የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የልምድ ልውውጥ አደረጉ
ታኅሣሥ 17 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ኅሩይ ባየ
ከታኅሣሥ 11-15 ቀን 2005 ዓ.ም. ለአምስት ተከታታይ ቀናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የልምድ ልውውጥ አደረጉ፡፡ የልምድ ልውውጡ የተከናወነው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ሲሆን በአምስቱ ዕለታት በየቀኑ እስከ አንድ ሺሕ ለሚሆኑ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መካፈላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ታኅሣሥ 11 ቀን 2005 ዓ.ም. በጉባኤው መክፈቻ ዕለት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ እና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና የኢሊባቡርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ጸሐፊና የአዲስ አበባ ምዕራብ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቢመን የላዕላይ ግብፅ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ቄስ ዳውድ ለሜይ የግብፅ መንበረ ማርቆስ ካቴድራል ካህን፣ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የአድባራት የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊዎች፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና የቅዱስ ጳውሎስ ሰዋሰወ ብርሃን ከፈተኛ ትምህርት ቤት ደቀ መዛሙርት፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ተገኝተዋል፡፡
“ተዘከር ማኅበረከ ዘአቅደምከ ፈጢረ ወአድኀንከ በትረ ርስትከ ደብረ ጽዮን ዘኀደርከ ውስቴታ… አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን የተቤዥሃትንም የርስትህን በትር በእርስዋ ያደርህባት የጽዮንን ተራራ አስብ” /መዝ.73፥2/ የሚለው የዳዊት መዝሙር በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅድሳን ገዳም ዲያቆናት ተሰብኮ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት በብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከተነበበ በኋላ የኪዳን ጸሎት ደርሷል፡፡ በመቀጠልም ዐቃቤ ርእሰ መንበሩ ግብፅና ኢትዮጵያ እኅትማማች ዓብያተ ክርስቲያናት መሆናቸውን አስታውሰው የቆየ ቤተሰባዊ ግንኙነታቸውን አጠናክረው በመቀጠል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የመጡ ግብፃውያንንና የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አመስግነዋል፡፡
ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በመሸፈን በአሜሪካና በግብፅ የሚገኙ የበጎ ፈቃደኛ አገልጋዮች ልዑካንን በመመደብ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት አምስት ቀናት የልምድ ልውውጥ እንዲደረግ ላደረገችው አስተዋጽኦ ምሥጋናቸውን የገለጡት የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የኤች አይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ መምሪያ ሓላፊ ቄስ ሶምሶን በቀለ ልማት ኮሚሽኑ በማስተባበር እና የቋሚ ተሳታፊ ሠልጣኞችን የትራንስፓርት ወጪ መሸፈኑን ገልጠዋል፡፡
በሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኮረው የልምድ ልውውጥ በከፍተኛ መነቃቃትና ፍላጎት ተካሂዷል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እነዚህን ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ለማስተማር ያላቸው ብቃት እንደተጠበቀ መሆኑን የገለጡት ቄስ ዳውድ ለሜይ በሥርዓት አፈጻጸሙ ላይ የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል በተጨማሪም ምእመናን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት፣ የሚታይና የማይታይ ጸጋ ለማግኘት እነዚህ ምሥጢራት ከሕይወታቸው ጋር አስተሳስረው ሁል ጊዜ በማንኛውም ቦታ በየትኛውም ጊዜ የምስጢራት ተካፋይ መሆን እንደሚያስፈልግ ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ልዑኩ በአጽንኦት ገልጠዋል፡፡
“ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ለእኛ አዲስ ናቸውን?” የሚሉ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አሳባቸውን ያቀረቡ ሲሆን ቄስ ዳውድ በምሳሌ እንዳስረዱት በጉባኤ የተገኘ አንድን ሕፃን ልጅ ጠርቼ አባትህ አለ? ብዬ ብጠይቀው ካለ አለ ማለቱ አይቀርም አሁንም ተጨማሪ ጥያቄ እንድጠይቀው ፍቀድልኝ አሉ አባትህ ስንት ብር በኪሱ ይዟል? አላውቅም አለ፡፡ የት ነው የሚሠራው? አላውቅም፡፡ ደመወዙ ስንት ነው? አላውቅም፡፡ የሚገርም ነው ሕፃኑ አባቱን ያውቃል ስለ አባቱ ግን የማያውቀው ብዙ ነገር አለ፡፡ … በማለት ምላሻቸውን በምሳሌ አስቀምጠዋል፡፡ በዚህ መነሻነት ሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን በጥልቀትና በዝርዝር ማወቅ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን በማብራራት ይልቁንስ በመንፈሳዊ ሕይወት ለመጠንከር፣ ከዲያብሎስ ቀስት ለማምለጥ፣ በመንፈስ ቅዱስ ለመቃኘት፣ ምስጢራቱን ማወቅ ሳይሆን መጠቀም እንዲገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኩል የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት፣ ከአዲስ አበባ ደቡብ ሀገረ ስብከት የተውጣጡ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከማኅበረ ቅዱሳን ዘማርያን ያሬዳዊ መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን ሦስት ወጣቶችም በገና እየደረደሩ ዝማሬያቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዝማሬ ስሰማ ንጉሥ ዳዊት በዓይነ ኅሊናዬ፤ ይመጣል በመጽሐፍ ቅዱስ የተዘረዘሩት የዜማ ዕቃዎች መልካቸቹውን ሳይቀይሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ መዝለቃቸውን አድንቀው ለወደፊት ይህ ትውፊት ሳይቋረጥ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በእነሱ በኩል ከሁለት የዘለለ የዜማ ዕቃ እንደሌላቸው ያስታወሱት ቄስ ዳውድ የእኛ ዜማ ጣዕም እጅግ የሚመስጥ ደስ የሚል እንደሆነ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል፡፡ በዝማሬያችን የተመሰጡት ግብፃውያን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በፍጹም ተመስጦ ለመዘመር ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡
የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ በአረብኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተለያዩ መዝሙራትን በማቅረብ የዝማሬውን መልእክት ቄስ ዳውድ አብራርተዋል፡፡
በአጠቃላይ በጉባኤው የተለያዩ ጥያቄዎች ተነሥተዋል፡፡ ተገቢና ግልጽ ምላሾች ተሰጠተዋል፡፡ ሆኖም በሁለቱ ዓብያተ ክርስቲያናት ያለው መሠረታዊ አንድነት የዶግማ እንጂ የሥርዐት ስላልሆነ በልምድ ልውውጡ የተገለጡ እንግዳ ሥርዓቶች ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንፃር መታየት እንዳለባቸው ሊቃውንቱ አሳስበዋል፡፡ ትምህርተ ኖሎት፣ ሐዋርያዊ ተልእኮ፣ በጎ አስተዳደርና የግጭት አፈታትን በሚመለከቱ የጥናት ጽሑፎች በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ቀርቦ ሰፊ ውይይትና በቂ ግንዛቤ ተገኝቶበታል፡፡
የልምድ ልውውጡ በጎ ገጽታ እንዳለው እና ለወደፊቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዕለቱ ከተሰጡ አስተያየቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡