ወርኀ ጳጕሜን

በዲያቆን ዳንኤል ክብረት

ጳጕሜን  ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የኢትዮጵያን የዘመን አቈጣጠር ለየት ከሚያደርጉት ነጥቦች አንዱ ‹ጳጕሜን› የምትባል ዐሥራ ሦስተኛ ወር መኖሯ ነው፡፡ ‹ጳጕሜ› ማለት በግሪክ ቋንቋ ‹ጭማሪ› ማለት ሲኾን፣ ወርኀ ጳጕሜን ዓመቱ በሠላሳ ቀናት ሲከፈል የሚተርፉት ዕለታት ተሰባስበው የሚያስገኟት፤ ወይም በየዕለቱ በፀሐይና በጨረቃ አቈጣጠር መካከል የሚፈጠሩት ልዩነቶች ተሰባስበው የተከማቹባት ተጨማሪ ወር ናት፡፡ ወርኀ ጳጕሜን የቤት ኪራይና የወር ደመወዝ የማንከፍልባትና የማንቀበልባት፤ መብራትና ውኃ ግን ከነሐሴ ወር ጋር ጨምረው የሚያስከፍሉባት፤ ሲሻት አምስት፣ ሲያስፈልጋት ስድስት፣ አልፎ አልፎ ሰባት የምትኾን ወር ናት፡፡ ከዐሥራ ሁለቱ የኢትዮጵያ ወሮች መካከል ወርኀ ጳጕሜን በብዙ መንገድ የተለየች ናት፡፡ በአንድ በኩል በጣም ትንሿ ወር ናት፡፡ ሲቀጥልም ወርኃዊ በዓላት የማይውሉባት ወር ናት፡፡ ደግሞም ከሌሎች ወሮች በተለየ መልኩ የቀኖቿ መጠን የሚቀያየሩ ብቸኛ ወር ናት፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወሮች በተለየም ስሟ ኢትዮጵያዊ ያልኾነ ወር ናት፡፡ በሁለት ዘመናት መካከል እንደ መሸጋገሪያ የምትታይም ናት፡፡

ዓመቱ በዐውደ ፀሐይ ሲለካ 365 ቀናት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ሲኾን፣ በጨረቃ ሲለካ ደግሞ 354 ቀናት ከ22 ኬክሮስ፣ ከ1 ካልዒት፣ ከ36 ሣልሲት፣ ከ52 ራብዒት፣ ከ48 ኀምሲት ነው፡፡ በሁለቱ አቈጣጠር መካከል (በፀሐይና በጨረቃ) በዓመት ውስጥ ያለው ልዩነት 11 ቀናት ከ7 ኬክሮስ ይኾናል፡፡ በዘመን አቈጣጠራችን ከዕለት በታች የምንቈጥርባቸው ስድስት መለኪያዎች አሉን፡፡ እነዚህም ኬክሮስ፣ ካልዒት፣ ሣልሲት፣ ራብዒት፣ ኀምሲትና ሳድሲት ናቸው፡፡ 60 ሳድሲት 1 ኀምሲት፣ 60 ኀምሲት 1 ራብዒት፣ 60 ራብዒት 1 ሣልሲት፣ 60 ሣልሲት 1 ካልዒት፣ 60 ካልዒት 1 ኬክሮስ ነው፡፡ 60 ኬክሮስ 1 ዕለት፤ 1 ኬክሮስ ደግሞ 24 ደቂቃ ነው፡፡ ወርኀ ጳጕሜንን ለማግኘት የሚረዳንም የየዕለቱን ልዩነታቸውን መመልከቱ ነው፡፡ በየዕለቱ በጨረቃና በፀሐይ መካከል ያለው የጊዜ ስሌት 1 ኬክሮስ ከ52 ካልዒት ከ31 ሣልሲት ይኾናል፡፡ ይህም ማለት 5 ሰዓት ከ48 ደቂቃ ከ46 ካልዒት ነው፤ ይህ ልዩነት በአንድ ወር ምን ያህል እንደሚደርስ ለማወቅ በ30 ብናበዛው 30 ኬክሮስ ከ1560 ካልዒት፣ ከ930 ሣልሲት ይኾናል፡፡ የዓመቱን ለማግኘት ደግሞ በ12 ብናበዛው 360 ኬክሮስ ከ18720 ካልዒት፣ ከ11160 ሣልሲት ይመጣል፡፡

360 ኬክሮስ ለ60 ሲካፈል 6 ዕለታትን ይሰጠናል፡፡ 18720 ካልዒትን በስድሳ በማካፈል 312 ኬክሮስን እናገኛለን፡፡ ይኸውም ትርፉን 12 ኬክሮስ ትተን 300ውን ኬክሮስ ለ60 በማካፈል 5 ዕለት እናገኛለን ማለት  ነው፡፡ ውጤቱም 5 ዕለት ከ12 ኬክሮስ ይኾናል፡፡ 11160 ሣልሲትን ለ60 ብናካፍለው 186 ካልዒት ወይም ደግሞ 3 ኬክሮስና 6 ካልዒት ይኾናል፡፡ ከላይ ኬክሮስን በዓመቱ ቀናት አባዝተን ያገኘነው 6 ዕለት ‹ሕጸጽ› ይባላል፡፡ ፀሐይና ጨረቃን እኩል መስከረም አንድ ላይ ዓመቱን ብናስጀምራቸው ፀሐይ የወሯ መጠን ምንጊዜም 30 ሲኾን፣ ጨረቃ ግን በአንደኛው ወር 29፤ በሌላኛው ወር ደግሞ 30 ስለምትኾን ዓመቱ እኩል አያልቅም፡፡ የጨረቃ ዓመት የሚያልቀው ነሐሴ 24 ቀን ነውና፡፡ ይህም ማለት ጨረቃ በሁለት ወር አንድ ጕድለት ታመጣለች ማለት ነው፡፡

ይህንን ነው ሊቃውንቱ ‹ሕጸጽ› (ጕድለት) ያሉት፡፡ በዚህም መሠረት ከላይ ኬክሮሱን በዓመቱ ቀናት አባዝተን ያገኘነውን 6 ዕለት ለጨረቃ ሕጸጽ ስንሰጠው የመስከረም (ጥቅምት) 1፣ የጥቅምት (ኅዳር) 2፣ የጥር (የካቲት) 3፣ የመጋቢት (ሚያዝያ) 4፣ የግንቦት (ሰኔ) 5፣ የሐምሌ (ነሐሴ) 6 ኾነው ተካፍለው ያልቃሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በጨረቃና በፀሐይ ዑደት መካከል በዓመት ያለው ልዩነት 11 ቀናት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ይኾናል፡፡ ስድስቱን ዕለታት ጨረቃ ለምታጋድልበት ሕጸጽ ብንሰጠው ቀሪ 5 ዕለት ይኖረናል፡፡ ወርኀ ጳጕሜን ማለት እነዚህ 5 ቀናት ናቸው፡፡ የዐሥራ አንዱን ዕለታት ከፈጸምን ሽርፍራፊዎቹን (15 ኬክሮስና 6 ካልዒትን) እንመልከት፤ ከላይ እንደ ተጠቀሰው በፀሐይና በጨረቃ ዓመታት መካከል የተፈጠሩትን 11 ቀናት ስድስቱ ለሕጸጽ ማሟያ ሲገቡ የቀሩት 5 ዕለታት ናቸው ጳጕሜን የምትባለውን ወር ያስገኟት፡፡

በጎርጎርዮሳውያኑ አቈጣጠር እነዚህ 5ቱ ዕለታት በጃንዋሪ፣ ማርች፣ ሜይ፣ ጁላይና ኦገስት ላይ ስለ ተጨመሩ ወሮቹ 31 ሊኾኑ ችለዋል፡፡ ይኽን የከፈለው ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ46 ዓ.ዓ የነበረው ዩልየስ ቄሣር ነው፡፡ ዩልየስ ለአራቱ ወሮች 30 ቀን፣ ለአንዱ 28 /29 (በየአራት ዓመቱ)፣ ለቀሩት ሰባት ወሮች ደግሞ 31 ቀን ሰጥቷቸዋል፡፡ አምስቱን ወሮች 31 ያደረጋቸው ከጳጕሜን ወስዶ ሲኾን ለሁለቱ ወሮች አንዳንድ ቀን የጨመረላቸው ደግሞ ከፌቡርዋሪ (የካቲት) 2 ቀናት ወስዶ ወሩን 28 በማድረግ ነው፡፡ ከእንግዲህ የሚተርፉት ከላይ የየዕለቱን ልዩነት በዓመት ስናባዛ የቀሩት 15 ኬክሮስና 6 ካልዒት ናቸው፡፡ ሁለቱን ከላይ ያገኘናቸውን ውጤቶች ስንደምራቸው (12 ኬክሮስ + 3 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት) 15 ኬክሮስ ከ 6 ካልዒት ይመጣሉ፡፡ 1 ዕለት 60 ኬክሮስ በመኾኑ 1 ዕለትን (60 ኬክሮስን) ለማግኘት ከላይ ያገኘነውን 15 ኬክሮስ በ4 ማባዛት ይኖርብናል፡፡

በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ጳጕሜን 6 ቀን የምትኾነውም እነዚህ በየዓመቱ የተሰባሰቡ 15 ኬክሮሶች አንድ ላይ መጥተው በአራት ዓመት አንድ ጊዜ አንድ ዕለት ስለሚኾኑ ነው፡፡ እርሷም ሠግር (leap year) ትባላለች፡፡ ጎርጎርዮሳውያኑ ይኽቺን ሠግር በፌቡርዋሪ ወር ላይ ጨምረው ወሩን በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ 29 ቀን ያደርጉታል፡፡ 15ቱ ኬክሮስ በአራት ዓመት ተደምረው አንድ ዕለት መጡና በአራት ዓመት አንድ ጳጕሜን ስድስት ቀን እንድትኾን አድርገዋታል፡፡ የቀረችው 6 ካልዒትስ የት ትግባ ከተባለ ካልዒት አንዲት ዕለት ትኾን ዘንድ 3600 ካልዒት ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን ያህል ካልዒት ለማግኘት ደግሞ 600 ዓመታት ያስፈልጉናል፡፡ ከዚኽ ስሌት አኳያ ጳጕሜን በየስድስት መቶ ዓመታት ሰባት ቀን ትኾናለች፡፡

ጳጕሜን 5 ቀን በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ‹ዕለተ ምርያ› ወይም ‹የተመረጠች ቀን› ትባላለች፡፡ ሊቃውንቱ የጌታችንን ልደት ሲያሰሉባት የቆየችው ዕለት በመኾኗ ነው ይህንን ስያሜ ያገኘችው፡፡ የጌታችንን ልደት ቀን የምትወስነው የጳጕሜን 5ኛዋ ቀን ናት፡፡ በዓለ ልደት የሚውለውም ጳጕሜን 5 በዋለበት ቀን ነው፡፡ ለምሳሌ ዘንድሮ (2009 ዓ.ም) ጳጕሜን 5 ቀን እሑድ ይውላል፤ ስለዚህም በ2010 ዓ.ም የሚበረው በዓለ ልደት እሑድ ይኾናል ማለት ነው፡፡ በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ ጳጕሜን 6 ቀን ስትኾን ልደት በ28 የሚከበረውም በዓለ ልደት ጳጕሜን 5 ቀንን (ዕለተ ምርያን) ስለማይለቅ ነው፡፡ በዘመነ ዮሐንስ ስድስተኛዋ የጳጕሜን ቀን በዓለ ልደትን በአንድ ቀን ዝቅ ብሎ እንዲከበር ስለምታደርገው ልደትን ታኅሣሥ 28 ቀን እናከብራለን፡፡ ታድያ ምነው ጥምቀት፣ ግዝረትና ሌሎችም በዓላት አይለወጡም? ቢሉ ሊቃውንቱ የሚሰጡት ምላሽ ‹‹ትውልድ ሱባዔ እየቈጠረ በተስፋ የጠበቃት ዕለተ ልደትን ስለ ኾነ ነው፡፡ ሌሎቹ በዓላት የመጡት በልደቱ ምክንያት ነውና›› የሚል ነው፡፡

በጎርጎርዮሳውያን አቈጣጠርም በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዓለ ልደት ዝቅ ብሎ ይከበራል፡፡ የእነርሱ በግልጽ የማይታወቀው ጭማሪዋ ፌብርዋሪ (የካቲት) ላይ ስለምትኾን ነው፡፡ ይህ ደግሞ አዲሱን ዓመት ካከበሩ በኋላ ይመጣል፡፡ በእኛ አቈጣጠር ግን ጭማሪዋ የምትወድቀው ጳጕሜን መጨረሻ ላይ ስለ ኾነና ከአዲስ ዓመት በፊት ተደምራ ስለምትቈጠር ቍጥሯ ጐልቶ ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ ‹ጳጕሜን› የምትባለው አስገራሚዋና ትንሿ ወራችን እንዲህ በስሌት የተሞላች፣ በሦስት ዓመታት አምስት ቀን ኾና ቆይታ በአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ ስድስት፣ በየስድስት መቶ ዓመት ደግሞ ሰባት ቀን የምትኾን ወር ናት፡፡ እንደዚሁም ታላላቆቹ ወሮች ምንም ሳይፈጥሩ የልደትን ቀን የምትወስን፣ የዓመቱን ሠግር የምታመጣ፣ ታሪከኛ ወርም ናት፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡