መፃጒዕ

ዲያቆን ደረሰ ተሾመ

መጋቢት ፳፤፳፻፲፮ ዓ.ም

አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት መፃጒዕ ይባላል፡፡ ስያሜው በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩ ላይ ከሚገኘው ኃይለ ቃል ያለ ነው፡፡ መፃጒዕ ደዌ የጸናበት በሽተኛ፣ ሕመምተኛ ማለት ነው፡፡ መፃጒዕ ለ፴፰ ዓመት በአልጋው ላይ ሆኖ ምሕረትን ሲጠባበቅ የኖረ ሰው ነው። ስፍራዋም “ቤተ ሳይዳ” ትባላለች።ቤተ ሣህል (የምሕረት ቤት) ማለት ነው፤ መጠመቂያዋም በሰሎሞን ቤተ መቅደስ አጠገብ የምትገኝ ናት፡፡ (ዘሌ.፱፥፪) “ቤተ ሳይዳ” ዘይሁዳና “ቤተ ሳይዳ” ዘገሊላ የሚባሉ እንዳሉ በግልጽ በቅዱሳት መጻሕፍት ተገልጿል። “ወቦ ውስተ ኢየሩሳሌም ምጥማቃት ዘጵሩጳጥቄ ቅልንብትራ ዘውእቱ ቀላየ አባግዕ ብሂል ወይቤልዋ ስማ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወባቲ ኃምስቱ ሕዋራት” …በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት” ብሎ ሲገልጽ ነው፡፡ (ዮሐ.፭፥፪)

ቤተ ሳይዳ ዘኢየሩሳሌም ባለ አምስት በር፣ እርከን (መመላለሻ)፣ አምስት ዓይነት ድውያን ፈውስን ለማግኘት ጥምቀቱን ሲጠባበቁ የሚኖሩባት ናት። ውኃው የቤተ አይሁድ ምሳሌ፣ አምስት መመላለሻ የሕግጋተ ኦሪት እና የአምስቱ መጻሕፍተ ሙሴ ምሳሌ በእነዚያ ተጠብቀው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው። ቀድሞ የገባባት አንዱ እንዲድን፣ እነርሱም አንድነት ቤተ እስራኤል ተሰኝተው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው። አንድም አምስቱ እርከን (መመላለሻ) የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር በዚያ ሊያምኑ ያሉ ተስፈኞችና ያመኑባትም ልጅነትን ያገኙባታልና። አምስቱ ዓይነት ድውያንም የአምስቱ ጾታ ምእመናን ከእነ ፈተናቸው ምሳሌ ነው፡፡ እነርሱም አእሩግ በፍቅረ ነዋይ፣ ወራዙት በዝሙት፣ አንስት በትውዝፍት (በምንዝር ጌጥ)፣ ካህናት በትዕቢት አእምሯችን ረቂቅ መዓረጋችን ምጡቅ እያሉ፣ መነኮሳት በስስት ምግብን በፈለጉት ጊዜ ባያገኙት ይልቁንም በአት እየፈቱ በከንቱ የመፈተናቸው ምሳሌ ሆኖ ይነገራል።

መልአከ እግዚአብሔር ወርዶ ውኃውን ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ የሚነጻባት፣ ነገር ግን በዕለቱ ከአንድ ሕመምተኛ በቀር ለሌላው ፈውስ የማይደገምባት ቦታ ናት። ሐተታው የመጠመቂያ ውኀው የማየ ጥምቀት ምሳሌ ሲሆን ውኃውን ያናውጥ (ይባርክ) የነበረው መልአክ የቀሳውስት (ካህናት) “ለቀድሶተ ማየ ጥምቀት” የመውረዳቸው ምሳሌ ነው፤ ፈውሱም የሚከናወነው በዕለተ ቀዳሚት ሲሆን የሚፈወሰው አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ የሚድነው አንድ ታማሚ ብቻ መሆኑ የአባቶቻቸው ምሕረት አለመቅረቱን ሲያሳይ፣ አለመደገሙ ደግሞ ፍጹም ድኅነት እንዳልነበረ ያሳያል፡፡

ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ የኖረ መፃጉዕን በአልጋው ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦ ያንን በሽተኛ “ትፈቅድኑ ትሕየው? … ባድንህ ፈቃድህ ነውን?” አለው። ማእምረ ኅቡዓት ክርስቶስ፣” አዎን፥ እንዲለው እያወቀ”፤ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ “የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና  የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም” ብሎ የመሰከረለት ጌታችን ፈውስን በመጠባበቅ ከመዳን ውጪ ሌላ ዓላማ ያልነበረውን ይህን ሰው አይቶ ፈቃዱን እያወቀ ግን ፍቀድልኝና ላድንህ አለው። (ዕብ.፬፥፲፪) “ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው?“ እንዲል፤ (መክ.፮፥፲፪) የሚያስፈልገንን ሳንነግረው የሚያውቅ የሚሰጠንም ከእርሱ ከፈጣሪው ውጪ በእውነት ማን አለ?

መፃጉዕ በኋላ የሚክድ ነውና “ሳልፈቅድለት ነው ያዳነኝና አልጋ ያሸከመኝ” እንዳይል፣ በዕለተ ዓርብ የሚከስበትን ሲያሳጣውና ለኋላ ጥፋቱ የገዛ ኅሊናው እንዲቀጣው ፈቃዱን ጠየቀው። “ሰው የሌለኝ ሆኖ እንጂ ያንንማ ማን ይጠላል” በሚል ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ድኅነትን ፈቅዶ ገለጠ። እስከ ውኃው መናወጥ ሳያቆየው “ተንሥእ ንሣእ ዓራተከ ወሑር …፤ ተነሥና አልጋህን አንሥተህ ሂድ” አለው፤ ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ ዘመን የተሸከመች አልጋ ተሸክሟት ሄደ።

ጌታችን መጉዕን ‹‹ተነተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› ያለው፦

  • አንደኛው ቅዱስ ኤስድሮስ እንዳለው አልጋው ጠንካራ የብረት አልጋ ነበረና ጽንዓ ተአምራቱን ለማሳየት ነው፡፡
  • ሁለተኛው ‹‹ታዲያ ቢያድነኝ በከንቱ መች ሆነና የገዛ አልጋዬን ትቼለት የመጣሁ ለመዳኔ ዋጋ የከፈልኩበት አይደለምን?›› እንዳይል “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ብሎታል።

ያለ ተረፈ ደዌ አንሥቶት “ያለህን ይዘህ ሂድ፤ እኔ ከአንተ አንዳች አልሻም” ባሰኘ ቃል ሸኝቶታል። ታዲያ ይህ ምስኪን መፃጒዕ “ሰው የለኝም” ብሎ የደረሰለትን ረሳ፤ ማን እንደሆነ እንኳን አላወቀውም። ወንጌላዊውም “ዘሐይወ ኢያእመረ ዘአሕየዎ …፤የዳነው ያዳነውን አላወቀውም” ይለዋል። ( ዮሐ.፭፥፲፫) ይህን ሁሉ ያደረገው አምላክ ተዘነጋ። ዛሬም ከደዌው፣ ከማጣቱ፣ ከችግሩ፣ ከሥጋ ኑሮ ጉድለቱ እንደ መፃጒዕ አምላኩን ያልረሳ ማነው? ተአምራቱን አይቶ፣ ቃሉን ሰምቶ አምላኩን ያስታወሰስ ማነው? ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠስ ማን ነው?” (ኤር. ፳፫፥፲፰)። እኛም ብንሆን ከአዳም በደል ነጻ ያደረገንን አምላክ ውለታ ዘንግተን የምናፌዝ ሁላችንንም ወደ ልባችን እንድንመለስ ነቢዩ እንዲህ ሲል ይመክረናል “እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ፡፡” (ኢሳ.፳፰፥፳፪ )

መፃጉዕ ያዳነው ማን እንደሆነ ሲጠየቅ እንኳን አላወቀም። ወንጌላዊውም የዳነው ያዳነውን አላወቀውም” ብሎ ገልጾታል። (ዮሐ.፭፥፲፫) በምኩራብ አግኝቶት ያዳነውን እንዳወቀውም ሄዶ ለአይሁድ “ያዳነኝ እርሱ ጌታ ኢየሱስ ነው” ብሎ ነገራቸው፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቤተ መቅደስ ሳለ ያን ያዳነውን ሰው አገኘውና “ዑቅ ኢትአብስ ዳግመ እንከ ከመ ዘየአኪ ኢይርከብከ፤ ከዚህ የከፋ “ስለ ደዌ ሥጋ ፈንታ ደዌ ነፍስ” እንዳያገኝህ ሁለተኛ እንዳትበድል” (ቁ.፲፬) ያለውን ዘንግቶ ደዌ ዘኃጢአትን ጠርቶ ተወዳጃት፤ በዕለተ ዓርብ የጌታውን ጉንጮች የጸፉች እጁም ደርቃ `ሰላ` ቀርታለች።

ዛሬም ቢሆን እንደ መፃጉዕ ሰዎች በኃጢአት ብዛት ልባቸው የደረቀና ያበጠ፣ ሰውነታቸው የሰለለ፣ ዓይነ ሕሊናቸው የታወረ፣ እግረ ልቡናቸው የተሰበረ ብዙዎች ሕሙማን በጠበል ቦታ፣ በገዳማት እና በአድባራት አሁንም አሉ፡፡ ፈውስን ይሻሉ፤ ድኅነትን ይፈልጋሉ፡፡ እንደ መፃጕዕ ቦታቸውን ሳይለቁ እግዚአብሔርን በተስፋ ቢጠብቁት አንድ ቀን ይፈወሳሉ።

ስለዚህ ይህ ሳምንት ጌታችን ድውያንን ስለመፈወሱ የሚነገርበትና እኛም ባለን ዓቅም በነፍስ በሥጋ የተቸገሩትን ሁሉ መርዳትና ማገዝ እንዳለብን የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡ ሕሙማንን መጠየቅ፣ የታሰሩትን መጎብኘትና ማስፈታት፣ የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስ፣ ያዘኑትን ማረጋጋት ከጌታችን የተማርናቸው ክርስቲያናዊ ምግባራት   ናቸው፡፡

በዚህ ዕለት የእግዚአብሔር አምላካችን ፈዋሽነትና አዳኝነት እንዲሁም ታዳጊነትና የወደቁትን የማይረሳ እውነተኛ መድኃኒት መሆኑ የሚዘከርበትና ምስጋና የሚቀርብበት ነው። ቅዱስ ዳዊትም “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፣ ወይመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ፣ አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ፤ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፣ እኔም አቤቱ ማረኝ እልሃለሁ” በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት በዝማሬው አረጋግጧል።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና” ሲል ሲቀኝ፣ (መዝ.፸፪፥፲፪)  ጻድቁ ኢዮብም እንዲሁ “ረዳት (ኃይል) የሌለውን ምንኛ ረዳኸው”  በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት መስክሯል፡፡ (ኢዮ.፳፮፥፪) ስለዚህ ገንዘብ፣ ሥልጣን፣ ወገን፣ ረዳት የለኝም በማለት ተስፋ የቆረጥን ሰዎች እግዚአብሔር ከሰውም፣ ከሥልጣንም፣ ከገንዘብም በላይ ነውና እርሱን ተስፋ አድርገን ሁል  ጊዜ በስሙ መጽናናት እና የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣል እንደሚገባን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ የሚፈልጉህ ሁሉ በአንተ ደስ ይበላቸው፤ሐሤትም ያድርጉ፡፡ ሁል ጊዜ ማዳንህን የሚወዱ ዘወትር እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን ይበሉ” እንዳለው ሁል ጊዜም በአምላካችን እግዚአብሔር ደስተኞች እንሁን። (መዝ.፵፥፲፮)

በኃጢአት ከሚመጣ ደዌ ተጠብቀን በአባታዊ ምሕረቱ የሚጠብቀንን ቸሩ አምላካችንን እያመሰገንን በቤቱ እንድንጸና መፃጒዕን “ተነሣ” እንዳለው እኛንም ከወደቅንበት ኃጢአት በንስሓ እንዲያነሣንና ዳግም ከመበደልም እንዲጠብቀን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት አይለየን፤ አሜን!

በመልእክታቱ የሚነበቡት

(ገላ.፭፥፩ እና ያዕ.፭፥፲፬) ስለ ድውያን መፈወስ የሚያወሱ ናቸው፡፡

 ከሐዋርያት ሥራ የሚነበውም እንዲሁ (ሐዋ.፫፥፩)

የዕለቱ ምስባክ፦ “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፤ ወይመይጥ ሎቱ ኵሉ ምስካቢሁ እምደዌሁ፤ አንሰ እቤ  እግዚኦ ተሣለኒ፤ በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሣ ይለውጥለታል፡፡ እኔስ “አቤቱ ይቅር በለኝ፤ አንተን በድያለሁና ለነፍሴ አስተስርይላት” አልሁ፡፡” ይላል (መዝ.፵፥፫)