Entries by Mahibere Kidusan

ከሁለት ሺሕ በላይ አዳዲስ አማንያን የሥላሴን ልጅነት አገኙ

ከተጠማቂዎቹ መካከል አንዱ የኾኑት በዝጊቲ ባቆሌ ቀበሌ ነዋሪና የሌላ እምነት ተከታይ የነበሩት አቶ ዘሪኹን ቱሎ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አምላክነት የሚሰበክባት፣ በጠበልና በእምነት ከሕመም መዳን የሚቻልባት እውነተኛ ሃይማኖት እንደኾነች በእኛ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ይነግሩኝ ነበር፡፡ ይህ ነገር ምን ያህል እውነት ነው እያልኹ ከራሴ ጋር ስሟገት ዓመታት ቢያልፉም ባለቤቴ ‹ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመለሱ› የሚል መልእክት በራእይ በመስማቷ ማንም ወደ ጥምቀቱ ሳያመጣን አምነን ተጠምቀን በዛሬዋ ዕለት የሥላሴን ልጅነት አግኝተናል›› በማለት የቤተ ክርስቲያን አባል የኾኑበትን ምሥጢር አስረድተዋል፡፡

የ፳፻፲ ዓ.ም የጥቅምት ወር ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤን መጀመር አስመልክቶ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሰጡት ሙሉ ቃለ ምዕዳን 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ለሁለት ሺሕ ዓመታት ያህል በአንድነትና በጥንካሬ ጠብቆ ያቆየ ጥበብ ኦርቶዶክሳዊና ሲኖዶሳዊ የሆነ የውሉደ ክህነት አመራር ጥበብ እንጂ የምዕራባውያንና የሉተራውያን ምክር ቤታዊና ዘመን አመጣሽ ፍልስፍና አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መርሕ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የምናያት አንዲት ሐዋርያዊትና ኃያል ቤተ ክርስቲያን ሳትሆን የተበታተነች የደከመችና መዓዛ ሐዋርያት የሌላትና የተለያት ቤተ ክርስቲያን ነበር የምናየው፡፡ ይሁን እንጂ አባቶቻችን ካህናት መሪዎች፣ ሕዝቡ ተመሪ ሆኖ በአንድ የእዝ ሰንሰለት እየተደማመጠ ካህኑ ተናገረ ማለት እግዚአብሔር ተናገረ ማለት ነው በሚል ቅንና ትሕትና የተመላ ታዛዥነት እንደዚሁም በውሉደ ክህነት አመራር ሰጪነት የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት እስከዛሬ ድረስ ተጠብቆ ቆይቷል፡፡

አሁን ግን ይህ ቀርቶ በአባቶች ላይ ተደራቢ አመራር ሰጪ፣ በአባቶች ላይ የስድብ ናዳ አውራጅ ትውልድ መበራከቱን ካየንና ከሰማን ውለን አድረናል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ከጎናችን ሳይሆኑ ከጎናችሁ አለን የሚሉ ወገኖችም ስለድርጊቱ አፍራሽነት በተመለከተ አንድ ቀንስንኳ የተቃውሞ ሐሳብ አለመሰንዘራቸው በስተጀርባው እነርሱራሳቸው ያሉበት እንደሆነ የሚያመላክት መስሎ አሳይቶባቸዋል፡፡ አሁን ዋናው ጥያቄ፣ ይህ ራስ ወዳድ አመለካከት ተቀብሎ የሚመጣውን ጥፋት ማስተናገድ ይሻላል? ወይስ ራስን መካድ የሚለውን የጌታ ትምህርት አሥርፆ ነገሮች ሁሉ በንሥሐ ወደነበሩበት መመለስ፣ ምርጫውን ለዚህ ዓቢይ ጉባኤ አቅርበነዋል፡፡

ተዝካሩን አውጥቶ ክርስቶስን የተከተለ ሐዋርያ

የቅዱስ ማቴዎስ ተጋድሎውና የምስክርነቱ ፍጻሜ ሲቃረብ ወደ አንዲት ከተማ ገብቶ አስተማረ፡፡ በዚያም ብዙዎችንም አሳመነ፡፡ አገረ ገዢውም ይዞ ከወኅኒ ቤት ጨመረው፡፡ በወኅኒ ቤቱም አንድ እጅግ የሚያዝን እስረኛ አገኘና ስለ ሐዘኑ ጠየቀው፡፡ እርሱም ብዙ የጌታው ገንዘብ ከባሕር እንደ ሰጠመበት ነገረው፡፡ ሐዋርያው ማቴዎስም እስረኛው የጠፋበትን ገንዘብ የሚያገኝበትን የባሕር ዳርቻ ጠቆመው፡፡ እስረኛውም ሐዋርያው በነገረው መሠረት የጠፋውን ገንዘብ አግኝቶ ለጌታውም ሰጠው፡፡ ጌታውም ከየት እንዳገኘው ቢጠይቀው ከወኅኒ ቤት ባገኘው በሐዋርያው ማቴዎስ ጥቆማ የጠፋውን ገንዘብ ሊያገኘው መቻሉን ነገረው፡፡ ጌታው ግን ሊያምነው አልቻለም ነበር፡፡

ይልቁንም እጅግ ተቆጥቶ ሐዋርያውን ከእስር ቤት አስወጥቶ ወደ ንጉሡ ወሰደው፡፡ ንጉሡም ተዝካሩን አውጥቶ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የተከተለውን ሐዋርያ ቅዱስ ማቴዎስን ወዲያው በሰይፍ ራሱን እንዲቆርጡት፣ ሥጋውንም ለሰማይ ወፎች እንዲጥሉት አዘዘ፡፡ የንጉሡ ወታደሮችም በታዘዙት መሠረት ጥቅምት ፲፪ ቀን በ፷ ዓ.ም የሐዋርያውን አንገት በሰይፍ ቆርጠው ራሱን ለብቻ፣ ሰውነቱን ለብቻ አድርገው አሞሮች እንዲበሉት ጥለውት ሔዱ፡፡ ምእመናንም ራሱንና ቀሪው ሰውነቱን በአንድ አድርገው ካባቶቹ መቃብር እንዲቀበር አደረጉ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ

በገድለ ሐዋርያት እንደ ተጠቀሰው ቅዱስ ማቴዎስ ከማረፉ በፊት በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል፤ በዚያም ሄሮድስ በግፍ በጨፈጨፋቸው ሕፃናት ክብረ በዓል ጌታችን ወደ እነርሱ ሲመጣ፣ መላእክትም በዙሪያው ከበው ሲያመሰግኑት ያይ ነበር፡፡ ከዚያ ተመልሶም በየአገሩ እየዞረ ወንጌልን አስተምሯል፤ ካስተማረባቸው አገሮችም ፍልስጥኤም፣ ፋርስ፣ ባቢሎን፣ ኢትዮጵያና ዓረቢያ ይጠቀሳሉ፡፡ የማስተማር ተልእኮው የተከናወነውም በታንሿ እስያ ውስጥ ነው፡፡ ግሪካውያን አሕዛብ ‹‹አምላካችንን ሰደበብን›› ብለው አሥረውት በነበረ ጊዜም ወኅኒ ቤት ኾኖ ወንጌልን ይሰብክ ነበር፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በ፵ ዓ.ም በአገራችን በኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ወንጌልን እንደ ሰበከና በዘመኑ የነበሩ ኦሪታውያን ነገሥታትን ጨምሮ በርካታ አሕዛብን አስተምሮ በማጥመቅ ወደ ክርስትና ሃይማኖት እንደ መለሰ፤ እንደዚሁም ለምጻሞችን በማንጻት፣ አንካሶችን በማርታት፣ ሕሙማንን በመፈወስ፣ ሙታንን በማስነሣት ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እንዳደረገ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና በትግራይ ክልል በማኅበረ ጻድቃን ዴጌ ገዳም የሚገኙ የብራና መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ወቅታዊ የአዘክሮ መልእክት

የማኅበሩ አባላትና ወዳጆቹ፣ እንዲሁም የአገልግሎት አጋሮቹና ተባባሪዎቹ ዂላችሁ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉልንን ምክሮች ከማዘከርና ዂልጊዜም ቢኾን ከክፉው ተጠብቀን መልካም የኾነውን አርአያና አብነት ከማድረግ ልንቆጠብ አይገባንም፡፡ በትንሹ እና ሕይወታችንን በሙሉ ሳይኾን ከትርፋችን የምናገለግላት ቤተ ክርስቲያናችን በምድር ላይ እንዳሉ ሌሎች ተቋማት የዚህ ዓለም አደረጃጀትና አሠራር ብቻ የሚመራት ምድራዊ ተቋም ሳትኾን ረቂቅነትን እና መንፈሳዊነትንም ገንዘብ ያደረገች አካለ ክርስቶስ እንደ መኾኗ መጠን የምንፈጽመው ዂሉ መንፈሳዊነት ከጎደለው፣ ርባና ቢስ መኾኑን ለአፍታም ቢኾን ልንዘነጋው የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ ለድርጊቶቻችን አብነት የምናደርገውም ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረው ብልሆቹን፣  መልካሞቹንና ደጎቹን እንጂ ሞኞቹን፣ ክፉዎቹንና ተንኮለኞቹን ሊኾን አይችልም፡፡ በዚያውም ላይ ከቅዱሳት መጻሕፍት ምክር ልንወጣ አይፈቀድልንም፡፡ ራሱ ጌታችን ‹‹ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ›› አለን እንጂ የተቃዋሚዎቻችን ሰይፍና ጎመድ ልንይዝ አልፈቀደልንም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ወገኖቻችንም ፍሬ ቢሶች እንዳይኾኑ፥ በሚፈለገውም ሥራ ጸንተው እንዲገኙ በጎ ምግባርን ይማሩ፤›› (ቲቶ. ፫፥፲፬) በማለት እንደ ገለጸው ከቤተ ክርስቲያን ወገን የኾናችሁ ዂሉ፣ በውጭ እንዳሉት ወደ ፍሬ ቢስነት ከሚወስድ ማንኛውም መንገድ ልትቆጠቡ ይገባችኋል፡፡

ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከትናንት እስከ ዛሬ

ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተመሠረተ ሕጋዊ ማኅበር እንደመኾኑ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት አመራርና አስፈጻሚ አባላቱን እየወከለ በአጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡ ማኅበሩ ስብከተ ወንልን በማስፋፋት፣ አዳዲስ ምእመናንን በማስጠመቅ፤ ለገዳማትና አብነት ትቤቶች ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ፤ ለአባቶች የስብከተ ወንጌልና ከአስተዳደር ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን በመስጠት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስፋፋት ያከናወናቸው ዐበይት ተግባራቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ከአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ጋር ተካተው ሲቀርቡ መቆየታቸውም የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ለአብነትም በጠረፋማ አካባቢዎች ስብከተ ወንጌልን በማዳረስ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከስድሳ ዘጠኝ ሺሕ ለሚበልጡ አዳዲስ አማንያን የሥላሴ ልጅነትን ማሰጠቱ፤ ለአብነት መምህራን እና ደቀ መዛሙርት ወርኃዊ የገንዘብ እና አስቸኳይ የቀለብ ድጋፍ ማድረጉ፤ የአብነትና ዘመናዊ ት/ቤቶችን፣ የመጠጥ ውኃና ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት ማስገንባቱ፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገኙ ከሁለት መቶ ሺሕ በላይ የሚኾኑ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ትምህርተ ወንጌል ማስተማሩና ዐርባ አምስት ሺሕ ያኽሉን ማስመረቁ፤ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ከሰባት መቶ ዐሥር ሺሕ በላይ ልዩ ልዩ የመዝሙር ቅጂዎችንና የኅትመት ውጤቶችን እንደዚሁም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሐመር መጽሔቶችንና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጦችን ማሠራጨቱ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሪፖርት ተካቶ በ፴፭ኛው አጠቃላይ መንፈሳዊ የሰበካ ጉባኤ ላይ መቅረቡ የሚታወስ ነው (ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት፣ ጥቅምት ወር ፳፻፱ ዓ.ም፤ ገጽ 75)፡፡

ዘመነ ጽጌ  

ከአምስቱ የዘመነ መጸው ክፍሎች መካከልም የመጀመሪያው ክፍል ‹ዘመነ ጽጌ› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ቀን ድረስ ያሉትን ፵ ቀናት ያጠቃልላል፡፡ ‹ጽጌ› ቃሉ ‹ጸገየ አበበ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም አባባ ማለት ነው፡፡ ‹ዘመነ ጽጌ› ደግሞ ‹የአበባ ወቅት፣ የአበባ ጊዜ፣ የአበባ ዘመን› ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት ዕፀዋት በአበባ የሚያጌጡበት፣ ምድር በአበቦች ኅብረ ቀለማት የምታሸበርቅበት፣ ወንዞች ንጹሕ የሚኾኑበት፣ ጥሩ አየር የሚነፍስበት፣ አዕዋፍ በዝማሬ የሚደሰቱበት፣ እኛም የሰው ልጆች ‹‹አሠርጎካ ለምድር በሥነ ጽጌያት፤ አቤቱ ምድርን በአበቦች ውበት አስጌጥሃት›› እያልን የዘመናት አስገኚ እና ባለቤት የኾነውን ልዑል እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት፤ ከዚህም ባሻገር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ጋር ከገሊላ ወደ ግብጽ ምድር መሰደዷን የምናስብበት ወቅት ነው፡፡