ተስእሎተ ቂሣርያ

ነሐሴ ፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፯ ቀን ከሚከበሩ በዓላት መካከል ‹‹ተስእሎተ ቂሣርያ›› አንደኛው ነው፡፡ የቃሉ (ሐረጉ) ትርጕም ‹‹በቂሣርያ አገር የቀረበ ጥያቄ›› ማለት ሲኾን ይኸውም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል?›› ብሎ ደቀ መዛሙርቱን መጠየቁን ያስረዳል፡፡

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው ጌታችን በቂሣርያ አውራጃ ሐዋርያቱን ሰብስቦ ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ (ኢየሱስ ክርስቶስን) ማን ይሉታል?›› ብሎ ሲጠይቃቸው እነርሱም ‹‹ዮሐንስ፣ ኤልያስ፣ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ›› የሚል ምላሽ ሰጥተውታል፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?›› የሚል ጥያቄ ባቀረበላቸው ጊዜ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያቱን ወክሎ ‹‹አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው፤ አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ›› ብሎ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚያስረዳ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽም ሰዎች ስለ ክርስቶስ ማንነት ከሚሰጡት ግምትና ከሐዋርያት ዕውቀት በላይ በመኾኑ ጌታችን ‹‹የእኔን አምላክነት ሰማያዊ አባቴ ገለጸልህ እንጂ ሥጋዊ ደማዊ አእምሮ አልገለጸልህም›› በማለት አድንቆለታል፡፡ ከዚህ በኋላ ‹‹አንተ አለት ነህ፤ በአንተ መሠረትነት ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፡፡ የገሃነም ደጆች (አጋንንት) አይችሏትም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ እሰጥሃለሁ፡፡ በምድር ያሠርኸው በሰማይም የታሠረ፤ በምድር የፈታኸው በሰማይም የተፈታ ይኾናል›› በማለት ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ለቤተ ክርስቲያናችን መታነፅ፣ ለምእመናን ድኅነት ምክንያት የኾነውን መዓርገ ክህነት ሰጥቶታል /ማቴ.፲፮፥፲፫-፲፱/፡፡

ይህም ሥልጣነ ክህነት በቅዱስ ጴጥሮስ አንጻር ከሐዋርያት ጀምሮ ለሚነሡ አባቶች ካህናት የተሰጠ ሰማያዊ ሀብት ነው፡፡ ዛሬ ምእመናን በኀጢአት ስንሰናከል ከካህናት ፊት ቀርበን የምንናዘዘውና ንስሐ የምንቀበለው፣ እንደዚሁም እየተባረክን ‹‹ይፍቱኝ›› የምንለው ጌታችን ለእነርሱ የሰጣቸውን ሥልጣነ ክህነት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ካህናትም ‹‹ይኅድግ ይፍታሕ ያንጽሕ ወይቀድስ …›› እያሉ ከናዘዙን በኋላ ‹‹እግዚአብሔር ይፍታ›› የሚሉን ከባለቤቱ የማሠር የመፍታት ሥልጣን ስለ ተሰጣቸው ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ስለ እርሱ የሚናገሩትንም፣ የሚያስቡትንም የሚያውቅ አምላክ ሲኾን በቂሣርያ ሐዋርያቱን ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል›› ብሎ መጠየቁ በአንድ በኩል አላዋቂ ሥጋን መልበሱን ለማጠየቅ፤ በሌላ ምሥጢር ደግሞ ሐዋርያቱን ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ›› ብሎ በመጠየቅ አምላክ ወልደ አምላክ መኾኑን ለመግለጥና መዓርገ ክህነትን ለሐዋርያትና ለተከታዮቻቸው (ለጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት) ለመስጠት ነው፡፡ ይህም በቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽና ጌታችን ለጴጥሮስ በሰጠው ሥልጣን ይታወቃል፡፡

በዚህ በተስእሎተ ቂሣርያ ጌታችን ሐዋርያቱ ማን እንደሚሉት ስለ ማንነቱ ከጠየቃቸው በኋላ ምላሻቸውን ተከትሎ ሥልጣነ ክህነትን መስጠቱ በብሉይ ኪዳን (እግዚአብሔር በሥጋ ከመገለጡ በፊት) አዳም የት እንዳለ እያወቀ ‹‹አዳም ሆይ ወዴት ነህ?›› /ዘፍ.፫፥፲/ ብሎ ከጠየቀውና ያለበትን እንዲናገር ካደረገው በኋላ ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚል የድኅንት ቃል ኪዳን መግባቱን ያስታውሰናል /ቀሌምንጦስ/፡፡

እንደዚሁም እግዚአብሔር በሦስትነቱ ከአብርሃም ቤት በገባ ጊዜ ሣራ ያለችበትን ቦታ እያወቀ አብርሃምን ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል ያለችበትን ቦታ ካናገረው በኋላ ‹‹ሣራ የዛሬ ዓመት ልጅን ታገኛለች›› የሚል በአንድ በኩል የይስሐቅን መወለድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና የሐዲስ ኪዳንን መመሥረት የሚያበሥር ቃል መናገሩ ከዚህ ትምህርት ጋር ተመሳሳይነት አለው /ዘፍ.፲፰፥፱-፲፭/፡፡

በሐዲስ ኪዳንም አልዓዛር በሞተ ጊዜ የተቀበረበትን ቦታ እያወቀ ‹‹አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት›› /ዮሐ.፲፩፥፴፯/ ብሎ መካነ መቃብሩን ከጠየቀ በኋላ በሥልጣኑ ከሞት እንዲነሣ ማድረጉም ከተስእሎተ ቂሣርያ ጋርና ከላይ ከጠቀስናቸው ምሳሌዎች ጋር የሚወራረስ ምሥጢር አለው፡፡ ይኼ ኹሉ ቃል እግዚአብሔር ያላወቀ መስሎ እየጠየቀ ሰዎች ስሜታቸውን እንዲገልጡ በማድረግ የልባቸውን መሻትና እምነት መሠረት አድርጎ ሥልጣንን፣ በረከትን፣ ጸጋንና ፈውስን እንደሚያድል የሚያስረዳ ትምህርት ነው፡፡ ለዚህም ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው በምድር በአካለ ሥጋ ሲመላለስ መዳን እንደሚፈልጉ እያወቀ ‹‹ልትድን ትወዳለህን? (ልትድኚ ትወጃለሽን?) ብሎ እየጠየቀ የልባቸውን መሻት እንዲናገሩ ካደረገ በኋላ እምነታቸውን አይቶ በአምላካዊ ቃሉ ‹‹ፈቀድኩ ንጻሕ /ንጽሒ፤ ፈቅጃለሁ ተፈወስ /ተፈወሺ›› እያለ ለሕሙማነ ሥጋ ወነፍስ ፈውስን ማደሉ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡

የእያንዳንዳችንን የልብ መሻት የሚያውቅ አምላክ እኛንም በቸርነቱ ከደዌ ሥጋ ወነፍስ እንዲፈውሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡