‹‹መኑ ውእቱ ገብር ኄር፤ ታማኝ አገልጋይ ማነው?››

በመ/ ምስጢረ ሥላሴ ማናየ

መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስያሜ የዐቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ ወይም ሳምንት ‹ገብር ኄር› ይባላል፡፡ ሰያሜውን የሰጠውም ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ከአምስቱ መጻሕፍቶቹ አንዱ በኾነው ጾመ ድጓ መጽሐፍ ሳምንቱን የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜዎች ከነሥርዓተ ማኅሌቱ አዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህ በስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ከዋዜማው ቅዳሜ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት ገብር ኄርን የሚያወሳ ነው ማለት ስለ ታማኝ አገልጋይ የሚያስረዳ ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ፳፭፥፲፬-፳፭ የተገለጸውና በዕለቱ የሚነበበው ወንጌል የሚነግረንም ይህንኑ ትምህርት ነው፡፡

አንድ ባዕለ ጸጋ ሰው ባሪያዎችን ጠርቶ ለአንዱ አምስት መክሊት ሰጠው፣ ሁለት መክሊት የሰጠውም አለ፣ አንድ መክሊትም የሰጠው አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደሩቅ አገር ሔደ፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት አትርፎ ዐሥር አደረገ፡፡ ሁለት የተቀበለውም አትርፎ አራት አደረገ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን መሬቱን ቆፍሮ በሻሽ ጠቅልሎ የጌታውን መክሊት ቀበራት፡፡ ከብዙ ጊዜ በኋላ ጌታቸው መጥቶ ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ‹‹ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ አምስት አተረፍኩ›› አለው፡፡ ‹‹ገብር ኄር ወምዕመን ዘበውሁድ ምእምነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እሰይመከ ባእ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፤ አንተ ታማኝ ባሪያ! በጥቂቱ ታምነሃልበብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ ሁለት የተቀበለውም ቀርቦ ‹‹ጌታዬ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ ወጥቼ ወርጄ ሌላ ሁለት አትርፌ አራት አድርጌአለሁ፤›› ብሎ መክሊቱን አቀረበ፡፡ ጌታውም፡- ‹‹አንተ ታማኝ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልበብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡

አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ‹‹ጌታዬ፣ አንተ ክፉና ጨካኝ፤ ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበት የምትሰበስብ፤ እንደ ኾንክ ስለ አወቅሁ መሬቱን ቆፍሬ ቀበርኋት እነኋት መክሊትህ›› አለው፡፡ ‹‹አንተ ሰነፍ ባሪያ! መክሊቴን በጊዜ ልትሰጠኝ በተገባህ ነበር፡፡ እኔም ወጥቶ ወርዶ ለሚያተርፍ በሰጠሁት ነበር፤›› አለና ‹‹ኑ፤ የዚህን ሐኬተኛ መክሊት ውሰዱና ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ላለው ይሰጡታል ይጨመርለታል ለሌለው ግን ያለውን ይቀሙታል›፡፡ ንዑ ይህን ሰነፍና ሐኬተኛ ባርያ እጅ እግሩን አሥራችሁ ጽኑ ጨለማ ወደ አለበት ውሰዱት! ጩኸትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨምሩት!›› የሚል ፍርድ ወሰነበት፡፡

ባዕለ ጸጋ የተባለው ጌታ ነው፡፡ መክሊት የተባለው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ ነው፡፡ ያተረፉት በሚገባ በታማኝነት ያገለገሉ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው መክሊቱን የቀበረው ደግሞ በታማኝነት በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ሲገባው ያላገለገለ ነው፡፡ ጌታቸው ሊቆጣጠራቸው መጣ ማለት ጌታችን በዕለተ ምጽአት ለዅሉም በሠራው ምግባር መጠን ዋጋ ለመስጠት እንደሚመጣ ያሳየናል፡፡ ያገለገሉትን ‹‹ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አላቸው ማለት ታማኝ አገልጋዮች መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉና፡፡ ሰነፉ አገልጋይ ወደ ጨለማና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ቦታ መወርወሩም ኀጥአን ወደ ሲኦል መግባታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

ከላይ ያነሳነው የቅዱስ ወንጌል ቃል፡- ‹‹ታማኝ አገልጋይ ማነው?›› ይላል፡፡ ይህ እያንዳንዱ በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረ የሰው ልጅ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ አምላካዊ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ከሰው ልጆች ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀጥለን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካቸው ከተመዘገበላቸው ታማኝ አገልጋዮች መካከል ሦስቱን ጠቅሰን ከእነርሱ ሕይወት እንድንማር የሚያነሣሣ መጠነኛ ትምህርት እናቀርባለን፤

ሙሴ

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ታማኝ አገልጋይ መኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ ‹‹በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ ወይም በሕልም አናግረዋለሁ፡፡ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም እርሱ በቤቴ ዅሉ የታመነ ነው፤›› እንዲል (ዘኍ.፲፪፥፮)፡፡ ይህ የፍጡር ቃል ሳይኾን በፈጣሪው የተሰጠ ምስክርነት ነው፡፡ በውኑ በዘመናችን እንኳን ፈጣሪ ፍጡራን ታማኝነቱን የሚመሰክሩለት አጋልጋይ ይኖር ይኾን? እንጃ! የሙሴን ታማኝ አገልጋይነት በረኃ፣ ስደት፣ መከራ፣ የፈርዖን ግርማ እና ቁጣ አልበገረውም፡፡ ዐርባ ዓመት ስለ ወንድሞቹ በመሰደድ ዐርባ ዓመት ደግሞ የተሰደደላቸው ወንድሞቹን በመምራት፣ ባሕር በመክፈል፣ ጠላት በመግደል፣ መና በማውረድ፣ ደመና በመጋረድ ውኃ ከዓለት አፍልቆ በማጠጣት መከራውን ከወገኖቹ ጋር በመቀበል የቀኑን ኃሩር፣ የሌሊቱን ቁር (ብርድ) ታግሦ በታማኝነት አገልግሏል፡፡ ታማኝነቱም እስከ ሞት ድረስ ነበር፡፡

‹‹ሙሴም ወደ እግዚብሔር ተመልሶወዮ እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፡፡ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አሁን ይህን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ? ከባለሟልነትህ አውጣኝ?›› ተብሎ ተጽፏል (ዘፀ.፴፪፥፴፩)፡፡ ታማኝ አገልጋይ የሚባለው እንደ ሙሴ ‹‹እኔ ልሙት ሌሎች ይዳኑ›› የሚል ሰው ነው፡፡ አሁን የምናየው ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ‹‹ሰዎች ይሙቱ፤ እኔ ልኑር፡፡ ሰዎች ጦም ይደሩ፤ እኔ ልብላ፡፡ ሰዎች ይራቆቱ፤ እኔ ልልበስ፡፡ ሰዎች ይዘኑ፤ እኔ ልደሰት›› ነው፡፡ ይህም ታማኝ አገልጋይ ያለ መኾን መገለጫ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ለሚያገለግላቸው ሰዎች ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ እንጂ የራሱን ጥቅም የሚያስቀድም አይደለም፡፡

ዛሬ በዓለማችን የምንመለከተው ድርጊት ግን ‹‹ጩኸት ለአሞራ መብል ለጅግራ›› የሚባለውን ዓይነት ነው፡፡ በታማኝ አገልጋዮች ድካም የሚሸለሙ፤ ታማኝ አገልጋዮች በሠሩት ሪፖርት የሚያቀርቡ፤ ባልሠሩት ሥራ የሚወደሱ፤ ከጥቅሙ እንጂ ከድካሙ መካፈል የማይሹ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እንቅፋት የሚመታው እግርን ነው፡፡ አክሊል የሚቀዳጀው ግን ራስ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ማለት እንደራስ አክሊል ዘውድ የሚጸፋ ብቻ ሳይኾን እንደ እግር እንቅፋቱን፣ እሾኹን፣ ውጣ ውረዱን፣ መከራውንና ድካሙን የሚቀበል ነው፡፡ በጥቅም ጊዜ ለራሱ በአካፋ የሚዝቅ፤ ሌሎች በጭልፋ የሚቆነጥር አይደለም፡፡ ሙሴ ባሕር የከፈለው፣ መና ያወረደው ደመና የጋረደው ውኃ ያፈለቀው ለራሱ አልነበረም፤ ለሚመራቸው ሕዝብ ነበር እንጂ፡፡ ታማኝ አገልጋይ ያሰኘውም ይኸው ነው፡፡ በዚህ ከብሮበታል፤ ተመስግኖበታልም፡፡

ዳዊት

ነቢዩ ዳዊት ዘመነ መሳፍንት አልፎ ዘመነ ነገሥት ሲተካ እስራኤልን በንጉሥነት እንዲመራ እግዚአብሔር ከበግ ጥበቃ የመረጠው ንጉሥ ነው፡፡ እርሱም በተሰጠው ሥልጣን ሳይታበይ በታማኝነት ሕዝበ እስራኤልን መርቷል፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ መሰከረው ዅሉ ስለ ለዳዊትም መስክሮለታል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር እንደ ልቡ የኾነ ሰው መርጧልናየዘይቱን ቀንድ ሞልተህ በልጆቹ መካከል ለእኔ ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (፩ሳሙ. ፲፫፥፲፫፤ ፲፮፥፪)፡፡

በመዝሙረ ዳዊትም ‹‹ወረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ወቀባዕክዎ ቅብዐ ቅዱስ፤ ባሪያዬ ዳዊትን አገኘሁት የተቀደሰ ዘይትንም ቀባሁት›› ተብሎ ተነግሮለታል (መዝ. ፹፰፥፳)፡፡ ይህንንም አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ሰዓታት ድርሰቱ፡- ‹‹ረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ብእሴ ምእመነ ዘከመ ልብየ፤ አገልጋዬ ዳዊትን እንደ ልቤ የታመነ ሰውን አገኘሁት›› ሲል ተርጕሞታል፡፡ ንጉሥ ዳዊት ከመንገሡ በፊት የተገኘው በታማኝነት ነበር፡፡ ከነገሠ በኋላም ታማኝ ነበር፡፡ አሁን በዚህ ዓለም የምንኖር እኛ ግን በድኅነት ታማኝ እንኾንና ሀብት፣ ሹመት፣ ሥልጣን ሲመጣ ታማኝነትን እናጣለን፤ እንዲያውም ታማኝነትን እንንቀዋለን፡፡ መስረቅ ጀግንነት ይመስለናል፡፡ መዋሸት ሥልጣኔ ይኾንልናል፡፡

ዳዊት ሳይሾም በጎቹን በመጠበቅ ታማኝ ነበር፡፡ በጎቹን የሚነጥቅ ተኩላ አንበሳ ቢመጣ በኋላው ተከትሎ ነብሩን በጡጫ፣ አንበሳውን በእርግጫ ብሎ በጎቹን ያስጥል ነበር፡፡ ‹‹እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር፡፡ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር፡፡ በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፤ ከአፉም አስጥለው ነበር፡፡ በተነሣብኝም ጊዜ ጉሮሮውን አንቄ እመታውና እገድለው ነበር፡፡ ይህም ፍልስጥኤማዊ ከነዚያ እንደ አንዱ ይኾናል፤ እንግዲህ እገድለው ዘንድ፤ ከእስራኤል ተግዳሮትን አስወግድ ዘንድ ዛሬ አልሔድምን? የሕያው አምላክ ጭፍሮችን ይገዳደር ዘንድ ይህ ቆላፍ ምንድን ነው? ከአንበሳና ከድብ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል!›› በማለት እርሱ እንደ ተናገረው (፩ኛሳሙ.፲፯፥፴፬)፡፡

ዛሬም ቢኾን በእስራኤል ዘነፍስ በምእመናን ላይ የሚገዳደሩ ብዙ ፍልስኤማውያን ተሰልፈዋል፡፡ እነዚህን ድል የሚነሣ፤ በጎቹን ምእመናን ከተኩላ፣ ከአንበሳና፣ ከድብ አፍ የሚታደግ ታማኝ አገልጋይ ማነው? ከምእመናን ተግዳሮት የሚያርቅ ፈጣሪዬ ከመከራ ያድነኛል ብሎ የሚታመን የኢ አማንያን ብዛት የማያስፈራው ማን ነው? ከትንሽነቱ እስከ ታላቅነቱ የታመነ አገልጋይ ማነው? ለተሾመበት ሓላፊነት ታማኝ ማነው? አሁንም ዓለማችን ከሥጋውያን ባለ ሥልጣናትም ኾነ ከመንፈሳውያን መሪዎች የምትሻው ታማኝ ሰው ነው፡፡ በሙስና ያልተዘፈቀ፤ ጉቦ አይኑን ያላጨለመበት፤ ለመንጋው አርአያና ምሳሌ የሚኾን ሰው፤ ታማኝ አገልጋይ ማለት እርሱ ነው፡፡ በመሐላ የተቀበለውን የአገልግሎት ሓላፊነት የማይዘነጋ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ መምህር፣ ሐኪም፣ ዳኛ፣ ነጋዴ፣ ተማሪ፣ ወታደር፣ የቤት ሠራተኛ፣ የቢሮ ሠራተኛ ታማኝ መኾን አለበት፡፡

መንጋው በክህደት ሲጠፋ ዝም ብሎ የሚያይ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ መምህር፣ ሰባኪ፣ ታማኝ አይደለም፡፡ ታማሚው እየተሰቃየ የሚዝናና ሐኪም ታማኝ አይደለም፡፡ ፍርድ የሚያጎድል፤ ድሆችን የሚበድል፤ ለደሃ አደጎች የማይፈርድ ዳኛ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡ ቅቤ በሙዝ እና በድንች ቀላቅሎ፣ በርበሬ በሸክላ አፈር ጨምሮ፣ ሌሎችን አጭበርብሮ የሚሸጥ ነጋዴ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡ እየነገደ ያለው በሰው ሕይወት መኾኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ ዅሉም እንደየአቅሙ በተሰጠው የአገልግሎት ዘርፍ ታማኝ መኾን አለበት፡፡

ዮሴፍ

ዮሴፍ ለወንድሞቹ ምግባቸውን ተሸክሞ የእርሱ ስንቅ ቢያልቅ የወንድሞቹን ስንቅ ያልበላ በትንሹ የታመነ ሰው ነበር፡፡ ወንድሞቹ ሸጠውት በቤተ ጲጥፋራ በሚያገለግልበት ጊዜም ታማኝ ነበር፡፡ ታማኝነቱ በጲጥፋራ ቤት ጌታ አድርጎታል፡፡ ‹‹ዮሴፍ ተሸጠአገልጋይም ኾነ፡፡ እግሮቹ በእግር ብረት ሰለሰሉ፡፡ ሰውነቱም ከብረት አመለጠች፡፡ ቃሉ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው፡፡ ንጉሥ ላከ፤ ፈታውም የሕዝብ አለቃ አድርጎ ሾመው፡፡ የቤቱም ጌታ አደረገው፡፡ በገንዘቡ ዅሉ ላይ ገዢ አደረገው፡፡ አለቆቹን እንደ እርሱ ይገሥፅ ዘንድ፤ ሽማግሌዎችን እንደ እርሱ ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ፤›› ተብሎ እንደ ተነገረለት (መዝ.፻፬፥፲፯)፡፡

በዚህ ኹኔታ የነበረው ዮሴፍ የጌታው ሚስት ሲወጣ ባቱን፣ ሲገባ ደረቱን እያየች ዐይኗን ጣለችበት፤ በዝሙት አይን ተመለከተችው፡፡ ‹‹ከእኔ ጋር ተኛ›› እያለችም በየቀኑ አስቸገረችው፡፡ እርሱ ግን ‹‹እምቢ›› አላት፡፡ ለጌታው ሚስትም፡- ‹‹እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ዅሉ ለእኔ በእጄ አስረክቦኛል፡፡ በቤቱ ያለውን ምንም የሚያውቀው የለም፡፡ በዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፡፡ ሚስቱ ስለ ኾንሽ ከአንቺ በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፡፡ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? እንዴትስ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአትን እሠራለሁ?›› በማለት የዝሙት ጥያቄዋን ውድቅ አደረገባት (ዘፍ.፴፱፥፯)፡፡

በዮሴፍ ታማኝነት የጌታው ቤት ተባርኳል፡፡ ሀብቱ በዝቷል፡፡ በታማኝነቱ በቤቱ ያለውን ዅሉ ተረክቦ ነበር፡፡ የቀረበለት ፈተና ግን ከባድ ነበር፤ ኾኖም ግን በታማኝነቱ ለማለፍ ችሏል፡፡ ዮሴፍ በታማኝ አገልጋይነቱ በመጣበት መከራ ቢታሰርም እንኳን ያለ ሹመት አላደረም፤ የእስረኞች አለቃ ነበር፡፡ ከእስር ቤት ሲወጣም ግብጽን በሙሉ መርቷል፡፡ በግብጻውያን ላይ ተሾሟል፤ በጥቂቱ ታምኗልና፡፡ ‹‹በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል›› እንዲል (ማቴ.፳፭፥፳፬)፡፡ዛሬ በእየአንዳንዱ ጓዳ እንደ እሳት የሚያቃጥሉ አገልጋዮች ናቸው ያሉት፡፡ ልጅ በፈላ ውኃ የሚቀቅሉ ናቸው የሚበዙት፡፡ እንኳን በዅሉ ገንዘብ ለመሾም በጥቃቅን ዕቃዎች እንኳን የሚታመን ሰው ጠፍቷል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- ‹‹አቤቱ አድነኝ፤ ደግ ሰው አልቋልና፡፡ ከሰው ልጆችም መተማመን ጎድሏልና፤›› በማለት እንደ ተናገረው በመካከላችን መተማመን የለም (መዝ.፲፩፥፩)፡፡

እናም ከእነዚህ ሦስት ታማኝ አገልጋዮች (ሙሴ፣ ዳዊት እና ዮሴፍ) ሕይወት ዅሉም የሰው ልጅ ታማኝ አገልጋይነት የሚያሰጠውን ክብርና ጸጋ ተመልክቶ በታማኝነት ማገልገል ይገባዋል፡፡ ታማኝ መኾን መጀመሪያ የሚጠቅመው ራስን ነው፤ ከዚያ በኋላ ለአገር፣ ለወገን፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ላመኑትም ላላመኑትም ዅሉ ጠቃሚ ይኾናል፡፡ በመጨረሻም የጽድቅ አክሊልን ይቀዳጃል፤ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳል፡፡ ታማኝነት በሰውም፣ በእግዚአብሔርም ፊት ያስከብራልና፡፡ ጻድቃን፣ ሰማዕታት ቅዱሳን በታማኝነት በማገልገላቸው ፈጣሪአቸውን ደስ አሰኝተው ከብረዋል፡፡

በሓላፊው ገንዘብ ያልታመኑት እነይሁዳ፣ ሐናንያ እና ሰጲራ የደረሰባቸውን ጉዳት አይተናል፡፡ አካን ወልደ ከርሚንም ተመሳሳይ ቅጣት ደርሶበታል (ሐዋ.፭፥፩-፳፭)፡፡ ስለ ኾነም ዅሉም በተሰማራበት የአገልግሎት መስክ ታማኝ አገልጋይ ኾኖ ‹‹አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙ እሾምሀለሁ፤›› የሚለውን የጌታውን የምስጋና ቃል ለመስማት ተዘጋጅቶ መጠበቅ ይገባዋል፡፡ መልካም አገልግሎት አገልግለን፣ በእግዚአብሔር ‹አግብርት ኄራን፤ ታማኝ አገልጋዮች› እንድንባል፤ መንግሥቱንም እንድንወርስ አምላካችን ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

በእንተ ጾም

በዲያቆን ዘአማኑኤል አንተነህ

መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጾም ‹‹ጾመ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም መተው፣ መጠበቅ፣ መከልከል ማለት ነው፡፡ ጾም ከምግብ መከልከል ብቻ ሳይኾን ከክፉ ተግባር ዅሉ መቆጠብ ጭምር ነው፡፡ ሠለስቱ ምዕትም፡- ‹‹ጾምሰ ተከልኦተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ፤ ጾምስ በታወቀው ሰዓት፣ በታወቀው ዕለት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው›› በማለት የጾምን ትርጕም ያስረዳሉ /ፍትሐ ነገሥት፣ አንቀጽ ፲፭/፡፡

ጾም በብሉይ ኪዳንም ኾነ በሐዲስ ኪዳን የታወቀ፣ በነቢያት የነበረ፣ በክርስቶስ የጸና፣ በሐዋርያት የተሰበከ እና የተረጋገጠ መንፈሳዊ ሕግ፤ ፈጣሪን መለመኛ መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡ ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይኾን ልዑል እግዚአብሔር የመሠረተው፣ ከእግዚአብሔር ለሰው ልጅ የተሰጠ የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒችን ኢየሱስ ክርስቶስም እከብር አይል ክቡር፣ እነግሥ አይል ንጉሥ፣ እጸድቅ አይል ጽድቅ የባሕርዩ የኾነ አምላክ ነው፡፡ ለእኛ አርአያ ቤዛ ሊኾነን፣ እናንተም ብትጾሙ ብትጸልዩ አጋንንትን ድል ትነሳላችሁ ሲለን፣ ጾምን ለመባረክ ለመቀደስ፤ በመብል ምክንያት ስተን ስለ ነበር ስለ እኛ ኀጢአት እና በደል ሲል ዐርባ ቀንና ሌሊት ጾሟል፡፡

ጌታችን ሲጾም ዐርባውን መዓልት እና ሌሊት ሙሉ ምንም እኽል ውኃ አልቀመሰም፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴም እንደዚሁ ጽላተ ሕጉን ከእግዚአብሔር ሲቀበል እኽል ውኃ አልቀመሰም ነበር፡፡ ምክንያቱም አምላካችን ‹‹በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ያደርጋል፤ ከእኔ የበለጠም ያደርጋል›› ብሏልና፡፡ አባቶቻችን ጻድቃንም ከዐሥረኛው ማዕረግ (ከዊነ እሳት) ላይ ሲደርሱ በእርሱ መንፈስ (በመንፈስ ቅዱስ) ኃይል ታግዘው ከእኽል ውኃ ተከልክለው ይጾማሉ፡፡ ይህም በሥጋዊ ዓይን ሲመዘን ፈጽሞ የሚከብድ ነው፡፡ ሃይማኖት ከሳይንስና ከአእምሮ በላይ ነውና፡፡ በዚህም  ሃይማኖት የሚቀበሉት እንጅ የሚጠራጠሩት የሚፈላሰፉት እንዳልኾነ እንረዳለን፡፡

የጾም ሥርዓት

መጽሐፍ ‹‹ተሰአሎ ለአቡከ ወይነግረከ፤ አባትህን ጠይቅ፤ ይነግርህማል፤›› /ዘዳ.፴፪፥፯/ እንዳለ ጾም እንዴት እንደሚጾም አባቶችን መጠየቅ እና የአባቶችን ፈለግ መከተል ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ  ኤጲፋንዮስ ‹‹ቤተ ክርስቲያን እናቱ ያልኾነች ሰው እግዚአብሔር አባቱ አይኾነውም›› በማለት እንደ ተናገረው ያለ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን፤ ያለ እግዚአብሔር ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ማወቅ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ዘወትር ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሔዱ ቃለ እግዚአብሔር መማር፣ መጸለይ፣ ሥጋውን ደሙን መቀበል መገስገስ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ለክርስቲያን›› እንዲሉ አበው፡፡ በጾም ወቅት ደግሞ ይህንን ተግባር ይበልጥ ማሳደግ ይገባል፡፡

በጾም ወቅት የሥጋ አለቃ ነፍስ ናት፡፡ ነፍስ ፈላጭ፣ ቆራጭ፣ አዛዥ ናት፡፡ ሰው መልካም ሥራ ከሠራ በነፍስ በሥጋው ይቀደሳል፤ ገነት (መንግሥተ ሰማያትን) ይወርሳል፡፡ ክፉ ከሠራ ደግሞ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ያጣል፤ ወደ ሲኦል (ገሃነመ እሳት) ይወርዳል፡፡ ሰው ኀጢአተኛ ነው ሲባል ፈቃደ ሥጋው ሠልጥኖበታል ማለት ነው፡፡ ጻድቅ  ነው ሲባል  ደግሞ ፈቃደ ሥጋውን አሸንፏል (ለፈቃደ ነፍሱ እንዲገዛ አድርጓል) ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ሲቀደስም፣ ሲረክስም የሚኖረው በፈቃደ ሥጋ እና ፈቃደ ነፍስ መካከል ባለው የአሸናፊነትና ተሸናፊነት ትግል ነው፡፡

ጾም ራስን ዝቅ የማድረግ፣ የጸሎት እና የንስሐ ጊዜ እንደኾነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡ /ዕዝ. ፰፥፳፩፤ ነህ. ፩፥፬፤ ዳን.፱፥፫/፡፡ ስለዚህም ራሳችንን ዝቅ በማድረግ (በትሕትና) መጾም ይገባናል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በምዕራፍ ፶፰ ቍጥር ፭ ላይ ‹‹እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን?›› ይላል፡፡ እንግጫ ማለት ባሕር ውስጥ የሚበቅል ሣር ነው፡፡ በቀዳም ሥዑር ካህናት ‹‹ጌታ ተመረመረ፤ ዲያብሎስ ታሰረ፤›› እያሉ ለደስታ መግለጫ የሚሰጡት እና ራስ ላይ የሚታሰር ለምለም ሣር ነው፡፡ እንግጫ (ግጫ – በአንዳንድ አካባቢዎች) ሲያድግ ራሱን ዝቅ ያደርጋል፤ እያደገ ሲሔድ ራሱን ይደፋል (ዝቅ ያደርጋል)፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ ራሳችሁን እንደ እንግጫ (ግጫ) ዝቅ አድርጉ ማለቱ  በጾም ወቅት ‹‹እንደዚህ ነው የምጾመው፤ እስከዚህ ሰዓት ድረስ ነው የምጾመው›› እያልን ውዳሴ ከንቱን መሻት የለብንም ሲል ነው፡፡ ሰው እያወቀ ሲሔድ ራሱን ይደብቃል እንጅ ራሱን ከፍ ከፍ አያደርግም፡፡ የጾም ወቅት ትሕትናን ገንዘብ የምናደርግበትና ይበልጥ የምናሳድግበት ወቅት ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ፈተናን ችሎ በትዕግሥት የሚያሳልፍ፣ እየሰማ የሚተው መኾን አለበት፡፡ ነቢዩ ዕዝራም በመጽሐፈ ዕዝራ ፰፥፳፩ ላይ ‹‹በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛ እና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ›› በማለት ራስን ዝቅ በማድረግ ለአምላክ ፈቃድ መገዛት እንደሚገባ ያስተምረናል፡፡

የጾም ሰዓት

ስለ ጾም ሲነገር የጾም ሰዓትም አብሮ ይነሣል፡፡ በዘፈቀደ ሳይኾን በሰዓት የተወሰነ ጾም መጾም እንደሚገባን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡ ‹‹የእስራኤልም ልጆች ዅሉ ሕዝቡም ዅሉ ወጥተው ወደ ቤቴል መጡ፤ አለቀሱም፡፡ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፡፡ በዚያም ቀን እስከ ማታ ድረስ ጾሙ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /መሳ.፳፥፳፮/፡፡ የጾም ሰዓትም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ተዘረዝሯል፡፡ ሠለስቱ ምዕት ‹‹ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ›› እንደዚሁም ‹‹በጾም ምክንያት ጠብ ክርክር ቢኾን መጾም ይገባል፤ ከመብላት መጾም ይሻላልና፤›› በማለት ከተወሰነው ሰዓት በላይ አብልጦ መጾም እንደሚቻልና ከመብል ይልቅ ለጾም ማድላት እንደሚገባ ነግረውናል /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቍጥር ፭፻፹፬/፡፡

ሰው ይረባኛል ይጠቅመኛል ብሎ አብዝቶ ከመጾሙ የተነሣ መላእክትን፣ አባ እንጦንስና አባ መቃርስን እንደሚመስል ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ አምላካችን ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል›› የሚል ቃል ኪዳን የሰጣቸው አባቶቻችን መምህራን የምንጾማቸውን አጽዋማት እና የምንጾምበትን የሰዓት ጊዜ ወስነውልናል፡፡ በቅዱሳን አባቶቻችን ላይ አድሮ ሥርዓቱን የሠራልን ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ምክንያቱም ካለ እርሱ ፈቃድ እጽፍ፣ እተረጕም ቢሉ አይቻልምና፡፡ ጌታችን በወንጌሉ ‹‹ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ዅሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፤ ትእዛዜን የሚያከብር እንጅ፤›› እንዳለ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተመርተው አባቶች  የደነገጉትን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ማክበር እና መጠበቅ አለብን፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በየጥቂቱ ማደግ ይገባል›› እንዳለው ዅሉንም ነገር በአቅም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጾምን ስንጾምም አቅምን ማወቅም ተገቢ ነው፡፡ ብዙ ለመጾም ስንወስን ጽናታችንና ልምዳችንን ግምት ውስጥ በማስገባት መኾን ይኖርበታል፡፡ ካለበለዚያ ጥብዓት ጎድሎን፣ ትዕግሥት አንሶን እግዚአብሔርን ልናማርር እንችላለን፡፡ ጾመን የማናውቅ ሰዎች በስሜት ተነሣሥተን በአንድ ጊዜ ቀኑን ሙሉ መጾም አለብን ማለት የለብንም፡፡ ክርስትና የስሜት ጉዞ አይደለምና፡፡ እስከ ሰባት ሰዓት ጹሞ የማያውቅ ክርስቲያን እስከ ዐሥራ ሦስት ሊጾም አይችልም፡፡ በስሜት የሚደረግ ማንኛውም ነገር ፍጻሜ አይኖረውምና ስንጾም አቅማችንን ማወቅ ተገቢ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ከንስሐ አባት ጋር መመካከር ይጠቅማል፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹እጅግም ድሀ አታድርገኝ፤ እጅግም ሀብት አትስጠኝ›› ይላል፡፡ እኛም ስንጾምም ስንለምንም በአቅማችን መኾን አለበት፡፡ ስለጾምና የሰዓት ገደብ ሲነገር ማስተዋል የሚገባን ቁም ነገር ከእኽል ውኃ ከመከልከል አኳያ ጾም በቍጥርና በጊዜ የተወሰነ ይኹን እንጂ ከክፉ ተግባር ከመራቅ አንጻር ክርስቲያን እስኪሞት ድረስ ጾመኛ ነው፡፡ ምንጊዜም ቢኾን ከክፉ ነገር፣ ከኀጢአት ዅሉ መጾም (መከልከል) ይጠበቅበታልና፡፡ ዅላችንም ይህን ክርስቲያናዊ ሓላፊነት መዘንጋት የለብንም፡፡ ከዚህ ላይ ግን አንድ ሰው በመጾሙ ብቻ አምላክን ያስደስተዋል ማለት አይደለም፡፡ መጾም ያለበትም ለሥራው ኀጢአት ማካካሻ አይደለም፡፡ የኀጢአት ስርየት የሚገኘው ንስሐ በመግባት እንጅ በመጾም ብቻ አይደለምና፡፡ ሌሎችንም የትሩፋት ምግባራት መሥራት ስንችል ነው ኀጢአታችን የሚሰርይልን፡፡ ስለዚህ ራሳችንን ዝቅ በማድረግ፣ ንስሐ በመግባት፣ በመጸለይ፣ በመመጽወት ከጾምን ኀጢአታችን ይሰረይልናል ማለት ነው ‹‹በጾም ወበጸሎት ይሰረይ ኵሉ ኃጢአት፤ በጾም በጸሎት ኀጢአት ዅሉ ይደመሰሳል፤›› እንዲሉ ሊቃውንት፡፡

ጾም እና ፈተና

‹‹ቤተ ክርስቲያን እየሔድኹ፣ እየጾምኹ፣ እየጸለይኹ፣ እፈተናለሁ፤ ለምንድን ነው?›› የምንል ብዙዎች ነን፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስሔድ ፈተና እየበዛብኝ ነው በማለት ከቤቱ የምንርቅም ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ብዙ ጊዜ ከመልካም ነገር በስተጀርባ ፈተና አለ፡፡ ከጌታችን የምንማረው ሕይወትም ይኸን ነው፡፡ የማይሾሙት ንጉሥ፣ የማያበድሩት ባለጠጋ፣ ዅሉን የፈጠረ፣ ዅሉን የሚገዛ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል ጾመ፤ ተራበ፤ በሰይጣን ተፈተነ፡፡ በእኛ ላይም ብዙ ፈተና ቢመጣብን ለምን ያስደንቃል? ቅዱስ ዳዊት ‹‹ነፍሴን በጾም አስመረርኋት፤ ለስድብም ኾነብኝ›› ይላል /መዝ.፷፱፥፲/፡፡ በክርስትና ሕይወቱ የሚበረታ ሰው ይሰደዳል፤ ይሸነገላል፤ ፈተና ይበዛበታል፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ለሚያሳድዱህ ጹምላቸው›› በማለት ቅዱሳን ሐዋርያት እንዳዘዙን ለሚያሳድዱን መጾም መጸለይ ይኖርብናል /ዲድስቅልያ ፩፥፭/፡፡ ክርስትና ሲገፉ መግፋት አይደለምና፡፡ በረከታቸው ይደርብንና ብፁዕ አቡነ በርናባስ ‹‹ከቤተ ክርስቲያንን የተጠጋ እንኳን ሰው ዛፉ ይለመልማል›› ይሉ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አባታችን፣ ቤተ ክርስቲያን እናታችን ብሎ የሚኖር ሰው ፈተና በየጊዜው ቢገጥመውም መጨረሻው ያማረ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ተከትሎ የወደቀ የለምና፡፡

የጾም ጥቅም

በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተገለጸው ጾም የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት፤

  • የሥጋን ምኞት ያጠፋል፤
  • የነፍስ ቍስልን ያደርቃል፤
  • ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ያስገዛል /ፍት.ነገ.፲፭፥፭፻፷፬/፤
  • መላእክትን መስሎ ለመኖር ያስችላል፤
  • ልዩ ልዩ መከራን ያቃልላል፤
  • አጋንንትን ያስወጣል /ኢያ.፯፥፮-፱/፤
  • ሰማያዊ ክብር እና ጸጋን ያስገኛል /ኛነገ.፲፱፥፰/፤
  • በመንግሥተ ሰማያት ለመኖር የሚያስችል ምግባርን ያሠራል /ሉቃ.፮፥፳፩/፤
  • ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ እና ምሕረትን ለማግኘት ይረዳል፤
  • አጋንንትና ጠላትን ድል ለማድረግ ያግዛል /ማቴ.፬፥፲፩፤ መጽሐፈ አስቴር ምዕ.፯/፤
  • ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመፈጸም ይረዳል /፩ኛነገ.፲፱፥፩/፤
  • ከእግዚአብሔር ቍጣ ለመዳን ያስችላል /ዮናስ ፫፥፩/፤
  • የተደበቀ ምሥጢርን ይገልጣል /ዳን.፲፥፲፬/፤
  • ጸጥታን እና ርጋታን ያስተምራል፤
  • ከቅዱሳን በረከት ያሳትፋል፤
  • ሕይወትን ያድሳል፤
  • መንፈሳዊ ኃይልን ያሰጣል /፩ኛሳሙ.፯፥፭/፤ጥበብን ይገልጣል /ዕዝራ ፯፥፮፤ ዳን.፱፥፪/፤
  • ክህደት ጥርጥርን በማጥፋት እምነትን ለማጠንከር ይረዳል፤
  • ዕድሜን ያረዝማል፤
  • ትዕግሥትን ያስተምራል፤
  • በመላእክት ጠባቂነት ለመኖር ያስችላል /ዘፀ.፲፬፥፲፱. ሐዋ.፲፥፫/፡፡

ጾም ከሚያስገኘው መንሳዊ ጸጋና በረከት ባሻገር በርካታ ሥጋውያን ጥቅሞችም እንዳሉት በጾም ዙሪያ የተደረጉ ልዩ ልዩ ሳይንሳዊ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በጥናቶቹ መሠረትም ጾም፡-

  • የደምና የስኳር መጠንን ይቆጣጠራል፤
  • የአንጎል እንቅስቃሴ የተቀላጠፈ እንዲኾን ያደርጋል፤
  • የስብ ክምችትን ይቀንሳል፤
  • የምግብ መፍጨት ስርዓታችንን ያስተካክላል፤
  • የካንሰር ሕዋሳት ዕድገትን ይከላከላል፤
  • የጠራ የሰውነት ቆዳ እንዲኖረን ያደርጋል፤
  • በሽታ የመከላከል አቅምን ይጨምራል፡፡

በአጠቃላይ ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ አይደለም፤ የመሠረተውም ራሱ ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ አምላካችን አዳምና ሔዋንን ‹‹ዕፀ በለስን አትብሉ›› ብሎ ባዘዛቸው ጊዜ የጾም ሕግን ሠርቶልናል፡፡ በዚህም ጾም የመጀመሪያ ትእዛዝ ናት እንላለን፡፡ አዳም በመብል ምክንያት ሕገ እግዚአብሔርን በመጣሱ ነው ከክብሩ የወረደው፡፡ እኛም ብንጾም እንጠቀማለን፤ ባንጾም ደግሞ በረከትን እናጣለን፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ሥጋዬ ቅቤ በማጣት ከሳ፤›› /መዝ.፻፱፥፳፬/፤ ነቢዩ ዳንኤልም ‹‹ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፤ ሥጋ እና ጠጅም በአፌ አልገባም፤›› /ዳን.፲፥፫/ ሲሉ እንደ ተናገሩት፣ በጾም ወቅት ከጥሉላት ምግቦች መከልከል አለብን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም፤›› ሲል ማስተማሩም ከመብል ተከልክለን መጾማችን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት መንገድ መኾኑን ያመላክታል /ሮሜ.፲፬፥፯፤ ፩ኛቆሮ.፰፥፰/፡፡ አበው ‹‹ጾም ገድፎ የወፈረ በዓል ሽሮ የከበረ የለም›› እንደሚሉት በጾም ወቅት በልተን ከምናገኘው ጥቅም ይልቅ ጾመን ከእግዚአብሔር ዘንድ የምንቀበለው በረከት ይበልጣል፡፡

ጾም ቍስለ ነፍስን የምትፈውስ፣ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፣ የበጎ ምግባራት ዅሉ መጀመሪያ፣ ጸጋ እግዚአብሔርን የምታሰጥ፣ ለጽሙዳን ክብራቸው፣ ለደናግል የንጽሕና ጌጣቸው፣ የጸሎት እናት፣ የዕንባ መገኛ ምንጭ፣ አርምሞን የምታስተምር፣ ለበጎ ሥራ ዅሉ የምታነቃቃ፣ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትሕትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት /ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፬ ምዕራፍ ፮/፡፡ እንደዚሁም ጾም ዕድሜን ያረዝማል፡፡ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ ረጅም ዕድሜ የኖሩ አባቶቻችን ሕይወትም ለዚህ ማስረጃ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ቄርሎስ ዘአንኮራይት ፻፰፤ ቅዱስ እንጦንስ ፻፭፤ ቅዱስ መቃርስ ዘእስክንድርያ ፻ ዓመት በምድር ላይ ቆይተዋል፡፡ ምእመናንም ጾምን ስንጾም አምላካችን ዕድሜአችንን ለንስሐ ያረዝምልናል፡፡ በጾም ወቅት መጸለይ፣ መመጽወት፣ መስገድ በጾም የምናገኘውን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ‹‹ስለ ኀጢአቱ እንደሚጾም፣ እንደሚጸልይ ሰው ኹኑ›› እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡

አንድ ክርስቲያን ጾም አልጾምም የማለት ሃይማኖታዊ ሥልጣን የለውም፡፡ ምክንያቱም ጾም ለዅሉም ክርስቲያን ሕግ ኾኖ የተሰጠ የአምላክ ትእዛዝ ነውና፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢዩኤል ‹‹ጾምን ቀድሱ፤ ጉባኤውንም አውጁ፤›› በማለት መጾም፣ መጸለይ ክርስቲያናዊ ግዴታ መኾኑን ነግሮናል /ኢዩ.፪፥፲፭/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም›› ሲል ምክንያት እየፈጠርን ከመንፈሳዊ ሕይወትና ከአገልግሎት ወደ ኋላ ማለት እንደሌለብን አስተምሮናል /፪ኛቆሮ.፮፥፫/፡፡ ብፁዕ አቡነ ሺኖዳ ‹‹በዐቢይ ጾም ሕይወቱን ያልቀየረ ክርስቲያን በሌሎች አጽዋማት ይቀይራል ለማለት ይከብዳል›› ይላሉ፡፡ እንደሚታወቀው በዐቢይ ጾም ከበሮ እና ጸናጽል ዅሉ ይጾማሉ፡፡ ይኸውም የጾሙን ትልቅነት ያረጋግጥልናል፡፡ የዜማ መሣሪያዎች ዐቢይ ጾምን ከጾሙ ለባዊነት ያለን የሰው ልጆችስ (ክርስቲያኖች) ለጾሙ ምን ያህል ዋጋ እንሰጥ ይኾን? ዅላችንም ጾሙን በደስታና በፍቅር ጾመን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እናገኝ ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተራዳዒነት አይለየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የዐቢይ ጾም ሳምንታት

በመምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

መጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፱ .

ዘወረደ

ትርጕሙ ‹ከሰማየ ሰማያት የወረደ› ማለት ነው፡፡ ከሰማየ ሰማያት የወረደውን፣ ከድንግል ማርያም የተወለደውን በጥንት ስሙ ወልድ፣ ቃል በኋላ ስሙ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አማኑኤል የተባለውን ሰው የኾነውን አምላክ ለማመስገን ርደቱን (ከሰማየ ሰማያት መውረዱን) ለመዘከር የሚጾም ጾም ነው፡፡ ጌታችን ጾመ ከማለት አስቀድሞ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም መወለዱን መናገር አስፈላጊ ነውና የመጀመሪያው ሳምንት ‹ዘወረደ› ተብሏል፡፡ ‹‹አንተ በሰማይ ወአንተ በምድር ወአንተ በባሕር ወአንተ በየብስ፤ አንተ በሰማይ አለህ፤ በምድር በባሕርም በየብስም አለህ፤›› የተባለውን በሰማይ በምድር ምሉዕ የኾነውን አምላክ ‹ወረደ፤ መጣ› ብሎ መናገር ‹ሰው ኾነ› ማለት ነው፡፡ ሰው ኾኖ መገለጡን ለማስረዳት ነው እንጂ መውረድ መውጣት የሚባሉ ቃላት በዅሉ ምሉዕ ለኾነው መለኮት አይስማሙትም፡፡ ቃላቱ ሰውኛ አነጋገርን የሚያመለክቱ ናቸውና፡፡ መተርጕማን አበው ‹‹‹ዘወረደ› ማለት ‹ሰው የኾነ› ማለት ነው›› ብለው ይተረጕማሉ፡፡ አምላካችን ሰው ከኾነ በኋላ ‹መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ› የሚሉ ቃላት ይስማሙታል፡፡ ምልዓቱን ሳይለቅ በሰው አካል ተወስኖ ታይቷልና፡፡ ስለዚህ ‹ወረደ› እግዚአብሔር ሰው ኾኖ መገለጡን፤ ‹ዐረገ› ደግሞ የሰውነቱን ሥራ መፈጸሙን ያሳያል፡፡ ዐረገ ስንልም ቀድሞ በሰማይ የለም ለማለት አይደለም፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ በዓለሙ ዅሉ ምሉዕ ነውና፡፡

ጾሙን ሐዋርያት፣ ስያሜውንና የምስጋናውን ሥርዓት ቅዱስ ያሬድ አዘጋጅተዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ነቢያትን በንባብ፤ ሐዋርያትን በስብከት፤ ሊቃውንትን በትርጓሜ፤ መላእክትን በዜማ ይመስላቸዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ የመላእክትን የምስጋና ሥርዓት ወደ ምድር አምጥቷል፡፡ የነቢያትን ትንቢት፣ የሐዋርያትን ትምህርት በሚገባ ተርጒሞ፣ አብራርቶ፣ አመሥጥሮ አዘጋጅቶታል፡፡ ሐዋርያት ጾሙን ጾመው የጾም ሕግ ደንግገዋል፤ ቅዱስ ያሬድም ለጾሙ ስያሜ ሰጥቶ ምስጋና ከነሥርዓቱ አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡ቤተ ክርስቲያናችንም የመጀመሪያው የዐቢይ ጾም ሳምንትን (ዘወረደን) ስያሜ እንደ ቅዱስ ያሬድ ከሐዋርያት ተቀብላ ታስተምራለች፡፡ ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ‹ጾመ ሕርቃል› እየተባለም ይጠራል፡፡ ሕርቃል (ኤራቅሊዮስ) በ፮፻፲፬ ዓ.ም የነበረ የቤዛንታይን ንጉሥ ነው፡፡ ለክርስቲያኖች ባደረገው ርዳታ ምክንያት አንድ ሳምንት ጾመውለት ነበር፡፡ ያላወቁ ‹ጾመ ሕርቃል› ብለው አንድ ጊዜ ጾመው ትተውታል፡፡ ጥንቱን የቅዱሳን ሐዋርያት መኾኑን ያወቁ ምእመናን ግን ዅልጊዜ በየዓመቱ ይጾሙት ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ጾመ ሕርቃል እየተባለ ይጠራል፡፡ ሙሉ ታሪኩ በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ አንቀጽ ፲፭ ላይ ይገኛል፡፡

ቅድስት

‹ቅድስት› ማለት ‹የተለየች፣ የነጻች፣ የከበረች› ማለት ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን ጾም የጀመረባት፣ ልዩ፤ የተቀደሰች፤ የከበረች፤ ልዩ፣ ንጹሕ፣ ክቡር በሚኾን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጾመች መኾኗን ያመላክታል፡፡ ይህች ጾም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አራት የተገለጠችው የጌታችን ጾም ስትኾን፣ ስያሜዋና የዕለቷ የምስጋና ሥርዓትም የቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ አምላካችን በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት በጾመበት ጊዜያት እነዚህ ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል አድርጓል፡፡ ሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ የሚባሉትም፡- ትዕቢት፣ ስስትና ፍቅረ ንዋይ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሦስት ኃጢአቶች ጌታችን በዲያሎስ በተፈተነ ጊዜ በትዕቢት ቢመጣበት በትሕትና፤ በስስት ቢመጣበት በትዕግሥት፤ በፍቅረ ንዋይ ቢመጣባት በጸሊዓ ንዋይ ጌታችን ዲያሎስን ድል አድርጎታል፡፡ ለእኛም እነዚህን ድል ለማድረግ የምንችልበትን ጥበብ – ጾምን ገልጦልናል፡፡ ትዕቢት ያልተሰጠንን መሻት፣ ስስት አልጠግብ ባይነት ስግብግብ መኾን፣ ፍቅረ ንዋይ ለገንዘብ ሲሉ ፈጣሪን መካድ ነው፡፡ አንደ ክርስቲያን ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል ካደረገ ሌሎችን ኃጣውእ በቀላሉ ድል ማድረግ ይቻለዋል፡፡

ምኵራብ

ሦስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹ምኵራብ› ይባላል፡፡ ምኵራብ አምልኮተ እግዚአብሔር ሲፈጸምበት፣ ሕገ ኦሪት ሲነበብበት የነበረ በአይሁድ የሚሠራ መካነ ጸሎት ነው፡፡ ዘወትር ቅዳሜ ብዙ ሕዝብ ይሰበሰብበት ስለ ነበር ጌታችን ለማስተማር ብዙ ጊዜ በምኵራብ ተገኝቶአል፡፡ ስያሜው የተወሰደው በዮሐንስ ፪፥፲፬ ‹‹ወረከበ በምኵራብ እለ ይሠይጡ አልህምተ ወአባግዐ ወአርጋበ …፤ በመቅደስም በሬዎችን፣ ላሞችን፣ በጎችን፣ ርግቦችን፣ የሚሸጡትን አገኘ …›› ተብሎ ከተገለጸው ኃይለ ቃል ላይ ሲኾን፣ ‹ምኵራብ› የሚለው ቃልም በአማርኛ ‹መቅደስ› ተብሎ ተተርጕሟል፡፡ ምኵራብ የሚባለው ሳምንት ጌታችን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማሩ የሚነገርበት፤ ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፤ እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት›› ብሎ በምኵራብ ይሸጡ፣ ይለውጡ የነበሩትን የገሠፀበት፤ ቤተ መቅደስን የከብት መንጃ የወርቅና የብር መነገጃ ያደረጉ ሰዎችን ከነሸቀጣቸው ከቤተ መቅደስ ያስወጣበት፤ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ የስሙ መጠሪያ፣ የጸሎት ሥፍራ መኾኗን ያስረዳበትና ያወጀበት፤ በቤተ መቅደስ የንግድ ሥራ ማከናወን እንደማይገባ ያረጋገጠበት ዕለት ነው፡፡

መጻጒዕ

አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹መጻጒዕ› ይባላል፡፡ ስያሜው በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩ ላይ ከሚገኘው ኃይለ ቃል የተወሰደ ነው፡፡ በዚህ የወንጌል ክፍል ጌታችን በቤተ ሳይዳ ሕሙማንን እንደ ፈወሰ ተነግሮአል፡፡ ብዙ ሕሙማን ፈውስ ሽተው አንዲት የመጠመቂያ ሥፍራን ከበው ይኖሩ ነበር፡፡ በዚያች ሥፍራ ቀድሞ የወረደ እና የተጠመቀ አንድ በሽተኛ ብቻ ይፈወስ ነበር፡፡ ጌታችን በዚህ ሥፍራ ተገኝቶ በሽተኞችን ጐብኝቷል፡፡ በዚያም ልዩ ልዩ ደዌ ያለባቸው አምስት ዓይነት ሕሙማን እንደ ነበሩ ተገልጧል፤ እነዚህም፡- ሰውነታቸው የደረቀ፣ የሰለለና ያበጠ፤ እንደዚሁም ዕውራን እና ሐንካሳን ነበሩ፡፡ ከዚህ አምስት የተለያየ ዓይነት በሽታ ከተያዙ ሰዎች መካከል ደዌው የጸናበት፣ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በደዌ ዳኛ፣ ባልጋ ቍራኛ ተይዞ የኖረው፤ ከደዌው ጽናት የተነሣ ‹መጻጒዕ› ተብሎ የተጠራው በሽተኛ አንዱ ነበር፡፡ መጻጒዕ ስም አይደለም፡፡ ደዌ የጸናበት በሽተኛ ሕመምተኛ ማለት ነው እንጂ፡፡ ሰውየው ከበሽታው ጽናት የተነሣ ስሙ ጠፍቶ በበሽታው ሲጠራ የነበረ ነው፡፡ አምላካችን ይህን ሰው ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› ብሎ ሠላሳ ስምንት ዘመን የተኛበትን አልጋ ተሸክሞ ወደ ቤቱ እንዲገባ ማድረጉ የሚነገርበት ወቅት በመኾኑ ሳምንቱ ‹መጻጒዕ› ተብሎ በተፈወሰው በሽተኛ ስም ተሰይሟል፡፡ (ሙሉ ታሪኩን በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩-፲፯ ይመልከቱ)፡፡ ዛሬም ቢኾን በሰዎች ላይ ልዩ ልዩ ደዌያት አሉ፤ የሥጋውን ደዌ ሐኪሞች ያውቁታል፡፡ ከዚህ የከፉ የነፍስ ደዌያት እጅግ ብዙዎች ናቸው፡፡ በኃጢአት ብዛት ልባቸው የደረቀና ያበጠ፤ ሰውነታቸው የሰለለ፤ ዓይነ ሕሊናቸው የታወረ፤ እግረ ልቡናቸው የተሰበረ ብዙዎች ሕሙማን አሁንም አሉ፡፡ ፈውስን ይሻሉ፤ ድኅነትን ይፈልጋሉ፡፡ እንደ መጻጕዕ ቦታቸውን ሳይለቁ እግዚአብሔርን በተስፋ ቢጠብቁት አንድ ቀን ይፈወሳሉ፡፡

ደብረ ዘይት

አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹ደብረ ዘይት› ይባላል፡፡ ስያሜው የተወሰደውም ከማቴዎስ ወንጌል ፳፬፥፫ ካለው ትምህርት ነው፡፡ ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኝ በወይራ ዛፎች የተሸፈነ ትልቅ ተራራ ነው፡፡ ጌታችን ምሥጢራትን በተለያየ ቦታ ገልጧል፡፡ ምሥጢረ ጸሎትን በጌቴሴማኒ፤ ምሥጢረ መንግሥቱን በደብረ ታቦር፤ ምሥጢረ ቊርባንን በቤተ አልዓዛር፤ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን በቤተ ኢያኢሮስ፤ ምሥጢረ ምጽአቱን ደግሞ በደብረ ዘይት ገልጧል፡፡ ደብረ ዘይት ጌታችን ዳግም ለፍርድ መምጣቱንና ምሥጢረ ምጽአቱን ለደቀ መዛሙርቱ በሚገባ የገለጠበት ዕለት ነው፡፡ ደብረ ዘይትን ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ለማደሪያነት ተጠቅሞበታል፡፡ ቀን ቀን በምኲራብ ያስተምራል፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በደብረ ዘይት ያድራል፡፡ ይህንም ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይመሰክራል፤ ‹‹ዕለት ዕለት በመቅደስ ያስተምር ነበር፡፡ ሌሊት ግን ደብረ ዘይት ወደምትባል ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር፡፡ ሕዝቡ ዅሉ ይሰሙት ዘንድ ማልደው በመቅደስ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር›› (ሉቃ. ፳፩፥፴፯)፡፡ በዚህ ለማደሪያነት ባገለገለው ተራራ ምሥጢረ ምጽአቱን ስለ ገለጠበት አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ደብረ ዘይት የሚል ስያሜ ተሰጥተታል፡፡ ደብረ ዘይት ጾሙ እኩል የሚኾንበት፤ አምላካችን በግርማ መንግሥቱ ለፍርድ በመጣ ጊዜ መልካም ለሠሩ ክብርን፣ ክፉ ለሠሩ ቅጣቱን የሚያስተላልፍ መኾኑ የሚነገርበት፤ ስለ ዓለም መጨረሻ እና ስለሚመጣው ሕይወት የምንማርበት የክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ዕለት ነው፡፡

ገብር ኄር

ስድስተኛው ሳምንት ‹ገብር ኄር› የሚል ስያሜ አለው፡፡ ‹ገብር ኄር› ማለት ‹በጎ፣ ታማኝ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ ስያሜው ከማቴዎስ ወንጌል ፳፭፥፲፬ የተወሰደ ሲኾን፣ ታሪኩም እግዚአብሔር በሰጠው ጸጋ በታማኝነት ማገልገል የሚያስገኘውን ዋጋ ያስረዳል፡፡ አንድ ሰው አገልጋዮቹን ጠርቶ ወጥተው፣ ወርደው፣ ነግደው እንዲያተርፉ ለአንዱ አምስት፤ ለአንዱ ሁለት፤ ለአንዱ ደግሞ አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው በተሰጠው መክሊት ነግዶ፣ ሌላ አምስት መክሊት አትርፎ፣ ዐሥር አድርጎ፣ ‹‹ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ወጥቼ ወርጄ አምስት አትርፌአለሁ›› ብሎ ለጌታው አቀረበ፡፡ ጌታውም ‹‹አንተ ጎበዝ እና ታማኝ ባሪያ! በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ፣ ወርዶ፣ አትርፎ አራት አድርጎ አቀረበ፡፡ እርሱንም ጌታው ‹‹አንተ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ አንድ የተቀበለው ሰው ግን መክሊቱን ወስዶ ቀበራት፡፡ ጌታው በተቈጣጠረው ጊዜም የቀበራትን መክሊት አምጥቶ ‹‹አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ እንደ ኾንኽ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ፈራሁና የሰጠኸኝን መክሊት ቀበርኳት፤ እነሆ መክሊትህ!›› ብሎ ምንም ሳያተርፍ መክሊቱን ለጌታው መልሶ አስረከበ፡፡ ጌታውም ‹‹አንተ ክፉና ሐኬተኛ ባሪያ! ወርቄን በጊዜው አታስረክበኝም ነበር? ነግዶ ለሚያተርፍ እሰጠው ነበር፡፡ ይህን ክፉና ሐኬተኛ ባሪያ እጅ እግሩን አስራችሁ ጨለማና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ሥፍራ ውሰዱት! መክሊቱን ቀሙና ለባለ ዐሥሩ ጨምሩለት!›› ብሎ አዘዘ፡፡

በዚህ ታሪክ እንደምናየው በተሰጠው መክሊት ያተረፈ ሰው (ክርስቲያን) ዋጋ አለው፡፡ በፈጣሪው ዘንድ መልካም፣ በጎ፣ ታማኝ ባሪያ ተብሎ ይሸለማል፡፡ ባያተርፍ ደግሞ ሐኬተኛ ባሪያ (አገልጋይ) ይባላል፤ ቅጣቱንም ይቀበላል፡፡ እንግዲህ እኛም ታማኝ አገልጋይ መኾን ይጠበቅብናል፡፡ ሳምንቱ ይህ መልእክት የሚተላለፍበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ዘመን በመክሊታቸው የሚያተርፉ እንዳሉ ዅሉ፣ መክሊታቸውን (ጸጋቸውን) ዝገት እስከሚያጠፋው ድረስ የሚቀብሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ መክሊትን (ጸጋን) መቅበር ዋጋ የማያሰጥ መኾኑን ተገንዝበን በቻልነው መጠን ለማትረፍ መትጋት እና ታማኝ አገልጋይ መኾን እንደሚገባን ከገብር ኄር ታሪክ እንማራለን፡፡

ኒቆዲሞስ

ሰባተኛው ሳምንት ‹ኒቆዲሞስ› የሚል ስያሜ ያለው ሲኾን፣ የስያሜው መነሻም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፫ የተመዘገበው ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ አለቃ ታሪክ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ በሦስት መንገድ የአይሁድ አለቃ ነበር፤ በሥልጣን፣ በዕውቀትና በሀብት፡፡ ሰው ሥልጣን ቢኖረው ሀብትና ዕውቀት ላይኖረው ይችላል፡፡ ዕውቀት ቢኖረው ደግሞ ሀብትና ሥልጣን ላይኖረው ይችላል፡፡ ሀብት ቢኖረውም ዕውቀትና ሥልጣን ላይኖረው ይችላል፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ሦስቱንም አንድ ላይ አስተባብሮ የያዘ የአይሁድ አለቃ ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ወንጌልን ለመማር ከአይሁድ ዅሉ ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ይሔድ ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ፈሪሳውያን ማመን ባልቻሉበት በዚያን ዘመን ጆሮውን ለቃለ እግዚአብሔር፤ ልቡን ለእምነት የከፈተ ሰው ነው፡፡ ብዙ ሰዎችን እናውቃለን ማለት ከመልካም ነገር ሲከለክላቸው ኒቆዲሞስ ግን ዐዋቂ ሳለ ራሱን ዝቅ አድርጎ፣ እምነት በማጣት የነጠፈችውን የፈሪሳውያንን ኅብረት ጥሎ፣ ሐዋርያትን መስሎ ጌታውን አግኝቶታል፡፡ ጌታችን ዓለምን ለማዳን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በለየባት በዚያች አስጨናቂ ሰዓት፤ ሐዋርያት በተበተኑባት አይሁድ በሠለጠኑባት በዕለተ ዓርብ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን በድርብ በፍታ ገንዞ የቀበረ፣ እሱን ያገኘ ያገኘኛል ሳይል በድፍረት ከእግረ መስቀሉ የተገኘ ሰው ነው – ኒቆዲሞስ፡፡ ስለዚህም ሰባተኛው ሳምንት በእርሱ ስም ተሰይሟል፡፡

ሆሣዕና

‹ሆሣዕና› ስምንተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ሲኾን፣ የሰሙነ ሕማማት መጀመሪያ ነው፡፡ ሆሣዕና ስያሜው በማቴዎስ ወንጌል ፳፩፥፱ ከሚገኘው ትምህርት የተወሰደ ሲኾን ትርጕሙም ‹መድኀኒት ወይም ‹አሁን አድን› ማለት ነው፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› የሚሉ የአዕሩግ፣ የሕፃናት ምስጋና እየቀረበለት ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ጉዞ ያደረገበት፤ ትሕትናውን የገለጠበት፤ ይህን ዓለም ከማዕሠረ ኃጢአት መፍታቱን በምሳሌ ያስረዳበት ዕለት ነው፡፡ ‹‹ተጽዕኖ›› ተብሎ ከሚጠራው የዐቢይ ጾም መጨረሻ (ዕለተ ዓርብ) እና ከሰሙነ ሕማማት መግቢያ ጀምሮ ያለው ሳምንት ሆሣዕና ይባላል፡፡ የክርስቶስን ነገረ ሕማሙን፣ ስቅለቱን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን ሆሣዕና ተብሎ ዓለምን ማዳኑን የሚናገሩ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚነበቡበት፤ አምላካችን ለሰው ልጅ መዳን መከራ መቀበሉና የማዳን ሥራው በሰፊው የሚታወጅት፤ በሰሙነ ሕማማት ለሚያርፉ ምእመናን ጸሎተ ፍትሐት የሚደረግበት፤ ወንጌል በአራቱ ማዕዘን የሚሰበክበት ሳምንት ነው – ሆሣዕና፡፡ ከዚያው አያይዞም ሰሙነ ሕማማት ይቀጥላል፤ ወቅቱም የክርስቶስን ነገረ ሕማሙንና ዓለምን ያዳነበት ጥበቡን የምንሰማበት ሳምንት ነው፡፡ በሞቱ ሞታችንን አጥፍቶ መንግሥቱን እንድንወርስ የፈቀደልን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይኹን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

‹‹ጾመ እግዚእነ አርአያሁ ከመ የሀበነ፤ አርአያነቱን ይሰጠን ዘንድ ጌታችን ጾመ፤›› (ቅዱስ ያሬድ)፡፡

በመምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

መጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጾም በብሉይ ኪዳንም በሐዲስ ኪዳንም በፈጣሪ መኖር ለሚያምኑ፣ የፈጣሪያቸውን ስም ጠርተው ለሚማጸኑ ዅሉ የተሰጠ አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ለሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር መገናኛነት ያገለገሉ፣ በነቢያት የተጾሙ አጽዋማት እንዳሉ መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ‹‹ሙሴም ወደ ተራራው ወጣ ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ቆየ፤›› (ዘጸ. ፳፬፥፲፰) ተብሎ እንደ ተጻፈው ሙሴ በተራራው የቆየው እየጾመ ነበር፡፡ ነቢያት በጾም ከፈጣሪያቸው ጋር ተገናኝተውበታል፡፡ ምንም እንኳን ድኅነተ ነፍስን ማግኘት ባይችሉም በመጾማቸው አባር፣ ቸነፈርን ከሕዝቡ አርቀዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን ያሉ አጽዋማት በሙሉ በፍጡራን የተጾሙ ናቸው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ጾም ግን የተጀመረው በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን አጽዋማት ረድኤተ እግዚአብሔር የሚገኝባቸው፣ ለሐዲስ ኪዳን አጽዋማት መነሻና ምሳሌዎች ናቸው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ከላይ በርእሱ በተጠቀሰው ኃይለ ቃል እንደ ገለጸው የጌታችን ጾም የሐዲስ ኪዳን አጽዋማት መጀመሪያ ነው፡፡ ይህ ጾም የአጽዋማት ዅሉ በኵር ነው፡፡ በኃጢአት ብዛትና በመርገም በጠወለገ ሰውነት የተጾሙ አጽዋማትን ጌታችን አድሷቸዋል፤ ቀድሷቸዋልም፡፡ ውኃ ከላይ ደጋውን፣ ከታች ቆላውን እንዲያለመልም፣ የጌታችንም ጾም ከላይ ከመጀመሪያ የነበረ የአበውን ጾም ቀድሷል፤ ጉድለቱንም ሞልቷል፡፡ ጌታችን ጾሞ ከእርሱ በኋላ የተነሡ ሐዋርያትን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ደናግልን፣ መነኮሳትን በአጭሩ የምእመናን ጾም ቀድሷል፡፡ በአጠቃላይ የጌታችን ጾም እንደ በር ነው፡፡ በር ሲከፈት ከውጭ ያለውን እና ከውስጥ ያለውን ያገናኛል፡፡ የጌታችን ጾምም ከፊት የነበሩትን የነቢያትን አጽዋማት ኋላ ከተነሡ ከሐዋርያት አጽዋማት ጋር ያገናኘ፤ በመርገም ውስጥ የነበሩትንና ከመርገም የተዋጁትን ያስተባበረ ጾም ነው፡፡

‹‹ጌታችን የጾመው ለምን ነው?›› የሚለውን ትልቅ ጥያቄ ‹‹አርአያነቱን ይሰጠን ዘንድ ጾመ›› በማለት ቅዱስ ያሬድ መልሶልናል፡፡ ጌታችን የጾመው እንደ ፍጡራን ክብር ለመቀበል ኃጢአት ኖሮበት ስርየት ለማግኘት አይደለም፡፡ አርአያነቱን አይተን፣ ፍለጋውን ተከትለን ልንጠቀምበት ጾምን ቀድሶ ሰጠን፡፡ ጾም ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት ጋሻ፣ ከኃጢአት የምንሰወርበት ዋሻ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ፣ መኾኑን አርአያ ኾኖ ሊያሳየን ጌታችን ጾመ፡፡ የጾምንም ጥቅም በግብር (በተግባር) አስተማረን፤ አስረዳን፡፡ ይህ የጌታችን ጾም – ‹ዐቢይ (ታላቅ) ጾም፣ ሁዳዴ፣ ዐርባ ጾም፣ የጌታ ጾም› እየተባለ ይጠራል፡፡ ዐቢይ ጾም ማለት ከግሱ እንደምንረዳው እጅግ ትልቅ ጾም ማለት ነው፡፡ በእርግጥ የጾም ትንሽ የለውም፤ አንድም ቀን ይሁን ሳምንት ጾም ትልቅ ነው፡፡ የጌታችን ጾም የታላቆች ታላቅ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ዅሉ ጌታ፣ የፍጥረታት ዅሉ ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጾመው ነው፤ ስምንት ሳምንታን፣ ኀምሳ አምስት ቀናትን በውስጡ የያዘ፣ በቊጥርም ከአጽዋማት ዅሉ እጅግ ከፍ ያለና የሐዲስ ኪዳን አጽዋማት ዅሉ በኵር ስለ ኾነ ዐቢይ (ታላቅ) ጾም ይባላል፡፡

ሁዳድ (የመንግሥት እርሻ)፡- በአንድ መንግሥት የሚተዳደሩ ሕዝቦች በሙሉ በግዳጅ ወጥተው የሚያርሱበት፣ የሚዘሩበት፣ የሚያጭዱበት መሬት እንደ ኾነ ዅሉ ይህም ጾም የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የመንግሥቱን የምስራች በምትነግር ወንጌል ያመኑ ምእመናን በአዋጅ በአንድነት የሚጾሙት ጾም በመሆኑ ‹ሁዳድ› ተብሎ ይጠራል፡፡ ‹ዐርባ ጾም› የተባለበት ምክንያትም ጌታችን የጾመው ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ስለ ኾነ ነው፡፡ ‹‹ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ጾመ›› እንዲል (ማቴ. ፬፥፪)፡፡ ጾሙ ስምንት ሳምንታትን ኀምሳ አምስት ቀናትን ያካተተ ነው ብለናል፡፡ ጌታችን የጾመው ዐርባ ቀን ነው፡፡ ለምን ኀምሳ አምስት ቀናት እንጾማለን? የሚሉ ጥያቄዎች በውስጣችን ሊመላለሱ ይችላሉ፡፡

ጌታችን በጾመው ዐርባ ቀን ላይ ቅዱሳን ሐዋርያት ከመጀመሪያው አንድ ሳምንት ከመጨረሻው አንድ ሳምንት ጨምረውበታል፡፡ በዚህ ምክንያት ጾሙ ከስድስት ወደ ስምንት ሳምንታት፣ ከዐርባ ወደ ኀምሳ አምስት ቀናት ከፍ ሊል ችሏል፡፡ ለምን ብለን ጥያቄ ማንሣት የለብንም፡፡ ምክንያቱን ቀኑን የጨመሩት ከጌታችን ጋር የዋሉ በቃልም፣ በተግባርም ከጌታችን የተማሩት፣ የምሥጢር ደቀ መዛሙርት፣ የሕግ ምንጮች፣ እኛ ወደ ክርስቶስ የምናደርገው ጉዞ መሪዎች ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸውና፡፡ እኛ የክርስትና ተቀባዮች እንጂ ጀማሪዎች ወይም መሥራቾች አይደለንም፡፡ በቅዱሳን ሐዋርያት መሠረትነት ላይ ተመሠረትን እንጂ፡፡ ‹‹እናንተስ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ተመሥርታችኋል›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (ኤፌ. ፪፥፳)፡፡ እናም ሕጋቸውንና ሥርዓታቸውን አምነን ከመቀበል ውጭ መቃወም አይቻለንም፡፡ የብሎኬት ድርድር መሠረት አያስፈልገኝም ሊል አይችልም፡፡ መሠረቱ ከተናደ ድርድሩ የት ሊቆም ይችላል? እኛም የሐዋርያትን ትእዛዝ ካልተቀበልን የማንን ትእዛዝ እንቀበላለን?

ቅዱሳን ሐዋርያት ከመጀመሪያው የጨመሩት የጌታችን ጾም መግቢያ መቀበያ ንጉሥ ሲመጣ በሠራዊት እንዲታጀብ፣ በብዙ ሕዝብ እንዲከበብ፣ ሕዝቡ ከፊት ከኋላ ከበውና አጅበው በክብር እንደሚቀበሉትና እንደሚሸኙት ዅሉ የንጉሣችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጾም ሲመጣም እንደ ሕዝብ፣ እንደ ሠራዊት የሚያጅቡ፣ የሚከቡ፣ የሚያከብሩ ሳምንታትንና ዕለታትን ማለትም ከመጀመሪያው ዘወረደን፤ ከመጨረሻው ደግሞ ሕማማትን ጨምረዋል፡፡ ደግሞም መልካም ምግባርንም ኾነ የጾምን ቀን መቀነስ እንጂ መጨመር አያስቀጣም፡፡ በክርስትና ሕይወት የተቀበሉትን መክሊት መቅበር እንጂ አትርፎ ማቅረብ ያስከብራል፤ ገብር ኄር (ታማኝ አገልጋይ) ያሰኛል፤ ያሾማል፤ ያሸልማል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል ሦስት

በልደት አስፋው

መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

፭. ደብረ ዘይት

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ስለዅሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን! ባለፈው ዝግጅታችን አራተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት የተመለከተ ትምህርት አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለ አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት (ስለ ደብረ ዘይት) አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን በተግባር ላይ እንድታውሉት እሺ? መልካም ልጆች! አሁን በቀጥታ ወደ ትምህርቱ እንወስዳችኋለን፤

ልጆች! እንደምታስታውሱት አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ደብረ ዘይት›› ይባላል፡፡ ትርጕሙም ‹‹የወይራ ተክል የሚገኝበት ተራራ›› ማለት ነው፡፡ ይህ ትልቅ ተራራ (ደብረ ዘይት) ከኢየሩሳሌም ከተማ በስተምሥራቅ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ ደብረ ዘይት ተራራ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዕለተ ምጽአትን ምልክት ለደቀ መዛሙርቱ (ለሐዋርያት) የገለጸበትና ያስተማረበት ቦታ ነው፡፡ ጌታችን በዚህ በደብረ ዘይት ተራራ ተቀመጦ ‹‹ማንም እንዳያስታችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፡፡ እስከ መጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል …›› እያለ ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯቸዋል፡፡

እነርሱም ስለ ዕለተ ምጽአት ምልክትና የመምጫው ጊዜ መቼ እንደሚኾን ጌታችንን ጠይቀውታል፡፡ እርሱም ቀኑን ከእርሱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም እንደማያውቀውና ክርስቲያኖች ከኀጢአት ርቀው በዝግጅት መጠባበቅ እንደሚገባቸው አስረድቷቸዋል፡፡ ልጆች! ዓለም የምታልፍበት ቀን ሲደርስ (በዕለተ ምጽአት) ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመላእከት ዝማሬ፣ በመለከት ድምፅ ታጅቦ በኃይልና በግርማ ከሰማይ ወደ ምድር ይመጣል፡፡

አምላካችን በመጣ ጊዜም በተዋሕዶ ሃይማኖትና በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንቶ የተገኘ ክርስቲያን በገነት (መንግሥተ ሰማያት) ለዘለዓለሙ በደስታ ይኖራል፡፡ ያለ ክርስቲያናዊ ምግባር ማለትም በኀጢአት ሥራ የኖረ ሰው ደግሞ ለዘለዓለሙ መከራና ስቃይ ወዳለበት ወደ ሲኦል (ገሃነመ እሳት) ይጣላል፡፡ ስለዚህ አምላካችን ለፍርድ ሲመጣ ለእያንዳንዳችን እንደ ሥራችን ኹኔታ ዋጋ ይሰጠናል ማለት ነው፡፡ የጽድቅ ሥራ ስንሠራ ከኖርን ወደ መንግሥተ ሰማያት (የጻድቃን መኖሪያ) እንገባለን፤ ኀጢአት ስንሠራ ከኖርን ግን ወደ ገሃነመ እሳት (የኀጢአተኞች መኖሪያ) እንጣላለን፡፡

ልጆች! እናንተም በዕለተ ምጽአት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንድትገቡ በምድር ስትኖሩ ከክፉ ሥራ ማለትም ከስድብ፣ ከቍጣ፣ ከተንኮል፣ ከትዕቢት እና ከመሳሰለው ኀጢአት ርቃችሁ በእውነት፣ በትሕትና፣ ሰውን በማክበር፣ በፍቅር እና በመሳሰለው የጽድቅ ሥራ ጸንታችሁ ለወላጆቻችሁ እየታዘዛችሁ ኑሩ፡፡ ይህንን ለማድረግ እንድትችሉ ደግሞ ከዘመናዊው ትምህርታችሁ ጎን ለጎን ከወላጆቻችሁ ጋር እየተመካከራችሁ (አስፈቅዳችሁ) መንፈሳዊ ትምህርት መማር፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መንፈሳውያን ፊልሞችን መመልከትና መዝሙራትን ማዳመጥ፣ እንደዚሁም በየጊዜው መቍረብ አለባችሁ እሺ?

በጣም ጥሩ ልጆች! ለዛሬው ከዚህ ላይ ይቆየን፡፡ በሚቀጥለው ዝግጅት ስለሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ትምህርት ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከኹላችን ጋር ይኹን!

የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው? – ክፍል ሁለት

በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ

መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

 ፬.  የሰው ልጅ እና የክህነት ክብርን፣ እንደዚሁም መንፈሳዊ ባህልን ማቃለል

ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ በታች በተጠቀሰው ትምህርቱ በመጨረሻው ዘመን የሚነሡ ሰዎችን ጠባይ ይነግረናል፡፡

 ‹‹ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ፡፡ ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይኾናሉና፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የኾነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይኾናሉ፡፡ የአምልኮት መልክ አላቸው፤ ኃይሉን ግን ክደዋል፡፡እነዚህ ደግሞ ራቅ፡፡ ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን፣ በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን፣ ዅልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደተቃወሙት እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸውስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ኾነው እውነትን ይቃወማሉ፡፡ ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ኾነ፤ ሞኝነታቸው ለዅሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም፤›› /፪ኛጢሞ. ፫፥፩-፯/፡፡

ይህንን ትምህርት ለማገናዘብ እግዚአብሔርን የማያምነውን ሕዝብ ትተን፣ በመላው ዓለም ዅሉ ካሉ የክርስትና ሃይማኖት አማኞች ተግባር አንጻር ጥቂት ነጥቦችን እንደሚከተለው እንመልት፤

ሀ. መንፈሳዊ ባህልን ማፍረስ

ዅሉም ባይኾኑ አንዳንድ አማኞች ‹‹… ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይኾናሉ፡፡ የአምልኮት መልክ አላቸውኃይሉን ግን ክደዋል …›› የሚያሰኝ ሕይወት የያዙ እንደ ኾኑ ቅዱስ ጳውሎስ አስረግጦ ነግሮናል፡፡ እንደ አማኝ በቤተ ክርስቲያን የሚገኙ፣ ነገር ግን መንፈሳዊ አምልኮ የማይፈጽሙና የራሳቸውን አሳብ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሊጭኑ የሚፈልጉትን ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የአምልኮት መልክ አላቸው፤ ኃይሉን ግን ክደዋል›› ያላቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት መታዘዝ፣ መከባበርና ሰላም የነገሠበት ነው፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ቦታ እንደሚስተዋለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመንፈሳዊው ባህል የጠነከሩ ብዙዎች እንዳሉ ዅሉ አንዳንድ ሥራ ፈቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፖለቲካ፣ ዘረኝነት፣ አሉባልታ፣ ወዘተ. የመሳሰሉ እኩያን ተግባራትን በማስፋፋት ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩአት ይስተዋላል፡፡

እነዚህም አይሁድ ቀንተው በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረጉትን ክፉ ሥራ ሲገልጥ፡- ‹‹አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም፣ ከግሪክ ሰዎች ብዙ፣ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ።  አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ፡፡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፤›› በማለት ቅዱስ ሉቃስ እንደ ተናገረላቸው ሰዎች ያሉ ናቸው /ሐዋ. ፲፯፥፭/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ከላይ እንደ ጠቀስነው ‹‹ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ዅልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና›› ይላቸዋል፡፡

ለ. የክህነትን ክብር ማቃለል

ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹… ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ኾነው እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፣ ሞኝነታቸው ለዅሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም …›› እንዳለው ዅሉ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት በአንብሮተ እድ የሰጣቸው፤ በትውፊት ከእኛ ላይ የደረሰው፤ የድኅነት መፈጸሚያ የኾነው ሥልጣነ ክህነት ዛሬ ካህናት ነን ከሚሉት ጀምሮ እስከ ምእመናን ድረስ እንደ ኢያኔስና ኢያንበሬስ ባሉ ሰዎች ዘንድ እየተናቀ፣ እየተቃለለ ነው፡፡ ከክህነት ጋር በተያያዘ በቤተ ክርስቲያን ከሚፈጸሙ ስሕተቶች መካከል ጥቂቶቹን ቀጥለን እንጠቅሳለን፤

በቅዱስ ወንጌል፡- ‹‹ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፤›› እንደዚሁም፡- ‹‹በዚያን ዘመን ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስበርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፡፡ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ፤›› ተብሎ እንደ ተነገረው /ማቴ. ፳፬፥፲/፤ ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት እንዲሁ ለዘመናት በአንድነት የኖረችውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በድፍረት የሚከፋፍሉ፤ አሳድጋ፣ አስተምራ፣ ክህነት የሰጠቻቸውን እናታቸውን እስከ ማውገዝ ድረስ የደረሱና በድፍረት ኀጢአት የሚበድሉ አገልጋዮች የሚገኙበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ‹‹ዅ ለንጹሖች ንጹሕ ነው፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የኾነ ምንም የለም፡፡ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሕሊናቸውም ረክሶአል፡፡ እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፡፡ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ፣ ለበጎ ሥራም ዅሉ የማይበቁ ስለ በሥራቸው ይክዱታል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ/ቲቶ. ፩፥፲፭/፡፡

ሠለስቱ ምእት በኒቂያ ጉባኤ ‹‹ያለ ኢጲስ ቆጶስ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተ ከክህነቱ ይሻር›› ብለው ደንግገዋል፡፡ ነገር ግን በተለይ በውጭ አገር እየተለመደ የመጣው ጉዳይ የትኛውንም ኤጲስቆጶስ ሳያስፈቅድ አንድ ካህን፣ ከዚያም አልፎ ዲያቆን ወይም ምእመን እንደ ማንኛውም ድርጅት ቤተ ክርስቲያን ከፈትኩ፤ ቦርድ አቋቋምኩ እያለ በድፍረት ምእመናንን ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ በሚደርግበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ለተቋቋሙ ‹አብያተ ክርስቲያናት› የሚገለገሉበት ሜሮን፣ ታቦት ከየት ተገኘ? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የላቸውም፡፡ ‹‹ብዙዎች ይስታሉ›› እንደ ተባለው በድፈረትና በስሕተት መሠረት ላይ የስሕተትና የድፍረትን ግድግዳ ማቆም፤ የስሕተትና የድፍረት ጣሪያንም ማዋቀር እንደ ሕጋዊ ሥራ ከተቈጠረ ሰነባበተ፡፡

‹‹የጥፋት ርኵሰት በተቀደሰው ሥፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ማቴ. ፳፬፥፲፭/፣ በየአጥቢያው የሚሰማውን ክፉ ወሬ ስናስተውል የዚህን ትንቢት ተፈጻሚነት እንረዳለን፡፡ የተሐድሶ ሤራ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጠረው ጭቅጭቅ፣ ሐሜት፣ ሙሰኝነት፣ ዘረኝነት፣ ወዘተ. ምን ይነግሩናል? በአንዳንድ የውጭ አገር ክፍሎችም አብያተ ክርስቲያናት በሰበካ ጉባኤ ሳይኾን ለካህናት ክብር በማይጨነቁ የቦርድ አመራሮች መተዳደር ጀምረዋል፡፡ ይህ አሠራር ለዘመናት ቤተ ክርስቲያን ከኖረችበት አገልግሎት አንጻር ስናየው እጅግ የራቀና የከፋ ነው፡፡ ጌታችን ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተው በሥልጣነ ክህነት እንድትተዳደር ሲኾን ይህኛው አሠራር ግን በተቃራኒ የቆመ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ምእመኑን አስተምራ፣ አጥምቃ፣ አሳድጋ እንደገና በተንኮለኞች ሤራ ልጆቹዋን ቀስጠው በእርሷ ላይ እንዲያምጹ ማድረግ የጥፋት ርኵሰት መኾኑን ስንቱ ተረድቶት ይኾን?፡፡ በመወጋገዙ ሒደት ያለው ጉዳትንስ ማን አስተዋለው? እግዚአብሔር ይማረን እንጂ እንደ ሰውኛው ከኾነ መጨረሻው ከባድ ነው፡፡

ከዚህ ዅሉ በደል ለመራቅም ቅዱስ ጳውሎስ፡- ‹‹ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር፣ ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በኾነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢኾን፣ በትዕቢት ተነፍቶአል፤ አንዳችም አያውቅም፡፡ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፡፡ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር፣ ስድብም፣ ክፉ አሳብም፣ እርስበርስ መናደድም ይወጣሉ፡፡ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው፣ እውነትንም በተቀሙ፣ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚኾን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ፤›› ሲል ያስተማረንን ትምህርት በተግባር ላይ ማዋል ይጠቅመናል /፩ኛጢሞ. ፮፥፫-፭/፡፡ በእርግጥ ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን ቢቃወሙትም ሙሴ ሥልጣኑ ከእግዚአብሔር የተሰጠው በመኾኑ የእግዚአብሔር ክብር በእርሱ ላይ፤ ቍጣው ደግሞ በበደለኞቹ ኢያኔስና አንበሬስ ላይ እንደ ተገለጠ ዅሉ፣ ዘለዓለማዊዋ ቤተ ክርስቲያናችንም ክህነታዊ ክብርዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ክቡር ነውና በአገልጋዮቿ መከፋፈል አትበተንም፤ አትፈርስም፡፡

ሐ. የሰው ልጅ ክብርንና የዕድሜ ደረጃን አለመጠበቅ

ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ፡- ‹‹ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይኾናሉና፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የኾነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ …›› በማለት የዘረዘረው የሰው ልጅ የዕድሜ፣ የቅደም ተከተል ትሥሥርና ክብር እንዲጠፋ ለሚሠሩ ሰዎች ተስማሚና በቂ ማስረጃ ነው /፩ኛጢሞ. ፫፥፩-፫/፡፡

በአጠቃላይ የምጽአት ምልክቶች ከመንፈሳዊው እስከ ዓለማዊው፣ ከምሁሩ እስካልተማረው፣ ከትልቁ እስከ ትንሹ ድረስ ያገባውም ያላገባውም፤ ካህኑም መነኵሴው ሳይቀር ብዙዎቹ በአንድነት ከቅድስና ርቀው ከጥፋት ርኵሰት፣ ከመከራ ሕይወት፣ ተቋደሽ መኾናቸውን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ቅዱስ ዳዊት፡- ‹‹ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ይመጣል።  አምላካችን ይመጣል፤ ዝምም አይልም፡፡ እሳት በፊቱ ይቃጠላል፤ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ፤›› ሲል እንደ ተናገረው /መዝ.፵፱፥፪-፫/፤ ቅዱሳት መጻሕፍትም ተባብረው እንደ መሰከሩት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንገት ይመጣል፤ አይዘገይም፡፡

ከላይ እንደ ተዘረዘረው ከመንፈሳውያን እስከ ዓለማውያን ድረስ ብዙ ሰዎች የተጠመዱበት በዓለማዊ ሥራ ላይ ነው፡፡ ከዚህም በኋላ የበለጠ በሥጋ ሥራ እየተወጠሩ ይሔዳሉ እንጂ ከጥቂቶቹ በስተቀር ወደ መንፈሳዊው የተጋድሎ ሕይወት የሚያዘነብል ሰው (ምእመን) ይኖራል ለማለት ያስቸግራል፡፡ እንዲያውም በዐመፅ እየበረታ በቤተ መቅደሱ ሳይቀር የድፍረት ኀጢአት የሚሠራው እየበዛ ሊመጣ ይችላል፡፡ ከዚህ ዅሉ ኀጢአት ለመራቅና ወደ መንፈሳዊው ተጋድሎ ለመምጣት እግዚአብሔርን ደጅ መጽናት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም ክርስቲያኖች ነን የምንል ዅሉ የጥፋት ትንቢቱ በእኛ ላይ እንዳይፈጸምብን አሁኑኑ ሳናመነታ ንስሐ መግባትና በትንቢት ከተገለጡት ርኵሰቶች ጨክነን መራቅ ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር! ወለወላዲቱ ድንግል! ወለመስቀሉ ክቡር!

የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው? – ክፍል አንድ

በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ

መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዐቢይ ጾም ውስጥ ካሉት ሳምንታት ደብረ ዘይት አምስተኛው ሳምንት ላይ ይውላል፡፡ ደብረ ዘይት ትርጕሙ ‹‹የወይራ ዛፍ፣ ተራራ›› ማለት ሲኾን፣ ይህም በኢየሩሳሌም በሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው?›› /ማቴ.፳፬፥፫/ ብለው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በጠየቁት ጊዜ እርሱም የማይቀረውን የዓለም ፍጻሜና አስቀድመው የሚፈጸሙ ምልክቶችን አስረድቷቸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ በደብረ ዘይት ሳምንት ታስበዋለች፤ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጠቀሱትን የትንቢት ምልክቶች ከተግባራዊ የዓለም ክንዋኔዎች አንጻር በማገናዘብ ለምእመናኑ ታስተምራለች፡፡ በመኾኑም በቤተ ክርስቲያናችን በደብረ ዘይት ሳምንት ምጽአትን የሚመለከቱ ምሥጢራት በሰፊው ይነገራሉ፡፡ በዚህ ዝግጅት በዓለም እየተከሠቱ ያሉ ወቅታዊ ምልክቶችን ከቅዱሳት መጻሕፍት ቃል ጋር በማገናዘብ መጠነኛ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፤

የሰው ልጅ ሲፈጠር ጀምሮ ስለ ራሱ መጨረሻና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምንነት ማወቅን እንደሚሻ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል፡፡ ከእነዚህም በተለይ በደብረ ዘይት ዕለት ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው?›› በማለት የጠየቁት ጥያቄ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ከመለሰላቸው ዋነኛውና ቀዳሚው የምጽአቱ ምልክት የሐሳዊ መሲሕ መምጣት ነው፡፡ ሐሳዊ መሲሕ ማለት በቀጥታ ትርጕሙ ‹‹ሐሰተኛ የኾነበኢየሱስ ክርስቶስ (በአምላክ) ስም የሚመጣ የክርስቶስ ተቃዋሚ›› ማለት ነው፡፡

ትርጕሙን አስፍተን ስንመለከተው ደግሞ ከሃይማኖት ጋር ተያያዥነት ያላቸውም ኾነ የሌላቸው፣ በዓለም ላይ እየተከናወኑ የሚገኙ ጉዳዮችንና የጥፋት መንገዶችን ያጠቃልላል፡፡ የሐሳዊ መሲሕ የጥፋት ሥራዎች በማወቅም ይኹን ባለማወቅ በዓለማውያንና በክፉ መናፍስት ተከታዮች እየተፈለሰፉ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር የተገኙ የሃይማኖት፣ የሥነ ተፈጥሮ፣ የጋብቻና የመሳሰሉ ድንበሮች ማፍለስን ዓላማ ያደረጉ፤ እንደዚሁም ሰብአዊ ክብር፣ መንፈሳዊና አገራዊ ባህል አገራዊ እንዲጠፋ የሚሠሩ አካላት ዅሉ ከሐሳዊ መሲሕ መደብና ከዓለም ፍጻሜ ምልክት አንጻር የሚታዩ ናቸው፡፡ ጉዳዩን ለማብራራት ያህል የሚከተሉት ነጥቦችን እንመልከት፤

፩. የሃይማኖት ድንበርን ማፍለስ

እግዚአብሔር በመጻሕፍቱ ‹‹አባቶችህ ያኖሩትን (የሠሩትን) የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፋልስ›› /ምሳ.፳፪፥፳፰/ በማለት ያዘዘውን ትምህርት መጣስ ማለትም የሃይማኖት ድንበርን ማፍለስ ከሐሳዊ መሲሕ ተግባር ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ አፈጻጸሙም ሰዎች የእግዚአብሔርን ማንነት እንዳያውቁ ከማድረግ ይጀምራል፡፡ ከዚህም አንዱ ሐሳዊ መሲሕ በእግዚአብሔር ስም በተለያየ ኹኔታና መንገድ መገለጥ ነው፡፡ ‹‹‹እኔ ክርስቶስ ነኝ› እያሉ ብዙ ሰዎች በእኔ ስም ይነሣሉ›› /ማቴ. ፳፬፥፭/፡፡

ይህም እንደ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና የቅዱሳን ሐዋርያት ስብከት መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ እንደ ኾነ የማይሰብክ ዅሉ ከሐሳዊ መሲሕ ትምህርት ይመደባል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በመልእክቱ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ዅሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፡፡ ይህም እንደማመጣ ሰምታችኋል፤ አሁንም እንኳ በዓለም አለ፤›› በማለት በእነዚህ ሐሳውያን ላይ ይመሰክርባቸዋል /፩ኛዮሐ. ፬፥፫/፡፡

በመኾኑም ከዚህ በፊት ያለፉ፣ አምላክ ነን ብለው እንደ ተነሡት ቴዎዳስ ዘግብጽና ይሁዳ ዘገሊላ /ሐዋ. ፭፥፴፮-፴፯/፤ ከዚያም በኋላ በየጊዜው እንደ ተነሡ መናፍቃን በዚህ ዘመንም ‹‹ኢየሱስ ነኝ … ኢየሱስ በእኛ ዘንድ አለ …›› እያሉ የዋሁን ሕዝብ የሚያጭበረብሩ ሐሳውያን መሲሖች መጥተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ክርስቶስን ከአብ የሚያሳንሱ (ሎቱ ስብሐት)፣ ነቢይ ነው ብለው የሚያምኑ፣ በመናፍስት አሠራር የሚጠነቁሉ፣ በማቴሪያሊስት (ቁሳዊነት) ወይም በኢቮሉሽን (በዝግመተ ለውጥ) ትምህርት አምነው አምላክ የለም የሚሉ፣ ወዘተ. ዅሉ የሐሳዊው መሲሕ አካላት ናቸው፡፡

አሁንም ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹ልጆች ሆይ! መጨረሻው ሰዓት ነው፤ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፡፡ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ እናውቃለን፤›› ይለናል /፩ኛዮሐ. ፪፥፲፰/፡፡ ከዚህ ቃል የምንረዳው የክርስቶስ ተቃዋሚ መምጣት የምጽአት ጊዜው መቃረብ ምልክት መኾኑን ነው፡፡ በተጨማሪም የምጽአትን መቅረብ ከሚያመለክቱ፣ ከሐሳዊው መሲሕ እና ከእርሱ ጋር ተዛማጅ የኾኑ ወቅታዊ ጉዳዮችን ለመረዳት የሚከተሉትን ትንቢቶች እንመልከት፣

‹‹የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ዅሉ ሊያስገድላቸው፣ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው። ታናናሾችና ታላላቆችም፣ ባለ ጠጋዎችና ድሆችም፣ ጌታዎችና ባሪያዎችም ዅሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፤ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፡፡ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው፤›› /ራእ. ፲፫፥፲፮-፲፰/፡፡

ይህ የቅዱስ ዮሐንስ ራእይ ከሚመሠጠርበት ትርጕም ውስጥ አንዲት ቅንጣት ብቻ ከዘመኑ አንጻር ብናይ ‹‹የሚናገር የአውሬው ምስል›› ማለት ለእርሱ ያልተገዙትን ወይም ቁጥሩን ያልያዙትን የሚናገርባቸው፤ ‹‹ምልክቱን ያልተቀበሉትን ሊገዙና ሊሸጡ እንዳይችሉ ያደርግል›› ማለት መኖር፣ መሥራት፣ መሸጥ፣ መለወጥ ወዘተ የሚያግዳቸው ሲል ነው፡፡ ይህም አሁን ባለው የዚህ ዓለም አኗኗር አንጻር ሲታይ ተመሳሳይ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ መታወቂያ ወረቀት፣ ፓስፖርት፣ ቪዛ፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወዘተ በዓለም አጠቃላይ አሠራር እና ባንድ ሰው የመኖር ማንነት ሚና ላይ ተጽዕኖ የሚያደርጉ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ መታወቂያ ወረቀቶች የሌሉት ሰው ካለበት የትም መንቀሳቀስ አይችልም፡፡

ከዚህም በላይ ጉዳዩን ስናሰፋው በሠለጠኑት ዓለማት አሠራር የእያንዳንዱ ሰው የጣት አሻራ በዘመናዊ (ኮምፒውተራይዝድ) መንገድ የተደራጀ በመኾኑ፣ ከዚህ አደረጃጀት ውስጥ ካልተካተተ በቀር ማንም ሰው በዚያች አገር ሊኖር፣ ሊዘዋወር፣ ሊሠራ፣ ሊነግድ ወዘተ. አይችልም፡፡ በዚህ የኮምፒውተር ድር አደረጃጀት ውስጥ ያለ አንድ ሰው ወደየትኛውም ዓለም ቢንቀሳቀስ በጣቱ አሻራ ይታወቃል፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ በትንቢቱ፡- ‹‹አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፤ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው፤››  የሚለውም ይህን ጉዳይ የሚያደራጀው ሌላ አካል ሳይኾን የሰው ልጅ መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ‹‹ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት›› የሚለው ቍጥር የሰው ልጅ የጅማት ቁጥር ነውና፡፡

ሌላው የምጽአት መቃረብ ምልክት የሐሳዊው መሲሕ ዘመቻን አውቀው በድፍረት፣ ላላወቁት በረቀቀ መንገድ እግዚአብሔርን ያመለኩ አስመስለው የእግዚአብሔርን ስም፣ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ በአጠቃላይ ቅዱሳንን መስደብ ነው፡፡ እነዚህ በልዩ ልዩ ዘመናት ሲፈጸሙ የቆዩ ተግባራት ዛሬም ተጠናክረው በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡ ሩቅ ሳንሔድ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችንን እየተፈታተነ ያለው የተሐድሶአውያን መናፍቃን ትልቁ ሤራ የእግዚአብሔር ወልድን አምላክነት፤ የድንግል ማርያምን ክብርና አማላጅነት፤ የታቦትንና የመስቀልን ክብር፤ የቅዱሳንን ቅድስና እና አማላጅነት መቃወም ነው፡፡ የተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ በሥራው የአውሬው መንፈስ አራማጅና መንገድ ጠራጊ መኾኑን ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዲህ በማለት ያረጋግጥልናል፤

‹‹ለዘንዶውም ሰገዱለት፤ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፡፡ ለአውሬውም ‹አውሬውን ማን ይመስለዋል? እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል?› እያሉ ሰገዱለ፡፡ ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፡፡ በዐርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው፡፡ እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፡፡ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ዅሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ዅሉ ይሰግዱለታል፤›› /ራእ. ፲፫፥፬-፰/፡፡

ሌላኛው በዓለም ላይ የሚታየው በሰዎች ዘንድ ክብርን፣ ዝናንና ታዋቂነትን ለማግኘት ሲባል ራስን ከፍ ማድረግና እንደ አማልክት መቍጠር ከሐሳዊው መሲሕ ጋር ያስመድባል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንደ ገለጸው የሰናዖር ሰዎችን ኀጢአት ስናስተውል የተነሡበት ዋነኛው ነጥብ ‹‹ስማችንን እናስጠራ›› የሚለው ነበር፡፡ ‹‹‹ኑ! ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው› አሉ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ዘፍ. ፲፩፥፬/፡፡ በዚህ እኩይ አሳብ ምክንያት ነው እግዚአብሔር ቋንቋቸውን የደባለቀባቸው፡፡ የሰናዖር ሰዎች ያሰቡትና የተመኙት ትውልዱ እግዚአብሔርን ማድነቅ ትቶ፣ ለዘለዓለም ስማቸውን ሲጠራና ሥራቸውን ሲያደንቅ እንዲኖርላቸው ነበር፡፡ ዛሬም ብዙዎቹ ይህንን የሰናዖርን ኀጢአትና የጥፋት ጉዞ እንደ ዓላማ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

፪. የሥነ ተፈጥሮ ሕግመጣስ

እግዚአብሔር አምላካችን የፈጠረው ፍጥረት ፍጹም በመኾኑ ይህ ቀረህ፤ ይህ ይጨመርልህ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት ሰው ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅም ለማግኘት ሲል ዝርያቸው የተለያየ ፍጥረታትን (እንስሳትና ተክሎችን) ማዳቀልንና ማደበላለቅን ተያይዞታል፡፡ በተቃራኒውም የሰውን ቍጥር ለመቀነስ የማያደርገው ሩጫ የለም፡፡ የሰውን ቍጥር ለመቀነስ በሚደረጉ ሕክምናዎች ምክንያትም ሰዎች ለተለያዩ በሽታዎች ተዳርገዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በዚህ መሰሉ ድጋፍና ማበረታቻ በተለይ በሠለጠኑ የዓለም ክፍሎች ብዙዎቹ የግብረ ሰዶም ፈጻሚና አስፈጻሚ ኾነዋል፡፡

ይህም አምላክ የሠራውን የፍጥረት ሕግ በማጣጣልና በመጣስ ሰው ላሻሽል ወደሚል ያዘነበለ መኾኑንና የሰውን ልጅ ቅጥ ያጣ ድፍረት ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ግን ሥነ ፍጥረቱን እንዲያደባልቁበት አይፈልግም፡፡ ለዚህም ነው ሊቀ ነቢያት ሙሴን፡- ‹‹ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፤›› ሲል ያዘዘው /ዘሌ. ፲፱፥፲፱/፡፡ ግብረ ሰዶምን በተመለከተም ‹‹ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፡፡ ደማቸው በላያቸው ነው፤›› ተብሎ ተጽፏል /ዘሌ. ፳፥፲፫/፡፡

፫.  ጋብቻን ማፍረስ (ማፋታት)

አውሬው (አስማንድዮስ የሚባለው ርኵስ መንፈስ) የጋብቻ ጠላት ኾኖ ነግሦአል፡፡ ስለዚህም ተጋቢዎች ፈተናውን መቋቋም አልቻሉምና በአንድ መኖራቸውን ጠልተው ይለያያሉ (ይፋታሉ)፡፡ አስማንድዮስ (ርኵስ መንፈስ) ከጋቻ ይልቅ ግብረ ሰዶምን እያበረታታ በአንዳንድ አገሮች እንደሚታየው ወንድን ከወንድ፣ ሴትን ከሴት ጋር እያቆራኘ በማምለኪያ ሥፍራዎቻቸው ሳይቀር ጋብቻቸውን እስከ መፈጸም አድርሷቸዋል፡፡ ይህንን ኀጢአት በሚመለከትም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፤

‹‹ስለዚህ እርስበርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፡፡ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን። ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፡፡ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፡፡ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ዓመፃ ዅሉ፣ ግፍ፣ መመኘት፣ ክፋት ሞላባቸው፡፡ ቅናትን፣ ነፍስ መግደልን፣ ክርክርን፣ ተንኰልን፣ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፡፡ የሚያሾከሹኩ፣ ሐሜተኞች፣ አምላክን የሚጠሉ፣ የሚያንገላቱ፣ ትዕቢተኞች፣ ትምክህተኞች፣ ክፋትን የሚፈላለጉ፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያስተውሉ፣ ውል የሚያፈርሱ፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ምሕረት ያጡ ናቸው፡፡ ‹እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል› የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም፤›› /ሮሜ.፩፥፳፬ እስከ ፍጻሜው/፡፡

 ይቆየን

ቅዱስ ፓትርያርኩ አዘንተኞቹን አጽናኑ

6w5a3729

ቅዱስ ፓትርያኩ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ከሌሎችም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ጋር ወደ አዘንተኞቹ ድንኳን ሲገቡ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በአዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ‹‹ቆሼ›› እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ መጋቢት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በድንገተኛ አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ምእመናን ቤተሰቦችን በትናንትናው ዕለት መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በሥፍራው ተገኝተው አጽናኑ፡፡

በደረሰው ድንገተኛ አደጋ ላለፉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተሰማቸውን ኀዘን ቅዱስነታቸው ገልጸው በቃለ እግዚአብሔርና በአባታዊ ምክራቸውም አዘንተኞቹን አጽናንተዋል፡፡

ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በሥፍራው የተገኙት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው፣ ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይና ምሥራቃዊ ዞን አዲግራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም እንደዚሁ ለአዘንተኞቹ የማጽናኛ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

ቆሼ ሠፈር

አደጋው የደረሰበት ቦታና አስከሬን የማውጣቱ ሥራ በከፊል

ቋሚ ሲኖዶሱ ከወሰነው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም በአደጋው ምክንያት በጊዜአዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች የአንድ መቶ ሺሕ ብር ድጋፍ ማድረጉን ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ከሰጡ በኋላ ቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ መንበረ ፓትርያርካቸው ተመልሰዋል፡፡

መጋቢት ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ቋሚ ሲኖዶስ በአደጋው ላለፉ ምእመናን የተሰማውን ኀዘን መግለጹና ቤታቸው በአደጋው በመፍረሱ ምክንያት በጊዜአዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖችም ከቤተ ክርስቲያኒቷ የሁለት መቶ ሺሕ ብር ርዳታ እንዲሰጥ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡

‹‹የአሁኑ እሳት በቍጥጥር ሥር ቢውልም ለወደፊቱ ግን ያሠጋናል … ልጁ ዐረፈ እንጂ ሞተ አይባልም፡፡›› የገዳሙ አበምኔት

ze1

ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መጋቢት ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሊበን ወረዳ ቤተ ክህነት ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አካባቢ (ዙርያ) መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ቀትር ላይ ተነሥቶ የነበረው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ በቍጥጥር ሥር መዋሉን የገዳሙ አበምኔት መምህር አባ ገብረ ሕይወት አስታወቁ፡፡

ከገዳሙ አባቶች አንዱ አባ ጥላኹን ስዩም እንዳብራሩት እሳቱ የተነሣበት አካባቢ ከገዳሙ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ከመኾኑ ባለፈ ቃጠሎው በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ስለነበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቈጣጠር ባይቻል ኖሮ ከደኑም አልፎ ተርፎ በገዳሙ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርስ ነበር፡፡

zuquala

የዝቋላ ገዳም መገኛና የአካባቢው መልክዐ ምድር

የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና የልዩ ልዩ ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች እሳቱን ለማጥፋት በመረባረብ ክርስቲያናዊ ሓላፊነታቸውን የተወጡ ሲኾን፣ በወቅቱ ከገደል ላይ ወድቆ በመጎዳቱ ሕክምና ሲደረግለት የነበረው ኦርቶክሳዊ ወጣት ሸገና ሉሉ (የክርስትና ስሙ ወልደ ዮሐንስ) ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን የአዳማ ማእከል ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ የገዳሙ አበምኔት መምህር አባ ገብረ ሕይወት ‹‹ልጁ ዐረፈ እንጂ ሞተ አይባልም፡፡ ከሰማዕታት እንደ አንዱ የሚቈጠር ነው›› ሲሉ የወልደ ዮሐንስ መጠራት ሰማያዊ ዋጋ የሚያስገኝ ሞት መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ወቅቱ ሌሊት በመኾኑ፣ በዚያውም ላይ ልጁ የአካባቢውን ተፈጥሮ ባለማወቁ ለኅልፈት ቢዳረግም ሞቱ ግን የሚወደድ እንጂ የሚያስቈጭ አይደለም›› ያሉት ደግሞ አባ ጥላኹን ስዩም ናቸው፡፡ በመጓጓዣ እጦት ምክንያት ማኅበረ መነኮሳቱ በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ለመገኘት እንዳልቻሉ ያስታወሱት አበምኔቱ ለወጣቱ በገዳሙ ጸሎተ ፍትሐት እንደተደረገለትና ለወደፊቱም ቤተሰቦቹን ለማጽናናት ኹኔታዎችን እያመቻቹ እንደሚገኙ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

%e1%8b%9d2

የእሳት ቃጠሎውን ለማጥፋት የምእመናን ተሳትፎ

አበምኔቱ ለዝግጅት ክፍላችን እንደ ገለጹት በገዳሙ አባቶች፤ በአካባቢው ነዋሪዎችና ከልዩ ልዩ ቦታዎች በመጡ የቤተ ክርስቲያን የቍርጥ ቀን ልጆች፤ እንደዚሁም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ አየር ኃይል፤ በኦሮምያ ፖሊስ እና በሊበን ወረዳ ፖሊስ ርብርብ ለገዳሙ ሥጋት የነበረው ይህ ከባድ ቃጠሎ በቍጥጥር ሥር ውሏል፡፡ የበረኃውን ሐሩር፣ የእሳቱን ወላፈን፣ እሾኽና ጋሬጣውን፣ ረኃቡንና ጥሙን ተቋቁመው እሳቱን በማጥፋት ገዳሙን ከጥፋት የታደጉ አካላትን ዅሉ አበምኔቱ በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ስም አመስግነዋል፡፡

‹‹ገዳማችን በስም የገነነ ነገር ግን በብዙ ችግርና ፈተና ውስጥ ያለ ገዳም ነው፡፡ የአሁኑ እሳት በቍጥጥር ሥር ቢውልም፤ ለወደፊቱ ግን ያሠጋናል፡፡ በየዓመቱ በየካቲትና መጋቢት ወሮች ‹እሳት መቼ ይነሣ ይኾን?› እያልን እንጨነቃለን፡፡ ችግሩን ለማስቀረትና ጋታችንን ለመቀነስ ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልገናል፤›› ያሉት አበምኔቱ፣ በመጨረሻም ገዳሙ ያለበትን ችግር ለመፍታትና የእሳት ቃጠሎውንም በዘላቂነት ለመቈጣጠር ያመች ዘንድ በገዳሙ የታቀዱ የገቢ ማስገኛ ተግባራትንና በጅምር የቀረውን የውኃ ጕድጓድ ለመፈጸም መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፍ ቢያደርግልን፣ ገዳሙ የቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን የአገርም ሀብት ነውና መንግሥትም መንገድ ቢሠራልን ሲሉ በቤተ ክርስቲያን ስም የርዳታ ጥሪአቸውን ያቀርባሉ፡፡

ziquala

ቃጠሎው በደኑ ላይ ያደረሰው ጉዳት በከፊል

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዕፀዋቱን ለማገዶና ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚጠቀሙ አካላት በመበራከታቸውና በተደጋጋሚ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ በደን የተሸፈነው ግዙፉ የዝቋላ ተራራ በመራቆት ላይ እንደሚገኝ፤ በሰሞኑ ቃጠሎም አብዛኛው የደን ክፍል እንደወደመ ከልዩ ልዩ ምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ታሪካዊው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳምም ቍጥቋጦ በሚበዛበት፣ ነፋስ በሚበረታበት፣ በረኃማና ወጣገባ መልክዐ ምድር ላይ የሚገኝ በመኾኑና በሌላም ልዩ ልዩ ምክንያት በተደጋጋሚ በእሳት ተፈትኗል፡፡ ለአብነትም መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም በገዳሙ ዙርያ ተነሥቶ በነበረው ከባድ ቃጠሎ በደኑ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ነው፡፡

መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በገዳሙ አካባቢ የተነሣውን እሳት ለማጥፋት ሲሯሯጥ በሞት ለተለየው ወጣት ሸገና ሉሉ (ወልደ ዮሐንስ) ሰማያዊ ዕረፍትን፣ ለቤተሰቦቹም መጽናናትን እየተመኘን የቤተ ክርስቲያችንንና የአገራችንን ሀብት የዝቋላ ገዳምን ህልውና ለማስጠበቅ፣ ገዳሙ ያለበትን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና ደኑንም ወደ ነበረበት ተፈጥሮ ለመመለስ ይቻል ዘንድ የሚመለከተን ዅሉ ብናስበበት መልካም ነው እንላለን፡፡

የኀዘን መግለጫ

img_0005

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስ ርእሰ መንበር እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

መጋቢት ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም  

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! መጋቢት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ‹‹ቆሼ›› እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ በድንገተኛ አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ ወገኖቻችን፣ ዛሬ መጋቢት ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠውን የሐዘን መግለጫ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

በአዲስ አበባ ከተማ መጋቢት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ምሽት በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን የሞት አደጋ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ የዘን መግለጫ፡፡

መጋቢት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ከምሽቱ ፪ ሰዓት ሲኾን በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ‹‹ቆሼ›› እየተባለ በሚጠራው ስፍራ በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ ድንገተኛ የሞት አደጋ ደርሷል፡፡ በደረሰውም አሳዛኝ አደጋ ከፍተኛ ዘን ተሰምቶናል፡፡

በመኾኑም እግዚአብሔር አምላካችን በደረሰው ኅልፈተ ሕይወት ለተጎዱ ወገኖች ቤተሰቦች መጽናናትን፣ ብርታትን እንዲሰጥልን፤ የሟቾችንም ነፍሳት በመንግሥቱ እንዲቀበልልን በመጸለይ የተሰማንን ዘን እየገለጽን፣ ለእነዚሁ በድንገተኛ አደጋ ለተለዩ ወገኖቻችን ከመጋቢት ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጀምሮ ለሰባት ቀናት በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግላቸው፤ እንዲሁም ቤታቸው በመፍረሱ ምክንያት በመጠለያ ለሚገኙ ወገኖቻችን ከቤተ ክርስቲያችን ብር 200,000.00 (ሁለት መቶ ሺሕ) ርዳታ እንዲሰጥ ቋሚ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

በክርስቶስ ሰላም

(ክብ ማኅተምና የብፁዕ አቡነ ገሪማ ፊርማ አለው)

አባ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ ዶክተር

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት፣

የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊ