ተዝካረ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ

ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

Tkle

አቡነ ተክለ ሃይማኖት

በዛሬው ዝግጅታችን ነሐሴ ፳፬ ቀን የሚከበረውን በዓለ ዕረፍታቸውን ምክንያት በማድረግ ከቅዱሳን ጻድቃን መካከል አንዱ የኾኑትን፣ ‹‹ሐዲስ ሐዋርያ›› እየተባሉ የሚጠሩትን የቅዱስ ተክለ ሃይማኖትን ዜና ሕይወት በአጭሩ ይዘን ቀርበናል፤

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ፣ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት፤ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፪፲፪ ዓ.ም. በቡልጋ አውራጃ በደብረ ጽላልሽ ኢቲሳ ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስተኛውም ቀን እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፡- አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ስማቸውን ‹‹ፍሥሐ ጽዮን›› ብለዋቸዋል፡፡ በተወለዱ በ፲፭ ዓመታቸው ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ቅስናን ከግብፃዊው ጳጳስ ከአባ ጌርሎስ /ቄርሎስ/ ተቀብለዋል፡፡

አንድ ቀን ወደ ጫካ ለአደን በሔዱበት ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱ ክርስቶስ ተገልጦላቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱን ካሰደረባቸው፤ እንደዚሁም ‹ሐዲስ ሐዋርያ› ብሎ ወንጌል ወዳተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸው ከነገራቸው፤ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡና አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም ‹ተክለ ሃይማኖት› እንደሚባልና ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው›› እንደ ኾነ ካስረዳቸው በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ንብረት ኹሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ‹‹አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደ ተከፈተ ተውኩልህ›› በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አንጸዋል፡፡

ከዚህ በኋላ በደብረ ሊባኖስ (ገዳመ አስቦ) ዋሻ በመግባትም ሁለቱን በፊት፣ ሁለቱን በኋላ ሁለቱን በቀኝ፣ ሁለቱን በግራ ስምንት ጦሮችን ተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማም፣ ሞትና ነገረ መስቀል በማሰብ በተመስጦ ሌሊትና ቀን ያለማቋረጥ በጾም፣ በጸሎት ተወስነው ሲጋደሉ፤ ከቊመት ብዛት የተነሣ በ፺፪ኛ ዓመታቸው ጥር ፬ ቀን ፲፪፹፱ ዓ.ም አንዲቱ የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የመንፈሳዊ አባታቸውን ስባረ ዐፅም አክብረው በሥርዓት አኑረዋታል፡፡ እግራቸው እስኪሰበር የቆዩባቸው ዓመታትም ፳፪ ናቸው፡፡ ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው ቆመው ያለ ምግብና ያለ ውኃ በትኅርምት ሌሊትና ቀን እንደ ምሰሶ ጸንተው በትጋት ለሰው ዘር ኹሉ ድኅነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡

ከሰባቱ ዓመታት ውስጥ ጥቂት ውኃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ እንደ ነበረ መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡ ጻድቁ አባታችን ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ የሚያልፉበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደእርሳቸው በመምጣት የሚያርፉበት ዕለት መድረሱን ነግሯቸው የተጋድሏቸውን ጽናት አድንቆ በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ስለ ተጋድሏቸው ጽናትም ‹‹በሰው እጅ የማይለካውን ይህንን የመንግሥት አዳራሽ ውሰድ›› በማለት የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያለው የጸጋ ልብስ አልብሷቸዋል፤ በመስቀል ምልክት ያጌጡ ሰባት የሕይወት አክሊላትንም አቀዳጅቷቸዋል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖትም የዕረፍታቸው ጊዜ መቃረቡን ባወቁ ጊዜ የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ሁሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፉ፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም ለአንድ ቅዱስ አባትና ካህን በሚገባ ሥርዓት በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀበሯቸው፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችንና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾ ታያቸው፤ ነፍሳቸውንም ‹‹የጠራሽ፣ ንጽሕት ነፍስ ሆይ ወደእኔ ነዪ›› ብሎ በክብር ተቀብሏታል፡፡ በመጽሐፈ ገድላቸው እንደተጠቀሰው ቅዱስ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም የኖሩበት ዕድሜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከዐሥር ወር ከዐሥር ቀን ነው፡፡ ገድላቸው ዕድሜያቸውን በመከፋፈል፡- በእናት አባታቸው ቤት ፳፪ ዓመት፤ በከተታ ፫ ዓመት፤ በይፋት ፱ ወር፤ በዳሞት ፲፪ ዓመት፤ በአማራ ፲ ዓመት፤ በሐይቅ ፲ ዓመት፤ በደብረ ዳሞ ፲፪ ዓመት፤ በትግራይ ገዳማት በመዘዋወርና ወደ ኢየሩሳሌም በመመላለስ ፩ ዓመት፤ ዳዳ በሚባል አገር ፩ ወር፤ በደብረ አስቦ ገዳም ፳፱ ዓመት ከ፲ ቀን መቆየታቸውን ይናገራል /ገ.ተ.ሃ.፶፱፥፲፬-፲፭/፡፡

በአጠቃላይ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው በተጨማሪ እንደቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያችንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፡፡ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከተናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋው አይጠፋበትም›› /ማቴ.፲፥፵-፵፪/ በማለት የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን መሠረት አድርጋ መጋቢት ፳፬ ቀን ፅንሰታቸውን፤ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ልደታቸውን፤ ጥር ፳፬ ቀን ስባረ ዐፅማቸውን፤ ግንቦት ፲፪ ቀን ፍልሰተ ዐፅማቸውን ነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸውን በትላቅ ደስታ ታከብራለች፡፡

ቅዱሳን ጻድቃን በመንፈሳዊ አርአያነታቸው፣ በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከከበቡን የነፍስ ጠላቶች፤ ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፣ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመሰወርና ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምን ጊዜም ይሠራል፡፡ በጻድቃን መኖር ሀገር ከጥፋት ትድናለች፡፡ የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለ ጻድቃን ብሎ እግዚአብሔርም ምሕረቱን ያድላል፡፡ ጻድቃንን ማሰብ ሥራቸውን መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምሳል፡፡ በነፍስ በሥጋ ይታደገናል፤ ይረባናል፤ ይጠቅመናል፡፡ ስለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቃንን እንድናስባቸው፣ በስማቸውም ለድሆችና ለጦም አዳሮች እንድንመጸውት መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የምትመክረን፤ የምታስተምረን /ማቴ.፲፥፵፩-፵፪/፡፡ ጻድቃንን በሕይወተ ሥጋ ሳሉም ቢኾን፤ ከሞቱም በኋላ በዐጸደ ነፍስ በጸሎታቸው ለሚታመኑ፣ በቃል ኪዳናቸው ለሚማጸኑ፣ የድኅነተ ሥጋ፣ የድኅነት ነፍስ ምክንያቶች ናቸው፡፡

የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የኹሉም ጻድቃን ጸሎትና በረከት ረድኤትና ምልጃ በመላው ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ጸንቶ ይኑር፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

መለከት መጽሔት ፲፰ኛ ዓመት፣ ቍጥር ፱፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን፡፡

ገድለ ተክለ ሃይማኖት፡፡