‹‹ጾመ እግዚእነ አርአያሁ ከመ የሀበነ፤ አርአያነቱን ይሰጠን ዘንድ ጌታችን ጾመ፤›› (ቅዱስ ያሬድ)፡፡

በመምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

መጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጾም በብሉይ ኪዳንም በሐዲስ ኪዳንም በፈጣሪ መኖር ለሚያምኑ፣ የፈጣሪያቸውን ስም ጠርተው ለሚማጸኑ ዅሉ የተሰጠ አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ለሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር መገናኛነት ያገለገሉ፣ በነቢያት የተጾሙ አጽዋማት እንዳሉ መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ‹‹ሙሴም ወደ ተራራው ወጣ ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ቆየ፤›› (ዘጸ. ፳፬፥፲፰) ተብሎ እንደ ተጻፈው ሙሴ በተራራው የቆየው እየጾመ ነበር፡፡ ነቢያት በጾም ከፈጣሪያቸው ጋር ተገናኝተውበታል፡፡ ምንም እንኳን ድኅነተ ነፍስን ማግኘት ባይችሉም በመጾማቸው አባር፣ ቸነፈርን ከሕዝቡ አርቀዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን ያሉ አጽዋማት በሙሉ በፍጡራን የተጾሙ ናቸው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ጾም ግን የተጀመረው በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን አጽዋማት ረድኤተ እግዚአብሔር የሚገኝባቸው፣ ለሐዲስ ኪዳን አጽዋማት መነሻና ምሳሌዎች ናቸው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ከላይ በርእሱ በተጠቀሰው ኃይለ ቃል እንደ ገለጸው የጌታችን ጾም የሐዲስ ኪዳን አጽዋማት መጀመሪያ ነው፡፡ ይህ ጾም የአጽዋማት ዅሉ በኵር ነው፡፡ በኃጢአት ብዛትና በመርገም በጠወለገ ሰውነት የተጾሙ አጽዋማትን ጌታችን አድሷቸዋል፤ ቀድሷቸዋልም፡፡ ውኃ ከላይ ደጋውን፣ ከታች ቆላውን እንዲያለመልም፣ የጌታችንም ጾም ከላይ ከመጀመሪያ የነበረ የአበውን ጾም ቀድሷል፤ ጉድለቱንም ሞልቷል፡፡ ጌታችን ጾሞ ከእርሱ በኋላ የተነሡ ሐዋርያትን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ደናግልን፣ መነኮሳትን በአጭሩ የምእመናን ጾም ቀድሷል፡፡ በአጠቃላይ የጌታችን ጾም እንደ በር ነው፡፡ በር ሲከፈት ከውጭ ያለውን እና ከውስጥ ያለውን ያገናኛል፡፡ የጌታችን ጾምም ከፊት የነበሩትን የነቢያትን አጽዋማት ኋላ ከተነሡ ከሐዋርያት አጽዋማት ጋር ያገናኘ፤ በመርገም ውስጥ የነበሩትንና ከመርገም የተዋጁትን ያስተባበረ ጾም ነው፡፡

‹‹ጌታችን የጾመው ለምን ነው?›› የሚለውን ትልቅ ጥያቄ ‹‹አርአያነቱን ይሰጠን ዘንድ ጾመ›› በማለት ቅዱስ ያሬድ መልሶልናል፡፡ ጌታችን የጾመው እንደ ፍጡራን ክብር ለመቀበል ኃጢአት ኖሮበት ስርየት ለማግኘት አይደለም፡፡ አርአያነቱን አይተን፣ ፍለጋውን ተከትለን ልንጠቀምበት ጾምን ቀድሶ ሰጠን፡፡ ጾም ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት ጋሻ፣ ከኃጢአት የምንሰወርበት ዋሻ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ፣ መኾኑን አርአያ ኾኖ ሊያሳየን ጌታችን ጾመ፡፡ የጾምንም ጥቅም በግብር (በተግባር) አስተማረን፤ አስረዳን፡፡ ይህ የጌታችን ጾም – ‹ዐቢይ (ታላቅ) ጾም፣ ሁዳዴ፣ ዐርባ ጾም፣ የጌታ ጾም› እየተባለ ይጠራል፡፡ ዐቢይ ጾም ማለት ከግሱ እንደምንረዳው እጅግ ትልቅ ጾም ማለት ነው፡፡ በእርግጥ የጾም ትንሽ የለውም፤ አንድም ቀን ይሁን ሳምንት ጾም ትልቅ ነው፡፡ የጌታችን ጾም የታላቆች ታላቅ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ዅሉ ጌታ፣ የፍጥረታት ዅሉ ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጾመው ነው፤ ስምንት ሳምንታን፣ ኀምሳ አምስት ቀናትን በውስጡ የያዘ፣ በቊጥርም ከአጽዋማት ዅሉ እጅግ ከፍ ያለና የሐዲስ ኪዳን አጽዋማት ዅሉ በኵር ስለ ኾነ ዐቢይ (ታላቅ) ጾም ይባላል፡፡

ሁዳድ (የመንግሥት እርሻ)፡- በአንድ መንግሥት የሚተዳደሩ ሕዝቦች በሙሉ በግዳጅ ወጥተው የሚያርሱበት፣ የሚዘሩበት፣ የሚያጭዱበት መሬት እንደ ኾነ ዅሉ ይህም ጾም የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የመንግሥቱን የምስራች በምትነግር ወንጌል ያመኑ ምእመናን በአዋጅ በአንድነት የሚጾሙት ጾም በመሆኑ ‹ሁዳድ› ተብሎ ይጠራል፡፡ ‹ዐርባ ጾም› የተባለበት ምክንያትም ጌታችን የጾመው ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ስለ ኾነ ነው፡፡ ‹‹ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ጾመ›› እንዲል (ማቴ. ፬፥፪)፡፡ ጾሙ ስምንት ሳምንታትን ኀምሳ አምስት ቀናትን ያካተተ ነው ብለናል፡፡ ጌታችን የጾመው ዐርባ ቀን ነው፡፡ ለምን ኀምሳ አምስት ቀናት እንጾማለን? የሚሉ ጥያቄዎች በውስጣችን ሊመላለሱ ይችላሉ፡፡

ጌታችን በጾመው ዐርባ ቀን ላይ ቅዱሳን ሐዋርያት ከመጀመሪያው አንድ ሳምንት ከመጨረሻው አንድ ሳምንት ጨምረውበታል፡፡ በዚህ ምክንያት ጾሙ ከስድስት ወደ ስምንት ሳምንታት፣ ከዐርባ ወደ ኀምሳ አምስት ቀናት ከፍ ሊል ችሏል፡፡ ለምን ብለን ጥያቄ ማንሣት የለብንም፡፡ ምክንያቱን ቀኑን የጨመሩት ከጌታችን ጋር የዋሉ በቃልም፣ በተግባርም ከጌታችን የተማሩት፣ የምሥጢር ደቀ መዛሙርት፣ የሕግ ምንጮች፣ እኛ ወደ ክርስቶስ የምናደርገው ጉዞ መሪዎች ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸውና፡፡ እኛ የክርስትና ተቀባዮች እንጂ ጀማሪዎች ወይም መሥራቾች አይደለንም፡፡ በቅዱሳን ሐዋርያት መሠረትነት ላይ ተመሠረትን እንጂ፡፡ ‹‹እናንተስ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ተመሥርታችኋል›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (ኤፌ. ፪፥፳)፡፡ እናም ሕጋቸውንና ሥርዓታቸውን አምነን ከመቀበል ውጭ መቃወም አይቻለንም፡፡ የብሎኬት ድርድር መሠረት አያስፈልገኝም ሊል አይችልም፡፡ መሠረቱ ከተናደ ድርድሩ የት ሊቆም ይችላል? እኛም የሐዋርያትን ትእዛዝ ካልተቀበልን የማንን ትእዛዝ እንቀበላለን?

ቅዱሳን ሐዋርያት ከመጀመሪያው የጨመሩት የጌታችን ጾም መግቢያ መቀበያ ንጉሥ ሲመጣ በሠራዊት እንዲታጀብ፣ በብዙ ሕዝብ እንዲከበብ፣ ሕዝቡ ከፊት ከኋላ ከበውና አጅበው በክብር እንደሚቀበሉትና እንደሚሸኙት ዅሉ የንጉሣችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጾም ሲመጣም እንደ ሕዝብ፣ እንደ ሠራዊት የሚያጅቡ፣ የሚከቡ፣ የሚያከብሩ ሳምንታትንና ዕለታትን ማለትም ከመጀመሪያው ዘወረደን፤ ከመጨረሻው ደግሞ ሕማማትን ጨምረዋል፡፡ ደግሞም መልካም ምግባርንም ኾነ የጾምን ቀን መቀነስ እንጂ መጨመር አያስቀጣም፡፡ በክርስትና ሕይወት የተቀበሉትን መክሊት መቅበር እንጂ አትርፎ ማቅረብ ያስከብራል፤ ገብር ኄር (ታማኝ አገልጋይ) ያሰኛል፤ ያሾማል፤ ያሸልማል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡