ክረምት – ካለፈው የቀጠለ

በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

ነሐሴ ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተዘራው ዘር በዝናቡና በተዘራበት አፈር አማካይነት ይፈርሳል፤ ይበቅላል፤ ይለመልማል፤ ያብባል፤ ፍሬ ይሰጣል፡፡ ሰውም እንደዚሁ ነው፡፡ ይፀነሳል፤ ይወለዳል፤ ያድጋል፤ ይሞታል፡፡ ወደ መሬት ይመለሳል፤ ይፈርሳል፡፡ ትንሣኤ ዘጉባኤን ጠብቆ ይነሣል፡፡ ይህን በተመለከተ ‹‹የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፡፡ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች፤›› በማለት ጌታችን አስተምሯል (ዮሐ. ፲፪፥፳፬)፡፡ ሰውም ካልሞተ አይነሣም፤ ካልተነሣም መንግሥተ ሰማያት ሊገባ አይችልምና፡፡ ምክንያቱም ግብር እምግብር ሳይለወጡ መንግሥተ ሰማያት መግባት አይቻልምና፡፡ ስለዚህ ሰው ትንሣኤ እንዳለው ገበሬ ከሚዘራው ዘር መማርና ብዙ ፍሬ ማፍራት ይጠበቅበታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ትንሣኤ ሙታንን ባስተማረበት መልእክቱ ወርኃ ዘር የትንሣኤ ሙታን መማሪያ መኾኑን አስረድቷል፡፡ ሐዋርያው ‹‹ነገር ግን ሰው ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ አይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይኾናል፡፡ አንተ ሞኝ፣ የቆሮንቶስ ገበሬ አንተ የዘራኸው ካልሞተ ሕያው አይኾንም፡፡ የምትዘራውም ስንዴ ቢኾን ከሌላም ዓይነት (በቆሎ፣ ኑግ) የአንዱ ቢኾን ቅንጣት (ፍሬ) ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚኾነውን አካል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል፤›› በማለት አስተምሯል (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፴፭)፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው የሰው ልጅ እንደ ዘር በመበስበስ ይዘራል፤ በአለመበስበስ ይነሣል፡፡ በውርደት (አራት አምስት ሰው ተሸክሞት) ይዘራል፤ ይቀበራል፤ በክብር ይነሣል፡፡ በድካም ይዘራል፤ በኀይል ይነሣል፡፡ በፍጥረታዊ አካል ይዘራል፤ ሟች፣ ፈራሽ፣ በስባሽ አካል ይቀበራል፡፡ በመንፈሳዊ አካል ይነሣል ማለት የማይሞት፣ የማይታመም፣ የማይደክም ኾኖ ይነሣል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ላይ አንድ ገበሬ ስንዴ ከዘራ ስንዴ፣ ጤፍ ከዘራ ደግሞ ጤፍ፣ በቆሎም ከዘራ በቆሎ፣ ኑግ ቢዘራ ኑግ እንደሚኾን አካሉን ለውጦ እንደማይበቅል ሰውም የራሱን ማንነት ይዞ የሚነሣ መኾኑንም ጭምር ነው ያስተማረን፡፡ ሰው ክፉ የሠራም፣ ጽድቅ የሠራም የራሱን ሥራ ይዞ ይነሣል እንጂ ጻድቁ ኀጥእ ኀጥኡ ጻድቅ ኾኖ አይነሣም፡፡ እንደ ሥራው ዋጋውን የሚቀበልበት ነውና፡፡ ‹‹ሰው የዘራውን ያጭዳል›› እንዲል (ገላ. ፮፥፯)፡፡ በሌላ አንቀጽ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፤ ‹‹በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ያጭዳል፤ በበረከትም የሚዘራ ደግሞ በበረከት ያጭዳል፤›› (፪ኛ ቆሮ. ፱፥፮)፡፡ ይህንም ስለ መስጠትና መቀበል አስተምሮታል፡፡ የዘራ እንደሚሰበስብ፣ የሰጠም ዋጋውን አያጣምና የተዘራባት ምድር የዘሩባት አብዝታ እንደምትሰጥ፣ በምጽዋት መልክ የተቀበሉ ነዳነያንም ትልቅ ዋጋ ያሰጣሉና በሚያልፍ የማያልፍ፤ በሚያልቅ የማያልቅ ዋጋ ያስገኛሉና፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ምጽዋትን በዘር መስሎታል፡፡ ‹‹ዘርን ለዘሪ፣ ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል፤›› እንዲል (፪ኛ ቆሮ. ፱፥፲)፡፡

‹‹ብዙ ጊዜ በእርሷ ላይ የሚወርደውን ዝናም የምትጠጣ መሬት ለሚያርሷትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና፡፡ እሾኽንና ኩርንችትን ግን ብታወጣ የተጣለች ናት፡፡ ለመርገምም ትቀርባለች መጨረሻዋ መቃጠል ነው፤›› (ዕብ. ፮፥፯) ተብሎ እንደ ተጻፈ መሬት የተባለ የሰው ልጅ፤ ዘር የተባለ ደግሞ ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ ዝናም የተባለ ትምህርት፤ እሾኽ የተባለ ኀጢአት፣ ክፋት ነው፡፡ ምድር የዘሩባትን ባታበቅል መጨረሻዋ መቃጠል እንደ ኾነ ዅሉ የሰው ልጅም አደራውን ባይጠብቅ፣ የንስሐ ፍሬ ባያፈራ ፍጻሜው መከራ ይኾናል፡፡ ሰው እንደ ዘር ወደ መሬት እንደሚመለስ ዘሩ ፈርሶ፣ በስብሶ ከበቀለ በኋላ ፍሬ እንደሚሰጥ ሰውም ከሞተ በኋላ ትንሣኤ ያለው መኾኑን በማሰብ መልካም ሥራን መሥራት ይገባናል፡፡ ከዚህ አለፍ ብለን ዘር የሚለውን ቃል ስንመለከተው ድንቅ ምሥጢር ያዘለ መኾኑን እንገነዘባለን፡፡ ‹‹የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በኾንን፤ ገሞራንም በመሰልን ነበር፤›› እንዳለ (ኢሳ. ፩፥፱)፡፡ ይህም እኛን ለማዳን ከእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደውን ክርስቶስን ያመላክታል፡፡ ‹‹የነሣውን ሥጋ ከመላእክት የነሣው አይደለም፡፡ ከአብርሃም ዘር ነው እንጂ፤›› እንዲል (ዕብ. ፪፥፲፮)፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህ ዘር ምን ያህል ታላቅ መኾኑን ሲያስረዳ ‹‹ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፤›› (፩ኛ ጴጥ. ፩፥፳፫)፡፡ የማይጠፋ ዘር የተባለውም ክርስቶስ ነው፡፡ ከእርሱ ተወልደናልና እርሱንም በመከራው መስለነው በትንሣኤውም ልንመስለው ያስፈልጋል፡፡

፫. ክረምት ወርኃ ልምላሜ ነው

በክረምት ወቅት ከዘር ተከትሎ ምድር በቅጠል በልዩ ልዩ የልምላሜ ዓይነቶች አሸብርቃ፣ ደምቃ በዋዕየ ፀሐይ የተራቆተ ማንነቷ በቅጠል የሚሸፈንበት ወቅት ነው፡፡ በመኾኑም ወቅ ወርኃ ልምላሜ ነው፡፡ ፍሬ ግን የለም፤ ይህን ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ሰማይን በደመና ይሸፍናል፤ ለምድርም ዝናምን ያዘጋጃል፡፡ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም፡፡ ለሚጠሩት ለቍራ ጫጩቶች ለእንስሶችም ምግባቸውን ይሰጣል፤›› (መዝ. ፻፵፮፥፰-፲) በማለት ወቅቱ የልምላሜ፣ የሣርና የቅጠል፤ እንስሳት ሣር ቅጠሉን ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ የሚያገኙበት ወቅት እንደ ኾነ ገልጿል፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በቢታንያ መንገድ ላይ በተራበ ጊዜ ያያት በለስ ቅጠል ብቻ እንደ ነበረች፤ ጌታችንም ‹‹ለዘለዓለሙ ፍሬ አይገኝብሽ›› ብሎ እንደ ረገማት፤ በለሲቱም ወዲያውኑ እንደ ደረቀች በወንጌል ተጽፏል (ማቴ. ፳፩፥፲፰)፡፡ ያ ጊዜ የክረምት ወቅት (የቅጠል ወቅት) ነበር፡፡ ይህም በነቢያት ዘመን ይመሰላል፡፡ በዘመነ ነቢያት ዅሉም በተስፋ ብቻ ይኖሩ ነበር፡፡ ‹‹ብዙ ነቢያትና ጻድቃን ሊያዩ ተመኙ፤ አላዩም፡፡ የምትሰሙትን ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም፤›› እንዳለ ጌታችን (ማቴ. ፲፫፥፲፮)፡፡ ገበሬውም የዘራውን ዘር መብቀል በተስፋ እየተመለከተ፣ አረሙን እየነቀለ፣ ዙሪያውን እያጠረ፣ እየተንከባከበ ይጠብቃል፡፡ ደግሞም ፈጣሪውን ከበረድ እንዲጠብቅለት እየተማጸነ የራት ሰዓት እስኪደርስ መቆያ እንዲቀምስ ይህ ቅጠል ፍሬ እስኪሰጥም በተስፋ አለኝ እያለ ቅጠሉን የዐይን ምግብ አድርጎ ይጠባበቃል፡፡

በሌላ መልኩ የእግዚአብሔር መንግሥት ዘሪ በእርሻው ላይ የዘራውን ዘር እንደምትመስል ተጽፏል፡፡ ‹‹በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንዲህ ናት፡፡ ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል፡፡ እርሱም (ገበሬው) እንዴት እንደሚኾን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድግማል፡፡ ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ፣ ኋላም ዛላ፣ በዘለላው ፍጹም ፍሬ ታፈራለች፡፡ ፍሬው ሲበስል መከር ደርሷልና ወዲያው ማጭድ ይልካል፤›› እንዳለ (ማር. ፬፥፳፮-፳፱)፡፡ በገበሬ የተመሰለው ኢየሱስ ክርስቶስም እኛ በዓለም ላይ ያለን የሰው ዘሮች በሙሉ በመከር ያፈራውም ያላፈራውም እንደሚሰበሰብ ያሳየናል፡፡ ‹‹እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፣ ጌታ እስኪመጣ ድረስ እነሆ ገበሬው የፊተኛውን፣ የኋለኛውን ዝናም እርሱን የታገሠ የከበረውን የምድር ፍሬ ይጠብቃል፡፡ እናንተም ደግሞ ታገሡ፤›› እንዳለ ሐዋርያው (ያዕ. ፭፥፯-፱)፡፡ ገበሬ ቅጠሉ ፍሬ እስከሚሰጥ ምን ያህል መከራን እንደሚታገሥ እኛም መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ቅጠል ብቻ የኾነ ማንነታችን የንስሐ ፍሬ እስኪያፈራ ድረስ መከራውን መታገሥ ይገባናል፡፡ ምድራዊ ፍሬ ለማግኘት ይህን ያህል መጠበቅና መታገሥ ካስፈለገ ሰማያዊ ዋጋ ለመቀበል ምን ያህል መታገሥ ያስፈልግ ይኾን? ከወርኃ ቅጠል ያለ ፍሬ ብንገኝ መርገምን እንደምናተርፍ፣ ብናፈራ ግን ገበሬ ምርቱን ደስ ብሎት እንዲሰበስብ ፈጣሪያችንም በእኛ እንደሚደሰትና ዋጋችንን እንደሚሰጠን እንማራለን፡፡ ክረምት ጥልቅ ትምህርት የምንማርበት እግዚአብሔር በሰፊው የሚገለጽበት ወቅት ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡