ተራ ጨዋታ ወደ ማድረግ የሚወስድ ነው፡፡ ሃይማኖትን በንቀት እንዲታይ የማራከስ አካሔድ ነው፡፡ ኤልያስ መጥቷልና አጅቡት ተቀበሉት እያሉ በየመንደሩ መቀስቀስ እገሌን ይጥላል እገሌን ያፈርሳል እያሉ በማውራት ለምእመናንን ምልክት ፈላጊነትን ማለማመድ ነው፡፡ ሰዎች ሃይማኖት ከምግባር ይዘው እንዲገኙ ከማስተማር ይልቅ ኤልያስን ፈልጉት እያሉ ማባዘን ተገቢ አይሆንም፡፡ ይህ “የአመንዝራ ትውልድ” ጠባይ ነው፡፡ ምልክትን የሚፈልግ ማኅበረሰብ እምነትን ይዞ ለመገኘት አይቻለውም፡፡

 

እነዚህ ወገኖች አሳባቸው ሥጋዊ ስለሆነ የትንቢቱን መፈጸም ሊነግሩን የሚቻላቸው አይደሉም ሊባል የሚችልበት ምክንያት አለ፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ኤልያስ የሚመጣው የአትዮጵያን ቤተክህነት አፍርሶ ሊያድስ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ቤተ መንግሥት  ሊያስተካክል ነው፡፡ ባንዲራውን ከአረንጓዴ ቢጫ ቀይም አልፎ በሰባቱ የቀስተ ደመና ረቂቅ ቀለማት /spectrum/ አስውቦ ሊተክል ነው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ እየከለሰ ሊያስጠናን ነው፡፡ ስብከተ ወንጌል የሚያካሒዱ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራትን ሊያፈርስ ነው፡፡ ሰንበትን ሊሽር ወይም ሊተካ ነው፡፡ ነግሦ የኢትዮጵያን ሕዳሴ ሊያመጣ ነው፡፡ ይህ ፍጹም ብሔርተኛና ፍጹም ሥጋዊ የሆኑ ሐሳቦች ናቸው፡፡ ካልሆነም የጥንቆላና የመናፍስት ሥራ ነው፡፡ ካልሆነም ለሥጋዊ ጥቅም የሚደረግ ሩጫ ነው፡፡ ካልሆነም ብዙዎች እንደሞከሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ለመፈታተን የመጣ ሌላ አዲስ የዘመቻ ጽንፍ ነው፡፡ በስሕተትም ቢሆን ግን ስሕተቱ ትንቢትን ለገዛ ራስ የመተርጎም ዝንባሌ ነውና ተረፈ አይሁዳዊነት ነው፡፡   

       
 
ማጠቃለያ
እነዚህ ወገኖች ያነሧቸው የማሳሰቻ ቅስቀሳዎች በራሳቸው የትም የማያደርሱ የተሰነካከሉ ሐሳቦች ቢሆኑም ፀጉሩን የገመደ፣ ቆዳ የለበሰ፣ ባዶ እግሩን የሚታይ “ባሕታዊ” አንድ መዓዝን ላይ ሲጮኽ አይተው ቆመው ለሚሰሙ የዋሐን ግን ጥርጥርና ማደናገሪያ ማሳቻ መሆኑ አይቀርም፡፡ ቡድኑ ከዚህ አልፎ በሕዝብ ዘንድ ይታወቃሉ የሚላቸውን አንዳንድ የዋሕ አርቲስቶች ቀስቃሽ ለማድረግ እንደ ስልት መያዙ ደግሞ የምር ታስቦበት ለመዝመት እየተሠራ መሆኑን ያሳያል፡፡

 

እነዚህ ወገኖች በየዓለሙ መዓዝን ዓለም ሊጠፋ ነው ብለው እንደሚቀሰቅሱት ምጽአት ናፋቂዎች ናቸው ብሎ ደፍሮ ለማውራትም የማይመች ነው፡፡ የሚያወሩልን ስለፍፃሜ ዓለምም አይደለም፤ ኢትዮጵያ በኤልያስ ገና ወደ ልዕልና እንደ ምትመጣ፣ በረከት መልካም ዘመን እንደሚቀርብ ሊነግሩን ነው፡፡ ስለዚህ ስለነገረ ምጽአት የሚነግሩን ከሆነ ምጽአት ናፋቂዎች ብለን ልንፈርጃቸው በቻልን፤ ነገር ግን ኤልያስን የሚፈልጉት አይሁድ የክርስቶስን መወለድ ለሚፈልጉበት ለሥጋቸው፣ በዓለሙ ላለ ልዕልናቸው ነው፡፡ የሀገርን ክብርና ልዕልና መመኘት መልካም ነው፤ ነገር ግን በሃይማኖት ስም ሰዎችን እያስጎመጁ እያማለሉ ከመንገዳቸው ማሳት ግን ነውር ነው፡፡

 

የቅዱሳንን ስም የሚያከብረው የኢትዮጵያ ክርስቲያን ወገን በቅዱስ ኤልያስ ስም የመጡ እነዚህን ስዱዳን ማንነት እንዲረዳ ያስፈልጋል፡፡ “ደቂቀ የሎስ” ሆነው የደካሞችን ነፍስ ሊነጥቁ መምጣታቸውን ማስገንዘብ አለብን፡፡ ከተቻለ ሁሉንም ማረምና ማስተካከል የቤተ ክርስቲያን ወገኖች ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡ ካልሆነ በዓላማ ለጥፋት እየሠሩ ካሉት ደበኞች የዋሐኑን መለየት ተገቢ ይሆናል፡፡ አስቀድመን በጽሑፉ መግቢያ ያነሣናት አሳች ሴት እንኳ ለረጅም ጊዜ በማሳቷ ጸንታ ምእመናንን ግራ ስታጋባ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ ይህም እንቅስቃሴ ይህቺ ሴት ባደረገችው መንገድ የመናፍስትና የጥንቆላ አሠራር አብሮ እየታከለበት ከሔደ ደግሞ ነገሩ ውስብስብ ስለሚሆን ካሁኑ ሁሉም ወገን የድርሻውን ተወጥቶ በእንጭጩ መቅጨት ይገባል፡፡

 

ሐመር መጽሔት 20ኛ ዓመት ቁጥር 12 ሚያዚያ 2005 ዓ.ም.

belaae sebe

በእንተ በላኤ ሰብእ

belaae sebe

ስምዖን/የበላኤ ሰብእ ታሪክ በተአምረ ማርያም ከተመዘገቡትና የእመቤታችንን አማላጅነት ከሚያሳዩት ታሪኮች አንዱ ነው፡፡ ዘወትር በየዓመቱ በየካቲት 16 ቀን ይዘከራል፣ ይተረካል፣ ይተረጎማል፡፡ የስምዖን በላኤ ሰብእ ዘመን በሁለት ይከፈላል፡-

 

ደገኛው የስምዖን/በላኤ ሰብእ ዘመን

በላኤ ሰብእ አስቀድሞ አብርሃማዊ ኑሮ የሚኖር ደገኛ ሰው ነበር፡፡ እንግዳ በመቀበል ዘመኑን የፈጀ ባዕለ ጸጋ ነው፡፡ ነገር ግን የሰውን ልጆች ጽድቅ የማይወደው ዲያብሎስ ሴራ አሴራበት፡፡ በቅድስት ሥላሴ አምሳል እንግዳ ሆኖ ወደ ቤቱ መጣ፡፡ በላኤ ሰብእም እንደ አብርሃም ዘመን ቅድስት ሥላሴ ከቤቱ በመገኘታቸው ተደስቶ ምንጣፍ ጎዝጉዞ ወገቡን ታጥቆ አስተናገደው፡፡ አብርሃም ለሥላሴ ከቤቱ ከብት መርጦ መሥዋዕት እንዳቀረበ በላኤ ሰብእም የሰባውን ፍሪዳ አቀረበ፡፡ ዲያብሎስ ግን የምትወደኝ ከሆነ ልጅህን እረድልኝ ሲል ጠየቀው፡፡

 

በላኤ ሰብእ የዋሕና ደግ ክርስቲያናዊ ስለ ነበር እሺ በጄ ብሎ ልጁን አቅርቦ ሰዋው፡፡ በኋላም “አስቀድመህ ቅመሰው” የሚል ትእዛዝ ሰጠው፡፡ በላኤ ሰብእም ትእዛዙን ፈጸመ፡፡ ዲያብሎስም ተሰወረው፡፡ በላኤ ሰብእ የልጁን ሥጋ በመብላቱ ደሙንም በመጠጣቱ እንዲሁም በዚህ ጊዜ ሥላሴ ነው ብሎ በቤቱ የተቀበለው ዲያብሎስ ምትሐቱን ጨርሶ በመሰወሩ የተፈጠረበት ድንጋጤ ጠባዩ እንዲለወጥ አእምሮው እንዲሰወር አድርጎታል፡፡ ዲያብሎስ ልቡናውን ስለሰወረበት ከዚያ በኋላ ያገኘውን ሰው ሁሉ የሚበላ ሆኗል፡፡

 

አሰቃቂው የስምዖን/በላኤ ሰብእ ዘመን

በላኤ ሰብእ አእምሮውን ካጣ በኋላ አስቀድሞ ቤተሰቦቹን በላ፤ ከዚያ በኋላ የውኃ መጠጫውንና ጦሩን ይዞ ከሀገሩ ወጣ፡፡ በየቦታው እየዞረ በጉልበቱ ተንበርክኮ፤ በጦሩ ተርክኮ ያገኘውን ሁሉ ይበላ ጀመር፡፡ ይኸ ጊዜ በላኤ ሰብእ ፍጹም በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር የዋለበት አሰቃቂው የበላኤ ሰብእ ዘመን ነበር፡፡

የንስሐ ዘመኑ

ያገኘውን ሁሉ እየገደለ የገደለውንም እየበላ ሲዘዋወር ከአንድ መንደር ደረሰ፡፡ በዚያውም የሚበላውን ሲሻ ሰውነቱን በቁስል የተወረረ ሰው ተመለከተ፡፡ ይበላውም ዘንድ ተንደረደረ፡፡ ያ ድኃ ፈጽሞ የተጠማ ነበርና ውኃ ይሰጠው ዘንድ በላኤ ሰብእን ለመነው፣ በእግዚአብሔር ስም፣ በጻድቃን በሰማእታት ሁሉ ለምኖት ሊራራለት አልቻለም፡፡ በመጨረሻም “ስለ እመቤታችን ብለህ” ሲለው ይህቺ ደግ እንደሆነች በልመናዋም ከሲዖል የምታድን እንደሆነች እኔም ከሕፃንነቴ ጀምሮ ሰምቼ ነበር አለው፡፡ በላኤ ሰብእ “ወደ ልቡናው ተመለሰ”፡፡ ጨካኝ የነበረው ልቡ ራርቶ ለድኃው ጥርኝ ውኃ ሰጠው፡፡ በሕይወቱም ከባድ ውሳኔ ወሰነ፡፡ ከእንግዲህ ከዋሻ ገብቼ ስለ ኀጢአቴ ማልቀስ ይገባኛል፣ እህል ከምበላ ሞት ይሻለኛል” ብሎ እየተናገረ ንስሓ ገብቶ እህልና ውኃ ሌላም አንዳችም ሳይቀምስ በእግዚአብሔር ኀይል ሃያ አንድ ቀን ከተቀመጠ በኋላ ይህ በላኤ ሰብእ ሞተ፡፡

 

ድኅነተ ስምዖን/በላኤ ሰብእ

ከዚህ በኋላ ተአምረ ማርያም የሚተርክልን የበላኤ ሰብእ መዳን ነው፡፡ የበላኤ ሰብእ ነፍስ በፈጣሪ ፊት ለፍርድ ቆመች፡፡ የመጀመሪያው ፍርድም ተሰማ፤ “ይህቺን ነፍስ ወደ ሲዖል ውሰዷት” የሚል፡፡ እመቤታችን ማርልኝ ስትል ለመነችው፡፡ በላኤ ሰብእ ያጠፋቸው ነፍሳትና የሰጠው ጥርኝ ውኃ በሚዛን ተመዘነ በመጀመሪያም የበላኤ ሰብእ ጥፋት መዘነ፡፡ ነገር ግን እመቤታችን ቃል ኪዳኗ ባረፈበት ጊዜ ጥርኝ ውኃው ሚዛን ደፋ፡፡ የበላኤ ሰብእ ነፍስ በእመቤታችን አማላጅነት ዳነች ይህም የእግዚአብሔር ቸርነት የሚያሳይ ነው፡፡ “እንበለ ምግባር ባህቱ እመ ኢየጸድቅ አነ ቦኑ ለከንቱ ኪዳንኪ ኮነ” በማለት የመልክአ ኪዳነ ምሕረት ደራሲ የተናገረው አስቀድሞም በወንጌልም በደቀ መዝሙር ስም ብቻ ቀዝቃዛ ውኃ ያጠጣ ዋጋው አይጠፋበትም /ማቴ.10፥42/ የሚለው ቃል ተፈጸመ፡፡

 

በምልጃዋ በላኤ ሰብእን ያስማረች እመ ብርሃን ሁላችንም ታስምረን፡፡ አሜን፡፡

ምንጭ፡-

  • ተአምረ ማርያም ባለ 402 ምዕራፍ፣ 1988 ዓ.ም.

  • ሐመር መጽሔት 1994 ዓ.ም. ነሐሴ እትም

photo 4

የ5ቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እጩ ፓትርያርኮች አጭር የሕይወት ታሪክ

የካቲት 19 ቀን 2005 ዓ.ም.

ዲ/ን ኅሩይ ባየ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስድስተኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ አስመራጭ ኮሚቴ በመሠየም እጩ ፓትርያርኮችን ለመምረጥ ከብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከካህናት፤ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች፤ ከማኅበረ ቅዱሳን፤ እንዲሁም ከምእመናን ጥቆማ እንዲያካሒዱ ተደርጓል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ጥቆማውን በግብአትነት በመጠቀም አምስት ሊቃነ ጳጳሳትን በእጩነት በማቅረብ የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አቅርቧል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም ከየካቲት 16 – 18 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ውይይት በማካሔድ አምስቱም ሊቃነ ጳጳሳት በእጩነት እንዲቀርቡ አጽድቋል፡፡ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ለሚካሔደው የስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የፓትርያርክ ምርጫ የቀረቡት ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፡-  ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢየሩሳሌም የኢትዪጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ  የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባና የከፋ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት አጭር የሕይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡-

 

ብፁዕ አቡነ ማትያስ :- photo 4

የቀድሞው የአባ ተክለ ማርያም ዐሥራት የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በ1934 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ቅዳሴ፣ ዜማ፣ ቅኔ፣ ባሕረ ሐሳብ፣ የመጻሕፍተ ሐዲሳት ትርጓሜ ተምረዋል፡፡ በ1948 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ዲቁናን ጮኸ ገዳም ተቀብለዋል፡፡ ከመ/ር ዐሥራተ ጽዮን ኰኲሐ ሃይማኖት መርገ ምንኩስናን ተቀብለዋል፡፡ በ1955 ዓ.ም በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ መርገ ቁምስናን ተቀብለዋል፡፡

 

በጮኸ ገዳም በቄሰ ገበዝነት፣ በመጋቢነትና በልዩ ልዩ ገዳማዊ ሥራ አገልግለዋል፡፡ በገዳሙ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ሐዲስ ኪዳንን አስተምረዋል፡፡ ከ1964 — 68 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅዳሴና በልዩ ልዩ አገልግሎቶች ተመድበው አገልግለዋል፡፡ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ዓመታት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ቀሲስና ምክትል ልዩ ጸሐፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ :-

photo 1የቀድሞው አባ ኅሩይ ወልደ ሰንበት የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በ1930 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ጸዋትዎ ዜማ፣ ቅኔ፣ ትርጓሜ መጻሕፍት፣ ፍትሐ ነገሥት፣ ባሕረ ሐሳብና ሐዲስ ኪዳንን ተምረዋል፡፡ በ1945 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ዲቁና፤ በ1964 ዓ.ም ምንኩስናን በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተቀብለዋል፡፡ በ1965 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ቅስና በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ሰላማ ቁምስናን ተቀብለዋል፡፡ በደብረ ጽጌ ገዳም በመዘምርነትና በቅዳሴ አገልግለዋል፡፡ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም  በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ የከፋ ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስ ተብለው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የሰሜን ጎንደር  ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ :-

ነሐሴ  16  ቀን  1944  ዓ.ም  በሰሜን  ሸዋ  ክፍለ  ሀገር  በሸኖ አውራጃ  ልዩ  ስሙ  ጨቴ  ጊዮርጊስ  በተባለው  ቦታ ተወለዱ፡፡ የቀድሞ ስማቸው photo 2 ቆሞስ  አባ ኀይለጊዮርጊስ ኀይለ ሚካኤል ይባላል፡፡ ፊደል የቆጠሩት፣ ዜማን የተማሩት፣ ቅኔን የተቀኙት በሀፋፍ ማርያም በኢቲሳ ደብረ ጽላልሽ ገዳም ነው፡፡ ቅዳሴን በዳግማዊ ምኒሊክ መታሰቢያ የቀሳውስት ማሠልጠኛ ት/ቤት ተምረዋል፡፡ በሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት ለ4 ዓመታት ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀው ዘመናዊ ትምህርታቸውን እስከ 12ኛ ክፍል በማጠናቀቅ በምዕራብ ጀርመን እሸት ኬርከሌ መንፈሳዊ ት/ቤት ስለ ገዳማት አስተዳዳር አጥንተዋል፡፡

 

ሐምሌ 5 ቀን 1991 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ተብለው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰአት የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡

ምንጭ፡- ዜና ቤተ ክርስቲያን 31ኛ የዓመት ቁ.3፣ ጥር 4 ቀን 1971 32ኛ ዓ.ም ቁ.4


ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፡-

photoየቀድሞ ስማቸው መልአከ ምሕረት አባ ሀብተ ማርያም ይባላል፡፡ ግንቦት 7 ቀን 1946 ዓ.ም በደቡብ ወሎ አማራ  ሳይንት ልዩ ስሙ ደብረ ብርሃን ለንጓጥ ሥላሴ ተወለዱ፡፡ አባታቸው ግራ ጌታ መኮንን ኀይሉ እናታቸው ወ/ሮ አታላይ ደርሰህ ይባላል፡፡ ዜማ፣ አቋቋም፣ ቅኔ፣ ፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ ተምረዋል፤ የቅኔ መንገድ ከነአገባቡ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል በ1956 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል ዲቁና ተቀብለዋል፡፡

 

ጳጉሜን 3 ቀን 1981 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ ገዳም ሥርዓተ ምንኩስና ፈጽመዋል፡፡ ኅዳር 12 ቅን 1982 ዓ.ም የቅስና ማዕረግ ከብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፤ ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ መዓርገ ቁምስና ተቀብለዋል፡፡  ከ1982 – 87 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ በጽርሐ ጽዮን ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ መምህር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከሠኔ 20 ቀን 1987-1990 ዓ.ም በምሥራቅ ሐረርጌ ሐደሬ ጤቆ መካነ ሥላሴ ደብር፣

 

ከየካቲት 1990-93 ዓ.ም የድሬዳዋ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ከሠኔ 1 ቀን 1993 ዓ.ም – ሐምሌ 1 ቀን 1994 ዓ.ም ጀምሮ ለጵጵስና መአርግ እስከ በቁበት ዘመን በአዲስ አበባ ቦሌ ደብረ ምጽላል እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 1994 ዓ.ም የሰሜን ወሎ ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ነሐሴ 22 ቀን 1997 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ተብለው ተሹመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የምዕራብና ደቡብ አዲስ አበባ ፤ የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት  ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፡-

በ1955 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ልዩ ስሙ ምንታምር ቀበሌ ከአቶ ጌታነህ የኋላሸትና ከወ/ሮ አምሳለ ወርቅ ማሞ ተወለዱ፡፡photo 3 አቋቋም፣ ቅኔ ከነአገባቡ ቅዳሴ ኪዳን አንድምታ፣ ዜማ፣ ሠለስት፣ አርያም፣ ጾመ ድጓ፣ ቁም ዜማ ተምረዋል፡፡ በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ዲቁና ተቀብለው ቅስና ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ተቀብለዋል፡፡ በ1975 ዓ.ም በደብረ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ሥርዓተ ምንኩስና ፈጽመዋል፡፡ በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ለ4 ዓመታት ያህል ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በሆላንድ ሆህ እስኩል የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ገብተው ለ4 ዓመታት ተምረው የመጀመሪያ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡

 

በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በሰበካ ጉባኤ አደራጅነት፣ በሰ/ት ቤት ሓላፊነት፣ አ/አ ሀገረ ስብከት ሸሮ ሜዳ መንበረ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በሰባኪነት፣ በአ/አ ሀገረ ስብከት በአቃቂ መድኀኔዓለም፣ በቃሊቲ ቅዱስ ገብርኤል፣ በሳሎ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ደብርና በሐረር ደብረ ገነት መድኀኔዓለም አብያተ ክርስቲያናት በአስሪተዳዳሪነት አገልግለዋል፡፡ በውጭ ሀገር በአሜሪካ ዳላስ ቅዱስ ሚካኤል በአውሮፓ ስዊዘርላንድ በጀኔቫ፣ በሎዛን፣ በዙሪክና በበርንባዝል ከተሞች ባሉ አድባራት በቀዳሽነትና በሰባኪነት አገልግለዋል፡፡

 

ነሐሌ 22 ቀን 1997 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የዋግ ህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ በአሁኑ ሰዓት የየወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡

ፍርድ ለነነዌ÷ ሥልጣን ለነነዌ

የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኩኖአምላክ


ኮናኔ በርትዕ÷ ፈታሄ በጽድቅ÷ የሆነው መድኀኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ጻፍት ፈሪሳውያንን በቋንቋቸው በዕብራያስጥ ቢያስተምራቸው “እንደ ሙሴ፡- ባሕር ከፍለህ÷ ጠላት ገድለህ÷ ደመና ጋርደህ÷ መና አውርደህ፣ እንደ ኢያሱ፡- በረድ አዝንመህ÷ ፀሐይ አቁመህ÷ እንደ ጌዴዎን፡- ፀምር ዘርግተህ ጠል አውርደህ፣ እንደ ኤልያስ ሰማይ ለጉመህ እሳት አዝንመህ ልታሳየን እንወዳለን” የሚል ጥያቄ በቀረበለት ጊዜ የሰጣቸው ምላሽ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል÷ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት  አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ÷ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈረዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና÷ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ” የሚል ነው፡፡ ጻፍት ፈሪሳውያንን ምልክት ያስፈለጋቸው ዋነኛ ምክንያት በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ለማመን አልነበረም፤ ይልቅስ እንደ ዘማ ሴት ምልክት በምልክት እየተደራረበ ማየትን በመናፈቅ ነው፡፡

 

በመጽሐፍ ቅዱሳችን በተደጋጋሚ እንደተገለጠው የአይሁድ ማኅበረሰብ ሁሉ የጌታችንን የባሕርይ አምላክነቱን አይተው ይረዱ ዘንድ ከሌሎቹ ይልቅ በእነርሱ መኖሪያና መንደር እየተዘዋወረ ድንቅ ሥራን ሠርቷል÷ ድውያነ ሥጋን በተአምራት÷ ድውያነ ነፍስን በትምህርት አድኗል፣ ሙታንን አንሥቷል (ማቴ.8÷28-34፣ ማቴ.9÷18-26፣ ዮሐ.9÷1 እስከ ፍጻሜ ምዕራፍ )፡፡ ነገር ግን ቤተ አይሁድ የእጁን ሥራ አይተው፣ የቃሉን ትምህርት ሰምተው ሊያምኑበት እየተገባቸው አላመኑበትም፡ አሁንም አሁንም እየመላለሱ ምልክትን ታሳየን ዘንድ እንወዳለን ይሉ ነበረ(ማቴ.12÷38)፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላካት ክታቡ “መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ” በማለት የአይሁድን መሻት (ፈቲው) ምን እንደሆነ ገልጦ ተናግሯል፡፡(1ኛ.ቆሮ. 1÷22)፡፡ ነባቤ መለኮት የተሰኘው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃንስ ወደ ዓለም የመጣው ነው፡፡በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ ዓለሙ ግን አላወቀውም፡፡ ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፡፡ ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡” በማለት መናገሩ የሚታወቅ ነው(ዮሐ.1÷9-12)፡፡የቃሉን ትምህርት ሰምተው፣ የእጁን ተአምር አይተው ሊያምኑበት እየተገባቸው በአንጻሩ ከሀገራችን ውጣልን የሚል ቃል ይናገሩት እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል፡፡ ጌታችንም “ ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው።”(ማር.6÷4) በአይሁድ መካከል እየተመላለሰ ማስተማሩ፣ ተአምር ማድረጉ÷ጌታችንን እንዲያምኑትና እንዲያከብሩት አላደረጋቸውም፡፡ ይልቁንም በገዛ ወገኖቹ ተይዞ ባልተገባ ፍርድ ለሞት ተላልፎ እንዲሰጥ ሆነ እንጂ፡፡

 

እንግዲህ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን በአይሁድ ላይ ተነስተው ይፈርዱባቸው ዘንድ ሥልጣንን ያሠጣቸው ዋነኛው ምክንያት በነቢዩ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተው  ከእግዚአብሔር ጋር ስለታረቁ ነው (ዮና.3÷10) ፡፡ ቁጥራቸው ከመቶ ሃያ ሺህ በላይ የነበሩና ግራና ቀኛቸውን የማይለዩ ተብሎ የተጻፈላቸው በአሁኑ ጊዜ ኩዌት ቀድሞ ነነዌ ትባል በነበረችው ከተማ የሚኖሩ ሰዎች እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ባለመመላለሳቸው ምክንያት የሚመጣባቸውን መቅሰፍት በንስሐ፣ በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው እንዲያርቁት እንዲያስተምራቸው ነቢዩ ዮናስን አዘዘው (ዮና.1÷2) ፡፡ በአጭር ቃል በነቢዩ ዮናስ አማካኝነት የተላለፈውን መንፈሳዊ ትእዛዝና መመሪያ ተቀብለው ተግባራዊ በማድረጋቸው የሚመጣባቸውን መዐት ማራቅ ቻሉ፡፡ “እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም”(ዮና.3÷10) መምህረ ዮናስ፣ የዮናስ ፈጣሪ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ መካከል እየተመላለሰ በሠራው ሥራ አለማመናቸው፣ በኀጢአታቸው ተጸጽተው ንስሐ አለመግባታቸው እንደሚስፈርድባቸው ነገራቸው፡፡ በዕለተ ምጽአት (በፍርድ ቀን) በአይሁድ ላይ ለመፍረድ የነነዌ ሰዎች ተነስተው “እኛ እግዚአብሔርን ባለመወቅ÷ እርሱንም በማሳዘን፡- በኀጢአትና በበደል ሥራ ተጠምደን ስንኖር ነቢዩ ዮናስን ልኮልን ባስተማረን ጊዜ ንስሐ ገብተን ምሕረት ቸርነቱ ተደረገልን፤ እናንተ ግን የዮናስ አምላክ፣ የዮናስ ፈጣሪ በመከከላችሁ እየተመላለሰ ያስተማረውን ትምህርት ባለመቀበላችሁ÷ የእጁን ተአምራት አይታችሁ ባለማድነቃችሁ ሊፈረድባችሁ ይገባል፤” ብለው ይፈርዱባችኋል አላቸው፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት ሕዝበ እግዚአብሔር እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት እስራኤላውያን የተደረገላቸውን ቸርነት ማድነቅ ሲገባቸው ነገር ግን አልተጠቀሙበትም፡፡ ወደ እነርሱ ከእግዚአብሔር ተልከው የሄዱትን ነቢያት፣ መምህራን  የእግዚአብሔር ሰዎችን ቃላቸውን ከመስማት ይልቅ÷ እኩሌቶቹን አሳደዱ፣ እኩሌቶቹን ደበደቡ፣ እኩሌቶቹን ገደሉ፡፡ቀዳሜ ሰማዕታት ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ እንደተናገረው ፡-“ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም።” (የሐዋ.ሥራ.7÷52-53)፡፡

 

ከነነዌ ሰዎች  የምንማረው ምንድር ነው?

1ኛ. የእግዚአብሔርን ቃል መስማትና ለመፈጸም መነሣትን፤ ሰብአ ነነዌ አስቀድመው ፈቃደ እግዚአብሔርን የማያውቁ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በትእዛዘ እግዚአብሔር ለመኖር የሚያስችላቸው ቃሉን እንኳ የሚነግራቸው ነቢይ ስላልነበራቸው በኃጢአት ተጠምደው መኖራቸው ታውቋል፡፡ “እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ  ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?” የሚለው የእግዚአብሔር ቃል የሚያስረዳን እኒህ የነነዌ ሰዎች ቃለ እግዚአብሔርን አለማወቃቸውን ነው፡፡ ይህንኑ አለማወቃቸውን ያሳውቃቸው ዘንድ ነቢዩ ዮናስ ያስተማራቸውን  የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ፈጽመዋል፡፡(ዮና.3÷4)

 

በዚህ ዘመን ያለን ሰዎች ከምንቸገርባቸው ምክንያቶች አንዱ ቃሉን ለመስማትና ለመፈጸም ያለን ትጋት ደካማ መሆን ነው፡፡ አምላካችን “ይሰሙኝስ ዘንድ ለማን እናገራለሁ? ለማንስ አስጠነቅቃለሁ? እነሆ፥ ጆሮአቸው ያልተገረዘች ናት ለመስማትም አይችሉም እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቃል ለስድብ ሆኖባቸዋል፥ ደስም አያሰኛቸውም” ብሎ የተነገረው ቃል እንዳይፈጸምብን ልናስብ ይገባናል፡፡ (ኤር.6÷10) ከዚህ ላይ አብሮ መታየት የሚገባው ዐቢይ ጉዳይ ቃሉን ከመስማት ባሻገር እንደቃሉ መኖር የሚገባ መሆኑን ነው፡፡ ብዙዎቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን ቃላት በማወቅ ደረጃ እናውቃቸው ይሆናል፤ ነገር ግን ማወቃችን ወደ ሕይወት (ወደ ተግባር) የተሻገረልን ስንቶቻችን እንሆን? እንጃ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ” በማለት የሰጠንን መንፈሳዊ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያሻናል፡፡(ያዕ.1÷22) ንስሐን የሚቀበል ልዑል እግዚአብሔር ኀጥአን ልጆቹን ከርኩሰታቸው ያጠራቸው ዘንድ በነቢዩ ኢሳይያስ አድሮ ባስተላለፈው የንስሐ ጥሪ ውስጥ “…እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ…” የሚል ቃል ተናግሯል(ኢሳ.1÷19)፡፡ እንግዲህ ልብ እናድርግ “እሺ” ብሎ ለቃሉ ምላሽ መስጠትና መታዘዝ የተለያዩ ነገራት ናቸው፡፡ ብዙዎቻችን “እሺ” እንል ይሆናል፤ ነገር ግን ታዝዘናል? እንደ ፈቃዱስ ኖረናል? የነነዌ ሰዎች ግን ከዮናስ አንደበት የተላለፈውን መመሪያ (ቃለ እግዚአብሔር) ሰምተው ተግባራዊ አድርገዋል÷ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ ፡-“ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ ጮኾም፡፡ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ፡፡ የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ ለጾም አዋጅ ነገሩ÷ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፡፡”(ዮና.3÷4-5)፡፡ እንግዲህ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት፥ አባቶቻችሁ እኔን የፈተኑበት የመረመሩበትም አርባ ዓመትም ሥራዬን ያዩበት በምድረ በዳ በፈተና ቀን በማስመረር እንደ ሆነ፥ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ” (ዕብ.3÷8-9) ተብሎ እንደተነገረ፤ ቃሉን በሰማን ጊዜ ልቡናችንን ከጥርጥር፣ ከትዕቢት አንጽተን ለንስሐ እንድንበቃ ፈጣሪያችን ይርዳን!

 

2ኛ. ነቢየ እግዚአብሔር ዮናስን  አክብረው መገኘታቸው፤  ከነነዌ ሰዎች ከምንማራቸው ተግባራት ሁለተኛው ነገር የእግዚአብሔር ሰዎችን አክብሮ መቀበልን ነው፡፡ “ከየት መጣህ? ዘርህ ምንድር ነው?…” የሚሉና እነዚያን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ነቢዩን አላስጨነቁም፡፡ ከእግዚአ ነቢያት፣ ከእግዚአ ካህናት የተላከ መሆኑን በመረዳት አክብረው፣ ተግሳፁንም ተቀብለው እንዳስተማራቸው ሆነው ተገኙ እንጂ፤ “ነነዌ ትጠፋለች፣ ነነዌ ትገለነጣለች፣ ትጠፋላችሁ የምትለን የምታሟርትብን አንተ ማነህ” በማለት ለሰይፍ ለእሳት አልዳረጉትም፡፡  “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ÷ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር÷…”(ማቴ.23÷37) በማለት መድኀኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረባት የኢየሩሳሌም ሰዎች እንኳ ፊት፡- ነቢያትን፣ የእግዚአብሔርን ሰዎች፤ ኋላም ሐዋርያትን ያሳደደችና የወገረች መሆኗን ገልጦ ተናግሯል፡፡

 

በዳዊት መዝሙር ውስጥ “እግዚኦ መኑ የኀድር ውስተ ጽላሎትከ፡፡ ወመኑ ያጸልል ውስተ ደብረ መቅደስከ…ዘያከብሮሙ ለፈራሀያነ እግዚአብሔር፤ አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?”(መዝ.14÷1-4) የሚል ቃል ይገኛል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቅዱሳን ነቢያትን፣ ሐዋርያትን ካህናትን በአጠቃላይ ከእግዚአብሔር የተላኩትን ማክበር እነርሱን የላከ ፈጣሪን ማክበር ነው፡፡ እነርሱን መቀበል የላካቸውን መቀበል ነው፡፡ ይህም ሊታወቅ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ በሰጣቸው ሐዋርያዊ ተልእኮ ውስጥ፡-“እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል÷ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል” በማለት የተናገረውን ልብ ይሏል፤(ማቴ. 10÷40) በሐዋርያት ሥራ ላይ እንደተጠቀሰው ያ ከእናቱ ማኅጸን ጀምሮ ሲወጣ አንካሳ ሆኖ የተወለደውና በቤተ መቅደስ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረውን ሰው÷ ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ “ወደ እኛ ተመልከት” በማለት ባዘዙት ጊዜ ወደ እነርሱ ተመልክቶ ከደዌው ለመፈወስ ችሏል፡(የሐዋ.ሥራ.3÷4-6) እኛም ወደ ቅዱሳን ገድል፣ ቃል ኪዳናቸው… ብንመለስ ወደ እግዚአብሔር መመለሳችን እንደሆነ አስበን÷ በቅዱሳኑ ጸሎት ምልጃና ቃል ኪዳን ለመጠቀም እንችል ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት አይለየን፡፡

 

3ኛ ኃጢአት በደልን አምኖ ንስሐ መግባትን ከነነዌ ሰዎች ልንማረው የሚገባን ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን በኀጢአት በበደል እንዲጸኑ ከሚያደርጓቸው ሁኔታዎች አንዱ ምክንያተኝነት ወይም ለራስ ይቅርታ ማድረግ ነው፡፡ በኀጢአታችን ንስሐ መግባት እየተጠበቀብን ነገር ግን ለፈጸምነው ስህተት ሌላ ምክንያት ስናቀርብ እንሰማለን፡፡ ይህ ነገርም ቅጣታችንን ያበዛው እንደሆነ እንጂ በበደል ከመጠየቅ ነጻ አያደርገንም፡፡ በመጽሐፍ እንዲህ ተብሎ እንደተገለጠው “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል፡፡”(ምሳ.28÷13) የነነዌ ሰዎች የሚያተምሩን አንዱ ነገር ኀጢአት በደልን መታመንን ነው፡፡ ስለሆነም ለበደላችን ምክንያትን የምንደረድር ሰዎች ምን ያህል ከጸጋ እግዚአብሔር እንደተራቆትን ልናስብ ልንጸጸትም ይገባናል፡፡ ንጉሥ ዳዊት ቤርሳቤህን አስነውሮ÷ ኦርዮንን ባስገደለ ጊዜ እግዚአብሔር በነቢዩ በናታን አድሮ ስለኀጢአቱ ሲወቅሰው፡-“ዳዊትም ናታንን፦ እግዚአብሔርን በድያለሁ አለው።” ተብሎ ነው የተጻፈው(2ኛ.ሳሙ12÷13)፡፡ ኃጢአት በደላችንን ብናምን እንደ ቅዱስ ቃሉም በካህናትም ፊት ቀርበን ብንናዘዝ አምላካችን ከኀጢአታችን ሊያነጻን የታመነ ነው፡፡ “በኀጢአታችን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡”ተብሎ እንደ ተጻፈ፡(1ኛ.ዮሐ.1÷8-9) እንግዲህ ከዚህ በመማር እንደ ሰብአ ነነዌና እንደ ዳዊት ኀጢአታችንን በማመንና ንስሐ በመግባት ምሕረት እንድናገኝ አምላካችን ይርዳን፡፡ዳዊት ኀጢአቱን በታመነ ጊዜ “ናታንም ዳዊትን፦ እግዚአብሔር ደግሞ ኀጢአትህን አርቆልሃል አትሞትም” ብሎታል፡፡ “የነነዌ ሰዎችም ከክፉ መንገዳቸው እንተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም፡፡” (2ኛ.ሳሙ12÷13፤ዮና.3÷10)

 

4ኛ ፍጹም የሆነ የጾም የጸሎት ሕይወትን እንማረለን፤ ሰብአ ነነዌ ባለማወቅ ሠርተውት ሊመጣባቸው ካለ መአት ለመዳን፣ ወደ እግዚአብሔርም ለመመለስ የተጠቀሙበት የጾም የጸሎት መንገዳቸው ፍጹም ሊያስተምረን ይገባል፡፡ በትንቢተ ኢዩኤል ላይ ፈጣሪያችን  እግዚአብሔር፥ “በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ።” (ኢዩ.2÷12)ብሎናል፡፡ ስለሆነም በፍጹም ልባችን (ያለ ተከፍሎ ልቡና) ወደ ፈጣሪይችን ተመልሰን ቸርነት ምሕረቱን ደጅ ልንጠና ይገባናል፡፡ የነነዌ ሰዎች ለሦስት ቀንና ለሦስት ሌሊት  በፍጹም ልቡናቸው ተጸጽተው፣ ጹመው ጸልየው  ምሕረትን አግኝተዋል፡፡ እኛ በቁጥር ከዚያ የበለጠውን ጾመን፣ ጸልየን ልመናችን ምላሽ ያላሰጠን ለምንድር ነው? በእርግጥ ጾም ጸሎታችን በፍጹም ልቡና የቀረበ ነው? በትንቢተ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል ቃልተጽፎ እናነባለን፡- “ስለ ምን ጾምን አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን÷ አንተም አላወቅህም? ይላሉ፡፡እነሆ÷ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ÷ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ፡፡ እንሆ÷ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን?ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን?እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን?እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል።”(ኢሳ.58÷3-9)

 

እንግዲህ ከነነዌ ሰዎች ተምረን ጾም ጸሎታቻንን÷ ከቂም፣ ከበቀል፣ ከአመጻና…ይህን ከመሳሰለው የሥጋ ፈቃድ ሁሉ ለይተን በፍጹም ልባችንና በፍጹም ሰውነታችን ወደ እግዚአብሔር በመመለስ÷ ንጹህ መስዋእት አድርገን ልናቀርበው ይገባናል፡፡  ፈጣሪያችን ልኡል እግዚአብሔር ወርሃ ጾሙን የንስሐ የምሕረት ያድርግልን! ለሰብአ ነነዌ የተለመነ ለእኛም ይለመነን! አሜን!!

KidaneMihret

ኪዳነ ምሕረት

የካቲት 15 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ኀይለ ኢየሱስ ቢያ

KidaneMihret

“ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ” 88፥3 በማለት በነቢዩ ቅዱስ ዳዊት አድሮ ራሱ እግዚአብሔር ከመረጣቸው አበው ነቢያት ጻድቃን ቅዱሳንና ሰማዕታት ጋር ቃል ኪዳን እንደ ገባና እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እግዝአብሔር እንደሚጠራ እንደሚያከብር እንደሚቀድስ ቃል ኪዳን እንደሚሰጥ ነግሮናል፡፡ /እንግዲህ እርሱ ራሱ ከጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎት የሚቃወማቸው ማን ነው? ብሏል፡፡ ሮሜ.8፥33

 

ቅዱስ ዳዊትም “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነውብሏል፡፡ መዝ.86፥3 ስለዚህ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የገባው ቃል ኪዳን ከቅዱሳን ቃል ኪዳን ሁሉ ልዩ ነው፡፡

 

ቃል ኪዳን መሐላ የሚለው መዝገበ ቃላዊ ፍች እንደሚከተለው ተገልጿል፡-

ኪዳነ ምሕረት የካቲት 16 ቀን እመቤታችን ከልጇ የምሕረት ቃል ኪዳን /ውል / ስምምነት፣ የተቀበለችበት ዕለት የበዓል ስም ነው፡፡ ኪዳን ማለት ኪዳን፡- ውል፣ መሐላ፣ ቃል ኪዳን፣ የውል ቃል ማለት ነው፡፡ ተካየደ፡- ተዋዋለ፣ ቃል ኪዳን ተጋባ፣ ተማማለ ማለት ነው፡፡ ዘዳ.29፥1፣ ኤር.31፥31-33፣ መዝ.88፥3 በሌላ በኩል ኪዳን፡- የጸሎት ስም ነው፡፡ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት ያስተማራቸው ጸሎት “ኪዳን” ይባላል፡፡

 

በየዓመቱ የካቲት 16 ቀን የምናከብረው በዓል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጎልጎታ በልጇ በመቃብር ላይ ሁና ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ “ኦ ወልድየ ወፍቁርየ እስእለከ በእንተ ዘተሰባእከ እምኔየ ወበማሕፀንየ ዘጸረተከ፤ ልጄ ወዳጃ ሆይ ከሥጋዩ ሥጋ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በቻለችህ ማኅፀኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለመሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ” እያለች ስትጸልይ÷ ጌታ እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ “ሰላም ለኪ ማርያም እምየ፤ እናቴ ማርያም ሰላም ላንቺ ይሁን እንዳደረግልሽ የምትለምኚኝ ምንድን ነው?” አላት፡፡

 

  • ኩሉ ዘጸውአ ስምዬ፤ በስሜ የተማጸነውን

  • ወዘገብረ ተዝካርየ፤ መታሰቢያዬን ያደረገውን

  • ስለስሜ ለችግረኛ የሚራራውን

  • በስሜ ቤተ ክርስቲያን ያነጸውን

  • በስሜ ለቤተ ክርስቲያን ዕጣንና ዘይት መብአ የሰጠውን

  • ከሃይማኖት ፍቅር ጽናት፣ ልጁን በስሜ የጠራውን ሁሉ ማርልኝ ከሞተ ነፍስ አድንልኝ” አለችው፡፡

 

ጌታም “ይህን ሁሉ እንዳደርግልሽ መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበአቡየ ወበመንፈስ ቅዱስ ሕያው” ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላት ዐርጓል፡፡

 

ከዚህ የተነሣ ነው ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው “ዳግመኛም በእናትህ በማርያም ተማፅነናል÷ ይህችውም አንተን በመውለድ እመቤታችንና የባሕርያችን መመኪያ ናት÷ አንተ መታሰቢያሽን ያደረገ÷ ስምሽንም የጠራ ÷የዘላለም ድኅነትን ይድናል ብለሃታልና፡፡” ያለው (ገጽ 242)

 

በዚህ ዕለት የሚታሰብ በተአምረ ማርያም መጽሐፍ….. የተገለጸ ሁለት ተአምር አለ፡፡

  1. ስምዖን የሚባል እንግዳ ተቀባይ ደግ ሰው ነበር፡፡ ሰይጣን ለምቀኝነት አያፍርምና ከዕለታት አንድ ቀን በእንግድነት እቤቱ ገብቶ “ልጅህን አርደህ ካላበላኸኝ÷ ሌላ ምግብ አልበላም” አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ስምዖን ወደ እርሱ የመጣውን “የእግዚአብሔር እንግዳ” ላለማሳዘን አወጣ አወረደ፤ በዚያውም ላይ “አብርሃም ልጁን ሰውቶ ነው፡ የእግዚአብሔር ሰው የተባለው፣” በማለት÷ ልጁን አርዶ ሰጠው፡፡ “በግድ ቅመስልኝ” አለው፡፡ ስምዖን አርዶ የቀቀለውን የልጁን ሥጋ በቀምሰ ጊዜ ተዋሕዶት፤ ቤተሰቦቹን ጎረቤቶቹን መንገደኛውን ሁሉ ይበላ ጀመር፡፡ በዚህም 78 ሰው በልቶ አንድ በቁስል የተመታ ሰው ሊበላው ሲል፡- “በሥላሴ ስም፣ በቅዱስ ሚካኤል ስም፣ በቅዱስ ገብርኤል ስም ውኃ አጠጣኝ” ብሎ ለመነው፤ ዝም አለው፡፡ በመጨረሻም “በድንግል ማርያም ስም” አለው፡፡የእመቤታችንን ስም በሰማ ጊዜ በላኤሰብእ ወደ ልቡናው ተመልሶ “እስኪ ድገመው” አለው፤ “ስለ ድንግል ማርያም ውኃ አጠጣኝ” ብሎ ለመነው፡፡ ያን ጊዜ “ይህችስ እንደምታስምር በልጅነቴ ሰምቻለሁ” ብሎ ጥቂት ውኃ ሰጠው፣ ጉሮሮ እንኳን ሳይርስለት ጨረስህብኝ ብሎ ነጥቆት ሄደ፡፡ “ገበሬው በላኤ ሰብ የምትባል አንተነህ?” አለው፡፡ ያን ጊዜ “ለካስ ሰው ሁሉ አውቆብኛል” ብሎ ዋሻ ገብቶ በመጸጸት በዚያው ሞተ፡፡ ነፍሱን መላእክተ ጽልመት መጥተው ሲወስዷት እመቤታችን “መሐር ሊተ ዛተ ነፍሰ ኦ ወልድየ ዘይትሔሰው ቃልከ፤ ልጄ ይህችን ነፍስ ማርልኝ ቃልህ ይትበላልን” አለችው፡፡ “ሰባ ስምንት ነፍስ ያጠፋ÷ ፈጣሪውን የካደ ይማራልን?” አላት፤ እመቤታችንም “በስሜ የተጠማውን ውኃ አጥጥቶ የለምን?” ብላ አስምራዋለች፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ብርሃን መጥተው ወደ ገነት አስገብተዋታል፡፡

  2. ከክርስቲያን ወገን የሆነ ሀብት አግኝቶ ያጣ አንድ ሰው ነበር፡፡ “ከብሬ በኖርሁበት ሀገር÷ተዋርጄ አልኖርም” ብሎ ጓዙን ጠቅልሎ ሲሄድ፣ ሰይጣን ያዘነ መስሎ÷ ደንጊያውን፡- በምትሐት ወርቅ አስመስሎ÷ “አብን ወልድን መንፈስ ቅዱስን፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታትን፣ መላእክትን ካድልኝና ይህን እሰጥሃለሁ” አለው፡፡ ካደለትና ተቀብሎ ዞር ሲል፤ “ምእመናን የሚመኩባት ድንግል ማርያም `የአምላክ እናት አይደለችም` ብለህ ካድልኝ” አለው፡፡ “እሷንስ አልክድም” አለው፡፡ በደንጊያ ቀጥቅጦ ገደለው፡፡ መላእክተ ጽልመት ነፍሱን እጅ አደረጉ፤ መላእክተ ብርሃንም አብረው ቀረቡ እመቤታችንም ቀርባ፤ “ልጄ ይህችን ነፍስ ማርልኝ” አለችው፡፡ “ከልብኑ ይታመሐር እምየ፤ እናቴ ውሻ ይማራልን” አላት፡፡ “ስምሽን የጠራውን መታሰቢያሽን ያደረገውን እምርልሻለሁ ያልኸው ቃል ይታበላልን” አለችው “ምሬልሻለሁ” አላት፡፡

 

እግዚአብሔር ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ ባለው መሠረት ከቅዱሳን ጋር ያደረጋቸው ቃል ኪዳኖች ብዙዎች ናቸው (መዝ.88፥3)፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የእመቤታችን ኪዳን/አማላጅነት/ ነው፡፡

 

አማላጅነትዋ

እንደሚታወቀው ማማለድ ማለት ስለሌላው መጸለይ፣ መለመን፣ የደረሰውን ችግር እንዲወገድ ማስደረግ፣ ማስማር ማለት ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከእግዚአብሔር በታች ከቅዱሳን ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር በተሰጣት የማማለድ ሥልጣን “ሰአሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኚልን” እያሉ ለሚለምኑአት ሁሉ ከእግዚአብሔር እያማለደችና እየለመነች ምሕረትን እንደምታሰጥ ቀናውንና የተመሰገነውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሁሉ ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር እናትና አገልጋይ በመሆንዋ ከሁሉም ቅዱሳን በበለጠ ለእግዚአብሔር ቅርብ ናትና፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድም ሆነ በሰው ዘንድ ባለሟልነት ወይም ቅርብ መሆን ጉዳይን ያስፈጽማል፡፡

 

ለምሳሌ

  • መልአኩ ቅዱስ ገብርአል በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም ባለሟል በመሆኑ የድኅነትን ምሥጢር አብሣሪ ሆኗል፡፡ ሉቃ.1፥19፣ 1፥26

  • አስቴር የንጉሡ አርጤክስስ ሚስት በመሆኗ በወገኖቿ አይሁድ የታወጀውን የሞት አዋጅ አስለውጣለች፡፡ መጽሐፈ አስቴር.3፥10

  • ነቢዩ ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ባለሟል በመሆኑ ለእስራኤላውያን ምሕረት አሰጠ፡፡ ዘጸ.32፥14 “ይህንን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው ያለዚያ ግን እኔን ከጻፈከው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለው እግዚአብሔርም ራራላቸው፡፡”

  • የቅድስት ድንግል ማርያምም አማላጅነት እንደ ፀሐይ የበራ ሐቅ ነው፡፡ ይህንን እውነት ቅዱስ ያሬድ ሲመሰክር “ወታስተሠርዪ ኀጢአተ ሕዝብኪ ተበውሀ ለኪ እም አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወከመ ትኩኒ ተንከተመ ለውሉደ ሰብእ ለሕይወት ዘለዓለም” ማለት “ለሕዝብሽ ለወገኖችሽ የኃጢአት ይቅርታን ታሰጪ ዘንድ ዘለዓለማዊ ሕይወትንም ለሚወርሱ ሁሉ መሸጋገሪያ ድልድይ ትሆኚ ዘንድ ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ÷ከአንድ አምላክ ሥልጣን አግኝተሻል በማለት አመስግኗታል፡፡” /አንቀጸ ብርሃን ተመልከት/

 

በአባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌው “ሶበሰ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ ፈለገ እሳት ወደይን እም አሰጠመ ኩሎ፤የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት ፤መርገም /ኀጢአት/ ባጠፋን ነበር” ብሏል፡፡

 

በሥርዓተ ቅደሴአችንም

  • ድኅነትን የምንለምንሽ ክብርን የተመላሽ ቅድስት ሆይ ደስ ይበልሽ

  • ሁል ጊዜ ድንግል የምትሆኚ አምላክን የወለድነሽ የክርስቶስ እናት ሆይ ኀጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ልጅሽ ወደ ወዳጅሽ ወደ ላይ ጸሎታችንን አሰርጊ፣

  • በእውነት የጽድቅ ብርሃን የሚሆን አምላካችንን ክርስቶስን የወለድሽልን ንጽሕት ሆይ ደስ ይበልሽ፣

  • ንጽሕት ድንግል ሆይ ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግ ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ጌታችን ለምኚልን፡፡

  • በእውነት ለሰው ወገን አማላጅ የምትሆኝ አምላክን የወለድሽ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡

  • የኀጢአታችንን ሥርየት ይሰጠን በልጅሽ በክርስቶስ ፊት ለምኝልን፣

  • በእውነት ንግሥት የምትሆኝ ንጽሕት ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ

  • የባሕርያችን መመኪያ ሆይ ደስ ይበልሽ

  • አምላካችን አማኑኤልን የወለድሽልን ሆይ ደስ ይበልሽ

  • በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እውነተኛ አስታራቂ ሆነሽ ታስቢን ዘንድ እንለምንሻለን፡፡

  • ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግልን ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሰርይልን ዘንድ” በማለት እንማጸናታለን፡፡

አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው

  • ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ

  • ማዓትን ያይደለ ምሕረትን አሳስቢ

  • ለጻድቃን ያይደለ ለኀጥአን አሳስቢ

  • ለንጹሐን ያይደለ ለተዳደፉት አሶስቢ ብሏል፡፡ ቁ.165-171

 

የእመቤታችን ክብር ከቅዱሳን ክብር ሁሉ የተለየ ነው፤ ይህም እንደምን ነው ቢሉ

  • ለአምላክ እናትነት የተመረጠች ልዩ እናት በመሆኗ ሉቃ.1፥26

  • አምላክ ከሥጋዬ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ከእርሷ በመወለድ

  • ከመለለዷ በፊት በወለደች ጊዜ ከወለደች በኋላ ምን ጊዜም ድንግል በመሆኗ ኢሳ.7፥14

  • በሁለቱም ወገን /በአሳብም በገቢርም/ ድንግል በክልኤ በመሆኗ

  • አማላጅነቷ የወዳጅነት ሳይነሆን የእናትነት በመሆኑ ዮሐ.2፥5

  • ዓለም ይድን ዘንድ የድኅነት ምክንያት አድርጎ አምላክ የመረጣት ስለሆነ የእመቤታችን ክብር /ቃል ኪዳን/ ከቅዱሳን ክብር ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ

“እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወዷታልና ይህች ለዘለዓለም ማረሪያዬ ናት መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ፡፡” በማለት ነግሮናል፡፡ እግዚአብሔር የመረጠውንና የከበረውን መቃወም እንደሣይቻ ሐዋርያውቅ ቅዱስ ጳውሎስም “እንግዲህ እርሱ ራሱ ከጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወመቸው ማን ነው” ብሏል፡፡ ስለዚህ ብዙ ከንቱ አሳቦችን ትተን እንደበላኤሰብ በቃል ኪዳኗ ተጠቅመን ንስሐ ገብተን ቅዲስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀበልን የስሙ ቀዳሽ የመንግሥቱ ወራሽ ለመሆን ያብቃን፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ተራደኢነት አይለየን፡፡

ዋቢ መጻሕፍት

  • ተአምረ ማርያም

  • ስንክሳር

  • መዝገበ ታሪክ

  • ክብረ ቅዱሳን

  • አማርኛ መዝገበ ቃላት

“ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይሰዐር ግብሮ ለጋኔን”

ጥር 27 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ኃይለ ኢየሱስ ቢያ

“የዲያብሎስን  ሥራ ይሽር ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ፡፡” 1ኛ ዮሐን.3፥8

 

ይህንን ኀይለ ቃል የተናገረው  ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ነው፡፡ የተናገረበት ምክንያት፡-

የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ የጌታችን መድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ /ሰው ሆኖ የማዳን ሥራውን/ መፈጸሙን ለመግለጥ  የተናገረው /የጻፈው ኀይለ ቃል ነው፡፡

  • መገለጥ ማለት ፡- ረቂቁ አምላክ በተአቅቦ ርቀቱን ሣይለቅ ውሱን ሥጋን ውሱኑም ሥጋ በተአቅቦ ውስንነቱን ሳይለቅ ረቂቅ መለኮትን የሆነበት በአጭር ቃል የቃል ግብር ለሥጋ የሥጋ ግብር ለቃል የሆነበት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቀዳማዊ ደኃራዊ የሆነው አምላክ ሞት የሚስማማው ሆነ፤ ዘመን የሚቆጠርለት ሥጋ ዘመን የማይቆጠርለት ሆነ፡፡ ሥጋ በማይመረመር ምስጢር የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ ቢያደርግ “ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ” /ራእ.1፥17/ ማለት የቻለበት ምስጢር ነው፡፡ የረቀቀው ገዝፎ የገዘፈው ረቆ፣ ሰማያዊው ምድራዊ  ምድራዊው ሰማያዊ ሆኖ መታየት ማለት ነው፣  ከዓለም ተሰውሮ የነበረው ምስጢር  ግልጥ ሆኖ መታየት ማለት ነው ይህንንም ምሥጢር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጢሞቴዎስ  መልእክቱ “እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የጠገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ ለመላእክት የታየ፣ በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣ በክብር ያረገ /1ጢሞ 3፥16/ በማለት፡፡ ከልደት እስከ ዓቢይ ጾም መጀመሪያ  ያለው ጊዜ  ዘመነ አስተርእዮ /የመገለጥ ዘመን/ የመታየት ወቅት ይባላል

 

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በፍጹም ተዋሕዶ ሰው መሆኑን /ዓለምን ለማዳን መወለዱን የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡

የእግዚአብሔር መገለጥም በ3 ዘመናት ከፍሎ ማየት ይቻላል

  1. በሕገ ልቡና፡- በቃል፣ በራእይ፣ በተአምር እየተገለጠ በማነጋገር አምላክነቱን አስረድቷል፡፡ ዘፍ.2፥8-18፣ ዘፍ.3፥9፣ ዘፍ.12፥1

  2. በሕገ ኦሪትም፡- በቃል በራእይ በተአምር እና ሕግና ሥርዓት በመስጠት አምላክነቱን አስረድቷል/አስተምሯል፡፡

  3. በሕገ ወንጌል፡- ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኖ በመካከላቸው ተገኝቶ መምህር ሆኖ የአምላክ ልጅ አምላክ መሆኑን በግልጽ አስረድቷል፡፡

 

“መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው፡፡ ብሏል” ዮሐ.1፥18

አስቀድመን የገለጥነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ

  • በሥጋ የተገለጠ

  • በመንፈስ የጸደቀ

  • በመላእክት የታየ

  • በአሕዛብ የተሰበከ

  • በዓለም የታመነ

  • በክብር ያረገ በማለት የገለጠው ፤/1ኛ ጢሞ.3፥16/

 

ጌታ ተወልዶ በመጀመሪያ የሠራው ሥርዓት ምሥጢረ ጥምቀትን ነው፡፡ ለምን ተጠመቀ ቢሉ፤

  • የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም መዝ.113፥3-6

  • አምላክነቱን ለመግለጥ /አንድነትና ሦስትነቱን/ ማቴ.3፥17

  • ለእኛ አብነት ለመሆን ማቴ.11፥28-29

  • የዕዳ ደብዳቤአችንን ለመደምሰስ ቆላ.2፥13-15

  • ውኆችን ለመቀደስ

  • በጥምቀት የሚገኘውን ኀይል /የልጅነት ጸጋ/ ለማስረዳት

እኛስ ለምን እንጠመቃለን ብንል

  • ከኀጢአት ለመንጻት ለመቀደስ ነው 1ኛ ቆሮ.6፥11

  • የሥላሴን ልጅነት ለማግኘት ነው ማቴ.28፥19፣ ዮሐ.1፥12፣ ዮሐ.3፥5

  • ለመዳን እንጠመቃለን ማር.16፥16፣ ኤፌ.1፥3-15

 

የእግዚአብሔር ልጅ ለምን ተገለጠ ቢሉ

1.    የሰይጣንን ሥራ ይሽር ዘንድ ነው፡፡

  • ሰይጣን ማለት፡- መስተጻርር፣ መስተቃርን ባለጋራ፣ ጠላት ማለት ነው 1ኛ ጴጥ.5፥8፣ ማቴ.13፥25

  • ጋኔን ማለት፡- ዕሩቅ፣ ውዱቅ የተጣለ ማለት ነው ራእ.12፥9፣ ራእ.20፥2

  • ዲያብሎስ ማለት፡- ዖፍ፣ ሠራሪ፣ ነድ፣ ውዑይ፣ /የተቃጠለ/ ፈታዌ አምላክነ /አምላክነትን የሚሻ/ ማለት ነው፡፡

 

የሰይጣን ሥራው ምን ነበር ቢሉ

በ3ቱ አርዕስተ ኀጦውዕ /የኀጢአት መሠረቶች/ በመጥለፍ /በማታለል/ የሰውን ልጅ ከክብር ማዋረድ ነው፡፡ በዚህም ሥራው የሰው ልጆችን ለ5500 ዘመን በኀልዮ በነቢብ እና በገቢር  ከመርገም በታች  አድርጎ ገዛ ዮሐ.14፥3

 

“እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፣ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፣ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለሞት ፍርሃት በባርነት ይታሠሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡” ብሏል ዕብ.2፥14-16

  • ስለዚህ ጌታ በዘር ይተላለፍ የነበረውን ኀጢአት  እንበለ ዘር በመፀነስ

  • የአዳምንን የሔዋን የዲያቢሎስ አገልጋይነት የሚያሳየውን በዮርዳኖስ የቀበረውን  የዕዳ ደብዳቤ በጥምቀቱ

  • በሲኦል ያኖረውን በስቅለቱ እንደሰውነቱ ረግጦ እንደአምላክነቱ አቅልጦ

  • ሞትን በትንሣኤው አጥፍቶ ነጻነትን  ሰብኮልናል 1ኛ ጴጥ.3፥19

 

ሦስቱ አርእስተ ኀጣውዕ የሚባሉትም፡-

  1. ስስት፡- ያልሰጡትን መሻት /መፈለግ ስግብግብነት ማለት ነው፡፡

  2. ፍቅረ ንዋይ፡- በቃኝ አለ ማለት ነው፡፡

  3. ትዕቢት፡- አምላክ እሆናለሁ ብሎ መሻት መፈለግ ነው፡፡

 

ዲያብሎስ ጌታን በእነዚህ በሦስቱ ኀጣውዕ ፈትኖት ድል ተነስቷል፡፡ ማቴ.4፥2-8 እኛም በስስት በፍቅረ ንዋይ እና በትዕቢት እንዳንጠፋ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ኑሮየ ይበቃኛል ማለትን ልንለምድ ይገባናል፡፡ ወደ ዓለም ያመጣነው አንዳች ነገር የለንም፤ ከእርሱም ልንወስደው የምንችል የለምና፡፡ ምግባችንንና ልብሳችንን ካገኘን ይበቃልና፡፡ ባለጸጋ ሊሆኑ የሚወዱ ግን በጥፋትና በመፍረስ፥ ሰዎችን የሚያሰጥምና በሚያሰንፍ፥ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና፥ በወጥመድም ይወድቃሉ፡፡ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ ይህንም በመመኘት ተሳስተው ሃይማኖታቸውን የለወጡ ብዙዎች ናቸውና፥ ለራሳቸውም ብዙ መቅሠፍትን ሽተዋልና፡፡” 1ኛ.ጢሞ.6፥6-11 በማለት መክሮናል፡፡

 

2.    ለሰው ልጅ ነጻነትን ይሰብክ ዘንድ ነው፡፡ /ይዋጀን ዘንድ ነው/

  • ለድኆች የምሥራችን ይነግራቸው ዘንድ፣ ለተማረኩትም ነጻነትን ይሰብክላቸው ዘንድ

  • ያዘኑትንም ደስ ያሰኛቸው ዘንድ፣ ዕውሮችም ያዩ ዘንድ፣ የተገፉትንም ያድናቸው ዘንድ፣ የታሰሩትንም ይፈታቸው ዘንድ የቈሰሉትንም ይፈውሳቸው ዘንድ

  • የተመረጠችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት ይሰብክ ዘንድ ነው፡፡ሉቃ.4፥18-20፣ ገላ.4፥4

 

3.    እኛ ከእግዚአብሔር እንወለድ ዘንድ ነው፡፡

አምላክ ሰው የሆነው በስሙ አምነን ተጠምቀን የመንግሥተ ሰማያት ዜጋ እንሆን ዘንድ ነው፡፡ ዮሐ.1፥12፣ ማቴ.28፥19፣ ዮሐ.3፥5፣ ማር.10፥16፣ ገላ.3፥26

 

4.    ጽድቅን ያስተምረን ዘንድ ነው፡፡

ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣበት ዋና ዓላማ ሰውን ለማዳን ሲሆን በተጨማሪ፡-

  • ክርቶስ ፍጹም በሆነ መልካም አኗኗሩ፣ ጠፍቶ የነበረውን የእግዚአብሔርን አርዓያና አምሳል /ዘፍ. 1፥26-27/ እንደገና ለመመለስ ለሰዎችም የመልካም ኑሮ አብነት ለመሆን፤

  • እንደመምህርነቱ እውነተኛውን ትምህርትና ዕውቀት ለመስጠት ሐሰት አስተምህሮዎች  አስተሳሰቦችን ለማረምና ለማስተካከል፤

  • እግዚአብሔር ሰውን የሚወድ ሰማያዊ አባት መሆኑን በተግባር ለማሳወቅና ልባችንም በፍቅር እንዲሞላ ለማድረግ፤

  • እንደ መልካም እረኛና ጠባቂ ድሆችንና ችግረኞችን ለመርዳት ነው፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲን ይኼንን ታምናለች፡፡ በመዋዕለ ስብከቱ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ፤ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና፡፡” ብሏል ማቴ.11፥28-29

 

5.    ፍቅርን ያሳየን ዘንድ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ረብ ጥቅም ሳይፈልግ እንዲሁ በከንቱ ወደደን፡፡ ዮሐ.3፥16

  • ፍቅር ሰሐቦ ለወልደ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሆ እስከ ለሞት በማለት ሊቃውንት የተናገሩበት ምክንት ይህ ነው፡፡
  • “እግዚአብሔር ምን ያህል እንደወደደን እነሆ እዩ እኛ ኀጢአተኞች ስንሆን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ እንግዲህ በደሙ  ከጸደቅን ከሚመጣው መከራ በእርሱ እንድናለን፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ጠላቶቹ ስንሆን በልጁ ሞት ይቅር ካለን ከታረቅን በኋላም በልጁ ሕይወት እንድናለን፡፡” ብሏል፡፡ ሮሜ.5፥8-11 ወንድሞቻችን ሆይ እግዚአብሔር ይህን ያህል ከወደደን እኛም እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔርንስ ከቶ ያያሉ ሰው የለም እርስ በርሳችን ከተዋደድን ግን እግዚአብሔር አብሮን ይኖራል፡፡ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል፡፡” ብሏል፡፡ 1ኛ ዮሐ.4፥10-13

 

እንግዲህ በአጠቃላይ እግዚአብሔር ወልድ በሕግም በቃልም በተግባርም ያስተማረን ገብቶን/ ተረድተን በሕይወታችን ዘመን ሁሉ እርሱ ባሳየን ባስተማረን ኖረን የስሙ ቀዳሽ የመንግሥቱ ወራሸ ለመሆን ያብቃን፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱሳን አማላጅነት አይለየን፡፡

 

kiduse entonse

እንጦንዮስ አበ መነኰሳት

ጥር  22 ቀን 2005 ዓ.ም.

  • ምንጭ፡- የበረሃው ኮከብ ቅዱስ እንጦንዮስ መጽሐፍ

 

ጨለማ በዋጠው በግብፅ በረሃ ውስጥ ለብዙዎች አርዓያ በሆነ የእምነት ገድል የቅድስናን ብርሃን በማብራቱ የበረሃው ኮከብ ብለው ብዙዎች ይጠሩታል፡፡

 

kiduse entonseብፁዐዊ ቅዱስ እንጦንስ በምንኩስና ሕይወት ለመኖር ከጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተማረው አብነታዊ ትምህርት (ማቴ.4፥1-10) ከዚህ ዓለም ተድላና ደስታ በመራቅ ከሰዎች ሁሉ ተለይቶ  ፍጹም መንፈሳዊ ተጋድሎን በመጋደል በተወለደ በ106 ዓመቱ ጥር 22 ቀን በ356 ዓ.ም. ከዚች ዓለም በሥጋ ተለይቷል፡፡ “ክቡር ሞቱ ለፃድቅ በቅድመ እግዚአብሔር” “የፃድቅ ሰው ሞቱ በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው” በማለት ክቡር ዳዊት እንደተናገረው፣ “ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን የልደታቸውን ጊዜ፣ የተጋድሏቸውን ሁናቴ፣ ቃል ኪዳን የተቀበሉባቸውንና ያረፉባቸውን ዕለታት በክብር ታስባለች፡፡ ይህም በቅዱስ መጽሐፋችን “የፃድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው”(ምሳ.10÷7)፡፡ በመሆኑም “ስለ ፅድቅ የሚሰደዱ ብጹአን ናቸው ÷ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” (ማቴ.5÷8) በሚለው በጌታችን ትምህርት የዚችን ዓለም ጣዕም ንቆ በምናኔ በመኖር ለመነኮሳት አብነት የሚሆናቸውን የቅዱስ እንጦንስን ዜና ሕይወት አቅርበናል፡፡ለመሆኑ ቅዱስ እንጦንስ ማን ነው? አስተዳደጉና የፈጸማቸው አገልግሎቶቹ ምን ይመስላሉ?

 

ልጅነት

እንጦንዮስ/እንጦንስ/ ትውልዱ ግብጻዊ ሲሆን ቤተሰቦቹም መልካሞችና ባለጸጎች ነበሩ፡፡ እነርሱም በሕፃንነት ኑሮው ከቤቱና ከወላጆቹ በስተቀር ምንም አላወቀም፡፡ እያደገና ዕድሜው እየጨመረ ሲሄድ ትምህርት ቤት አልገባም ነበር፡፡ ይህም ከሌሎች ልጆች ጋር ጓደኝነት ባለመፈለጉ ነበር፡፡ የእርሱ ፍላጎት በቅዱስ መጽሐፍ ተጠቅሶ እንደሚገኘው እንደ ያዕቆብ በብቸኝነትና በጭምትነት በቤቱ በመቀመጥ ቀላል ሕይወትን መምራት ነበር፡፡ ዘፍ.25፥27 በእርግጥ ከወላጆቹ ጋር ቤተ ክርስቲያን እየሄደ ያስቀድስ ነበር፡፡ በዚህም ከአንድ ልጅ ወይም ከአንድ ወጣት የሚታየው የመሰልቸትና የጥላቻ መንፈስ በጭራሽ አልታየበትም፡፡ ለወላጆቹ በመታዘዝ የሚሰጡትን ትምህርቶችና የሚነበቡትን ቅዱሳት መጻሕፍት በጥሞና ይከታተል ነበር፡፡ ከነዚህም የሚቀስመውን ጥቅም በልቡ በማስተዋል አኖረ፡፡ በሌላም በኩል በልጅነቱ ወራት ምንም እንኳ ያለ አንዳች ችግር ቢኖርም ወላጆቹን ለቅንጦትና ለድሎት ለምግብም ሲል አያስጨንቃቸውም ነበር፡፡ ይህን በመሰሉት ሁሉ አይደሰትም ነበር፡፡ በፊቱ በሚቀርብለት ብቻ ይረካ ነበር፡፡ ተጨማሪም አይጠይቅም፡፡

 

መጠራት

ወላጆቹ ከሞቱ በኂላ እንጦንዮስ ገና ልጅ ከነበረች አንዲት እኅቱ ጋር ብቻኛ ሆነ፡፡ በዚህ ወቅት ዕድሜው ከ18 እስከ 20 ዓመት ገደማ ነበር፡፡ ቤቱንና እኅቱንም ይጠብቅ ጀመር፡፡ እነርሱን ካጣ ከስድስት ወር በኋላ እንደ ልማዱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ በመንገድ በኅሊናው ያስብ ጀመር፡፡

 

ሐዋርያት ሁሉን ትተው ጌታን እንደተከተሉት (ማቴ.10፣ 20፣19፣ 27)፤ በግብረ ሐዋርያት ሕዝቡ ያላችውን ሁሉ ሸጠው ለድሆች ይከፋፈል ዘንድ በሐዋርያት እግር ሥር ስለማኖራቸው (ሐዋ.4፡35)፤ ይህን ለመሳሰሉ ሥራዎች በሰማያት እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ እንዳላቸው (ኤፌ.1፡18 ቆላ.1፡15) እኒህን አሳቦች በኅሊናው እያወጣና እያወረደ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ፡፡ በዚያም ወቅት ወንጌል ይነበብ ነበር፤ ሲያዳምጥ ጌታ በሀብታሙ ሰው የተናገረውን የሚጠቅሰው ምዕራፍ ተነበበ፡፡

 

“ልትጸድቅ ብትወድድ ሂደህ ያለህን ሁሉ ሽጥና ለድሆች ስጥ፡፡ መጥተህም ተከተለኝ፡፡ በሰማያት መዝገብ ታከማቻለህ፡፡” ማቴ.19፡21 ፡፡ እግዚአብሔር ቀድሞ ስለ ቅዱሳን እንዲያስብ እንዳደረገውና እዚህም የተነበበው በቀጥታ ለእርሱ እንደተነገረ ስለተሰማው እንጦንዮስ በቀጥታ ከቤተ ክርስቲያኑ በመውጣት ከዘመዶቹ የወረሰውን 300 ሄክታር ወይም 12 ጋሻ መሬት ለድሆች አከፋፈለ፡፡ መሬቱ ለምና ለዐይንም ያማረ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለእርሱም ሆነ ለእኅቱ እንቅፋት እንዲሆንባቸው አልፈለገም፡፡ የተረፈውን ሁሉን ተንቀሳቃሽ ሀብቱን ሸጠ፡፡ አብዛኛውን ለድሃ ሰጥቶ ጥቂቱን ለእኅቱ አስቀመጠው፡፡

 

እንጦንዮስ በሌላ ቀን እንደገና ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ሳለ ጌታ በወንጌል የተናገረውን ሲነበብ አደመጠ፡፡ “ለነገ አትጨነቁ” ይል ነበር ጥቅሱ ማቴ.6፡34፡፡ ይህንንም ሰምቶ ሳይዘገይ ወደ ቤቱ በመመለስ የተረፈውን ሁሉ ለድሆች ያከፋፍል ጀመር፡፡ እኅቱን ግን የታወቁና የታመኑ ወደሆኑ ደናግል ማኅበር ወሰዳት፡፡ በዚያም ታድግ ዘንድ ለደናግል ትቷት ተመለሰ፡፡ ከዚያ በኋላ ብቻውን በመሆኑ ንቁ ሆኖ ራሱን በመካድ በመኖሪያ ቤቱ አጠገብ ጊዜውን ለብሕትውና ሕይወት ሰጠው፡፡

 

ትሕትና

እንጦንዮስ ራሱን ዝቅ በማድረግና በነፍስ ትሕትና የጸና ነበር፡፡ ምንም እንኳ ታላቅና ዝነኛ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያንን ልዑካንና ጸሐፍትን ከእርሱ ይልቅ እንዲከበሩ ይሻ ነበር፡፡ በጳጳሳትና በካህናት ፊት እራሱን ዝቅ አድርጎ እጅ ሲነሣ አሳፋሪ አያደርገውም፡፡ ዲያቆን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ጠቃሚ ነጥብን ካገኘም ላገኘው ዕውቀት ሳያመሰግን አያልፍም፡፡

 

በገጽታው ሊገለጽ የማይቻልና ታላቅ የሆነ ብሩህ ገጽ ይነበብበታል፡፡ በመነኮሳት ጉባኤ ተቀምጦ ሳለ ቀድሞ የማይተዋወቀውን ሰው ሊያነጋግረው ከፈለገ ማንም ሳያመለክተው በዓይኖቹ እንደተሳበ ሁሉ ሌሎቹን አልፎ በቀጥታ ወደ እንጦንዮስ ይሄዳል፡፡ ከሌሎቹ ልዩ አድርጎ የሚያሳውቀው ቁመናው ምስሉ ሳይሆን የረጋ ባሕርይውና የነፍሱ ንጽሕና ነበር፡፡ ነፍሱ የማትነዋወጽ በመሆንዋ አፍአዊ ገጽታውም የረጋ ነበር፡፡ በመጽሐፍ  “ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል፡፡ በልብ ኀዘን ግን ነፍስ ትሰበራለች፡፡”ተብሎ እንደተነገረው (ምሳ.15፥13)፡፡ ለምሳሌ ያዕቆብ አጎቱ ደባ ተንኮል እንዳሰበበት ባወቀ ጊዜ ለሚስቶቹ እንዲህ ብሏቸው ነበር የአባታችሁ ፊት ከእኔ ጋር እንደዱሮ እንዳልሆነ አያለሁ፡፡ ዘፍ.31፥5፡፡ ነቢዩ ሳሙኤል ዳዊትን ንጉሥ አድርጎ ይቀባው ዘንድ በተላከ ጊዜ ደስታን የሚያንጸባርቁ ዓይኖቹንና እንደ ወተት የነጡ ጥርሶቹን አይቶ አወቀው፡፡ 1ሳሙ.16፥10፡፡ እንጦንዮስም እንዲሁ ይታወቅ ነበር፡፡ አይነዋወጽም፡፡ ነፍሱ እርጋታ ነበራትና፡፡ አያዝንም፡፡ አዕምሮው ደስታን የተሞላ ነበር፡፡

 

ቅዱስ እንጦንዮስ ፍቅረ ነዋይ ላለቀቀው መነኩሴ ያስተማረው ትምህርት

ዓለመን ንቆ ገንዘብ ስለመውደድ ከመነኮሰ በኋላ ለድሆች ካከፋፈለ በኋላ ለራሱ ጥቂት ያስቀረ አንድ ወንድም ወደ ባሕታዊው ወደ እንጦንዮስ መጣ፡፡ እንጦንዮስም ይህን ካወቀ በኋላ እንዲህ አለው፡፡ “ መነኩሴ ለመሆን ከፈለግህ ወደ መንደር ሂድና ጥቂት ሥጋ ገዝተህ ራቁትህን በሰውነትህ ላይ ተሸክመህ ተመለስና ወደእኔ ና” አለው፡፡ያም ወንድም ይህን ባደረገ ጊዜ ወፎችና ውሾች በሰውነቱ እያንዣበቡ ይታገሉት ጀመር፡፡ በደረሰም ጊዜ እንጦንዮስ እንዳዘዘው ማድረጉን ጠየቀው፡፡ እርሱም የቆሰለውን ሰውነቱን ባሳየው ጊዜ እንጦንዮስ እንዲህ አለው፡-“ዓለምን ከናቁ በኋላ ገንዘብ የሚመኙትም እንደዚሁ በአጋንንት ይገደላሉ፡፡” አለው፡፡

 

ቅዱስ እንጦንስ ስለ ዕረፍቱ በቀደ መዛሙርቱ ፊት የተናገረው የመጨረሻ ንግግር

የአባቶቼን መንገድ እሄዳለሁ

እንደልማዱ መነኮሳትን ይጎበኝ ዘንድ በተራራው ውጭ ሳለ በጌታ ቸርነት አስቀድሞ ስለ ሞቱ ስላወቀ ለወንድሞች እንዲህ ሲል ተናገራቸው፡፡ “ይህ ከናንተ ጋር የማደርገው የመጨረሻው ግንኙነት ነው፡፡ በዚህም ሕይወት ዳግመኛ እንተያይ እንደሆነ እንጃ እጠራጠራለሁ፡፡ ዕድሜዬ አንድ መቶ አምስት ዓመት ገደማ ሆኗልና አሁን እኔ የምሞትበት ጊዜ ነው፡፡” ይህን በሰሙ ጊዜ ሽማግሌውን ሰው አቅፈው እየሳሙ ያለቅሱ ጀመር፡፡ እርሱ ግን ከውጭ ከተማ እንደሚለይ ሁሉ በደስታ ያወጋቸው ነበር፡፡ በጥብቅም መከራቸው፡፡ “ከጥረታችሁ ግዴለሽ አትሁኑ፡፡ በብሕትውና ሕይወት ፍጹም ተስፋ አትቁረጡ፡፡ ዕለት ዕለት እንደምትሞቱ ሆናችሁ ኑሩ፡፡ አስቀድሜ እንደተናገርኩት ነፍስን ከርኩስ አሳቦች ለመጠበቅ በሥራ ትጉ፡፡ ቅዱሳንን ምሰሉ፡፡ ቅድስና የሌለውን የስንፍና ትምህርታቸውን ታውቃላችሁና ወደ መለጣውያን (መናፍቃን) አትቅረቡ ኑፋቄያቸው ለማንም ግልጽ ነውና፡፡

 

በመጽሐፈ መነኮሳት (ፊልክስዮስ) መቅድም ላይ ስለ ቅዱስ እንጦንስ ከተፃፈው የሚከተለው ይገኛል፡-እንጦንዮስ (እንጦንስ) አባቱ ባለጸጋ ነበር፡፡ አገሩም ጽኢድ ዘአምፈለገ አቅብጣ ናት፡፡ …በሕጻንነቱ ከትምህርት ቤት ሄደ፡፡ ተምሮ ሲመለስ አባቱ “ሕግ ግባ” አለው፡፡ እርሱ ግን “አይሆንም” አለ፡፡ምነው ቢሉ ፈቃዱ እንደ ቀደሙ ሰዎች እንደ ኤልያስ፤ እንደ ኋላ ሰዎች እንደ ዮሐንስ ንጽሕ ጠብቆ፣ ከሴት ርቆ በድንግልና መኖር ነውና፤ ግድ አለው፡፡ “ግድማ ካልከኝ …ፍቀድልኝና ለእግዚአብሔር አመልክቼ ልምጣ እንጂ” አለ፡፡ “ደግ አመልክተህ ና” አለው፡፡ሄዶ ባቅራቢያው ካለ ዋሻ ገባ፡፡ ወዲያው አባትህ ታመመ አሉት፡፡ ቢሄድ አርፎ አገኘው፡፡ ገንዘቡን ሦስት ነገር አስቦ አስቀድሞ ይመጸውታል፡፡ መጀመሪያ ያባቴ በድኑ ከመቃብር ሳይከተት መብሉ በከርሰ ርሁባን፤ መጠጡ በጉርኤ ጽሙአን፤ ልብሱ በዘባነ ዕሩቃን ይከተት ብሎ፡፡ ሁለተኛው ወኢይወርድ ምስሌሁ ኩሉ ክብረ ቤቱ /ሀብቱ ንብረቱም ሁሉ አብሮ መቃብር አይወርድም/ ያለውን የነቢዩን ቃል ያውቃልና፤ ሦስተኛ የሚመንን ነውና ልብ እንዳይቀረው፡፡ ሲመጸውትም አየቴ ኀይልከ፤ አይቴ አእምሮትከ አይቴ ፍጥነትከ /ኀይልህ የት አለ እውቀትህስ የት አለ ፍጥነትህስ የት አለ/ እያለ መጽውቶታል፡፡ መጽውቶ አባቱን አስቀብሮ ሲያበቃ ቅዳሴ ለመስማት ከቤተክርስቲያን ገብቶ ቆመ፡፡ ቄሱ ወንጌል ብሎ ወጥቶ ሲያነብ እመሰ ፈቀድከ ትኩን ፍጹመ ሲጥ ኩሉ ንዋይከ ወሀብ ለነዳያነ ወነዓ ትልወኒ ያለውን ቃል ሰማ፡፡ ይህ አዋጅ የተነገረ ለኔ አይደለምን? ብሎ እኅት ነበረችው ከደብረ ደናግል አስጠግቶ ሂዶ ፊት ከነበረባት ዋሻ ገብቶ ተቀመጠ፡፡

 

ከዕለታት አንድ ቀን ወለተ አረሚ ሠናይተ ላህይ ይላታል ከደንገጡሮቿ ጋር በቀትር ጊዜ መጥታ ከዛፉ እግር ከውኃው ዳር አረፈች፡፡ ፊት እሷን አስጠጓት፤ ኋላ እርስበሳቸው ይተጣጠቡ ጀመር፡፡ እሱም እርቃናቸውን እንዳያይ ዓይነ ሥጋውን ወደ ምድር ዓይነ ነፍሱን ወደ ሰማይ አድርጎ ሲጸልይ ቆየ፡፡ ያበቃሉ ቢል የማያበቁለት ሆነ፡፡ ኋላ ደግሞ ቆይተው ነገረ ኀፊር እያነሱ ይጨዋወቱ ጀመር፡፡ ምነው እንግዲህማ አይበቃችሁም? አትሄዱም? አላቸው፡፡ ኦ እንጦኒ! ኦ እንጦኒ!፤ ለእመ ኮንከ መነኮሰ ሑር ኀበ ገዳም እንጦኒ ሆይ መነኩሴ እንደሆንክ ከዚህ ምን አስቀመጠህ ከበረሃ አትሄድም ነበርን?/ አለችው፡፡ ከዚያ አስቀድሞ መነኩሴ አልነበረ መነኮስ ማለት ከምን አምጥታ ተናገረች? ቢሉ ጌት ለአበው ትምህርት የሚሆነውን ነገር በማናቸውም ባልበቃ ሰው አድሮ መናገር ልማዱ ነው፡፡ አንድም እሱ ከመነኩሴ ፊት እንዲህ ያለ ኀፊር ትናገሪያለችን? አላት፡፡ ከሱ ሰምታ ኦ እንጦኒ ኦ እንጦኑ እመሰ ኮንከ መነኮሰ ሑር ሐበ ገዳም አለችው፡፡

 

እንጦኒ ኦ እንጦኒ እመሰ ኮንከ መነኮሰ ሑር ሐበ ገዳም እያለ ራሱን እየገሰጸ ፊቱን እየሰፋ ጽሕሙን እየነጨ ከዚያ ተነሥቶ አናብስት፤ አናምርት፤ አካይስት፤ አቃርብት ካሉበት ነቅዐ ማይ፤ ልምላሜ ዕፅ ከሌለበት ድሩክ ለተአቅቦ ይላል ዘር ተክል ከማይገኝበት ገዳመ አትፊር ሄደ፡፡ የዚህ መንገዱ ፍለጋ የለውም፡፡ አሸዋ ላሸዋ ነው፡፡ ነጋድያን ሲጓዙ የወደቀውን ያህያና የግመል ፋንድያ እያዩ በዚያ ምልክት ይሄዳሉ፡፡ በረሃነቱም ጽኑ ነው፡፡ ከሐሩሩ ጽናት የተነሣ በቀትር ጊዜ ከደንጊያ ላይ ተልባ ቢያሰጡ ይቆላል፡፡ እሱም ከዚያ ሄዶ ሲጋደል አጋንንት ጾር አነሱበት፡፡ ኦ ሕጹጸ መዋዕል እፎ ደፈርከ ዝየ፡፡ /በእድሜ ሕፃን የሆንክ ከዚህ እንደምን ደፍረህ መጣህ?/ አዳም ከወጣበት ገነት እንጂ እገባ ብሎ ነው፡፡ ብለው ዘበቱበት፤ እሱም በትሕትና ይዋጋቸዋል፡፡ መሆንማ ይሆን ብላችሁ ነውን? እናንተ ብዙ አኔ አንድ ብቻዬን፤ እናንተ ረቂቃን እኔ ግዙፍ፡፡ እናንተ ኀያላን እኔ ደካማ በኀይለ ክርስቶስ ብችላችሁ ነው እንጂ ያለዚያስ አልችላችሁም እያለ በትሕትና ሲዋጋቸው ኖረ፡፡

 

ከዕለታት ባንድ ቀን ይኸን ፆር አልቻልሁትም ልሂድ እንጂ ብሎ ሲያስብ አደረ፡፡ ማለዳ በትረ ሆሣዕና ነበረችው ያችን ይዞ ከደጃፉ ላይ ቆመ፡፡ እንዳይቀርም ፆሩ ትዝ እያለው እንዳይሄድም በዓቱ እየናፈቀው አንድ እግሩን ከውስጥ፤ አንድ እግሩን ከአፍአ አድርጎ ሲያወጣ ሲያወርድ መልአኩ የሰሌን ቆብ ደፍቶ፤ የሰሌን መቋረፊያ ለብሶ፤ የሰሌን መታጠቂያ ታጥቆ ብትን ሰሌን ይዞ መጣ፡፡ ምን ሊያደርግ ይሆን? ሲል ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ቆመ፡፡ ወዲያው ጸሎተ ወንጌልን፤ ነአኩቶን፤ ተሠሀለኒን፤ ደግሞ መጀመሪያ ለሥላሴ እጅ ነሳ፡፡ ከዚያ በኋላ አንድ አቡነ ዘበሰማያት ሠላሳ ስድስት ሰጊድ አድርሶ በመጨረሻ አንድ ጊዜ እጅ ነሥቶ ተቀመጠ፡፡ ወዲያው ያን ብትን ሰሌን አቅርቦ ይታታ ጀመር፡፡ እንጦንዮስም እንግዲህማ የዚህን ፍጻሜ ሳላይ እሄዳለሁን? ብሎ ተቀምጦ ይመለከተው ጀመር፡፡ ሠለስት ሲሆን ደግሞ ተነሥቶ አቡነ ዘበሰማያቱንም ሰጊዱንም ያንኑ ያህል አደረሰው፡፡ የቀሩትንም የሰዓቱንም የሠርኩንም እንደዚሁ አድርጎ አሳየው፡፡ በሠርክ ኦ እንጦኒ ከመ ከመዝ ግበር ወለእመገበርከ ዘንቱ ትድኀን እምጸብአ አጋንንት አለው /እንጦኒ ሆይ እንደዚህ እንደዚህ ሥራ፤ ይህንን ከሠራህ ከአጋንንት ጠብ ትድናለህ/፡፡ ማለት ነው፡፡ የንዋሙን የመንፈቀ ሌሊቱን ግን እርሱ ጨምሮታል፡፡ ንዋም ጌታ የጸለየበት፤ ቀትር የተሰቀለበት፤ ሰዓት ነፍሱን ከሥጋው የለየበት፤ ሰርክ መቃብር የወረደበት ነውና ይህን ሁሉ አንድ አድርጎ ዳዊት ሰብአ ለዕለትየ እሴብሐከ ብሏል፡፡ /መዝ.118፥164/

 

ሠላሳ ዓመት ሲሞላው ጌታ በዕለተ ዓርብ የለበሰውን ልብስ አልብሶታል፡፡ ማየት ከመልአክ፤ መቀበል ከአምላክ እንዲሉ ይህም ምሳሌ ነው፡፡ ቆብ የአክሊለ ሦክ፤ ቀሚሱ የከለሜዳ፤ ቅናቱ የሀብል፤ ሥጋ ማርያም የሥጋ ማርያም፤ አስኬማ የሰውነት ወተመሰለነ በአስኬማሁ እንዲል፤እርሱም ይህን ተቀብሎ በዚህ ዓለም እኔ ብቻ ነኝን ሌላም አለ? ብሎ ወደ እግዚአብሔር አመለከተ፡፡ ጌታም አለ እንጂ አንድ ጊዜ ተራምዶ ሁለተኛውን ሳይደግም የሚሠራውን ሥራ ዓለሙ ሁሉ ቢሰበሰብ የማይሠራው፡፡ በጸሎቱ ዝናም የሚያዘንም ፀሐይ የሚያወጣ፤ እንደዚህ ያለ ወዳጅ አለኝ አለው፡፡ ይኸን ሰው ለማየት ልሂድን ልቅር? ቢለው ሂድ አለው፡፡ መልአኩ እየመራ አደረሰው፡፡ ጳውሎስ /ጳውሊ/ ከበዓቱ ወጥቶ ፀሐይ ሲሞቅ ነበር፡፡ ሲመጣ አይቶ ከበዓቱ ገብቶ ወወደየ ማእጾ ውስተ አፈ በዓቱ /ከበዓቱ አፍ ውስጥ መዝጊያ ጨመረ/ ይላል ዘጋበት፡፡ ከደጃፉ ቆሞ አውሎግሶን አውሎግሶን አለ፡፡ ስለ እግዚአብሔር ብለህ ክፈትልኝ ማለት ነው፡፡ ሰው እንደሆንክ ግባ ብሎ ከፈተለት፡፡ ገብቶ ማን ይሉሃል? አለው ስሜን ሳታውቅ እንደምንም መጣህ? አለው፡፡ እንጦንዮስም ፍጹም ነውና ቢጸልይ ወዲያው ተገልጾለት፤ ጎድጎድኩ ወተርህወ ሊተ ሀሰስኩ ወረከብኩ ጳውሎስ ገዳማዊ አለው፡፡

 

ጳውሎስ/ጳውሊ/ ትባላለህ ቢለው አደነቀ፡፡ ተጨዋውተው ሲያበቁ ባጠገቡ ለብቻው በዓት ሰጠው፡፡ እንጦንዮስም ከዚያ ሆኖ ጸሎቱን ሲያደርግ ዋለ፡፡ ወትሮ ለጳውሊ መንፈቀ /ግማሽ/ ኅብስት ይወርድለት የነበረ ማታ ምሉዕ ኅብስት ወረደለት፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር መምጣቱን ያን ጊዜ አወቀው፡፡ ወዲያው ያን ኅብስት ከሁለት ገምሶ እኩሌተውን ለራሱ አስቀርቶ እኩሌታውን ሰጠው፡፡ ያን ተመግበው ሌት ሁሉም በየሥራቸው ክብራቸው ተገልጾ ሲተያዩ አድረዋል፡፡ ጳውሎስ አሥር ጣቶቹን እንደ ፋና ሆነው እያበሩለት አራቱን ወንጌል ሲያደርስ እንጦንዮስም እንደ አምደ ብርሃን ተተክሎ ሲያበራ ተያይተዋል፡፡

 

በዚያች ሌሊት ከዚያ ቦታ ጨለማ ጠፍቶ አድሯል፡፡ በነጋው ሠለስት እላፊ ሲሆን ጸሎታቸውን አድርሰው ሲያበቁ ተገናኝተው ሲጨዋወቱ፤ እንጦንዮስ ያረገውን ቆብ አይቶ፤ ይህማ ከማን አገኘኸው? አለው፡፡ እርሱ ባለቤቱ ስጠኝ አለ፡፡ እርሱም የጌታን ቸርነት ያደንቅ ጀመር፡፡ እንጦንዮስም እስኪ በኔ ብቻ የሚቀር እንደሆነ ለሌላም የሚያልፍ እንደሆነ አመልክትልኝ አለው፡፡ አመለከተ፡፡ ወዲያው ተገለጸለት፡፡ ወአክሞሰሰ ይላል፡፡ ደስ አለው፡፡ ምን አየህ? ቢለው ጽዕድዋን አርጋብ /ነጫጭ ርግቦች/ በጠፈር መልተው አንተ እየመራሀቸው ተከትለውህ ሲሄዱ አየሁ አለው፡፡ ምንኑው ቢለው? እሊህማ በዚህ በቆቡ የምትወልዳቸው ንጹሐን ጻድቃን ልጆችህ ናቸው አለው፡፡  ሁለተኛ አመልክትልኝ አለው፡፡ አመለከተ ወደመነገጹ ይላል፡፡ አዘነ ምነው ቢሉ በክንፋቸው ጥቁር ተቀላቅሎባቸው አየሁ አለው፡፡ ምንድንናቸው ቢለው ጽድቅና ኀጢአት እየቀላቀሉ የሚሠሩ ልጆችህ ናቸው አለው፡፡ ሦስተኛ አመልክትልኝ አለው፡፡ አመለከተ ገአረ ወበከየ ይላል፡፡ ቃሉን ከፍ አድርጎ ጮኸ፡፡ ምነው አለው አርጋብስ አርጋብ ናቸው አለው፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ ዘመን የሚነሡቱ እንደ ቁራ ጠቁረው አየሁዋቸው አለ፡፡ ምንድናቸው? ቢለው ሀሳሲያነ ሢመት /ሹመት ፈላጊዎች/፤ መፍቀሪያነ ንዋይ /ገንዘብ የሚወዱ/ እለ ይሠርኡ በነግህ ማዕደ ምስለ መኳንንት /ከመኳንንት ጋር በጥዋት ማዕድ የሚቀመጡ/ ይላቸዋል፡፡ በፍጻሜ ዘመን የሚነሡ ኀጥአን ልጆችህ ናቸው፡፡ አለው፡፡ ያለ ንስሓ ባይጠራቸው እስኪ አመልክትልኝ አለው፡፡ አመለከተ፡፡ የዚህ ምላሽ አልመጣለትም ይላሉ፡፡

 

ከዚህ በኋላ ጳውሊ እንግዲህ ይህን ከራስህ ያደረግኸውን ለኔ ስጠኝ ላንተ ሌላ ሠርተህ አድርግ አለው፡፡ ይህንንስ እንዳልሰጥህ ከባለቤቱ ተቀብዬዋለሁ፡፡ ነገር ግን ሥራውን ለምጄዋለሁ ሌላ ሠርቼ ላምጣልህ አለው፡፡ እንዲያስ አትዘግይ ቶሎ ሠርተህ አምጣልኝ አለው፡፡ ጊዜው እንደደረሰ አውቆታልና ይላሉ፡፡ እንጦንስም ሠርቶ ይዞ ሲመጣ ጳውሊ አርፎ ነፍሱን መላእክተ ብርሃን ይዘዋት ሲያርጉ አየ፡፡ ማነው ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ያ ሰው አርፏልና ሂደህ ቅበረው አሉት ይህንሳ የያዝኩትን ቆብ ልተወውን? አላቸው፡፡ አትተው አድርግለት ብለውታል፡፡ ከምንኩስና አስቀድሞ የሠሩትን ሥራ ከንቱ እንዳይደለ ለማጠየቅ ነው፡፡

 

ቢሄድ መጽሐፉን ታቅፎ፤ አጽፉን ተጎናጽፎ፤ ከበዓቱ አርፎ፤ አገኘው፡፡ ከራስጌው ቆሞ ሲያለቅስ ሁለት አናብስት መጡ፡፡ የመቃብሩን ነገር እንደምን ላድርግ ነኝ አያለ ሲጨነቅ በእጃቸው እንደመጥቀስ አድርገው አሳዩት፡፡ ልኩን ለክቶ ሰጣቸው፡፡ ቆፈሩለት እሱን ቀብሮ እንግዲህ ከዚህ እኖራለሁ ብሎ አሰበ፡፡ ጌታ ግን ዛሬ በሱ ቦታ ላይ ሌላ ሰው አላየበትምና አይሆንልህም ሂድ አለው፡፡ አጽፉንና መጽሐፉን ይዞ ሂዶ እስክንደርያ ሲደርስ ሊቀ ጳጳሱ አትናቴዎስ ወዴት ሄደህ ነበር? አለው፡፡ እንዲህ ያለ ሰው ልጠይቅ ሄጄ ነበር፡፡ አርፎ አግኝቼ ቀብሬው መጣሁ፡፡ አለ፡፡ ልሄድና ከዚያ ልኑር? አለው አይሆንልህም አትሂድ እኔም አስቤ ነበር፡፡ የማይሆንልኝ ሆኖ መጣሁ እንጂ አለው፡፡ ባይሆን ለበረከት ያህል አጽፊቱን ጥለህልኝ ሂድ ብሎ ትቶለት ሄደ፡፡ መዓርግ ሲሰጥ ሥጋውን ደሙን ሲለውጥ በውስጥ ያቺን ይለብስ ነበር፡፡

 

ከዚያ በኋላ በዚህ ቆብ እንጦንዮስ መቃርስን፤ መቃርስ ጳኩሚስን፤ ጳኩሚስ ጳላሞንን፤ ጳላሞን ቴዎድሮስ ሮማዊውን ቴዎድሮስ ሮማዊ አቡነ አረጋዊንና አባ ዳንኤልን ይወልዳል፡፡ አባ ዳንኤል አቡነ አውስጣቴዎስ፤ አቡነ አረጋዊ እስከ አቡነ ተክለሃይማኖት ያሉትን ወልደዋል፡፡ ከዚህ በኋላ መነኮሳቱ እንደ ሳር እንደ ቅጠል በዝተው ተነሥተዋል፡፡ ይሩማሊስ፤ ጳላድዮስ የሚባሉ ሁለት ሊቃውንት መነኮሳት ከግብፅ ተነሥተው አገር ላገር እየዞሩ የአበውን ዜና በሕይወት ያሉትን ከቃላቸው የሞቱትን ከአርድአቶቻቸው እየጠየቁ ቃለ አበው፣ ዜና አበው እያሉ ጽፈዋል፡፡

አምላካችን ከቅዱስ እንጦንስ በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡

“ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ፡፡”

ጥር 20 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ሰሎሞን መኩሪያ

ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ቁ.6

በረከቱ ይደርብንና ይህንን ቃል የተናገረ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወዳጅ የሆነው ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በብሉይ ዘመን በቅዱስ ዳዊት ሕይወት የተከወነውን በምስጢር ስቦ አምጥቶ የሰማዕታትን ክብር አጎልቶ ተናግሮበታል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትን እግዚአብሔር አምላክ ለእስራኤል አነገሠው፡፡ በዙሪያው የነበሩ ኤሎፍላዊያንን አጥፍቶ ደብረ ጽዮንን /መናገሻ ከተማውን/ አቅንቶ ሲኖር ከዕለታት አንድ ቀን ዳዊት ታመመ፡፡የዳዊትን መታመም ሰምተው፣ ካሉበት ተነስተው የዳዊትን ከተማ በተለይም ቤተልሔምን ከበቧት፡፡ ዳዊት ይህ ሰምቶ “ወይ እኔ ዳዊት! ድሮ ታመምሁና ጠላቶቼ ሰለጠኑ ሲል የኀያላኑን ልቦና ለመፈተን ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባመጣልኝ?” አለ፡፡ በዚህ ጊዜ የጭፍሮቹ አለቆች ሦስቱ ማለትም አዲኖን፣ ኢያቡስቴ ኤልያና ረዋታቸውን /የውኃ መያዣ/ ይዘው፣ ጦራቸውን አሰልፈው፣ ጠላቶቹን ድል ነስተው፣ ዳዊት ሊጠጣ የወደደውን ውኃ አመጡለት፡፡ቅዱስ ዳዊትም ያንን ውኃ አፈሰሰው “ለምን አፈሰስከው?” ቢሉት “ደማችሁን መጣጠት አይደለምን?” ብሎ፤ ይህም ከጽድቅ ገብቶ ተቆጠረለት፡፡ 2ሳሙ.23፥13-17

 

አባቶቻችን ይህንን ሲያመሰጥሩት የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ አባታችን አዳም ከተድላ ገነት ወደ ምድረ ፋይድ፥ ከነጻነት ወደ መገዛት፥ ከልጅነት ወደ ባርነት፥ በወረደና  ፍትወታት እኩያት ኀጣውእ በጠላትነት በተነሱበት ጊዜ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከተገኘ ከጌታ ጎን የተገኘ ማየ ገቦ ይጠጣ ዘንድ ወደደ፡፡ የትሩፋት አበጋዞች ሃይማኖት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ ፈጥነው ተነሱ፡፡ በአጋንንት ከተማ ተዋጉለት ይጠጣው ዘንድ የወደደውን ማየ ገቦ አመጡለት፡፡ ማለትም የአዳም ልጅነት በከበረው የክርስቶስ የደሙ ፈሳሽነት የሥጋው መሥዋዕትነት ተመለሰለት፡፡ ይህንን ለአዳምና ለልጆቹ የባህርይ አምላክ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን ፀዋትወ መከራ እያሰቡ ሰማዕታት በእግዚአብሔር ፍቅር ተቃጥለው “እግዚአብሔርን ካዱ ለጣዖት ሰገዱ” ሲባሉ “እግዚአብሔርን አንክድም ለጣዖት አንሰግድም” ብለው ደማቸውን አፈሰሱ ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረላቸው፡፡ /ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ዘሐሙስ/

 

“ሰማዕት” ማለት ምስክር ማለት ነው፡፡ ይህ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብሎ ማፍሰስ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረላቸው፥ የዳዊት ወታደሮች ስለ ዳዊት ፍቅር ብለው “ደማችን ይፍሰስ” እንዲሉ፤ ዳዊትም ያመጡለትን ውኃ መጠጣት ደማችሁን እንደመጠጣት ነው ብሎ በፍቅር ምክንያት ውኃውን እንዳፈሰሰው፥ ይህም ጽድቅ ሆኖ እንደተቆጠረለት፥ የእግዚአብሔር ወዳጆች የሆኑ ቅዱሳን ሰማዕታትም እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር ሃይማኖት የሆነችው እውነተኛይቱን ሃይማኖት ወደው ደማቸውን አፈሰሱ፣ አጥንታቸውን ከሰከሱ፣ ስለዚህ እንደ ፀሐይ አብርተው በሰማያት ዛሬም ስለ እኛ እየማለዱ አሉ፡፡ “ለመሆኑ ከዚህ ክብር የደረሱት እንዴት ነው?” ብሎ ለሚጠይቅ ቅዱስ ኤፍሬም ሲመልስ ሦስት ነገሮችን ያነሣል፡፡

 

1.    “ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም ናቁ” ይላል

ዓለም እንደየዘመኑ የተለያየ ጠባይ አላት፤ ልክ እንደ እስስት ትለዋወጣለች፡፡ ስለዚህ ሁል ጊዜ ከእውነት ይልቅ ሐሰት፥ ከፍቅር ይልቅ በእውነተኞቹ ላይ ጥላቻ፥ በግልጽ ይታይባታል፡፡ የራሷ የሆነውን እጅግ አድርጋ ትወዳለች ስለዚህም በተለያየ መረብ እያጠመደች ለዘለዓለሙ ትጥላለች፡፡ “ሰማዕታት” /ምስክሮች/ ግን የዚችን ዓለም ጣዕም ናቁ፤ ማለትም እውነት እግዚአብሔርን፥በሐሰት ጣዖት አልለወጡም ስለዚህ በእግዚአብሔር ዘንድ በክብር ተቀምጠው ስለ እኛ እያማለዱ አሉ፡፡ ትምህርታችንን የበለጠ ግልጽ እንዲያደርግልን እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ባሕር አሸዋ ቁጥራቸው ከበዛ በእግዚአብሔር ዘንድ ክብር ካላቸው ቅዱሳን ሰማዕታት መካከል የሰማዕታት አለቃ ተብሎ በፈጣሪው በእግዚብሔር ዘንድ ስለተሾመው ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተጋድሎ ሕይወት ጥቂት እንመለከታለን፡፡

 

በረከቱ ይደርብንና ቅዱስ ጊዮርጊስ የአባቱ ስም ዘሮንቶስ የእናቱ ስም ቴዎብስታ ይባላል፡፡ አባቱ በፍልስጥኤም አገር መስፍን ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሕፃን ሳለ አባቱ በሞት ተለየው ከዚያ 20 ዓመት ሲሞላው የአባቱን ሹመት ለመቀበል ወደ ዱድያኖስ ንጉሥ ዘንድ ሄደ፡፡ ንጉሡም ጣዖት አቁሞ ጣዖትን እንዲያመልኩ ሰዎችን ሁሉ ሲያስገድዳቸው አገኘው፡፡ ይህንን አይቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ አዘነ፤ በእርሱ ዘንድ ያለውን ለንጉሡ እጅ መንሻ ያመጣውን ገንዘቡን ለድሆች እና ለምስኪኖች ሰጠ፡፡ ባሮችንም ነጻ አወጣቸው ከዚህ በኋላ በንጉሥ ፊት ቁሞ “በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ በግልጽ እኔ ክርስቲያን ነኝ” አለ፡፡ ያን ጊዜ ንጉሡ ዱድያኖስ በዘመኑ ከነበሩ በሥልጣኑ በሥሩ ከሚተዳደሩ 70 ነገሥታት ጋር ሆኖ አባብለው እግዚአብሔርን እንዲክድ ለጣዖት እንዲሰግድ ይህንን ቢያደርግ ብዙ ብር እና ወርቅ እንደሚሰጠው ከእርሱም በታች ባለ ሥልጣን እንደሚያደርገው ቃል ገባለት፡፡

 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ይህንን አልተቀበለም፡፡ በፊቱ ናቀው እንጂ ጌታ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረ “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል” ማቴ.16፥26 እንዳለ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በወጣትነቱ እግዚአብሔርን ክዶ ለጣዖት ሰግዶ የሚያገኘውን ወርቅ እና ብር እንዲሁም ሥልጣን ናቀ፡፡ ይህ እግዚአብሔር ለማገልገል በሕይወቱ ያሳየውን ቆራጥነት እራስን መካድን ያሳየናል፡፡ ማቴ.16፥24፡፡ ከዚህ ቅዱስ ሕይወት ተምረን እኛም በዓለም ውስጥ ከሚሠራው የኀጢአት ሥራ በንስሐ ሕይወት በጽድቅ ሥራ መለየት ይገባናል በዘመናችንም እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዓለምን ጣዕም መናቅ ማለት እውነትን በሐሰት አለመለወጥ ማለትም እውነተኛ ሆኖ መገኘት የሚበላውን ከማይበላው ጋር ቀጥቅጦ አለመሸጥ በሚዛን አለመበደል ፍርድ አለማጉደል ጉቦ ተቀብሎ ድኃ አለመበደል በምንሠራበት መሥሪያ ቤተ ሰነድ አለመሰረዝ አለመደለዝ ባጠቃላይ በሕይወታችን በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ በእውነት ታምነን መገኘት ይገባናል፡፡ ለዚህም የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎትና ምልጃ ይርዳን፡፡

 

2.    ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ

እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው ዱድያኖስ ንጉሥ የዚችን ዓለም ጣዕም አቅምሶ ቅዱስ ጊዮርጊስ በማባበል ለጣዖት ማሰገድ በተሳነው ጊዜ የወሰደው እርምጃ በዘመኑ በነበረው የተለያየ መሣሪያ ተጠቅሞ የቅዱስ ጊዮርጊስን ደም ማፍሰስ ነበር፡፡ በገድለ ጊዮርጊስ እንደተጻፈ ለቆመው የወርቅ ምስል አልሰግድም እነርሱንም አላመልክም ይልቁንም ዐይን እያላቸው የማያዩ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ እጅ እያላቸው የማይዳስሱ እግር እያላቸው የማይሄዱ በአፋቸው ትንፋሽ የሌለ ግዑዛን ናቸው፡፡ እነርሱን የሚያመልኩ እንደነርሱ ይሁኑ ብሎ በቅዱስ ዳዊት ቃል ንጉሡን እና ጣዖታቱን በዘለፈ ጊዜ መዝ.113፥12-16 ዱድያኖስ ንጉሥ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስገረፈው በተገረፈ ጊዜ ደሙ እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ከዚያም ጨለማው ጥልቅ ወደ ሆነ የእስር ቤት ጣሉት፡፡ ዱድያኖስና ሰባው ነገሥታት በዚህ መከራ ይሞታል የእርሱን መከራ መቀበል የደሙንም መፍሰስ የተመለከቱ ሌሎች ሰዎችም በመፍራት በእኛ የጣዖት አምልኮ ሥርዓት ፀንተው ይኖራሉ ብለው አስበው ነበር፡፡

 

ነገር ግን የቅዱስ ጊዮርጊስን መከራ መቀበል የደሙንም መፍሰስ የወደደ ይህንንም ለክብር ሊያደርግለት ፈቃዱ የሆነ ቅዱስ እግዚአብሔር በግርፋቱና በደሙ መፍሰስ እንዲሞት አልተወውም ስለዚህ ወደ እስር ቤቱ የጨለማውን ጥልቀት በብርሃን የሚገልጥ ቁስሉንም የሚፈውስ የሚያጽናና መልአክ ላከለት፤ መልአኩም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገብቶ ቁስሎቹን ፈወሰ፤ እርሱንም አጽናንቶ ፣ እግዚአብሔር ለእርሱ ያደረገለት ያለውን ሁሉ በግልፅ ነግሮት በክብር አረገ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ሲነጋ የዱዲያኖስ ወታደሮች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጡ ጊዜ ምንም የግርፋትና የደም መፍሰስ ምልክት ባላገኙ ጊዜ፣ ይልቁንም ቅዱስ ጊዮርጊስ ደስ ብሎት እግዚአብሔርን ሲያመሰግን  አግኝተው ተደነቁ፡፡ ከዚያም “እኛም በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ እናምናለን፡፡” ብለው ብዙ ሰዎች ሰማዕትነት ተቀበሉ፡፡አንድ ዛፍ በተቆረጠ ጊዜ ከስሩ ብዙ ችግኝ እንዲገኝ በቅዱስ ጊዮርጊስ መከራ መቀበል ብዙ ሰዎች ወደ ሃይማኖት መጡ፡፡

 

3. ስለ መንግሥተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ

ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲህ ያለውን ተአምት በማድረግ ብዙ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንደተመለሱ የተመለከተ ዱድያኖስ አሁንም በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የሚደርሰውን የመከራ ስልት በመቀያየር አትናስዮስ የተባለ ጠንቋይ አስመጥቶ መርዝ በጥብጦ እንዲጠጣ አዘዘ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም የቀረበለትን መርዝ በሰው ሁሉ ፊት በትእምርተ መስቀል አማትቦ ባጣጣመ ጘራራ የሆነውን የሞት ጽዋ ተጎንጭቶ ከባድ መከራ ተቀብሎ እንዲሞት የእግዚብሔር ፈቃዱ ቢሆንም የቅዱስ ጊዮርጊስን ክብር እርሱን ፍፁም መውደዱን ለመግለጽ አምላካችን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርምን ባለሟሎቹ ቅዱሳን መላእክትን ወዳጆቹ ነቢያት ሐዋርያት ቅዱሳንን አስከትሎ አፅሙ ወደ ተዘራበት ወደ ይድራስ ተራራ ወረደ በክብር ወረደ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልን አዘዘው የተበተነው የወዳጄን የቅዱስ ጊዮርጊስን አፅም ስብሰባህ አምጣ አለው እርሱም እንደታዘዘው ሰበስቦ ወደ ጌታችን አቀረበ ያን ጊዜ ጌታችን በምሕረት እጁ ተቀብሎ  አዳምን የፈጠሩ እጆቼ አንተንም የፈጠሩ አሁንም ወዳጄ ጊዮርጊስ እኔ አዝዤአለሁ ከሞት ተነሣ አለው፡፡ ያን ጊዜ ከጫጉላ ቤት እንደሚወጣ ሙሸራ አምሮበት ከሞት ተነሣ ጌታችንም በአፍ መሳም ሳመው የሚጸናበትን ቅዱስ መንፈሱን አሳደረበት ከዚያም ሊቀበለው ያለውን መከራ የሚያገኘውን ዋጋ ነግሮት በክብር አረገ፡፡

 

ይህ የሆነው ጥር 18 ቀን ነው፡፡ ይህንን መራራ ሞት በእሳት መቃጠል በመንኮራኩር መፈጨት እንደ እህል መዘራት ታግሶ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተደረገለት ተአምራት ከሞትም በመነሣቱ ብዚ ሰዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ አምነው ወደ እውነተኛይቱ ሃይማኖት ተመልሰዋል፡፡ እንግዲህ በገድሉ መጽሐፍ እንተጻፈ ለ7 ዓመት መራራ መራራ የሆነ ብዙ መከራዎችን ታግሶ በስተመጨረሻ በሰይፍ ተከልሎ /አንገቱን ተቆርጦ ከአንገቱም ደም ውኃ ወተት ፈሶ ለተጋድሎው 7 የድል አክሊል ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለ የከበረ ቃል ኪዳን የተቀበለ ሰማዕት ነው፡፡ እኛም ከዚህ ቅዱስ ገድል ተምረን አሰረ ፍኖቱን በመከተል ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን እንድናጸና ዘመኑ የሚጠይቀውን ሰማዕትነት ምግባር ማቅናት እንድናቀና የሠማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎትና ቃል ኪዳን ተራዳኢነት አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች የክብርት እመቤታችን አማላጅነት የቅድስት ሥላሴ ቸርነት አይለየን አሜን፡፡

አስተርእዮ

ጥር 20 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ለማ በሱፈቃድ

 

አስተርእዮ ማለት መታየት፣ መገለጥ  የመሳሰሉትን ፍች ይይዛል፡፡ ቃሉ አስተርአየ ታየ፣ ተገለጠ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ የጥር ወር በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ በመባልም ይታወቃል ምክንያቱም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ የተገለጠበት/የታየበት ወቅት በመሆኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ ዘመነ አስተርእዮ ተባለ፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን አንድነት ሦስትነቱም የተገለጠው  በዚሁ ወር ነውና ዘመነ አስተርአዮ ተብሎ ይጠራል፡፡

 

 

በዚህ ጽሑፍ የምናተኩረው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ሥጋ ለብሶ የመታየቱ/የመገለጡ ዋና ዋና መክንያቶቹ ምንድናቸው የሚለው ነው፡፡

 

1.    የገባውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ

እግዚአብሔር ሰውን ፈጥሮ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጅቶ በክብር ይኖር ዘንድ ገነትን አወረሰው፡፡ በማየት የሚደሰትበትና የሚማርበትንም ሥነ ፍጥረትን ፈጠረለት የሚበላውንና የማይበላውንም ለይቶ ሰጥቶት ነበር ነገር ግን የሰው ልጅ አትብላ ያለውን አምላካዊ ትእዛዝ ሳይጠብቅ የተከለከለውን ዕፀ በለስ በመብላቱ ምክንያት ከገነት ተባረረ፡፡ ዘፍ.2፥16 በዚያን ጊዜ ነው ርህራሄ የባህርዩ የሆነ አምላክ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው የሚለው የተስፋ ቃል ኪዳን ሰጠው ሲራ.24፥6፡፡

 

አዳምም ከነ ልጆቹ ለአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመናት ይህንን ቃል ኪዳን ሲጠባበቅ ኖሯል፡፡ ነቢያቱም ትንቢት ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ ጌታ ራሱ ምልክትን ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች በማለት ተስፋውን በትንቢተ ነቢያት በማስታወስ ቆይቷል፡፡ ኢሳ.7፥14

 

በዚህ ዘመን ደቂቀ አዳም በሙሉ በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዘው ተስፋውን ሲጠባበቁ የነበሩበት ዘመን ከዚሁ የጭለማ ዘመን ለመዳን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ውጤት ያላመጣ ነበርና ጊዜው/ ቃል ኪዳኑ እስኪፈጸም ድረስ በተስፋ ይጠባበቅ ነበር፡፡ ኢሳ.26፥20 ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ ተብሎ እንደተጻፈው ይህችን ቃል ኪዳን ይፈጽማት ዘንድ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ በሥጋ ተገለጠ ማለት ሥጋን ተዋሐደ፡፡

 

2.    የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ

ወዘሰ ይገብራ ለኀጢአት እምነ ጋኔን ውእቱ እስመ ቀዳሚሁ ለሰይጣን አበሰ ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይሰዐር ግብሮ ለጋኔን” ኀጢአትን የሚሠራትም ከዲያብሎስ ወገን ነው፡፡ ጥንቱንም ሰይጣን በድሎአልና ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ተገለጠ የዲያብሎስን ሥራ ይሽር ዘንድ 1ዮሐ.3፥8 በማለት ሐዋርያው እንደገለጸው ሰይጣን የሰውን ልጅ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን የመሰለ ቦታ እንዲያጣ ከደስታ ወደ ዘለዓለም ሐዘን ከነጻነት ወደ ግዞት ከብርሃን ወደ ጨለማ ይገባ ዘንድ ረቂቅ ሥራ ሠርቶ ነበርና ይህንን የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ዲያብሎስ በሥጋ ከይሲ/በእባብ ሥጋ ተሰውሮ ነገት ገብቶ አዳምና ሔዋንን እንዳሳተ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሰውን ልጅ ሥጋ ተዋሕዶ የደያብሎስን ሥራ አፍርሶበታል፡፡ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን አስቶ የግብር ልጆቹ ይሆኑ ዘንድ አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለደያብሎስ ብለው የፈረሙትን ደብዳቤ በዮርዳኖስና በሲዖል የቀበረውን የጥፋት የተንኮል ሥራውን ያፈርስ ዘንድ ሰው ሆኖ ተገለጠ፡፡ ይህንን የዲያብሎስ ሥራ በዮርዳኖስ ባሕር የተቀበረውን በጥምቀቱ በሲዖል የተቀበረውን በስቅላቱ በሞቱ ደምስሶበታልና “ወነስተ አረፍተ ማእከል እንተ ድልአ በሥጋሁ” በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፈረሰ፡፡ ኤፌ.2፥14 በማለት ሐዋርያው እንደተናገረው የዲያብሎስን ክፉ ሥራ የጥል ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ በሥጋ ተገለጠ፡፡

 

3.    አንድነት ሦስትነቱን ይገልጥ ዘንድ

የምስጢረ ሥላሴ ትምህርት በብሉይ ኪዳን ዘመን በግልጥ አይታወቅም ነበር የተገለጠ የታወቀ የተረዳ የአንድነቱን ሦስትነቱን ትምህርት በሚገባ ለማስተማር የተቻለው ጌታችን ሥጋ ለብሶ ከተጠመቀ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ “ወርእየ መንፈሰ እግዚአብሔር እንዘ ይወርድ በአምሳለ ርግብ ወናሁ መጻአ ቃል እምሰማይ ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ” የእግዚአብሔር መንፈስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲቀመጥ ለመሥዋዕትነት የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው፡፡ ማቴ.3፥17 /ሉቃ.3፥21፡፡ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል አብ በደመና ሆኖ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚለው ቃል በተገለጸ ጊዜ  የአዳምና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ይሽር ዘንድ የአንድነት እና ሦስትነት ምሥጢር ገልጿአል፡፡ ይህንን ምሥጢር ይገልጠ ዘንድ በሥጋ ተገለጠ ታየ፡፡ ይህ ምስጢር ጥንተ ዓለም ሳይታወቅ ሳይገለጥ ተሰውሮ ይኖር ነበር፡፡ በእንተ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኅቡእ ኅርመቱ እምቅድመ ዓለም፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር ተሰውሮ ነበር ከነቢያት ቃል የተነሣ በዚህ ዘመን ተገለጠ፡፡ ሮሜ.16፥24

 

4.    ፈጽሞ እንደወደደን ለመግለጽ

እግዚብሔር ሰውን ምን ያህል እንደወደደ ለመረዳት እግዚብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ዕፁብ ድንቅ ነውና ማንም ሳያስገድደው ሰው ሁን ብሎ ሳይጠይቀው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ዘመኑን ጠብቆ ሰው ሆኖ ከኀጢአት በስተቀር ሁሉን ፈጽሞ በገዛ ፈቃዱ መከራ ሥጋን ተቀብሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ የዘለዓለም ሕይወትን መስጠት ምን ያህል ፍጹም ፍቅሩን እንደገለጸልን እንረዳለን፡፡ “አልቦ ዘየዐቢ እምዝ ፍቅር ከመ ዘቦ ዘይሜጡ ነፍሶ ህየንተ አእርክቲሁ” ስለወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ያለ እንደሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም ዮሐ.15፥12 ያጠፋው የሰው ልጅ ይሰቀል ይሙት ሳይል እኔ ልሙት ማለት ፍጹም ፍቅር ነው፡፡ ሰው ሰውን የሚወደው ገንዘቡንና የመሳሰሉትን እስከ መስጠት ሊሆን ይችላል፡፡ ሕይወቱን እስከ መስጠት የሚወድ የለም አልነበረም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወደደውን የሰውን ሥጋ ለብሶ መኪራ ሥጋን ተቀብሎ ሰውን በሞቱ ያድን ዘንድ ሞትን የሞተው ፈጽሞ እንደወደደን ለመግለጥ ነው፡፡ 1ዮሐ.4፥9፡፡ ይህም ፍቅሩ ይቃወቅ ዘንድ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ስለዚህ ሊቃውንቱ አስተርእዮ በማለት ሰይመውታል፡፡

“ወአርአየ ስብሐቲሁ ወአምኑ ቦቱ አርዳኢሁ” ዮሐ. 2፤11

ጥር 12 ቀን 2005 ዓ.ም

መ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ


“ጌትነቱን ገለጠ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበዐላት አከባበር ቀመር ከበዓለ ልደት ፤ግዝረት፤ ጥምቀት ቀጥሎ ቃና ዘገሊላ ይከበራል፡፡ ምክንያቱም ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ወደዚህ ዓለም በመጣበት ወቅት ልዩ ልዩ የሆኑ ድንቅ ተአምራት አድርጓል፡፡ ከእነዚህም የመጀመሪያው በቃና ዘገሊላ በሰርግ ቤት ተገኝቶ ያደረገው ተአምር ተጠቃሽ ነው፡፡

 

ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ እንዲህ ጽፎታል፡፡ “በሦስተኛው ቀን በገሊላ ቃና ሠርግ ሆነ” ምን በሆነ በሦስተኛው ቀን የሚል ጥያቄ በሁላችንም እዕምሮ እንደሚመላለስ አያጠያይቅም፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ጥር 11 ቀን ተጠምቆ ሳይውል ሳያድር ዕለቱን ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሞ ፤ዲያብሎስን ድል ነስቶ፤ መዋዕለ ጾሙን ፈጽሞ ለእኛም ዲያብሎስን ደል የምንነሳበትን መንገድ አሳይቶን ከገዳመ ቆሮንቶስ መልስ ደቀ መዛሙርቱን መረጠ፡፡ ከጥር አሥራ አንድ እስከ የካቲት ሃያ አርባ ቀን ይሆናል፡፡ መዋዕለ ጾሙን የካቲት ሃያ ፈጽሞ በወጣ በሦስተኛው ቀን ገሊላ አውራጃ ቃና በተባለች መንደር ሰርግ ሆነ፡፡ በዚህ ሰርግ ብዙ ሰዎች የታደሙ መሆኑን የወይን ጠጁ ማለቅ ያስረዳል፡፡ በእርግጥም የተጠሩት ሰዎች ብዙ ቢሆንም ብዙዎች መመገብ የሚችል አምላክ በሰርግ ቤት መጠራቱ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ሰርግ ከሠዎች በተጨማሪ ሦስት አካላት ተጠርተዋል፡፡

1. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም

“ወሀለወት ህየ እሙ ለእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ” የጌታ እናት ከዚያ ነበረች እንዲል እንዲያው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ በደግ ሰው ልማድ ተጠርታ እንጂ እመቤታችን በማኅበራዊ ሕይወት የነበራትን ተሳትፎ እና በሰዎች ዘነድ የነበራትን ተዋቂነት ያመለክታል፡፡ በሌላ መልኩ በቤተ ዘመድ ልማድ ማንኛውም ዘመድ እንደተጠራው ሁሉ እርሷም በገሊላ በነበሩት ሰዎች ዘንድ ታላቅና ተዋቂ ስለበረች እና ቤተ ዘመድ በመሆኗ በዚህ ሠርግ ተጠርታ ነበር፡፡የተገኘችው የሰው ሰውኛው ይህ ቢሆንም በዚያ ሠርግ ቤት ማንም ሊሠራው የማይችል የሥራ ድርሻ ነበራት፡፡ይህ በሰዎች ዘንድ የማይታወቅ በእግዚአብሔርና በእርሷ መካከል ያለ አማላጅነት ነው፡፡ የጎደለውን መሙላት ለሚችል ውድ ልጇ የጎደለውን እንዲሞላ ማማለድ ነው ፡፡ እመቤታችን ከሰው ልጆች የተለየች ክብርት ቅድስት ንፅህት ልዩ በመሆኗ የምታውቀውም ምሥጢር ከሰው የተለየ ነው፡፡ “ወእሙሰ ተአቀብ ዘንተ ኩሎ ነገር ወትወድዮ ውስተ ልበ” ማርያም ግን ይህንን ሁሉ ትጠብቀው በልቧም ታኖረው ነበር ሉ.2፤19 ይህን ሁሉ ያለው ድንግል ማርያም አምላክን በመውለዷ ከሰው ልጆች የራቀ ምስጢር የተገለጠላት መሆኑን ያስረዳል፡፡ ይህንን ሁሉ ብሎ እንደ ሸማ ጠቅልሎ እንደ ወርቅ አንከብሎ የተናገረው የተገለጠላት ምስጢር በሰው አንደበት ተነግሮ የማያልቅ እንደሆነ ነው የሚገልጠው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሁለት ብለን የምንቆጥረው አይደለምና መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እንደዚሁ “ፀጋን የተሞላሽ” በማለት የገለጠው ለእርሷ የተሰጠው ባለሟልነት ልዩ መሆኑን ለማስረገጥ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ በሠርጉ ቤት የምትሰራውን ሥራ በውል ታውቅ ነበርና፡፡

 

2. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠርቶ ነበር

“ወፀውእዎ ለእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ” ጌታ ኢየሱስንም ጠሩት” ዮሐ.2፤2 እናትን ጠርቶ ልጅን መተው ተገቢ አይደለምና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጠርተው ልጇም ጠርተውታል፡፡ ይህም ፍፁም ሰው መሆኑን ያስረዳል፡፡ ሰው ነውና እንደ ሰውነቱ ወደ ሰርግ ቤት ተጠራ፤አምላክ ነውና ጌትነቱን ገለጠ፡፡

 

ከሚደሰቱት ጋር መደሰት ከሚያዝኑ ጋር ማዘን ተገቢ መሆን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር አስተማረ፡፡ በቃና ዘገሊላ ከሠርግ ቤት እንደሄደ በአልአዛር ቤት ለለቅሶ መገኘቱን ልብ ይሏል፡፡ወደ ሠርግ ቤት የሄደው በደስታ ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ እንደገለጠው “ሖረ ኢየሱስ በትፍስህት ውስተ ከብካብ እንዘ ይገብር ተአምረ ወመንክረ በውስተ አህዛብ፤ ኢየሱስ በአህዛብ ፊት ተአምራትንና ድንቆችን እያደረገ በደስታ ወደ ሠርግ ሄደ” ወደ አልአዛር ቤት ሲሄድ ግን “ጌታች ኢየሱስ ክርስቶስም እርሷ (ማርታ) ስታለቅስ ባየ ጊዜ በልቡ አዘነ፡፡በራሱም ታወከ(ራሱን ነቀነቀ፡-የሀዘን ነው) ጌታችን ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ ፡፡አይሁድም ምን ያህል ይወደው እንደነበር እዩ አሉ” ዮሐ.11÷33-38

 

ከዚህ እንደ ምንመለከተው ከኀጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ መሥራቱን የሰውን የተፈጥሮ ሕግ ምን ያህል እንደ ከበረ እና እንደፈጸመ ያሳያል በመደሰት እና በማዘን ፍጹም ሰው መሆኑን ሲያስረዳን ፍጹም አምላክ መሆኑን በሰርጉ ቤት ውኃውን የወይን ጠጅ በማድረግ በልቅሶ ቤትም ዓልዓዛርን ከአራት ቀናት በኋላ በማስነሣት አስረዳን፡፡ አምላክ ነኝ ከሠርግ ቤት አልሄድም ከልቅሶም ቤት አልገኝም አላለም በትሕትና ራሱን ዝቅ አድርጎ በሰርግ ቤት እንዲሁም የሚያዝኑትን ለማጽናት በልቅሶ ቤት በመገኘቱ ሁሉንም የሰውነት ሥራ አከናወነ፡፡ አምላክ ነው በሰርግ ቤት የጎደለውን መላ፡፡ አምላክ ነውና የሞተውን አልዓዛርን መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱኝ ሳይል እንዲነሣ አደረገ፡፡

 

በዚህ የሰርግ ቤት ባይገኝሰዎች ምን ያህል ሀፍረት ይሰማቸው ይሆን? የእርሱ እንዲሁም የእናቱ በሰርጉ ቤት መገኘት ለባለሰርጉና ለታዳሚዎች ሙላት ነበር እርሱ ባይኖር የሰርጉ ቤት የሃዘን ቤት ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም በዚህ ሰርግ ቤት ተመላጅነት የአምላክ አማላጅነት ደግሞ የፍጡራን መሆኑን አስተምሯል፡፡

“ወሶበ ሀልቀ ወይኖ ወይትቤሎ እሙ ወይንኬ አልቦሙ” ዮሐ.3÷3 “የወይን ጠጅ ባለቀባቸው ጊዜ እመቤታችን የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው አማላጅነት የፍጡራን ገንዘብ ነው፡፡ እርሱ አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ÷ ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ አንቺ ያልሽውን ልፈጽም አይደለም ሰው የሆንኩት አላት ጊዜ ገና አልደረሰም የሚለው ሥራውን ያለ ጊዜው አይሠራውምና ነው፡፡ ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ አለው” እንዲል፡፡ መዝ.118÷126 በሌላ መልኩ በአምላክነቱ ማንም የማያዝዘው ግድ ይህን አድርግ ብሎ ማንም ሊያሰገድደው የሚችል የወደደውን የሚያደርግ ቢፈልግ የሚያዘገይ ሲፈልግ በዐይን ጥቅሻ በፈጠነ መልኩ መፈጸም የሚችል በራሱ ፈቃድ እንጂ በሰምች ፈቃድ የማይመራ መሆኑን ያስተምረናል፡፡

 

“ፈቃድ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ማቴ.6÷ ብላችሁ ለምኑኝ ያለው ለዚህ ነው በሌላ መንገድ የወይን ጠጅ በሙሉ አላላቀም፡፡

 

ያለውን ቢያበረክተው ተአምራቱን አናደቅም፥ ፈጽሞ ጭል ብሎ እስከሚያልቅ “ጊዜ ገና አልደረሰም” አለ፡፡ሰው ቢለምን ቢማልድ በእርሱ ፈቃድ ጊዜው ሲደርስ ነው የሚፈጸመው፡፡ምልጃው አልተስማም ተቀባይነት አላገኝም ማለት ግን አይደለም ተቀባይነት ያገኘ መሆኑ የሚታወቀው በመደረጉ ነው፡፡

 

አማላጅ ያስፈለገው እርሱ የሚያውቀው ነገር ኖሮት በስምአ በለው ለመንገር አይደለም ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ይታወቅ ዘንድ እና የሰው ልጆችን ከችግር የሚያወጣበት መንገዱ ብዙ መሆኑን ለማስረዳት ነው እንጂ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሚዜዎችን “ኩሎ ዘይቤለክሙ ግበሩ፤ያዘዛችሁን ሁሉ አድርጉ፡፡” ማለቷ “አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ” የሚለው የጌታችን መልስ “እሺታ ይሁንታን” የሚገልጽ መሆኑን ያስረዳል፡፡ “እሱም ውኃ ቅዱና ጋኖችን ምሏቸው” አለ፡፡ እነርሱም በታዘዙት መሠረት እመቤታችን ያላችሁን አድርጉ እንዳለቻቸው ውኃውን ቀድተው ጋኖችን ሞሏቸው፡፡ ውኃውንም ክብር ይግባውና በአምላካዊ ችሎታው ወደ ወይን ጠጅ ለወጠው፡፡ ለአሳዳሪውም ሰጠው አሳዳሪው የወይን ጠጅ የሆነውን ውኃ ቀምሶ አደነቀ ከወዴት እንደመጣ ግን አላወቀም ድንቅ በሆነ አምላክ ሥራ እንደተለወጠም አልተረዳም፡፡ ያን ምስጢር የሚያቀው ባለሰርጉ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ውኃውን የቀዱ ሰዎች ናቸውና፡፡

 

ታዳሚዎችም “ሰው ሁሉ የተሻለውን ወይን አስቀድሞ ያቀርባል በኋላም ተራውን የወይን ጠጅ በኋላ ያቀርባል አንተስ መናኛውን ከፊት አስቀድመህ ያማረውን ከኋላ ታመጣለህን” ብለው አድንቀዋል፡፡ ድሮም የአምላክ ሥራ እንደዚያ ነው ብርሃን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ጨለማን ፈጥሯል ከጨለማ ቀጥሎ “ብርሃን ይሁን” በማለት ብርሃንን ፈጥሯል፡፡ መጀመሪያ ብርሃን ተፈጥሮ ኋላ ጨለማ ቢፈጠር ይከብድ ነበርና መጀመሪያ 21 ፍጥረታት ፈጥሯል፡፡ በመጨረሻም በአርዓያውና በአምሳሉ የሥነ ፍጥረት የሆነውን የሰው ልጅ ፈጥሯል፡፡ ናትናኤልንም እንዲህ ብሎታል፡፡ “ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የሚባልጥ ታያለህ” ማለቱ የእግዚብሔር ሥራ እየቆየ ውብ ያማረ መሆኑን ያመለክታል ሰው ግን ጥሩ ነው፡፡ ያለውን ያስቀድማል ያ ሲያልቅ የናቀውን ይፈልጋል፡፡ “የወደዱትን ቢያጡ ያጡትን ይቀላውጡ” እንዲሉ እግዚብሔር ልማዱ ነው፡፡ ተራውን ከፊት ታላቁን ከኋላ ማድረግ ለሰው መጀመሪያ የተሰጠው የሚያልፈው ዓለም ነው በኋላ የማያልፈው መንግሥተ ሰማያት ይሰጠዋል ሰው መጀመሪያ ይሞታል በመጨረሻ ትንሣኤ አለው፡፡ ሰው መጀመሪያ ሲወለድ ርቀቱን ነው፡፡ ኋላ ልብስ ያገኛል፡፡ ሁብታም ይሆናል፡፡ ሰው ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ዓለምን የሚያገኛት የሚተዋወቃት በልቅሶ ነው፤ ኋላ ግን ይደሰታል በሀሳር በልቅሶ ወደመቃብር ይወርዳል፡፡ በደስታ “መቃብር ክፈቱልኛ፥ መግነዝ ፍቱልኝ” ሳይል ይነሣል ይህን የአምላክ ሥራ አድንቆ መቀበል እንጂ መቃወም አይችልም፡፡

 

3. ቅዱሳን ሐዋርያት በዚህ ሠርግ ነበሩ

“ወለአርዳኢሁ ውስተ ከብካብ” እንዲል፡፡ ዮሐ.2፥2 “ደቀመዛሙርቱንም ጠሯቸው” መምህርን ጠርቶ ደቀ መዝሙርን መተው ተገቢ አይደለምና፤ ደቀ መዛሙርቱ ከመምህራቸው ከክርስቶስ ጋር አብረው በሠርግ ቤት ተገኝተው በተደረገው ተአምር ጌትነቱን አምነዋል፡፡ ተአምራቱን ተመልክተዋል፣ ከዋለበት የሚውሉ፥ ከአደረበት የሚያድሩ፥ ተአምራት የማይከፈልባቸው፥ ይህን ዓለም ለማስተማር የተመረጡ ናቸውና፤ አየን ብለው እንጂ ሰማን ብለው አያስተምሩምና፡፡በጠቅላላው የእነርሱ በሰርጉ ቤት መገኘት የሚያስተምርና ካህናት የሌሉበት ሰርግ ሊደረግ እንደማይገባው ነው፡፡ በሰርግ ቤት የካህናት መገኘት እና ቡራኬ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ያስተምራል፡፡ በፍትሐ ነገሥት አን.24 የተገለጸውም ይህ ነው “ወማዕሰረ ተዋሰቦሶ ኢይትፌጸም ወኢይከውን ዘእንበለ በሀልዎተ ካህናት ወጸሎት ዘለዕሌሆሙ” የጋብቻ አንድነት ካህናት ቢኖሩ እንጂ ያለእነርሱ አይጸናም ጸሎት ቢያደርጉ እንጂ ያለ ጸሎት አይፈጸምም” እን. በቃና ዘገሊላው ሰርግ ጋብቻን በጥንተ ፍጥረት “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ረዳት እንፍጠርለት” ዘፍ.2፥19 ያለ አምላክ የሐዲስ ኪዳን ጋብቻ በካህናት ቡራኬና ጸሎት መከናወን እንደሚገባው ሲያስተምረን ቅዱሳን ሐዋርያትን ይዞ ተገኝቷል፡፡ የቃና ዘገሊላ ሰርግ እና በሰርጉ ላይ የታዩ ተአምራት ምልጃዎች ሁሉ ሌላም ምሥጢር ያዘሉ ናቸው፡፡ እመቤታችን “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” ማለቷ “ወይን” በተባለው የክርስቶስ ደም ዓለም እንዲድን ያስረዳል፡፡ ደምህን አፍሰህ ሥጋህን ቆርሰህ አጽናቸው ማለቷ ሲሆን “ጊዜዪ ገና ነው” የሚለው የጌታ መልስ “ደሙ በዕለተ ዓርብ የሚፈስበት ጊዜ ገና መሆኑን ያስረዳል” ጥንቱን ዓለምን ለማዳን አይደለምን፣ ሰው የሆንኩት ሥጋ የለበስኩት ለዚህ ዓለምን ለማዳን አይደለምን ሲል ነው፡፡

ይቆየን፡፡