ተዝካረ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ

ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

Tkle

አቡነ ተክለ ሃይማኖት

በዛሬው ዝግጅታችን ነሐሴ ፳፬ ቀን የሚከበረውን በዓለ ዕረፍታቸውን ምክንያት በማድረግ ከቅዱሳን ጻድቃን መካከል አንዱ የኾኑትን፣ ‹‹ሐዲስ ሐዋርያ›› እየተባሉ የሚጠሩትን የቅዱስ ተክለ ሃይማኖትን ዜና ሕይወት በአጭሩ ይዘን ቀርበናል፤

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ፣ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት፤ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፪፲፪ ዓ.ም. በቡልጋ አውራጃ በደብረ ጽላልሽ ኢቲሳ ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስተኛውም ቀን እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፡- አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ስማቸውን ‹‹ፍሥሐ ጽዮን›› ብለዋቸዋል፡፡ በተወለዱ በ፲፭ ዓመታቸው ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ቅስናን ከግብፃዊው ጳጳስ ከአባ ጌርሎስ /ቄርሎስ/ ተቀብለዋል፡፡

አንድ ቀን ወደ ጫካ ለአደን በሔዱበት ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱ ክርስቶስ ተገልጦላቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱን ካሰደረባቸው፤ እንደዚሁም ‹ሐዲስ ሐዋርያ› ብሎ ወንጌል ወዳተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸው ከነገራቸው፤ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡና አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም ‹ተክለ ሃይማኖት› እንደሚባልና ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው›› እንደ ኾነ ካስረዳቸው በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ንብረት ኹሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ‹‹አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደ ተከፈተ ተውኩልህ›› በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አንጸዋል፡፡

ከዚህ በኋላ በደብረ ሊባኖስ (ገዳመ አስቦ) ዋሻ በመግባትም ሁለቱን በፊት፣ ሁለቱን በኋላ ሁለቱን በቀኝ፣ ሁለቱን በግራ ስምንት ጦሮችን ተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማም፣ ሞትና ነገረ መስቀል በማሰብ በተመስጦ ሌሊትና ቀን ያለማቋረጥ በጾም፣ በጸሎት ተወስነው ሲጋደሉ፤ ከቊመት ብዛት የተነሣ በ፺፪ኛ ዓመታቸው ጥር ፬ ቀን ፲፪፹፱ ዓ.ም አንዲቱ የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የመንፈሳዊ አባታቸውን ስባረ ዐፅም አክብረው በሥርዓት አኑረዋታል፡፡ እግራቸው እስኪሰበር የቆዩባቸው ዓመታትም ፳፪ ናቸው፡፡ ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው ቆመው ያለ ምግብና ያለ ውኃ በትኅርምት ሌሊትና ቀን እንደ ምሰሶ ጸንተው በትጋት ለሰው ዘር ኹሉ ድኅነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡

ከሰባቱ ዓመታት ውስጥ ጥቂት ውኃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ እንደ ነበረ መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡ ጻድቁ አባታችን ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ የሚያልፉበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደእርሳቸው በመምጣት የሚያርፉበት ዕለት መድረሱን ነግሯቸው የተጋድሏቸውን ጽናት አድንቆ በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ስለ ተጋድሏቸው ጽናትም ‹‹በሰው እጅ የማይለካውን ይህንን የመንግሥት አዳራሽ ውሰድ›› በማለት የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያለው የጸጋ ልብስ አልብሷቸዋል፤ በመስቀል ምልክት ያጌጡ ሰባት የሕይወት አክሊላትንም አቀዳጅቷቸዋል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖትም የዕረፍታቸው ጊዜ መቃረቡን ባወቁ ጊዜ የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ሁሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፉ፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም ለአንድ ቅዱስ አባትና ካህን በሚገባ ሥርዓት በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀበሯቸው፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችንና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾ ታያቸው፤ ነፍሳቸውንም ‹‹የጠራሽ፣ ንጽሕት ነፍስ ሆይ ወደእኔ ነዪ›› ብሎ በክብር ተቀብሏታል፡፡ በመጽሐፈ ገድላቸው እንደተጠቀሰው ቅዱስ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም የኖሩበት ዕድሜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከዐሥር ወር ከዐሥር ቀን ነው፡፡ ገድላቸው ዕድሜያቸውን በመከፋፈል፡- በእናት አባታቸው ቤት ፳፪ ዓመት፤ በከተታ ፫ ዓመት፤ በይፋት ፱ ወር፤ በዳሞት ፲፪ ዓመት፤ በአማራ ፲ ዓመት፤ በሐይቅ ፲ ዓመት፤ በደብረ ዳሞ ፲፪ ዓመት፤ በትግራይ ገዳማት በመዘዋወርና ወደ ኢየሩሳሌም በመመላለስ ፩ ዓመት፤ ዳዳ በሚባል አገር ፩ ወር፤ በደብረ አስቦ ገዳም ፳፱ ዓመት ከ፲ ቀን መቆየታቸውን ይናገራል /ገ.ተ.ሃ.፶፱፥፲፬-፲፭/፡፡

በአጠቃላይ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው በተጨማሪ እንደቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያችንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፡፡ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከተናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋው አይጠፋበትም›› /ማቴ.፲፥፵-፵፪/ በማለት የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን መሠረት አድርጋ መጋቢት ፳፬ ቀን ፅንሰታቸውን፤ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ልደታቸውን፤ ጥር ፳፬ ቀን ስባረ ዐፅማቸውን፤ ግንቦት ፲፪ ቀን ፍልሰተ ዐፅማቸውን ነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸውን በትላቅ ደስታ ታከብራለች፡፡

ቅዱሳን ጻድቃን በመንፈሳዊ አርአያነታቸው፣ በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከከበቡን የነፍስ ጠላቶች፤ ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፣ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመሰወርና ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምን ጊዜም ይሠራል፡፡ በጻድቃን መኖር ሀገር ከጥፋት ትድናለች፡፡ የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለ ጻድቃን ብሎ እግዚአብሔርም ምሕረቱን ያድላል፡፡ ጻድቃንን ማሰብ ሥራቸውን መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምሳል፡፡ በነፍስ በሥጋ ይታደገናል፤ ይረባናል፤ ይጠቅመናል፡፡ ስለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቃንን እንድናስባቸው፣ በስማቸውም ለድሆችና ለጦም አዳሮች እንድንመጸውት መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የምትመክረን፤ የምታስተምረን /ማቴ.፲፥፵፩-፵፪/፡፡ ጻድቃንን በሕይወተ ሥጋ ሳሉም ቢኾን፤ ከሞቱም በኋላ በዐጸደ ነፍስ በጸሎታቸው ለሚታመኑ፣ በቃል ኪዳናቸው ለሚማጸኑ፣ የድኅነተ ሥጋ፣ የድኅነት ነፍስ ምክንያቶች ናቸው፡፡

የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የኹሉም ጻድቃን ጸሎትና በረከት ረድኤትና ምልጃ በመላው ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ጸንቶ ይኑር፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

መለከት መጽሔት ፲፰ኛ ዓመት፣ ቍጥር ፱፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን፡፡

ገድለ ተክለ ሃይማኖት፡፡

ክብረ ድንግል ማርያም

ነሐሴ ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ታደለ ፈንታው

mariam[1]

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ጋር

እግዚአብሔር ዘላለማዊ ኃይሉንና አምላክነቱን ለዓለም ከገለጸበት ታላቅ ሥራ መካከል በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የገለጸው ድንቅ ሥራው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ይህንን ኹኔታ ድንግል ማርያም ‹‹ብርቱ የኾነ እርሱ ታላቅ ሥራን በእኔ አድርጓል፤ ስለዚህም ፍጥረት ኹሉ ያመሰግኑኛል›› /ሉቃ.፩፥፵፱/ በማለት ገለጸችው፡፡

ቅድስት ኤልሳቤጥም ‹‹የጌታዬ እናት›› አለቻት /ሉቃ.፩፥፵፫/፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ›› አላት /ሉቃ.፩፥፳፰/፡፡ ቅዱስ ዳዊት ደግሞ ‹‹ልጄ›› ይላታል /መዝ.፵፬፥፱/፡፡ ሰሎሞንም ‹‹እኅቴ›› ይላታል /መኃ.፭፥፩/፡፡ ለወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም እናት ኾና ተሰጥታዋለች /ዮሐ.፲፱፥፳፮/፡፡ ይህን ድንቅ ምሥጢር ውስንና ደካማ የኾነ አእምሮ ሊገነዘበው ከሚችለው በላይ ነው፡፡

ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንደገለጸው ‹‹የቅድስት ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና፤ አማኑኤልን መውለዷና የማይሞተው ጌታ መሞቱ›› እነዚህ ሦስቱ ከዚህ ዓለም ጥበበኞችና ገዢዎች የተሰወሩ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹እነዚህ ድንቅ ምሥጢራት በራሳቸው ከንግግርና ከቋንቋዎች ኹሉ በላይ ኾነው የሚነገሩ በእግዚአብሔር የዝምታ መጐናጸፊያ የተጠቀለሉ ድብቅና ጣፋጭ ምሥጢሮች ናቸው›› ይላል፡፡

የእመቤታችን ምስጋናዋ የበዛለት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም ‹‹አቤቱ መሰንቆ ልቡናዬን አነቃቃ፤ የልቤንም እንዚራ፡፡ ድምፁን ከፍ አድርጎ የዳዊት ልጅ የኾነችውን፣ የጌታውን እናት ድንግል ማርያምን ያመሰግናት ዘንድ፤ ለዓለም ሕይወት የሚሰጠውን የወለደች እናቱ የኾነች እርሷን ከፍ ከፍ ያደርጋት ዘንድ›› ብሏል፡፡ በሌላም አንቀጽ ደግሞ ‹‹ከሕሊናት ኹሉ በላይ ለኾነ ለዚህ ነገር አንክሮ ይገባል፡፡ ምድራዊት ሴት ፈጣሪዋን ወለደችው፤ እርሱም እናቱን ፈጠረ›› አለ፡፡ ስለእነዚህ ነገሮች ኹሉ ምን ማለትን እንችላለን? እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስለ ድንግል ማርያም ያልተናገረበት ጊዜ፤ ያላናገረው ቅዱስ እንደሌለ እንመለከታለን፡፡

‹‹በእግዚአብሔር፣ በመላእክትና በሰው ፊት የከበረ ሰው መታሰቢያው ለዘለዓለም ነው፡፡ በቤቱ በቅጥሩ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምን ይቀበላልና›› /ኢሳ.፶፭፥፫/፡፡ ይህንን ታላቅ በረከት እንደሚሰጣቸው የተናገረው የማይዋሸው ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ወልድ እናት ከድንግል ማርያም የበለጠ በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ማንን ልንጠራ እንችላለን? እንደ እርሷስ ሊታሰብ፣ ሊከበርም የሚችል በቅድስና ሕይወት ያለፈ ማን ይኖራል?

ቅዱስ እግዚአብሔር ፍጥረቱንና ዓለሙን ለማዳን የወሰነው ጊዜ በደረሰ ጊዜ ከድንግል ማርያም በድንግልና ተወለደ፡፡ አስቀድሞ በመልአኩ አፍ እንዳናገረ ክብሩ በእርሷ ላይ ታየ /ኢሳ.፷፥፪/፡፡ ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በእርስዋ አደረ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእመቤታችን ላይ የማደሩ ምሥጢር ያነጻቸው፤ ይቀድሳቸው፤ በሥጋም በነፍስም መርቶ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ያገባቸው ዘንድ በነቢያት፣ በሐዋርያት ላይ እንዳደረው ዓይነት አይደለም፡፡ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ (ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ) ከሥጋዋ ሥጋን፣ ከነፍስዋ ነፍስን ነስቶ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ ኾነ እንጂ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ይህን ዘለዓለማዊ እውነት ‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል፡፡ ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል›› በማለት ገልጾታል /ሉቃ.፩፥፵፭/፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ደራሲና ገጣሚ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም ‹‹የእስራኤል ንጉሥ በእስራኤል ልጅ አደረ፤ የዳዊት አምላክ ከዳዊት ልጅ ሥጋን ለበሰ፡፡ የዕብራውያን ጌታ በዕብራውያን ልጅ ማኅፀን ተወሰነ፡፡ ለአብርሃም የዕብራይስጥ ልሳን ያስተማረው ከቀድሞም ያልሰማውን ልሳን እንዲናገር አፉን ጆሮውን የከፈተለት ከዕብራዊት ድንግል ተወለደ፤ በድንግልና ወተት ጥቂት ጥቂት እያለ አደገ፡፡ የሕፃናትን ሥርዓት እንዳያጎድል አፉን የሚፈታባት ዘመን እስኪፈጸም ጥቂት ጥቂት እያለ በዕብራይስጥ ልሳን ሲናገር ኖረ፡፡ ለሙሴ በዕብራይስጥ ልሳን በጣቶቹ የተጻፉትን ዐሠርቱ ቃላትን የሰጠ የዕብራይስጥ ፊደል ለመማር ከመምህር እግር በታች ተቀመጠ፡፡ የባቢሎን አውራጃ በምትኾን ሰናዖርም የፍጥረትን ሁሉ ቋንቋ የበተነ እርሱ የአሕዛብን ቋንቋ እንደማያውቅ ኹሉ እናቱ አፍ በፈታችበት ልሳን በዕብራይስጥ ልሳን ሲናገር ኖረ፡፡ ጆሮ ይህንን ነገር ከመስማት የተነሣ የሚለመልምበት ይህ ነገር ዕፁብ ድንቅ ነው፡፡ ለዚህ አንክሮ ይገባል›› አለ፡፡ ይህ በሰው ጥበብ በብራናና በቀለም የተጻፈ እውነት ሳይኾን ለድኅነት በተጠሩ ሰዎች ሁሉ ልቡና በአምላክ ጥበብ የተጻፈ እውነት ነው፡፡

የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ይደርብን፤ የልጇ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክረስቶስ ጸጋ ይብዛልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

በዓለ ፍልሰታና ሻደይ

ነሐሴ ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በሰቆጣ ማእከል

ሻደይ

ልጃገረዶች የሻደይን በዓል ሲጫወቱ

በአገራችን ኢትዮጵያ በተለይ በሰሜኑ ክፍል ሕዝበ ክርስቲያኑ ለረጅም ዘመናት ሥርዓተ አምልኮ ሲፈጸሙባቸው የነበሩና አሁንም እየተፈጸመባቸው የሚገኙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ መንፈሳውያን ቅርሶች በርካቶች ናቸው። ከእነዚህ ቅርሶች መካከልም መንፈሳውያን በዓላት የሚከበሩበት ሥርዓት አንደኛው ነው፡፡ ከእነዚህ መንፈሳውያን በዓላት ውስጥ በዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ምእመናን ዘንድ የሚከበረው የሻደይ ምስጋና (ጨዋታ) ልጃገረዶች በአማረ ልብስ ደምቀው ‹‹አሸንድዬ›› በሚባል የቄጠማ ጉንጉን ወገባቸውን አሥረው እየተጫወቱ የሚያከብሩት በዓል ነው።

ከነሐሴ ፲፮ እስከ ነሐሴ ፳፩ ቀን ድረስ የሚከበረው ይህ በዓል በዋግ ኽምራ ‹‹ሻደይ››፣ በላስታ ‹‹አሸንድዬ››፣ በትግራይ ‹‹አሸንዳ››፣ በቆቦ አካባቢ ‹‹ሶለል››፣ በአክሱም አካባቢ ደግሞ ‹‹ዓይነ ዋሪ›› እየተባለ ይጠራል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የሻደይ በዓል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ አለው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና እንደሚናገሩት የአዳም ከገነት መባረር፣ የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ፣ የዘመን መለወጫ፣ የመጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንገት መቈረጥ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ (ፍልሰታ) እና የመሥፍኑ ዮፍታሔ ልጅ ታሪክ ከሻደይ በዓል ተያያዥነት ያላቸው ሲኾን በተለይ የእመቤታችን ትንሣኤ (በዓለ ፍልሰታ) ከሻደይ በዓል ጋር የጎላ ግንኙት እንዳለው የቤተ ክርስቲያን መምህራንና የአገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ እያንዳንዱ ታሪክ ከሻደይ በዓል ጋር ያለውን ግንኙነት በአጭሩ እንመልከት፤

የአዳም ከገነት መባረር

አባታችን አዳም ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፉ ጸጋ እግዚአብሔር ርቆት እርቃኑን በኾነ ጊዜ አካሉን ለመሸፈን የበለስ ቅጠል ማገልደሙን ለማስታዎስና አዳምና ሔዋን ክብራቸውን ተገፈው ከገነት የተባረሩባትን ዕለት ለማሰብ በወቅቱ ያገለደሙትን ቅጠል በምልክትነት በመውሰድ ልጃገረዶች የሻደይ ቅጠልን በገመድ ላይ ጎንጉነው በወገባቸው አገልድመው ያሥራሉ፡፡ አዳምና ሔዋን ከገነት ከመውጣታቸው በፊት ግብረ ሥጋ ግንኙነት ያልጀመሩ ደናግላን ስለነበሩ ያንን በመከተልና በምሳሌነት በመውሰድ ያላገቡ የአገው ልጃገረዶች ተሰባስበው የሻደይ ጨዋታን መጫወት ወይም ማክበር እንደጀመሩ ይነገራል።

የሻደይ በዓልና የጥፋት ውኃ

በኖኅ ዘመን ከተላከው የጥፋት ውኃ በኋላ ውኃው መጕደሉንና አለመጕደሉን እንድታጣራ ኖኅ ርግብን በላካት ጊዜ በምድር ሰላም መኾኑን የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ በመምጣት ለኖኅ የምሥራች ነግራዋለች። ከዚሁ ጋር በተገናኘ በዓሉን ያንን ለምለም ቅጠል ወገባቸው ላይ በማሰር ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋገርን ሲሉ ማክበር እንደጀመሩ አበው ከታሪኩ ጋር አያይዘው ያስቀምጡታል።

የሻደይ በዓልና የመሥፍኑ ዮፍታሔ ልጅ ታሪክ

ዮፍታሔ ወደ ጦርነት በሔደ ጊዜ በድል ከተመለሰ ወደ ቤቱ ሲመለስ መጀመሪያ የሚቀበለውን ሰው እንደሚሠዋ ስእለት ተስሎ ነበር፡፡ ድል አድርጎ ሲመለስም ያለ ወትሮዋ ልጁ እየዘፈነች ልትቀበለው ወጣች፤ በዚህም በጣም አዘነ። ልጁም ለአምላኩ የገባውን ስእለት እንዳያስቀር ብላ ሁለት ወር ስለ ድንግልናዋ አልቅሳ ስእለቱን እንዲፈጽም ጠይቃው ከሁለት ወር በኋላ ልጁን ሠውቷታል፡፡ አባቷ የገባውን ቃል ኪዳን እንዳያጥፍ በማበረታታት በመሥዋዕትነት የቀረበችውን የዮፍታሔን ልጅ በማሰብ በየዓመቱ እየተሰባሰቡ ሙሾ ያወጣሉ፡፡

የልጃገረዶች የቡድን አመሠራረት

በሻደይ በዓል የልጃገረዶች የቡድን አመሠራረት ደብርን (አጥቢያን) መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የሻደይ ጨዋታ በዓል በሚያከብሩበት ጊዜ ልጃገረዶች የተለያዩ ባሕላዊ አልባሳትን ለብሰው ከበሮ እና ለምስጋና የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማሟላት ተጠራርተው በመጀመሪያ ወደ አጥቢያቸው በመሔድ የቤተ ክርስቲያኑን በር አልፈው ዘልቀው ጣዕመ ዝማሬ እያሰሙ ሦስት ጊዜ ይዞሩና ደጃፉን ተሳልመው በቅጥር ግቢው አመቺ ቦታ ፈልገው ምስጋናቸውን ይጀምራሉ፡፡

ከበሯቸውን እየመቱ፣ የታቦቱን ስም እየጠሩ በሚያምር ድምፃቸው፣ ሽብሻቦ፣ ውዝዋዜ፣ ጥልቅ መልእክትን በያዙ ግጥሞች፣ ለዚህ ያደረሳቸውን አምላክና ታቦት ያወድሳሉ፣ ያሞግሳሉ፣ ያከብራሉ፣ ያመሰግናሉ፡፡ ምስጋናው ለዚህ ዓመት ያደረሳቸውን አምላክ ቀጣዩ ዓመትም እንደዚሁ የሰላም፣ የጤና የተድላ እንዲኾን የሚማጸኑበት፣ ተስፋቸውን የሚገልጹበትና ስእለት የሚሳሉበት በመኾኑ ምስጋናቸውን ሞቅ፣ ደመቅ አድርገው በአንድነት፣ በፍቅር፣ በደስታ፣ በመተሳሰብና በሰላም ይጫወታሉ፡፡ ‹‹ለእግዚአብሔርና ለደብራችን ታቦት ያልኾነ›› እያሉ ጉልበታቸውን፣ ችሎታውንና ልምዳቸውን ሳይቈጥቡ በምስጋናው ይሳተፋሉ።

ከቤተ ክርስቲያን መልስ በአካባቢው ወዳሉት ታላላቅ አባቶች ዘንድ ሔደው በመዘመር ቡራኬ ይቀበላሉ። ከዚያም ተመልሰው ወደ ተራራማ ሥፍራ በመውጣት ክብ ሠርተው ይዘምራሉ፡፡ የዝማሬዎቻቸው ግጥሞችና ዜማዎችም መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውና ከግለሰባዊ ስሜት ወይም ከግለሰብ ውዳሴ የራቁ ናቸው፡፡ አጥቢያቸውን እንደማያስደፍሩና እንደሚጠብቁ በምስጋናቸው ይገልጻሉ፡፡ የወከሉትን ደብር ታቦት ስም እየጠሩ ለአባት እናት፣ ለቤተሰብ ጤና፣ ጸጋ፣ ሀብት፣ ሰላም በአጠቃላይ መልካሙን ኹሉ እንዲያደርግላቸው እግዚአብሔርን ይማጸናሉ፡፡

የምስጋናቸው ዜማና ግጥም ተመሳሳይ ቢኾንም የወከሉትን ደብር ስም ብቻ በማቀያየር በተመሳሳይ ዜማ ማወደስ እና መማጸን በኹሉም የሻደይ ተጨዋች ቡድኖች ይስተዋላል፡፡ ልጃገረዶቹ በዚህ የምስጋና ጊዜ የሚሰበስቧቸውን ስጦታዎችም ለቤተ ክርስቲያን ያበረክታሉ።

የሻደይ በዓልና ፍልሰታ

የሻደይ በዓል አጀማመርን በተመለክተ ከላይ ከተቀመጡት ታሪኮች በተጨማሪ በአካባቢው ሕዝብና በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ተደጋግሞ የሚነሣው ታሪክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ በዓል ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአዳምና ሔዋን ከአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት በኋላ ወደዚህ ዓለም አንድያ ልጁን ልኮ ከኀጢአት እሥራት ነጻ እንደሚያወጣቸው በገባላው ቃል ኪዳን መሠረት አምላክ የተወለደባት እና ትንቢቱ የተፈጸመባት፣ ከገነት የተባረረው የሰው ልጅ ወደ ገነት እንዲመለስ ምክንያት የኾነችው፣ የሰው ልጆች መመኪያ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም ድካም ካረፈች በኋላ ሞትን ድል አድርጋ ከመቃብር ተነሥታ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡

በፍልሰታ ወቅት በዓሉ መከበሩም ለሻደይ ተጨዋቾች ተምሳሌትና የድንግልናቸው አርአያ የሚያደርጓት ድንግል ማርያም አካላዊ ሥጋዋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፤ እንደዚሁም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ምክንያት በማድረግ እንደኾነ የሚገልጹት የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል መምሪያ ሓላፊ መጋቤ ምሥጢር ገብረ ሕይወት ኪዳነ ማርያም ‹‹የሻደይ በዓል በልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ የኾነው በሔዋን ምክንያት የተዘጋው ገነት በእመቤታችን አማካኝነት በመከፈቱ ነው። እመቤታችን መመኪያቸው ስለ ኾነች ልጃገረዶች በዓሉን በደስታ ያከብሩታል፤ ድንግልናቸውንም አደራ የሚሉት ለእርሷ ነው›› ሲሉ ይናገራሉ።

እመቤታችን በነሐሴ ፲፮ ቀን በቅዱሳን መላእክት ሽብሸባ፣ ዕልልታና ዝማሬ ታጅባ ከምድር ወደ ሰማይ ስታርግ ሐዋርያት በታላቅ ደስታ ይመለከቱ፣ ይደነቁም ነበር፡፡

ደናግልም ከቅዱሳን መላእክት ከተመለከቱት ሥርዓት በመነሣት ነጫጭ ልብሶችን ለብሰው፣ አምረውና አጊጠው፣ ረጃጅምና ለምለም ቅጠል በወገባቸው አሥረው  እንደ መላእክቱ አክናፍ ወገባቸውን ከግራ ወደ ቀኝ እያመላለሱ፣ እያዘዋወሩና እያሸበሸቡ፣ በአንደበታቸው እየዘመሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ በአንድነት ተሰባሰባስበው በፍቅርና በሐሴት የወቅቱ መታሰቢያ የኾነውን የሻደይን በዓል ያከብራ፡፡

እናቶችና እኅቶች በዐደባባይ ወጥተው የድንግል ማርያምን ትንሣኤና ዕርገት እንደ ነጻነታቸው ቀን በመቍጠር ከበሮ አዘጋጅተው ‹‹አሸንድዬ›› የተባለውን ቄጠማ በወገባቸው ታጥቀው ምስጋና በማቅረብ በዓሉን ይዘክራሉ፡፡

በአጠቃላይ የሻደይ ጨዋታ የፍልሰታ በዓል መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በምእመኑ ዘንድ ለበርካታ ዓመታት እየተከበረ የኖረ ሃይማኖታዊ በዓል ነው፡፡ ይህንን ሃይማኖታዊ መሠረትነት ያለውን ትውፊት የመጠበቅና የማስጠበቅ ሓላፊነት ከኹላችንም ይጠበቃል። የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም›› /መዝ.፻፴፩፥፰/

ነሐሴ ፲፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በመ/ ሳሙኤል ተስፋዬ

St.Marry

የእመቤታችንን መቀብርና ከሞት ተነሥታ ማረጓን የሚሳይ ሥዕል

እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ስደትህን በስደቴ፣ ሞትህን በሞቴ አጥፍቼ፤ የቀደመ ክብርህን መልሼ ያጣኸውን ርስት፣ ገነትን (መንግሥተ ሰማያትን) አወርስሃለሁ›› በማለት ለአባታችን አዳም የገባው ቃል ኪዳን /ገላ.፬፥፬/ ፍጻሜው በደረሰ ጊዜ ለእግዚአብሔር ወልድ ማደሪያነት የተመረጠች፣ ለአዳም እና ለዘሩ መዳን ምክንያት የኾነች ‹‹የልጅ ልጅ›› የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዳ ፲፭ ዓመት ሲኾናት በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት የእግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ማደሪያ ኾነች፡፡ ልጇን በወለደች ወቅት የሰብአ ሰገልን ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ›› የሚለውን ዜና የሰማ ሄሮድስ ሕፃኑን ለመግደል ዐዋጅ ዐወጀ፡፡ እመቤታችንም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማዳን ወደ ግብጽ ይዛው ተሰደደች /ማቴ.፪፥፲፪/፡፡

የስደቱ ዘመን አልቆ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ በኋላም ኢየሱስ ክርስቶስ ፴ ዓመት ሲኾነው ስለ መንግሥተ ሰማያትና ስለ ሰው ልጆች ነጻነት ይሰብክ ጀመር፡፡ ከዚህ በኋላ የአዳምና የዘሩን ሞት ለማጥፋት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ፤ በሦስተኛው ቀን ተነሥቶ፣ ባርነትን አስወግዶ ለሰው ልጅ ነጻነትን ዐወጀ፡፡

በዚህ ኹሉ የድኅነት ጉዞ ውስጥ ያልተለየችና ምክንያተ ድኂን የኾነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደች በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ዐርፋለች፡፡ ይህን የእመቤታችን ሞት የሚያስደንቅ መኾኑን ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ኹሉ የተገባ ነው፡፡ የማርያም ሞት ግን ኹሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን የከበረ ሥጋዋን ገንዘውና ከፍነው ለማሳረፍ ወደ ጌቴሴማኒ መካነ ዕረፍት (የመቃብር ቦታ) ይዘው ሲሔዱ አይሁድ በቅናት መንፈስ ተነሳሥተው «ቀድሞ ልጇን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ፤ በዐርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል›› እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ እርሷንም እንደ ልጇ ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን? ኑ! ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት» ብለው ተማከሩ፡፡

ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የከበረ ሥጋዋን የተሸከሙበትን አጎበር (የአልጋ ሸንኮር) በድፍረት ያዘ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሰይፍ ሁለት እጆቹን ቆረጣቸው፡፡ እጆቹ ተንጠልጥለው ከቆዩ በኋላ በእውነት የአምላክ እናት ናት በማለት ስለ አመነ እጆቹ ተመልሰው እንደነበሩ ሆነውለታል፡፡ ከዚህ በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ  ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሐዋርያት ሲመጣ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ በገነት መኖሩን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አግኝተው  ለመቅበር በነበራቸው ምኞትና ጉጉት ‹‹ዮሐንስ አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን? ብንጠየቅስ ምን እንመልሳለን?›› በማለት በነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ ጀምረው ሲጾሙና ሲጸልዩ ከሰነበቱ በኋላ በሁለተኛው ሱባዔ መጨረሻ (ነሐሴ ፲፬ ቀን) ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ የከበረ ሥጋ አምጥቶ ሰጥቷቸው በታላቅ ዝማሬና ውዳሴ በጌቴሴማኒ ቀብረውታል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዐት ሲፈጸም አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን  እንደ ልጇ ተነሥታ ስታርግ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቀድሞ የልጅሽን፣ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ›› ብሎ ቢያዝን እመቤታችን ከእርሱ በቀር ሌሎች ሐዋርያት ትንሣኤዋን እንዳላዩ ነግራ አጽናናችው፡፡ ወደ ምድር ወርዶ የኾነውን ኹሉ ለሐዋርያት እንዲነግራቸው አዝዛው፣ ለምልክት ይኾነው ዘንድም የተገነዘችበትን ሰበኗን ሰጥታው ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡

ቅዱስ ቶማስም ሐዋርያት ወደ አሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ «የእመቤታችን ነገር እነዴት ኾነ?»  ብሎ ቢጠይቃቸው፤ «እመቤታችንን እኮ ቀበርናት» ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም ዐውቆ ምሥጢሩን ደብቆ «አይደረግም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር  እንደምን ይሆናል?» አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ መጠራጠር ልማድህ ነው፡፡ ቀድሞ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንም›› ብሎ  የእመቤታችን መካነ መቃብር ሊያሳዩት ይዘውት ሔዱ፡፡ መቃብሩን ቢከፍቱ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አጡት፤ ደነገጡም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሥታ ዐርጋለች» ብሎ  የኾነውን ኹሉ ተረከላቸውና የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ እነርሱም ማረጓን አምነው ሰበኗን ለበረከት ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሔዱ፡፡ በየሀገረ ስበከታቸውም ሕሙማንን ሲፈውሱበትና ገቢረ ተአምር ሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡

በዓመቱ ‹‹ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እንዴት እኛ ይቅርብን?›› ብለው ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ ሱባዔ ገብተው ነሐሴ ፲፮ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልመናቸውን ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ (ረዳት) ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሠናይ (ዋና) ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ አቍርቧቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ እመቤታችንን ሐዋርያት በግልጽ ትንሣኤዋን ዕርገቷን እያዩዋት ከጌታችን ጋር በክብር በይባቤና በዝማሬ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ «እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች በሰማይም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች» እንዳለ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ትንሣኤ ጊዜያዊና ዘለዓለማዊ በመባል ይታወቃል፡፡ ጊዜያዊ ትንሣኤ የሚባለው የእግዚአብሔር ከሃሊነት የሚገለጽበት ተአምራዊ ሥራ ኾኖ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የሚፈጸምና ዳግም ሞትን የሚያስከትል ነው፡፡ ለምሳሌ ኤልያስ ያስነሣውን ወልደ መበለት /፩ኛነገ. ፲፯፥፰-፳፬/፤ ዐፅመ ኤልሳዕ ያስነሣውን ሰው /፪ኛነገ. ፲፫፥፳-፳፩/፤ ወለተ ኢያኢሮስን /ማቴ.፱፥፰-፳፮/፤ በዕለተ ስቅለት ከመቃብር ወጥተው በቅድስት ከተማ የታዩ ሙታንን /ማቴ. ፳፯፥፶፪-፶፫/፤ በቅዱስ ጴጥሮስ ጸሎትና ምልጃ የተነሣችዋን ጣቢታን /ሐዋ.፱፥፴፮-፵፩/፤ እንደዚሁም ትንሣኤ አልዓዛርን መጥቀስ ይቻላል /ዮሐ.፲፩፥፵፫-፵፬/፡፡ እነዚህ ኹሉ ለጊዜው ከሞት ቢነሡም ቆይተው ግን ተመልሰው ዐርፈዋል፡፡ ወደፊትም ትንሣኤ ዘጉባኤ ይጠብቃቸዋል፡፡

የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ግን የክብርና የሕይወት ትንሣኤ ሲኾን ሁለተኛ ሞትን አያስከትልም፤ ትንሣኤ ዘጉባኤንም አይጠብቅም፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኵር ኾኖ በሞተ በሦስተኛው  ቀን ተነሥቷል፡፡ እመቤታችንም በልጇ ሥልጣን፤  እንደ ልጇ ትንሣኤ በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳትጠብቅ በክብር ዐርጋለች፡፡  እንደዚህ ያለውን ትንሣኤ ከእርሷ በቀር ሌሎች ቅዱሳን ወይም ነቢያትና ሐዋርያት አላገኙትም፡፡ በዚህም ኹኔታ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ከማናቸውም ትንሣኤ ልዩ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ትንሣኤ ዘለዓለማዊ የኾነ ከዳግም ሞተ ሥጋ ነጻ የኾነ ትንሣኤ ነው፡፡

ይህ የእመቤታችን ዕርገት በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው ከእነ ሄኖክና ኤልያስ ዕርገት የተለየ ነው፡፡ «ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም» ተብሎ እንደ ተጸፈ /ዕብ ፲፩፥፭/፣ ሄኖክ ወደ ሰማይ ያረገው በምድር ሳለ እግዚአብሔርን በእምነቱና በመልካም ሥራው ስላስደስተና በሥራውም ቅዱስ ኾኖ ስለ ተገኘ ሞትን እንዳያይ ሲኾን ወደፊትም ገና ሞት ይጠብቀዋል፤ ሞቶም ትንሣኤ ዘጉባኤ ያስፈልገዋል፡፡ ነቢዩ ኤልያስም በእሳት ሠረገላም ቢነጠቅም /፪ኛነገ.፪፥፲/ ወደፊት ሞት ይጠብቀዋል፤ ትንሣኤ ዘጉባኤም ያስፈልገዋል፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በትንቢቱ «ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅድስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም» /መዝ.፻፴፩፥፰/ በማለት አስቀድሞ የክርስቶስን ትንሣኤ ከገለጸ በኋላ ቀጥሎ የመቅደሱ ታቦት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ከሞት እንደምትነሣ ተናግሯል /ማቴ.፭፥፴፭፤ ገላ.፬፥፳፮፤ ዕብ. ፲፪፥፳፪፤ ራእ.፫፥፲፪/፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ‹‹በቃልዋ የታመነች፣ በሥራዋም የተወደደች ቅድስት ድንግል ማርያምን መላእክት እያመሰገኗትና በመንፈሳዊ ደስታ እያጀቧት ወደ ሰማይ አሳረጓት›› ሲል እንደ ገለጸው፣ በመጽሐፈ ስንክሳርም እንደ ተመዘገበው ቅዱስ ዳዊት ‹‹በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ፣ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች›› /መዝ.፵፬፥፱/ በማለት የተናገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ አባቷ ዳዊት በበገና፣ ነቢዩ ዕዝራ በመሰንቆው እያመሰገኗት፤ በቅዱሳን መላእክት፣ በቅዱሳን ነቢያትና ጻድቃን ዝማሬ በብሩህ ደመና ወደ ሰማይ ዐርጋ በክብር ተቀምጣለች፡፡ በዚያም ሥፍራ ሁለተኛ ሞት ወይም ኀዘን፣ ጩኸትና፣ ስቃይ የለም፡፡ የቀደመው ሥርዐት አልፏልና /ራእ.፳፩፥፬-፭/፡፡

ስለዚህም የእመቤታችን ዕረፍቷ፣ ትንሣኤዋና ዕርገቷ በሚታሰብበት በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት ምእመናንን ከአካባቢያቸው ራቅ ብለው በተለያዩ ገዳማትና አድባራት በመሔድ አለዚያም በየአጥቢያቸው በመሰባሰብ እመቤታችን በተለያዩ ጊዜያት ሞቷንና ትንሣኤዋን ለሐዋርያት የገለጸችበትን ኹኔታ ያስባሉ፡፡ በጾም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት የድንግልን አማላጅነት በእምነት ኾነው ይማጸናሉ፡፡ እንደዚሁም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነሐሴ ፲፮ ቀን እናቱን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳዒ ካህን፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ ሐዋርያትንም እመቤታችንንም ማቍረቡን በመዘከር ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ሱባዔው ሲፈጸምም «በእውነት ተነሥታለች» እያሉ በደስታ የጾሙን ወቅት ይፈጽማሉ፡፡

የእመቤታችን አማላጅነት፣ የትንሣኤያችን በኲር የኾነው የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት ከኹላችን ጋር ይኹን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

አስደናቂው የድንግል ማርያም ሞትና ትንሣኤ

ነሐሴ ፲፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ታደለ ፈንታው

St.Merry

እመቤታችን ከሙታን ተነሥታ በክብር እንዳረገች የሚያሳይ ሥዕል

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የጌታ ልደቱና ጥምቀቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና ዳግመኛ መምጣቱ በነገረ ድኅነት ትምህርታችን እጅግ ጠቃሚ የኾኑ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ቤተልሔም የሥጋዌውን ምሥጢር ሲያሳይ ዮርዳኖስ ቀዳማዊ ልደቱን ያሳያል፡፡ የመጀመርያው የእኛ ባሕርይ ሲኾን ሁለተኛው የጌታ የራሱ የባሕርይ ገንዘቡ የኾነ ነው፡፡ እርሱ የሰው ልጅ ኾነ፤ እኛ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ኾንን፡፡ ይህ ኹሉ የተደረገው ከድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ ነው፡፡ እርሱ የእኛን ተፈጠሮ ገንዘቡ ስላደረገ፤ እኛ ደግሞ የእርሱን ቅድስና ገንዘብ በማድረግ የመንግሥቱ ተካፋዮች ለመኾን በቃን፡፡ በእርሷ ምክንያት የእኛ የኾነው ኹሉ የእግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር የኾነው የእኛ ኾኗል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ እናደርገዋለን፤ ለዚህ ክብር በቅታ ያከበረችንን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያዛመደችንን እመቤታችንንም እናከብራታለን፡፡

እርስዋ ከኪሩቤል ትበልጣለች፤ ከሱራፌልም ትከብራለች፡፡ ጌታችን የሱራፌልን፣ የኪሩቤልን ባሕርይ ባሕርዩ አላደረገም፡፡ የመላእክትንም ባሕርይ እንደዚሁ፤ የእርሷን አካል ባሕርዩ አደረገ እንጂ፡፡ የእኛ መንፈሳዊ ልደት የተገኘው ጌታ በሥጋ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው ልደት ነው፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን አምላክና የሰው ልጆች የተገናኙበት፤ አምላክና ሰው የተዋሐዱበት መካነ ምሕረት ነው፡፡ እግዚአብሔር ዙፋኑን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀናት የዘረጋበት መካነ ሰላም ነው፡፡ የእግዚአብሔር ዙፋን ፍጹም በማይናወጥና ጸጥታ በነገሠበት ሥፍራ የሚዘረጋ የክብር ዙፋን ነው፡፡ ይህም ዙፋን የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ነው፡፡

ድንግል ማርያም በአባት በእናቷ ቤት ሦስት ዓመት፤ በቤተ መቅደስ ዐሥራ ሁለት ዓመት፤ ከልጇ ጋር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር፤ ከጌታችን ስቅለት በኋላ ደግሞ ዐሥራ አምስት ዓመታት በምድር ኖራለች፡፡ ጌታን የፀነሰችበትን ወራት ስንጨምር በዚህ ዓለም በሥጋ የቆየችበት ጊዜ ስድሳ አራት ዓመት ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ አርጋኖን ድርሰቱ ‹‹ከሚያሰጥመው ባሕር ሞገድ የተነሣ የማትነቀነቅ፣ መልኅቆቿም በሦስቱ ሥላሴ ገመድ የተሸረቡ ናቸው ይህቺ ደግሞ ከነፋሳት ኃይል የተነሣ የማትናወጥ በጭንጫ ላይ ያለች የዕንቈ ባሕርይ ምሰሶ ናት፤ እርሷን የተጠጋ መውደቅ መሰናከል የለበትም›› የሚላት እመቤታችን ሞት አይቀርምና እርሷም እንደሰው የምትሞትበት ጊዜ ደርሶ ጥር ሃያ አንድ ቀን ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ዐርፋለች፡፡ እግዚአብሔር አያደላምና /ሮሜ.፪፥፲፩/፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም የኃያሉ እግዚአብሔር እናቱ፣ መቅደሱ፣ ታቦቱ፣ መንበሩ ኾና እያለ ሞትን መቅመሷ በራሱ የሚያስገርም ምሥጢር ነው፡፡ የዚህ ከኅሊናት ኹሉ በላይ የኾነው የእመቤታችን ዕረፍትም እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፤ ‹‹ለምንት ይዜኃር ኃያል በኃይሉ ወባዕል በብዝኃ ብዕሉ ኢያድለወ ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ፡፡ ኃይለኛ በኃይሉ ለምን ይታጀራል? ባለ ጸጋም በሀብቱ ብዛት፡፡ ክርስቶስ ለአካሉ አላደላም፡፡ ሞትስ ለሟች ይገባዋል፤ የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ሞት ግን አስደናቂ ነው›› /መጽሐፈ ዚቅ/፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ ‹‹ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነይ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፤ ዝናሙም አልፎ ሔደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቍርዬም ቃል በምድር ላይ ተሰማ፤›› /መኃ.፪፥፲-፲፬/፡፡ ይህ ትንቢት የዚህ ዓለም ድካሟ ኹሉ መፈጸሙን ያስረዳል፡፡ ልጇን ይዛ ከአገር ወደ አገር በረሀብና ጥም የተንከራተተችበት ጊዜ አሁን አለፈ፡፡ ታናሽ ብላቴና ሳለች ልጇን አዝላ በግብጽ በረሃ የተቀበለችው መከራ ኹሉ ፍጻሜ አገኘ፡፡ ከእግረ መስቀል ሥር ወድቃ የልጇን የቈሰለ ገላ እየተመለከተች የደረሰባት ልብ የሚሰነጥቅ ኀዘን ወደ ደስታ ተለወጠ፡፡ ‹‹በነፍሷ ሰይፍ ያልፋል›› ተብሎ የተነገረው ልብ የሚሰነጥቅ መከራ እንደ ነቢዩ ቃል ትንቢት የሚቀጥልበት ጊዜ ተፈጸመ፡፡

የቤተ ክርስቲያን ትውፊት የድንግል ማርያም ሞት በሚከተሉት ምክንያቶች እንደ ኾነ ያስረዳል፤ የመጀመሪያው ‹‹ለመለኮት ማደርያ ለመኾን የበቃችው ኃይል አርያማዊት ብትኾን ነው እንጂ እንደ ምድራዊት ሴትማ እንደምን ሰማይና ምድር የማይችለውን አምላክ ልትሸከመው ይቻላታል?›› የሚሉ ወገኖች ነበሩና እግዚአብሔር ወልድ የተዋሐደው የሰው ልጆችን ሥጋ መኾኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲያስረዳ ‹‹እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፣ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፡፡ በሕይወታቸው ኹሉ ስለሞት ፍርሃት በባርነት ይታሠሩ የነበሩትን ኹሉ ነጻ እንዲያወጣ፣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም›› አለ /ዕብ.፪፥፲፬-፲፭/፡፡ በዚህም ድንግል ማርያም የአዳም ዘር መኾኗ ታወቀ፡፡ ሁለተኛው ቅዱስ ያሬድ እንደተናገረው ጌታችን በፍርዱ አድልዎ የሌለበት መኾኑ ይታወቅ ዘንድ ነው፡፡ ሥጋ የለበሰ ኹሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ የግድ ነውና፡፡

እመቤታችን ባረፈች ጊዜ ሐዋርያት ሊቀብሯት ሲሹም ከአይሁድ ክፋት የተነሣ ልጇ ሌላ ክብርን ደረበላት፡፡ ከጌቴሴማኒ ሥጋዋ ተነጥቆ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር እስከ ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይታለች፡፡ ልጇ ወዳጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሥልጣኑ እንዳሸነፈ የልጇ መለኮታዊ ኃይል ሞትን አሸንፋ እንድትነሣ አደረጋት፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ስለ ትንሣኤዋ የተናገረው ቃል ተፈጸመ፡፡ ሊቁ ‹‹ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ ወአግዓዛ እምእኩይ ውስተ ሠናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ በድንግል ማርያም ላይ የአብ የባለጸግነቱ ብዛት ተገለጠ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከክፉ ዓለም ወደ በጎ ዓለም አሸጋግሯታልና›› ሲል የተነጋረውም ይኼንን ምሥጢር የሚገልጽ ነው፡፡

ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና ከሞት ወጥመድ በላይ እንኳን የኾነ ሌላ ኃይል አለ፤ ይኼውም ሞት ፈጽሞ ሊያሸንፈውና ሊገዳደረው የማይችል የእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይል ነው፡፡ ሕያው የኾነው እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነውና ሞት ሊያሸንፈው፣ ሊደርስበትም የማይችለውን ሕይወት ይሰጣል፡፡ ይህንን እርሱ የሚሰጠውን ሕይወት ሰይጣን በእጁ ሊነካው ከቶውንም አይችልም፡፡ ከሞት ሥልጣንና ኃይል በላይ የኾነው ይኸው የእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥልጣን የድንግል ማርያምን ሥጋ ለፍርድ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ በመቃብር ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይ፤ ፈርሶና በስብሶ በምድር ላይ እንዲቀር አላደረገም፡፡ ከሙታን መካከል ተለይታ ተነሥታለች፡፡ እንድትነሣም ያደረገ የእግዚአብሔር ኃይል ነው እንጂ በራሷ ሥልጣን የተነሣች አይደለችም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን በትንቢት እንዳናገረ ትንሣኤዋንም በትንቢት ሲያናግር ኖሯልና ይህ ታላቅ ምሥጢር በቅዱስ ዳዊት አንደበት ‹‹ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም›› ተብሎ ተገልጿል /መዝ.፻፴፩፥፰/፡፡

ቅዱስ ዳዊት በዚህ የትንቢት ክፍል ትንሣኤዋን አስረድቷል፡፡ ታቦት የጽላቱ ማደሪያ ነው፡፡ በታቦቱ ውስጥ የሚያድረው በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፈው ሕጉ ነው፡፡ ይህ እግዚአብሔር ያከበረው ነገር ኾኖ ሊመጣ ላለው ነገር ማሳያ ነው፡፡ እውነተኛዋ ታቦት ማርያም ናት፡፡ ሙሴ በተቀበለው ታቦት ውስጥ ያለው ጽላት በውስጡ የያዘው ሕጉን ነው፤ በድንግል ማርያም ላይ ያደረው ግን የሕጉ ባለቤት ነውና፡፡ ከፍጡራን ከፍ ከፍ የማለቷ ድንቅ ምሥጢርም ይህ ነውና፡፡ የእመቤታችን ትምክህቷም፣ ትውክልቷም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኾነ ወንጌላውያኑ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው መስክረውላታል፡፡ እርሷም ‹‹ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ፣ በመድኃኒቴ ሐሤትን ታደርጋለች›› በማለት ተናግራለች /ሉቃ.፩፥፵፯/፡፡

እመቤታችን ባለችበት ሥፍራ የሕይወት ትንሣኤ ያላቸው ሰዎች ይኾኑ ዘንድ አስቀድማ ከሙታን ተለይታ በመነሣት የተጠበቀልን ተስፋ ማሳያ ኾነችን፡፡ ከእንግዲህ በኋላ ልጇ ሲንገላታ፣ ሲሰደድ፣ ሲገረፍ፣ ሲሰቀል፣ ሲቸነከር ያየችበት ዓለም አለፈ፡፡ አሁን የልጇን ልዕልና ከሚያደንቁ ጋር ታደንቃለች፤ ከፍ ከፍ ከሚያደርጉት ጋር ታከብረዋለች፡፡ ይኸውም ከገቡ የማይወጡበት፤ ኀዘን፣ መከራ፣ ችግር የሌለበት ሰማያዊ አገር ነው፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ስደት፣ መከራ፣ ኀዘን፣ ሰቆቃ፣ መገፋት፣ መግፋትም የለም፡፡ ቅዱሳን ሩጫቸውን ጨርሰው የድል አክሊልን የሚቀዳጁበት ሥፍራ ነው፡፡ በዚህም ከፍጡራን ኹሉ ከፍ ባለ በታላቅ ክብርና ጸጋ ለዘለዓለም እንደምትኖር እናምናለን፡፡ ልመናዋ፣ ክብሯ፣ ፍቅሯ፣ አማላጅነቷ፣ የልጇም ቸርነት በኹላችን ላይ አድሮ ይኑር፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡ሐመር ፲፰ ዓመት፣ ቍጥር

ደብረ ታቦርና ቡሄ

ነሐሴ ፲፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በዓሉ ይከበራል፡፡ ይህ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ‹‹ቡሄ›› በመባል ይታወቃል፡፡

ቡሄ ማለት /መላጣ ፣ ገላጣ/ ማለት ነው፡፡ በአገራችን ክረምቱ፣ አፈናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለኾነ ‹‹ቡሄ›› እንደ ተባለ ይገመታል፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት፣ ብርሃን የታየበት፣ ድምፀ መለኮት የተሰማበትና ችቦ የሚበራበት ዕለት ስለ ኾነ ደብረ ታቦር የብርሃን ወይም የቡሄ በዓል ይባላል፡፡

ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ጥቢ የሚያመራበት፣ ወደ መፀው የሚገባበት፣ ወገግታ የሚታይበት፣ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፣ የሚሸጋገርበት ወቅት በመኾኑ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም፡፡ ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንዲሉ፡፡በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የቡሄ ዕለት ማታ ምእመናን ችቦ ያበራሉ፡፡ ይህም በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ ነው፡፡

ሕፃናቱ ይህ በዓል ከመድረሱ በፊት ቀደም ብለው ጅራፍ ሲገምዱና ሲያጮኹ (ሲያኖጉ) ይሰነብታሉ፡፡ እናቶችም ለዚህ በዓል የሚኾን ዳቦ ለመጋገር ስንዴያቸውን ሲያጥቡ፣ ሲፈትጉ ይሰነብታሉ፡፡ በበዓሉ ዋዜማ (ነሐሴ ፲፪ ቀን) ሕፃናት በየቤቱ እየዞሩ ‹‹ቡሄ ና በሉ፤ ቡሄ በሉ፡፡ ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ፡፡ …›› እያሉ ይጫወታሉ፡፡ ‹‹ቡሄ›› ያሉት ዳቦውን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ እያነሡ ይሰጧቸዋል፡፡

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል፡፡ «ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ የሚበራው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ ልጆችም ዳቧቸውን እየገመጡ ጅራፍ ሲገርፉ ይውላሉ፡፡ የጅራፉ መጮኽ የድምፀ መለኮት፣ ጅራፉ ሲጮኽ ማስደንገጡ ነቢያትና ሐዋርያት በድምፀ መለኮት መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን ያስታውሳል፡፡

በተጨማሪም ለክርስትና ልጅ፣ ለአማች፣ ለምራት፣ ለዘመድ አዝማድ ኹሉ የቡሄ ዳቦ ይሰጣል፡፡

ደብረ ታቦር ወይም ቡሄ በአብነት ተማሪዎች ‹‹ስለ ደብረ ታቦር›› እያሉ እህል፣ ጌሾ ከምእመናን በመለመንና ገንዘብ በማዋጣት ጠላውን ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎውን ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ የመጡትን ምእመናን በመጋበዝ በታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፡፡

መምህረ ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ተማሪዎቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ በደብረ ታቦር ምሥጢር መግለጡን በማስታዎስ የአብነት ተማሪዎች ከመምህራቸው ጋር በመኾን በዓለ ደብረ ታቦርን (ቡሄን) ያከብራሉ፤ ስሙን ይጠራሉ፡፡ ይህም እስከ አሁን ድረስ በትምህርት ቤቶች የሚሠራበት ነባር ትውፊት ነው፡፡

ነገር ግን በአንድ አካባቢዎች በተለይ በከተማ ዙሪያ በዓለ ደብረ ታቦር (ቡሄ) ሃይማኖታዊ ትውፊቱን የለቀቀ ይመስላል፡፡ ለዚህም ልጆች የሚጫወቱበት መዝሙር ግጥሙና ዜማው ዓለማዊ መለእክት የሚበዛበት መኾኑ፤ በወቅቱ ችቦ ከማብራት ይልቅ ርችት መተኮሱና በየመጠጥ ቤቱ እየሰከሩ መጮኹ፤ ወዘተ. የበዓሉን መንፈሳዊ ትውፊት ከሚያደበዝዙ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከዚሁ ኹሉ ጋርም በዚህ በዓል ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ የሚሽቀዳደሙ ነገር ግን የበዓሉን ታሪካዊ አመጣጥ የማያዉቁ ልጆችም ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው የበዓለ ደብረ ታቦርን መንፈሳዊነት፣ የመዝሙሮቹን ያሬዳዊነትና አከባበሩን ከቤተ ክርስቲያን መምህራን በመጠየቅ ማስተማር፤ ልጆችም ከወላጆች ወይም ከመምህራን በመጠየቅ የበዓሉን አከባበር መረዳትና የዚህን በዓል መንፈሳዊ ትውፊት ሳይበረዝ ለትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ ነው እንላለን፡፡

በመጨረሻም በቡሄ በዓል ‹‹ድምፅህን ሰማና በብሩህ ደመና፤ የቡሄው ብርሃን ለእኛ በራልን፤ …›› የሚለውንና ይህን የሚመስሉ መንፈሳውያን መዝሙራትን እየዘመሩ በየቤቱ በመዞር የሚያገኙትን ዳቦና ገንዘብ ለነዳያንና ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ ልጆችን ማበረታታትና አርአያነታቸውን መከተል ይኖርብናል መልእክታችን ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ ፳፻፭ ዓ.ም፣ ገጽ ፫፻፲፭-፫፻፲፯፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፤ ፳፻፯ ዓ.ም፣ ገጽ ፻፲፩፡፡

ተስእሎተ ቂሣርያ

ነሐሴ ፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፯ ቀን ከሚከበሩ በዓላት መካከል ‹‹ተስእሎተ ቂሣርያ›› አንደኛው ነው፡፡ የቃሉ (ሐረጉ) ትርጕም ‹‹በቂሣርያ አገር የቀረበ ጥያቄ›› ማለት ሲኾን ይኸውም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል?›› ብሎ ደቀ መዛሙርቱን መጠየቁን ያስረዳል፡፡

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው ጌታችን በቂሣርያ አውራጃ ሐዋርያቱን ሰብስቦ ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ (ኢየሱስ ክርስቶስን) ማን ይሉታል?›› ብሎ ሲጠይቃቸው እነርሱም ‹‹ዮሐንስ፣ ኤልያስ፣ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ›› የሚል ምላሽ ሰጥተውታል፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?›› የሚል ጥያቄ ባቀረበላቸው ጊዜ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያቱን ወክሎ ‹‹አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው፤ አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ›› ብሎ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚያስረዳ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽም ሰዎች ስለ ክርስቶስ ማንነት ከሚሰጡት ግምትና ከሐዋርያት ዕውቀት በላይ በመኾኑ ጌታችን ‹‹የእኔን አምላክነት ሰማያዊ አባቴ ገለጸልህ እንጂ ሥጋዊ ደማዊ አእምሮ አልገለጸልህም›› በማለት አድንቆለታል፡፡ ከዚህ በኋላ ‹‹አንተ አለት ነህ፤ በአንተ መሠረትነት ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፡፡ የገሃነም ደጆች (አጋንንት) አይችሏትም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ እሰጥሃለሁ፡፡ በምድር ያሠርኸው በሰማይም የታሠረ፤ በምድር የፈታኸው በሰማይም የተፈታ ይኾናል›› በማለት ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ለቤተ ክርስቲያናችን መታነፅ፣ ለምእመናን ድኅነት ምክንያት የኾነውን መዓርገ ክህነት ሰጥቶታል /ማቴ.፲፮፥፲፫-፲፱/፡፡

ይህም ሥልጣነ ክህነት በቅዱስ ጴጥሮስ አንጻር ከሐዋርያት ጀምሮ ለሚነሡ አባቶች ካህናት የተሰጠ ሰማያዊ ሀብት ነው፡፡ ዛሬ ምእመናን በኀጢአት ስንሰናከል ከካህናት ፊት ቀርበን የምንናዘዘውና ንስሐ የምንቀበለው፣ እንደዚሁም እየተባረክን ‹‹ይፍቱኝ›› የምንለው ጌታችን ለእነርሱ የሰጣቸውን ሥልጣነ ክህነት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ካህናትም ‹‹ይኅድግ ይፍታሕ ያንጽሕ ወይቀድስ …›› እያሉ ከናዘዙን በኋላ ‹‹እግዚአብሔር ይፍታ›› የሚሉን ከባለቤቱ የማሠር የመፍታት ሥልጣን ስለ ተሰጣቸው ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ስለ እርሱ የሚናገሩትንም፣ የሚያስቡትንም የሚያውቅ አምላክ ሲኾን በቂሣርያ ሐዋርያቱን ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል›› ብሎ መጠየቁ በአንድ በኩል አላዋቂ ሥጋን መልበሱን ለማጠየቅ፤ በሌላ ምሥጢር ደግሞ ሐዋርያቱን ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ›› ብሎ በመጠየቅ አምላክ ወልደ አምላክ መኾኑን ለመግለጥና መዓርገ ክህነትን ለሐዋርያትና ለተከታዮቻቸው (ለጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት) ለመስጠት ነው፡፡ ይህም በቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽና ጌታችን ለጴጥሮስ በሰጠው ሥልጣን ይታወቃል፡፡

በዚህ በተስእሎተ ቂሣርያ ጌታችን ሐዋርያቱ ማን እንደሚሉት ስለ ማንነቱ ከጠየቃቸው በኋላ ምላሻቸውን ተከትሎ ሥልጣነ ክህነትን መስጠቱ በብሉይ ኪዳን (እግዚአብሔር በሥጋ ከመገለጡ በፊት) አዳም የት እንዳለ እያወቀ ‹‹አዳም ሆይ ወዴት ነህ?›› /ዘፍ.፫፥፲/ ብሎ ከጠየቀውና ያለበትን እንዲናገር ካደረገው በኋላ ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚል የድኅንት ቃል ኪዳን መግባቱን ያስታውሰናል /ቀሌምንጦስ/፡፡

እንደዚሁም እግዚአብሔር በሦስትነቱ ከአብርሃም ቤት በገባ ጊዜ ሣራ ያለችበትን ቦታ እያወቀ አብርሃምን ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል ያለችበትን ቦታ ካናገረው በኋላ ‹‹ሣራ የዛሬ ዓመት ልጅን ታገኛለች›› የሚል በአንድ በኩል የይስሐቅን መወለድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና የሐዲስ ኪዳንን መመሥረት የሚያበሥር ቃል መናገሩ ከዚህ ትምህርት ጋር ተመሳሳይነት አለው /ዘፍ.፲፰፥፱-፲፭/፡፡

በሐዲስ ኪዳንም አልዓዛር በሞተ ጊዜ የተቀበረበትን ቦታ እያወቀ ‹‹አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት›› /ዮሐ.፲፩፥፴፯/ ብሎ መካነ መቃብሩን ከጠየቀ በኋላ በሥልጣኑ ከሞት እንዲነሣ ማድረጉም ከተስእሎተ ቂሣርያ ጋርና ከላይ ከጠቀስናቸው ምሳሌዎች ጋር የሚወራረስ ምሥጢር አለው፡፡ ይኼ ኹሉ ቃል እግዚአብሔር ያላወቀ መስሎ እየጠየቀ ሰዎች ስሜታቸውን እንዲገልጡ በማድረግ የልባቸውን መሻትና እምነት መሠረት አድርጎ ሥልጣንን፣ በረከትን፣ ጸጋንና ፈውስን እንደሚያድል የሚያስረዳ ትምህርት ነው፡፡ ለዚህም ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው በምድር በአካለ ሥጋ ሲመላለስ መዳን እንደሚፈልጉ እያወቀ ‹‹ልትድን ትወዳለህን? (ልትድኚ ትወጃለሽን?) ብሎ እየጠየቀ የልባቸውን መሻት እንዲናገሩ ካደረገ በኋላ እምነታቸውን አይቶ በአምላካዊ ቃሉ ‹‹ፈቀድኩ ንጻሕ /ንጽሒ፤ ፈቅጃለሁ ተፈወስ /ተፈወሺ›› እያለ ለሕሙማነ ሥጋ ወነፍስ ፈውስን ማደሉ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡

የእያንዳንዳችንን የልብ መሻት የሚያውቅ አምላክ እኛንም በቸርነቱ ከደዌ ሥጋ ወነፍስ እንዲፈውሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ፅንሰተ ማርያም ድንግል

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል …፤ ልዑል እግዚአብሔር ማደሪያውን መረጠ፤ አከበረ፤ ለየ፤ ቀደሰ …›› /መዝ.፵፭፥፬/ በማለት እንደተናገረው፣ አምላክን በማኅፀኗ ለመሸከም የተመረጠችው ማኅደረ ማለኮት፤ የዓለሙን ቤዛ በመውለዷ ‹‹ቤዛዊተ ዓለም›› እየተባለች የምትጠራው፤ በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር የነበረችው የድኅነታችን ምክንያት የኾነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማኅፀን የተቋጠረችው ነሐሴ ፯ ቀን ነው፡፡ ፅንሰቷም እግዚአብሔር በባረከውና ባከበረው ቅዱስ ጋብቻ በተወሰኑት ወላጆቿ በቅዱስ ኢያቄምና በቅድስት ሐና ሥርዓት ያለው ግንኙነት አማካይነት ነው፡፡ ‹‹ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በሥጋዊ ፈቃድ የተፀንሽ አይደለሽም፤ ሕጋዊ በኾነ ሥርዓት ከሐና እና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ›› እንዲል /ቅዳሴ ማርያም/፡፡

ታሪኩን ለማስታዎስ ያህል የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ቴክታ እና በጥሪቃ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለጠጎች እና መካኖች ነበሩ፡፡ በጥሪቃ ሚስቱ ቴክታን ‹‹አንቺ መካን፤ እኔ መካን፡፡ ይህ ኹሉ ገንዘብ ለማን ይኾናል?›› አላት፡፡ ቴክታም ‹‹እግዚአብሔር ከእኔ ልጅ ባይሰጥህ ከሌላ ይሰጥህ ይኾናል፡፡ ሌላ ሚስት አግብተህ ልጅ አትወልድምን?›› ብትለው ‹‹ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃል›› አላት፡፡ ኹለቱም እያዘኑ ሲኖሩ አንድ ቀን ነጭ እንቦሳ (ጥጃ) ከበረታቸው ስትወጣ፤ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ልጅ ስትደርስና ስድስተኛዪቱ እንቦሳም ጨረቃን፣ ጨረቃም ፀሐይን ስትወልድ ራእይ አዩ፡፡

ራእያቸውን ለሕልም ተርጓሚ ሲነግሩም ‹‹የጨረቃዪቱ ትርጕም ከፍጡራን በላይ የምትኾን ልጅ እንደምታገኙ የሚያመለክት ነው፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጠልኝም፡፡ እንደ ነቢይ፣ እንደ ንጉሥ ያለ ይኾናል፤›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ጊዜ ይተርጕመው ብለው›› ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ቴክታ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ሄኤሜን አለቻት፡፡ ትርጕሙም ስእለቴን (ምኞቴን) አገኘሁ ማለት ነው፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና ለዓቅመ ሄዋን ስትደርስም ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡ እነርሱም እንደ በጥሪቃና ቴክታ መካኖች ነበሩ፡፡ በእስራኤላውያን ባህል መካንነት የእርግማን ምልክት ተደርጎ ይቈጠር ነበርና ሐና እና ኢያቄም ብዙ ዘለፋና ሽሙጥ ይደርስባቸው ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደስ ቢሔዱ የዘመኑ ሊቀ ካህናት ሮቤል መካን መኾናቸውን ያውቅ ነበርና ‹‹እናንተማ ‹ብዙ ተባዙ› ብሎ እግዚአብሔር ለአዳም የነገረውን ያስቀረባችሁ ርጉማን አይደላችሁምን? እግዚአብሔር ቢጠላችሁ እንጂ ቢወዳችሁማ ልጅ ይሰጣችሁ አልነበረምን?›› ብሎ መሥዋዕታቸውን ሳይቀበላቸው በመቅረቱ፤ አንድም ከአዕሩገ እስራኤል (ከአረጋውያን እስራኤላውያን) የተወለዱ ሰዎች የሚመገቡትን ተረፈ መሥዋዕት እንዳይመገቡ በመከልከሉ እያዘኑ ሲመለሱ ከልጆቻቸው ጋር የሚጫወቱ ርግቦችንና አብበው ያፈሩ ዕፀዋትን ሐና ተመለከተች፡፡ እርሷም ‹‹ርግቦችን በባሕርያቸው መራባት እንዲችሉ፤ ዕፀዋትን አብበው እንዲያፈሩ የምታደርግ ጌታ እኔን ለምን ልጅ ነሳኸኝ?›› ብላ አዘነች፡፡

ከቤታቸው ሲደርሱም ‹‹እግዚአብሔር ልጅ ቢሰጠን ወንድ ከኾነ ለቤተ እግዚአብሔር ምንጣፍ አንጣፊ፣ መጋረጃ ጋራጅ ኾኖ ሲያገለግል ይኑር፤ ሴት ብትኾንም መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ መጋረጃ ፈትላ ስታገለግል ትኑር›› ብለው ከተሳሉ በኋላ ሐምሌ ፴ ቀን ሐና ለኢያቄም ‹‹በሕልሜ ፀምር (መጋረጃ) ሲያስታጥቁህ፤ በትርህ አፍርታ ፍጥረት ኹሉ ሲመገባት አየሁ›› ብላ ያየቸውን ራእይ ነገረችው፡፡ ኢያቄም ደግሞ ለሐና ‹‹ጸዓዳ ረግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በራስሽ ላይ ስታርፍ፣ በቀኝ ጆሮሽ ገብታ በማኅፀንሽ ስታድር አየሁ›› ብሎ ያየውን ራእይ ነገራት፡፡ ሕልም ተርጓሚው ‹‹ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› ባላቸው ጊዜም ‹‹አንተ አልፈታኸውም፤ ጊዜ ይፍታው›› ብለው ተመልሰዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ‹‹ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› ብሎ ነግሯቸው ሐዲስ ኪዳን ሊበሠር፤ ጌታችን ሊፀነስ ፲፬ ያህል ዓመታት ሲቀሩ ነሐሴ ፯ ቀን በፈቃደ እግዚአብሔር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀንሳለች፡፡ እመቤታችን በሐና ማኅፀን ውስጥ ሳለች ከተደረጉ ተአምራት መካከልም በርሴባ የምትባል አንድ ዓይና ሴት (አክስቷ) ሐናን ‹‹እግዚአብሔር በረድኤት ጐበኘሽ መሰለኝ ጡቶችሽ ጠቁረዋል፤ ከንፈሮችሽ አረዋል›› ብላ ማኅፀኗን በዳሰሰችበት እጇ ብታሸው ዓይኗ በርቶላታል፡፡ ይህንን አብነት አድርገውም ብዙ ሕሙማን ከደዌያቸው ተፈውሰዋል፡፡

ዳግመኛም ሳምናስ የሚባል ያጎቷ ልጅ በሞተ ጊዜ ሐና የአልጋውን ሸንኮር ይዛ ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት ከሞት ተነሥቶ ‹‹ሰላም ለኪ ኦ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ፤ ሰማይና ምድርን የፈጠረው አምላክ አያቱ ሐና ሆይ ሰላም ላንቺ ይኹን›› ብሎ ሕልም ተርጓሚው ያልፈታውን ራእይ በመተርጐም ከሐና እመቤታችን፤ ከእመቤታችን ደግሞ እውነተኛ ፀሐይ የተባለው ክርስቶስ እንሚወለድ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ /ምንጭ፡- ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ ፭፥፴፰/፡፡

በአጠቃላይ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹‹ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን፤ ማርያም ሆይ እውነተኛውን ምግብ፣ እውነተኛውን መጠጥ አስገኝተሽልናልና እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፤›› በማለት እንደ አመሰገናት እኛም ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠውን፤ ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ ማዳን የሚቻለውን፤ እውነተኛውን ምግበ ሥጋ ወነፍስ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለወለደችልን ‹‹እናታችን፣ አማላጃችን፣ የድኅነታችን ምክንያት፣ ወዘተ›› እያልን እመቤታችንን እናከብራታለን፤ እናገናታለን፤ እናመሰግናታለን፡፡ እናቱን በአማላጅነት፤ ራሱን በቤዛነት ለሰጠን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው፤ የእመቤታችን በረከት አይለየን፡፡

ፅንሰተ ድንግል ወተስእሎተ ቂሣርያ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በነሐሴ ወር በሰባተኛው ቀን ከሚከብሩ በዓላት መካከል በዛሬው ዝግጅታችን የእመቤታችንን ፅንሰት እና ተስእሎተ ቂሣርያን የተመለከተ ጽሑፍ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ በመጀመሪያም ፅንሰተ ድንግል ማርያምን እናስቀድም፤

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሲል በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ የቈረሰውና ያፈሰሰው፤ እርሱን የበሉና የጠጡ ኹሉ መንግሥቱን የሚወርሱበት፤ ዘወትር በቤተ መቅደሱ የሚፈተተው ቅዱስ ሥጋውና የሚቀዳው ክቡር ደሙ ከንጽሕተ ንጹሐን፣ ከቅድስተ ቅዱሳን ከወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም የተዋሐደው ሥጋና ደም ነው፡፡ እመቤታችንን እናታችን፣ አማላጃችን፣ የድኅነታችን ምክንያት፣ ወዘተ እያልን የምናከብራት፣ የምናገናት፣ የምንወዳት ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠውን፤ ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ ማዳን የሚቻለውን፤ እውነተኛውን ምግበ ሥጋ ወነፍስ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለወለደችልን ነው፡፡ ‹‹ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን፤ ማርያም ሆይ እውነተኛውን ምግብ፣ እውነተኛውን መጠጥ አስገኝተሽልናልና እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፤›› እንዳለ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡

ቅዱስ ዳዊት ‹‹ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል …፤ ልዑል እግዚአብሔር ማደሪያውን መረጠ፤ አከበረ፤ ለየ፤ ቀደሰ …›› /መዝ.፵፭፥፬/ በማለት እንደተናገረው አምላክን በማኅፀኗ ለመሸከም የተመረጠችው ማኅደረ ማለኮት ቅድስት ድንግል ማርያም የተፀነሰችው ነሐሴ ፯ ቀን ነው፡፡ ፅንሰቷም እግዚአብሔር በባረከውና ባከበረው ቅዱስ ጋብቻ በተወሰኑት ወላጆቿ በቅዱስ ኢያቄምና በቅድስት ሐና ሥርዓት ያለው ግንኙነት አማካይነት ነው፡፡ ‹‹ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በሥጋዊ ፈቃድ የተፀንሽ አይደለሽም፤ ሕጋዊ በኾነ ሥርዓት ከሐና እና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ›› እንዲል /ቅዳሴ ማርያም/፡፡

ታሪኩን ለማስታዎስ ያህልም የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ቴክታ እና በጥሪቃ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለጠጎች እና መካኖች ነበሩ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በጥሪቃ ከቤተ መዛግብት ገብቶ የገንዘባቸውንና የንብረታቸውን ብዛት አይቶ ሚስቱ ቴክታን ‹‹አንቺ መካን፤ እኔ መካን፡፡ ይህ ኹሉ ገንዘብ ለማን ይኾናል?›› አላት፡፡ ቴክታም ‹‹እግዚአብሔር ከእኔ ልጅ ባይሰጥህ ከሌላ ይሰጥህ ይኾናል፡፡ ሌላ ሚስት አግብተህ ልጅ አትወልድምን?›› ባለችው ጊዜ ‹‹ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃል›› አላት፡፡ በዚህ ጊዜ ኹለቱም እያዘኑ ሳሉ ነጭ እንቦሳ (ጥጃ) ከበረታቸው ስትወጣ፤ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ልጅ ስትደርስና ስድስተኛዪቱ እንቦሳም ጨረቃን፣ ጨረቃም ፀሐይን ስትወልድ ራእይ አዩ፡፡

ራእያቸውን ለሕልም ተርጓሚ ሲነግሩም ‹‹የጨረቃዪቱ ትርጕም ከፍጡራን በላይ የምትኾን ልጅ እንደምታገኙ የሚያመለክት ነው፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጠልኝም፡፡ እንደ ነቢይ፣ እንደ ንጉሥ ያለ ይኾናል፤›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ጊዜ ይተርጕመው ብለው›› ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ቴክታ ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ሄኤሜን አለቻት፡፡ ትርጕሙም ስእለቴን (ምኞቴን) አገኘሁ ማለት ነው፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና ለዓቅመ ሄዋን ስትደርስም ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡ እነርሱም እንደ በጥሪቃና ቴክታ መካኖች ነበሩ፡፡ በእስራኤላውያን ባህል መካንነት የእርግማን ምልክት ተደርጎ ይቈጠር ነበርና ሐና እና ኢያቄም ብዙ ዘለፋና ሽሙጥ ይደርስባቸው ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደስ ቢሔዱ የዘመኑ ሊቀ ካህናት ሮቤል መካን መኾናቸውን ያውቅ ነበርና ‹‹እናንተማ ‹ብዙ ተባዙ› ብሎ እግዚአብሔር ለአዳም የነገረውን ያስቀረባችሁ ርጉማን አይደላችሁምን? እግዚአብሔር ቢጠላችሁ እንጂ ቢወዳችሁማ ልጅ ይሰጣችሁ አልነበረምን?›› ብሎ መሥዋዕታቸውን ሳይቀበላቸው በመቅረቱ፤ አንድም ከአዕሩገ እስራኤል (ከአረጋውያን እስራኤላውያን) የተወለዱ ሰዎች የሚመገቡትን ተረፈ መሥዋዕት እንዳይመገቡ በመከልከሉ እያዘኑ ሲመለሱ ከልጆቻቸው ጋር የሚጫወቱ ርግቦችንና አብበው ያፈሩ ዕፀዋትን ሐና በተመለከተች ጊዜ ‹‹ርግቦችን በባሕርያቸው መራባት እንዲችሉ፤ ዕፀዋትን አብበው እንዲያፈሩ የምታደርግ ጌታ እኔን ለምን ልጅ ነሳኸኝ?›› ብላ አዘነች፡፡

ከቤታቸው ሲደርሱም ‹‹እግዚአብሔር ልጅ ቢሰጠን ወንድ ከኾነ ለቤተ እግዚአብሔር ምንጣፍ አንጣፊ፣ መጋረጃ ጋራጅ ኾኖ ሲያገለግል ይኑር፤ ሴት ብትኾንም መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ መጋረጃ ፈትላ ስታገለግል ትኑር›› ብለው ከተሳሉ በኋላ ሐምሌ ፴ ቀን ሐና ለኢያቄም ‹‹በሕልሜ ፀምር (መጋረጃ) ሲያስታጥቁህ፤ በትርህ አፍርታ ፍጥረት ኹሉ ሲመገባት አየሁ›› ብላ ያየቸውን ራእይ ነገረችው፡፡ ኢያቄም ደግሞ ለሐና ‹‹ጸዓዳ ረግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በራስሽ ላይ ስታርፍ፣ በቀኝ ጆሮሽ ገብታ በማኅፀንሽ ስታድር አየሁ›› ብሎ ያየውን ራእይ ነገራት፡፡ ሕልም ተርጓሚው ‹‹ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› ባላቸው ጊዜም ‹‹አንተ አልፈታኸውም፤ ጊዜ ይፍታው›› ብለው ተመልሰዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ‹‹ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› ብሎ ነግሯቸው ሐዲስ ኪዳን ሊበሠር፤ ጌታችን ሊፀነስ ፲፬ ያህል ዓመታት ሲቀሩ ነሐሴ ፯ ቀን በፈቃደ እግዚአብሔር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀንሳለች፡፡ እመቤታችን በሐና ማኅፀን ውስጥ ሳለች ከተደረጉ ተአምራት መካከልም በርሴባ የምትባል አንድ ዓይና ሴት (አክስቷ) ሐናን ‹‹እግዚአብሔር በረድኤት ጐበኘሽ መሰለኝ ጡቶችሽ ጠቁረዋል፤ ከንፈሮችሽ አረዋል›› ብላ ማኅፀኗን በዳሰሰችበት እጇ ብታሸው ዓይኗ በርቶላታል፡፡ ይህንን አብነት አድርገውም ብዙ ሕሙማን ከደዌያቸው ተፈውሰዋል፡፡ ዳግመኛም ሳምናስ የሚባል ያጎቷ ልጅ በሞተ ጊዜ ሐና የአልጋውን ሸንኮር ይዛ ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት ከሞት ተነሥቶ ‹‹ሰላም ለኪ ኦ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ፤ ሰማይና ምድርን የፈጠረው አምላክ አያቱ ሐና ሆይ ሰላም ላንቺ ይኹን›› ብሎ ሕልም ተርጓሚው ያልፈታውን ራእይ በመተርጐም ከሐና እመቤታችን፤ ከእመቤታችን ደግሞ እውነተኛ ፀሐይ የተባለው ክርስቶስ እንሚወለድ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ /ምንጭ፡- ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ ፭፥፴፰/፡፡

በየዓመቱ ነሐሴ ፯ ቀን የሚዘከረው ሌላኛው በዓል ደግሞ ‹‹ተስእሎተ ቂሣርያ›› የሚባለው የጌታችን በዓል ነው፤ የቃሉ (ሐረጉ) ትርጕም በቂሣርያ አገር የቀረበ ጥያቄ ማለት ሲኾን ይኸውም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል?›› ብሎ ደቀ መዛሙርቱን መጠየቁን ያስረዳል፡፡ በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈ ጌታችን በቂሣርያ አውራጃ ሐዋርያቱን ሰብስቦ ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ (ኢየሱስ ክርስቶስን) ማን ይሉታል?›› ብሎ ሲጠይቃቸው እነርሱም ‹‹ዮሐንስ፣ ኤልያስ፣ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ›› የሚል ምላሽ ሰጥተውታል፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?›› የሚል ጥያቄ ባቀረበላቸው ጊዜ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያቱን ወክሎ ‹‹አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው፤ አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ›› ብሎ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚያስረዳ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽም ሰዎች ስለ ክርስቶስ ማንነት ከሚሰጡት ግምትና ከሐዋርያት ዕውቀት በላይ በመኾኑ ጌታችን ‹‹የእኔን አምላክነት ሰማያዊ አባቴ ገለጸልህ እንጂ ሥጋዊ ደማዊ አእምሮ አልገለጸልህም›› በማለት አድንቆለታል፡፡ ከዚህ በኋላ ‹‹አንተ አለት ነህ፤ በአንተ መሠረትነት ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፡፡ የገሃነም ደጆች (አጋንንት) አይችሏትም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ እሰጥሃለሁ፡፡ በምድር ያሠርኸው በሰማይም የታሠረ፤ በምድር የፈታኸው በሰማይም የተፈታ ይኾናል›› በማለት ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ለቤተ ክርስቲያናችን መታነፅ፣ ለምእመናን ድኅነት ምክንያት የኾነውን መዓርገ ክህነት ሰጥቶታል /ማቴ.፲፮፥፲፫-፲፱/፡፡

ይህም ሥልጣነ ክህነት በቅዱስ ጴጥሮስ አንጻር ከሐዋርያት ጀምሮ ለሚነሡ አባቶች ካህናት የተሰጠ ሰማያዊ ሀብት ነው፡፡ ዛሬ ምእመናን በኀጢአት ስንሰናከል ከካህናት ፊት ቀርበን የምንናዘዘውና ንስሐ የምንቀበለው፣ እንደዚሁም እየተባረክን ‹‹ይፍቱኝ›› የምንለው ጌታችን ለእነርሱ የሰጣቸውን ሥልጣነ ክህነት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ካህናትም ‹‹ይኅድግ ይፍታሕ ያንጽሕ ወይቀድስ …›› እያሉ ከናዘዙን በኋላ ‹‹እግዚአብሔር ይፍታ›› የሚሉን ከባለቤቱ የማሠር የመፍታት ሥልጣን ስለ ተሰጣቸው ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ስለ እርሱ የሚናገሩትንም፣ የሚያስቡትንም የሚያውቅ አምላክ ሲኾን በቂሣርያ ሐዋርያቱን ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል›› ብሎ መጠየቁ በአንድ በኩል አላዋቂ ሥጋን መልበሱን ለማጠየቅ፤ በሌላ ምሥጢር ደግሞ ሐዋርያቱን ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ›› ብሎ በመጠየቅ አምላክ ወልደ አምላክ መኾኑን ለመግለጥና መዓርገ ክህነትን ለሐዋርያትና ለተከታዮቻቸው (ለጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት) ለመስጠት ነው፡፡ ይህም በቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽና ጌታችን ለጴጥሮስ በሰጠው ሥልጣን ይታወቃል፡፡

በዚህ በተስእሎተ ቂሣርያ ጌታችን ሐዋርያቱ ማን እንደሚሉት ስለ ማንነቱ ከጠየቃቸው በኋላ ምላሻቸውን ተከትሎ ሥልጣነ ክህነትን መስጠቱም በብሉይ ኪዳን (እግዚአብሔር በሥጋ ከመገለጡ በፊት) አዳም የት እንዳለ እያወቀ ‹‹አዳም ሆይ ወዴት ነህ?›› /ዘፍ.፫፥፲/ ብሎ ከጠየቀውና ያለበትን እንዲናገር ካደረገው በኋላ ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚል የድኅንት ቃል ኪዳን መግባቱን ያስታውሰናል /ቀሌምንጦስ/፡፡ እንደዚሁም እግዚአብሔር በሦስትነቱ ከአብርሃም ቤት በገባ ጊዜ ሣራ ያለችበትን ቦታ እያወቀ አብርሃምን ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል ያለችበትን ቦታ ካናገረው በኋላ ‹‹ሣራ የዛሬ ዓመት ልጅን ታገኛለች›› የሚል በአንድ በኩል የይስሐቅን መወለድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና የሐዲስ ኪዳንን መመሥረት የሚያበሥር ቃል መናገሩ ከዚህ ትምህርት ጋር ተመሳሳይነት አለው /ዘፍ.፲፰፥፱-፲፭/፡፡

በሐዲስ ኪዳንም አልዓዛር በሞተ ጊዜ የተቀበረበትን ቦታ እያወቀ ‹‹አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት›› /ዮሐ.፲፩፥፴፯/ ብሎ መካነ መቃብሩን ከጠየቀ በኋላ በሥልጣኑ ከሞት እንዲነሣ ማድረጉም ከተስእሎተ ቂሣርያ ጋርና ከላይ ከጠቀስናቸው ምሳሌዎች ጋር የሚወራረስ ምሥጢር አለው፡፡ ይኼ ኹሉ ቃል እግዚአብሔር ያላወቀ መስሎ በመጠየቅ የሰዎችን ስሜት እንደሚገልጥና የልባቸውን መሻትና እምነት መሠረት አድርጎ ሥልጣንን፣ በረከትንና ጸጋን እንደሚያድል የሚያስረዳ ትምህርት ነው፡፡ ለዚህም ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው በምድር በአካለ ሥጋ ሲመላለስ መዳን እንደሚፈልጉ እያወቀ ‹‹ልትድን ትወዳለህን? (ልትድኚ ትወጃለሽን?) እያለ በመጠየቅ የልባቸውን መሻት እንዲናገሩ ካደረገ በኋላ እምነታቸውን አይቶ ‹‹ፈቀድኩ ንጻሕ /ንጽሒ፤ ፈቅጃለሁ ተፈወስ /ተፈወሺ›› እያለ በአምላካዊ ቃሉ ለሕሙማነ ሥጋ ወነፍስ ፈውስን ማደሉ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡

በአጠቃላይ ‹‹እመቤታችን ከእርሷ እንድትወለድ ዐውቆ አዳም ሔዋንን ሕይወቴ ነሽ ይላት ነበር›› እንደ ተባለው የኹላችንም ሕይወት፤ የዓለሙን ቤዛ በመውለዷ ቤዛዊተ ዓለም እየተባለች የምትጠራው፤ በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር የነበረችው የድኅነታችን ምክንያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማኅፀን የተቋጠረችው፤ ዳግመኛም በቂሣርያ ሐዋርያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት የመሰከሩት፣ እርሱም ሥልጣነ ክህነትን የሰጣቸው በዚህች ዕለት ነውና በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በየዓመቱ ነሐሴ ፯ ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ እናቱን በአማላጅነት፤ ራሱን በቤዛነት ለሰጠን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው፤ የእመቤታችን በረከት አይለየን፡፡

ጾመ ፍልሰታ ለማርያም

 ነሐሴ ፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው  

በነገረ ማርያም ተጽፎ እንደምናገኘው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሲሔዱ አይሁድ “እንደ ልጇ ተነሣች፤ ዐረገች እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” ብለው በዓመፃ ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም አጎበሩን ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጥቶታል፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡

 

ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ከዚህ ላይ “ስምንት ወር ሙሉ ምን ይዘው ቆይተው ነሐሴ ላይ ሱባዔ ገቡ?” የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ በእውነቱ ቅዱሳን ሐዋርያት ከስብከተ ወንጌል፣ ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከገቢረ ተአምራት፣ ተለይተው እንደማያውቁ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ምስክር ነው፡፡

 

በመኾኑም እመቤታችን ካረፈችበት ቀን ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ ጥያቄያቸውንና ጸሎታቸውን ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ነው፡፡ ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሠውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ?

 

ሁለት ሱባዔ ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፭ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም እንደ ልጇ እንደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ” ያሰኘውም ይህ ታሪክ ነው፡፡

 

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?” ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” እንዲል፡፡ እመቤታችንም “አይዞህ አትዘን፤ ባልነጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃል” ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡

 

እርሱም ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ “የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ?” አላቸው፡፡ እነርሱም “አግኝተን ቀበርናት” ሲሉት “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይኾናል?” አላቸው፡፡  በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ኹሉ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡ ቅዱስ ቶማስም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ ሲሰማው ቆየ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሔዶ መቃብሯን ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡

 

ቅዱስ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ” ብሎ የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡

 

በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት “ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ጌታችን ሥጋዋን እንዲሰጣቸው በጠየቁበት በዚሁ ወቅት ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ቢይዙ ጌታችን ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል /ትርጓሜ ውዳሴ ማርያም/፡፡

 

ይህንን ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩-፲፭ ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል /ፍት.ነገ.አን.፲፭/፡፡ ይህ ጾምም “ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)” ወይም “ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)” እየተባለ ይጠራል፡፡ ‹ፍልሰት› የሚለው ቃልም “ፈለሰ ሔደ፤ ተሰደደ” ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡ ‹ፍልሰታ ለማርያም› ሲልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን የሚያስረዳ መልእክት አለው፡፡

 

በጾመ ፍልሰታ በቤተ ክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለተዋሕዶ በእግዚአብሔር መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡

 

በጾመ ፍልሰታ ባሕታውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ እኛም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ በተጨማሪም ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡

 

ኹላችንም ጌታችን በስሙ ሁለትም ሦስትም ኾነን ለጸሎትና ለመልካም ሥራ ብንሰባሰብ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ የገባልንን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ /ማቴ.፲፰፥፳/ በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡ በኋላም ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡

 

ነገር ግን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ በዚህ ወቅትም ኾነ በሌላ ጊዜ ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉ ወጣቶች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም አረጋውያንና ሕፃናት ብቻ ሳይኾኑ ወጣቶችም ጭምር የመቍረብና የመዳን ክርስቲያናዊ መብት እንዳለን በመረዳት ራሳችንን ገዝተን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይገባናል፡፡ አምላካችን በማይታበል ቃሉ “ሥጋዬን የሚበላ፤ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው” በማለት ተናግሯልና /ዮሐ.፮፥፶፬/፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡