የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የቀብር ሥነ ሥርዓት የቀጥታ ዘገባ

ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም.

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}kebre{/gallery}
  • 4፡00 የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ አስከሬን አርፎ ከሰነበተበት ከሐያት ሆስፒታል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የደብር አስተዳዳሪዎች ካህናትና ቀሳውስት የሰንበት ትምህርት ቤቶች መዘምራን ዘመድ አዝማድና ምእመናን ታጅቦ ጠቅላይ ቤተ ክህነት  ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ደረሰ፡፡

  • 4፡30 አስከሬኑ በመንበረ ፓትርያርክ ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ካረፈ በኋላ መርሐ ግብሩ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጸሎት ተጀመረ፡፡

  • 4፡36 በርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ካህናት ጸሎተ ወንጌል እየተደረሰ ነው፡፡

  • 4፡50 በብፁዕ አቡነ ናትናኤል መሪነት ጸሎተ ኪዳን እየተደረሰ ነው፡፡

  • 4፡57 በስብከተ ወንጌል አዳራሹ የነበረው መርሐ ግብር ተጠናቆ የቅዱስነታቸው አስከሬን ወደ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ማርያም ገዳም እየተወሰደ ነው፡፡

  • 8፡30 ጸሎተ ቅዳሴው ተጠናቋል፡፡ በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት የቅዱስነታቸው አስከሬን በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የአድባራት አለቆች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና ምእመናን እንዲሁም ክቡራን እንግዶች ታጅቦ ወደ ወንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጉዞ ጀምሯል፡፡

  • 9፡50 የቅዱስነታቸው አስከሬን በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የአድባራት አለቆች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና ምእመናን እንዲሁም ክቡራን እንግዶች ታጅቦ ወደ ወንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል  እያመራ ሲሆን አሁን አራት ኪሎ አደባባይ ደርሷል፡፡

  • 10፡25 የቅዱስነታቸው አስከሬን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካትድራል በክብር ደርሷል፡፡

synodos akabi meneber

የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ምርጫ አስመልክቶ የቅዱስ ሲኖደስ ጽ/ቤት መግለጫ ሰጠ፡፡

ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}synodos{/gallery}

ብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንት ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ በመለየታቸው ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መረጠ፡፡

 

መግለጫውን የሰጡት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሸካ ቤንችና ማጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ ሲሆኑ “በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 17 መሠረት ቀደምትነት ካላቸው ብፁዓን አባቶች መካከል በመምረጥ ዋናው የፓትርያርክ ምርጫ እስከሚከናወን ድረስ ብፁዕ አቡነ ናትኤል የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ሆነው እየሠሩ እንዲቆዩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተወስኗል” በማለት ገልጸዋል፡፡

 

“የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊም ሆነ ማኅበራዊ ተግባር ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ይህንኑ ከፍጻሜ ለማድረስ ቋሚ ሲኖዶሱን ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል” ያሉት ብፁዕነታቸው የዋናው ፓትርያርክ ምርጫ እስከ ሚከናወን ድረስ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩና ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር አብረው የሚሠሩ ሰባት አባላት መመረጣቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

በዚህም መሠረት፡-

  1. ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ

  2. ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የሲዳማና ጌዴዎ አማሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

  3. ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

  4. ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በክልል ትግራይ የምዕራብ ሴቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

  5. ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ

  6. ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የወላይታና ዳውሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

  7. ብፁዕ አቡነ አብርሃም የምሥራቅ ሀረርጌና የኦጋዴን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

ሰሞኑን የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ምርጫ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር በኋላ እንደሚሆን የተገለጸ ቢሆንም ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ውይይት ዐቃቤ መንበር መምረጡ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ በመግለጫው ተወስቷል፡፡ እንደ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ገለጻ  “መንበሩ ያለ ሓላፊ መቆየት የሌለበት በመሆኑና ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ የሚያሰናብት አባት መኖር አስፈላጊ ስለሆነ ቅድሚያ ተሰጥቶታል፡፡”

 

synodos akabi meneber

picture2

01 abune natenale

ሰበር ዜና ቅዱስ ሲኖዶስ አቃቤ መንበር ሰየመ

ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም.

 

በእንዳለ ደምስስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ01 abune natenale ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚመራ ዐቃቤ መንበር ሰየመ፡፡ በዚህም መሠረት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዐቃቤ መንበር ሆነው የተሾሙ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ፓትርያርክ እስኪመርጥ ድረስ ቤተ ክርስቲያንን በበላይነት ይመራሉ፡፡

mkresearcher

የ፬ኛ ዓመታዊ ዐውደ ጥናት ግብዣ

mkresearcher

abune paulose

ስለ ቅዱስ ፖትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር መግለጫ ተሰጠ

ሐሴ 12 ቀን 2004 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

መካነ ድራችን  በግልጥ ባልታወቀ ምክንያት የሲስተም ችግር ገጥሞት ስለነበር መረጃዎችን በወቅቱ ማድረስ ባለመቻላችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፖትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ሥርዓተ ቀብር በማስመልከት ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጠ፡፡

 

መግለጫውን የሰጡት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ዋና ጸሓፊ፣ የከፋ ቤንችና ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑabune paulose በመግለጫቸውም “ቅዱስነታቸው ሐሙስ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ መለየታቸውን በዕለቱ መግለጻችን ይታወቃል፡፡ በቀጣይነትም የቅዱስነታቸውን የቀብር ሥነ ሥርዓት አፈጻጸም ጊዜና ቦታ በተከታታይ የሚገለጽ መሆኑን በሰጠነው ማሳሰቢያ መሠረት የቀብር ሥነሥርዓቱ ሐሙስ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ እስከዚያው ድረስ ምእመናንና ምእመናት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመገኘት ሃዘናቸውን መግለጽ የሚችሉ መሆኑን እንገልጻለን” ብለዋል፡፡

 

ስለ አሟሟታቸው ማብራሪያ እንዲሰጡ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ቅዱስነታቸው ሱባኤውን ሳያቋርጡ እሑድ ቀድሰው ሰኞና ማክሰኞም ቅዳሴውን እየመሩ መገኘታቸውንና ከሰዓት በኋላ ህመም ስለተሰማቸወ ወደ ሕክምና መሔዳቸውን የገለጹ ሲሆን እረፍት እንዲያደርጉ በሐኪም ከተነገራቸው በኋላ በዚያው የእግዚአብሔር ጥሪ ሆኖ ሌሊት 11፡00 ሰዓት ላይ ማረፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ስለ ቅዱስነታቸው ሕመም ሲያብራሩ “ብዙ ታመው ቤት አልዋሉም፡፡ ሥራም አላቋረጡም፣ ያልታሰበ ነገር ስለነበር በሞታቸው በጣም ተደናግጠናል፡፡ ሕመማቸው የስኳር ሕመም ጠንቅ ነው፡፡ ቀዶ ጥገናም አልተደገላቸውም በትናንትናው ዕለት እኔ ነኝ አጥቤ የገነዝኳቸው፡፡” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያኑ ቀኖና እንደሚያዘው አንድ ፖትርያርክ ሲያርፍ አቃቤ መንበር በዕለቱ መሠየም እንዳለበት ይገልጻልና ይህ ለምን ተፈጻሚ አልሆነም? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በፓትርያርኩ ጽ/ቤት ሓላፊ እንዲሁም በቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ አማካይነት ሥራዎች እንደሚከናወኑ፣ ከቅዱስ ፖትርያርኩ የቀብር ሥነ ሥርዓት በኋላ አቃቤ መንበር እንደሚሰይምና ይህም በመመካከርና በመስማማት ውሳኔውን መወሰናቸውን አብራርተዋል፡፡

 

ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያኑን ለመምራት ምን ያህል ዝግጁ ነው? ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱም “ይህ ጸሎት የሚጠይቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር abune paulosእየረዳን፣ በምዕመናን ጸሎት እየተረዳን የተቻለንን ሁሉ እንጥራለን፡፡” ያሉ ሲሆን ከሰሜን አሜሪካ ካሉ አባቶች ጋር እየተካሄደ የነበረው እርቀ ሰላም እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

 

የቅዱስነታቸው የቀብር ቦታን አስመልክቶ እንዳልተናዘዙና በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ከልጅነታቸው ጀምሮ በቅስና እያሉ ባገለገሉበት፣ በተማሩበት፣ ከእስር ቤት ከተፈቱ በኋላ ክብር ባገኙበት በመንብረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲሆን ተወስኗል” ብለዋል፡፡

 

የቅዱስ ፖትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር ዝርዝር መረጃም እንደሚከተለው ሰጥተዋል፡፡

  • ረቡዕ ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ የቅዱስነታቸው አስከሬን ከመንበረ ፓትርያርክ በግልጽ ሠረገላ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያመራል፡፡
  • ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ ጸሎተ ፍትሀት እየተከናወነ ያድራል፡፡
  • ሌሊት ሥርዓተ ቅዳሴ በሦስቱም መንበር በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ይቀደሳል፡፡
  • ከሥርዓተ ቅዳሴ በኋላ አስከሬናቸው ወደ ዐውደ ምሕረት በማውጣት ምዕመናን በተገኙበት ጸሎተ ፍትሀቱ ይቀጥላል፡፡
  • ከውጭ ሀገር የመጡ የአኀት ቤተ ክርስቲያናት ፖትርያርኮች ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ፡፡
  • የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ንግግር ያደርጋሉ፡፡
  • የቅዱስነታቸው የሕይወት ታሪክ በቅዱስ ሲኖዶስ በተፈቀደላቸው ሊቀ ጳጳስ ይነበባል፡፡
  • አስከሬናቸው በቤተ ክርስቲያኑ ዑደት ያደርጋል፡፡
  • በመጨረሻም ሥርዓተ ቀብራቸው ይፈጸማል፡፡

 

picture1

ራሱን “ጉባኤ አርድእት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” ብሎ የሚጠራውን ቡድን የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አገደ

ነሐሴ 9 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዲ/ን አብርሃም አንዳርጌ

 

በጠቅላይ ቤተ ክህነት አካባቢ ራሱን “ጉባኤ አርድእት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” ብሎ የሰየመውን ቡድን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የእገዳ ደብዳቤ ጣለበት፡፡

 

የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የጉባኤው ዓላማና ፍላጎት ምን እንደሆነ እንደማይታወቅና እንዲህ ዓይነቱ ጉባኤ በቅዱስ ሲኖደስ ካለመቋቋሙም በላይ እውቅና ሳያገኝና ሳይፈቀድለት በራሱ ተነሳሽነት የሚንቀሳቀስ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤትም የማያውቀውና ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ዋና ጸሓፊና የከፋ ሸካ ቤንች እና ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ፊርማ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በቁጥር 486/836/2004 ሐምሌ 25 ቀን 2004 ዓ.ም. በተጻፈው ደብዳቤ መታገዱ ተገልጿል፡፡

 

“ጉባኤ አርድእት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” በማለት ስለ ተቋቋመው ቡድን ያነጋገርናቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነት አንዳንድ የመምሪያ ሓላፊዎች ቡድኑ በምን ምክንያት እንደተቋቋመና ለምንስ በኅቡዕ መንቀሳቀስ እንደፈለገ እንዳልተረዱ ጠቅሰው ጉዳዩን ለቤተ ክርስቲያኗ ደኅንነት ሲባል በአንክሮ እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተናግረው በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ሆነው የዚህን ሕገ ወጥ ቡድን አባላት በሆኑ ግለሰቦች ላይ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ርምጃዎች በቀጣይ እንደሚወስድም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ገልጸውልናል፡፡

 

ጉባኤውን እያደራጁ የሚገኙ ግለሰቦች አብዛኛዎቹ በሚሠሩባቸው ቦታዎች ተቀባይነት እያጡ የመጡ ግለሰቦች እንደሆኑ የሚናገሩት የቤተ ክህነቱ ምንጮች ቅዱስ ሲኖዶስ እነዚህ ግለሰቦች ሊፈጥሩት ካሰቡት ከፍተኛ አደጋ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊታደጋት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

 

የዚህ የእገዳ ደብዳቤ ግልባጭ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ለሃይማኖትና ሥነ ሥርዐት ዳይሬክቶሬት ጀኔራል፣ ለብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት፣ እንዲሁም ለፌደራል ፖሊስ ኮምሽን እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን ግልባጭ የተደረገ መሆኑን ለመረዳት ችለናል፡፡

 

picture1

የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ የ2004 ዓ.ም. እቅዶቹን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡

ነሐሴ 8 ቀን 2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

 

በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር በ2004 ዓ.ም. ሊያከናውናቸው ካቀዳቸው የአገልግሎት ዘፍፎች በአብዛኛው እያጠናቀቀ መሆኑን ገለጸ፡፡

 

የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ክፍል ሓላፊ የሆኑት ሊቀ ብርሃናት ሃይማኖት ተስፋዬ 2004 ዓ.ም. የክፍሉ የአገልግሎት አፈጻጸም አስመልክቶ እንደገለጹት “በታቀደው መሠረት በመላው ሀገሪቱ 200 የሕዝብ ጉባኤያትን 15 ሐዋርያዊ ጉዞዎችን ለማድረግ ታስቦ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ እንዲሁም በ10 ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ለሚገኙ ካህናት የትምህርተ ኖሎትና የአስተዳደር የአሠልጣኞች ሥልጠና ለመስጠት ታስቦ በ8ቱ ሀገረ ስብከቶች ተተግብረዋል፡፡ በ10 ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ለሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች የተተኪ መምህራን ሥልጠና በታሰበው መንገድ ተሰጥቷል፡፡ ሰልጣኞቹም በየሀገረ ስብከታቸው በመንቀሳቀስ እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ሠላሳ ሠላሳ ሌሎች ሰልጣኞችን እንዲያሰለጥኑ በመደረግ ላይ ሲሆን ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል፡፡

 

የሰለጠኑት ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ወደታች ወርደው ሥልጠናውን ሲሰጡ ለመገምገም መቻሉን የገለጹት ሊቀ ብርሃናት ሃይማኖት ተስፋዬ “ሥልጠናው የካህናትና የተተኪ መምህራን ብቃት የሚያጎለብት እንደሆነ ጨምረው የገለጹ ሲሆን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ያልተቋቋመባቸው ቦታዎች ላይ በማቋቋም የማጠናከሪያ አገልግሎት በመስጠት ወደተግባር መሸጋገራቸውን በተደረገወ ግምገማ ለማረጋገጥ መቻሉን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

በ2005 ዓ.ም. ይህ አገልግሎት ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን የክፍሉ ሓላፊ ሊቀ ብርሃናትት ሃይማኖት ተስፋዬ ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት ያሰለጠናቸው አቅም ያላቸው ተማሪዎችና ከመንፈሳዊ ኮሌጆች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙና የተመረቁ መምህራን ወደየመጡበት ሀገረ ስብከት በክረምቱ ስለሚሄዱ ሥልጠናዎችንና የስብከት አገልግሎት እንዲሰጡ በቅንጅት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

 

ስላጋጠማቸው ችግር ሲገልጹም “ከፍተኛ ችግራችን የገንዘብና የመገልገያ ቁሳቁስ እጥረት ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም. 10 የስብከት 10 የመዝሙር ካሴቶችንና በ4 የተለያዩ ቋንቋዎች መጻሕፍት ተዘጋጅተዋል፡፡ በኦሮምኛና በሲዳምኛ መዝሙር በኦሮምኛና በአማርኛ መጻሕፍት ተዘጋጅተዋል፡፡ እነዚህን ለምእመናን ለማዳረስ መታተም አለባቸው፡፡ ነገር ግን ዝግጅቶቹ ቢጠናቀቁም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሊሳካልን ባለመቻሉ በእጃችን ይገኛሉ፡፡ እነዚህንና ሌሎችም የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማስፋፋት እንድንችል ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልገናል፡፡ ይህንንም ከበጎ አድራጊ ምእመናን እንጠብቃለን፡፡ በተጨማሪም የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ የተጠቀሙበትና የቀየሩት ኮምፒውተር፣ ፕሪንተርና ሌሎችም ድጋፍ ያደረጉ የገጠር ቤተ ክርስቲያናትን፣ የወረዳና ሀገረ ስብከቶችን ለማጠናከር ጠቀሜታ ስላላቸው ከምእመናን ብዙ ይጠበቃል በማለት ሊቀ ብርሃናት ሃይማኖት ተስፋዬ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱ የ2004 ዓ.ም. ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግሞ የአዲስ ዓመት ዕቅድን አጸደቀ፡፡

ነሐሴ 3 ቀን 2004 ዓ.ም.

ከጅማ ማእከል

  • ቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ አውጥቶ ያዋቀረውን ማኅበር በአክራሪነት መፈረጅ ቤተ ክርስቲያንን መፈረጅ ነው፡፡

የጅማ ሀገረ ስብከት ጠቅላላ ጉባኤ የ2004 ዓ.ም. ዕቅድና ክንውንን በመገምገም፣ የ2004 ዓ.ም. ዕቅድን በማውጣትና መመሪያ በመቀበል ሰኔ 28-29 ቀን 2004 ዓ.ም. ተካሂዶ ተጠናቀቀ፡፡

 

ጉባኤውን የመሩት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጠቅላላ ጉባኤው የ2004 ዓ.ም. የሥራ ግምገማ ማድረጉ ካለፈው ተሞክሮ በመውሰድ ለቀጣይ የተሻለ ለመሥራትና የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማሻሻል የሚረዳ በመሆኑ በቀጣይም የተሳካ ሥራን ለመሥራት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ስለሺ አስፋው ከ2004 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በተጨማሪ ሀገረ ስብከቱ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ለማስከፈት ይረዳ ዘንድ እየተሠራ ያለው ባለ 5 ፎቅ ሕንፃ ግንባታን በተመለከተ የሒሳብ ራፖርት አቅርበዋል፡፡ ለዚህ ሥራም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አድባራትና ግለሰቦችን አመሰግነዋል፡፡

 

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይም ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት በአንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ አውጥቶ ያዋቀረውን ማኅበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት ስም መፈረጅ ቤተ ክርስቲያንን መጥቀስ በመሆኑ ይህን የሚያደርጉ አንዳንድ አካላት ከድርጊታቸው መታረም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

 

በመጨረሻም በሀገረ ስብከቱ በበጀት ዓመቱ ብልጫ ሥራ የሠሩ አካላት የተሸለሙ ሲሆን የማኅበረ ቅዱሳን የጅማ ማእከል የዓመቱ ልዩ ተሸላሚ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

በሀገረ ስብከቱ በዘንድሮው ዓመት ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ወገኖች ከተለያዩ ቤተ እምነቶች ወደ ኦርቶዶክሰ ተዋሕኦ ሃይማኖት እንደተመለሰም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ የ2005 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤን በአጋሮ ከተማ እንዲዘጋጅ በመወሰን ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

 

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 19ኛ ዓመት ቁጥር 22 ከነሐሴ 1-15 ቀን 2004 ዓ.ም.

yseraamerare 005

ማኅበረ ቅዱሳን የ20 ዓመት ጉዞውን ሊገመግም ነው፡፡

ነሐሴ 1 ቀን 2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ

ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን ያሳለፋቸውን ሁለት ዐሥርት ዓመታት ጉዞውን የሚገመግም መሆኑ ተገለጸ፡፡

 

yseraamerare 005የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም በነሐሴ ወር የሚደረገውን የማኅበሩን ጠቅላላ ጉባኤ አስመልክተው እንደገለጹት ማኅበረ ቅዱሳን ያከናወናቸው የ20 ዓመት ጉዞዎች በጠቅላላ ጉባኤው ላይ አንሥቶ እንደሚገመግም ገልጸዋል፡፡

 

ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ በየ2 ዓመት ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ መጀመሩን የገለጹት ሰብሳቢው ማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት የሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ታሪካዊ ነው ብለዋል፡፡ ከነሐሴ 26-28 ቀን 2004 ዓ.ም. ለ3 ቀናት በሚዘልቀው ጉባኤ ቁጥራቸው ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች የሚገኙበት ሲሆን በዚህም ጉባኤ ከሀገር ውስጥና ከውጪ ማእከላት፣ ወረዳ ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት የሚሳተፉበት እንዲሁም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ተጋባዥ እንግዶች የሚገኙበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 

ለ3 ቀናት በሚካሄደው 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቀጣይ የ4 ዓመት ስልታዊ እቅድ ከማጽደቅ ጀምሮ ቀጣዩን የአመራር ምርጫም እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

 

ለ10ኛ ጊዜ በሚደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ከሀገር ውስጥ 44 ማእከላት፣ ከውጪ 9 ማእከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች፣ 303 ወረዳ ማእከላት፣ እንዲሁም የግቢ ጉባኤያት ተወካዮች እንደሚገኙና ተጋባዥ እንግዶችን ጨምሮ ከአንደ ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በጉባኤው ላይ ይታደማሉ፡፡

dsc01699

የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍሉ ለአረጋውያን እርዳታ አደረገ፡፡

ሐምሌ 24 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍል ባሳለፍነው ሳምንት ረጅም ዘመናትን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ላሳለፉ አረጋውያን ጊዜያዊ የአልባሳትና የሕክምና እርዳታ አደረገ፡፡

የአገልግሎት ክፍሉ አብዛኛውን የእድሜ ዘመናቸውን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ አድርገው ለኖሩ ሰባት አባቶች የአልባሳት እገዛ dsc01699ያደረገው በ2004 ዓ.ም. መሪ እቅዱ መሠረት መሆኑን የጠቀሱት የክፍሉ ሓላፊ ወይዘሪት መቅደስ ዓለሙ፤ “ይህንን ለማቀድ ምክንያት የሆነን አባቶቻችን ከሰፊ የአገልግሎት ዘመናቸው በኋላ የሚታሰብላቸው የጡረታ አበል አለመኖሩ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ አባቶችም በቅርብ የሚረዳቸውና የሚንከባከባቸው ሰው የሌላቸው ናቸው፡፡ ስለሆነም ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳልሰጡ በቂ ትኩረት ተነፍጓቸውና ተረስተው በየመቃብር ቤቱና ንጽሕና በተጓደለባቸው ሥፍራዎች ወድቀው የሚገኙትን አባቶች፤ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር ባካሄድነው ጥናትና ባገኘነው መረጃ መሠረት መርጠን ረድተናል፡፡” በማለት ምክንያቱን አስረድተዋል፡፡

የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍሉ በልዩ ልዩ ቦታዎች ለሚገኙ አረጋውያን ካበረከተው የአልባሳት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በበጎ አድራጊdsc01709 ምእመን ቤት ተጠግተው ለሚኖሩ አንድ አባት ሙሉ የሕክምና ወጪ በመሸፈን እንዲታከሙ አድርጓአል፡፡

 

በስተመጨረሻም ወይዘሪት መቅደስ ዓለሙ “ከጊዜያዊ እርዳታ ባለፈ በቀጣይ አረጋውያኑን ለማቋቋምና ኑሮአቸውን ለማሻሻል በክፍሉ ምን ታስቧል?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይህ እቅድ በ2005 ዓ.ም. ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ክፍሉም እንደ ክፍል በአቅም ከፍ ይላል ብለን እናስባለን፡፡ እናም በቀጣዩ ዓመት ከጊዜያዊ እርዳታ ይልቅ የተሻለ እገዛ ማበርከት የምንችልበትን ዝግጅት አጠናቅቀናል፤ ጊዜው ሲደርስም ይህንኑ እንፈጽማለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡” ብለዋል፡፡

 

በተያያዘ ዜና የአገልግሎት ክፍሉ በበኪ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤት ለሚገኙ ተማሪዎች ማቋቋሚያ የሚሆን ፕሮጀክት ነድፎ እየሠራ መሆኑን በተለይ  ለመካነ ድራችን በሰጠው መግለጫ አስረድቷል፡፡ ከዚህ ቀደም  በአገልግሎት ክፍሉ አማካኝነት ለተማሪዎች ጊዜያዊ የአልባሳትና የቀለብ እገዛ የተደረገ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ግን ተግባራዊ የሆነውና  በሦስት ሔክታር መሬት ላይ  ያርፈው የእርሻ ሥራ ሙሉ ለሙሉ የተማሪዎችን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

dsc01744በሦስት ሔክታር መሬት ላይ ጤፍ ለመዝራት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ያወሱት የአገልግሎት ክፍሉ ኃላፊ ወይዘሪት መቅደስ “መሬቱን በትራክተር ከታረሰበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት የአከባቢው ገበሬዎች አርባ ጥማድ በሬዎቹን ይዘው እንዲሁም፤  ምእመናን በገንዘባቸውና በጉልበታቸው  አማካኝነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ … ከደብሩ አስተዳደር ጀምሮ ሌሎችም መደበኛ  አገልጋዮችና ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት በጋራ እንሥራ የሚለውን መርሕ የተቀበሉ ናቸው፡፡ ይህም በሌሎች ቦታዎች ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አካላት መልካም ተሞክሮ ነው፡፡” በማለት በማጠቃለያ መልእክታቸው በፕሮጀክቱ ትግበራ ላይ የተባበሩትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡