ቅዱስ ሩፋኤል
የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአት ቍስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ ነው፡፡ ‹‹በበሽታ ዅሉ ላይ በሰው ልጆችም ቍስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው›› በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል (ሄኖክ ፲፥፲፫)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ኾነ ቍስል ይፈውስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ‹‹በሰው ቍስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው›› እንዳለ ሄኖክ (ሄኖክ ፮፥፫)፡፡ ለቈሰሉ ፈውስን የሚያሰጣቸው፤ ላረገዙ ሴቶች ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም፡፡ ሕፃኑ (ኗ በማኅፀን እያለ (ች) ተሥዕሎተ መልክዕ (በሥላሴ አርአያ መልኩ /ኳ/ መሳል) ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል በጥበቃው አይለያቸውም፡፡ በመውለጃቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀልላቸዋል፡፡