ቅድስት አፎሚያ

ሰኔ 12 ቀን 2006 ዓ.ም.

በመ/ር ፍቃዱ ሣህሌ

በወርኃ ሠኔ መታሰቢያ ከሚደረግላቸው ቅዱሳን መካከል እግዚአብሔርን የሚፈራ የአስተራኒቆስ ሚስት የሆነች የቅድስት አፎምያን ታሪክ በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡

 

ቅድስት አፎምያ በትዳር በነበረችባቸው ዘመናት እግዚአብሔርን ከሚወድ ባለቤቷ ጋር እግዚአብሔርን ስታገለግለው የኖረች ሴት ነበረች፡፡ በየወሩ በ29 ቀን የጌታችንን የልደቱን፣ ወር በገባ በ21 የእመቤታችንንና ወር በገባ በ12 የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያደረጉ ነዳያንን ይጎበኙ እንደነበር ታሪካቸው ይነግረናል፡፡

 

ባለቤቷ አስተራኒቆስ ከዚህ ዓለም የሚያርፍበት ጊዜ እንደደረሰ ባወቀ ጊዜ ይሰጡት የነበረውን ምጽዋት እና የሦስቱን በዓላት መታሰቢያ ማድረግ እንዳታስታጉል ከአደራ ጋር አዘዛት፡፡ እሷም የመልአኩን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ባለቤቷን ጠይቃ አሠርቶ ሰጣት፡፡ በከበረ ቦታም አኖረችው፡፡

 

ባሏ ካረፈ በኋላ ያዘዛትን መንፈሳዊ ሥራ ከወትሮው አስበልጣ መሥራት ቀጠለች፡፡ የሰው ልጆች ጠላት የሆነው ሰይጣንም በመልካም አገልግሎት ስትበረታ ባያት ጊዜ ዝም ብሎ ሊተዋት አልወደደም፡፡ በመጀመሪያ ባል ሳታገባ ማገልገሏን ትታ፣ ሌላ ባል አግብታ፣ ልጅ ወልዳ እንድትኖር በብዙ ማባበል ጠየቃት፡፡ ባሏ መንግሥተ ሰማያትን ስለወረሰ ምንም ምጽዋት እንደማይሻ አስመስሎ ነገራት፡፡

 

ቅድስት አፎምያ ግን ዳግመኛ ትዳር ላለመመሥረት ቃል ኪዳን እንደገባች ርግብንና ዖፈ መንጢጥን አብነት አድርጋ፤ እነሱ እንኳ በሕይወት ዘመናቸው ከአንድ ባል ውጪ ሌላ ባል እንደማያውቁ በመጥቀስ አሳቡን እንደማትቀበለው ገለጸችለት፡፡ ሰይጣንም አስመሳይ መሆኑ አላዋጣ ሲለው ማንነቱን ቀይሮ ሊያንቃት ቢሞክር የእግዚአብሔርንና የቅዱስ ሚካኤልን ስም ጠርታ አባረረችው፡፡ እሱም ተመልሶ መጥቶ እንደሚያጠፋት ዝቶባት እንደአቧራ በኖ፤ እንደ ጢስም ተኖ ጠፋ፡፡

 

በሠኔ ፲፪ ቀን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያዘጋጀች ሳለች ሰይጣን ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ገልጾ የመጀመሪያውን የመሰለ ከንቱ ምክሩን አሰማምሮ አቀረበላት፡፡ አሳቡንም የእግዚአብሔር ፈቃድና አሳብ እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን ሞከረ፡፡ ሰይጣን አስቀድሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገዳመ ቆሮንቶስ መጻሕፍትን እየጠቀሰ እንደተፈታተነው ሁሉ ቅድስት አፎምያንም ለማሳመንም አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዳዊትን የመሳሰሉ ደጋግ አባቶችን ታሪክ እየጠቀሰ ወደ ትዳር እንድትገባ ደጋግሞ ወተወታት፡፡

 

ቅድስት አፎምያም በእግዚአብሔር ኃይል ጸንታ በቅዱስ ሚካኤልም ተራዳኢነት ታምና “የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ መንፈሳዊ ማረጋገጫህ የሆነው የመስቀል ምልክት የታለ?” በማለት በምድራዊ ንጉሥና በጭፍራው መካከል የሚኖርን የጋራ መግባቢያ መንገድ ዋቢ አድርጋ ጠየቀችው፡፡

 

ለጊዜው “በኛ በመላእክት ዘንድ እንዲህ አይደለም” ብሎ ሊሸነግላትና አቋሟን ሊያስቀይራት ሞከረ፡፡ ከቤቷ ያለ የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ላይ ያለውን ምልክት አብራርታ የእሱ ግን ከዛ ጋር አንድነት እንደሌለው አረጋገጠችበት፡፡ ከቤቷ ላለው ለቅዱስ ሚካኤል ሥዕል እጅ እንዲነሣ ጠየቀችው፡፡ በዚህ ጊዜ መልኩ ወደ ትክክለኛ ማንነቱ ተለወጠና ጨለማ ለብሶ እየዛተ አነቃት፡፡ ቅድስት አፎምያም የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን “ድረስልኝ” እያለች በጠራችው ጊዜ መልአኩም ፈጥኖ በመድረስ ከሰይጣን እጅ አዳናት፡፡

 

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለሰይጣኑ ተገቢውን ቅጣት ሰጥቶ ቅድስት አፎምያን ባረካት፡፡ የዕረፍት ቀኗ በዚህ ቀን መሆኑን ነግሮ ቤቷን እንድታዘጋጅ አዘዛት፡፡ የበዓሉን ዝግጅት አከናውና ሥጋ ወደሙን ተቀብላ ኤጲስ ቆጶሱንና ካህናቱን እንደየመዓርጋቸው ጠርታ በቤቷ አክብራ ተቀበለቻቸው፡፡ ለነዳያንና ለጾም አዳሪዎች በኤጲስ ቆጶሱና በካህናቱ እጅ ገንዘቧን መጽውታ መንገዷን አሳመረች፡፡ ስለ ኃጢአቷ እንዲጸልዩላት ተማፅና በፊታቸው ተንበርክካ ጸለየች፡፡ ባሏ ያሠራላትን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አቅፋ ስማ ከተማጸነች በኋላ ሠኔ ፲፪ ቀን በሰላም ዐረፈች፡፡

 

ይህች የታመነች ቅድስት አፎምያ በሰላም እስክታርፍ ጊዜ ድረስ የተጓዘችበትን መንፈሳዊ ጎዳና አስተውለን ይሆን? አስቀድማ ከባሏ ጋር አንድ ሆና በታማኝነት ፈጣሪዋን አገለገለችው፡፡ በኋላም የባሏን ኑዛዜ አክብራ ምንም እንኳን ኃጢአት ባይሆንባትም በሁለተኛ ትዳር ራስዋን ማጠላለፍ አልፈለገችም፡፡ በጎ ሥራ አብልጣ በመሥራት እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ተፋጠነች እንጂ፡፡

 

ሰይጣን ልጅ አለመውለዷን ተጠቅሞ ያቀረበላትን የጋብቻ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ “መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ መናፍስት ከእግዚአብሔር እንደሆኑ መርምሩ” ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የታዘዘውን መመሪያ ተጠቅማ ሰይጣንን በተወክሎ እግዚአብሔር ተቃውማ አሸነፈችው፡፡ የቅዱስ ሚካኤልን ርዳታ ያገኘችውና በሰላም ዐርፋ ወዳገለገለችው እግዚአብሔር በክብር የሔደችው በጽናት ተጋድላ ነው፡፡

 

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በጸሎቷ ይማረን፤ የቅዱስ ሚካኤል የረድኤቱ ኃይል ሁላችንንም ይጠብቀን፣ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡ 

ምንጭ፡- ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ፣ ድርሳነ ሚካኤል ዘወርኃ ሰኔ

 

 

 

 

ጾመ ሰብአ ነነዌ

 የካቲት 3 ቀን 2006 ዓ.ም.

ርዕሰ ደብር ብርሃኑ አካል

ጾመ ነነዌ ከአዋጅ አጽዋማት አንዱ ሲሆን የምትጾመውም ለሦስት ቀናት ነው፡፡ ጾሙ የሚጀመርበት ዕለትም ልክ እንደ ዐቢይ ጾም ሰኞን አይለቅም፡፡ ጾሙ የሚጀመርበት ቀን ደግሞ ሲወርድ ወይም ወደ ኋላ ሲመጣ እስከ ጥር 17 ቀን ድረስ ነው፡፡ ሲወጣ ወይም ወደፊት ሲገፉ ደግሞ እስከ የካቲት 21 ድረስ ነው፡፡ በእነዚህ 35 ቀናት/ዕለታት/ ስትመላለስ ትኖራለች፡፡ ከተጠቀሱት ዕለታት አይወርድም አይወጣም ማለት ነው፡፡

የሦስት ቀኑን ጾም የጾሙት በነነዌ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ሲሆኑ ከተማዋ በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ መሥራቿም ናሞሩድ ነው፡፡ ዘፍ.10፥11-12 ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦር መነሻ የሆነ ከተማ እጅግ ሰፊና ያማረ ፤ የከተማው ቅጥር ርዝመት አሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ነበር፡፡ ሰናክሬም ብዙ ሕንፃዎችንም ሠርቶበት ነበር፡፡ /ዮናስ. 4፥11/

የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ በኃጢአታቸው ምክንያት ሊጠፉ ሲሉ ቸርነትና ምህረቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር ነቢዩ ዮናስ መክሮ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሐ እንዲገቡ ወደ ነነዌ ሕዝብ ሂድ አለው፡፡ ሉቃ.11፥30 ዮናስ የስሙ ትርጉም “ርግብ” ማለት ነው፡፡ በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይ ነው፡፡ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንዲመልስ ትንቢትን ተናግሯል፡፡ ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፡፡ አባቱም አማቴ ይባላል ፡፡ 2ነገ14፥25፣ ት.ዮና1፥1

እግዚአብሔርም “ሄደህ በነነዌ ላይ ስበክ” ባለው ጊዜ “አልሄድም” አለ፡፡ “አንተ መሀሪ ነህ ልትጠፉ ነው ብዬ ተናግሬ ስትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ፡፡” ብሎ ላለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ፡፡ እግዚአብሔር ግን ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧበማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩት ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባህሩ መጣል ሲጀምሩ ነቢዩ ዮናስ “በእኔ ምክንያት የመጣ ስለሆነ ንብረታችሁን ሳይሆን እኔን ወደ ባህር ጣሉኝ” ብሎ ተማጸናቸው፡፡ እነሱም “የሰው ደም በእጃችን እንይሆንብን አይሆንም” አሉት፡፡ ዕጣም ቢጣጣሉ ዮናስ ላይ ወጣ፡፡ ነጋድያኑ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ወዲያው የእግዚአብሔር የማዳን መልእክት ዮናስ እንዲያደርስ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን በአፉ ተቀብሎ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ነነዌ አደረሰው፡፡ ዮናስም ከእግዚአብሔር መኮብለል አለመቻሉን ሲረዳና ነነዌ መሬት ላይ መድረሱ ሲነገረው ለነነዌ ሰዎች “ንስሐ ግቡ” ብሎ መስበክ ጀመረ ዮናስ 1እና2 ፡፡ የነነዌ ሰዎች ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ማራቸው /ዮና.3/

ነቢዩ ዮናስም ውሸታም ላለመባል መኮብለሉ ስህተት መሆኑን እግዚአብሔር ቅልን ምሳሌ በማድረግ አስረዳው፡፡ /ዮና.4/ ነቢየ ሐሰት እንዳይባልም እሳቱ እንደ ደመና ሆኖ ታይቶአል፡፡ የታላላቁ ዛፍ ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ አድርቆ ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ንስሐቸው በከንቱ እንዳልቀረ አስረድቷቸዋል፡፡ በስንክሳር ታኅሣሥ 5 እንደሚነግረን ፤ወበልዓ አሐደ ኀምለ ይላል ንስሐ ያልገቡ አንድ አገር አጥፍቶአል፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የስራጵታ መበለት ሕፃን ዮናስ እንደሆነ /1ነገሥ.17፥19/ ሲያስረዳን ፤ክርስቶስ የዮናስን ከዓሣ ሆድ መውጣት የራሱ ትንሣኤ ምሳሌ አድርጎታል፡፡ /ማቴ.12፥19-42/ ሉቃ.11፥30-32/፡፡

ጾመ ነነዌ የሦስት ቀን ሱባኤ ናት፡፡ ይሄውም አስቴር አስቀድማ ሦስት ቀን ጾማ ጸልያ በእሥራኤል ላይ የመጣውን መቅሠፍት እንዲመለስ አድርጋለች ኢሳ.4፥15-16፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከበዓል ስትመለስ ልጇ ሕፃኑ ኢየሱስ መንገድ ላይ ጠፍቶአት ከሦስት ቀን ፍለጋ በኋላ በቤተ መቅደስ እንዳገኘችው ሁሉ ሉቃ.2፥46 ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሄሮድስ በሰጠው መልስ ሦስት ቀን የሱባኤ ፍጻሜ መሆኑን ገልጿል ሉቃ.13፥32፡፡

የነነዌ ሰዎች የተነሳህየን ምሳሌ ናቸው ይህም ማለት ሰው ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ከገባ እግዚአብሔር ይቅር ማለቱን አይተውም፡፡ ለዚህም ነው ዮናስን አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ በላይ ሕዝቦችና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለሆኑ ያሳዝኑኛል ያለው፡፡

ዛሬ ዓለማችን በኃጢአት ማዕበል እየተናወጠች ባለበት ወቅት እኛም ብንመለስ እና ንስሐ በንገባ ቸሩ ፈጣሪያችን ይቅርታና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ ስለሆነ “ወደኔ ተመለሱ እኔም ይቅር እላችኋለሁ ”ብሎ አስተምሯል፡፡ ቀደምት አባቶቻችን ይህን እና ሌሎች አጽዋማትን እንድንጾም የወሰኑልን ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ጾመ ነነዌ የሚከተሉትን ምሳለዎች እናገኝባታለን ታሪኩን በማስታወስ የእግዚአብሔርን ቸርነትና መሀሪነት የምናስታውስበት ነው፡፡ ይኸውም ፍጥረቶቹ በበደልን ጊዜ ፈጽሞ ከማጥፋት ይልቅ ምክንያት ፈልጎ እንድንድን ያደርጋል፡፡ ዮናስ ፈቃደኛ ባይሆን እንኳ በተለየ ጥበቡ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ሌላ ነቢይ አጥቶም አይደለም እሱንም ጭምር ሊያስተምረው ስለፈለገ እንጂ፡፡

በዮናስ አማካይነት የተደረጉ ተአምራትን መገንዘብና ካለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት ቀላል አለመሆኑን ተገንዝበን ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሃይማኖት አባቶች አና ለወላጆች መታዘዝን እንማርበታለን፡፡ እንደ ነነዌ ሰዎች እኛም ጾመን ጸልየን ከኃጢአታችን እንድንነፃ ነው፡፡ ብንጾም እራሳችን፣ ሃገራችንን፣ እጽዋቱንና እንስሳቱም ሳይቀር በኛ በደል ምክንያት በድርቅ በቸነፈር እንዳይጠፋ እግዚአብሔር ይቅር ስለሚል ነው፡፡

ጾመን እንድናበረክት ይርዳን

ይቆየን

 

limena

የጎዳና ላይ ልመና የቤተ ክርስቲያን ገጽታ የጠቆረበት ሕገ ወጥ ተግባር

 

ዲ/ን ማለደ ዋስይሁን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነበራትን መተዳደሪያ በደርግ ዘመን ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል ደረጃ ማጣቷ ይታወቃል፡፡ ይህ በመሆኑ ለብዙ ደካማ ገጽታዎች መፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ አጥቢያዎች ለካህናት ደሞዝ፣ ለንዋየ limenaቅድሳት መግዣ፣ በአጠቃላይ ለአገልግሎቱ መስፋትና ማደግ የሚያስፈልገውን መተዳደሪያ ገንዘብ፣ ቁስ፣ ጉልበት ለማግኘት ከምእመናን ገንዘብ መለመን ግድ ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡

 

ቤተክርስቲያን አስቀድሞም መተዳደሪያዋን የምታገኘው ቤታቸው ከሆነችላቸው ከተገልጋዮቹ ካህናትና ምእመናን ነው፡፡ አማኞች ዐሥራት በኩራት ማውጣት ሃይማኖታዊ ግዴታቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚያ ደረጃ የምእመናን ተሳትፎ ባልተሟላበት ሁኔታ አገልግሎቱ እንዲቀጥል የሚፈልጉ የቤተክርስቲያን ቤተሰቦች ገንዘብ በመስጠት በመሰብሰብ የአጥቢያቸውን አገልግሎት የሰመረ ያደርጋሉ፡፡

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን በማስፋት፣ በማሳደግ ረገድ ነገሥታቱን ጨምሮ በሀገሪቱ ትልቅ ክብርና ስም ከነበራቸው ልጆቿ ጀምሮ የሚበረከትላትን መባዕ ማለትም ገንዘብ፣ መሬት፣ ወርቅ፣ ብር ወዘተ ስትጠቀም ኖራለች፡፡ በኋላ ዘውዳዊ ሥርዓቱ እንዲጠፋ ሲደረግ ቤተክርስቲያን መተዳደሪያዋ ሁሉ በመወረሱ የካህናቱ አገልግሎት ፈተና አጋጥሞታል፡፡ ስለዚህ መውጫ መንገድ ነው የተባለው የሰበካ ጉባኤ አደረጃጀት እንደ አንድ መፍትሔ የደረሰላት ቢሆንም አሁንም ግን በሚፈ ለገው ደረጃ አገልግሎቷን መደገፍ የሚያስችል በቂ ገቢ ባለመኖሩ ችግሩ እንዳለ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የበለጠ እየተጎዱ ያሉት ደግሞ የገጠር አብያተ ክርስቲ ያናት ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያን የምትሰ በስበውን ገንዘብ አሰባሰብና ሥርጭቱ አጠቃቀሙ የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓቱ መሻሻል ያለበት ቢሆንም ባለው ደረጃም ቢሆን በችግር ላይ ያሉ አጥቢያዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ችግረኛ ገዳማትና አድባራት የሚያስፈልጋቸውን ገቢ ለማግኘት በዓመታዊ በዓላት ከምእመናን የሚያገኙት ገቢ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ልመና ለማድረግ እየተገደዱ ቆይተዋል፡፡ ልመናውንም በተለያዩ አጥቢያዎች በማድረግ የተወሰነ ገቢ አግኝቶ አገልግሎታቸውን ለማስቀጠል እየተንገዳገዱ ነው፡፡

 

ይሔ በእንዲህ እያለ በተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት ስም በጎዳና ላይ ልመና የማድረግ አካሔድ እየሰፋና እያደገ መምጣቱ ይታያል፡፡ ይሔ አካሔድ እጅግ አደገኛና የቤተክርስቲያንንም ገጽታ እየጎዳ ያለ ሕገወጥ አካሔድ ነው፡፡

በቤተክርስቲያን ስም የሚፈጸም የጎዳና ላይ ልመና ገጽታ ሲገመገም አብዛኛው ስምሪት በአዲስ አበባና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የሚደረግ ነው፡፡ የሚደረጉት የጎዳና ላይ ልመናዎች በዓላት በሆኑ ጊዜያትም ከበዓላትም ውጪ የሚደረጉ ናቸው፡፡ የሚደረጉት ልመናዎች ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውጪ በተገኙ ተገቢ ባልሆኑ ጎዳናዎች ላይ ነው፡፡ የሚደረጉትን የጎዳና ላይ ልመናዎች የሚያከናውኑት ካህናት የሚመመስሉም የማይመስሉም ሰዎች ናቸው፡፡ ልመናዎቹ የሚደረጉት በቡድን ወይም በተናጠል ነው፡፡ የጎዳና ላይ ልመናዎች ሲፈፀሙ ጥላ ተዘርግቶ የቅዱሳን ሥዕላት ተይዘው ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳት ሥዕላት በክብር የተያዙ ያልተያዙም ናቸው፡፡

 

የጎዳና ላይ ልመናዎች ሕገ ወጥነት

የጎዳና ላይ ልመናዎች ሕገ ወጥ የሚሆኑባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡

1/ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፈቃድ ያልያዙ የጎዳና ላይ ለማኞች


በቅዱሳን እና በአብያተክርስቲያናት ስም የሚለምኑ የተወሰኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ሁሉም ሕጋዊ የቤተክርስቲያኒቱ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ከአጥቢያ ቤተክርስቲያናቸው፣ ከወረዳ ቤተክህነት፣ ከሀገረ ስብከት፣ ከጠቅላይ ቤተክህነት የተጻፈ ምንም የፈቃድ ደብዳቤ ሳይዙ በሕገ ወጥነት በማጭበርበር የሚሰ ለፉም ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት የራሳቸውን የግል ወይም የቡድን ጥቅም ለማርካት ወይም የቤተክርስቲያንን ስም ለማጉደፍ በድፍረት የተሰለፉ ናቸው፡፡
እነዚህ ወገኖች ምእመናን የቅዱሳን ስም ሲጠራ ራርተው ይሰጣሉ በሚል እምነት በድፍረት ገንዘባቸውን ለመሰ ብሰብ የሚሹ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት የትኛውም ሕግ በማይደግፋቸው አግባብ በማን አለብኝነት የዋሕ ወገኖችን እያታ ለሉ ያሉ ናቸው፡፡

2/ የተጭበረበሩ ደብዳቤዎች የያዙ የጎዳና ላይ ልመናዎች

አንዳንዶች ደግሞ ሕጋዊ ለማኝ ለመምሰል ከአጥቢያ የተጻፉ የሚመስሉ ከጠቅላይ ቤተክህነት የተጻፉ በሚመስሉ ደብዳቤዎችን በጎዳና ላይ ደርድረው የሚለምኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ደብዳቤዎች ሕጋዊ ማኅተም የሌላቸው ወይም ማኅተምን ቢኖራቸውም በማጭበርበር በማስመሰል የተዘጋጁ ወይም ከዚህ ቀደም ተጽፈው ቀንና ቁጥራቸው ላይ ለውጥ በማድረግ አመሳስለው የሚይዟቸው ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕገ ወጥ ናቸው፡፡

3/ በመመሳጠር የተዘጋጁ ደብዳቤዎችን መጠቀም

በአንዳንድ አጥቢያዎች ያሉ የሰበካ ጉባኤ ሓላፊዎች ወይም ሰነዶችን ሕጋዊ የማድረግ ዕድል ያላቸው ግለሰቦች ከአጠቃላዩ የሰበካ ጉባኤ፣ ከማኅበረ ካህናቱና ከምእመናን ስምምነት ሳይደ ረስባቸው ቤተክርስቲያኑ በጎዳና ላይ እንዲለምኑለት ለተወሰኑ በስም ለተጠቀሱ ግለሰቦች ፈቃድ የሰጠ በማስ መሰል በሚወጡ ደብዳቤዎች የሚፈጸሙ የጎዳና ላይ ልመናዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደብዳቤዎችን ይዞ አንድ መርማሪ በአጥቢያው ያሉ የሁሉንም የሰበካ ጉባኤ አባላት ወይም የልማት ኮሚቴ ዎች ስምምነት ያገኘ ወይም ያላገኘ ስለመሆኑ ማስረጃ ቢፈልግ በቀላሉ እንዲህ መሰል ደብዳቤዎች የሚወጡበትን የሙስና መንገድ ሊደርስበት ይችላል፡፡

4/ ከያዟቸው ደብዳቤዎች የፈቃድ ሐሳብ በወጣ መልኩ ልመና ማድረግ

ከየትኛውም የቤተክህነት አካል በሕጋ ዊነት የሚወጡ ደብዳቤዎች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን የሚፈጽሙ ወገኖች የቤተክርስቲያንን ወይም የቅዱሳንን ስም እየጠሩ ሥዕል ይዘው በጎዳና ላይ እንዲለምኑ ፈቃድ አይሰጥም፡፡ በአብዛኞቹ የምእመናን ድጋፍ እንዲጠይቁ ፈቃድ የሚሰጣቸው አገልጋዮች ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን ውጪ እንዲህ ባለ ግብር እንዲገኙ አያዝም፡፡ አብዛኞቹ በተለይም ከጠቅላይ ቤተክህነት የተጻፉ ደብዳቤዎችን ስናይ ልመና እንዲፈጸም የሚያዙት ልመናው ከሚደረግበት አጥቢያ ጋር በመነጋገርና በመስማማት በዚያው በአጥቢያው ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ ከአጥቢያ ውጪ የሚለምኑ ወገኖች ከያዙት የፈቃድ ደብዳቤ ሐሳብ ውጪ የሚራመዱ ከሆነ ሕገ ወጥ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡

5/ ገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ የሌላቸው የጎዳና ላይ ለማኞች

በጎዳና ላይ የሚለምኑ ሁሉም ማለት ይቻላል ግለሰቦችና ቡድኖች በየትኛውም መጠን ለሚቀርብላቸው ምጽዋት የሚቀ በሉበት ሕጋዊ ደረሰኝ የላቸውም፡፡ ስለዚህ በአድባራትና በገዳማት የሚለምኑት ወገኖች የሰበሰቡት የገንዘብ መጠን ሊታወቅ አይችልም ማለት ነው፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ቤተክርስቲያን እውነተኛ ፈቃድ ስትሰጥ በሕጋዊ ደረሰኝ እንዲሰበሰብ እንጂ ከዚያ በመለስ ምንም ያህል መጠን ያለው ገንዘብ ከምእመናን ቢሰበሰብ ለተለመነለት አጥቢያ በተሰበሰበው መጠን መድረሱን ወይም አለመድረሱን ከዚያም አልፎ የግለሰቦቹ መጠቀሚያ ሆኖ ቀርቶም እንደሆነ በውል ማወቅ አያስችልም፡፡

የዚህ ችግር መንሥኤ ምንድ ነው?

1/ የቤተክርስቲያን ቁጥጥር ልል መሆን


ቤተክርስቲያናችን የራሷ አካል በሆኑ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ስም የሚፈጸሙ ይሔን መሰል የማጭበርበር ድርጊቶች ለመቆጣጠር የዘረጋችው ጊዜያዊ ወይም ቋሚ አሠራር የለም፡፡ ቢኖርም በንቃት አልተንቀሳቀሰም፡፡ ችግሩን በቀላሉ መቅጨት የሚቻል ቢሆንም እየተባበሰ መሔዱ የአሠራር ድክመቱን ያሳያል፡፡ ቤተክርስቲያን ይሔንን ችግር መቆጣጠር የሚኖርባት ለቤተክርስ ቲያኒቱ ክብር ብቻ ሳይሆን በቤተክር ስቲያን ስም የሕዝብ ገንዘብ በግለሰቦች እየተመዘበረ በመምጣቱም ጭምር ነው፡፡ በሌላም በኩል ክርስቲያኖች ቤተክርስቲያንን ለመደገፍ የሚሔዱ በትን ፈቃድ በየጎዳናው በመጥለፍ በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ጸሎት አድርሰው ተባርከው መባቸውን በሥርዓት አስገ ብተው እንዳይሔዱ የሚያደርግ ልማድ ፈጥሯል፡፡ ቤተክርስቲያን በየጎዳናው ላይ ሁሉ እንዳለች እያሰቡ በኪሳቸው ያለውን ገንዘብ እየሰጡ እንዲያልፉ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ የዚህ ሁሉ ተጎጂ ራሷ ቤተ ክርስቲያን መሆኗን አውቆ ልል የሆነውን የቁጥጥር ሥርዓት ጠበቅ ማድረግ፣ ምክር መስጠት፣ ካልሆነም ከሕግ አስከባ ሪዎች ጋር በመተባበርም እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

2/ ሙስና

ቤተክርስቲያን እንዲህ መሰል ጥፋቶች በስሟ የሚበቅሉት የግልጽና ስውር የሙስና አሠራሮች በመኖራቸው ነው፡፡ የጎዳና ላይ ልመናዎች እንዲከናወኑ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የተሰለፉ በየደረጃው ያሉ የቤተክርስቲያን አስተዳደር ሹማም ንትም እንዳሉ ይጠረጠራሉ፡፡ ለአንድ ቤተክርስቲያን የሚለመንበት በቂ ምክንያት ሳይኖር ወይም ለአንድ ለተወሰነ ጊዜ ችግር የሆነን ነገር ሁሌ እንዳለ በማስመሰል ፈቃድ በመስጠት እንዲለመን የሚያደርጉ ወገኖች አሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ሕንፃ ቤተክርስቲያን በማሠራት ስም ፕሮጀክቱን በማራዘም ለረጅም ጊዜ እንዲለመንበት በማድረግ ወይም ካለቀም በኋላ ያለ በማስመሰል ልመናዎች እንዲ ቀጥሉ የማድረግ አሠራር አለ፡፡ በዚህም ቢያንስ ዘረፋ ወይም ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት የሚሠሩ ወገኖች አሉ፡፡

3/ ሕዝበ ክርስቲያኑ በየዋህነት በማመን መመጽወቱ

ክርስቲያኖች ለለመነ፣ ለጠየቀ መስጠት አግባብና ክርስቲያናዊ ሥነምግባር መሆኑን ስለሚያምኑ በቅዱሳን ስም ተጠርቶ የቅዱሳን ሥዕል ተይዞ ሲለመን ማለፍ ይከብዳቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ እንዲለምኑበት የተሰጣቸውን የፈቃድ ወረቀት ሐሳብ ወይም የሚቀበሉበትን ሕጋዊ ደረሰኝ የማይጠይቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ በሌላም በኩል ለሚሰጡት ሽርፍራፊ ሳንቲም ደረሰኝ መጠየቅ አስፈላጊ ነው ብለው አያምኑም፡፡ ስለዚህም ለእነዚህ ሕገወጥ የጎዳና ላይ ልመናዎች መበራከት የምእመናንንም ድርሻ አለበት፡፡

በእርግጥ አንዳንድ ክርስቲያኖች የተጎዱ አብያተ ክርስቲያናትን ለመርዳት በሚያ ስችል መልክ ተሰባስበው ቀጣይነት ያለው ሕጋዊነትና ሥርዓት ያለው ድጋፍ ችግረኛ ለሆኑ አብያተ ክርስቲ ያናት መስጠት በመጀመራቸው የችግሩ ስፋት የሚቀንስበት ዕድል ሊኖር ይችላል፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ምእመናን የጎዳና ላይ ልመና የቤተክርስቲያንን የሃይማኖ ታቸውን ገጽታ የሚያበላሽና ሥርዓት ያጣ ስርቆትንም የሚያባብስ መሆኑን ተረድተው ከዚህ መቆጠብ ካልቻሉ ገንዘባ ቸውን አነሰም በዛም በግልም ይሁን በቡድን ለቤተክርስቲያን በሕጋዊ መንገድ ገቢ ማድረግ እስካልቻሉ ድረስ ችግሩ መቀጠሉ የማይቀር ይሆናል፡፡

limena1የጎዳና ላይ ልመና የሚያስከትለው ችግር

1/ የቤተ ክርስቲያንን ገጽታ ማጥፋቱ

ይህቺ ቅድስትና በቸር ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሠረተች ቤተክር ስቲያን ክብር ያላት ናት፡፡ ለብዙዎች የእግዚአብሔርን ጸጋ የምታሰጥ ባዕለጸጋ ቤተክርስቲያን ነች፡፡ ‹‹እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግም›› እያለች ስታስ ተምር የኖረች ቤተክርስቲያን ነች፡፡ ለምስኪኖች፣ ለተቸገሩ፣ ለደሀ አደጎች ለእጓለ ማውታ ሁሉ የምትደርስ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ‹‹ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው›› እያለች የምታሰተምር ቤተክርስቲያን ነች፡፡

 

ቤተክርስቲያን ከምእመናን ዐሥራት በኩራታቸውን ተቀብላ የእግዚአብሔርን ገንዘብ የምታስተዳድር እንጂ ዋነኛ ተግባሯ ሙዳየ ምጽዋት መሰብሰብ አይደለም፡፡ ስብከተ ወንጌልን የማንገሥ እንጂ ማዕድን የማገልገል ፍላጎት ያላት አይደለችም፡፡ ማድረግ ሲገባት ደግሞ በሥርዓትና በታማኝነት የምትፈጽምበት አሠራር አላት፡፡

 

የጎዳና ላይ ልመናዎች ግን የቤተ ክርስቲያን መገለጫ ሆነው ተስለዋል፡፡ ማንም ጥላ ይዞ የሚለምን፣ ሥዕል ያንጠለጠለ፣ እጁን የዘረጋ ሁሉ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መገለጫ እየሆነ ነው፡፡ ሌሎች ዐበይት ቤተክርስቲያናዊ ተግባራትን ባከናወንን መጠን ክርስቲ ያኖች ሳይጠይቁ የሚያደርጉትን ነገር እኛ ግን ዐበይት ተግባሮቻችንን ቸል ብለን የጎዳና ላይ ልመና ዋነኛ የሥራ ሂደታችን ያደረግነው ያስመስላል፡፡

 

ስለዚህ ነው ቤተክርስቲያናችን የጎዳና ላይ ልመናዎችና መሰል ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት ለቤተክርስቲያኒቱ ታሪካዊነት የአርአያነት ሚና የታማኝነት ደረጃ ወዘተን የሚያኮስሱ ይሆናሉ፡፡

2/ የቅዱሳንን ክብር የሚነካ ይሆናል


ቅዱሳንን እግዚአብሔር ያከበራቸው ናቸው፡፡ ሰዎች ክብርን የሚሰጧቸው ወይም የሚቀንሱባቸው አይደሉም፡፡ እነርሱን በማክበር ግን ቤተክርስቲያንና ልጆቿ በረከት ያገኛሉ፤ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛሉ፡፡

ነገር ግን በጎዳና ላይ ልመናዎች የምናየው ነገር የቅዱሳን መላእክትን የቅዱሳን ሰዎችን ስም ጠርተው ሥዕል ይዘው የሚለምኑ ወገኖች በተለያዩ አካሔዶቻቸው ቅዱሳንን ያዋርዳሉ፡፡ በስማቸው ሕገ ወጥ ሥራ የስርቆት ተግባር መፈጸማቸው ጽርፈት ነው፡፡ ንዋየ ቅድሳት ከሥርዓት ውጪ በተያዙ መጠን ይጉላላሉ፡፡ ሥዕሎ ቻቸውን ይዘው አጓጉል ቦታዎች ቆመው መታየታቸው ጽርፈት ነው፡፡ ለቅዱሳት ሥዕላት ክብር በሚነፍግ መልኩ በአያያዝ የተጎዱ በሥርዓት ያልተሠሩ ፀሐይና ዝናብ የተፈራረቀባቸው ሥዕላትን ይዞ መቆም ለሃይማኖት ቤተሰቡም ሆነ ለሚከበሩት ቅዱሳን ክብር አለመስጠት ነው፡፡

3/ የክህነትን ክብር የሚነካ ነው

ብዙ ጊዜ በጎዳና ልመና ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ካህናት የሆኑም ያልሆኑም ወገኖች ናቸው፡፡ ነገር ግን አርአያ ክህነትን ተላብሰው ስለሚታዩ ሁልጊዜም በጎዳና ላይ ልመና የሚታዩት ካህናት ናቸው ብሎ ሰዎች እንዲያምኑ እያደረገ ነው፡፡ ካህናት የቤተክርስቲያን መልክና ምልክቶች ናቸው፡፡ በእነርሱ ውስጥ የምትከብረው ወይም ገጽታዋ የሚደበዝዘው የቤተክርስቲያን ነው፡፡ የመላው ካህናት ገጽታ ነው፡፡ ካህናትን ዘወትር የሚሰጡ ሳይሆን የሚቀበሉ፣ የሚመጸውቱ ሳይሆን የሚመጸወቱ አስመስሎ ያቀርባል፡፡ ከዚያም አልፎ በክህነት የሚፈጸመው ዋነኛ ተግባር ልመና እንደሆነ አድርገው በክህነት የሚያምኑም ሆነ የማያምኑ ወገኖች እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡

4/ የሀገርን ገጽታ ይጎዳል


ቤተክርስቲያን በሙዳየ ምጽዋት የምእ መናንን የለጋስነት ስጦታ መሰብሰቧ፣ ዐሥራት በኩራትን መሰብሰቧ በሃይማኖቱ ሕግና ሥርዓት የታወቀ መንፈሳዊ ተግባሯ ነው፡፡ ስለዚህ የትኛውም ተመልካች ቤተክርስቲያን በአጥቢያዋ ካሉ ምእመናን ዐሥራት በኩራት ምጽዋትን ሰበሰበች ብሎ የሚነቅፋት አይኖርም፡፡ ነገር ግን በተገቢው መልኩ በተገቢው ቦታና በሕጋዊ መልክ ካልሆነ ይነቅፋል፡፡

 

የጎዳና ላይ ልመና ግን ከቤተክርስቲያን አልፎ ለሀገርም ገጽታን የሚያጎድፍ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር ጎብኚዎችም ዘንድ ደስ የማያሰኝ በመሆኑ ለሀገራችን አይጠቅምም፡፡ ሀገር ልመናን በመቀነስ ሥራና ሠራተኛነትን ለማስፋፋት ጥረት ማድረግ የሚገባትም ለሰሚና ተመልካች ሳቢ ሁኔታን ለመፍጠር ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ከአጥቢያ ቤተክር ስቲያን ግቢ ውጪ ወጥቶ ከዕለታዊ ችግራቸው የተነሣ ሕዝብ ባለበት ዐደባባይ ከሚለምኑ ነዳያን ጎን ተሰልፎ ከአማ ኙም ከኢአማኒውም ለቤተክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት መግዣ፣ ለሕንፃዋ ማሠሪያ ገንዘብ ለመለመን መሞከር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡

 

5/ የአጥቢያና የሀገረ ስብከቶችን ክብር ይነካል

 

የሚለመንላቸው አጥቢያዎች ስማቸው አለአግባብ በየጎዳናው ለረጅም ጊዜ መነሣቱ ክብር አይሆንላቸውም፡፡ በስማቸው ሕገ ወጥ ተግባር ሲከናወን ሲታይ አጥቢ ያውን ለሚያውቁ ምእመናንና ካህናት የሚያምም ይሆናል፡፡ ለአጥቢያው ብቻ ሳይሆን በዚህ ሀገረ ስብከት በዚህ ወረዳ ለሚገኘው ተብሎ ስለሚለመን ለዚያ ሁሉ ወገን የሚያምም ይሆናል፡፡

6/ ሥራ ፈትነትን ያበረታታል

ቤተክርስቲያን ያላት ትምህርት ‹‹ሊሠራ የማይወድ አይብላ›› የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ልመናዎች በአቋራጭ መክበርን ያለሥራ ያለድካም መጠቀምን የሚያመጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ጉዳቱ ለዜጎች ሁሉ ነው፡፡ የሚሠራውን ተስፋ የሚያስቆርጥና ተመሳሳይ የአቋራጭ መንገዶችን እየፈለገ ምርታማ ባልሆኑ ሥራዎች በመሰማራት ከዚያም አልፎ በሥራ ፈትነት በሕገ ወጥ ተግባራት ውስጥ እንዲገባ ያበረታታሉ፡፡ የቤተክርስቲያንን አርአ ያነትም ያጎድፋል፡፡

7/ ለቤተ ክርስቲያን ቤተሰቦች ያሳፍራል

ቤተ ክርስቲያንና ቤተሰቦቿ ከሥራ ይልቅ ልመናን የሚመርጡ ስለሚያስ መስል በሌሎች ወገኖች በሚደርስብን ትችት ምእመናን ይሸማቀቃሉ፡፡ ምእመናን የሚፈለገውን ያህል በማይ ወስኑባት በማይመክሩባት ቤተክርስቲያን ውስጥ ይሔ መሆኑ ደግሞ ምእመናንን የሚያስቆጣበት ደረጃ ላይ ያደርሳል፡፡ ካህናት አመኔታ እንዲያጡ በር ይከፍታል፡፡

8/ ምእመናንን ያዘናጋል

ምእመናን ምጽዋትና ዐሥራት በኩራትን ለይተው ማድረግ እንደሚገባቸው በውል ትምህርት በበቂ ባልተሰጠበት ሁኔታ ውስጥ እንዲህ ያሉ ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ልመናዎች ሲበራከቱ የዋህ ምእመናን ቤተክርስቲያንን ያገኙ ስለሚመስላቸው ዐሥራት በኩራታቸውን በአግባቡ ለማውጣት ይቸገራሉ፡፡ በጥቂቱ በመርካት ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን በአፍአ ይቀራሉ፡፡ ምጽዋታቸውንም በአግባቡ ሊሰጡ የሚችሉበት ዕድል አይኖራቸውም፡፡

9/ ሌሎች ችግሮች

የጎዳና ላይ ልመናዎች የሚያስከትሉት ሌላው ጉዳት ከሚለምኑት ሰዎች ማንነትና ተግባር ጋር በተያያዘ የሚያስ ከትለው ችግር ነው፡፡ በልመና ላይ የዋሉ ሰዎች የውሏቸው መጨረሻ የት ነው? የት ያመሻሉ? የት ያድራሉ? ከእነማን ጋር ይውላሉ? የሚለው ሌላው አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ ያለደረሰኝ በሕገ ወጥ መልክ የተሰበሰበውን ገንዘብ ይዘው በየመጠጥ ቤቶች ተሰይመው የሚያመሹ በርካቶች ናቸው፡፡ ተደራ ጅተው፣ ማደሪያ ተከራይተው በዓላት ባሉበት የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሁሉ ቆመው ውለው ማታ ተሰባስበው ያገኙትን ገንዘብ ተካፍለው የሚበተኑ ቡድኖች አሉ፡፡ የቡድኖቹ አስተባባሪዎችም አሉ፡፡ ያዘጋጁትን የፈቃድ ደብዳቤ የሚመስል ማጭበርበሪያ ይዘው የሚለምኑ ሰዎችን አደራጅተው ደብዳቤውን ፎቶ ኮፒ አድርገው የሚያሰማሩ ከዚያም ከየለማኞቹ የድርሻቸውን ተቀብለው ለቀጣዩ ዙር ልመና ተቀጣጥረው የሚበታተኑ ሁሉ አሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚፈጸመው በቤተክር ስቲያኒቱ ስም መሆኑ ሲታሰብ የሚያሳዝን ነው፡፡

 

ሌላው አሳሳቢው ነገር በየቦታው በሚታዩ ልመናዎች የሚያስተባብሩት ወይም የሚለምኑት ሰዎች ተጠሪነታቸው ለጥቂትና ተመሳሳይ ሰዎች የመሆኑ ነገር ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የፈቃድ ደብዳቤ ብለው በሚይዙት ላይ በልዩ ልዩ ሥፍራዎች ያሉ ሰዎች በያዟቸው የፈቃድ ደብዳቤዎች ላይ በአንድም በሌላ መንገድ ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በተለይም የአዲስ አበባን የጎዳና ላይ ልመናዎች ገዢ ሆነው የተቀመጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ምናልባትም ሕጋዊ መልክ እንዲኖራቸው ከቤተክህነቱ አንዳንድ ግለሰቦች ጋር የጥቅም ግንኙነት ያላቸውም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የሚለምኑት ከሚያስለምኑ ሕጋዊ ነን ከሚሉ ገዢዎቻቸው ጋር ተቀናጅተው የሚፈጽሙት ጥፋት ነው፡፡

 

ሌላው አሳሳቢው ነገር የሀገሪቱን ሕግ የሚያስከብሩ ደንብ አስከባሪዎችና ፖሊስ ቤተክርስቲያንን እና ክርስቲያኑን ማኅበረሰብ በመፍራት ለመጠየቅ የሚደፍ ሯቸው አለመሆናቸው ነው፡፡ በፊታቸው የሚዘረጓቸውን ማስፈራሪያ ወረቀቶች አይተው ወይም የሚሰጣቸውን መጽዋች ፈርተው ወይም አይመለከተንም በማለት ወዘተ የሕግ አስከባሪዎች ስለሚያልፏቸው ጠያቂ እንደሌላቸው በማሰብ እነዚህ በቤተክርስቲያን ስም በመለመን የብዙዎችን ገንዘብ አለአግባብ እየዘረፉ ይገኛሉ፡፡

መፍትሔ

ቤተክርስቲያን በስሟ የሚፈጸሙ ልመናዎችን ለማስቆም መትጋት ያለባት አሁን ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ሙስናን ከቤተክርስቲያን ለማጥፋት እሠራለሁ ብሎ እየተጋ ባለበት በዚህ ዘመን ከእነዚህ ጥቃቅን ቀበሮዎች ጀምሮ ወደ ታላላቆቹ መገስገስ ይገባዋል፡፡ ታላላቆቹ ሙሰኞች በእነዚህ ጥቃቅን መሠረቶች ላይ የቆሙ ናቸው፡፡

 

ቤተክርስቲያን እንዲህ ያሉ ሕገ ወጦችን ማጥፋት የሚገባት የቅድስና ባለቤት በሆነችው ቤተክርስቲያን ስም የሚፈጸም የስርቆት ተግባር ኃጢአት በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በልመና ላይ የተሰማሩትን ጨምሮ በዚሁ የጥፋት መንገድ ለመሳተፍ እየተንደረደሩ ያሉትን ለመታደግ ይረዳታል፡፡ በሌላ መልኩ ምእመናን ገንዘባቸውን በቤተክርስቲያን ስም እንዳይዘረፉ ከመጠበቅ አንጻር ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የቤተክርስቲያንን ገጽታ እንዳይጎድፍ ከመጠበቅ አንጻር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቤተክርስቲያኒቱ መሠልጠን ያለበት ሕጋዊ አሠራር ብቻ መሆኑን አስረግጦ ለማስረዳት ለማሳየት ይጠቅማል፡፡

 

ስለዚህም በቅድሚያ በቤተክርስቲያን ስም በጎዳና ላይ መለመን ከብዙ ነገሮች አንጻር ምን ያህል አግባብ ነው የሚለውን በውል በማጤን ግልጽ አቋም መያዝ ከቤተክርስቲያን ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አስከትሎም አሁን በጎዳና ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ልመናዎችን ሕጋዊነት መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ለጎዳና ላይ ልመናዎች ፈቃድ የሚሰጠው ማን ነው? ፈቃዱን ለእነማን ሰጠ? ለምን ዓላማ ሰጠ? ተግባሩ ፈቃድ በተሰጠበት አግባብ ተፈጽሟል? ፈቃዱ እስከ መቼ የሚሠራ ነው? በፈቃዱ የተሰበሰበው ገንዘብ ለታሰበው ዓላማ እየዋለ ነው? በትክክል የፈቃድ ደብዳቤው ወጣ ከተባለበት መዝገብ ቤት ወጥቷል? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን አንሥቶ የቤተክርስቲያኒቱ ታማኝ የሕግ አስከባሪ አካላት ከተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር መመርመርና እርምጃ ማስወሰድ አለባቸው፡፡

ከቤተክርስቲያን አስተዳደር ሌላ ግን ከመንግሥት አካላት ጋር ተባብሮ ቢያንስ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ሌሎች ቁጭቱ ያላቸው አገልጋዮችም የእነዚህን የጎዳና ላይ ልመናዎች ለማስቀረትና የቤተክርስቲያናችንን ክብር ማስጠበቅ አለብን፡፡

መሰናክል ያለበትን ገንዘብ የሚሰበስብ ሰው ገንዘብ በመሰብሰቡ ኃጢአት አድርጓልና እንዳይሰበስብ ይገባዋል/ፍት.ነገ. አንቀ.16 ቁ.648/

ዳግመኛም ገንዘብ እያለው ምጽዋት ለሚቀበል ሰው ወዮለት አለ፤ ራሱን መርዳት እየተቻለው ከሌሎች መቀበልን የሚወድ ሰው ወዮለት እንዲህ ያለውን ግን በፍርድ ቀን እግዚአብሔር ይመረምረውል››/ፍት.ነገ.አንቀ.16 ቁ.634/

ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት፤21ኛ ዓመት ቁጥር 7፤ ኅዳር 2006 ዓ.ም.

 

ዘመነ አስተርእዮ

 ጥር 21 ቀን 2006 ዓ.ም.

 

ር/ደብር ብርሃኑ አካል

አስተርእዮ ቃሉ የግእዝ ቃል ሲሆን መታየት መገለጥ ማለት ነው፡፡ ገሐድ የሚለው ቃልም በጾምነቱ ሌላ ትንታኔ ሲኖረው ትርጉሙ ያው መገለጥ ማለት ነው፡፡ በግሪክ ኤጲፋኒ ይሉታል፡፡ የኛም ሊቃውንት ቀጥታ በመውሰድ ኤጲፋኒያ እያሉ በዜማ መጻሕፍቶቻቸው ይጠሩታል፡፡ ትርጉሙም ከላይ ከጠቀስናቸው ጋር አንድ ነው፡፡

አስተርአየ የተባለው ግሥ ራሱን ችሎ ሳይለወጥ በአምስቱ አዕማድ የሚፈታ ብቸኛ ግሥ ነው፡፡ ይህም ማለት፡- አስተርአየ፤ ታየ፤ ተያየ፤ አሳየ፤ አስተያየ፤ አየ ተብሎ ይፈታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዘመነ አስተርእዮ ሲያጥር ከጥር 11 ቀን እስከ ጥር 30 ቀን ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት 20 ቀናት ይሆናሉ፡፡ ሲረዝም ደግሞ ከጥር 11 ቀን እስከ መጋቢት 3 ቀን ይሆናል፡፡ ይህም 53 ቀናት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

 

ጌታን ለሐዋርያት ህፅበተ እግር ያደረገበት ቀንም ከጸሎተ ሐሙስ እስከ ጰራቅሊጦስ ቢቆጠር 53 ቀናት ስለሚሆኑ የእነዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ዮሐንስ በጥምቀት ዕለት ለልዕልና /ጌታ ሰውን ምን ያህል እንዳከበረው/ ለማሳየት እጁን ከጌታ ራስ በላይ ከፍ እንዳደረገ ጌታም ለትህትና እጁን ከሐዋርያት እግር በታች ዝቅ አድርጎ እግራቸውን አጥቧቸዋልና ነው፡፡ ጥምቀት የህጽበት አምሳል ሲሆን፤ /ህጽበት/ መታጠብ በንባብ አንድ ሆኖ ሁለት ምሥጢራት አሉት፡፡

አንደኛ፤- ምእመናን የእንግዳ እግር እንዲያጥቡ ትምህርት ማስተማሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው ለሐዋርያት ጥምቀት ነው፡፡

በጸሎተ ሐሙስ ቢጠመቁም መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉት የጰራቅሊጦስ ነውና ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፤ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያን ስለ ቅዱሳን ሐዋርያት ጥምቀት እንደጠየቀውና ጥምቀታቸው ህጽበተ እግር መሆኑን እንደመለሰለት፡፡

 

በሌላ በኩል ከዘመነ ልደት እስከ ጥምቀት ተወልደ፤ ተሰገወ /ሰው ሆነ/ ይባላል እንጂ አስተርአየ አይባልም፡፡ ከጥምቀት በኋላ ግን አብሮ ተባብሮ ተጠምቀ፤ ተወለደ፤ ተሰገወ አስተርአየ ይባላል፡፡ ከጥምቀት በፊት አስተርእዮ ለመባሉ በሦስት ነገሮች ነው፡፡

 

አንደኛ፡- የማይታየው ረቂቅ አምላክ በበረት ተወልዶ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ ቢታይና እንደ ሕፃን ሲያለቅስ ቢሰማም ሰው ሁሉ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው ሙሉ ሰው ይሆናል እንደሚባለው፤ አምላክ ነኝ ብሎ በአንድ ቀን ሳያድግ በጥቂቱ ማደጉንና ስደት እንደ ውርደት ሆኖ እንዳይቆጠር ለሰዎች ጀምሮ ለመስጠት፤ ሄሮድስም ሊገድለው ይፈልገው ስለነበር የሚሰደድበት እንጂ የሚታይበት ስላልነበረ ነው፡፡

 

ሁለተኛ፡- ሰው በተፈጥሮም ሆነ በትምህርት አዋቂ ቢሆን ለሚመለከተው ሥራና ደረጃ እስከ ተወሰነ ጊዜ ይህ ሕፃን ለእንዲህ ያለ ማዕረግ ይሆናል አይባልም፡፡ ተንከባክባችሁ አሳድጉት ይባላል እንጂ፤ አዋቂ ነው አይባልም፡፡ ያውቃል ተብሎም ለትልቅ ደረጃ አይበቃም፡፡ በየትኛውም ሓላፊነት ላይ አይሰጥም ራሱን በመግዛት ይጠበቃል እንጂ፡፡ እንዲሁም ጌታ የመንፈሳዊ እና የሥጋዊ ባለሥልጣን ቢሆንም ፍፁም ሰው ሆኗልና የሰውን ሥርዓት ከኃጢአት በቀር ለመፈጸም በበሕቀ ልሕቀ ይላል፡፡ አምላክ ነኝና ሁሉን በዕለቱ ልፈጽም ሳይል በየጥቂቱ ማደጉን እናያለን፡፡ በዚህም የተነሣ ሰው ሁሉ 30 ዓመት ሲሆነው ሕግጋትን እንዲወክል እንዲወስን እስከ 30 ዓመት መታገሡ ስለዚሁ ነው፡፡ ከሠላሳ ዓመት በኋላ ግን ሰው ቢመቸው ይወፍራል፤ ቢከፋው ይከሳል እንጂ ቁመት አይጨምርም አይቀንስም፡፡ ስለዚህ ጌታ ሙሉ ሰው የ30 ዓመት አዕምሮው የተስተካከለለት ሰው /ጎልማሳ ሆኖ በመታየቱ ዘመነ አስተርእዮ ተብሏል፡፡

 

ሦስተኛው፤- በ30 ዓመት እሱ ሊጠመቅበት ሳይሆን የመጀመሪያ መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት መሠረት የሆኑ ጥምቀትንና ጾምን ሰርቶ በመሳየትና መመሪያ አድርጎ በመስጠት አምስት ገበያ ያህል ሰው የቃሉን ትምህርት ለመስማት፤ የእጁን ተአምራት ለማየት፤ እሱ ሙሉ ሰው ሆኖ ተገልጾ ትምህርት፤ ተአምራት የሚያደርግበት ሥራዬ ብሎ የመጣበት መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት የተፈጸመበት ዘመን ነው፡፡

 

የታየውም ብቻ አይደለም፤ አብ ይህ የምወደው ልጄ ነው፤ ሲል መንፈስ ቅዱስም በእርግብ አምሳል ረቂቁ የታየበት የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ምሥጢር የተገለጠበት ስለሆነ ዘመነ አስተርእዮ ተብሏል፡፡

 

በዚህ ምክንያትም ሌሎች በዓሎችም ይጠሩበታል፡፡ ለምሳሌ ድንግል ማርያም ጥር 21 ቀን ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይቶ በደመና ተነጥቃ ወደ ገነት በመግባት ለጻድቃን ሰዎችና ለመላእክት በሰማይና በምድር የተሰጣት ጸጋና ክብር የተገለጸበት ዕለት ስለሆነ በዓሉ አስተርእዮ ማርያም ይባላል፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት በዚህ ቃል ሐሳባቸውን ያስተባብራሉ፡፡ ቅዱስ ያሬድ አምላክ በሥጋ ከድንግል መወለዱን በዚህ አካለ መጠን ለዓለም መገለጡን አስተርእዮ ብሎ ሲናገር፤ አባ ጽጌ ብርሃን ደግሞ በማኅሌተ ጽጌ “የትንቢት አበባ እግዚአብሔር እኛን ሥጋ የሆነውን የአንቺን ሥጋ ለብሶ በምድር እንደተገለጠ ለእኛም እንዲታወቅ ድንግል ሆይ የወገናችን መመኪያ ዛሬ ለእናታችን ለማርያም በሰማይ ፍጹም በደስታ መገለጥ ሆነ እያልን እናመሰግናለን” ብሏል፡፡ ዳዊትም እንዲህ አለ “በከመ ሰማዕና ከማሁ ርኢነ” መዝ. 47፡6 ፡፡ በነቢያት ይወለዳል ሲባል የሰማነው በበረት ተጥሎ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው እንዲሁም በዮርዳኖስ ሲጠመቅ አየነው፡፡

 

christmas 1

በድንግልናሃ ንጹሕ እግዚአብሔር ተወልደ

 ታኅሣሥ 26 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

christmas 1
በፈቃደ አቡሁ ወረደ፣ኀበ ማርያም ተአንገደ፤ በድንግልናሃ ንጹሕ እግዚአብሔር ተወልደ። በጎለ እንስሳ ተወድየ፣ አምኃ ንግሡ ተወፈየ፤ ወከመ ሕጻናት በከየ፣ እንዘ ይስእል እምአጥባተ እሙ ሲሳየ።

በአባቱ ፈቃድ ወረደ፣ በማርያም ዘንድ፣ እንግዳ ሆነ፣ እግዚአብሔር በንጹሕ ድንግልናዋ ተወለደ። በእንስሳት በረት ተጨመረ፣ የንግሡንም እጅ መንሻ፡ ተቀበለ፣ ከእናቱ ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕጻናት አለቀሰ። (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ)
እግዚአብሔር አምላክ ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ፈጠረ ሌሎች ፍጥረታት ለአንክሮ ለተዘክሮ ሲፈጠሩ ሰውና መላእክት ግን ፍቅሩን ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ተፈጠሩ፡፡ ዘፍ 1፡1

የሰው ልጅን /አዳምን/ ፈጥሮ የሚያስፈልገውን አዘጋጅቶ፣ ዕውቀትንና ሥልጣን ሰጥቶ፣ በጸጋ አምላክነትን ሾሞ ፣መመሪያ ሰጥቶ፣ በክበር እንዲኖር ፈቀደለት ፡፡ በመጀመሪያው ዕለትና ሰዓት ከተፈጠሩት መላእክት መካከል በክብር ይልቅ የነበረው ሳጥናኤል /የኋላ ስሙ ዲያብሎስ / አምላከነት በመሻቱ ተወርዶ ሳለ አዳምንም በተዋረደበት ምኞትና ፍላጎት እንዲወድቅ ክብሩን እንዲያጣ ከአምላኩም እንዲለይ አደረገው፤ እግዚአብሔርን፣ ጸጋውን፣ ሹመቱን፣ ወዘተ አጣ /ኃጥአ/፡፡ ኃጢአት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከዚህ የተወሰደ ነው፡፡

አዳም ከእግዚአብሔር በመለየቱና ክብሩን በማጣቱ ተጸጽቶ ንሰሐ ገባ ፡፡ ሥርየተ ኃጢአት የሚሆን መስዋእትም በማቅረቡ፤ እግዚአብሔር አምላክ ልመናውንና መስዋእቱን ተቀብሎ እርሱንና ዘሩን ለማዳን እንደሚመጣ ቃል ኪዳን ገባለት “መልዓትንና ዓመታትን በዚህ ምድር ላይ ሠራሁልህ፡፡ ይኸውም እነርሱ እስኪፈጸሙ ድረስ በምድር ላይ ትኖርና ትመላለስ ዘንድ ነው፡፡ የፈጠረችህና የተላለፍካት ከገነት ያወጣችህና በወደቅህም ጊዜ ያነሳችህ ዳግመኛም አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም የምታድንህ ቃሌን እልክልሃለሁ” /ገድለ አዳም/ ብሎ እግዚአብሔር ለአዳም ነገረው፡፡ አዳምም አምስት ቀን ተኩል የሚለውን ቃል ከእግዚአብሔር በሰማ ጊዜ የእነዚህን ታላላቅ ነገሮች ትርጓሜ ሊያስተውል አልቻለም፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምስት ቀን ተኩል ማለት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት መሆናቸውን ገልጾ አርአያውና አምሳያው ለሆነው አዳም በቸርነቱ ተርጎመለት፡፡ እርሱንና ዘሩን ለማዳን እንደሚመጣ ተስፋ ሰጠው፡፡ ዘፍ 2፡7 ፣ሔኖክ 19 ፡19 ፣ ኩፋሌ 5፡6

አዳምም ይህንን ተስፋ ለልጆቹ አስተማራቸው፤ ልጆቹም ተስፋው የሚፈጸምበትን ጊዜ ለማወቅ በፀሐይ፣ በጨረቃና በክዋክብት /ዛሬም ቤተክርስቲያናችን ይህንን አቆጣጠር ትጠቀምበታለች/ ዘመናትን እየቆጠሩ “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ” ያለውን የአዳኝ ጌታ መወለድን ነብያት ትንቢት እየተናገሩ፤ አበውም ሱባኤ እየገቡ ተስፋውን ይጠብቁ ነበር፡፡ ከነሱም ውስጥ:-

1. ሱባኤ ሔኖክ

ሔኖክ ሱባኤውን ሲቆጥር የነበረው በአበው ትውልድ ሲሆን ሰባቱን መቶ ዓመት አንድ እያለ ቆጥሯል። በስምንተኛው ሱባኤ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወለድ ትንቢት ተናግሯል። አቆጣጠሩም ከአዳም ጀምሮ ነው። 8×700=5600ዓመት ይሆናል። 5500ዓመተ ዓለም ሲፈጸም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተወለደ ያጠይቃል።

ትንቢቱም እንዲህ ይላል። “ስምንተኛይቱ ሰንበት ጽድቅና ኩነኔ የሚታወቅባት ሰባኤ ናት፡፡ ሰይፍም ለርሰዋ ይሰጣታል፤ ታላቁ ንጉሥ የሚመሰገንበት ቤትም በርሰዋ ይሰራል፡፡ ምሥጋናውም ዘላለማዊ ነው፡፡” ሔኖክ 35፡ 1-2 ክፍል 91 በማለት ሲተነብይ መተርጉማን እንዲህ ይመልሱታል፡፡ ለርሰዋ ሰይፍ ይሰጣታል ማለቱ፤ ጸድቅና ኩነኔ የሚታወቅበት ወንጌል ያን ጊዜ በዓለም ሁሉ ትሰበካለች ማለት ነው፡፡ የታላቁን ንጉሥ ቤት ይሠራል ማለቱ፤ የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቱስ የሚመሰገንበት ቤተክርስቲያን ትሰራለች ማለት ነው፡፡ ምስጋናውም ዘላለማዊ ነው ማለቱ፤ ሰውና መላእክት በአንድነት ሆነው “ሰብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር” እያሉ ዘወትር ያመሰግናሉ ማለት ሲሆን ስምንተኛይቱ ሰንበት ለክርስቲያኖች የተሰጠችበትን ዕለት ልደት ክርስቶስ ናት ይሏታል፡፡

2 ሱባኤ ዳንኤል

yeledeteስለ ጌታችን ሰው መሆን ጊዜ ወስኖ ሱባኤ ቆጥሮ የተናገረው ዳንኤል ነው፡፡ የዳንኤል ሱባኤ የሚቆጠረው በዓመት ነው ፡፡ ዳንኤል 70ው ዘመን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ ተብሎ በኤርምያስ የተገረውን ትንቢት እያስታወስ ሲጸልይ መልአኩ ቅ/ገብርኤል በሰው አምሳል ተገልጾ እንዲህ ብሎታል፡፡ “እግዚአብሔር ልምናህን ሰምቶሃልና እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፡፡ አሁንም ነገሩን መርምር ራእዩንም አስተዋሉ ኅጢአት የሚሰረይበትን ቅዱሰ ቅዱሳን ጌታም የባህርይ ክብሩን ገንዘብ የሚያደርግበት ሰባው ሱባኤ ሊደርስ ሊፈጸም ነው ብለህ ወገኖችህን ቅጠራቸው ብሎታል፡፡” /ዳን 9፡22- 25 ኤር 29፡1ዐ/

ሰባ ሱባኤ አራት መቶ ዘጠና ዓመት ነው /7ዐX7= 490/ ይህ ጊዜ ከሚጠት እስከ ክርስቶስ መምጣት ያለው ጊዜ ነው /ትርጓሜ ሕዝ፡4፡6/

3. ሱባኤ ኤርምያስ

ኤርምያስ ከባቢሎን እንደተመለሰ በፈረሰው ቤተ መቅደስ ውሰጥ ሆኖ ሲጸልይ ሳለ ራዕይ አየ በሦስተኛው ቀንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ “ፈጣሪያችንን በአንድ ቃሉ አመሰግኑ የአብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን አመስግኑ ከዚህ በኋላ ሰው ሊሆን ሥጋ ሊለብስ ወደዚህ ዓለም ሊመጣ የቀረው 333 ሱባኤ ዕለት ነውና እርሱ ወደዚህ ዓለም ይመጣል፡፡ አሥራ ሁለት ሐዋርያትንም ይመርጣል…፡፡” ተረፈ ኤር 11፤37 ፣38፣42-48፡፡ ኤርምያስ ሱባኤውን የጀመረበትን ትንቢቱን የተናገረበት ራእዩን ያየበት ዘመን ዓለም በተፈጠረ 5054 ዓመት ነው፡፡ ስለዚህ ትንቢቱ ከተነገረበት እስከ ክርስቶስ ልደት ያለው ጊዜ 446 ዓመት ነው፡፡

ይኸውም በኤርምያስ ሱባኤ አንዱ 49ዐ ዕለት ነው መላው ሱባኤ 49ዐX333 = 163,170 ዕለት ሲሆን ወደ ዓመት ሲለወጥ 163, 170÷365 =446 ዓመት

ኤርምያስ ሱባኤውን መቁጥር የጀመረበት ዘመን …….. 5ዐ54 ዓመተ ዓለም

ትንቢቱ ከተነገረበት ዓመት እስከ ክርስቶስ ልደት ……. 446 ዓመት

በተነገረው ትንቢት በተቆጠረው ሱባኤ መሠረት 55ዐዐ ዓመት ሲፈጸም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቱስ መወለዱ በዚህ ይታወቃል፡፡

4. ዓመተ ዓለም

የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱሳት መጻሕፍትን መርምረው ሱባኤያትንና ሰንበታትን አውቀው ከአዳም እስከ ክርስቶስ ያለውን ዘመን ቁጥር 55ዐዐ ዓመት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ይኸውም ከአዳም አስከ ኖኅ …… 2256 ዓመት

ከኖኅ እስክ ሙሴ ……… 1588 ዓመት

ከሙሴ እስከ ሰሎሞን …. 593 ዓመት

ከሰሎሞን አስከ ክርስቶስ 1063 ዓመት

                        55ዐዐ ዓመት

ጌታችን ኢየሱስ በተነገረው ትንቢት፤ በተቆጠረው ሱባኤ መሠረት /ዓመተ ዓለም፣ ዓመተ ኩነኔ ፣ዓመተ ፍዳ/ አምስት ቀን ተኩል / 55ዐዐ ዓመት/ ሲፈጸም /በእግዚአሔር ዘንድ 1ዐዐዐ ቀን እንደ አንድ ቀን ናት፡፡ 2ኛ ጴጥ. 3፤8 / በ5501 ዓመት ማክሰኞ ታኀሣሥ 29 ቀን ተወለደ፡፡

“ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ሥምረቱ ለሰብእ” አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዘመኑ ፍጻሜ /የገባው ቃል ኪዳን፣ የተነገረው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባዔ/ ሲደርስ ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ያጣነውን ልጅነት ሊመልስልን፣ ከተቀማነው ርስት ሊያስገባን፣ የገባንበትን እዳ ሊከፍልልን ተወለደ፡፡

የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት ተወለደ ፡፡ ገላ 4፣4 እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፤ ቅዱስ ኤፍሬምም “ ቅድስት ድንግል ማርያም ፍጥረታትን ያስገኘ፤ የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችልን፡፡ የአሮን በትር ለምልማና ፍሬ አፍርታ ተገኝታ ነበር፤ ይህም ክርስቶስ በድንግልና የመወለዱ ምሳሌ ነው፡፡ እጹብ ድንቅ የሆነ ልደት በዛሬዋ ቀን እውን ሆነ፡፡ ድንግል የሆነችው ቅድስት ማርያም በድንግልና ጌታችንን መድኃኒታችንን ወለደችልን፡፡” ብሏል፡፡

“የእሥራኤል እረኛ ሆይ አድምጥ … በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ” ብሎ የለመነዉ የዳዊት ልመና በእዉነት ተፈጸመ፡፡ መዝ 70፥1። የእስራኤል እረኛ፤ በእረኞች መካከል በከብቶች በረት ተወለደ። ሉቃ 2፥7፡፡ እረኞች ለእረኛቸው ዘመሩ፤ ላሞች፣ በጎችና አህዮች በበረት የተኛውን ሕፃን በትንፋሻቸው አሟሟቁ። በኦሪት ድንኳን በሙሴ ሕግ መሠረት ለመሥዋዕት ይቀርቡ የነበሩ እንስሳት በልደቱ ደስ ተሰኙ፤ የነርሱን መሥዋዕት የሚያስቀር አማናዊው የእግዚአብሔር በግ ተወልዷልና።

ለሰው ሁሉ ብርሃን የሚሰጥ እግዚአብሔር በጨለማው ዓለማችን ተወለደ። (ዮሐ.1፥9-14) ነቢያትና መምህራን ጠፍተውባት፣ የኃጢአት ጨለማ ዉጧት፣ በድንቁርና ባሕር ውስጥ ሰጥማ በነበረችው የሰው ልጆች ዓለም የእውነት ፀሐይ ወጣ። እነሆ ይህን ይገልጥ ዘንድ መድኅን በእኩለ ሌሊት በጨለማ ተወለደ፤ በተወለደ ጊዜ ግን ክብሩ በዙርያው አበራ። (ሉቃ.2፥8-9)

ለመንግሥቱ ወርቅ ተገበረለት። ኃያል መንግሥቱን ግን በምድር ላይ በትህትና ነበር የገለጣት፤ በከብቶች በረት በመወለድና በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ በመሄድ። (ሉቃ.19፥28-38) የአባታችን የዳዊት መንግሥት ያለልክ ከፍ ከፍ አለች፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ የዳዊት ልጅ ሆኗልና። ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠራት ጊዜ “እርሱ ታላቅ ይሆናል፣ የልዑል ልጅም ይባላል፤ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፣ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለዉም” ብሎ የተናገረዉ ዛሬ ተፈጸመ፡፡ (ሉቃ.1፥32)፡፡

በባሕርይው የፍጥረት ሁሉ ገዥ የሆነዉ የእግዚአብሔር ልጅ ከዳዊት ልጅ ሥጋን ነስቶ ሰዉ በሆነ ጊዜ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን እስከ ጽርሐ አርያም ድረስ ከፍ ከፍ አደረጋት። እነሆ ንጉሥ ክርስቶስ በያዕቆብ ቤት (በምእመናን) ላይ ለዘላለም ነገሠ። ለመንግሥቱ የአሕዛብ ነገሥታት ተገዙላት፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ናትና ፍጥረታት ሁሉ ይገዙላታል። (ኤር.23፥5)

ለክህነቱ ዕጣን ተሰጠው። ክህነቱም የአበውን እና የሌዋውያንን ክህነት የምትፈጽም የዘላለም ሰማያዊት ሥራው ናት። እነሆ የአብ ሊቀ ካህናት እርሱ የሰውን ባሕርይ ከራሱ ጋር አስማማ። ራሱ ካህን፣ ራሱ መሥዋዕት፣ ራሱ ተቀባይ ሆኖ የፈጸማት የክህነት ሥራው የዘላለም ድኅነትን አስገኘች።

ለሞቱ ከርቤ ቀረበለት። እነሆ እግዚአብሔር ሰው የሆነበት ዋናው ምክንያት በሞቱ ሞትን ድል ለመንሣት ነውና በልደቱ ሞቱ ተሰበከ። ከርቤ ለሞቱ ሲቀርብለት የማይሞተው እርሱ ለሰው ልጆች ሲል የሚሞት ሥጋን እንደለበሰ ታወቀ።

የአሕዛብ ነገሥታት ወርቅ ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ጽሩይ፣ ንጹሕ፣ ሰማያዊ የሆነ ልቦናን እና እምነትን ለእርሱ እናቀርባለን። (1ኛ ጴጥ.1፥6) ሰብአ ሰገል ራሱ የፈጠረውን ወርቅ ገበሩለት፤ እኛም በርሱ ጸጋና ሥራ ያገኘነውን ንጹሕና ሰማያዊ እምነታችንን እናቀርብለታለን (ይሁ.3)።

ነገሥታቱ ዕጣን ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ቂም በቀል የሌለበትን፣ ከመልካም እና ከንጹሕ ልብ የሚወጣ የምስጋና ጸሎት እናቀርባለን፤ “ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፥ እጅ መንሣቴንም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን።” እንዳለ ንጉሥ ዳዊት (መዝ.140፥2) ።

ስለሰው ልጆች ፍቅር ሲል ለሚቀበለው ሞት ከርቤ ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ለእግዚአብሔርና ለሰው ልጆች ያለንን ፍቅር ለእርሱ እናቀርባለን። ነገሥታቱ እርሱ ከፈጠረው ከርቤ ወስደው እጅ መንሻ አቀረቡ፡፡ ምእመናን ደግሞ ከእርሱ ከተማርነው፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ከተቀበልነው ፍቅር መልሰን ለእርሱ እናቀርባለን። “እርሱ ስለኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል፡፡ (1ኛ ዮሐ.3፥16)።”

ነቢዩ ኢሳይያስ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸዉ” ብሎ የተናገረዉ ትንቢት ተፈጸመ (ኢሳ.9፥2)። የቅድስናዉ ተራራና ማደሪያው ወደ ሆነች ወደ መንግሥተ ሰማያት ይወስደናል፡፡ በዚች የዘላለም ሃገራችንም የሚያበራልን ፀሐያችን እርሱ ነዉ፡፡ (ራእይ.21፥23)።

እነሆ ሰው የመሆኑ ዜና የሰው ልጆች ሁሉ ደስታ ነው፡፡ “እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፡፡ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” የሚል ዜና በሰማያውያን መላእክት ተሰበከ። (ለቃ.2፥11)

የምድር ኃያላን ነገሥታት በከብቶች በረት ውስጥ በጨርቅ ተጠቅልሎ ለተኛው ሕፃን መብዓ አቀረቡ። ንጹሐንና ኃያላን የሚሆኑ የሰማይ መላእክት ደግሞ እግዚአብሔር ለሰው ፍቅር ሲል እንደ ሕፃን ተጠቅልሎ ሲያዩ በታላቅ ትሕትና ከእረኞች ጋር ዘመሩ። (ሉቃ.2፥13)

በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ድንቅ ነገር ተደረገ። ዳዊት በወርቅ ያጌጠ የተልባ እግር መጎናጸፊያ የለበሰባት ቤተልሔም የሰማይና የምድር ፈጣሪ በጨርቅ ተጠቅልሎ ተገኘባት። ቤተልሔም ከዳዊት ዘመን አብልጣ ከበረች፤ የእግዚአብሔር ክብር አብርቶባታልና፤ የልዑላን መላእክት ዝማሬ ተሰምቶባታልና። (ሚክ.5፥2)

በዚህች ዕለት እግዚአብሔር ወደ ኃጢአተኞች መጣ፤ ስለዚህ ጻድቁ በኃጢአተኞች ላይ አይታበይ፡፡ በዚህች ቀን የሁሉ ጌታ የሆነው እርሱ ወደ ባሮቹ መጣ፤ እናንተ ጌቶች ሆይ እንደ ጌታችን ለአገልጋዮቻችሁ ቸርነትን አድርጉላቸው፡፡ በዚህች ቀን ባለጠጋ የሆነው እርሱ ስለ እኛ ሲል ደሃ ሆነ፡፡ እናንተ ባለጠጎች ሆይ ከማዕዳችሁ ለድሃው አካፍሉ፡፡ በዚህች ቀን እኛ ያላሰብነውን ስጦታ ከጌታ ዘንድ ተቀበልን፤ እኛም ምጽዋትን ለሚጠይቁን ድሆች ቸርነትን እናድርግ፡፡ ከእኛ ይቅርታን ሽተው የመጡትን ይቅር እንበላቸው፡፡ በዛሬዋ ቀን የፍጥረት ጌታ የሆነው እርሱ ከባሕርይው ውጪ የሰውን ተፈጥሮ ገንዘቡ አድርጎ በሥጋ ተገልጦአልና፣ እኛም ወደ ክፉ ፈቃድ የሚወስደንን ዐመፃ ከእኛ ዘንድ አርቀን በአዲስና እርሱ በሰጠን መንፈሳዊ ተፈጥሮ እንኑር፡፡… እኛ በአምላክ ማኅተም እንድንታተም እርሱ አምላክነቱን ከእኛ በነሳው ሥጋ አተመው፡፡…ሰው አምላክ ሆነ አምላክ ሰው ሆነ ማለት ነው፡፡

የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር ፍቅሩን እያሰብን በኃጢያታችን ምክንያት ከልባችን ያወጣነው ሁሉ ዛሬም በልባችን እንዲወለድ ያስፈልጋል፡፡ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት አለ?” ማቴ. 2÷1
እግዚአብሔር ለምን ሰው ሆነ?

ከንጹሕ ባሕርይ ተፈጥሮ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ በደስታ ይኖር የነበረ ሰው የፈጣሪውን ትዕዛዝ በመተላለፉ ከንጽህና ወጥቶ ኃጢአትን ለበሰ:: ሕይወቱን አስወስዶ ሞትን ተቀበለ:: የእግዚአብሔር ልጅነቱን አስቀርቶ የዲያቢሎስ ምርኮ ሆነ:: ደስታውን አጥቶ ኃዘን አገኘው:: ተጸጽቶ የጥንት ሕይወቱንና ደስታውን ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም፤ ንጹህ ባሕርይው ስላደፈበት የሞት ፍርድን ሊያስቀርለት አልቻለም::

ዳግማዊ አዳም የተባለ የፍቅር አምላክ፣ የሁሉ ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሞት ፍርድን ሊያስቀር ኃጢአትን ደምስሶ ከሞት ፍርድና ከገሃነም ነጻ ሊያወጣ ዘር ምክንያት ሳይሆነው ሰው ሆነ፤ ተወለደ:: “እርሱም ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም።” 1ዮሐ 3:5

በዚህም መሰረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመተ ዓለም ዘመነ ዮሐንስ መጋቢት ሀያ ዘጠኝ ቀን እሑድ ከቀኑ ሶስት ሰዓት ተጸነሰ:: በአምስት ሺህ አምስት መቶ አንድ ዓመተ ዓለም በዘመነ ማቴዎስ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ማክሰኞ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ተወለደ::

ገናና የገና ጨዋታ

ገና-ጌና-ገኒን-ገነ፤ልደት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን በዓል ገና ወይም በዓለ ልደት በመባል ይታወቃል:: ገና የሚለው ቃል ገነወ አመለከ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወሰደ ነው:: የጌታችን ልደትም የአምላክ ሰው፤ ሰው አምላክ የመሆን ምሥጢር የተገለጠበት ታላቅና ገናና ስለሆነ ገና ተብሏል:: አምላክ አለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል እንዲል ሃይማኖተ አበው::

የገና ጨዋታ

በሃገራችን በኢትዮጵያ የገና በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ደምቆ ይከበራል:: በተለይ በገጠሩ ያገራችን ክፍል ከዚህ በዓል ጋር በተያያዘ አባቶችና እናቶች ክብረ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በገና ይደረድራሉ:: ወጣቶችም የገና ጨዋታ ይጫወታሉ:: “በገና” ስሙን ያገኘው በገና በዓል ወቅት የሚደረደር በመሆኑ ነው ሲሉ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያስተምራሉ:: በሌላም ትውፊት በተለይ በገጠሩ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶችና አዛውንቶች የሚጫወቱት የገና ጨዋታ ራሱን የቻለ ባህልና ትውፊት አለው:: የገና ጨዋታ ራሱ በተቆለመመ በትርና ሩር የተባለ ከዛፍ ሥር በተሠራ ክብ እንጨት(ኳስ) እያጎኑ የሚጫወቱት ጨዋታ ነው፡፡

ሰብአ ሰገል በኮከብ እየተመሩ ወደ ቤተልሔም ሲሔዱ “የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት አለ” በማለት ቢጠይቁ ይህንን አስደንጋጭ ጥያቄ የሰማው ንጉሥ ሔሮድስ “እኔ ንጉሥ ሆኜ ሳለሁ ሌላ ንጉሥ እንዴት ይወለዳል” በማለት የተወለደውን ንጉሥ ለመግደል አገልጋዮቹን ከሰብአ ሰገል ጋር ሄደው ቦታውን አይተው እንዲመለሱ ላካቸው፡፡ የሔሮድስ አገልጋዮች ከተቀላቀሉ በኋላ እየመራ ያመጣቸው ኮከብ ጌታ የተወለደበትን ቦታ መምራቱን አቆመ፡፡ ሰብአ ሰገል ተጨንቀው “የኮከቡ እርዳታ ለምን ተለየን” ብለው ሲመረምሩ ከነሱ ዓላማ ውጭ ሌላ ሀሳብና ተንኮል ይዘው የተገኙ ሰዎችን አገኙ፡፡ “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔርን እርዳታ አጣን”፡፡ ብለው ሦስቱም ነገሥታት(ሰብአ ሰገል) ከአንዱ ወደ አንዱ እየተቀባበሉ በብትር እየመቱ አስወገዷቸው፡፡

ኮከቡም እየመራ ጌታ በተወለደበት ቦታ ቤተልሔም አደረሳቸው ከእረኞችና ከመላእክት ጋራ አመሰገኑት፡፡ እረኞች ጌታ በተወለደ ጊዜ ጨለማ ተሸንፎ አካባቢያቸው በብርሃን ተመልቶ መንፈስ ቅዱስ በገለጸላቸው ምስጢር ከመላእክት ጋራ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ሥምረቱ ለሰብእ” እያሉ ሲያመስግኑና ሲደሰቱ አድረዋል፡፡ በአሉ እረኞች ክብር ያገኙበት ምስጢር የተገለጠላቸው ስለሆነ በስነ ቃል “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እየተባለም በጨዋታ እንደሚከበር እንደሆነ አበው ይናገራሉ፡፡

ይህ ትውፊት የገና ጨዋታ እየተባለ ወጣቶች አዛውንቶች በጨዋታ ያከብሩታል፡፡ ራሱ የተቆለመመውና ሩሯን የሚያጎነው በትር የጌታችን ምሳሌ ሲሆን ሩሩ ደግሞ የሳጥናኤል ምሳሌ ነው:: ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድረጎ የሰውን ሥጋ በመልበስ ወደዚህ ምድር እንደመጣና በሩር የተመሰለውን ሰይጣንን እንደቀጠቀጠው የሚያሳይ ምሥጢር ያለው ጨዋታ ነው::

 

 

 

sidet2

ከስደት የመመለሱ ምሥጢር

 ኅዳር 5 ቀን 2006 ዓ.ም.

ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ

እግዚአብሔር በሐዲስ ኪዳን ሊያደርገው ያሰበውን ነገረ ድኅነት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳንና ቅድመ ብሉይ ኪዳን ለሕዝቡ በተለያየ መንገድ መግለጹን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክሩልናል ዕብ 1÷1:: ምክንያቱም ፈታሒነቱና መሐሪነቱ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ነው ይሏል፡፡ የሰው ልጆች በዚያ ዘመን እግዚአብሔር ፈታሒነቱን በተከፈላቸው የኃጢአት ደመዎዝ የተረዱ ሲሆን መሐሪነቱን ደግሞ በተለያየ ኅብረ አምሳል መግለጹ አልቀረም:: ከእነዚያ ብዙ ከምንላቸው ኅብረ አምሳላት አንዱ እንዲህ የሚለው ነው “በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ ጎበዝ መሆን በጀመረ ጊዜ ወንድሞቹን ሊጎበኛቸው ወደ ወንድሞቹ ወጣ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታ ተመለከተ” ዘጸ.2÷11፡፡ በፈርዖን ቤተ መንግሥት ላደገው ለዚያ ሰው የተነገረለት ቃል በዕውነት አስደናቂ ነው፡፡ ዕድሜው በአባቶቻችን አነጋገር አርባ ዓመት ሆኖት የነበረው ይህ ሰው በጉብዝናው ወራት ወደ ወገኖቹ ሲመጣ ከተማው መከራ የበዛበት፤ ሕዝቡ ለቅሶና ዋይታ የጸናበት አስቸጋሪ ወቅት ሆኖ ነበር የጠበቀው፡፡ የሰው ልጆች ከአስገባሪዎቻቸው የተነሣ እስከ ጽርሐ አርያም ዘልቆ የሚሰማ ጩኸታቸውን አሰምተው የጮሁበት፤ እግዚአብሔርም የሰውን ጩኸት የሰማበት ጊዜ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር የመከራው ማለቂያ፤ የመጎብኘቱ ዘመን መግቢያ ነበር ማለት ነው፤ በመከራ ዘመን የሚጎበኝ ወዳጅ ታማኝ ወዳጅ ነውና፡፡

ይህ የመጎብኘት ወራት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚመጣበት ወራት አምሳል መርገፍ የሚሆን ወቅት ነበር፡፡ በዚያኛው ወራት የተነሣው ጎበዝ በመከራ ውስጥ ለነበረው ሕዝብ የደረሰለላቸው በአርባኛው ዓመቱ ነበር፡፡ በዚህኛው ወራት የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶከስም ለሕዝቡ የደረሰለት በአራተኛው ክፍለ ዘመን ነው (ዘመነ አበው፣ ዘመነ መሳፍንት፣ ዘመነ ነገሥት፣ ዘመነ ካህናት) እነዚህ አራት ክፍላተ አዝማናት በእውነት የሙሴን አርባ ዓመታት ይመስላሉ፡፡ የሙሴ አርባ ዓመታት በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ በዝምታ ያለፉ ዓመታት ናቸው፡፡

እስከ አርባ ዓመት ድረስ ሙሴ ወደ ወገኖቹ ሳይወጣ ለምን ዘገየ? በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ ያደገ ሰው ቢሆንም ቅሉ ፈረዖናዊ እንዳልሆነ ከእናቱ የሰማው ገና በልጅነት ዘመኑ አልነበረምን? ቢሆንም ግን ዘገየ፡፡ የፈርዖናውያን ግፍ እስኪፈጸም፤ የእስራኤልም መከራ እስኪደመደም አልጎበኛቸውም ነበር፡፡ ዛሬ የእስራኤል የመጎብኘት ወራት ከመድረሱም ባሻገር ሙሴ ጎበዝ በመሆኑ ግብፃዊውን ገድሎ እስራኤላዊውን ማዳን የሚችልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው፤ ስለዚህም ወደ ወገኖቹ ወጣ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዝምታ ያሳለፋቸው አራቱ ክፍላተ አዝማናትም ከዚህ ጋር ተመሳሳዮች ናቸው፡፡ የሰው ልጅ የቀኖና ጊዜውን እስኪያጠቃልል መንጸፈ ደይን ወድቆ ለዘመን ዘመናት ያለቀሰ ቢሆንም በአራቱም ክፍላተ አዝማናት የነበረው የእግዚአብሔር ዝምታ አንዳንዶችን “ኢሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እስራኤል አዶናይ፤ በዚህ ሰማይ እስራኤልን የሚጠብቅ ጌታ እግዚአብሔር የለምን?” ብለው በሰለለ ድምፅ እንዲናገሩ አድርጓቸዋል፡፡

የመጎብኘት ጊዜው ሲደርስ የዲያብሎስ ምክሩ እንዲፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ወደ ወገኖቹ መጣ፡፡ ይህ ወራት የአዳም ሥጋ ጎበዝ እየሆነ የመጣበት ወራት በመሆኑ በወገኖቹ ላይ የነበረውን ፍዳና መርገምን እንቢ ብሎ ያለ ኃጢአትና ያለ በደል ሆኖ ተፀነሰ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የግብፃዊው ምሳሌ የሆነው ዲያብሎስ ጉድጓዱ ተማሰ፤ ወገኖቹን ሊጎበኛቸው በመጣው በዚያ ሰው በኩል የማይደፈረው ተደፈረ፤ ግብፃዊው ተቀበረ፡፡ ይህ ጎበዝ እየሆነ የመጣው የሙሴ ወገኖች የተስፋ ምልክት እንደነበረ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳን ለተደረገለት ቅዱስ ሕዝብም እግዚአብሔር ወደ ወገኖቹ የመጣባት የመጀመሪያዋ ዕለተ ፅንስ ከሲዖል እስከዚህ ዓለም ለነበሩ ነፍሳት የፀሐይ ብርሃን ብልጭ ያለባት ዕለት ናት፡፡ ከዚህም የተነሣ የዓመተ ምሕረት መጀመሪያ አድርገን እንቆጥራታለን፡፡

ምንም እንኳን ሙሴ ግብፃዊውን ገድሎ ሊታደጋቸው የሚችል መሆኑን ያስመሰከረ ቢሆንም ወገኖቹ ግን በእልልታ የተቀበሉት አይደሉም፡፡ እርሱ ግን በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያምኑ ይመስለው ነበር ሐዋ.ሥራ.7÷25፡፡ እስራኤልን የመታደግ ሥራውን ግብፃዊውን በመግደል የጀመረው ያ ታላቁ ታዳጊያቸው ከሁለት ቀን በኋላ ባደረገው ወገኖቹን የመጎብኘት ሥራ ከወገኖቹ በጎ ነገርን ሊያስገኝለት አልቻለም፤ ከሀገር ወጥቶ እንዲሰደድ የሚያደርግ ክፉ ሀሳባቸውን ሰማ እንጂ፡፡ ከወገኖቹ ከንቱ ሀሳብ የተነሣ አርባ ዓመታትን ያለ ኃጢአትና በደሉ በስደት አሳለፈ የምድያምን ካህን በጎች እየጠበቀ በባዕድ ምድር ለረጅም ዘመን ተቅበዘበዘ፡፡ ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ሲሄድ የንጉሡ የልጅ ልጅ መባልን እንደ መቀማት አልቆጠረውም ራሱን ዝቅ አድርጎ በምድያማውያን ምድር ለሚገጥመው የመስቀል መከራ እንኳን የታዘዘ ሆነ እንጂ፤ የግብፅ ጌታዋ ሙሴ እንደ ባሪያ ዝቅ ብሎ የበግ እረኛ ሆነ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከቀደሙት መሳፍንት ሁሉ በላይ የሆነ ስምን ሰጠው በግብፅ ካለው ተድላ ደስታ ይልቅ ከወገኖቹ ጋር መከራ መቀበልን መርጧልና መከራ በተቀበለላቸው ወገኖቹ ላይ ሹም አድርጎ ደስ አሰኘው፡፡

sidet2የአባቶቹን ዕዳ ሊከፍል የመጣው ዳግማዊው ሙሴ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዓለም ነቢያትን እንዳሳደደች እርሱንም እንዲሁ አደረገችበት፡፡ ሙሴ ግብፃዊውን በገደለውና ለእስራኤልም የመዳን ተስፋን ባሳየ በሁለተኛው ቀን ከሀገር አስወጥታ እንዳሳደደች፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በሰው ልጆች ታሪክ ጉልህ ስፍራ የነበረውን ቁራኝነትን በማጥፋት ይቅርታውን አሐዱ ብሎ በጀመረበት በሁለተኛ ልደቱ ሲገለጥ በገዛ ወገኖቹ በካህናትና በነገሥታት ምክር ከሀገር ወጥቶ ተሰደደ፡፡ ሙሴ ወደ ወገኖቹ የመጣባት ሁለተኛይቱ ቀን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም በሥጋ የመጣባት ሁለተኛይቱ ልደቱ ሲነጻጸሩ እጅግ ይገርማሉ፡፡ ስለ ወገን እንጂ ስለ ራስ መኖርን የሚያስንቁ ዕለታት! እንደዚያኛው ወራት በዚህም ወራት ስለ ሕዝቡ የሚቆረቆር ሌላ ሙሴ ለምድር ተወልዶላታል፡፡ እግዚአብሔርነቱን እንደ መቀማት ሳይቆጥረው የባሪያውን መልክ ይዞ ከሰማይ ወደ ምድር መጣ፡፡ በብዙ ሠራዊት ዘንድ ጌታ የሆነው እርሱ ከአብ ጋር ተካክሎ ሲኖር ሳለ በፈቃዱ ከክፉ ወገኖቹ መካከል ተለይቶ ወደ ምድረ አፍሪቃ ተሰደደ፡፡ ሙሴን የሕዝቡ መከራ ውል ብሎ እየታየው በፈርዖን ቤት በደስታ መኖርን እንደከለከለው ከሕዝቡ ጋርም ስለሕዝቡ መከራ መቀበልን እንዲመርጥ እንዳደረገው ኢየሱስ ክርስቶስንም በሕዝቡ የደረሰው ግፍ ከሰማይ ወደ ምድር አመጣው፤ ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች እስኪል ድረስ አስጨነቀው ፡፡

ሙሴ ስለ ሕዝቡ ወደ ምድረ አፍሪቃ ወርዶ በግ ጠባቂነትን ሥራ አድርጎ ኖረ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ራሱን የገለጠው በዚህ ስም እንደነበረ ቅዱስ ወንጌል ምስክርነትን ይሰጠናል “እኔ የበጎች እረኛ ነኝ” እንዲል ዮሐ10÷11፡፡ በእውነት እዚህ ላይ ያለውን የእግዚአብሔር ዐሳብ እስኪ በደንብ ተመልከቱት፡፡ ለአርባ ዓመታት ግብፃዊነትን ስሙ አድርጎ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን ተቀብሎ ይኖር የነበረው ሰው ሙሴን አስነስቶ በጉብዝናው ወራት ወገኖቹን አስጎበኘው፡፡ ያንን ተከትሎ ግብፅን ለቆ እንዲወጣ አድርጎ ከሌሎች ዐርባ ዓመታት በኋላ ተመልሶ ወገኖቹን እንዲያድናቸው አደረገው፡፡ እግዚአብሔር ጥበበኛ አምላክ ነው፤ ያባቶቹን የያዕቆብንና የአስራ ሁለቱን አባቶች ስደት የሚመልስ ትውልድ አስነስቶ ከግብፅ በተገኘው ሰው ግብፅን በዘበዛት፡፡ ይህንንም በማድረጉ በዚህኛው ወራት ለኛ ሊያደርጋት ያሰባትን በጎ ነገር አስቀድሞ ነገረን፡፡ በዚያኛው ወራት ሕዝቡን የታደገው መሪ በግብፅ ምድር ተወልዶ በፈርዖን ቤት ያደገ ነው እንዳልን ሁሉ በዚህኛው ዘመን ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ሊያድናቸው የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስም ከግብፃዊው ሰው ከአዳም የተገኘ ተገኝቶም ስለ ወገኖቹ የሚቆረቆር ሆነ፡፡ በአባ እንጦንስ አነጋገር ግብፃዊ ማለት ሥጋዊ ስሜቱን ብቻ የሚንከባከብ ሰው ስያሜ ነው፡፡ አባ እንጦንስ ወደ ገዳማቸው እንግዳ ሲመጣ ስለመጣው እንግዳ መረዳት ሲፈልጉ እንግዳውን ለሚቀበለው ደቀ መዝሙር የሚያቀርቡት ጥያቄ “ግብፃዊ ነው? ወይስ ኢየሩሳሌማዊ?” የሚል ነበር:: ሥጋዊው በግብፃዊ መንፈሳዊው በኢየሩሳሌም ይሰየማሉና፡፡

የሙሴ እናት በፈርዖናዊው የባርነት ወቅት ሳለች ሙሴን ወለደች ለሌላው ትውልድ መድኃኒት እንዲሆን ታስቦም ለሦስት ወራት ሸሸገችው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም የተወለደው ዓለም በዲያብሎስ ብርቱ የዐመጻ ውጊያ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ ነበር፡፡ በተወለደበት ወቅት ብዙ ሕፃናት ለሞት የተዳረጉ ቢሆንም እርሱ ግን ለብዙዎቹ ለመዳናቸው፤ ለመነሣታቸው የተሾመ ነበርና እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ሶስት ዓመታትን ሸሸገችው፡፡ ከዚያም በኋላ በግብፃውያን መካከል አድጎ ለግብፃዊቷ ዓለም ይደርስ ዘንድ ስደትን ገንዘብ አደረገ የአባቱ ያዕቆብ እና የሌሎችም ቅዱሳን ስደት እንዲያበቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰደደ፡፡ ሲሰደድ ከጥቂቶቹ በስተቀር ስደቱን ማን አወቀ? ሕዝቡን ሲያወጣ ግን በሁሉም ዘንድ የተገለጠ ነበር፡፡ ስደቱ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ መዳን ምክንያት ይሆናል ብሎ ማን አሰበ? ግን ሆነ፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አፍሪቃ ምድር ተሰዶም እንደ ሙሴ በእግዚአብሔር መልአክ እስኪጠራ ድረስ በምድረ አፍሪቃ መቀመጥን መረጠ ዘጸ3÷4፤ማቴ2÷20፡፡ ለዚህም ነው በመነኮሳቱ መጽሐፍ “ንዑ ንርአዮ ለወልደ መንክራት” ተብሎ የተጻፈው፡፡ ሙሴ ከግብፅ አስማተኞች ጋር ባደረገው ክርክር አሸንፎ ሕዝቡን ይዞ በመኮብለል ከግብፅ ወጣ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በግብፅ ያሉትን ገዳመ ሲሐትን፤ ገዳመ አስቄጥስን ባርኮ፤ በግብፃውያን የሚመሰሉ አጋንንትን አባሮ እስክንድርያን መንበር አደረጋት፡፡ ከዚያ እስከ ዛሬ ግብፅ ያፈራቻቸው ቅዱሳን ሁሉ የዚያ ስደት ውጤቶች ናቸው፡፡ በሙሴ ወደ ግብፅ መመለስ የሞቱትም በሕይወት ያሉትም እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደ ተመለሱ፤ አማናዊው ሙሴ ኢየሱስ ክርስቶስም በስደቱ ለሞቱትም በሕይወት ላሉትም አባቶቻችን ተስፋ እያደረጓት ሳያገኟት ከሩቅ እየተሳለሟት ወደ አለፏት ቅድስት ምድር መንግሥተ ሰማያት ለመመለሳቸው ምልክት ሆነ፡፡ የክርስቶስ ከኢየሩሳሌም ወደ ግብፅ መሄድ ከገነት ወደ ሲኦል ያለውን የሰው ልጆች ስደት የሚያመለክት ሲሆን፤ ከግብፅ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገው መመለስ ደግሞ ከሲኦል ወደ መንግሥተ ሰማያት ያደረግነውን የይቅርታ ጉዞ ያሳያል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በሙሴ መታዘዝና ወደ ግብፅ መውረድ ሕገ ኦሪት በሙሴ ተመሠረተች፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ መስቀል የደረሰ መታዘዝ ወንጌል ተመሠረተች፡፡ ለሁሉም ግን መሠረቱ ስደት መሆኑን ልብ ይሏል ፡፡ በዚያኛው ወራት በሙሴ የተመሰረተችው ማኅበር በዚህኛው ወራት በኢየሱስ ክርስቶስ ለተመሰረተችው ማኅበር ምሳሌ ነበረች፡፡ አባቶቻችን ነቢያቱ የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን እንደ ስደተኛ ቆጥረው “ተመየጢ ተመየጢ ሱላማጢስ፤ ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ ተመለሽ” መኃ 7÷1 እያሉ ሊያዩአት ሲመኙ ነበሩ ጊዜው ሲደርስ የሄሮድስ ሞት የስደት ዘመኗን አሳለፈው፡፡ ሔሮድስ የዲያብሎስ ምሳሌ ሲሆን ዲያብሎስ በመስቀል ራስ ራሱን ተቀጥቅጦ ሲሞት ቤተ ክርስቲያን ግን መኖር ጀመረች፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ በጠላቶቿ ላይ ድልን እየተቀዳጀች፤ ጠላቶቿን አሳልፋ ባለ ማለፍ ጸንታ ትኖራለች፡፡

እመቤታችን የሄሮድስን ሞት ከሰማች በኋላ ቁስቋም ከሚባል ተራራ ላይ ሆና ደስታዋን አብረዋት መከራን ከተቀበሉት ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር አከበረች፡፡ የቤተ ክርስቲያንም ደስታ የሚጀምረው በተራራ ላይ ነው፡፡ እመቤታችን ደብረ ቁስቋም ላይ ሆና ከአባቷ ዳዊት ጋር “ርኢክዎ ለኃጥእ አብየ ወተለዐለ ከመ አርዘ ሊባኖስ ወሶበ እገብዕ ኃጣዕክዎ፤ ኃጥእ ሔሮድስን ከፍ ከፍ ብሎ ተመለከትኩት ስመለስ ግን አጣሁት” መዝ 36÷35 ብላ ዘመረች፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ቀራንዮ ላይ ለዘመን ዘመናት ያስጨነቃት ዲያብሎስ ተወግዶላት የሞቱትንም በሕይወት ያሉትንም አንድ አድርጋ በደስታ ዘመረች፡፡ የዚያኛው ወራት ስደት ለቀደመው የእግዚአብሔር ሕዝብ ከግብፅ መውጣት፤ የዚህኛው ወራት ስደት ለአሁኑ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከሲኦል መውጣት ፊታውራሪ ነው፡፡ ያኛው ሕዝብ በዚያኛው ስደት እንደተዋጀ ይሄኛው ሕዝብ ደግሞ በዚህኛው ስደት ተዋጀ፡፡ ምክንያቱም ስደቱ ስደታችንን ሲያመለክት መመለሱ መመለሳችንን ያሳያልና፡፡

 

አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል

 መስከረም 20 ቀን 2007 ዓ.ም. 

በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል አምላካችን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፤ እንደ ሕፃናት ቀስ በቀስ አድጎ፤ ወንጌልን ለዓለም ሰብኮ፤ ለሰው ልጆች ቤዛ ይሆን ዘንድ፤ በሞቱ ሞትን ይሽር ዘንድ፤ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ በትንሣኤውም ለሰው ልጆች ትንሣኤን አወጀ፡፡ በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል የነበረውንም የጥል ግድግዳ አፈረሰ፡፡ የሰው ልጆች ያጣነውን የእግዚአብሔር ልጅነትንም አገኘን፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ወወሀብኮሙ ትዕምርተ ለእለ ይፈርኁከ ከመ ያመስጡ እምገጸ ቅስት ወይድኅኑ ፍቁራኒከ” ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው መዝ.49፡4 እንዲል፡፡ “ጠላቶቻችንን በአንተ ድል አናደርጋቸዋለን” በማለት የመስቀልን ክብርና አሸናፊነት አብስሯል፡፡መዝ. 43፡5፡፡

“እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኀኒተ በማዕከለ ምድር” እግዚአብሔር ዓለም ከመፈጠሩም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድርም መካከል መድኀኒትን አደረገ፡፡ መዝ. 73፡16 በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደተቀኘው እግዚአብሔር የሰውን ልጆች ለማዳን የቃልኪዳን ቦታዎችን በዚህች ምድር ላይ አዘጋጅቷል፡፡ በዓለም ላይ ቃል ኪዳን ከተሰጣቸው ቅዱሳት መካናት መካከል አብዛኛዎቹ በኢትዮጵያ ሀገራችን ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በግምባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም አንዷ ናት፡፡ አባቶቻችን “ግሸን ደብረ ከርቤ መካነ መስቀሉ ለክርስቶስ እንተ ይእቲ ኢየሩሳሌም” የክርስቶስ መስቀል መንበር የሆነችው ግሸን ደብረ ከርቤ ናት ይህችውም ኢየሩሳሌም ናት በማለት ግሸን ደብረ ከርቤ ከኢየሩሳሌም ጋር እኩል መሆኗን መስክረውላታል፡፡

የጌታን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ መስቀል በቅድስት እሌኒ በ325 ዓ.ም. ከተቀበረበት ከወጣና በክብር ለረጅም ዓመታት በኢየሩሳሌም ከተቀመጠ በኋላ ዐረቦች ኢየሩሳሌምን በመውረራቸው ምክንያት በአረማውያን እጅ እየተማረከ ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ ሀገር ሲንከራተት ቆይቷል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖችም በመስቀሉ መማረክ ያዝኑና ይበሳጩ ስለነበር ጦራቸውን አሰልፈው መስቀሉ ወደሔደበት ሀገር በመዝመት ጦርነት ያካሔዱ ነበር፡፡

በ778 ዓ.ም. አራቱ አኅጉራት ለበረከት ይሆናቸው ዘንድ በአራቱ የመስቀሉ ክንፍ የተያያዙት ምልክቶችን በማንሳት የተከፋፈሉ ሲሆን በወቅቱ በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ዐረቦች በእስክንድርያ ለሚኖሩ አባቶች የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሮቹ እና እጆቹ ተቸንክረው የተሰቀለበትን ሙሉ መስቀል ላኩላቸው፡፡ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስም በክብርና በጥንቃቄ እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡

የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር መስቀሉ ለብዙ ዘመናት በግብፅ እስክንድርያ ከቆየ በኋላ የግብፅ እስላሞች ቁጥራቸው በመበራከቱ በክርስቲያኖች ላይ የመከራ ቀንበር ስላጸኑባቸው ከዚህ ስቃይ ይታደጓቸው ዘንድ ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዐፄ ዳዊት “ንጉሥ ሆይ በዚህ በግብፅ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና ኃይልህን አንስተህ አስታግስልን” ብለው ይልካሉ፡፡ አንዳንድ መጻሕፍት ደግሞ የግብፅ ንጉሥ አቡነ ሚካኤልንና አቡነ ገብርኤልን በማሰሩ ምክንያት ከዚህ አስከፊ ችግር እንዲታደጓቸው ክርስቲያኖች መልእክት እንደላኩባቸው ይገለጻል፡፡ መልእክቱ የደረሳቸው ፄ ዳዊትም ስለ ሃይማኖታቸው በመቅናት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት አሰልፈው ወደ ግብፅ ይዘምታሉ፡፡ በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከልም እርቅ እንዲወርድ ተደረገ፡፡

የግብፅ ክርስቲያኖችም ዐፄ ዳዊት ስላደረጉላቸው መልካም ነገር እጅ መንሻ ይሆናቸው ዘንድ ብዛት ያለው ወርቅና ብር ያቀርባሉ፡፡ ዐፄ ዳዊት ግን ፍላጎታቸው ወርቅና ብሩን መውሰድ ሳይሆን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል እንዲሰጧቸው ይጠይቃሉ፡፡ በጥያቄያቸውም መሠረት ተሰጣቸው፡፡ “መስቀልየ ይነብር በዲበ መስቀል” የሚል ራዕይ አይተው ስለነበር ጉዟቸውን በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ያደርጋሉ፡፡ በመንገድም እያሉ ያርፋሉ፡፡ ዐፄ ዳዊት መስከረም 10 ቀን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከግብፃውያን የተቀበሉበት ቀን በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ተቀጸል ጽጌ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡

ከዐፄ ዳዊት በኋላ በቦታቸው የተተኩት ዐፄ ዘርዐያዕቆብ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” የሚል ራዕይ በማየታቸው መስቀሉን በ1443 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት በተለያዩ ቦታዎች ለማሳረፍ ጥረት አድርገዋል፡፡ በደብረ ብርሃን፤ በሸዋ ደርሄ ማርያም፤ በጨጨሆ፤ በአንኮበር፤ በመናገሻ አምባ፤ በእንጦጦ፤ ወዘተ አሳርፈውት አልተሳካላቸውም፡፡ በመጨረሻም መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም. በራዕይ በተነገራቸው ቅዱስ ስፍራ በግሸን ደብረ ከርቤ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አኑረውታል፡፡

የተራራው ተፈጥሯዊ አቀማጥ ሲመለከቱት አንድ ጥሩ አናፂ ከጥሩ እንጨት ባማረ ጌጥ ጠርቦ የሰራው ግሩም የእጅ መስቀል ይመስላል፡፡ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም መሠረቱ የተጣለውና ቤተ ክርስቲያን ሊታነጽ የበቃው በ514 ዓ.ም. በዐፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት አባ ፈቃደ ክርስቶስ በሚባሉ አባት ነው፡፡ አባ ፈቀደ ክርስቶስ የዐፄ ካሌብ የንስሐ አባት ሲሆኑ በየመን ሀገረ ናግራን ላይ የነበሩ የእግዚአብሔር አብና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሁለት ጽላቶችን ወደ ኢትዮጵያ ይዘው በመምጣት በግሸን ደብረ ከርቤ ተራራ ላይ በማኖር ሲቀደስባቸውና ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደረስባቸው ቆይተዋል፡፡ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም የአሁኑን ስም ከማግኘቷ በፊት በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ስሞች ስትጠራ የቆየች ሲሆን ደብረ ነጎድጓድ፤ ደብረ እግዚአብሔር፤ ደብረ ነገሥት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና መጻሕፍት ለአፍሪካ የደረሰው የመስቀሉ ቀኝ ክንፍ ብቻ ነው ሲሉ፤ የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም አበው ሊቃውንት ግን አጥብቀው እንደሚቃወሙት መጻሕፍት ያረጋግጣሉ፡፡ መስቀሉ ለአራቱ ክፍለ ዓለማት ሲከፋፈል መስቀሉ ላይ ተለጥፈው የነበሩት ምልክቶች በማንሳት ለሦስቱ ክፍለ ዓለማት እንደተሰጠና ለአፍሪካ ግን ሙሉ መስቀል እንደደረሰ ይመሰክራሉ፡፡ ዛሬም በኢትዮጵያ ውስጥ በግሸን ደብረ ከርቤ በእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው መስቀል የቀኝ እጁ በኩል ብቻ ሳይሆን ሙሉው የክርስቶስ መስቀል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያያናችንም ይህንን መሠረት በማድረግ መስከረም 21 ቀን በየዓመቱ በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በድምቀት ታከብራለች፡፡

  • ምንጭ፡- አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል 1990 ዓ.ም.

ግሸን ደብረ ከርቤ የቃል ኪዳን አምባ ቀሲስ በላይ ተገኝ 1996 ዓ.ም.

ቅዱሳት መካናት በኢትዮጵያ ዘመድኩን በቀለ 1992 ዓ.ም.

 

meskel damera

ወሰአረ መርገመ በዲበ ዕፀ መስቀል

መስከረም 16 ቀን 2006 ዓ.ም.

በመ/ር ምስጢረ ሥላሴ ማናየ

 

  • መርገምን በመስቀል ላይ ሻረ” ቅዱስ አትናቴዎስ ሃይማኖተ አበው

በቅmeskel dameraድሚያ ከዘመን ወደ ዘመን ያሸጋገረን ለብርሃነ መስቀሉ ያደረሰን በሀብቱ የሳበን በረድኤቱም ያቀረበን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡

ከላይ በርዕሱ ያነሣነው ኃይለ ቃል ቅዱስ አትናቴዎስ የመስቀሉን ነገር በተናገረበት ድርሳኑ የተናገረው ነው፡፡ አስተሀፈረ ኃጢአተ በዲበ ምድር ወሰአረ መርገመ በዲበ ዕፀ መስቀል ወአብጠለ ሞተ በውስተ ሲዖል ወነሰተ ሙስና እምውስተ መቃብር”

“በምድር ላይ ኃጢአትን አሳፈረ መርገምን በመስቀል ላይ ሻረ ሞተ ነፍስን በሲዖል አጠፋ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን በመቃብር አፈራረሰ” በማለት ጌታችን ለሰው ልጆች ነጻነት እና ድኅነት የከፈለውን የቤዛነት ሥራ በተናገረበት ክፍል የተናገረው ነው የሰው ልጆች ነጻነታቸው የተዋጀው በመስቀል ተሰቅሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በሥልጣኑ ለይቶ ዲያብሎስን በመስቀሉ ገሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲዖል ወርዶ ነፍሳትን ከዲያብሎስ ባርነት ከአጋንንት ቁራኝነት ከሲዖል ግዛት ነጻ አውጥቷቸዋልና፡፡

“ሞተ በሥጋ ወሐይወ በመንፈስ ወወረደ ኀበ እለ ሙቅሕታ ትነብር ነፍሶሙ ወሰበከ ሎሙ ግዕዛነ” በሥጋ ሞተ በመንፈስ /በመለኮት/ ግን ሕያው ነው እርሱም ደግሞ ሄደ በወህኒ /በሲዖል/ ለነበሩ ነፍሳት ነጻነትን ሰበከላቸው” 1ጴጥ.3፡18

መስቀል በዓለመ መላእክት
መስቀል በዓለመ መላእክት በጥንተ ፍጥበረት ሰባቱ ሰማያት በተፈጠሩበት ዕለተ እሑድ ሥላሴ ጽርሐ ዓርያምን ከእሳት ዋዕዩን ትቶ ብርሃኑን ነሥቶ በፈጠረበት ጊዜ በውስጧ ታቦት ዘዶርንና የብርሃን መስቀልን ቀረፀባት ይላል ሊቁ ኤጲፋንዮስ ሥነ ፍጥረትን አምልቶ አጉልቶ በጻፈበት አክሲማሮስ በተባለ መጽሐፉ ይህ በእንዲህ እንዳለ እግዚአብሔር መላእክትን ፈጥሮ በተሰወራቸው ጊዜ ዲያብሎስ እኔ ፈጠርኳቸው ባለበት ሰዓት በአለመ መላእክት በመላእክትና በዲያብሎስ በተደረገው ጦርነት መላእክት ዲያብሎስን ድል ያደረጉት በመስቀል መሣሪያነት ነው፡፡

“በሰማይ ሰልፍ ሆነ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን /ዲያብሎስን/ ተዋጉት ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውም ከዚያም ወዲያ በሰማይ ቦታ አልተገኘለትም ዓለሙን የሚያስተው ሁሉ ምድር ተጣለ መላእክቱም /ሠራዊተ ዲያብሎስ/ ከእርሱ ጋር ተጣሉ” ራዕ.12፡7፡፡

በዚህ ውጊያ መካከል የነበረውን ሁኔታ ሲገልፅ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዲያብሎስ ሁለት ጊዜ ዲያብሎስ ድል ነሳቸው በሦስተኛው ፈጣሪያቸውን ጠየቁ ፈቃድህ አይደለምን ዲያብሎስን እንድንዋጋው አሉት፤ መላእክት ፈቃዴስ ነው ግን ድል የምታደርጉበትን ኃይል እንድታውቁ ብዬ ነው ብሎ በክንፋቸው ላይ የብርሃን መስቀል ቀረጸላቸው በእጃቸው የብርሃን መስቀል አስያዛቸው ሄደው ገጠሙት “ጐየ እግዚእ ምስለ ዓርያሙ” ጌታ ሰማይን ጠቅልሎ ሸሸ ብሎ እየደነፋ ወደ ምድር ወረደ ይላል፡፡ ስለዚህ መስቀል ፀረ ዲያብሎስነቱ የታወቀው ጌታችን ከመሰቀሉ በፊት ነው፡፡ ኃይሉም የተገለጠው ያን ጊዜ ነው፡፡

በሌላ መልኩ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ የመላእክትን ምስጋና በገለጠበት እንዲህ ሲል ጽፏል “ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን ከፍ ባለ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ አየሁት ኪሩቤልና ሱራፌል ዙሪያውን ነበሩ ለእያንዳንዱም ስድስት ስድስት ክንፍ ነበራቸው በሁለት ክንፋቸው ፊታቸውን ይጋርዳሉ በሁለት ክንፋቸው እግራቸውን ይጋርዳሉ በሁለት ክንፋቸው ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይበራሉ፡፡ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ እያሉ ያመሰግናሉ” ኢሳ.6፡1-6፡፡

ሲበሩ ክንፋቸውን መዘርጋታቸው የመስቀል ምልክት ከመሆኑም በተጨማሪ አምላክ ሰው ሆኖ በመስቀል ተሰቅሎ ዓለምን እንደሚያድነው ምልክት ነበር፡፡
ይህን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “በአርአያ ትዕምርተ መስቀል” በመስቀል ተሰቅለህ ዓለምን ታድናለህ ሲሉ ነው ብሎ ተርጉሞታል፡፡

መስቀል በዘመነ አበው
በዘመነ አበው መስቀል የመባረኪያ ምልክት እንደነበረ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ ለምሳሌ፡-
“በተአምኖ አመይመውት ያዕቆብ ባረኮሙ ለደቂቀ ዮሴፍ ለእለ አሐዱ” ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ የዮሴፍን ልጆች በእምነት ባረካቸው” ዘፍ.47፡31፣ ዕብ.11፡22 “ወአስተሐለፈ እዴሁ ላዕለ ርዕሰ ኤፍሬም ወምናሴ” እጆቹን በኤፍሬምና በምሴ ላይ በመስቀል አምሳል አመሳቀለ እጆቹንም በራሳቸው ላይ ጭኖ ባረካቸው ይላል፡፡ 

ዛሬም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህኑ ቀድሶ በሚወጣበት ጊዜ በእጆቹ ይባርካል ይህም የሚያሳየው ቤተ ክርስቲያኗ መሠረቷ ከላይ በዓለመ መላእክት ከታች በዘመነ አበው ያየነው መስቀል መሆኑን ነው፡፡ “በአምስት ቀን ተኩል ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመስቀል ተሰቅዬ ሞቼ አድንሃለሁ” የሚል የተስፋ ቃል ተሰጥቷል፡፡

መስቀል በዘመነ ነቢያት እና በዘመነ ነገሥት
መስቀል በዘመነ ነቢያት በዘመነ ነገሥት እንደየሀገሩ ግእዝን /ሁኔታ/ ልዩ ልዩ ተግባራት ሲፈጽሙበት ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ፡- ለወንጀለኞች መቅጫነት አገልግሏል በዕርግጥ አሁንም የወንጀለኞች የአጋንንት መቅጫ ነው ለሚያምኑበት ግን የጭንቅ መውጫ የነጻነት መገለጫ ነው፡፡

በተለይ ፋርስ ሰዎችን ሰቅሎ መግደል መገለጫዋ ነበር የተጀመረውም በፋርስ ነው ሰውን በመስቀል ሰቅሎ መግደል የባቢሎን እቶነ እሳት እና አናብስት፣ የሮማውሪያንና የፋርስ ስቅለት የአይሁድ ውግረት  መቅጫቸው ነው፡፡

መርዶክዮስን ሊሰቅል ባዘጋጀው መስቀል የተሰቀለው ሐማ በፋርስ ሕግ ነበር “እነሆ ሐማ ለንጉሡ በጎ ለተናገረው ለመርዶክዮስ ያዘጋጀው አምሳ ክንድ የሆነ ግንድ በሐማ ቤት ተተክሎአል “ንጉሡም በእርሱ ላይ ስቀሉት አለ ሐማንም ለመርደክዮስ ባዘጋጀው ግንድ ላይ ሰቀሉት” አስቴ.7፡9፡፡

በእርግጥም ይህን አልን እንጂ ይህ ሥርዓት ከፋርስ ወደሮማውያን ተላልፎ በመቅጫነት አገልግሎአል፡፡ አይሁድም ብዙ ጊዜ ወንጀለኞችን የሚቀጡት በውግረት በእሳት በማቃጠል ቢሆንም በመስቀልም ይቀጡ ነበር፤ ምክንያቱም መነሻው ኦሪት ነውና የኦሪት መደበኞች ደግሞ ፋርሶች ወይ ሮማውያን ሳይሆኑ እነርሱ ናቸው፡፡

“ርጉም ውእቱ ኩሉ ዘስቁል ዲበ ዕፅ” ዘዳ.21፡23 ሰርቆ ቀምቶ በእንጨት የተሰቀለ የተረገመ ይሁን” ተብሎ የተጻፈው በኦሪት ነው፡፡ ስለዚህ መስቀል የወንበዴ የሌባ መቅጫ የጥፋተኛ መቀጥቀጫ ነበር፡፡ በአይሁድ ሕግ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች አይገረፉም በመስቀል ይቀጡ ነበር፡፡ ከተገረፉ ደግሞ አይሰቀሉም፤ የፈጸሙት በደል ለዚያ ርግማን የሚያበቃ አይደለም፡፡ ማለት ነው፡፡

መስቀል በዘመነ ነቢያት በብዙ ኅብረ ትንቢት አሸብርቆ በብዙ ኅብረ አምሳል ደምቆ የመጣ እንጂ፤ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ድንገት የተገኘ አይደለም፡፡ ለእስራኤል በ40 ዘመን ጉዟአቸው ውስጥ ተአምራት በማረግ የታዩት የሙሴ በትር እና በምድረ በዳ ሙሴ የሰቀለው አርዌ ብርት የታየበት አላማ የመስቀል ምልክቶች ወይም ምሳሌዎች ነበሩ፡፡

የሙሴ በትር ባሕር ከፍሏል ጠላት ገሏል መና አውርዷል ደመና ጋርዷል ውኃ ከአለት አፍልቋል፤ በግብጻውያን ላይ ድንቅ ድንቅ ተአምራት አድርጓል፡፡ ሙሴም ምሳሌው የሆነለት ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀልም ባሕረ እሳትን ከፍሏል ማየ ገቦን ደመ ገቦን ለመጠጣችን ለጥምቀታችን አስገኝቷል፡፡ ኃይሉን በዲያብሎስና በአጋንንት ላይ አሳይቷል፡፡ ነፍሳትን ከሲዖል ባርነት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነጻ አውጥቷል፡፡ “ወሀደፎሙ በመስቀሉ” በመስቀሉ አሻገራቸው” እንዲል መጽፈሐፈ ኪዳን፡፡ ሙሴ በምድረ በዳ የሰቀለው የነሐስ እባብ ክርስቶስ በመሰቀል የሚፈጽመውን የማዳን ሥራ የሚያሳይ ነበር፡፡

“ሙሴም ስለ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ እግዚአብሔርም ሙሴን “የናስ እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል እባቡም ሰውን ቢነድፍ የተነደፈው ሁሉ ይመልከተው ይድናልም” ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ እባቡም የነደፊችው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ” ዘኁ.21፡7፡፡

የነሐሱ እባብ የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ የነሐሱ አባብ ጽሩይ ነው ክርስቶስም ጽሩየ ባሕርይ ነውና የነሐሱ እባብ መርዝ የለበትም ክርስቶስም መርገመ ሥነጋ መርገመ ነፍበስን የሚያርቅ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን የሚያድል ክፋት ተንኮል የሌለበት ነውና እባቡ የተሰቀለበት ዓላማው ደግሞ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀልምሳሌ ነበር፡፡

እባብ የነደፈው ሁሉ በተመለከተው ጊዜ ይድን እንደነበር የሰው ልጅ በሙሉ በእባብ ዲያብሎስ መርዝ ተነድፎ ቆስሎ በኃጢአት ተመርዞ ሲኖር በመስቀል በተፈጸመው የቤዛነት ሥራ ድኗልና፡፡
“ወበከመ ሙሴ ሰቀሎ ለአርዌ ምድር በገዳም ከማሁ ሀለዎ ለወልደ እጓለመሕያው ይሰቀል ከመ ኩሉ ዘየአምን ቦቱ ኢይትሐጐል አላ የሐዩ ለዓለም”

ሙሴ እባብን በምድረ በዳ እንደሰቀለው እንዲሁ የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል የአመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል” ዮሐ.3፡15፡፡

ከነቢያት ዳዊት እንዲሁም ልጁ ሰሎሞን የመስቀሉን ነገር አምልተው አጉልተው ተናግረዋል፡፡ “ወወሀብኮሙ ትዕምርተ ለእለይፈርሁከ ከመ ያምስጡ እምገፀ ቅሥት”  “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው ወዳጆችህ እንዲድኑ” መዝ.59፡4 ለመዳን የተሰጠ ምልክት ደግሞ መስቀል ነው ለዚህ ነው እኛ ኦርቶዶክሳውያን በአንገታችን የምናስረው በእጃችን የምንይዘው የምንሳለመው የምንባረክበት ምክንያቱም የመዳን ምልክት ነውና፡፡

ጥበበኛው ሰሎሞንም የመስቀሉን ነገር በተናገረበት አንቀጽ እንዲህ ይላል “ሐረገ ወይን ኮነ መድኃኒትየ ዘእምሐሲሦን ይትገዘም ወበጎልጎታ ይተከል” “የወይን ሐረግ /መስቀል/ መድኃኒቴ ሆነ ሐሲሦን ከተባለ ቦታ ይቆረጣል በጎልጎታ ይተከላል” መኃ.3፡44 ግዕዙን ተመልከት፡፡

ዳዊት ለመዳን የተሰጠ መሆኑን ሲገልጽ ልጁ እንጨቱ ከየት ተነቅሎ በየት ቦታ እንደሚተከል እና መድኃኒትነቱን አጉልቶታል ስለዚህ መስቀል በብሉይ ኪዳን ትልቅ ቦታ ይዟል ማለት ነው፡፡
መስቀል በሐዲስ ኪዳን

መስቀል ከብሉይ ኪዳን ይልቅ የመዳን ምልክት መሆኑ የተረጋገጠበት በክርስቶስ ደም የተቀደሰ የጠብ ግድግዳን ያፈረሰ ቅድስና ያለው ክብር ያለው የአበው ተስፋ የተፈጸመበትም ሰው ከውድቀቱ የተነሳበት መሆኑ ተረጋጋጧል፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን ጌታችን የተሰቀለበት መስቀል የተዘጋጀው ከሰባት ዓይነት ዕፅዋት ነው፡፡
1.    ሳኦል ከገነት ያስመጣው ዕፅ
2.    ሰሎሞን ቤተ መቅደስን በሠራበት ወቅት ሠረገላ አድርጎ የተጠቀመበት ዕፅ
3.    ከመቃብረ አዳም የበቀለ ፅፀ ሕይወት
4.    ሎጥ በእንባው ያለመለመው ፅፀ ከርካዕ
5.    ታቦተ ጽዮንን ይሸከሙበት የነበረው ሠረገላ
6.    ጌታችን በቢታንያ የረገማት ዕፀ በለስ
7.    ዘኬዎስ ጌታችንን ለማየት የወጣበት ዕፀ ሠግለ /ሾላ/ ከእነዚህ ሰባት ዕፅዋት በተዘጋጀ መስቀል ነው ጌታችን የተሰቀለው /መጽሐፈ ኪዳን ትርጓሜ ተመልከት/ 

ጌታችን ከእነዚህ ዕፅዋት የተዘጋጀ መስቀሉን ተሸክሞ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀሉ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ ቀድሶታል በዚህ የተነሣ መስቀል ነዋይ ቅዱስ ነው መስቀል በሐዲስ ኪዳን ሁለት መሠረታዊ ትርጉሞች አሉት፡፡
1.    ጌታችን የተሰቀለበት ከሰባት ዕፅዋት የተዘጋጀውን መስቀለኛ እንጨት /ቅዱስ መስቀል/
2.    ጌታችን ዓለምን ለማዳን የተቀበለው መከራ መስቀል ይባላል መስቀል ስንል እነዚህን ከላይ ያነሳናቸውን ሁለት አበይት ትርጉሞች ማስታወስ የግድ ይላል፡፡

ስለ መስቀል የክርስቶስ ትምህርት
ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ደጋግሞ ነገረ መስቀልን አስተምሯል፡፡ “ዘኢጻረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይጸመደኒ” መስቀሉን የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ የእኔ ሊሆን አይገባውም” ማቴ.10፡38፣ 16፡24፣ ማር.8፡34፣ ሉቃ.9፡23፣ 14፡27፡፡

ጌታችን ይህንን ያስተማረው ከመሰቀሉ በፊት መሆኑ ግልፅ ነው በቃል ካስተማረው በኋላ በተግባር ፈጸመው መስቀሉን እንድንሸከም መከራውን እንድንቀበል አስቀድሞ አስጠነቀቀን መስቀሉ የሌለው የክርስቶስ ሊሆን እንደማይችል አስረግጦ ነገረን፡፡

ከዚህ የተነሣ ክርስቶስ ራሷ የሆነላት ሐዋርየዊት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መስቀሉን በየዓመቱ በየወሩ ታከብረዋለች ትሸከመዋለች፡፡ በመስቀሉ የሚገኘውን መከራ ትቀበላለች በመስቀሉ የሚገኘውን በረከት ታድላለች ክርስቶስን በግብር ትመሰለዋለች በእግር ትከተለዋለች የእርሱ መሆኗ መልክት መስቀሉ ነው፡፡

“በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” ማቴ.16፡24፡፡ “የሰው ልጅ /ክርስቶስ/ ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል” ማቴ.20፡18፡፡ መስቀል ስንል ይህን ሁሉ መከራ ያጠቃልላል ይህ ሁሉ መከራ የተፈጸመበት ነዋይ ቅዱስም መስቀል ይባላል፡፡

“ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንዲሆን ታውቃላችሁ የሰው ልጅ ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል” ማቴ.26፡1፡፡ ይህ እስከ አሁን ጌታችን በቃል ያስተማረውን ተመልክተናል ተግባሩ እነሆ፡-“የአይሁድ ንጉሥ ሰላም ላንተ ይሁን እያሉ ዘበቱበት ተፉበትም መቃውን ይዘው ራሱን መቱት ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት ልብሱንም አለበሱት ሊሰቅሉት ወሰዱት ሲወስዲትም ስምዖን የተባለ የቀሬና /ሊቢያ/ ሰው አገኙ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት ትርጓሜው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ሥፍራ በደረሱ ጊዜ ሰቀሉት” ማቴ.27፡29፡፡ መስቀል ማለት ይህን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡

ሰሎሞን የወይን ሐረግ መድኀኒቴ ሆነ ከሀሲሦን ይቆረጣል በጎልጎታ ይተከላል” ያለው ተፈጸመ መድኃኒት መስቀል መድኃኒት ክርስቶስን ተሸክሞ ታየ መድኃኒት ክርስቶስ የሚሰቀልበትን መስቀል ተሸክሞ ደፋ ቀና ብሎ መከራን ሲቀበል ተመለከትን መስቀሉን እርሱ ብቻ አይደለም ተከትዮቹ እነስምዖን ቀሬናዊም ተሸከሙት የድካሙ ተካፋይ ሆኑ፡፡ ልዩነቱ እነ ስምዖን ተገደው እኛ ግን ወደን ነው፡፡ እነ ስምዖን በአጋጣሚ እኛ ክርስቲያኖች ግን በዓላማ ክርስቶስን እንመስለው ዘንድ መስቀሉን የማይሸከም ለእኔ ሊሆን አይገባውም ብሎ አስተምሮናልና በተግባርም ፈጽሞ አሳይቶናልና፡፡
ከሰቀሉትም በኋላ እንዲህ ዘበቱበት “የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምንበታለን” ማቴ.27፡40-42

“ኢየሱስንም ይዘው ወሰዱት መስቀሉንም ተሸክሞ በእብራይስጥ ጎልጎታ ወደተባለው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ በዚያም ሰቀሉት” ዮሐ.19፡17፡፡ ራስ ቅል ስፍራ ማለት የአዳም የራስ ቅል የተቀበረበት ቦታ ነው መስቀሉ የተተከለበት ቦታም ይህ ነበር ለአዳምና ለልጅ ልጆቹ የተፈጸመ ካሳ ነውና፡፡

“እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር” እግዚአብሔር ከዓለም በፊት ንጉሥ ነው በምድር መካከል መድኀኒትን አደረገ” መዝ.73፡13፡፡ ይህ መድኃኒት ዓለም የዳነበት ቅዱስ መስቀሉ አይደለምን?

“ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል” የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ በቀራንዮም መድኃኒት መስቀል ተተከለ” እንዲል ስለሆነም መስቀልን ስናስብ ለእኛ የተከፈለውን የአምላካችንን የቤዛነት ሥራ የተቀበለውን መከራ የተገረፈውን ግርፋት የታሰረበት ሀብል የተሰቀለበትን መስቀል የጠጣውን መራራ ሐሞት እደቹ እና እግሮቹ የተቸነከሩበትን ቅንዋት /ችንካሮች/ ጎኑ የተወጋበትን ጦር የፈሰሰውን ደሙን የተቆረሰ ሥጋውን በጠቅላላው ለእኛ ሲል አምላካችን የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ እናስባለን፡፡

ስለ መስቀል የሐዋርያት ትምህርት
ስለ ቅዱስ መስቀል ከክርስቶስ ቀጥሎ ያስተማሩት ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው፡፡ ርዕሰ ሐዋርየት ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ያስተምራል፡፡ “ወበእንተ ኃጣውኢነ ውእቱ ተሰቅለ ዲበ ዕፀ በሥጋሁ ከመያውጽአነ እምኃጣውኢነ” ስለ ኃጢአታችን እርሱ በእንጨት /በመስቀል/ ላይ ተሰቀለ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ” 1ጴጥ.1፡24 በማለት በመስቀሉ ክርስቶስ የከፈለልንን ዋጋ ነገረን፡፡
“ወንገረ መስቀሉሰ እበድ ውእቱ በኃበ ህጉላን ወለነሰ ለእለ ድኅነ ኃይለ እግዚአብሔር ወጥበበ እግዚአብሔር ውእቱ” 1ቆሮ.1፡18፡፡ 

“የመስቀሉ ቃል /ትምህርቱ/ ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚብሔር ኃይል ነው በማለት እግዚአብሔር ኃይሉን የገለጠበት ማዳኑን ያሳየበት ትድግናው የተከናወነበት መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ይህን ዓለም አልተቀበለውም አላወቀምና፡፡

“እኛስ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” 1ቆሮ.1፡2 ሲል የክርስቶስ መገለጫው መስቀሉ ነው፡፡ ዙፋኑ ነውና ዲያብሎስን የቀጣበት ኃይሉን የሻረበት ነውና ሰው ይህን መቀበል ካልቻለ ሰው መሆኑ ያጠራጥራል፡፡

“እስመ ይቤ መጽሐፍ ርጉም ውእቱ ኩሉ ዘስቁል ዲበ ዕፅ ወለነሰ ተሣሃለነ እመርገማ ለኦሪት” መጽሐፍ በእንጨተ የተሰቀለ ሁሉ ርጉም ይሁን ይላልና እኛን ግን ከኦሪት ርግማን በእንጨት ተሰቅሎ ዋጀን” ገላ.3፡12፡፡

የኦሪትን ርግማን ተቀብሎ በእንጨት መስቀል ተሰቅሎ መርገሙን ወደበረከት ለወጠልን መስቀል የእርግማን ምልክት ሳይሆን የድል፣ የነጻነት፣ የበረከት ምልክት መሆኑን አወጀልን፡፡ እኛም ይህን ተቀብለን መስቀል ኃይላችን ነው መስቀል መድኃኒታችን ነው እንላለን፡፡ በመስቀሉ እንመካለን ጥግ አድርገን ጠላታችንን እንዋጋበታለን፡፡

“በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሏችሁ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው ገላ.5፡12፡፡ ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት /ከኃጢአት/ የተለየበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት /ከኃጢአት የተለየሁበት/ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ”

እዚህ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ከኃጢአት የተለየበት ከእግዚአብሔር ጋር የታረቀበት መመኪያው መስቀል እንደሆነ ከመሰከረ እኛስ ከእርሱ አንበልጥም እኔን ምሰሉ ብሎናልና” 1ቆሮ.11፡1፡፡ ስለዚህ ነው በመስቀሉ የምንመካው የምናከብረው ኃይላችን ብለን የምንጠራው መስቀሉን መስቀል የሰላም መሠረት ነው ጥልን /ዲያብሎስን/ የገደለ /ድል የነሣ/ ለሰው ሰላም የተደረገበት ነው፡፡

“ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን /ሕዝብና አሕዛብን/ በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው” ኤፌ.2፡16፡፡ “ወገብረ ሰላመ በደመ መስቀሉ ለእለ ውስተ ሰማይ ወእለ ውስተ ምድር ወዘታህቴሃ ለምድር በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ለራሱ /ከራሱ ጋር/ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና ቆላ.1፡20፡፡ ለዚህ ነው መስቀል ሰላም ነው የሰላም ምልክት ነው የምንለው ሰውና መላእክት ሰውና እግዚአብሔር ሕዝብና አሕዛብ ነፍስና ሥጋ የታረቁበት ነውና፡፡

“በትዕዛዛት የተጻፈውን የእዳ ጽሕፈት ደመሰሰው እርሱንም በመስቀል ጠርቆ አስወግዶታል ቆላ.2፡14፡፡ እንግዲህ የዕዳ ደብዳቤያችን የተሻረበት እኛ ጸጋና ክብርን የተጎናጸፍንበት የዕርቅ የሰላም የመዳን ምልክት ነው መስቀል፡፡

ስለዚህ ብዙዎች መስቀልን ይወዱታል በአንጻሩም ብዙወች ባለማወቅና በክፋት ይጠሉታል ሊቀብሩት ፈለጉ ለምን? ተአምራት በማድረጉ ድውይ በመፈወሱ ሙት በማስነሣቱ፣ እውር በማብራቱ ባለቤቱን ክርስቶስን እንደጠሉት ሁሉ መስቀሉን የጠሉ አይሁድ መስቀሉን ለ300 ዓመታት ቀበሩት መስቀል ገቢረ ተአምራት የሚያደረግ ተቀብሮ ይቀር ዘንድ የማይቻል ነውና በእሌኒ ንግሥት አማካኝነት ከተቀበረበት ወጣ መስቀል በጎልጎታ ብቻ አይደለም የተቀበረው በክርስቶሳውያን ልቡና ጭምር እንጂ ስለሆነም ቀብሮ ማስቀረት አይቻልም ይልቁንም ቤዛነቱን ኃይሉን ተአምራቱን አምኖ መቀበል ነው፡፡

በጥንታውያን ክርስቲያኖች መስቀል ተቀብሮ ከወጣበት ጊዘ ጀምሮ እሌኒ ንግሥት ቤተ መቅደስ ከሠራችለት ጊዜ ጀምሮ በመስከረም አሥራ ሰባት ቀን አሁን በኢትዮጵያ እንደሚከበረው ይከበር ነበር፡፡ ዛሬ ግን በኢትዮጵያ ብቻ በደማቅ ሁኔታ ሲከበር በሌሎች ታስቦ ይውላል፡፡ ይህም የሚያሳየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቱያን ታሪክን በመጠበቅ ከሌሎች ይልቅ ምን ያህል ብርቱ እንደሆነች ያሳያል፡፡

ለመስቀሉ ጠላቶች የተሰጠ ተግሳጽ
ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና ብዙ ጊዜ ስለ እርሱ አልኳችሁ አሁንም እንኳ እያለቀስኩ እላለሁ መጨረሻቸው ጥፋት ነው ሆዳቸው አምላካቸው ነው ክብራቸው በነውራቸው ነው አሳባቸው ምድራዊ ነው” ፊል.3፡18፡፡

የመስቀሉ በረከት ይደርብን

anoros gedam 5.jpg

አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ

መስከረም 13 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

anoros gedam 5.jpgአቡነ አኖሬዎስ በ13ኛው መ.ክ.ዘ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ናቸው፡፡ ትልቁ አኖሬዎስ ይሏቸዋል፡፡ የአቡነ ዜና ማርቆስ የእኅት ልጅ ናቸው፡፡ አባታቸው ቄስ ሰላማ እናታቸው ክርስቶስ ዘመዳ ሲባሉ የትውልድ ቦታቸው ምዕራብ ሸዋ ሙገር አካባቢ ልዩ ስሙ ማትጌ በሚባል ቦታ ነው፡፡ ገድለ ዜና ማርቆስ አባቱ ዘርዐ አብርሃም የተባለ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት ዘመድ ነበረ ይላል፡፡

ለአቡነ አኖሬዎስ ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ናርዶስ ሲሆን በሕፃንነታቸው የዳዊትን ንባብና የመጻሕፍትን ትርጓሜ ከተማሩ በኋላ በወቅቱ ከነበሩበት ግብፃዊ ጳጳስ ዲቁና ተቀበሉ፡፡ በወቅቱ ሐራንኪስ የተባለ የትርጓሜ መጻሕፍትና የዜማ ዐዋቂ በቤታቸው በእንግድነት ለብዙ ጊዜ በቆየበት ወቅት ለአቡነ አኖሬዎስ ዜማና ትርጓሜ መጻሕፍት በሚገባ አስተምሯቸዋል፡፡ በዚህም ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ዜማና ትርጓሜ መጻሕፍት የበለጠ ለመረዳት ከነበራቸው ፍላጎት አንጻር ወደ ደብረ አስቦ (ደብረሊባኖስ) በመሔድ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር ተገናኙ፡፡ በደብረ አስቦ (ደብረሊባኖስ) በገዳም ለረዥም ዓመታት ካገለገሉና ከተማሩ በኋላ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት እጅ መንኩሰው አባ አኖሬዎስ ተባሉ፡፡

የገዳሙ መነኮሳት በሊቀ ዲያቆንነት መርጠዋቸው ትርጓሜ መጻሕፍትና ዜማ ያስተምሯቸው ነበር፡፡  ትጋታቸውን ያዩት የገዳሙ መነኮሳትም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት በታች የገዳሙ መጋቢ አድረገው መረጧቸው፡፡ በዚያ ዘመን በገዳሙ ወንዶች እና ሴቶች መነኮሳዪያት በአንድነት ይኖሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አቡነ አኖሬዎስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አማክረው የሴትና የወንድ ገዳም እንዲለይ አደረጉ፡፡ ከዚህ በኋላ በወቅቱ በነበሩት አቡነ ቄርሎስ ዘንድ ተልከው ቅስናን ተቀበሉ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካረፉ በኋላ ወደ ትግራይ ጸዐዳ አምባ ተጉዘው ከአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ጋር ቆዩ፡፡ ነገር ግን አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ወዲያው ስላረፉ ወደ ደብረ አስቦ ተመልሰው አበ ምኔቱን እጨጌ ፊልጶስን እየተራዱ ገዳሙን ማገለግሉ ጀመሩ፡፡

anoros gedam 7.jpgበ1317ዓ.ም ንጉሥ ዓምደ ጽዮን በዘመነ መንግሥቱ የስብከተ ወንጌልን መስፋፋት ሥራ አጠናከረ፡፡ ይኸውም ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ ሲያርፉ ወደ ግብፅ ልዑካንን ልኮ አቡነ ያዕቆብን አስመጣ፡፡ በዚህ ወቅት አቡነ ያዕቆብ ከአቡነ ፊልጶስ ጋር በመነጋገር “ኢትዮጵያ በአንድ ጳጳስ መወሰን የለባትም፡፡” በማለት እጨጌ አቡነ ፊልጶስን ኤጲስ ቆጶስነት ሰይመው ሐዋርያዊ አገልግሎት እንዲፈጽሙ ዐሥራ ሁለቱን ንቡራነ ዕድ ለስብከተ ወንጌል በመላዋ አገሪቱ ክርስትና እንዲስፋፋ አቡነ ያዕቆብ ባቀረበው ሀሳብ መሠረት ተሰማሩ፡፡ እነሱም አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ /ኤጲስ ቆጶስ/፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘሞረት፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋር፣ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣አቡነ አኖሬዎስ ዘወረብ፣አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፣አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘግድም፣ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመርሐ ቤቴ፣ አቡነ አድኃኒ ዘዳሞት፣ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል፣ አቡነ ኢዮስያስ ዘወጅ፣ አቡነ ዮሴፍ ዘእናርያ ነበሩ፡፡

ሀገረ ስብከት ተሰጥቷቸው ለሐዋርያዊ ተልእኮ ተሰማሩ፡፡ ይህ የተቀናጀ የስብከተ ወንጌል ሥምሪት ሲደረግ ከተሰዓቱ ቅዱሳን በኋላ መጀመሪያና ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነው፡፡ እነዚህ ዐሥራ ሁለቱ አበው “ንቡረ እድ” የሚል መጠርያ ኖሯቸው ክህነት ከመስጠት ውጭ ያለውን የኤጲስ ቆጶሱን ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ለአቡነ አኖሬዎስ እንደ ግብጦን የተባለ ቦታ ደረሳቸው፡፡ ይህ ቦታ ከግንደ በረት እስከ ባሌ ያለውን አገር ያካትታል፡፡ እርሳቸውም ባሌ በመሄድ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ተክለው ክርስትናን አስፋፉ፡፡ የሐዋርያነት አገልግሎታቸው እስከ ኬንያ ድንበር ደርሶ ነበር፡፡

በአካባቢው ስብከተ ወንጌልን ካስፋፉ በኋላ ባርጋባን የተባለ የአካባቢው ሰው ደግነታቸውንና ትምህርታቸውን ተመልክቶ በጽጋጋ ገዳም (ደሴ አካባቢ) እንዲመሠርቱ ጋበዛቸው፡፡ ጽጋጋ እንደ ደረሱ መምለክያነ ጣዖታት በእጅጉ ተቃውመዋቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በትምህርታቸውና በበርጋባን ረዳትነት ተቃውሞው በረደ፡፡ በርጋባንም በትምህርታቸው ይማረክ እንጂ ክርስቲያን አልነበረምና ተጠምቆ ዘካርያስ ተባለ፡፡ አቡነ አኖሬዎስም የአካባቢውን ሕዝብ ለማስተማር ካላቸው ፍላጎትና የምነና ሕይወትንም ለማጠናከር በጽጋጋ ገዳም መሠረቱ፡፡ በገዳሙ የሚሰበሰቡት መነኮሳትም ቁጥር በየቀኑ ይጨምር ነበር፡፡ ከትውልድ አካባቢያቸውም በየጊዜው ብዙዎች ይመጡ ነበር፡፡

አቡነ አኖሪዎስ ዘወረብ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ ይህም ወረብ በሚባለው ሥፍራ በተጋድሎ የቆዩበት ቦታ በመሆኑና ዐፅማቸው በዚያ እንደተቀበረ ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንድ የእስልምና ተከታይ ወረብ ከተባለው አካባቢ የአቡነ አኖሪዎስ ነው ብሎ ያመጣው መስቀል አሁን በጽጋግ ገዳማቸው ይገኛል፡፡

 አቡነ አኖሬዎስ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን 1297-1317 ዓ.ም የአባቱን ዕቁባት ማግባቱን ሰሙ በጉዳዩም እጅግ አዝነው እጨጌ አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ፣ አቡነ ናትናኤል፣ አባ እንድርያስ፣ አባ ድምያኖስ፣ አባ ዮሐንስ፣ አባ ገብረ ናዝራዊ፣ አባ ዘርዐ ክርስቶስ፣ አባ ገብረ አምላክ፣ አባ ብንያም፣ አባ አቡነ አሮን ዘደብረ ዳሬት ይዘው ወደ ንጉሡ ከተማ መጡ፡፡

ንጉሥ ዓምደ ጽዮንም የአባቶችን ድንገት መምጣት አይቶ “ምን አመጣችሁ?” ብሎ ሲጠይቃቸው አቡነ አኖሬዎስ “የአባትህ ዕቁባት እናትህ ማለት ስለሆነች ማግባትህ አግባብ አይደለም፡፡ መኝታህን ማርከስህን ተው፡፡ ያለበለዝያ እንለይሃለን፤ ሥጋ ወደሙንም አናቀብልህም አሉት” ንጉሡም መነኮሳቱን አስደበደባቸው፡፡ ደማቸውም በአደባባይ ፈሰሰ፡፡ በዚያ ዕለት በከተማው እሳት ተነሥቶ እስከ ቤተ መንግሥቱ በመድረሱ ማስደብደቡን ትቶ በአማካሪዎቹ የቀረበለትን ሐሳብ በመቀበል ወደ ሩቅ አገር ለማጋዝ ወሰነ፡፡ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን ይህንን ተግሳጽ ከቁም ነገር አልቆጠረውም ነበር፡፡ ነገር ግን ሥጋወ ደሙ በድፍረት  ሊቀበል በቀረበ ጊዜ አባቶች “የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ” ተብሏል ብለው  ከለከሉት፤ እየተናደደ ወደ ቤተ መንግሥት ገባ፡፡ በቤተ መንግሥቱም ጳጳሱን፣ ንቡራነ እዱንና በአንድ ሐሳብ የጸኑ ሌሎች ሰባ ሁለት ካህናት አስጠርቶ አቡነ ያዕቆብ ከእኔ አያስጥላችሁም፡፡ በአስቸኳይ ወደ ሀገሩ(ግብፅ) እልከዋለሁ፡፡ ሲል በቁጣ ተናገራቸው፡፡ እነርሱ ግን “በቤተ ክርስቲያን ትምህርት መሠረት ኑር፣ የአባትህን ሚስት መፍታት ይገባሃል” ብለው ጸኑበት፡፡

በዚህ ምክንያት አባቶች እየተጋዙ በሰሜን በደቡብና በምዕራብ ኢትዮጵያ ተሰደዱ፡፡ ከእነርሱ ስደት በኋላ ብዙ ካህናትና መነኮሳት ወደ ንጉሡ መጡ፡፡ በድፍረትም ይገሥጹት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት መነኩሴ ወደ ከተማ እንዳይገባ እስከ መከልከል ደርሷል፡፡ በመጨረሻ አባ እንድርያስ የተባሉ አባት ወደ ንጉሡ መጥተው መክረው ንስሐ አስገብተው ወደ ቤተ ክርስቲያን መለሱት፡፡
አቡነ አኖሬዎስ ወደ ወለቃ /ደቡብ ወሎ ጋሥጫ አካባቢ/ ተጉዘው ለጥቂት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ዓምደ ጽዮን ዐረፈ፡፡ መንግሥቱንም ሰይፈ አርዕድ ወረሰ፡፡ ንጉሥ ሰይፈ አርዕድም የተጋዙት አባቶች በሙሉ እንዲመለሱ ዐወጀ፡፡ አቡነ አኖሬዎስም ወደ በኣታቸው ጽጋጋ ተመለሱ፡፡

ንጉሥ ሰይፈ አርዕድ እንደ አባቱ የአባቱን ዕቁባት ማግባቱን ሰሙ፡፡ ቀድሞ ንጉሥ ዓምደ ጽዮንን የገሰጹት እነዚያ ቅዱሳን አባቶች ተሰባስበው ወደ ንጉሡ መጡ፡፡ አቡነ አኖሬዎስ አፈ ጉባኤ ሆነው ንጉሡን ገሰጹት፡፡ ንጉሡም በወታደሮቹ አስደበደባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ከአፍ እና ከአፍንጫቸው ብዙ ደም ፈሰሰ፡፡ በኋላም ምድረ ጸወን ወደምትባል አገር /ደቡብ ወሎ፣ ቦረና/ ተጋዙ፡፡ በዚያም እጅግ ብዙ ተአምራት ማድረጋቸውና የንጉሡን ተግባር መቃወማቸው ስለተሰማ እንደገና ወደ ዝዋይ ደሴት ገማስቄ በምትባል ሥፍራ እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡

በዝዋይ እያሉም ነገረ ሠሪዎች ወደ ንጉሡ ቀርበው “አኖሬዎስ ሠራዊትህን ሁሉ ማርኮ ሊያመነኩሳቸው ነውና አንድ ነገር አድርግ፡፡” ብለው ስለ መከሩት አቡነ አኖሬዎስ የፊጥኝ በወታደሮች ታስረው እንዲመጡ አደረገና፡፡ ባሌ ግድሞ ወደ ተባለው አገር እንዲጋዙ አደረገ፡፡

እዚያም ለብዙ ዓመታት ገዳም መሥርተው በሐዋርያነት እያገለገሉ ከቆዩ በኋላ ወደ ጥንት በኣታቸው ጽጋጋ እንዲመለሱ ተፈቀደላቸው፡፡ በዚያም በማስተማርና በምነና ሕይወት ሲተጉ ኖሩ፡፡ ኋላም የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ዐፅም በደብረ ሊባኖስ ከሌሎች አበው መነኮሳት ጋር አፍልሰው ከቀበሩ በኋላ በተወለዱ በ104 ዓመታቸው መስከረም 18 ቀን 1471 ዓ.ም በጽጋጋ ገዳማቸው ዐረፉ፡፡ በረከታቸው በሁላችንም ይደር፤ አሜን፡፡

 

  • ምንጭ፡- ገድለ አቡነ አኖሬዎስ፣ ገድለ ተክለ ሃይማኖት፣ የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠርና አጠቃቀሙ ክፍል 2

 መስከረም 22 ቀን 2005 ዓ.ም.

ዲ/ን ኃ/ኢየሱስ ቢያ

 

መጥቅዕ እና አበቅቴ ከየት መጣ ቢሉ

  1.  የፀሐይና የጨረቃ ቀን አቆጣጠር ልዩነት ነው፡፡ አንድ ዓመት በፀሐይ 365 ቀን ከ15 ኬክሮስ ሲሆን በጨረቃ 354 ቀን ከ22 ኬክሮስ ነው፡፡ ስለዚህ የሁለቱ ልዩነት 365 – 354 = ይህ ልዩነት አበቅጽ ተባለ፡፡

  2.  ሁለተኛው የቅዱስ ዲሜጥሮስ ሱባኤ ውጤት ነው፡፡ በዓላትና አጽዋማት የሚውሉበት ቀን በጥንተ ዕለቱ እንዲውል ለማድረግ ይመኝ ነበርና ከሌሊቱ 23 ሱባኤ ከቀኑ 7 ሱባኤ ገብቷል፡፡ ይህንን 23×7=161 ይሆናል፡፡ 161 ሲካፈል ለ30= 5 ይደርስና 11 ይተርፋል ይህን ቀሪ አበቅቴ አለው፡፡ 7 x7 = 49 ይሆናል፡፡ 49 ለ 30 ሲካፈል 1 ጊዜ ደርሶ 19 ይቀራል ይህን ቀሪ መጥቅህ አለው፡፡

– ዓመተ ዓለሙን

– ወንጌላዊውን

– ዕለቱን

– ወንበሩን

– አበቅቴውን

– መጥቁን

– መባጃ ሐመሩን

– አጽዋማትን

በዓላትን ለይቶ ለማወቅ ሒሳባዊ ሰሌቱ እንዲሚከተለው ነው፡፡ 

1. ዓመተ ዓለሙን ለማግኘት ስሌቱ ዓመተ ኩነኔ ሲደመር ዓመተ ምሕረት እኩል ይሆናል ዓመተ ዓለም፡፡ ምሳሌ 5500 + 2006= 7500 ዓመተ ዓለም ይባላል

2. ወንጌላዊውን ለማግኘት ስሌቱ፡- ዓመተ ዓለሙን ለአራት ማካፈል ማለትም ሰባት ሺህ አምስት መቶ ስድስት ለአራት ሲካፈል ለአንድ ወንጌላዊ አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሰባ ስድስት ደርሶ ሁለት ይተርፋል፡፡ ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ ይባላል፡፡
ዓመተ ዓለሙ ለ4 ተካፍሎ፡-

– ቢቀር ማቴዎስ

– ቢቀር ማርቆስ

– ቢቀር ሉቃስ

እኩል ሲካፈል ዮሐንስ ይሆናል፡፡

3. ዕለቱን/መስከረም 1 ቀንን ለማግኘት ስሌቱ ዓመተ ዓለም ሲደመር መጠነራብዒት /ለአንድ ወንጌላዊ የደረሰውን/ ሲካፈል ለሰባት ለምሳሌ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ስድስት ሲደመር አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሰባ ስድስት እኩል ይሆናል ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ሰማንያ ሁለት፡፡ ይህን ለሰባት ሲያካፍሉት ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ሰማንያ ሁለት ለሰባት ሲካፈል አንድ መቶ ሰላሳ አራት ደርሶ ሁለት ይቀራል፡፡

ዓመተ ዓለሙና መጠነ ራብዒት ተደምሮ ለሰባት ተካፍሎ

1. ቢቀር ማክሰኞ

2. ቢቀር ረቡዕ

3. ቢቀር ሐሙስ

4. ቢቀር ዓርብ

5. ቢቀር ቅዳሜ

6. ቢቀር እሑድ

እኩል ሲካፈል ሰኞ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የዘንድሮው ቀሪ 2 ስለሆነ ዕለቱ ረቡዕ ነው፡፡

4. ተረፈ ዘመኑን /ወንበሩን/ ለማግኘት ስሌቱ ዓመተ ዓለሙ ለሰባት ተካፍሎ ቀሪው ተረፈ ዘመን/ ወንበር ይባላል፡፡ ከቀሪው ላይ ስለተጀመረ ተቆጠረ ስላልተፈጸመ ታተተ/ ተቀነሰ ብሎ አንድ መቀነስ ቀሪው ወንበር ይባላል፡፡
ለምሳሌ፡- 7506፥7=395 ደርሶ 1 ይቀራል 1-1=0 ዘንድሮ ወንበሩ ዜሮ ሆነ ማለት ነው፡፡

5. አበቅቴን ለማግኘት ስሌቱ ወንበር ሲባዛ በጥንት አበቅቴ /11/ ሲካፈል ለሰላሳ ቀሪው አበቅቴ ይባላል፡፡ የዘንድሮ ወንበሩ ዜሮ ስለሆነ በአሥራ አንድ ሲባዛ ውጤቱ ዜሮ በመሆኑ አበቅቴ ዜሮ/አልቦ/ ነው፡፡

6. መጥቅዕን ለማግኘት ስሌቱ ወንበር ሲባዛ በጥንተ መጥቅዕ /19/ ሲካፈል ለሰላሳ ቀሪው መጥቅዕ ይባላል፡፡ የዘንድሮ ወንበሩ ዜሮ/አልቦ ስለሆነ በአሥራ ዘጠኝ ሲባዛ ውጤቱ ዜሮ/አልቦ በመሆኑ መጥቅዕ ዜሮ/አልቦ ነው፡፡
እዚህ ላይ ስትደርስ አዋጁን ተመልከት

አዋጁ/መመሪያው – መጥቅዕ ከ14 በላይ ከሆነ በመስከረም ይውላል የመስከረም ማግስት/ሳኒታ የካቲት ነው፡፡

– 14 ራሱ መጥቅዕ መሆን አይችልም፡፡

– መጥቅዕ ከ14 በታች ከሆነ በጥቅምት ይውላል የጥቅምት ማግስት/ሳኒታ ጥር ነው፡፡

– መጥቅዕ ሲደመር አበቅቴ ሁል ጊዜ 30 ነው፡፡

– መጥቅዕ አልቦ ዜሮ ሲሆን መስከረም 30 የዋለበት የቀኑ ተውሳክ መባጃ ሐመር ይሆናል፡፡

7. መባጃ ሐመርን ለማግኘት ስሌቱ የዕለት ተውሳክ ሲደመር መጥቅዕ ሲካፈል ለሰላሳ ይሆናል፡፡ ለ30 መካፈል ካልቻለ እንዳለ ይወሰዳል፡፡
ስለዚህ ዘንድሮ መጥቅዕ አልቦ ስለሆነ መስከረም ሰላሳ የዋለበት ዕለት ሐሙሰ ነው፡፡ የሐሙስ ተውሳክ 3 ነው፡፡ ሦስት ከዜሮ ጋር ተደምሮ ለ30 መካፈል ስለማይችል እንዳለ ይወሰዳል፡፡ ስለዚህ መባጃ ሐመሩ 3 ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የአጽዋማትና የበዓላትን ተውሳክ እየደመርክ አውጣ፡፡

8. ጾምን ለማግኘት ስሌቱ መባጃ ሐመር ሲደመር የጾም ተውሳክ ሲካፈል ለሰላሳ ይሆናል /ለ30 መካፈል ካልቻለ እንዳለ ይወሰዳል/

9. በዓልን ለማግኘት ስሌቱ መባጃ ሐመር ሲደመር የበዓል ተውሳክ ሲካፈል ለሰላሳ ይሆናል፡፡ /ለ30 መካፈል ካልቻለ እንዳለ ይወስዳል

በዚህ መሠረት የ2006 ዓ.ም. አጽዋማትና በዓላትን አውጣ

1. ጾመ ነነዌ = 3 + 0=3 የካቲት 3 ቀን ሰኞ ይውላል፡፡

2. ዐቢይ ጾም = 3 + 14 = 17 የካቲት 17 ቀን ሰኞ ይውላል፡፡

3. ደብረ ዘይት = 3 + 11= 14 መጋቢት 14 ቀን እሑድ ይውላል፡፡

4. ሆሣዕና = 3 + 2= 5 ሚያዚያ 5 ቀን እሑድ ይውላል፡፡

5. ስቅለት = 3 + 7= 10 ሚያዚያ 10 ቀን ዓርብ ይውላል፡፡

6. ትንሣኤ = 3 + 9= 12 ሚያዚያ 12 ቀን እሑድ ይውላል፡፡

7. ርክበ ካህናት = 3 + 3= 6 ግንቦት 3 ቀን ረቡዕ ይውላል፡፡

8. ዕርገት = 3 + 18= 21 ግንቦት 21 ቀን ሐሙስ ይውላል፡፡

9. ጰራቅሊጦስ = 3 + 28= 31 – 30 = 1 ሰኔ 1 ቀን እሑድ ይውላል፡፡

10. ጾመ ሐዋርያት = 3 + 29= 32 – 30= 2 ሰኔ 2 ቀን ሰኞ ይውላል፡፡

11. ጾመ ድኅነት = 3 + 1= 4 ሰኔ 4 ቀን ረቡዕ ይውላል፡፡

ሃሌ ሉያ ባዘ ንዜከር ሐሰበተ ሕጉ

ወትዕዛዛትሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኀኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ

ሐሳበ ነቢያት ወሐዋርያት

ሐሳበ ጻድቃን ወሰማዕታት

ሐሳበ ደናግል ወመነኮሳት

ሐሳበ ኄራን መላእክት እንዘ ሀሎነ በዘመነ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ቡሩክ ያበጽሐነ እስከ ዘመነ ቅዱስ ሉቃስ ፍስሐ ዘናዊ በሰላመ እግዚአብሔር አሜን፡፡

በሃምሳ ምዕት ወበ ሃምሳቱ ምዕት ኮነ ዓመተ ኩነኔ ዓመተ ፍዳ፡፡ /5500/

በሰብአ ምዕት ወበሃምስቱ ምዕት ወስድስቱ ኮነ ዓመተ ዓለም /7506/

በእስራ ምዕት ወስድስቱ /2006/ ኮነ ዓመተ ምሕረት ዮም ሠረቀ ለነ ሠርቀ ወርህ መስከረም ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ወርኃ ጥቅምት በሰላመ እግዚአብሔር አሜን፡፡

ረቡዑ ሠረቀ ዕለት /ዕለቱ ረቡዕ/

አሚሩ ሠረቀ መዓልት /ቀኑ አንድ/

ሰኑዩ ሠርቀ ሌሊት /ሌሊቱ ሁለት/

ስድሱ ሠርቀ ወርኅ /በጨረቃ ስድስት ሆነ ማለት ነው/

ስብሐት በል ቀጥሎም አቡነ ዘበሰማያት በል

 

የሌሊት አቆጣጠር ስሌቱ

– አበቅቴ ሲደመር ህፀፅ ሲደመር መዓልት እኩል ይሆናል ሌሊት፡፡

የጨረቃ አቆጣጠር ስሌቱ

– አበቅቴ ሲደመር ህፀፅ ሲደመር መዓልት ሲደመር ጨረቃ እኩል ይሆናል የጨረቃ ሌሊት፡፡

አበቅቴ የተረፈ ዘመን ቁጥር ነው፤ ህፀፅ ጨረቃ ጠፍ ሆና የምታድርበት ሌሊት ነው፡፡ አንድ ጊዜ 29/30 ስለምትሆን የሁለት ወር ህፀፅ አንድ ነው፡፡ መዓልት ከ1-30 ያለው የወሩ ቀን የደረሰበት ዕለት ነው፡፡ የጨረቃ ህፀፅ ሁል ጊዜ 4 ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር