ክረምት – የመጀመርያ ክፍል

በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

ነሐሴ ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹ክረምተ ወሐጋየ ዘአንተ ፈጠርከ፤ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ፤›› (መዝ. ፸፫፥፲፯) በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደ ገለጸው እግዚአብሔር አምላክ የዓለምን ምግብ ሥጋዊውንም መንፈሳዊውንም በአራት ወቅት ከፍሎታል፡፡ ሥጋዊውን በአራቱ ክፍላተ ዘመን፤ መንፈሳዊውን በአራቱ ወንጌላዊያን ትምህርት፡፡ የሰው ልጅ ሥጋዊ ምግብና ከአራቱ ክፍላተ ዘመን እንደማይወጣ ዅሉ መንፈሳዊ ምግብናውም ከአራቱ ወንጌላውያን አይወጣም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሥጋም የነፍስም ፈጣሪ፣ መጋቢ ነውና፡፡ ከአራቱ ክፍላተ ዘመን አንዱ አሁን የምንገኝበት ዘመነ ክረምት ነው፡፡ በዘመነ ክረምት ከሥጋዊ ምግብ ያለፈ መንፈሳዊ ምግብም እናገኛለን፡፡

ክረምት ምንድን ነው?

ክረምት ማለት ‹ከርመ – ከረመ› ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን ‹መክረም፣ የዓመት መፈጸም፣ ማለቅ፣ መጠናቀቅ› ማለት ነው፡፡ ክረምት፣ በፀሐይ የደረቁ ኮረብቶች፣ ተራሮች በዝናም አማካይነት ውኃ የሚያገኙበትና በልምላሜ የሚሸፈኑበት፤ የደረቁ ወንዞች፣ ጉድጓዶች በውኃ የሚሞሉበት፤ በፀሐይ የተቃጠለች ምድር ከሰማይ በሚወርድ ጠል በረከት የምትረካበት፤ በውኃ ጥም የተሰነጣጠቁ የምድር ጉረሮዎች ውኃን የሚጠግቡበት፤ ሰማይ በደመና፣ የተራሮች ራስ በጉም የሚሸፈኑበት፤ በሙቀት ፋንታ ቅዝቃዜ፣ በድርቅ ፈንታ ልምላሜ የሚነግሥበት፤ ተሰባብሮ የወደቀ ሐረግ (ተክል) ቀና ብሎ የሚቆምበት፣ የሚያድግበት ወቅት ነው፡፡

፩. ክረምት ወርኃ ማይ (የውኃ ወቅት) ነው

ውኃ፣ እግዚአብሔር አምላክ ለፈጠረው ፍጥረት ዅሉ በጣም አስፈላጊ ፍጥረት ነው፡፡ ምድር የዘሩባትን እንድታበቅል፣ የተከሉባትን እንድታጸድቅ፣ ያጸደቀችውን ተክልም ለፍሬ እንድታበቃ ውኃ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለ ውኃ ለምግብነት የሚውል ነገር በዓለማችን ውስጥ የለም፡፡ ምግብ የሚዘጋጀውም የሚወራረደውም በውኃ ነው፡፡ ‹‹ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ? ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡ?›› በማለት አበው የውኃን ጥቅም ያስረዳሉ፡፡ ቁሳቁሱ የሚታጠበው፤ ቤት የሚሠራው፤ ሕንጻ የሚገነባው በውኃ ነው፡፡ በባሕርም በየብስም ለሚኖሩ፤ ለምግብነት ለሚዉሉትም ለማይዉሉትም ውኃ አስፈላጊ ነው፡፡ እንስሳትም፣ እፀዋትም፣ ምድርም ውኃ ይፈልጋሉ፡፡ በጠቅላላው የፍጡራን ሕይወት የውኃ ጥገኛ ነው፡፡ የሰው ልጅ የሚጠቀምባቸው ፍጡራን ዅሉ ያለ ውኃ ምግብ አይሰጡም፡፡ ስለዚህ ከፍጡራን በተለየ መልኩ ውኃ ለሰው ልጅ ያስፈልገዋል፡፡ በዓለማችን ብዙውን ቦታ የሚሸፍነው ውኃ መኾኑን ሥነ ፍጥረትም ሳይንስም ይስማሙበታል፡፡ ምክንያቱም በምድር ላይ ካለ ፍጡር ውኃ የማያስፈልገው የለምና፡፡

ከዚህ አለፍ ብለን ስንመለከት በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረ የሰው ልጅ ከተፈጠረባቸው አራት ባሕርያት አንዱ ውኃ ነው፡፡ የሰው ልጅ በመሬትነት ባሕርዩ እየፈረሰና እየተቆረሰ ዓለምን እንዳያጠፋ በውኃነት ባሕርዩ አንድነቱ ጸንቶለት ይኖራል፡፡ በእሳትነት ባሕርዩ ዓለምን እንዳያቃጥል በውኃነት ባሕርዩ እየቀዘቀዘ ይኖራል፡፡ ሰው ከእናቱ ተወልዶ የእናቱን ጡት ጠብቶ እንዲያድግ ሰውም ከውኃ፣ ከእሳት፣ ከነፋስና ከመሬት ተፈጥሮ እነዚሁ የተገኘባቸውን እየተመገበ በምድር ይኖራል፡፡ የአራቱ ባሕርያት አስታራቂ ሽማግሌ ውኃ ነው፡፡ ጠበኞች የኾኑ ነፋስና መሬት በውኃ ይታረቃሉ፡፡ ነፋስ መሬትን ይጠርገዋል፡፡ መሬትም ነፋስን ይገድበዋል፡፡ ዝናም በዘነመ ጊዜ ትቢያው (የመሬት ላይኛው ክፍል) በውኃ አማካይነት ከታችኛው ክፍል ጋር አንድ ይኾናል፤ በነፋስ ከመወሰድም ይተርፋል፡፡

ከዚህም ሌላ ውኃ የእግዚአብሔር መሣሪያ ነው፡፡ የሰው ልጆች ሕገ እግዚአብሔርን ሲጥሱ፣ ትእዛዘ እግዚአብሔርን ሲያፈርሱ ከሥርዓቱ ሲወጡ፣ ከአምልኮቱ ሲያፈነግጡ ውኃ መቅጫ መሣሪያ ነው፡፡ ለምሳሌ በኀጢአት የተበላሸው፣ የቆሸሸው ዓለም የተቀጣው በውኃ ነው (ዘፍ. ፮፥፩፤ ፯፥፩፤ ፰፥፩)፡፡ ነቢዩ ኤልያስ፣ አምልኮተ እግዚአብሔርን በአምልኮተ ጣዖት ተክተው፣ ሃይማኖተ ኦሪትን ትተው፣ የጣዖት ውሽማ አበጅተው ያስቸገሩትን አክአብና ኤልዛቤልን እንደዚሁም መሰሎቻቸውን የቀጣው ዝናም ለዘር፣ ጠል ለመከር እንዳይሰጥ ሰማይን ለጉሞ፣ ዝናምን አቁሞ ነው፡፡ በአንጻሩ በረድና እሳት አዝንሞ እንደ ነበርም መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡ ‹‹ኤልያስ እንደኛ የኾነ ሰው ነበር፡፡ ዝናም እንዳይዘንም አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናም አልዘነበም፡፡ ሁለተኛም ጸለየ፤ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ፤ ምድር ፍሬዋን አበቀለች፤›› በማለት ሐዋርያው እንደ ተናገረው (ያዕ. ፭፥፲፯)፡፡

ውኃ እስከ አሁን የተመለከትነው በሥጋዊ ምግብነቱ የሚሰጠውን አገልግሎት ነው፡፡ ውኃ መንፈሳዊ ምግብና (ምግብነት ወይም አገልግሎት) አለው፡፡ ደገኛዋ የሰው ልጆች ጥምቀት በውኃ መፈጸሟ የውኃ ጥቅም የጎላ መኾኑን ያሳየናል፡፡ የጥምቀታችን መሥራች ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቶቻችንና በእኛ ላይ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ያጠፋልን በውኃ ተጠምቆ ነውና (ማቴ. ፫፥፲፫)፡፡ ‹‹ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዮሐ. ፫፥፭)፡፡ ይኸውም ውኃ ከሥጋዊ ምግብናው ባሻገር እኛ የእግዚአብሔር ልጆች የምንኾንበት ምሥጢር መፈጸሚያ መኾኑን ያስረዳል፡፡ በሌላ መልኩ ጌታችን የእኛን ሥጋ ለብሶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተገልጾ ባስተማረ ጊዜ ‹‹እንጀራ ለመነ›› ሳይኾን ‹‹ውኃ ለመነ›› ተብሎ ነው የተነገረለት፡፡ ‹‹ውኃ አጠጪኝ አላት›› እንዲል (ዮሐ. ፬፥፯)፡፡ እስራኤልን ዐርባ ዓመት ውኃ ከጭንጫ እያፈለቀ ያጠጣ አምላክ ውኃ የለመነው ውኃ አጥቶ አይደለም፡፡ ውኃ ትልቅ ምሥጢር የሚፈጸምበት መኾኑን ለመግለጽ ነው እንጂ፡፡ ይኸውም ሊታወቅ ‹‹የእግዚአብሔርን ስጦታና ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መኾኑን ብታውቂስ አንቺ ደግሞ በለመንሺው፤ እርሱም የሕይወትን ውኃ በሰጠሸ ነበር … እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ለዘለዓለም አይጠማም፤›› በማለት አስተምሮአል፡፡

ጌታችን በመስቀል ላይ ከተናገራቸው ሰባቱ ንግግሮች አንዱ ‹‹ተጠማሁ›› የሚል ነበር (ዮሐ. ፲፱፥፳፱)፡፡ ይህ ከሥጋ መጠማት ያለፈ የእኛን የነፍሳችን ጥማት እንደ አጠፋልን የምንማርበት ነው፡፡ እኛን የሕይወት ውኃ ያጠጣን ዘንድ ተጠማሁ አለም፤ በዓለም ላሉ ፍጡራን ዅሉ ውኃ አስፈላጊ ቢኾንም ቅሉ በተለይ ለሰው ልጆች እጅግ አስፈላጊ እንደ ኾነ ሲያስረዳም ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ ‹‹እናንተ የተጠማችሁ ዅሉ ወደ ውኃ ኑ፤ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ፤›› (ኢሳ. ፶፭፥፩)፡፡ ‹‹የተጠማ ይምጣ፤ ይጠጣ፤›› የሚለው ኃይለ ቃል ብዙ ምሥጢር አለው፡፡ ጌታችን የአይሁድ በዓል በሚከበርበት ቦታ ተገኝቶ ቀደም ሲል በኢሳይያስ የተነገረው ቃል ስለ መንፈስ ቅዱስ የተነገረ መኾኑን ገልጿል፡፡ ‹‹ኢየሱስም ቆሞ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፡፡ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ፡፡ ይኼን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስለ አላቸው ስለ መንፈስ ቅዱስ ተናገረ፤›› እንዲል (ዮሐ. ፯፥፴፯-፴፱)፡፡ ስለዚህ ውኃ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ኾኗል ውኃ ከቆሻሻ፣ ከዕድፍ እንዲያነጻ መንፈስ ቅዱስም ከኀጢአት፣ ከርኵሰት፣ ከክፋት፣ ከተንኮል፣ ከበደል ሰውን ያነጻልና፡፡

፪. ክረምት ወርኃ ዘር (የዘር ወቅት) ነው

ገበሬው በበጋ ያረሰውን የከሰከሰውን ደረቅ መሬት በዝናብ ወቅት አለስልሶ አዘጋጅቶ ከጎታው ወይም ከጎተራው ያስቀመጠውን ዘር ባዘጋጀው መሬት ላይ አውጥቶ ይዘራል፡፡ መሬቱ ያብቅል አያብቅል ፍሬ ይስጥ አይስጥ ሳያውቅ እግዚአብሔር በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ ይመግበኛል ብሎ በማመን ያለ ምንም ጥርጥር የጎታውን እኽል ለመሬት አደራ ይሰጣል፡፡ ከላይ ዝናሙን ከታች ጭቃውን ታግሦ በሬዎችን እየነዳ በትከሻው ላይ ዘርና ቀምበር ተሸክሞ ዘር ለመዝራት ይሰማራል፡፡ የገበሬውን ኹኔታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ገልጾታል፤ ‹‹ዘሪ ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም አንዳንዱ ዘር ከመንገድ ዳር ወደቀ፡፡ በጭንጫ ላይ የወደቀ ዘር አለ፡፡ በእሾኽ መካከል የወደቀ ዘርም አለ፡፡ በመልካም መሬት ላይም የወደቀ ዘር አለ፡፡ መቶ፣ ስልሳ፣ ሠላሳ ፍሬ ሰጠ፤›› (ማቴ. ፲፫፥፩)፡፡ ጌታችን ራሱን በገበሬ፣ ቃሉን በዘር፣ የሰማዕያንን ልቡና በመንገድ፣ በዐለት፣ በእሾኽ፣ በለሰለሰ መሬት መስሎ አስተምሯል፡፡ በመንገድ የተመሰለው ሰምተው የማያስተውሉ ሰዎች ልቡና ነው፡፡ የሰማይ ወፎች የተባሉ ደግሞ አጋንንት ናቸው፡፡ ‹‹ኢትሕሚ ሰብአ በቤትከ እስመ ዖፈ ሰማይ ያወጽዖ ለነገርከ፤ የሰማይ ወፍ (ሰይጣን) ቃልህን ያወጣዋልና፣ ክንፍ ያለውም ነገርህን ያወራዋልና በልብህ ዐሳብ እንኳን ቢኾን ንጉሥን አትሳደብ፤ በመኝታ ቤትህም ባለ ጠጋን አትማ፤›› እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን (መክ. ፲፥፳)፡፡

በዐለት የተመሰሉት ፈጥነው የሚሰሙ ግን ተግባር ላይ የሌሉ በእሾኽ የተመሰሉትም የዚህ ዓለም ዐሳብ፣ ምድራዊ ብልጽግና፣ ፍቅረ ዓለም አስሮ የያዛቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በመልካም መሬት የተመሰሉት ደግሞ ቃሉን ሰምተው የጽድቅ ሥራን የሚሠሩ ናቸው፡፡ በወርኃ ዘር የምንማረው ትልቁ ትምህርት ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ነው፡፡ በወርኃ ማይ ምሥጢረ ጥምቀትን እንደተማርን ገበሬው በጎታው ያከማቸውን እኽል ከአፈር ጋር አንድ እንደሚያደርገው ማለት በአፈር ላይ እንደሚዘራው የሰው ዘርም እንዲሁ ‹‹ውሎ ውሎ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት›› እንዲሉ ሲሞት በመቃብር ከአፈር ጋር አንድ ይኾናል፤ ይፈርሳል ይበሰብሳል፤ ወደ አፈርነቱ ይመለሳል፡፡ ‹‹ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፡፡ አፈር ነህና ወደ አፈርነትህም ትመለሳለህና፤›› እንዳለ (ዘፍ. ፫፥፲፱)፡፡

ይቆየን